- Details
- Category: Property Law
- Hits: 10273
የህዝብ ንብረት አገልግሎት (Public Domain)
አገራችን ኢትዮጵያ አሁን እየተከተለችው ባለ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 8(1) “የኢትዮጵያ ብሄር-ብሄረሰቦች ህዝቦች የኢትዮጵያ ልኡላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡” በማለት የሚደነግግ ሲሆን የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 40(3) እንደዚሁ ከንብረት ባለቤትነት መብት አንፃር “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው ፡፡” በማለት ይደንግጋል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰልጣን የሚገኘው በህዝባዊ ምርጫ እንደመሆኑ መጠን ህዝቡ በተወካዮቹ በቀጥታ በሚያደርገው ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት እንደሆነ በአንቀፅ 8(3) ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ከነዚህ ህገ-መንግስታዊ መርሆች መገንዘብ የሚቻለው የመንግስት ስልጣን መሰረቱ ህዝብ እንደሆነና መንግስት በአንቀፅ 89(2) የተሰጠውን የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማሻሻል እኩል እድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታውን ለመወጣት ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂ ነድፎ ዜጐች በያደረጃቸው የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሰፊው እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ፖሊሲና ሰትራተጂ ከግብ ለማድረስና ኢንቨስትመንትን ለማሳድግ መንግስት መሬትንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን የህዝቡ የጋራ ንብረት አድርጐ ማስተዳደሩ የአገሪቱ ተጨባጥ ሁኔታ የሚጠይቀው ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 89(5) መሰረት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በህዝቡ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለህዝብ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውል የማድረግ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የፍ/ብሄር ህግ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ከመውጣቱ በፊት በአፄው ዘመነ መንግስት የወጣ በመሆኑ እነዚህን መሰረታዊ የመሬትና የተፈጥሮ ሃብቶች የህዝብ ንብረቶች ስለመሆናቸው የህገ-መንግስቱን መርሆች ተከትሎ የወጣነው ባይባልም የንብረት ህጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1444 እስከ 1459 ባሉ ድንጋጌዎች የህዝብ ንብረት አገልግሎት የሚላቸውን ንብረቶች ኣካቶ የያዘ ለመሆኑ ከፍ/ብሄር ህጉ ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1445 (ሀ) እና (ለ) አንድ ንብረት መቼ የህዝብ ንብረት መባል እንዳለበት ሲገልፅ “ንብረቱ አንድም ህዝብ እንዲገለገልበት በቀጥታ የተመደበ ወይም የተተወ መሆን እንዳለበት ወይም ንብረቶቹ በተፈጥሯቸው ወይም በተደረገላቸው ለውጥ ምክንያት ለተለየ የህዝብ አገልግሎት ብቻ ወይም በይበልጥ ለዚሁ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉ እንደሆኑ የህዝብ ንብረት ይባላሉ፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡ በሌላ አነጋገር ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የማያሟሉ ሆነው ግን ደግሞ በመንግስት እጅ ያሉ ንብረቶች በፍታብሄር ህጉ አነጋገር የህዝብ ንብረት ሳይሆኑ የመንግስት የግል ንብረቶች ተብለው እንደሚወሰዱ የሚደነግግ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ህግ አነጋገር የህዝብ ንብረት የሚባሉት በፍ/ብ/ህ/ቁ 1446-1447 እና 1220-1256 ተዘርዝረው የምናገኛቸው ሲሆኑ እነዚህን እንደ ጥርግያ መንገዶች፣ ካናሎች፣ የውሃ መስመሮች፣ የመብራት መስመሮች፣ ሃይቆች ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ንብረቶች ናቸው፡፡
የህዝብ ንብረት (public domain) መብት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሆነው የዚህ መብት ምንጭ (source) ህግ ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከህገ-መንግስቱ አንስቶ ከህገ-መንግስት መውጣት በኃላ የህዝብ ንብረትን በማስመልከት የወጡ አዋጆችን ያየን አንደሆነ የህዝብ ንብረት መብት ምንጩ ህግ ነው ለሚለው አባባል ዋቢ ናቸው፡፡ አንድ ዜጋ ይህን የህዝብ ንብረት (public domain) የሆነን ንብረት በቀን ልቦና ባለይዞታነት (possession in good faith or usucaption) ወይም በመያዝ (occupation or accession) የባለቤትነት ይሁን የባለ ይዞታነት መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1454-1455) ይህ ማለት ግን መንግስት እንደ ህዝብ አስተዳዳሪነቱ አንድን የህዝብ ንብረት የነበረን ንብረት የህዝብ ንብረትነቱ ቀርቶ የግል ንብረት እንዲሆን ማድረግ አይችልም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሰት ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንድን የግል የሆነን ይዞታ በማስለቀቅ (expropriation) or (alignment) ያንን ንብረት የህዘብ ንብረት ማድረግ የሚችል ሲሆን በዚህ ሁኔታ የሚገኝ የህዝብ ንብረት በሚመለከት የግል ባለ ንብረቱ ተመጣጣኝ ክፍያ በቅድሚያ ማግኘት እንዳለበት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(8) ፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1453/3፣ 1470-1477 እና አዋጅ ቁጥር 455/1997 አንቀፅ 7- 8 ላይ ተደንግጐ የምናገኛቸው ቢሆኑም አሁን ተፈፃሚነት ያላቸው ህጐች ግን ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የወጡት አዋጅ ቁጥር 455/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ሊወሰድ የሚችለው የኋልኞቹ ህጎች ያለውን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መሰረት በማድረግ የወጡና ያለውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲገዙ የአገሪቱን ሁለንተናዊ የዘላቂ ልማት ሰትራተጂ ታሳቢ በማድረግ የተደነገጉ በመሆናቸው እነዚህ ድንጋጌዎች የፍ/ብሄር ህጉን ድንጋጌዎች በግለፅ ባይሽሩም መፈፀም ያለባቸው እነሱ በመሆናቸውና ወደ ፍ/ብሄር ህጉም የሚያስኬድ በቂና ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ ነው፡፡ አንድ የህዝብ ንብረት የህዝብ ንብረትነቱን ቀሪ የሚሆንበት እና ወደ ግል ንብረትነት ሊዛወር የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በሁለት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን እነሱም፡-
1.በህግ የህዝብ ንብረትነቱ ቀርቶ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘወር በህግ ስልጣን በተሰጠው አካል ሲወሰን ለምሳሌ፡- የመብራት አገልግሎት ኢ.መ.ኃ.ኮ መሆኑ ቀርቶ በግል ኩባንያ እንዲያዝ የሚያደርግ የመንግስት ውሳኔ ሲተላለፍ፡፡
2.ንብረቱ በራሱ ግዜ ለህዝብ አገልግሎት መዋሉ ሲቋረጥ ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጥርግያ መንገድ ለህዝብ አገልግሎት መዋሉ ሲቋረጥና ጥርግያ መንገድ መሆኑ ሲቀር ወደ ግል ይዞታነት ሊቀየር ይችላል፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የህዝብ አገልግሎት ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል መንግስት የግል ይዞታን በማስለቀቅ ወያም በተፈጥሮ ይዞታና አጠቃቀማቸው ሊገኝ የሚችል ሲሆን በዋናነት እውቅና የተሰጣቸውን የዜጎች የንብረት መብቶችና ሃገሪቱ የምትከተለውን የማህበረ-ኢኮኖሚና የመሰረተ-ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ተግባራዊ ለማድረግና ዜጐች በየደረጃው የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግን እንደግብ በመውሰድ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ግዴታውን እንዲወጣ የሚያስችለው የመንግስትና የህዘብ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ሰርዓት የህዝብ ንብረት ሲባል በፍታብሄር ህጉ ከተዘረዘሩት ነገሮች ሰፋ ባለመልኩ የገጠርና የከተማ መሬት ባለቤትነትንም ጭምር የሚያካትት መሆኑ ግለፅ ሊሆን ይገባል፡፡