ሰበር ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 11270 የሚቀራረብ ጭብጥ አጋጥሞት ነበር፡፡ በዚህ መዝገብ የሚሟገቱት የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና አንድ የቀድሞ ሰራተኛዉ ናቸዉ፡፡ ጥያቄዉ ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 42/83 ይሸፈናል ወይ የሚል ነበር፡፡ ይህን የተመለከተዉ ሰበር ችሎቱ በመጋቢት 23 ቀን 1997 በሰጠዉ ዉሳኔ እንዲህ ብሏል፡፡
ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለዉና የአመልካች መስሪያ ቤትን ያቋቋመዉ አዋጅ ቁ.266/76 በአንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ መስሪያ ቤቱ የመንግስት መስሪያ ቤት እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ይህም ማለት በመርህ ደረጃ አመልካች መስሪያ ቤት አስተዳደራዊ ስራዎችን የሚሰራ ሆኖ በአጋጣሚ ግን ከምርት ዉጤቶቹና ከአገልግሎት ዋጋ ገቢ ያገኛል፡፡ የመስሪያ ቤቱን በጀትም የተመለከትን እንደሆነ በአብዛኛዉ ከመንግስት ከሚሰጥ አመታዊ ድጋፍ እንደሚገኝ የማቋቋሚያዉ አዋጅ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መስሪያ ቤት በትምህርት ሚኒስቴር ስር ሆኖ በመቋቋሙ አስተዳደራዊ ስራዎችን ከመስራት በቀር በትርፍ ስራ ላይ ሊሰማራ እንደማይችል እንረዳለን፡፡ በመጨረሻም በአንቀጽ 9 ንኡስ ቁጥር 2/ሀ/ ላይ እንደተመለከተዉ መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን የሚቀጥረዉ፤ የሚያስተዳደረዉም ሆነ የሚያባርረዉ በመንግስት ሰራተኞች ሕግ ነዉ፡፡
በአጠቃላይ መስሪያ ቤቱ ተጠሪ በተሰናበተበት ጊዜ በዋናነት አስተዳደራዊ ስራዎችን የሚሰራ በመሆኑ እና በጀቱንም በዋናነት ለመንግስት በየአመቱ የሚያገኝ በመሆኑ አመልካች መስሪያ ቤት በአዋጅ ቁ.42/85 የሚሸፈን አልነበረም፡፡
በመሆኑም ይህ ችሎት በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ያለዉን ግንኙነት የሚገዛዉ አዋጅ ቁ.42/85 አይደለም ሲል ወስኗል፡፡ በዚህም አቤቱታ የቀረበባቸዉን የስር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሰረት ሽሮታል፡፡
የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በኋላ ላይ እንደ ልማት ድርጅት መልሶ ተደራጅቷል፡፡ በፊት ግን የራሱ የሕግ ሰዉነት ያለዉ ድርጅት ሲሆን የሚተዳደረዉ በትምህርት ሚኒስቴር ስር ሲሆን እንቅስቃሴዎቹን በየአመቱ በሚወሰን በጀት ይሸፍናል፡፡ ሰበር ችሎቱም ድርጀቱ በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደርና በአመታዊ በጀት የሚደገፍና ምንም እንኳ ገቢ ቢያመጣም የአስተዳደር ስራ የሚሰራ መስሪያ ቤት በሚል ወስኗል፡፡