- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9695
የማይንቀሳቀስ ንብረት ይዞታ በማድረግ ባለሃብት መሆን (Usucaption) (ፍ/ሕግ ቁ.1168)
የዚህ ቃል (Usucaption) ትርጉም አንድ ነገር በመጠቀም ባለቤት መሆን ማለት ነው (acquired by usage) ። ይህ የሃብት ማግኛ መንገድ ተፈፃሚ የሚሆነው በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ብቻ ሆኖ በተከታታይ ረዘም ላለ ጊዜ የተጠቀመበት እንደሆነ የሚገኝ የባለሃብትነት መብት ነው።
አንድ ነገር በመጠቀም ባለሃብት መሆን ክስ ከሚቀርብበት የይርጋ ጊዜ የተለየ ፅንስ ሓሳብ ነው።
ሀ/ የይርጋ ጊዜ (period of limitation) ማለት አንድ በንብረት ላይ መብት ያለው ሰው መብቱን ሲነካበት መብቱን በነካ ሰው ላይ ክስ የሚያቀርብበት የጊዜ ገደብ ሆኖ፤ ይህ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ ክስ ያቀረበ እንደሆነ ግን ከተከሳሽ ወገን ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ነው።
ለ/ ባለሃብትነት የሚያቋርጥና የሚያሰገኝ የይርጋ ጊዜ (Acquisitive prescription and extinctive prescription)
- 1.የባለሃብትነት መብት እንዲቋርጥ የሚያደርግ የይርጋ ጊዜ ፤ ይህ የይርጋ ጊዜ አንድ ሰው በአንድ ንብረት ላይ የነበረው የባለሃብትነት መብት የሚቋረጥበት ሁኔታ የሚያመለክት ሆኖ ባለሃብትነቱ ሲቋርጥ ጊዜም ሌላ መተኪያ መብት የማይገኝበት ነው ለምሳሌ፦ ፍ/ሕግ ቁ.1192፣
- 2.የባለሃበትነት መብት ማግኛ የይርጋ ጊዜ (usucaption) ፤ ይህ የይርጋ ጊዜ ደግሞ ለሌላ አዲስ ሰው የባለሃብትነት መብት የሚያስጨብጥ ነው። የይርጋ ጊዜ ርዝመቱ ከአገር አገር ሊለያይ የሚችል ነው። ለምሳሌ የፈረንሳይና ጀርመን የ30 ዓመት የይርጋ ጊዜ አላቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን ንብረቱ በቅን ልቦና የያዘው መሆን እንዳለበትም እንደ ተጨማሪ መለኪያ ይጠቀማሉ።
በኢትዮጵያ ፍ/ሕግ በቁጥር 1168 ላይ ከላይ የተመለከትነው የይርጋ ጊዜ (usucaption) ተደንግጎ ይገኛል። ይኸውም የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለይዞታ በመሆን ለተከታታይና ለ15 ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ በሰሙ ግብር እየከፈለበት የቆየ ሰው የዚህ ንብረት ባለሃብት እንደሚሆን ነው። የፍ/ሕጉ በወጣበት ወቅት ይህ ድንጋጌ በመሬትና በህንፃዎች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን ታስቦ የተደነገገና የፊዩዳሉ ስርዓት እስከተገረሰሰበት ጊዜ ድረስ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ ነው። መሬት የመንግስት ንብረት እንዲሆን ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ግን ድንጋጌው በህንፃዎች ላይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በመሬት ላይ ተፈፃሚ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ ነው። እንዲሁም ድንጋጌው ለህዝብ ጥቅም ተብለው በተመደቡ ንብረቶች እና በአለባ ምክንያት በተያዙ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ተፈፃሚነት የለውም (ፍ/ሕግ ቁ.1455 ፣ 1314 ይመለከተዋል)።
እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ አንድ ሰው የራሱ ያልሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዴት አድርጎ ግብር ሊከፍልበት ይችላል የሚል ነው። ይህ ሁኔታ በተለያየ ምክንያት ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ ፦ በማታለል ወይም ባገኘው የውከልና ስልጣን ተጠቅሞ ወይም የጋራ ሃብት የሆነውን ንብረት በመያዙ ምክንያት በስሙ ግብር እየከፈለበት ለተከታታይ 15ዓመት የቆየ እንደሆነ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።
ቁጥር 1168 ስር የተቀመጠው የ15 ዓመት የይርጋ ጊዘ (ሃብት የሚገኝበት ይርጋ) ሊቋረጥ የሚችለው በፍ/ሕግ ቁጥር 1851-1852 መሰረት መሆኑን ግንዛቤ ሊወስድበት ይገባል።
የዋና ተጨማሪ ነገር (Accession)
የዋና ተጨማሪ ነገር አራተኛው የሃብት ማግኛ መንገድ ነው። የፍ/ሄር ሕጋችን የዚህ ትርጉም ባያስቀምጥም ከአጠቃላይ ይዘቱ ተነስተን ሰናየው ግን አንድ ባለሃብት በነበረው ንብረት ወይም ሃብት ላይ ሌላ ሃብት ሲጨመርለት የሚያመለክት ነው። ይህ የተጨመረ ነገር በተፈጥሮ ሓይል ወይም በሰው ጉልበት አማካኝነት የመጣ ሊሆን ይችላል። የእነዚህ ተጨማሪ ነገሮች ባለሃብት ደግሞ የዋናው ነገር ባለሃብት የሆነው ሰው ነው። ይህ ተጨማሪ ነገር በሚንቀሳቀስ ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ሊከሰት ይችላል።
ሀ/ የማይንቀሳቀስ ንብረት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ሲጨመር፤ ይኸውም በሁለት መንገድ ሊፈፀም ይችላል።
- 1.ጐርፍ ጠርጎ ያመጣውን አፈር በሌላ ሰው መሬት ላይ ሲያርፍ የዚሁ መሬት ባለቤት ሃብት ይሆናል። (Alluvium ይሉታል) ።
- 2.ጐርፍ አቅጣጫው ቀይሮ ሲሄድ ከአሁን በፊት የጐርፍ መሄጃ የነበረ ቦታ ሊታረስ ወይም ለሌላ ጥቅም ሊውል የሚችል ቦታ ስለሚሆን በአቅራቢያው ያለ ባለ መሬት የዚያ ቦታም ባለሃብት ይሆናል። (Accretion ይሉታል) ።
እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት ግን በአገራችን የመሬት ባለቤት መንግስትና ህዝብ በመሆናቸው የመሬት ባለቤት ከማለት የልቅ ባለይዞታ ቢባል የተሻለ ይሆናል።
ለ/ ተንቀሳቃሽ ንብረት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ሲጨመር
የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት የሚችለው አንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሙሉ ክፍል (intrinsic element) ሲሆን ነው። ይህ በራሱ በሁለት መንገድ ይፈፀማል።
- 1.አንድ የሚንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብት የሌላ ሰው ሃብት ከሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ በማደባለቅ ሙሉ ክፍል ሲያደርገው ነው። ለምሳሌ፦ አንድ ሰው በሌላ ሰው መሬት ላይ እህል የዘራ ወይም ዛፍ የተከለ እንደሆነ ወይም ህንፃ የገነባ እንደሆነ ጉዳዩ መታየት ያለበት ይህ ስራ ሊያከናውን የቻለው በባለመሬቱ ፈቃድ ነው ወይስ አይደለም? ባለመሬቱ እየተቃወመ ባለበት ሁኔታ ወይስ ሳይቃወመው ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በቅድሚያ በመመርመር ነው።
እዚህ ላይ ትኩረት የሚሻ ነጥብ በአሁኑ ወቅት በአገራችን መሬት በግል ባለሃብትነት ሊያዝ የሚችልበት ሁኔታ ስለተቀየረ ብፍ/ሕግ ቁጥር 1172-1180 ላይ የተደነገጉትን የተፈፃሚነታቸው ጉዳይ ምን ያህል ነው የሚለውን ጉዳይ አጠያቂ ሆነዋል።
ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ ያለው ልምድ አመላካች የሆኑ ሁለት የፍ/ቤት ጉዳዮች ቀርቧል፦
ሀ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በአመልካች አቶ ብርሃነ ገረመ እና በተጠሪዎች እነ ተወልደ ገረመ የነበረ ክርክር በሰበር መ/ቁ.16031 የካቲት 22/1997 ዓ/ም የሚከተለውን-ውሳኔ ሰጥቷል።
ጉዳዩ የተጀመረበት በትግራይ ማእኸላዊ ዞን ማእኸላይ ፍርድ ቤት የአሁን አመልካች በአድዋ ከተማ ቀበሌ 08 ውስጥ ስፋቱ 173.04 በሆነ በ1ኛ ተጠሪ ስም በተመራ ቦታ ላይ የተሰራውን ቤት ግምት ብር 110,000.00/አንድ መቶ አስር ሺ ብር/ ሌሎች ወጪዎች ተጨምሮ ሊከፈለኝ ይገባል በማለተ በአሁን ተጠሪዎች ላይ ክስ ይመስርታል። የግራ ቀኝ ክርክር እና ማስረጃቸውን ከሰማ በኃላ ቤቱን የሰራው ከሳሽ /አመልካች/ መሆኑን በምስክሮች የተረጋገጠ በመሆኑና ተከሳሾቹም መስራቱን አለመቃወማቸውን ስለተረዳን በሚል በፍ/ብ/ሕግ ቁ. 1180(2) መሰረት ተከሳሾቹ የግምቱን ሩብ ብር 27,500.00 እና ሌሎች ወጪዎች ጭምር ለከሳሹ ይክፈሉት ሲል ወሰነ። የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚና ሰበር ሰሚ ችሎቶችም የቀረበላቸው አቤቱታ ውድቅ ያረጉታል።
በመቀጠልም አመልካች ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታውን አቀረበ። የቅሬታው ዋናው ነጥብ ቤቱን የሰራሁት በተጠሪዎች ስምምነት ስለሆነ የካሳው መጠን በፍ/ስ/ሕግ ቁ. 1179 እና 1180 መሰረት ሊሰላ አይገባም፣ ቤቱን ለመስራት ያወጣሁት ብር 110,000.00 ሲሆን ይህንንም ተጠሪዎች አልተቃወሙትምና ቤቱን ከወሰዱት ግምቱን በሙሉ ሊከፍሉኝ ይገባል የሚል ነው ። ተጠሪዎችም የግምቱን ¼ኛ እንድንከፍል በመወሰኑ የተጎዳነው እኛ እንጂ እርሱ አይደለም ብለው ይከራከራሉ።
ሰበር ችሎትም አመልካች ግምትን ላገኝ ይገባኛል የሚለውን ቤት የሰራው እርሱ መሆኑ በስር ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል። በሌላ በኩል ግን ተጠሪዎች መሬቱን የተመሩ ባለይዞታዎች እንጂ የመሬቱ ባለቤቶች አይደሉም። መሬት የመንግስት ሃብት መሆኑ ግልፅ ሆኖ ሳለም የይዞታ መብት ብቻ ያላቸውን ተጠሪዎች እንደመሬት ባለቤት መቁጠርና ጉዳዩን ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የፍ/ብ/ሕጉ ድንጋጌዎች አንፃር መርምሮ ዳኝነት መስጠት የሚቻል እንዳልሆነ ያስቀምጣል።
ተጠሪዎች ቤቱን በሌላ ፍርድ ከአመልካች መረከባቸውን መዝገቡ እንደሚያስረዳ ገልፆ፤ አመልካች ቤቱን ለመስራት ብር 110,000.00 ማውጣቱ በስር ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ማግኘቱን ከፍርዱ ይዘት መገንዘብ ይቻላል ካለ በኃላ አመልካቹ የጠየቀውን ግምት ብር 110,000.00 የማያገኝበት ሕጋዊ ምክንያት እንደሌለ በማስቀመጥ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ በመሻር፤
1.ተጠሪዎች ለአመልካቹ ብር 110,000.00 ሊከፍሉት ይገባል፣
- 2.ተጠሪዎች የመጀመሪያውን አማራጭ ካልተቀበሉት ደግሞ በቦታው ላይ በአመልካቹ የተሰራውን ቤት እንዳለ ሊያስረክቡትና ሰመ ሃብቱንም በስሙ ሊያዞሩለት ይገባል ሲል ወስኗል።
አንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት በሌላ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ሲጨመር የሚያመጣው ውጤት ሆኖ በሶሰት መንገዶች ይገለፃል።
1 በመለወጥ (Transformation or Specification) (ፍ/ሕግ ቁ. 1182)
አንድ ሰው የራሱ ጉልበት አና እንዲሁም በቅን ልቦና የሌላ ሰው ተንቀሳቃሽ ንብረት ተጠቅሞ ሌላ አዲስ ነገር የሰራ እንደሆነ የሚከሰት ነው። የዚህ አዲስ ነገር ወይም የተለወጠው ነገር ባለቤት ማን ሊሆን ይገባል የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ በሁኔታ ላይ የተመሰረተ ነው። ይኸውም የጉልበቱ ዋጋ ከተሰራው /ከታደሰው/ ነገር ዋጋ የበለጠ እንደሆነ የተሰራው አዲስ ነገር ወይም የተለወጠው ነገር ጉልበቱን አፍስሶ ለስራው ወይም ለለወጠው ሰው ይሆናል። የታደሰው ንብረት ዋጋ የሚበልጥ ከሆነ ደግሞ የተሰራው ወይም የታደሰው ነገር ለባለ ንብረቱ ይሆናል። የስራው ግምት እና የታደሰው ነገር ዋጋ እኩል በሚሆንበት ጊዜስ የተሰራው /የታደሰው/ ነገር ለማን መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ ግን መልስ አይሰጥም።
በአጠቃላይ በዚህ ነጥብ ስር ላይ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው መመዘኛዎች፦
- ስራው አዲስ ነገር የፈጠረ መሆን አለበት
- ስራውን የሰራው ሰው በቅን ልቦና ያደረገው መሆን አለበት
- በስራው ላይ የዋለ የጉልበት ዋጋ ከታደሰው/ከተለወጠው/ነገር ዋጋ የበለጠ መሆን አለበት። እነዚህ ሁኔታዎች ከተማሉ የተሰራው (የታደሰው ወይም የተለወጠው) ነገር ጉልበቱንና ዕውቀቱን ተጠቅሞ ለስራው (ለለወጠው) ሰው ይሆናል።
የሌላ ሃብት የሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት ተጠቅመው አዲስ ነገር ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎች ለምሳሌ፦ ስኣሊዎች፣ ሸማኔዎች፣ ወርቅ ሰሪዎች፣ ልብስ ሰፊዎች፣ ሓወልት ሰሪዎች (የሚቀርፁ) ፣ ዳቦ ጋጋሪዎች፣ ምግብ ኣብሳዮች የመሳሰሉት ናቸው።
2 መቀላቀል (መወሃድ) (merger or Confusion) (ፍ/ሕግ ቁ.1183(1))
መቀላቀል ማለት የተለያዩ ሰዎች ንብረት የሆኑትን ሁለት ወይም ከዛ በላይ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አንድ ላይ ሲቀላቀሉ ወይም ሲወሃዱ የሚከሰት ሆኖ በጣም ሳይጐዱ ወይም ሳይበላሹ ወይም በከባድ ስራ ወይም በብዙ ኪሳራ ካልሆነ በስተቀር ሊለያዩ ወይም ሊላቀቁ የማይችሉ እስከመሆን የተቀላቀሉ ወይም የተጣበቁ እንደሆነ ነው። የእነዚህ ነገሮች ቅልቅል ውጤት የሆነው ነገር የእነዛ ሰዎች እንደየድርሻቸው የጋራ ሃብት ይሆናል።
3 ሙሉ ክፍል መሆን (Embodiment/Adjunction) (ፍ/ሕግ ቁ.1183(2))
ሙሉ ክፍል መሆን (መቀላቀል) ማለት የተለያዩ ሰዎች ሃብት የሆኑትን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አንድ ላይ ሲጣመሩ (ሲቀላቀሉ) የሚያመለክት ሆኖ እያንዳንዳቸው ለመለየት የሚቻል ቢሆንም /ቅልቅላቸው ውህደት ስላልሆነ/ አንዱ ንብረት እንደ ዋና ሌላኛው እንደ ሙሉ ክፍል (intrinsic element) የሚታዩበት ሁኔታ ስለሚፈጠር የዋናው ነገር ባለቤት የሙሉ ክፍሉም ባለቤት ይሆናል።
መ/ ፍሬ (Fruits)
ፍሬ ሲባል ዋና ነገር /ንብረት/ እንዳለ ሆኖ በዚሁ ላይ ሌላ ፍሬ ሲጨመር ነው። በዚሁ ሁኔታ ተጨማሪው /ፍሬው/ ከዋናው ነገር ተለይቶ ሲወጣ ወይም ከእሱ ጋር ሲደመር የሚገኝ ነው። በዚህ ስር ሊካተቱ የሚችሉትን ሁለት ነገሮች ናቸው።
1 በተፈጥሮ የሚገኙ ፍሬዎች፦ የእንስሳት ውላጅ፣ የአትክልት ፍሬ የመሳሰሉት ሲሆኑ የእንስሳቱ ባለቤት የውላጅም ባለቤት ይሆናል። የአትክልቱ ባለቤት የፍሬ‘ውም ባለቤት ይሆናል።
2 ሰው ሰራሽ ፍሬዎች፦ ሰው ሰራሽ (Artificial) ፍሬዎች የምንላቸው በሁለት ሊከፈሉ የሚችሉ ሆኖው ሲቪል እና ኢንዳስትሪያል ይባላሉ። ሲቪል የምንላቸው ሰዎች በመካከላቸው በሚያደርጉት ውል/ስምምነት መሰረት የሚገኝ ነው። ለምሳሌ ፦ከቤቶች ክራይ የሚሰበሰብ ገንዘብ የቤቱ ባለቤት ሃብት ይሆናል። የገንዘብ ወለድም እንዲሁ የዋና ገንዘብ ባለቤት ሃብት ይሆናል። ኢንዳስትሪያል ፍሬዎች የምንላቸው ደግሞ መሬትን በማልማት የሚገኙ ፍሬዎች ናቸው።