- Details
- Category: Property Law
- Hits: 7416
ስለኃብት
ሃብት እንዴት እንደሚገኝ የሃብት ማግኛ መንገዶችስ ምንድን ናቸው የሚሉትን ርእሰ ጉዳያች ከላይ በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል። በግል ባለሃብትነት የሚያዘው ንብረት የግድ በአንድ ሰው ባለቤትነት ስር የነበረ መሆን እንደሌለበት አይተናል። ባለቤት ያልነበራቸውንና ከባለቤታቸው የጠፉ ወይም ባለቤታቸው የተጣሉትን ንብረቶች በመያዝ ባለሃብት መሆን እንደሚቻል ተመልክተናል።
ባለሃብትነትን ለማስተላለፍ ግን የግድ የንብረቱ ባለቤት መኖር እንዳለበት ታሳቢ የሚያደርግ ነው። አንድ ንብረት የሚተላለፍለት ሰው (transferee) መብት በአስተላለፈው (transferor) መብት ላይ የተመሰረተ ነው። አንድ ሰው የሌለው ነገር ለሌላ ሰው ሊያስተላለፍ ስለማይችል ተቀባዩም ቢሆን አስተላላፊው ካለው መብት በላይ እንዲሰጠው ሊጠይቅ አይችልም።
ባለሃብትነት ከአንድ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ የሚችልበት መንገድ ሁለት ናቸው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። እነዚህም፦
- 1.በሕግ መስረት የሚኖር ሃብትን የማስተላለፍ ስርዓት፡
- 2.በሕጋዊ ተግባር (Juridical act) የሚኖር ሃብትን የማስተላለፍ ስርዓት ናቸው፣
በሕግ መሰረት ሊተላለፉ የሚችሉ፦
-ያለ ኑዛዜ ውርስ ሲተላለፍ (ፍ/ሕግ ቁ. 842-852)
- አንድ ሰው በአካሉ ወይም በንብረቱ ላይ ጉዳት ሲደርስበት እንዲከፈለው የሚጠይቀው ካሳ (ፍ/ሕግ ቁ. 2027…)
-መንግስት ለህዝብ ጥቅም ብሎ አንድ የግል ንብረት በሚወርስበት ጊዜ ለባለንብረቱ የሚሰጥ ካሳ (ኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 4018) ፣ (ፍ/ሕግ ቁ. 1460-1488 እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ሕጎች)
በሕጋዊ ተግባር መሰረት ሊተላለፍ የሚችሉትን
- ሰዎች በሚያደርጉት ውል መሰረት አንድ ንብረት ከአንዱ ተዋዋይ ወገን ወደ ሌላኛው ተዋዋይ ወገን ሲተላለፍ (ጠቅላላ የውል ሕግ እና ሌሎች ልዩ የውል ሕጎች)
- ሟች በሰጠው ኑዛዜ መሰረት በኑዛዜው ላይ የጠቀሳቸው ንብረቶች ለተናዘዘላቸው ሰዎች ሲተላለፍ፣
- በፍርድ ኣፈፃፅም አማካኝነት በሓራጅ ያልተሸጠ ንብረት ለፍርድ ባለሃብቱ ሲተላለፍ፣
- በመያዣ ምክንያት በአበዳሪ እጅ የገባ ንብረት ገንዘቡ ካላገኘ መያዣው የሚረከብበት ሁኔታ ሲኖር፣
ባለሃብትነት ተላልፏል የሚባልበት ጊዜ መቼ እና እንዴት እንደሆነ
ተንቀሳቃሽ ንብረትን በተመለከተ፦
በፈረንሳይ የሕግ ስርዓት እንደ አስፈላጊ መለኪያ ተደርጎ የሚወሰደው በሃብት አስተላለፊና በሃብት ተቀባይ መካከል ውል ማድረግ ብቻ እንደ በቂ ሁኔታ ይወስዳል። ውል በሚያደርጉበት ጊዜ ለውሉ ምክንያት የሆነው ንብረትም እንደተላለፈ ይቆጠራል። እንደ የጀርመን የሕግ ስርዓት ደግሞ ውል ከማድረግ በተጨማሪ ለውሉ ምክንያት የሆነውን ንብረትም ወደ ተቀባዩ መተላለፍ አለበት ይላሉ። በጀርመን የሕግ ስርዓት አንድ ዕቃ /ንብረት/ ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ፦
ሀ/ የቀድሞው ባለሃብት በንብረቱ ያለው መብት ለሌላ ሰው የሚያስተላልፈው ሲሆን ዕቃው ግን በአዲሱ ባለሃብት ስም ሆኖ ይይዝለታል (constructive possession)
ለ/ በአዲሱ ባለሃብትና ዕቃውን በያዘው ሰው መካከል በሚደረግ ውል ባላደራው ወደ ባለሃበትነት ሊለወጥ ይችላል።
ሐ/ አንድ ሰው በሶሰተኛው ወገን እጅ የሚገኘውን ንብረቱ ሌላ ሰው እንዲወሰደው ለተቀባዩ ስልጣን በመስጠት አማካኝነት ነው።
ለምሳሌ፦ አቶ “ሀ” ባለሃብት፣ አቶ “ለ” በአቶ“ሀ” ስም ዕቃውን የያዘ እና አቶ “መ” ዕቃውን የገዛ፣
መ/ በንብረቱ ምትክ ንብረቱን የሚመለከት ሰነድ በማስተላለፍ
የአገራችን ፍ/ሕግ ብንመለከት አንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት ለሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚቻለው ንብረቱን በማስረክብ ነው (ፍ/ሕግ ቁ.1186(1))። እዚህ ላይ የሚነቀሳቀስ ንብረት ስንል ልዩ ተንቀሳሽ ንብረትን የሚያጠቃልል እንዳልሆነ መርሳት የለብንም። (ፍ/ሕግ ቁ.1186(2))። የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን ከማስተላለፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፍ/ሕግ ቁጥር2274፣ 2395 መመልከት ግንዛቤአችን እንዲሰፋ ይረዳል።
የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ፦
በሁሉም የሕግ ስርዓቶች የማይንቀሳቀስ ንብረትን ለማስተላለፍ የሚከተሉት ስርዓት ተመሳሳይ ነው።
ይኸውም በውል፣ በኑዛዜ ወይም በሕግ መሰረት የሚገኝ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማስተላለፍ የግድ በማይንቀሳቀስ ንብረት መመዝገቢያ መዝገብ ውስጥ መስፈር ይጠይቃል። ይህ ድንጋጌ የፍ/ሕግ ቁ.1185 በውል እና በኑዛዜ መሰረት ለሚተላለፉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ብቻ ነው የደነገገው። በሕግ መሰረት ለሚተላለፉት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ለምን ሳያካትት እንደቀረ ግልፅ አይደለም።
የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማስተላለፍ ምዝገባ ያስፈለገበት ምክንያት፦
- 1.የሶሰተኛ ወገኖች መብት ለመጠበቅ ነው። ይኸውም የምዝገባ ሂደቱ ሲፈፀም ብዙ ሰው በሚያውቀውና በመንግስት መ/ቤት የሚከናወን በመሆኑ ሶሰተኛ ወገኖች የማወቅ ዕድላቸው ያሰፋላቸዋል ተብሎ ስለሚገመት ነው።
- 2.ልዩ የሆነ ጥበቃ የሚያስፈለገውና ቀዋሚ ቦታ ያላቸው ንብረቶች በመሆናቸው ነው።
- 3.መንግስት የተለያዩ ስራዎች ለማከናወን እንደ መነሻነት ሊያገለግለው ስለሚችል። ለምሳሌ፦ ግብር ለመሰብሰብ፣ የመኖርያ ቤቶች ለመስራት ወዘተ…
የሚንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ያላስፈለገበት ምክንያት
- 1.ቀዋሚ ቦታ ስለሌላቸውና ለአስራር አመቺ ባለመሆናቸው
- 2.ሰዎች ንብረታቸውን በነፃ እንዲያንቀሳቅሱና በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል እንቅፋት ለማስወገድ ስለሚጠቅም ወዘተ ነው።
ሃብት ስለሚቀርበት (extinction of ownership) (ፍ/ሕግ ቁ.1188-1192)
ባለሃብትነት መቅረት ሲባል አንድ ሰው በንብረት ላይ የነበረውን የባለቤትነት መብት በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠል ሳይችል ሊቀር ነው። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ የንብረት መብት /ባለሃብትነት/እንዲኖር የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲጠፉ ወይም ሲሰረዙ ወዘተ ነው። ባለሃብትነት መቅረት ፍፁም (absolute) ወይም ተነፃፃሪ (relative) ሊሆን ይችላል። የባሃብትነት መቅረት ፍፁም ነው የሚባለው ያለ ተከታይ ወይም አዲስ ባለሃብት ንብረቶቹ ጠፍተው ወይም ተጥለው ሲቀሩ የሚያመለክት ነው /ፍ/ሕግ ቁ.1188 እና 1191/። የባለሃብትነት መቅረት ተነፃፃሪ ነው የሚባለው ደግሞ በንብረቱ ላይ የባለቤት ለውጥ ብቻ ሲኖር የሚኖር መቅረት (extinction) ነው (ለምሳሌ ፍ/ሕግ ቑ.1189)። ባሃብትነት በባለሃብቱ ፍላጐት ወይም ከባሃብቱ ፍላጐት ውጭ ሊቀር /ሊቋረጥ/ ይችላል። ባለሃብትነት የሚያስቀሩ ምክንያቶች በፍ/ሕግ ውስጥ ተካትተዋል። ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል።1.ንብረቱ ሲወድም ወይም መለያ ባህሪው ሲጠፋ (ፍ/ሕግ ቁ.1188 ይመለከተዋል) ። ለምሳሌ፦ አንድ ነገር ከሌላ ነገር ሲዋሃድ፣ ዕቃው ታድሶ ወይም እንደአዲስ ተሰርቶ ወደ ሌላ ነገር ሲለወጥ፣
- 2.በሕግ መሰረት ንብረቱ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ (ፍ/ሕግ ቑ. 1189)። ይህ ድንጋጌ በሕግ መሰረት ለሚተላለፉ ንብረቶች ብቻ የደነገገ ይመስላል። በሕጋዊ ተግባር (juridical act) ለሚተላለፉ ንብረቶች ለምን ሳያካትቶ እንደቀረ ግን ግልፅ አይደለም።
- 3.የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚመለከት ሲሆን የባለሃብትነት መብት ከመዝገብ ሲሰዘረዝ (ፍ/ሕግ ቁ.1190)
- 4.ባለሃብቱ በማያጠራጥር ሁኔታ መብቱን የመተው ሃሳቡ ያስታወቀ እንደሆነ (ፍ/ሕግ ቁ.1191) ። መብትን የመተው ጉዳይ ኣካል መጠን ላልደረሱና የኣምሮ በሽተኞች ለሆኑት የሚመለከት አይሆንም።
- 5.የሚንቀሳቀስ ንብረት በሚመለከት
ሀ/ ባለሃብቱ ንብረቱ የት እንዳለ ወይም የእሱ ንብረት ስለመሆኑ ሳያውቅ 10/ዓሰር/ ዓመት ያለፈበት እንደሆነ (ፍ/ሕግ ቁ. 1192)።
ለ/ የንብረቱ ዓይነት በመብረር ላይ ያለ ንብ ሲሆንና ባለሃብቱ ወዲያውኑ ሳይከተለው የቀረ እንደሆነ (ፍ/ሕግ ቁ. 1153)።
ሐ/ የጠፉ እንስሳትን ባለቤታቸው እስከ አንድ ወር ውስጥ ተከታትሎ ሳይዛቸው የቀረ እንደሆነ (ፍ/ሕግ ቁ. 1152)።
- 6.መንግስት በሕግ መሰረት ንብረቱን የወረሰው እንደሆነ (ፍ/ሕግ ቁ.1460-1488)።
ስለ ሃብትነት ማስረጃ (Proof of ownership) (ፍ/ሕግ ቁ. 1195-1203)
ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው አንድ ሰው የንብረት ባለሃብት ለመሆን አንዲችል አንዳንድ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። ይኸውም ንብረቱ እጅ ማድረግ፣ እንዲመዘገብ ማድረግ ወዘተ። ስለዚ ባለሃብትነት ቀርቷል/ተቋርጧል/ የሚል ወገን ሃብትነት ለማግኘት ይሁን ለማስተላለፍ ጠቃሚ የሆኑትን እነዚህ ፍሬ ነገሮች /ንብረት እጅ ማድረግ ወይም መመዝገብ/ያለመኖሩ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። በመሆኑም የሃብትነት ማስረጃ ማለት የፍሬ ነገሮችን ማስረጃ ሆኖ አንድ ንብረት በአንድ ሰው ባለሃብትነት ስር የገባ መሆኑን ወይም ለሌላ ሰው የተላለፈ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። በሌላ አገላለፅ የሃብትነት ማስረጃ ማለት አንድ ንብረት በሃብትነት ስለመያዙ ወይም ስለመተላለፉና ሃብትነት አለመቅረቱ የሚያሳዩ አግባብነት ያላቸው ፍሬ ነገሮች ለማረጋገጥ/ለማስረዳት/ የሚያገለግል መሳሪያ ነው። ምን ዓይነት ፍሬ ነገሮች ናቸው በማስረጃ መረጋገጥ ያለባቸው የሚለውን ደግሞ ሃብት ለማግኘት ወይም ለማስተላለፍ የሚያገለግሉ መመዘኛዎች (requirements) እንደሚለያዩ ሁሉ በማስረጃ የሚረጋገጡ ፍሬ ነገሮችም ይለያያሉ። ያም ሆኖ ግን ሕጉ ያስቀመጠው የሕግ ግምት (presumption of law) እንጂ ሌላ ማስረጃ (proof) አይደለም። አንድ ተከራካሪ ወገን ባለሃበትነት ስለመኖሩ ወይም ስለመተላለፉ የሚገልፁ መሰረታዊ የሆኑ ፍሬ ነገሮችን ስለመኖራቸው ያስረዳ እንደሆነ ሕጉ ሃብትነት እንዳለ ይገምታል።
- 1.ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው መደበኛ ተንቀሳቃሽ (ordinary movables) ንብረቶች ላይ ያለ የሃብትነት መብት መተላለፍ የሚችለው የእነዚህ ንብረቶች ባለይዞታ በመሆን ነው። ምክንያቱ የአንድ ተንቀሳቃሽ ንብረት ባለይዞታ መሆን የእዛ ንብረት ባለሃብት እንደሆነ ስለሚያስገምተው ነው። ይህ የሕግ ግምት ቢኖርም ባሃብትነት የለም ብሎ የሚከራከር ወገን ባለሃብትነት አለመኖሩ የሚያረጋግጥለት ማስረጃ በማቅረብ የሕጉ ግምት ማፍረስ ይችላል። የሕጉን ግምት ለማፍረስ ሊቀርቡ የሚችሉትን የማስረጃ ዓይነቶ፦
- የሰው ምስክርነት
- የፅሑፍ ማስረጃ የሚያስፈልጋቸው የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ሲሆኑ የተመዘገቡበት ፅሑፍ ወይም በምዝገባው መሰረት የሚሰጥ የባለቤትነት ደብተር፣
- ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ያለበት ወገን በፍ/ሕግ ቁጥር 336 መሰረት ለአካል መጠን ያልደረሰ እንደሆነ ማናቸውንም ዓይነት ማስረጃ ማቕረብ ይቻላል።
- 2.የማይንቀሳቀስ ንብረት /ህንፃ/ ባሃብትነት በሚመለከት ማስረዳት የሚቻለው በባለቤትነት ምስክር ወረቀት ነው። ይህ የባለቤትነት ምስክር ወረቀት (title deed) የያዘ ሰው የንብረቱ ባለሃብት እንደሆነ ይገመታል። አንድ የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ለመስጠት ስልጣን ያለው ኣካል ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር ስለአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚመለከት የባለቤትነት ምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ አዲስ ለሆነው ባለሃብት ከመስጠቱ በፊት ቀደም ሲል ለሌላ ሰው ተሰጥቶ የነበረ የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ከቀድሞው ባለቤት እንዲመለስ መጠየቅ አለበት።
የቀድሞው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት (title deed) ጠፍቷል ወይም ወድሟል የተባለ እንደሆነ ደግሞ አዲስ ባለቤት ለመሆን እያመለከተ ያለ ወገን ሳይጠፋ ወይም ሳይወድም ጠፍቷል ወይም ወድሟል በማለቱ በሶሰተኛ ወገን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የአስተዳደር ክፍሉ በቂ ዋስትና እንዲያደርግ አዲሱን አመልካች ሊጠይቀው ይችላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ሕጉ በመንግስት ላይ የጣለው ሃላፊነትም አለ። ይኸውም የሚመለከተው የአስተዳደር ክፍል ሕጋዊው መንገድ ሳይከተል ትክክለኛ ያልሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚመለከት የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ለአንድ ሰው በመስጠቱ ወይም መሰረዝ ያለበት የምስክር ወረቀት ባለመስረዙ በዚህ ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት መንግስት ሃላፊነት እንዳለበት ነው። የመንግስት ሓላፊነት ከውል ውጭ በሚደርስ ሃላፊነት የመነጨ በመሆኑ ሃሓላፊነቱ ከተወጣ በኃላ ይህ ጥፋት የሰሩትን የአስተዳደር ክፍሉ ሃሓላፊዎች/ሰራተኞች የከፈለው ኪሳራ እንዲመልሱለት ሊጠይቃቸው እንደሚችልም በፍ/ሕጉ ላይ ተካትቷል።
በሚሰጠው /በተሰጠው/አዲስ የባለሃብትነት ምስክር ወረቀት ላይ ሶሰተኛ ወገኖች መቃወሚያ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታም የፍ/ሕጉ አስቀምጧል። እነዚህም፦
ሀ/ የምስክር ወረቀቱ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ወይም ስልጣን በሌለው የአስተዳደር ክፍል የተሰጠ ነው፣ ወይም
ለ/ የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው በማይረጋ (invalid) ፅሑፍ የሆነ እንደሆነ፣ ወይም
ሐ/ ተቃዋሚው /ሶሰተኛው ወገን/ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት ያገኘው የምስክር ወረቀቱ ከተሰጠ በኃላ የሆነ እንደሆነ ናቸው።
እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ “የማይረጋ ፅሑፍ” (invalid act) ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ነው። ይህ ነጥብ አጠቃላይ የውል አመሰራረት ከሚወስኑ መመዘኛዎች (requirements) ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ነው። አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚመለከት ውል መደረግ ያለበት በፍ/ሕግ ቁ.1723 መሰረት መሆኑን ይታወቃል። ይህ ድንጋጌ ሳይከተል የተደረገ ውል መሰረት በማድረግ የተሰጠን የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት ተቃውሞ የቀረበበት እንደሆነ የምስክር ወረቀቱ ውድቅ ሊደረግ ይችላል ማለት ነው።
ለማጠቃለል ያህል ሃብትነት ከሁሉም በላይ የሰፋ መብት ሆኖ ሶስት መሰረታዊ የሆኑ ማለት የመጠቀም/መገልገል/፣ ፍሬውን የመሰብሰብ እና ለሌላ ሰው የማስተላለፍ የማስወገድ መብቶችን አጠቃልሎ የያዘ ነው:: ሃብት በተለያዩ መንገዶች ሊገኝ አንደሚችል አይተናል:: ሃብት ከሚያስገኙ መነገዶቸ ባለቤት የሌላቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ማለትም የጠፉ፣ ባለቤት የሌላቸው፣ የተቀበረ ገንዘብ እና የተተዉ ንብረቶች በመያዝ፤ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በቅን ልቦና ይዞታ በማድረግ፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ይዞታ በማድረግ፤ እና አንድ ነገር የዋና ተጨማሪ ነገር የሆነ እንደሆነ ነው:: ሃብት በሕግ መሰረት ወይም በህጋዊ ተግባር አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችልም አይተናል:: እንዲሁም ሃብትነት እንዲቀር የሚያደርጉ በረከት ያሉ ምክንያቶች እንዳሉም ያየን ሲሆን፤ ሃብትነት ስለመኖሩ ወይም ስለመቅረቱ ለማስረዳትም ለተንቀሳቃሽና ለማይንቀሳቀስ ንብረት የሚኖር የማሰረጃ ጉዳይ ሊለያይ እንደሚል ነው::