- Details
- Category: Property Law
- Hits: 7409
የግል ባለሃብትነት (Private ownership Right)
ሃብትነት ከሁሉም ከንብረት ጋር ተያያዥነት ካላቸው መብቶች አንፃር ሲታይ ከፍተኛው ቦታ የያዘ መብት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ሃብት እንዴት እንደሚገኝ፣ እንደሚተላለፍ፣ እንደሚቀርና እንደሚረጋገጥ ከማየታችን በፊት የሃብት ትርጉም ምን እንደሆነ ማየቱ ተገቢነት ስለሚኖረው በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል። የፍትሐብሄር ሕጋችን በምዕራፍ ሁለት ክፍል አንድ ላይ “ሃብትነት ማለት በአንድ ግዙፍ ንብረት ከሁሉ የሰፋ መብትን የያዘ ማለት ነው” በሚል መልኩ ተገልፆ ይገኛል። ቢሆንም የድንጋጌው አባባል ትርጉም ነው ብሎ ማስቀመጥ የሚያስደፍር አይደለም። ትርጉም ነው ሊባል አይችልም ብቻ ሳይሆን ንብረትን የሚገልፁ ነገሮችን በበቂ ሁኔታ ተገልፆአል ለማለትም ያስቸግራል። ምክንያቱም ይህ መብት እንዴት ሰፊ ሊሆን ቻለ የሚል ጥያቄ እንኳ የመለሰ አይደለም። በተጨማሪ በአንድ ግዙፍ ንብረት ላይ (corporeal things) የሚኖርን መብት ብቻ አስቀመጠ እንጂ ግዙፋዊ ህልውና ስለሌላቸው (incorporeal things) በተመለከተ ሳያካትት ቀርተዋል:: ሃብትነት ከሁሉም የሰፋ መብት ነው ሲባል ግን ከይዞታ፣ ከአለባ እና ከንብረት አገልግሎት መብቶች አንፃር ሲታይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
ባለሃብትነት ማለት ማንም ሰው በንብረቱ ላይ የሚኖረው የመጠቀም (usus) ፣ ፍሬው የመሰብሰብ (fructus) እና የባለሃብትነት መብት ለሌላ ሰው የማስተላለፍ (abusus) መብት ነው። እዚህ ላይ abusus ማለት በኑዛዜ ወይም በውል ለሌላ ሰው ማስተላለፍ፣ አይጠቅመኝም ብሎ መጣል የሚያጠቃልል ፅንብ ሓሳብ ነው።
ባለሃብትነት ከሁሉም በላይ የሰፋ መብት ነው ሲባል ግን ምንም በሕግ የተቀመጠ ገደብ (restriction) የለውም ማለት አይደለም። ማንኛውም ባለሃብት የሌሎች ግለሰቦች ወይም የህዝብ መብትና ፍላጎት በሚፃረር መልኩ መብቱን ሊጠቀምበት ይችላል ማለት አይደለም። የባለሃብትነት መብት ከሁሉም በላይ የሰፋ መብት ቢሆንም የሌሎች መብት እስካልተቃረነ ድረስ የሚጠቀምበት ስለሚሆን ገደብ የተበጀለት መብት ነው ። (ፍ/ሕግ ቁ.1204(1) እና 1205(1)ይመለከተዋል)
ባለሃብትነት በተለይ የግል ባለሃብትነት በተመለከተ በተለያዩ ሙሁራን፣ ፈላስፋዎች እና የኢኮኖሚ ሙሁራን መካከል ሲያከራክር የቆየ ነው። የግል ባለሃብትነት የሚባል ነገር መኖር የለበትም የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት ምክንያት ፤ አንዳንዶቹ እንደሚሉት አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ ብዝበዛ እንዲያደርግ ሊፈቀድለት አይገባም። ሌሎች እንደሚሉትም ሰዎች በመካከላቸው በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። ወደ የኢኮኖሚ አናርክነት ሊያመራም ይችላል ይላሉ።
የግል ባለሃብትነት የሚደግፉ ወገኖች የሚያቀርቡት አስተያየት ደግሞ፤ የግል ባለሃብትነት የማንደግፍ ከሆነ ስለግለሰቦች መናገር ትርጉም አይኖረውም። የባለሃብትነት መብት ተፈጥሮኣዊ መብት እና የኢኮኖሚ እድገት መሳሪያ ነው፣ ለግለሰቦች ነፃነት ዋስትና የሚሰጥ ነው። የጋራ እድገት ለማሳካትም ቢሆን የግል ሃብት የሕግ ጥበቃ በስተቀር ሳያገኝ ሊታሰብ አይችልም ይላሉ። ይህ ሓሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነቐባይነት ያገኘና እንደ ተፈጥሮአዊ መብት ተደርጎ የተወሰደበት ሁኔታ ነው ያለው። ሕገ መንግስታችንም ከፍተኛ ግምት እንደሰጠው ነው መገንዘብ የሚቻለው።
ሃብት ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ ሃብትን ስለማስተላለፍ፣ ሃብት ስለሚቀርበትና ስለ ሃብትነት ማስረጃ
1 ሃብት ስለሚገኝበት ሁኔታ
ሃብት ማግኘት ማለት አንድ ሰው ያለምንም ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ የንብረቱ ባለቤት የሚሆንበት፣ ሕግና ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት በእጁ የሚያስገባበት ሁኔታ የሚገልፅ ሆኖ ሕግ ራሱ የባለቤትነት ደረጃ (status) የሚሰጠው ነው። በዚህ መሰረት የተለያዩ የሃብት ማግኛ መንገዶች ኣሉ። እነዚህ የሃብት ማግኛ መንገዶች እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን።
ሀ) ባለቤት የሌላቸው ንብረቶች በመያዝ ባለሃብት ስለመሆን(0ccupation)
አንድ ባለቤት የሌለው ንብረት በመያዝ ባለሃብት የመሆን ጉዳይ ከሁሉም የሃብት ማግኛ መንገዶች በላይ ረዥም ዕድሜ ያለው ነው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የበለጠ የሃብት ማግኛ አግባብም ነው።
መያዝ ሲባል አንድ ባለቤት የሌለው ግዙፍነት ያለው ነገር /ንብረት/ የእዛ ነገር ባለቤት ለመሆን በማሰብ በቁጥጥር ስር ማድረግ ወይም መያዝ ማለት ነው። (ፍ/ሕግ ቁጥር 1151 ይመለከተዋል) ። አንድ ነገር በመያዝ ባለቤት ለመሆን አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው።
6. ንብረቱ ግዙፍነት ያለው ተንቀሳቃሽ ነገር መሆን አለበት
- 1.በግል ባለቤትነት ሊያዝ የሚችል መሆን አለበት
- 2.ንብረቱ ባለቤት የሌለው መሆን አለበት
- 3.የንብረቱ ባለሃብት ለመሆን ሓሳብ (intention) መኖር አለበት።
ንብረቱ ግዙፍነት ያለው ተንቀሳቃሽ ንብረት መሆን አለበት። በሌላ አባባል ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች /ምሳሌ የፈጠራ ስራ/ ለመያዝ ከምዝገባ ውጭ ሊሆን ስለማይቻል ነው። የእነዚህ ንብረቶች ባለመብት ማን እንደሆነ በምዝገባ የሚታወቅ ሆኖ ምዝገባው የተሰረዘ እንደሆነ ግን መብቶቹ ትርጉም የለሽ የሚያደርጋቸው ስለሚሆን ነው። እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ንብረት መሆን አለባቸው ሲባል የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በመርህ ደረጃ መያዝ የሚቻለው በምዝገባና የባለቤትነት ደብተር በመያዝ ስለሆነ ነው።አንዳንድ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች በተለይ ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚባሉ እንደተሽከርካሪዎች፣ መርከብ፣ ኣውሮኘላን ወዘተ የመሳሰሉትን በመያዝ አማካኝነት የግል ሃብት ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው። በተጨማሪም ለህዝብ ጥቅም ወይም አገልግሎት ተብለው የተመደቡ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ቢሆኑም በግል ሊያዙ አይችሉም (ፍ/ሕግ ቁ.1448 እና 1457)።
በመያዝ አማካኝነት ባለሃብት መሆን የሚቻልባቸው የተንቀሳቃሽ ንብረት ዓይነቶች እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል።
- 1.ባለቤት የሌላቸው ነገሮች (Master less things)
- 2.የተቀበረ ገንዘብ (Treasure)
- 3.የጠፋ ንብረት (lost things)
- 4.የተተው ነገሮች (abandoned things)
- 5.ከጠላት የተገኘ ንብረት (Seizure of Enemy property)
- 1)ባለሃብት የሌላቸው ነገሮች የምንላቸው፤ ባለቤት ኖሮአቸው የማያውቁ ነገሮች ሆኖው ለመጀመርያ ጊዜ በባለቤትነት የተያዙ ናቸው። እንዲሁም ከመያዛቸው በፊት በባለቤትነት ስር የነበሩ ቢሆኑም ኃላ በባለቤቱ የተጣሉ ንብረቶች ናቸው። የተጣሉ ነገሮች ናቸው የሚባሉት የቀድሞ ባለቤታቸው የይመለስልኝ አቤቱታ ሊያቀርብባቸው የማይችሉ ናቸው።
እንስሳትና ንብ (ፍ/ሕግ ቁ.1152-1153)
እንስሳት ስንል ለማዳ እንስሳት ኖሮው በኃላ የጠፉ ወይም በባለቤትነት ስር ገብተው የማያውቁ የዱር አንስሳት ሊሆኑ ይችላሉ። ባለቤታቸው የጣላቸው /የተዋቸው/ ወይም ከባለቤታቸው እጅ የጠፉ እንስሳት የምንላቸው አንደ ከብት፣ ፍየልና በግ፣ የጋማ ከብቶች፣ ውሾች እና ሌሎች ለማዳ የነበሩ እንስሳት የሚያጠቃለል ነው። እንደ እነዚህ የመሳሰሉትን ለማዳ የነበሩና ኃላ የጠፉ ወይም የተጣሉ እንስሳት ባለቤት ለመሆን በሕግ የተቀመጠ የይርጋ ጊዜ ማለፍ ያስፈልጋል። የይርጋው ጊዜ ከማለፉ በፊት የቀድሞው ባለሃብት የእኔ ንብረት ነው ብሎ ንብረቱን ካገኘ /ከያዘ/ ሰው ከመጠየቅ የሚያግደው ነገር አይኖርም። በፍ/ሕግ ቁ.1152(1) ስር እንደተደነገገው ለማዳ የሆኑ ወይም የተያዙ እንስሳት ባለሃብት ከሆነው ሰው ቢያመልጡና ቢጠፉ ባለቤቱም በሚከተለው ወር ውስጥ ሳይፈለጋቸው የቀረ እንደሆነ ወይም አንድ ወር ሙሉ መፈለጉን ቢተው ባለቤት የሌላቸው ይሆናሉ። እነዚህ አምልጠው የጠፉ እንስሳት ሌላ ሰው ቢያገኛቸውና የተቀመጠው የአንድ ወር የይርጋ ጊዜ ቢያልፍ ይህ ሰው የእነዚህ ነገሮች ባለቤት ይሆናል። ቢሆንም ይህ የይርጋ ድንጋጌ ለቀንድ ከብቶች፣ ለጋማ ከብቶችና ለግመሎች ተፈፃሚ እንደማይሆን በቁጥር 1152(2) ተመልክቷል። ይህ ልዩነት የተፈጠረበት ምክንያት ለምንድነው? ውድ ለሆኑና ከፍተኛ ጠቀሜታ ላላቸው ንብረቶች/እንስሳት/አጭር የይርጋ ጊዜ ማስቀመጥ ፍትሓዊ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አንድ ሰው ይህን የመሰሉ እንስሳት ጠፍተውበት ችላ ብሎ ይተዋቸዋል ተብሎም አይገመትምና ነው። የአንድ ወር የይርጋ ጊዜ አይመለከታቸውም ማለት ግን ፈፅሞ ይርጋ የላቸውም ማለት ነውን?
ከቀንድ ከብቶች፣ ከጋማ ከብቶች እና ከግመሎች ውጭ ያሉት እንስሳትን በተመለከተ የአንድ ወር የይርጋ ጊዜ ያስቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ከሌሎች ጋር ሲወዳደሩ ውድ ካለ መሆናቸውና ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ ተብለው ስለማይገመት ባለቤታቸው ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ለፍለጋቸው ያጠፋል ተብሎ ስለማይገመት ይመስላል።
የዱር እንስሳት ከሚባሉት ወፎች፣ ዓሳዎች፣ ንቦች ወዘተ መጥቀስ የሚቻል ሆኖ ባለቤት ያልነበራቸው ተብሎ ከሚጠሩ እንስሳት ጠቂቶቹ ናቸው። እነዚህ እንስሳት አብዛኛው ጊዜ በግል ባለሃብትነት እንዳይያዙ የተከለከሉ አይደሉም። ይሁን እንጂ እንደዚህ የመሳሰሉት እንስሳት ለመያዝ ወይም ለማደን፣ ዓሳ ለማጥመድ ወዘተ የአገሪቱ ሕግና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ሊፈፀም እንደሚገባው ግን መዘንጋት የለበትም ነው። ፈቃድ አስፈላጊ ከሆነም ከሚመለከተው ኣካል መጠየቅና ፈቃድ መያዝ ያስፈልጋል።
ንቦችን በተመለከተ በፍ/ሕግ ቁጥር 1153 ላይ የተደነገገ ሲሆን፤ ቆፎአቸውን ትተው የሄዱ ንቦች በቆፎአቸው ከወጡበት ቀን አንስቶ ባለቤት የሌላቸው ይሆናሉ፣ ወደ ሌላ ቆፎ የገቡ እንደሆነ የቆፎው ባለቤት የንቦችም ባለቤት ይሆናል፣ ንቦች ከቆፎአቸው ወጥተው በሚበሩበት ጊዜ የቀድሞው ባለቤት እየተከተላቸው የሄደ እንደሆነና ወደ ሌላ ቆፎ ሲገቡ የደረሰባቸው እንደሆነ መልሶ ሊወስዳቸው እንደሚችል ነው ከሕጉ መገንዘብ የሚቻለው።
ጠፍተው የተገኙ ነገሮች (ፍ/ሕግ ቁ.1154-1158)
አንድ ሰው በቸልተኝነት ወይም ከፍላጐቱ ውጭ በሆነ ሁኔታ ንብረቱ ከእጁ የጠፋ እንደሆነና ያ የጠፋው ንብረት ሌላ ሰው ያገኘው እንደሆነ ጠፍቶ የተገኘ ዕቃ (ነገር) ይባላል። ለምሳሌ፦ በዝናብ ሓይል፣ በጐርፍ፣ በንፋስ ወዘተ የተወሰደበት እንደሆነ፣ የንብረቱ ባለቤት የሆነ ቦታ ላይ ረስቶት የሄደ እንደሆነ፣ ንብረቱ በሌላ ሰው የተደበቀበት እንደሆነ፣ በእንስሳት የተወሰደበት እንደሆነ፣ ከሌላ ሰው ንብረት ጋር በመደባለቁ ምክንያት ሳያገኝ የቀረ እንደሆነ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ምክንያት ንብረቱ የት እንዳለ ለማወቅ ያልቻለ እንደሆነ ነው። እንደዚህ ዓይነት ንብረት በአንድ ወይም በብዙ ሰዎች ሊገኝ ይችላል።
የጠፋ ንብረትና በማወቅ የተጣለ (የተተወ) ንብረት ልዩነት አላቸው። ይኸውም፤ የጠፋ ንብረት ሲሆን በሕግ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ (ይርጋ) እስኪያልፍ ድረስ የቀድሞው ባለቤት (ባለሃብት) መብት እንደተጠበቀ ይቆያል። የጠፋ ንብረት በሚሆንበት ጊዜ ያ ንብረት ባገኘ ሰው ላይ ሕጉ ግዴታዎች አስቀምጧል፤ እንዲሁም መብቶቹም ደንግጓል።
የጠፋ ንብረት ያገኘ ሰው ግዴታዎች፦
- 1.የአስተዳደር ደንብ በሚያዘው መሰረት ለሚመለከተው የመንግስት አካል የጠፋ ንብረት ያገኘ ስለመሆኑ የማሳወቅ ግዴታ (ቁ.1154(1)) ።ይህንን ግዴታ ካልተወጣ በኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ ተጠያቂ ይሆናል።
- 2.ንብረት የጠፋበት ሰው ንብረቱ የተገኘ መሆኑንና መልሶ እንዲወስድ በማስታወቅያ የመንገር (ቁ.1154(2)) ግዴታ አለበት። ይህ ማስታወቀያ በመጋናኛ ብዙሃን በመንገር ወይም በገበያ ላይ በመግለፅ ወይም በሌላ መንገድ ሊፈፀም ይችላል። ሆኖም ግን በመጋናኛ ብዙሃን መንገር ብዙ ሲሰራበት የማይታይ ከመሆኑም በላይ ከወጪ አንፃር ሲታይም ውድ ሊሆን ይችላል። ሌላ የማሳወቅያ መንገድም ቢሆን ብዙ ሲሰራበት አይሰተዋልም።
- 3.ያገኘውን ንብረት ለመጠበቅ ተገቢ ጥንቃቄ ማደረግ ይጠበቅበታል (ቁ.1155(2))። የጠፋ ንብረት ያገኘ ሰው ንብረቱ እንዳይሰረቅ ወይም እንዳይበላሽ እንደራሱ ንብረት እንክብካቤ ሊያደርግለት ይገባል። ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ንብረቱ ጉዳት የደረሰበት ወይም የተበላሸ እንደሆነ ግን ተጠያቂ አይሆንም።
የጠፋ ንብረት ያገኘ ሰው መብቶች፦
ሀ/ የንብረቱ ባለቤት እስኪመጣ ድረስ በእጁ አድርጎ የማስቀመጥ (ቁ.1155 (1))
ለ/ ጠፍቶ የተገኘው ንብረት ሊበላሽ ወይም ሊበሰብስ፣ ሊያረጅ የሚችል ወዘተ ወይም ለጥበቃው ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ከሆነ ግልፅ በሆነ ቦታ ላይ በሓራጅ የመሸጥ (ቁ.1156 (1)) ። ለብዙ ወጪ የሚዳርግ ከሆነ የሚለውን አባባል ከንብረቱ ዋጋ በማወዳደር የሚታይ ነው።
ሐ/ ከንብረቱ ባለቤት አንድ አራተኛው የንብረቱ ዋጋ በጉርሻ መልክ እንደየሁኔታው ሊያገኝ
ይችላል። እዚህ ላይ ጉርሻው የመስጠት ወይም ያለመስጠት ስልጣን ለዳኞች የተሰጠ ነው
(ቁ.1158 (1)) ። የጉርሻው መጠን ሊወሰን የሚችለው ንብረቱ ያገኘውን ሰው እና የንብረቱ ባለቤት ያላቸው ሃብትና እንዲሁም የንብረቱ ባለቤት የጠፋውን ንብረት ፈልጎ ለማግኘት የነበረው ዕድል መጥበብና መስፋት ታሳቢ ያደረገ ነው።
መ/ለንብረቱ ጥበቃ ወይም ለሽያጭ ፣ የንብረቱ ባለቤት ቀርቦ ንብረቱን እንዲረከብ ለማስታወቅ ያወጣውን ወጪ እንዲተካለት የመጠየቅ መብት (ቁ.1157(2))። የንብረቱ ባለቤት የሆነ ሰው ላግኚው ወጪዎቹ እስካልተካለት ድረስ ንብረቱን በዕዳ ይዞ የማቆየት መብት አለው።
ሰ/ የይርጋ ጊዜው ያለፈ እንደሆነ የጠፋውን ንብረት ባለቤት የመሆን (ቁ.1157(1))። ይህ መብት ከፍ/ሕግ ቁጥር 1192 ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።
የተጣሉ ወይም የተተው ነገሮች /ንብረቶች/ ከጠፉ ንብረቶች ልዩነት እንዳላቸው ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል። ንብረቶች ከባለቤታቸው ፈቃድ ውጭ፤ ማለትም ከቸልተኝነት የተነሳ ወይም ከዓቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ሊጠፉ እነደሚችሉ ከላይ ተመልክተናል። የተጣሉ ወይም የተተው ንብረቶች ግን የእነዚህ ንብረቶች ባለቤት በማወቅ ከአሁን በኃላ አይጠቅሙኝም ብሎ የጣላቸው ወይም የተዋቸው ናቸው። ስለሆነም የቀድሞው ባለቤት የባለሃበትነት መብቱ ንብረቶቹን እንደጣላቸው ወዲያውኑ ይቋርጣል። እነዚህ ነገሮች እንደተጣሉ ወዲያውኑ ሌላ ሰው ያገኛቸው ወይም ያነሳቸው እንደሆነ ያ ሰው ካገኛቸው /ካነሳቸው/ ጊዜ ጀምሮ የእነዚህ ነገሮች ባለሃብት ይሆናል። ስለዚህ እዚህ ላይ እንደ ዋና ነጥብ ተደርጎ የሚወስደው የቀድመው ባለሃበት ንብረቱ ከእጁ ሊወጣ የቻለው በራሱ ፈቃድ ነው ወይስ አይደለም የሚል ይሆናል።
ስለተቀበረ ገንዘብ (Treasure) (ፍ/ሕግ ቁ.1159-1160)
የተቀበረ ገንዘብ የሚባለው ቀደም ሲል ባለቤት የነበረው ነው ተብሎ የሚታመን ሆኖ ኃላ ግን አንድ ቦታ ላይ እንደተቀበረ ተረስቶ የቀረ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። ይህ ድንጋጌ ተጠፍቶ የተገኘ ንብረት የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ልዩ ሁኔታ (exception) ነው ማለት ይቻላል። አንድ ነገር የተቀበረ ገንዘብ ነወ ብሎ ለመሰየም፦
- 1.ተቀብሮ የተገኘው ንብረት ተንቀሳቃሽ ንብረት መሆን አለበት፣
- 2.በሚንቀሳቀስ ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ውስጥ ተቀብሮ የቆየ ነገር መሆን አለበት፣
- 3.የራሱ ነፃ ህልውና ኖሮት ተቀብሮ ከተገኘበት ንብረት ጋር በቀላሉ ሊለያይ የሚችል መሆን አለበት፣ ከመያዣው ሊለያይ የማይችል ከሆነ የእዛ መያዣ ሙሉ ኣካል /ክፍል/ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚቆጠር ነው።
- 4.ቢያንስ ለ50/ሃምሳ/ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የነበረ መሆን አለበት
- 5.ገንዘቡ ሲገኝ ባለቤት ያልነበረው ወይም የእኔ ነው ብሎ አሳማኝ ነገር ሊያቀርብበት የማይችል መሆን አለበት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጥያቄ ተቀብሮ የተገኘውን ገንዘብ ባለቤት የሚሆነው ማን ነው የሚልው ነው። ይህ ጥያቄ ለመመለስ ሁለት ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይኸውም፤ የተቀበረውን ገንዘብ ያገኘ ሰው የመያዥውም ባለቤት የሆነ እንደሆነ ገንዘቡም የራሱ ይሆናል። የተቀበረው ገንዘብ ያገኘ ሰው የመያዣው ባለቤት ካልሆነ ደግሞ ሁለት ሁኔታዎች ይኖራሉ። አንደኛው ገንዘቡ ሊያገኘው የቻለው በራሱ ጥረት ወይም በአጋጣሚ የሆነ እንደሆነ የተገኘውን ገንዘብ /ንብረት/ ግማሹ በጉርሻ መልክ ለራሱ ግማሹ ደግሞ ለመያዣው ባለቤት ይሆናል። ሁለተኛ ንብረቱ ሊያገኝ የቻለው በመያዣው ባለቤት ትእዛዝ የሆነ አንደሆነ ግን የጉልበቱ ዋጋ ያገኝ እንደሆነ እንጂ ከተገኘው ገንዘብ/ንብረት/ ተካፋይ ሊሆን አይችልም።
እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር ቢኖር አንቲካ የሚባሉ ጥንታዊ ዕቃዎች ፤ ለምሳሌ በአርኪዮሎጂ ቁፈራ የሚገኙትን ነገሮች እንደተቀበረ ንብረት እንደማይቆጠሩና ለእነሱ መተዳደርያ ተብለው በሚወጡ ልዩ ሕጎች/ደንቦች እንደሚመሩ ነው።
ስለ ጥንታዊ ታሪካዊ ቅርሶች የሚደነግገውን ኣዋጅ ቁጥር 229/1958 በአንቀፅ 2/ሀ/ ስር የተመለከተ ሲሆን “ጥንታዊ ቅርስ ማለት ከ1850 ዓ/ም በፊት የተሰራ ማናቸውም ዓይነት ሰው ሰራሽ ስራ ወይም ዕቃ ማለት ነው” በሚል መልኩ አስቀምጦታል። የእነዚህ ንብረቶች ባለቤት መንግስት ወይም የአገሪቱ ሃብቶቸ እንደሆኑና የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደሚያጠቃልልም በዚሁ አዋጅ ዓነቀፅ 3 ላይ ተመልክቶ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ጥንታዊ ቅርስ በእጁ ይዞ የሚገኝ ሰውም ከሚመለከተው የመንግስት አካል ፊት ቀረቦ ማስመዝገብ እንዳለበትና እስኪያስረክብ ድረስ ብቻ በእጁ ማቆየት እንደሚችል ነው ከአዋጁ አንቀፅ 4 መረዳት የሚቻለው:: ይህ አዋጅ ቁጥር 229/1958 በአዋጅ ቁጥር 36/1982 የተሻረ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 36/1982 ደገሞ በአዋጅ ቁጥር 209/1992 ተሽረዋል::
በ1992 ዓ.ም ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 209/1992 ቅርስን አስመለክቶ-የደነገገው ፍ/ሕጉ ካስቀመጠው ለየት ባለ መልኩ ነው::
ቅርስ የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ወይም ግዙፍነት ያለው ወይም የሌለው ነገር ሊሆን እንድሚችል በአዋጁ አንቀፅ 3 ስር የተካተተ ሲሆን፤ በአዋጁ ዓነቀፅ 14(1) ደግሞ ቅርሶቸ በመንግስት ወይም በማናቸውም ሰው ባለቤትነት ሊያዙ እንደሚችሉ ይገልፃል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅርስ ከሌላ ሃብት የሚለይበት ሁኔታዎቸ አሉት:: እነዚህም በግዴታ (duties) እና በገደብ (restriction) መልክ የተቀመጡ ናቸው::
የቅርስ ባለሃብት ግዴታዎች በተመለከተ በአዋጁ አንቀፅ 18 ላይ የተደነገጉ ሲሆን፤ ማናቸውም ቅርስ በባለቤትነት ያየዘ ሰው:
1. በራሱ ወጭ ለቅርሱ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ
2. ቅርሱን ለኤግዚብሽን ወይም በሌላ ሁኔታ ለህዝብ እንዲታይ በባለስልጣን ሲጠየቅ መፍቀድ
3. ለቅርሱ አያያዝና አጠቃቀም የሚመለከቱ የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎችና በአዋጁ መሰረት የወጡ ደንቦችና መመርያዎችን ማክበረ አለበት ይላል
እነዲሁም ማናቸውመ ሰው በባለቤትነት የያዘውን ቅርስ ሚኒስትሩ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት የማስመዘገብ ግዴታ እንዳለበት (አንቀፅ 16(1))፤ የማይንቀሳቀስ ቅርስን እና የተመዘገበ ተንቀሳቃሽ ቅርስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ነው ከአዋጁ ይዘት ግንዛቤ መውሰድ የሚቻለው (አንቀፅ 21)::
ቅርሶች በመንግስት ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ሰው በባለቤትነት ሊያዙ እንደሚችሉ አይተናል:: ይሁን እንጂ ይህ የቅርስ ባለቤትነት ለሌላ ሰው ለማስተላለፍ እንደ ሌላ የንብረት ዓይነት በባለ ይዞታው ወሳኔ ብቻ የሚፈፀም አይደለም:: በአዋጁ አንቀፅ 23 ላይ እንደተመለከተው፤ ማንኛውም ሰው የያዘውን ቅርስ በማናቸውም ሁኔታ ለሌላ ሰው ሲያሰተላልፍ ሁለቱም ወገኖች በቅድሚያ ባለስልጣኑን በፅሑፍ ማሳወቅ እንዳለባቸው እና ባለስልጣኑ ደግሞ ለሽያጭ የቀረቡ ቅርሶችን የመግዛተ ቅድሚያ መብት እንዳለው ተመልክተዋል::
ቅርሶችን በሽያጭ መልክ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደሚቻል አዋጁ ቢጠቁምም በሌላ መልኩ ደግሞ ለንግድ ዓላማ ሲባል መግዛትና መሸጥ እንደማይቻል በሕግ ተገድበዋል (አንቀፅ 24(1) ይመለከተዋል):: ይህ ብቻ ሳይሆን ተገቢ ጥበቃ፣ ጥገናና እድሳት ያልተደረገለት ወይም ለብልሽት የተጋለጠ ወዘተ ቅርስ ሲሆን፣ በቤተመዘክር ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እና ፈቃድ ሳያገኝ ወደ ውጭ አገር ሲወጣ የተገኘ እንደሆነም በመንግስት ሊወረስ እንደሚችል ነው(አንቀፅ 25):: በተጨማሪም በፍለጋ፣ ግኝትና ጥናት የተገኘ ቅርስ በአዋጁ (አንቀፅ 35(3)) መሰረት ለመንግስት እንድሚያስረክብ (አንቀፅ 29) እና ስለቅርስ ጥናት ያካሄደ ሰው የጥናቱ ውጤት የሆነውን ማናቸውንም ፅሑፍ በሚመለከት የባለሃብትነት መብት በፍ/ሕግ መሰረት እንደሆነ ተመለክተዋል(አንቀፅ 40):: እነዲሁም ማንኛውም ሰው የማኣድን፣ የህንፃ፤ የመንገድ ወይም ተመሳሳይ ስራ ለማካሄድ ባደረገው ቁፋሮ ወይም በማናቸወም አጋጣሚ ሁኔታ ቅርሶችን ያገኘ እንደሆነ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ያለበት ሆኖ ሽልማት የማግኘት መብት እንዳለውም በአዋጁ ውስጥ ተካትተዋል (አንቀፅ 41 ይመለከተዋል)::
በአጣቃላይአዋጁ ሲታይ አንድ ሰው የቅርስ ባለቤት ሊሆነ እንደሚችል ቢደነግግም እንደሌላ ዓይነት ንብረት የፈለገው ነገር ሊያደረገው አይችልም:: ይህ የሆነበት ምከንያት ደግሞ በቅርስ ባለቤትነት ላይ በርከት ያሉ ግዴታዎች (duties) እና ገደቦቸ (restrictions) ያሉበት በመሆኑ ነው::
የጠላት ንብረት መያዝ (Seizure of enemy property)
የጠላት ንብረት በመያዝ ባለቤትነት /ባለሃብትነት/ ማረጋገጥ የሚቻለው ለውግያ /ጦርነት/ ተብሎ የተመደበውን ንብረት በሌላ ሓይል ወይም መንግስት ሲማረክ ወይም በቁጥጥር ስር ሲገባ ነው። ንብረቱ ከተማረከ በኃላ የማራኪው ሓይል ወይም መንግስት ንብረት ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በዓለም አቀፍ ሕግና በፓብሊክ ሎዉ የሚመራ ይሆናል። በግለሰብ ደረጃም ሊያዝ የሚችል ነው ተብሎ አይታሰብም።