- Details
- Category: Property Law
- Hits: 8643
ይዞታ የሚተላለፍበት መንገድና የመተላለፉ አስፈላጊነት
ሀ/ ይዞታ የሚተላለፍበት መንገድ፤
1.ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን በቀጥታ ለሌላ ሰው ሲያስተላልፍ (ርክክብ ሲፈፀም ጊዜ) (ፍ/ሕግ ቁ. 1143)
2.የባለይዞታነት መብት ስለመኖሩ የሚያረጋግጡ ሰነዶች አዲሱ ባለይዞታ ለሚሆኖው ሰው በማስረከብ። ይኸውም ንብረቱ በሰነዱ ላይ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ተዘርዝሮ ሊተላለፍ ይገባል። ይህ ዓይነት የመተላለፍያ መንገድ በተለይ በመጓጓዥ ውል (Bill of Lading) አማካኝነት ለሚተላለፉ ንብረቶች /ዕቃዎች/ ይመለከታል። /ፍ/ሕግ ቁ.1144(1) ይመለከተዋል/። ዕቃውን የሚመለከት ሰነድ በያዘና ዕቃውን በአካል በቁጥጥሩ ስር ባደረገ ሰው መካከል ክርክር የተነሳ እንደሆነ ክፉ ልቦና ወይም ተንኰል ከሌለው በስተቀር ዕቃውን በእጅ ያደረገ /ባለይዞታ/ ሰው ብልጫ /ቅድሚያ መብት/ ያገኛል። /ፍ/ሕር ቁ.1144(2) ይመለከተዋል/።
3.የቀድሞ ባለይዞታ ንብረቱ የያዝሁት ወደ ፊት አዲስ ባለይዞታ ለሚሆነው ሰው ነው ብሎ በማያጠራጥር /ግልፅ በሆነ ሁኔታ/ የገለፀ እንደሆነ ነው። /Constructive transfer/ ይሉታል። (ፍ/ሕግ ቁ. 1145(1))። ያም ሆኖ ግን የቀድሞ ባለይዞታ የከሰረ እንደሆነ ወደፊት አዲስ ባለይዞታ ለሚሆኖው ሰው ነው የያዝሁት ቢልም ከእርሱ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች መብት እንደተጠበቀ መሆኑን ሕጉ ያመለክታል (ፍ/ሕግ.1145(2) )
ለ/ ይዞታን የማስተላለፍ አስፈላጊነት፤
የይዞታ መብት የማስተላለፍ አስፈላጊነት የባለሃብትነት መብት ለማስተላለፍ ወይም ንብረቱ በሌላ ሰው እጅ ሆኖ እንዲጠቀምበትና እንዲገለገልበት ለማድረግ ወይም የእዳ መያዣ እንዲሆን ለማድረግ ይጠቅማል።
የባለቤትነት/ባለሃብትነት/መብት ለማስተላለፍ የሆነ እንደሆነ ይዞታ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ሃሓላፊነትም አብሮ የሚተላለፍ ይሆናል። በሌላ አባባል የዕቃው ርክክብ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ የጉዳት ሃላፊነትም አዲስ ባለሃብት ለሚሆኖው ሰው አብሮ ይተላለፋል (ፍ/ሕግ ቑ.2324 (1))
የይዞታ መብት ማስከበርያ መንገዶች፤
በአንድ ንብረትና በባለቤቱ ወይም በባለይዞታ መካከል ያለውን ግንኙነት ሕግ እውቅና ሰጥቶ ከማንኛውም ሰው የሚመጣን ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት ቅሚያ በመከላከል ሕግ ጥበቃ ያደርጋል። ሕግ ለንብረት መብት ጥበቃ በማድረግ ሊደርስ የሚፈልግበት ግብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በመንከባከብ ሰዎች ጥሪቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲችሉ የሚያነሳሳቸው ይሆናል። በመሆኑም ከንብረቱ ጋር በሕግ ተቀባይነት ያለው ግንኙነት ያለው ሰው ባገኘው የንብረት መብት ላይ ሌላ ሰው ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ የንብረት መብት ማስከበሪያ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም የንብረት መብቱ እንዲከበርለት ማድረግ ይችላል።
አንድ ባለይዞታ መብቱን በሁለት መንገድ ማስከበር ይችላል።
- (1)ባለይዞታ በንብረቱ ላይ የተፈጠረን ሁከት ለማስወገድ ሓይል ተጠቅሞ ለመከላከል ይችላል። ይኸውም ንብረቱን ከነጣቂ ወይም በድብቅ ከሚወሰድ ሰው ማስለቀቅ ይችላል። በይዞታ ላይ የሚፈጠር ሁከት በሓይል ለመከላከል ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሁኔታዎች ኣሉ።
ሀ/ በሓይል የመከላከል፣ የተወሰደብህ ንብረት የማስመለስ፣ ህውከት የማስወገድ መብት ተግባራዊ መሆን የሚገባው ለችግሩ ምክንያት በሆነው ወይም ችግሩ በፈጠረው ሰው ላይ እንጂ በሶሰተኛ ወገን ላይ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይገባው፣
ለ/ ሓይል የመጠቀም መብት ከደረሰው ችግር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበትና ልኩን አልፎ መሄድ የተከለከለ መሆኑን፣
ሐ/ ለመከላከል ብሎ ሓይል የመጠቀም ተግባር ወዲያውኑ ለመከላከል ምክንያት የሆነው ችግር እንደተፈጠረ መሆን እንዳለበት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በወንጀል ሕግ አንቀፅ 78-ከተደነገገው-የመከላከል-መብት-ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው ይመለላል።
በግል የመከላከል መብት የተቃጣን ጥቃት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ባለይዞታው ሓይል ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ በፍ/ሕግ ቁጥር 1148(1) እና (2) ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ይኸውም፦
“1. ባለይዞታ የሆነ ሰው እንዲሁም ለሌላ ሰው የያዘው ቢሆንም ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም
በይዞታው ላይ ሁከት ለማንሳት የሚያደርገውን ማንኛውንም ሓይል በመከላከል ለመመለስ
መብት ኣለው።
2. እንዲሁም እጅ ያደረገው ነገር በንጥቂያ ወይም በስውር የተወሰደበት እንደሆነ ነጣቂውን
በማስወጣት ወይም ነገሩን በግፍ ሲወስድ ከተገኘው ወይም ይዞ ሲሸሽ ከተያዘው ነጣቂ ሰው
ላይ ወዲያውኑ በጉልበት በማስለቀቅ የተወሰደበትን ነገር ለመመለስ ይችላል።” ይላል።
የተቃጣን ጥቃት በመመለስ ህይወት፣ ኣካልን ወይም ሌላ ማናቸውም ፍትሓዊ መብት (legally protected right) በመከላከል ማስቀረት የመቻል መብት ህገወጥ ጥቃትን በሚያወግዝ ጠቅላላ መግባቢያ ላይ የቆመ ነው። በመሆኑም ከጥቃት ወይም ከሕገ ወጥ ድርጊት የራስን ይዞታ በመከላከል አጥቂውን መመለስ ወደ ፍርድ ቤት ሳይኬድ መብትን የማስከበርያ መንገድ (extra-judicial remedy) ነው።
ስለዚህ በሕግ በተደነገገው መሰረት የባለይዞታነት መብት ያለው ሰው በይዞታው ላይ የመንጠቅ ወይም ሁከት የማንሳት የሓይል እርምጃ ሲቃጣበት ከወንጀል ሕግም ሆነ ከፍትሓብሔር ሕግ ድንጋጌዎች ባገኘው መብት መነሻ ባለመብቱ በሓይልና ራሱን የመርዳት (self-help) መብት ይኖረዋል።
ሓይልን ሓይል በመጠቀም የመመለሱ ሁኔታ በተለይም ጉዳዩን ለፍ/ቤት ለማቅረብ ዳኝነት ለመጠየቅ ጊዜ በማይኖርበት አጋጣሚ ብቸኛ አማራጭ ይሆናል። በዚህም ባለመብቱ ለራሱ ጉዳይ ዳኛ በመሆን የተቃጣበትን ጥቃት ለመመለስ የሚወስደው እርምጃ በሕግ ተቀባይነት አለው።
በይዞታ ላይ የሚፈጠር ሁከት በፍርድ ስለማስወገድ
በሕጋዊ ይዞታው ላይ ሁከት የተፈጠረበት ወይም ከሕግ ውጭ ንብረቱ የተወሰደበት ሰው ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በማቅረብ በይዞታው ላይ የተፈጠረው ሁከት እንዲወገድ ወይም የተነጠቀው ንብረቱ እንዲመለስ በመጠየቅ የክስ አቤቱታ ሊያቀርብ ይችላል።
በፍ/ብሔር ሕግ ቁ.1149 ላይ ስለ ሁከት ማስወገጃ ክስ እንደሚከተለው ተመልክቷል፦
“1. ይዞታው የተወሰደበት ወይም በይዞታው ላይ ሁከት የተነሳበት ሰው የተወሰደበት ነገር እንዲመለስለት ወይም የተነሳው ሁከት እንዲወገድለት እንዲሁም ስለደረሰበት ጉዳት ኪሳራ እንዲሰጠው ለመጠየቅ ይችላል።
2. የያዘው ነገር ከተነጠቀበት ወይም በይዞታው ላይ ሁከት ከተነሳበት ቀን አንስቶ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በፍርድ ካልጠየቀ እጅ ይዛወርልኝ የማለት ክስ መብቱ ይቀርበታል።
3.ተከሳሹ የሰራውን አደራረግ የሚፈቅድ ለርሱ የሚናገለት መብት መኖሩን በፍጥነት እና በማይታበል ዓይነት ካላስረዳ በቀር ዳኞቹ የተወሰደው ነገር እንዲመለስ ወይም የተነሳው ሁከት እንዲወገድ ያዛሉ።”
ከተጠቀሰው ድንጋጌ ይዘት መረዳት እንደሚቻለው ሁከት ለማስወገድ በፍ/ብሔር ሕግ ቁ.1149 መሰረት የሚቀርብ የክስ ኣቤቱታ (possessory action) ይዞታን የመከላከል ግብ አለው። የይዞታ መብት የሕግ ጥበቃ ስለሚደረግለትም በሕግ ላይ የተደነገገውን ስርዓት በመከተል ሌላ ባለመብት ነኝ የሚል ወገን መብቱን ከሚያስከብር በስተቀር ሓይልን በመጠቀም ባለይዞታውን ማስለቀቅ በሕግ ተቀባይነት አይኖረውም።
የዳኝነት ተቋማትም የሓይል ጥቃት ሰለባ ሆነው የባለይዞታነት መብታቸውን ከሕግ ውጭ የሚያጡ ሰዎች የሚያቀርቡትን የሁከት ማስወገጃ ክስ የተፋጠነ ሁኔታ በማየት ውሳኔ ለመስጠት ካልቻሉ ሕገ ወጥነትን ለመከላከልም ሆነ ለማስወገድ ያላቸው ብቃት የተዳከመ ይሆናል። በተለይም ሁከት ከመፈጠሩ በፊት በባለይዞታው በኩል ሁከቱ ሊፈጠር መሆኑን ከሚያስረዳ ማሰረጃ ጋር ለፍ/ቤት የቀረበ የሁከት ይወገድልኝ ክስ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሓይል ተግባራት ተፈፅሞ የሕ/ሰቡ ሰላምና ደህንነት ከመረበሹ አስቀድሞ የዳኝነት ተቋሙ ተገቢውን የሕግ ማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል። የሁከት ድርጊቱ ከተፈፀመ በኃላ ሰሚቀርብ የሁከት ማስወገጃ ክስ የተከሳሹ የሓይል ተግርባር መፈፀም ያለመፈፀምና የከሳሹን ይዞታ መንጠቅ ያለመንጠቅ ተገቢውን ስነ-ስርዓት ተከትሎ መጣራትና በፍጥነት ውሳኔ ማግኘት ያለበት ጭብጥ ነው።
በመሆኑም በፍ/ብሔር ሕግ ቁ.1149 (3) አነጋገር ተከሳሹ የስራውን አደራረግ የሚፈቅድለት ለርሱ የሚናገርለት መብት (right) መኖሩን በፍጥነት እና በማይታበል ዓይነት (forthwith and conclusively) ማስረዳት የሚጠበቅበት መሆኑን ስለሚያሳይ የማስረዳት ሸክሙና የጊዜውን አጠቃቀም ፍርድ ቤቶች ከግንዛቤ ማስገባት የሚጠበቅባቸው ይሆናል።
ከሁከት ማስወገጃ ክሶች አንፃር በፍርድ ቤቶች መካከል የአፈፃፀም ልዩነት ይታያል። የክሱን ይዘት የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ አድርጎ መመልከት እንደሌሎች ጉዳዮች መደበኛውን ስነ-ስርዓት ተከትሎ መምራት እና የጉዳዮችን የተፋጠነ መፍትሄ ፈላጊነት ትኩረት ያለመስጠትና የማስረዳት ሸክሙን የትኛው ወገን መወጣት እንዳለበት የተለያዩ አቋሞችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
ለማጠቃለልያህል በዚህ ምእራፍ ስር ለማየት እንደተሞከረው የይዞታ ትርጉም አንድ ሰው አንድን ነገር በእጁ አድርጎ በእውነት የሚያዝበት ሆኖ ሲገኝ ማለት እንደሆነ፣ ይዞታ ስለመኖሩ የሚያረጋግጡ ሁለት ነገሮች እንዳሉ፣ አንደኛው ንብረቱ እጅ ማድረግ ሲሆን ሁለኛው ደግሞ ንብረቱ ለመቆጣጠርና ለመጠቀም ሓሳብ መኖር ሲሆን የሁለቱ ነገሮች መምሟላት ይዞታን የሚያስገኙ እንደሆኑ አይተናል:: ይዞታ ሊቀር የሚቸለውም በባለይዞታው ፈቃድ ለሌላ ሰው የተላለፈ እንደሆነ፣ ባለይዞታ የመሆን ሓሳብ ቢኖርም ነብረቱ የጠፋ እንደሆነ እና ንብረቱ ከእጁ በይወጣም ባለይዞታ የመሆን ሓሳብ የጠፋ እንደሆነ መሆኑን ተገነዝበናል:: ይዞታ ቀጣይነተ የሌለው፣ በሓየል የተገኘ፣ በድብቅ የተያዘ እና እውነተኛ ይዞታ ስለመኖሩ የሚያጠራጥር በሆነ ጊዜ ይዞታው ጉድለት ያለበት ነው እነደሚባልም አይተናል:: የይዞታ መብት የሕግ ጥበቃ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ሕ/ሰብ በአጠቃላይ ንብረቱን በሰላም እንዲጠቀምበተና እንዲገለገልበት ለማድረግ መሆኑን ተረድተናል:: ነገሩን በቀጥታ በመስጠት ወይም ይዞታ ስለመኖሩ የሚየረጋግጡ/የሚያስረዱ/ ሰነዶችን በማስረከብ ይዞታን ማሰተላለፍ እነደሚቻልም ለማየት ሞክረናል:: የይዞታ መብት አንደየሁኔታው በሓይል ወይም በፍርድ ቤት አማካኝነተ ማስከበር የሚቻል መሆኑንም ለመገንዘብ ችለናል::