- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ዳኞች በአንድ ሀገር የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የማይተካ እና ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ሕግ የመተርጎም፣ የሚቀርቡ ማስረጃዎችን የመመርመርና የመመዘን እንዲሁም በችሎቶች የሚካሄዱ የክርክር ሂደቶችን መምራት ዋነኛ የዳኞች ተግባራት ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዳኞች እውነት እና ፍትሕን በማፈላለግ ሂደት ገለልተኛ ውሳኔ ሰጪዎች ናቸው፡፡
የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮች ታይተውና ተመርምረው ውሳኔ የሚሰጥባቸው በዳኞች በመሆኑ በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡ የሰው፣ የሠነድ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ተዓማኒነትና ተቀባይነት የመመርመር እንዲሁም የሚቀርቡ የሕግና የፍሬ ነገር ክርክሮችን በተገቢው ሁኔታ አድምጦ የመወሰን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደ አጠቃላይም ዳኞች በክርክር ሂደት በሚሠጧቸው ትዕዛዝ፣ ውሳኔና ፍርድ የተከራካሪ ወገኖችን ሕይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የመወሰን ሥልጣን ተሠጥቷቸዋል፡፡
በመሆኑም የፍትሕ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆኑ ዳኞች የሚቀርብላቸው ጉዳይ ላይ ትክክለኛውን ዳኝነት ለመስጠት በብዙ መልኩ ብቁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም ዳኞች ብቁና ውጤታማ ናቸው የሚባሉት ምን ምን መመዘኛዎች ሲያሟሉ ነው? የዳኞች አመላመልና አስተዳደርስ መመዘኛው ምን መሆን አለበት? የሚሉት ነጥቦች ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት ከዳበሩ ልምዶችና ሕጎች አንፃር በአጭሩ እንፈትሻለን፡፡
በዚሁ መሠረት በተለያዩ ሀገራት ዳኞች ከሹመት በፊትና በኋላ ብቁ እና ውጤታማ ናቸው ለማለት በዋናነት የሚከተሉትን መመዘኛዎች ሊያሟሉ ይገባል፡፡ እነዚህም፡ -
1. ለዳኝነት ሥራ የሚመጥን መልካም ጠባይ መላበስ፡- ዳኞች ሕጉን ከፍሬ ነገር አዛምደው የሚወስኑት ውሳኔ በተከራካሪ ወገኖች ላይ የሚያስከትለውን ውጤት የሚረዱት በዋናነት ከጠበቆች፣ ምስክሮች፣ ተከራካሪ ወገኖች እንዲሁም ሌሎች በዳኝነት ሥራቸው ከሚያገኟቸው ሠዎች ጋር እርጋታና አክብሮት በተሞላበት፣ የማዳመጥ ፍቃደኛነት ባለበት እና በተቻለ መጠን ሕግን ሳይጥሱ የተከራካሪ ወገኖችን ሀሳብ ከክርክሩ ጋር አዛምደው ሲመለከቱ ነው፡፡ ዳኞችም ከመሾማቸው በፊትና ከሹመት በኋላ በሥራ ላይ ትዕግስተኛ፣ አርቆ አሳቢ፣ ሰው አክባሪ፣ ብልህ፣ ታታሪ፣ ቀጠሮ አክባሪ፣ ነገሮችን በቀላሉ የሚረዱና ትሁት መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ዳኞችም እነዚህን የዳኝነት ጠባያት ሊያሳዩ የሚገባው ሁልጊዜ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሚያበሳጩና በሚያናድዱ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ትዕግስትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዳኞች ከሌሎች መመዘኛዎች ባልተናነሰ መልኩ መልካም ጠባይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቀደመ የሥራ አፈፃፀማቸውም ሆነ በአኗኗራቸው በሙሉ መልካም ስምና ጠባይ ያተረፉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የቀደመ የሥራም ሆነ የሕይወት ታሪካቸው ከኢ-ሞራላዊና መጥፎ ስም የፀዳ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
2. በቂ የሕግ ዕውቀት፡- ዳኝነት እንዲሰጥበት ከቀረበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች ማወቅ፣ ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ፣ ሕጉን ከጉዳዩ ጋር በተገቢው ሁኔታ አገናዝቦ ትንታኔ መስጠት እንዲሁም አዳዲስ ጉዳዮችንና ሀሳቦችን በፍጥነት መረዳት፣ መገንዘብና መላመድ ከዳኞች የሚጠበቅ መሠረታዊ የብቃት መለኪያ ነው፡፡
3. የማንበብ ልምድ፡- ዳኞች በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡ የክስ ማመልከቻ፣ መልስ፣ የሠነድ ማስረጃዎች እና ሌሎች ሠነዶችን እንዲሁም ዳኝነት ከሚሠጡበት ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች እና መጽሐፍት ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ አንብቦ የመወሰን ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
4. ሥነ ምግባር፡- ዳኞች የግልና የሙያ ሥነ ምግባርን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዳኞች የግል ሥነ ምግባራቸውን በተመለከተ በኅብረተሰቡ የተሠጣቸውን ከፍ ያለ ከበሬታና ደረጃ የማይነካ ሥነ ምግባር ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን አሠራራቸውም ቢሆን የሙያውን ክብር የማይቀንስና በሙያው የተቀመጡ የሥነ ምግባር ደንቦችን ያከበረ ሊሆን ይገባል፡፡
5. ድፍረት እና ሀቀኝነት፡-
ድፍረት፡- ዳኞች መስራት እና መወሰን ያለባቸው ሕጉ በሚለው መሠረት እንጂ ብዙኃኑ ወይም አቅምና ሥልጣን ያላቸው ተከራካሪዎች በሚፈልጉት መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ዳኞች ሕጉን በሥራ ላይ ለማዋል እንዲሁም ሊመጣባቸው የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ተፅዕኖና ጫና ተቋቁሞ ለመስራት የሚያስችል ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሀቀኝነት፡- ዳኞች የሚሠጡት ውሳኔ በተከራካሪ ወገኖች ማንነት፣ ዘር፣ ፆታ፣ የፖለቲካ አመለካከትና ሥልጣን፣ ኃብት፣ ዝምድና እና የተከራካሪ ወገኖች ጠበቆች ማንነት ተፅዕኖ ሳያድርባቸው በሀቀኝነት ሕጉንና ማስረጃዎችን ብቻ አይተው መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡
6. የትምሕርት ደረጃ እና የሥራ ልምድ፡- ዳኞች ከሁሉም በላይ ሊያሟሉ የሚገባው ነገር የሕግ ትምሕርት እና የሥራ ልምድ ነው፡፡ ዳኞች ከመሾማቸው በፊት የሕግ ትምሕርት ያጠናቀቁ በተቻለ መጠንም በውጤታቸው የላቁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የዳኞች የትምሕርት ደረጃ ምን መሆን እንዳለበት እንደየሀገሩ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን የሚመደቡበት ችሎትም በልዩ ሁኔታ ካጠኑበት የሕግ ዘርፍ ጋር የተያያዘ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዳኞች ከመሾማቸው በፊት በሕግ መምሕርነት፣ የሕግ ባለሙያነት፣ የተለያዩ የሕግ ፅሁፎችና የምርምር ውጤቶችን ለኅትመት በማብቃት፣ በጠበቃነት፣ ዓቃቤ ሕግነት፣ ነገረ ፈጅነትና ሌሎች የሕግ ሥራዎች ላይ የካበተ ልምድ እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ዳኞች ሊኖራቸው የሚገባው የሥራ ልምድና መጠኑ ተሹመው የሚሠሩበት ችሎትና ደረጃ ሊለያይም ይገባል፡፡
7. የሥራ ጫናን የመሸከም ብቃት፡- ፍርድ ቤቶች በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከፍተኛ የመዝገብ መደራረብና የሥራ ጫና ይታያል፡፡ በመሆኑም ያለማቋረጥ የሚቀርቡ ጉዳዮችን ተመልክቶ የሥራ ጫናን ተቋቁሞ በተቀላጠፈ ሁኔታ ዳኝነት መስጠት ከዳኞች የሚጠበቅ የብቃት መለኪያ ነው፡፡
8. የትምሕርት ደረጃን በየጊዜው ማሻሻል፡- ዳኞች የትምሕርት ደረጃቸውን በየጊዜው እያሻሻሉ ከአዳዲስ ሀሳቦች፣ የዳበሩ አስተሳሰቦች እና በየጊዜው ከሚለዋወጡ ሁኔታዎች ጋር እራሳቸው ብቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ዳኞች ከተሸሙበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ የሚሾሙትም ከሹመት በኋላ የትምህርት ታሪካቸው አንፃር በየጊዜው ራሳቸውን በትምህርት ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያደርጉት ጥረት የብቁ ዳኛ መለያ ነው፡፡
9. የመግባባት ችሎታ፡- ዳኞች በችሎት ታዳሚ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር እንዲሁም በውሳኔና ትዕዛዝ አፃፃፍ ላይ ግልፅ፣ አጭር፣ ፍሰቱን በጠበቀና ትክክለኛ መንገድ በጽሑፍም ሆነ በቃል የመግባባትና ሀሳባቸውን የማስተላለፍ እንዲሁም ከተከራካሪዎችና ምስክሮች የሚነገራቸውንም ነገር በቀላሉ ተረድቶ ምላሽ የመስጠት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የመግባባት ችሎታ ዋነኛው አካል የሆነውን የማዳመጥ ችሎታም ዳኞች እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ዳኞችም እንደ አጠቃላይ የተከራካሪ ወገኖችን አቤቱታ፣ ቅሬታና፣ ክርክር በአግባቡ የማድመጥ የመናገርና የመፃፍ ችሎታ ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን በክርክር ሂደት ላይ ክስ የመስማት፣ የሚሠጡ ትዕዛዝና ውሳኔዎችን መፃፍ እንዲሁም የተፃፈውን ውሳኔ በሚገባና ቀላል በሆነ መልኩ ለተከራካሪ ወገኖች ማሳወቅ የመግባባት ችሎታ እንዲኖራቸው ግድ ይላል፡፡
እነዚህ ከፍ ብለው የተጠቀሱት መመዘኛዎች የዳበረ የፍትሕ ሥርዓት ባለቸው በተለያዩ ሀገራት ለዳኞች አመላመልና አስተዳደር እንዲሁም ብቁና ምርጥ ዳኞች ለመለየት በመመዘኛነት ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህ መመዘኛዎች በተጨማሪም የዕድሜ ሁኔታ፣ የጤና ሁኔታ፣ ዳኛ ሆኖ ለመስራት ፍቃደኝነት የማጣሪያ ፈተና ማለፍ፣ ቅድመ ስልጠና መከታተል የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን እና ሌሎችም ነጥቦች ለዳኝነት ሹመት ወይም ስራ በመመዘኛነት ይቀመጣሉ፡፡
ለመሆኑ በሀገራችን ያሉ ዳኞች ከፍ ብለው ከተጠቀሱት መመዘኛዎች ምን ያህሉን ያሟላሉ? አሠራራቸውስ ሁሉንም የምርጥ ዳኛ መለኪያዎች ያሟላል ወይ? ምን ያህሎቹ ዳኞቻችን የዳኝነት ጠባይ ተላብሰዋል? የተመደቡበት ችሎት ላይ የሚታዩ መዛግብት ላይ ለመወሰን በቂ ዕውቀት አላቸው? ምን ያህሎቱ ዳኞቻችን ውሳኔ የሚሰጡበትን መዝገብ እና ተያያዥ ሕጎችና መጻሕፍትን አንብበው ይወስናሉ? ግላዊና ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ይሠራሉ? በድፍረትና በሀቀኝነት ይሠራሉ? በሕግ ትምሕርት የበቁ እና በሚሠሩበት ችሎት ላይ የሚታዩ ጉዳዮችን ለመመልከት የካበተ ልምድ አላቸው? የሥራ ጫናን ተቋቁሞ የመስራት ብቃት አላቸው? ከተሸሙ በኋላስ የትምሕርት ደረጃቸውን ራሳቸውን ብቁ ያደርጋሉ? በቃልም ሆነ በጽሑፍ የመግባባት ችሎታ አላቸው? መልካም ጠባይ የተላበሱስ ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች በተከራካሪዎች፣ ጠበቆች፣ አንባብያንና ሌሎች አስተያየት እንዲሰጡበት በመተው ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፡፡
- Abiyou Girma Tamirat By
- Hits: 18228
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ምንድንነው? በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 760/2012) መሠረት ምዝገባ ዘንድሮ መጀመር ያለበት ቢሆንም ምዝገባ እስካሁን ለምን አልተጀመረም? በአዋጅ የተቋቋመው ኤጀንሲ ምን በመስራት ላይ ነው? ምዝገባው መቼ ይጀመር ይሆን? የሚሉትና ሌሎች ጉዳዮችን ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ነፃነት ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን አስነብቧል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ምንድንነው? የሚሰጠው ጠቀሜታስ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሞት፣ ልደት፣ ጋብቻና ፍችን የመመዝገብ ሥራ ነው። የምዝገባው ጠቀሜታ ሦስት ዋና ጥቅሞች አሉት። ለኢኮኖሚያዊ፣ ለማህበራዊ አገልግሎት፣ ለሕግና ለሕዝብ አስተዳደር አገልግሎት ይውላል።
ለኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ሲባል በአገሪቱ የሚታቀዱ ፖሊሲዎችና እቅዶች መሠረት የሚያደርጉት የኩነቶችን መረጃ ነው። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት መነሻ የሚሆነው የአካባቢው ሕዝብ ነው። ትክክለኛ የሕዝብ ቁጥርን መረዳት የሚቻለው በዓመታት ልዩነት የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃና ሰከንድ የሚከሰቱ ኩነቶችን በመመዝገብ ነው።
ከሕግ አንጻርም በማስረጃ እጦት በሀሰት ምስክር ኢኮኖሚያዊ መብት የሚታጣባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አንዱን እንኳ ብንመለከት ልጅነትን መካድ አንዱ ነው። ልጆች የቤተሰ ቦቻቸውን ንብረት በእኩል የማግኘት መብት እያላቸው በመረጃ ባለመኖሩ በአንድ ቤተሰብ አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ተጎጂ ይሆናሉ። ምዝገባው ይህን ያስቀረዋል። የሕዝብ አስተዳደርን በተመለከተ ለምርጫ፣ ለበጀት ድልድልና ለተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።
አዲስ ዘመን፦ባለፉት ጊዜያት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ይካሄድ ነበር። ለምን ኤጀንሲ ማቋቋም አስፈለገ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ ከአሁን በፊት ምዝገባ ይካሄድ የነበረው በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች ነው። አስገዳጅ ሕግ የለውም። በአገልግሎት ጠያቂው በኅብረተሰብ ፈላጊነት ብቻ የሚካሄደው ነው። የሞት፣የልደት የፍችና የጋብቻ ባለጉዳዩ ፈልጎ ሲመጣ ነው የሚሰጠው። አሁን ግን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በከተሞች ብቻ ተንጠልጥሎ የሚቀር ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ሲቋቋም በአዋጅ የተሰጡት ኃላፊነቶች አሉ። ምን ያህል ተወጥቷቸዋል?
ወይዘሮ ነፃነት፦ የወሳኝ ኩነቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመር ግዙፍ ሥራ ያስፈልጋል። ይህን ግዙፍ ሥራ ለመስራት አዋጁ ባስቀመጠው መሠረት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
በ2006 ዓ.ም የኤጀንሲውን ዋና ዋና የሥራ ሂደቶችን በጥናት በመለየት የማዋቀር፤ አስፈላጊ የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ፤ ኤጀንሲውን በምክር ቤትና በቦርድ እንዲመራ አዋጁ ያስቀምጣል። እነዚህን ማደራጀት፤ ለቢሮ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስና ቢሮ የማደራጀት ስንሰራ ነው የቆየነው። ኤጀንሲውን በሁለት እግሩ አቁመናል።
ራሱን ከማቋቋም ባለፈ ክልሎች የየራሳቸውን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ እንዲያቋቁሙ የማስተባበርና የመደገፍ ኃላፊነትን ተወጥቷል። ለሁሉም የሚሆን መነሻ የማቋቋሚያ አዋጁ ሰርቶ ሰጥቷል። ወጥ የሆነ መረጃ ለማሰባሰብ የሚያስችል ደንብ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ክልሎች ተልኳል። በፌዴራል ደረጃ የወጣውን መሠረት በማድረግ ክልሎች የራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ጨምረው ደንብ አውጥተዋል። ከቀበሌ ጀምሮ የሚኖራቸውን መዋቅርና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ምን ዓይነት መሆን እንደሚገባቸው የሚመለከቱ አጫጭር ስልጠናዎች ተካሂደዋል።
የዘንድሮውን ዓመት የዝግጅት ጊዜ አድርገን ነው የወሰድነው። ኩነቶችን ለመመዝገብ የሚያስችሉ መመሪያዎችን እያዘጋጀን ነው። የአቅም ግንባታ ሥራ ከቀበሌ ጀምሮም እንሰራለን። ኩነቶችን እንዲመዘግቡ ኃላፊነት የተሰጣቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ድርጅት የማብቃትና መመሪያዎች የማዘጋጀት ሥራ ይሰራል። ምዝገባውን ለመጀመር የሚያስችሉ አጠቃላይ የዝግጅት ሥራ እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው አዲስ እንደመሆኑ መጠን በፌዴራልና በክልል በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በሚፈለገው ደረጃ እያሟላ ነው?
ወይዘሮ ነፃነት፦በፌዴራል ደረጃ ዋነኛ የሥራ ዘርፎች የመረጃ ቅበላ፣ የወሳኝ ኩነቶች ጥናትና ምርምር የአሠራር ግንባታ፣ የትምህርትና ስልጠናና የቴክኖሎጂ የሥራ ሂደቶች ከሃምሳ በመቶ በላይ የሰው ኃይላቸውን አሟልተናል። በቀጣይም ሰባ አምስት በመቶ ለማድረስ እየሰራን ነው።
ሆኖም ዋና ችግር የሆነብን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ለአገራችን አዲስ በመሆኑ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል የለም። ከተለያየ የሥራ መስክ የመጣውን ባለሙያ ማሰልጠን ትልቅ ፈተና ሆኖብናል። የኤጀንሲውን ባለሙያዎች ለማብቃት እየጣርን ነው። ቢሯችንን በቁሳቀስ ለማደራጀትም ተሞክሯል። ወደ ምዝገባው ስንገባ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልገናል። እስካሁን መንግሥት በጀት መድቦልናል። በቀጣይ የመንግሥት ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብርን እንሰራለን።
ከአሁን በኋላ ትልቅ ሥራ የሚሆነው ክልሎች ጋር ያለው ነው። ብዙ ክልሎች ኤጀንሲያቸውን አቋቁመዋል። ነገር ግን ኤጀንሲያቸውን ማቋቋም ብቻ በቂ አይደለም። የወሳኝ ኩነቶች ትልቁ ሥራ የሚሰራው ቀበሌዎች ላይ ነው። በአገሪቱ ውስጥ ከአስራ ሰባት ሺ በላይ ቀበሌዎች አሉ። በየቀበሌው የሚከሰትን ኩነት ለመመዝገብ አደረጃጀቱ መመለስ አለበት። የሰው ኃይሉ ፍላጎት መለየት አለበት። ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ወደ ዞን ከዚያም ወደ ክልልና ፌዴራል የሚኖረው ትስስር መፈታት አለበት። ሠራውን ለመጀመር ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ክልሎች ዝግጅታቸውን ካላጠናቀቁ መጀመር አስቸጋሪ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ የሄዱ ክልሎች እንዳሉ ሁሉ ወደ ሥራም ያልገቡ አሉ። ስለዚህ ሁሉንም ወደ አንድ መስመር ማስገባት ትልቁ ፈተና ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ክልሎችን በምን መልኩ ነው እያገዛችኋቸው ያላችሁት?
ወይዘሮ ነፃነት፦ለሁሉም ክልሎች የሚሰራ መመሪያ አዘጋጅተናል። በሁሉም ክልሎች ከቋንቋ በስተቀር ወጥ የሆነ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እንዲኖር ነው የሚያስፈልገው። ወጥ የሆነ መረጃ ለመሰብሰብ በአገር ደረጃ የሁሉንም ባህል ያካተተ የአሠራር ሥርዓት ተቀርጿል። በሁለተኛ ደረጃ ከልሎችን ስልጠና በመስጠት ነው እያገዝን ያለነው። በዘን ድሮ ዓመት ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሠራ እንሰራለን ተብሎ ይጠበቃል። በቀበሌ ደረጃ ኩነቶችን የሚመ ዘግቡ አስራ ሰባት ሺ ሰዎችን እናሰ ለጥናለን። የተለያዩ አገሮች ልምድ ልውውጥ የማስቀ ስም ሥራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መረጃዎች ለመለዋወጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖ ሎጂን ትጠቀማላችሁ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ ወደ ቴክኖሎጂ ከመሄዳችን በፊት የወረቀቱ ሥራ በተጣራ መልኩ መሠራት አለበት። ምክንያቱም የእጁ ሥራ ነው ወደ ቴክኖ ሎጂው የሚሸጋገረው። ለሁለት ዓመት ሥራ ላይ የምናውለው የእጅ ሥራ ነው። የእጁ ሥራ ያሰራናል የሚል እምነት ነው ያለው። በቀጣይ ግን በቴክኖሎጂ ለመታገዝ በጥናት ለመመለስ በእቅዳችን ይዘነዋል።
አዲስ ዘመን፦አዋጁ በ2007 ዓ.ም ምዝገባ እንደሚጀመር ነው ያስቀመጠው። ለምን አልጀመ ራችሁም?
ወይዘሮ ነፃነት፦አዋጁ እንደሚያስቀምጠው ሁለት ዓመት የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋል። እኛ ወደ ሥራ የገባነው አዋጁ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው። አዋጁ እንደዋጣ ወዲያው ኤጀንሲው መቋቋም ነበረበት። ነገር ግን አልተቋቋመም። መተዳደሪያ ደንብ ወጥቶለት ወደ ሥራ የገባው በ2006 ዓ.ም ነው። አዋጁ ያስቀመጠው የዝግጅት ጊዜ አልተሰጠንም። ዘንድሮ የኩነቶች ምዝገባ ያልተጀመረው አንድ ዓመት ዘግይቶ በመቋቋሙ ነው። ዘግይቷል መባል ካለበት በትክክል የተሰጠውን የዝግጅት ጊዜ ተጠቅሞ ጨርሷል ወይም አልጨረሰም የሚል ከሆነ በተሰጠው ጊዜ መሠረት እየሰራ ነው። እንዲያም ሆኖ በአዋጁ ከተሰጠው ጊዜ በአንድ ዓመት ለመጨረስ ሰፊ ሥራ ተሰርቶ ነበር። ነገር ግን የኤጀንሲው ሥራ ብቻ በአገር ደረጃ የወሳኝ ኩነቶችን ለመመዝገብ በቂ አይደለም። ክልሎች መዘጋጀት ነበረባቸው። ክልሎች ኤጀን ሲያቸውን ቢያቋቁሙም ለመመዝገብ አልደረሱም። በዚህ ምክንያት ነው ዘንድሮ ምዝገባ ያልጀመረው።
አዲስ ዘመን፦ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሌሎች የሚደግፏችሁ አካላት በምን ደረጃ እየደገፏችሁ ነው?
ወይዘሮ ነፃነት፦ተጠሪነታችን ለፍትህ ሚኒስቴር ነው። ፍትህ ሚኒስቴር የተቻለውን ያህል ለመደገፍ ጥረት እያደረገ ነው። ከኤጀንሲው ጋር በጋራ ገምግመን ችግሮች የሚፈቱበትን መፍትሔ እናስቀምጣለን። መደገፍ ባለበት እየደገፉን ነው። ፍትህ ሚኒስቴር የራሱ አንገብጋቢ ሥራ ስላለበት አሁን ከሚደግፈው በላይ መደገፍ አለበት ለማለት ትንሽ ያስቸግራል። የክልል ኤጀንሲዎችን ለመደገፍ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የሥራው ባለቤቶች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው። በአጠቃላይ ግን መደገፍ በሚገባው መጠን እየተደገፈ ነው ማለት አይቻልም። አዲስ ኤጀንሲ ለማቋቋም ትልቅ ፈተና አለው።
አዲስ ዘመን፦የኤጀንሲው ቦርድ ወቅቱን ጠብቆ አላካሄደም ምክንያቱ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ነፃነት፦ቦርዱ በየወሩ እየተገናኘ የኤጀንሲውን ሥራ መገምገም እንዳለበት መመሪያ ደንቡ ያስቀምጣል። በየወሩ መካሄድ ነበረበት ግን አልተካሄደም። ያልተካሄደበት ምክንያት ሁለት ነው። የሚቀርቡ ውሳኔዎችን በየወሩ ቦርዱ ይዞ መቅረብን ችላ ብሎ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ የቦርድ አባላት በስብሰባ ላይ መገኘት አልቻሉም። ይህ ትክክል አለመሆኑ አዳማ ባካሄድነው ስብሰባ አንስተን ተነጋግረናል። ለማስተካከልም ተስማ ምተናል።
አዲስ ዘመን፦የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በእርግጠኛነት መቼ ትጀምራላችሁ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ በ2008 ዓ.ም መስከረም ወይም ጥቅምት ወር ላይ እንጀምራለን። ከቻልን ከዚያ በፊት ልንጅምር እንችላለን።
አዲስ ዘመን፦አብረዋችሁ የሚሰሩ አካላት ምዝገባውን ለማገዝ ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ድርሻ ያላቸው አካላት እንደ ጤና ጥበቃ፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ የፍትህ አካላት፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ባለድርሻ አካላት በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነቱን ለመወጣት በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። እነኝህ አካላት በቂ ዝግጅት ካላደረጉ ምዝገባውን ለማካሄድ ተጽዕኖው ቀላል አይሆንም።
ከኤጀንሲው የሚገኘውን መረጃ የሚያወጣው ማዕካለዊ ስታትስቲክስ ስለሆነ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ራሱን መፈተሽና ዝግጅት ማድረግ አለበት። የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የኤጀንሲው ሥራ ብቻ ሳይሆን የብዙ አካላት ትብብር ውጤት ነው። በመሆኑም በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል። የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በኩነቶች መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው። ስለሆነም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት። የራሱ ጉዳይ ነው ብሎም ሊደግፈን ይገባል። ሚዲያዎችም ሥራዎቻችንን ለሕዝብ ጆሮ በማድረስ ሊተባበሩን ይገባል።
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 19531
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
እናንት ዳኞች የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለይግባኝ ተቀብያለሁ፡፡ ይግባኝ ብዬ ጉዳዬን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለውና በይግባኝ የአፄ ኃ/ስላሴን ፊት ማየት አልፈቅድም፡፡
በእግዚያብሔር ስም ተሰይማችሁ ከተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን የዛሬውን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስብና ፍርድ እስከዚህ መርከሱን ስታዘብ ሀዘኔ ይበዛል፡፡
እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ሕግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስር እና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጎላሉትን ሕዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ነፃነትና ርምጃ የተነሳሁ ወዳጅ ነኝ እንጂ ለማፋጀት የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም፡፡ ይህንን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሰራዊትና መሣሪያ ሳላጣ ዛሬ እዚህ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር፡፡
እኔ ከኃ/ስላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት የተራቡ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና አገር ለማፍረስ አለመምጣቴን የሚያረጋግጥልኝ እናንተ በትዕዛዝ ያገኛችሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው፡፡
ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው ንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡ በየአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ግፍ ሽልማት በመሆኑ እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ሥልጣን አላፊ ነው፡፡ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ስልጣን ነበረኝ፡፡ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ የሚበደልበት ሥልጣንና ድሃ የማይካፈለው ኃብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ፡፡ አሁንም እሞታለሁ፡፡ ሰው ሞትን ይሸሻል፡፡ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ኽዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትን አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄአለሁ፡፡ የጀመርኩት ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ አልተሸነፍኩም፡፡ ወገኔ የሆነው ድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመርኩለትን ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈፅሞ ራሱን በራሱ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም፡፡
ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልሰራለት ካሰብኳቸው ስራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን ይህ ሃሳቤ ህይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡
ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡
እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ሕግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስር እና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጎላሉትን ሕዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር፡፡
ከእናንተ ከዳኞቹና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ እኔ ፍርድ ተቀባይ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ፡፡
የኔ ከጓደኞቸ መካከል ለጊዜው በህይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የመመዘኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡
ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተና ለገዢአችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡ በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባላደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡
መንግስቱ ንዋይ : መጋቢት 19 ፣ 1953 ዓ.ም
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 18933
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
- ሕገ መንግሥታዊ መሰረት
- የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት
- የዋና አዘጋጅ ኃላፊነት
- በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለሚፈፀሙ ወንጀሎች የኃላፊነት ቅደም ተከተል
እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? በዛሬው ፅሁፋችን የምናነሳው ስለመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 540/2000 እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች ምን እንደሚሉ እንመለከታለን።
ሕገ መንግሥታዊ መሠረት
ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 29 ሥር ካረጋገጣቸው ነፃነቶች አንዱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ነው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል። በተጨማሪ ይህን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማረጋገጥ በአንቀጽ 29(3) ስር የፕሬስና የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን ይደነግጋል። በተለይ የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ
- በማንኛውም መልኩ ቅድመ ምርመራ ክልክሏል፣
- የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት እድል የፕሬስ ተቋሙ እንደሚኖራቸው ማረጋገጫ ሰጥቷል።
ሆኖም ግን ይህ መብት ፍፁም አይደለም። ይሄን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ስር ሌሎች መብቶችንና ጥቅሞችን ለመጠበቅ ሲባል ገደብ ሊጣልበት ይችላል። ሆኖም ግን ገደቦቹ ሊጣሉ የሚገቡት የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትለው በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ሕጎች ብቻ መሆኑን ያሰምርበታል። በተጨማሪ የወጣቶችን ደህንነት ለመጠበቅ የሰውን መልካም ስም እና ክብር ለመጠበቅ ሲባል እነዚህ ነፃነቶች በህግ ሊገደቡ እንደሚችሉ ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠ ሲሆን የጦርነት ቅስቀሳዎችና ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ መሆናቸውንና እነኚህን ሕጎች ጥሶ የተገኘ የተቀመጡትን ገደቦች የተላለፈ ማንኛውም ዜጋ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ተደንግጓል።
ይህን ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ መሠረት በማድረግ ወደወጣውና በስራ ላይ ያለውን ሕግ እንመልከት።
በአዋጁ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ አራት ላይ በሕገ መንግሥታችን ለመገናኛ ብዙሃን የተሰጠውን እውቅና በማስተጋባትና ቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ መከልከሉን በድጋሚ በመደንገግ ይጀምራል። በአንቀጽ 4(3) ላይ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ ከተለያዩ የመንግስት አካላት መረጃ በመንፈግ ወይም መረጃ እንዳያገኙ እንቅፋት በመሆን ሊያሳድሩባቸው የሚችሉትን ተፅዕኖ ለመከላከል
- ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት፣
- በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ፣
- የተለያዩ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም የሕዝብን አስተያየት የመቅረፅ ሂደት የመሳተፍ መብታቸውን ማክበር እንደሚኖርባቸው ደንግጓል። ይህ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ሊገደብ የሚችለው በግልፅ በሕገ መንግሥቱና በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ አንቀጽ 4(2) በሚወጡ ሕጎች ብቻ ነው።
የማሳተምና የመደራጀት መብት
የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ በአንቀጽ 5 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰው በመገናኛ ብዙሃን ስራ የመሰማራት መብት እንዳለው ይደነግጋል። ይህ መብት የተሰጠው ለግለሰቦቹ ሳይሆን በአዋጁ አንቀጽ 7(6) መሠረት በሀገራችን ሕግ መሠረት እውቅና ለተሰጣቸው ተቋማት ወይም ድርጅቶች ብቻ ነው። እነዚህ ድርጅቶችም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ ኩባንያዎች መሆን አለባቸው ይህም ማለት
- የኩባንያው የካፒታል ምንጭ ሙሉ በሙሉ ከሀገር ውስጥ የሆነ እና
- የአክስዮን ባለድርሻዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን የሆኑበት ማለት ሲሆን
የሀገር ውስጥ ማህበር ለመባል ደግሞ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕግ መሠረት እንደ አገር በቀል ማህበር የተመዘገበ ማህበር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን በአንድ ዓላማ ወይም አደረጃጀት ባለው ተቋም ውስጥ ውጤታማ ተፅዕኖ ያለው ሰው በተመሳሳይ ቋንቋ በሚታተምና በተደራራቢ ገበያ የሚሰራጭ የህትመት ሥራን ከሚሰራ ሌላ ኩባንያ ካፒታል ወይም አክስዮን ላይ ውጤታማ ቁጥጥር እንዳይኖረው በአዋጁ አንቀጽ 7(3) ላይ የተደነገገ ሲሆን ውጤታማ ቁጥጥር የሚለካበት ሕግ እስኪወጣ ድረስ ውጤታማ ቁጥጥር የሚባለው በማንኛውም ኩባንያ ወይም ድርጅት አክስዮኖች ወይም ካፒታል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ 15 ከመቶ በላይ ድርሻ ያለው ሰው ነው።
በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል የመገናኛ ብዙሃን ማለት በየጊዜው የሚወጡ የህትመቶች እና ብሮድካስቶችን የሚያካትት መሆኑን ይገልጻል። የህትመት ሥራን ሲተረጉም ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንንና በህዝብ እንዲደርሱ ታስበው የሚሰራጩ የሙዚቃ ስራዎችን፣ የአዲዮቪዥዋል ሥራዎችን፣ ስዕሎችን፣ ተውኔቶችን፣ ካርቱኖችን መፅሐፍትን፣ በራሪ ፅሁፎችን፣ ፊልሞችን፣ ፖስተሮችን የንግድ ማስታወቂያዎችን፣ ዜና አገልግሎትንና ማንኛውም አይነት ሌሎች ህትመቶችን የሚያካትት በመሆኑ ከተለመዱት ጋዜጣ መፅሄቶች መፅሐፍት በተጨማሪ በርካታ ሃሳብን የመግለጫና መረጃ የማስተላለፊያ መንገዶችን እንደሚያካትት መረዳት ይቻላል።
በየጊዜው የሚወጡ ህትመት የሚባለው ደግሞ አንድ ቋሚ ስያሜ በመያዝ በተወሰነ የጊዜ ክፍተት ሳይቋረጥ በተከታታይ እንዲወጣ ታስቦ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም አጠቃላይ ስርጭት ያለውና በጠቅላላው ህብረተሰብ ወይም በአንድ በተወሰነ የህዝብ ክፍል እንዲነበብ ታስቦ የሚሰራጭ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን የሚያካትት የህትመት ሥራ መሆኑን አዋጁ አንቀጽ 2(3) ይደነግጋል።
በመገናኛ ብዙሃን ስራ ውስጥ ዋና አዘጋጅ ትልቁን ሚና የሚጫወትና ሙሉ ኃላፊነት የኤዲቶሪያል ስልጣን ያለው ሰው ነው። በአዋጁ አንቀጽ 6 ላይ በዋና አዘጋጅነት የሚሾም ሰው በስሩ የሚታተሙትን ህትመቶች ይዘት የመቆጣጠርና ማንኛውንም ነገር ያለ ፈቃድ እንዳይታተም የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶታል። ይህን ስልጣኑን የሚገድብ ማንኛውም አይነት አሰራር ወይም ስምምነት በሕግ ፊት ፈራሽ ነው።
ይህን ስልጣኑን ተግባራዊ ለማድረግ ዋና አዘጋጁ ሙሉ የሕግ ችሎታ ያለው ሊሆን ይገባል። ይህም ማለት እድሜው ለአካለ መጠን የደረሰ በአእምሮ ወይም በአካል ጉዳት በፍ/ቤት ያልተከለከለ ወይም በተጣለበት የወንጀል ቅጣት ከመብቶቹ ያልተሻረ መሆን አለበት።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ለዋና አዘጋጁ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ሰጥቶታል። በመሆኑም ለመገናኛ ብዙሃኑ ውጤት ይዘቶች ሙሉ የሕግ ተጠያቂነት አለበት።
በአዋጁ አንቀጽ 2(12) አሳታሚ ማለት የመገናኛ ብዙሃኑን የሚወክል ወይም የመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤት የሆነ፣ በድርጅቱ ውስጥ የጎላ የባለንብረትነት ጥቅም ያለው ወይም የድርጅቱን የሥራ አስተዳደር የሚመራ ማንኛውም ሰው ሲሆን አታሚ የሚባለው ደግሞ የህትመት ሥራውን ለማተም ከአሳታሚው ጋር የተዋዋሉ ማተሚያ ቤቶችን የሚመለከት ነው።
አዋጁ አከፋፋይ እና አስመጪ የሚባሉትን በመገናኛ ብዙሃን ስርጭት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን አካላትም ትርጓሜ ተሰጥቷቸዋል። አከፋፋይ የህትመት ስራን በጅምላ ለማከፋፈል በአሳታሚው የተሾመ ወይም የተዋዋለ ሰው ነው። አስመጪ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን በሀገር ውስጥ ለማሰራጨት በማሰብ ወደ ሀገር የሚያስገባ ወይም በሀገር ውስጥ የሚያሰራጩ የውጭ ህትመቶች ወኪል የሆነ ማንኛውም ሰው ነው።
በመገናኛ ብዙሃን የሚፈፀም ኃላፊነት የሚያስከትል ድርጊትን በተመለከተ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 43 ላይ በቅደም ተከተል ያስቀመጠ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂነቱ የፕሬስ ውጤቱ ሲታተም በዋና አዘጋጅነት ወይም በምክትል አዘጋጅነት የተመዘገበ ሰው ለወንጀሉ ኃላፊ ሲሆን ዋና አዘጋጁ፤ ዋና አዘጋጅ ለመሆን የሚያበቃ ሁኔታዎችን ካላሟላ ወይም በዋና አዘጋጅነት መስራቱን ካቆመ የፕሬሱ አሳታሚ ኃላፊ ይሆናል። አሳታሚው ካልታወቀ አታሚው፣ አታሚውም ሊታወቅ ካልቻለ የፕሬስ ውጤቱ ያሰራጨው ሰው የወንጀል ኃላፊነት እንደሚኖርበት ይደነግጋል።
- ኪዳኔ መካሻ By
- Hits: 17245