- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
‹‹ይሄ የማይታመን ነው፡፡ ዛሬ ለስድስተኛ ጊዜ ዳኛው ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሩኝ፡፡ ከጠዋት 3፡00 እስከ 6፡30 ተቀምጬ እጠባበቃለሁ፡፡ የያዝኩት ጉዳይ ሲጣራ ዳኛው ጉዳዩ ውስብስብ ስለሆነ አይተው እንዳልጨረሱ ይነግሩኛል፡፡
የጉዳዮች ብዛትና የዳኞች ቁጥር እንደማይመጣጠን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም ላልተሠራ ነገር ደንበኛዬና ወዳጅ ዘመዶች በዚህ የትራንስፖርት ችግር በሌሊት ከቤት ወጥተውና ሥራ ፈተው እዚህ መቀመጣቸው በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ፍትሕ ለማግኘት እምነት ቋጥረው ቢመጡም፣ በየቀኑ መሠረታዊ የመብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው፡፡››
ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሪፖርተር ዘጋቢ በቅርቡ ለሥራ በሄደበት ወቅት ያገኛቸው ጠበቃ የነገሩት ቅሬታ ነበር፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት ወይም የፍትሕ ተደራሽነት ላይ ቅሬታ ያላቸው ጠበቆች ብቻ አይደሉም፡፡ በሒደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎች፣ ራሳቸው ዳኞችና የማረሚያ ቤት መኮንኖችን ጨምሮ ተገልጋዩ ማኅበረሰብ ፍትሕ የማግኘት መብት አፈጻጸም መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ይገልጻሉ፡፡ የመንግሥት ይፋዊ ሪፖርቶችም ችግሩን ለመቅረፍ የተደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ላይ ቢያተኩሩም፣ ችግሩ አሁንም ጥልቀት እንዳለው ግን ይቀበላሉ፡፡ ነገር ግን የችግሩ ምንጭና ምክንያት ላይ ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ጉዳዮችን አይጠቅሱም፡፡
ይህ መሠረታዊ ልዩነት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በኢትዮጵያ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ II በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት››ን አስመልክቶ ያዘጋጀው የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት፣ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቸርችል ሆቴል በተዘጋጀበት ወቅት በስፋት ተንፀባርቋል፡፡ ጠበቆች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተሳተፉበት በዚህ ውይይት፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ከሚያስፋፉት ይልቅ የሚገድቡት ጉዳዮች የገዘፉ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብት ይዞታ በኢትዮጵያ
በፓናል ውይይቱ ላይ ፍትሕ የማግኘት መብት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ያለውን ገጽታ አስመልክቶ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ቀደም ብሎ ዳኛና አክሽን ፕሮፌሽናል አሶሴሽን ፎር ፒፕል የተሰኘ አገር በቀል ሲቪል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቶ ደበበ ፍትሕ የማግኘት መብትን ዜጎች ወይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሕ ለማግኘት የሚጠይቁበት፣ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኙበት ሥርዓት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡ ይህ መብት ሦስት አንኳር ክፍሎችን እንደሚያቅፍ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህም ፍትሕ የመጠየቅ ችሎታ፣ የተጠየቀውን ፍትሕ የማግኘት ዕድልና በምን ያህል ጊዜ ፍትሕ ይገኛል የሚሉት ጉዳዮች ናቸው፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብት ሦስት መሠረታዊ ባህርያት እንዳሉትም አቶ ደበበ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው ሰብዓዊ መብት መሆኑ፣ ሌሎችን መብቶች ለማስከበር መሣሪያ ሆኖ ማገልገሉና እንደ በሕግ ፊት እኩል ሆኖ የመታየት መብት ካሉ ተያያዥ መርሆዎች ተነጥሎ ለብቻው የሚቆም አለመሆኑ ናቸው፡፡
አቶ ደበበ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕገ መንግሥቷ ፍትሕ የማግኘት መብትን በአግባቡ መያዛቸውን ያስገነዝባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍትሕ የማግኘት መብት ጋር የተቆራኙ መርሆዎችን መቀበሏን ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህ መርሆዎች መካከልም ቁልፍ የሚባሉት በሕገ መንግሥቱና በሕግ የተሰጠን መብት ለማስከበር መንግሥት የገባው ኃላፊነት፣ ብቃት ያለው፣ በሕግ የተቋቋመ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት በመጠቀም ግልጽና ፍትኃዊ የፍርድ ሒደት ማደራጀት፣ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሕግ ዕርዳታ መስጠትና ተነፃፃሪ በሆነ አቅም ላይ ተከራካሪዎችን ማስቀመጥ (Equality of arms) በኢትዮጵያ ሕጎች ቦታ እንደተሰጣቸው አቶ ደበበ ያስረዳሉ፡፡
በሕጎቹ አማካይነት ኢትዮጵያ እነዚህን መርሆዎች ብትቀበልም፣ አፈጻጸማቸውን ለማሳለጥ ተቋማት ብታደራጅም፣ ሥነ ሥርዓትና አሠራሮችን ብትቀርፅም ፍትሕ የማግኘት መብትን በአግባቡ ለመፈጸም በርካታ ጋሬጣዎች ወይም መሰናክሎች እንዳሉ ግን አቶ ደበበ ይጠቁማሉ፡፡ የፍትሕ ተደራሽነትን ከሚያውኩ ዋና ዋና ጋሬጣዎች መካከል አቶ ደበበ ማኅበራዊና ባህላዊ፣ የሕግና የአስተዳደር፣ በፍትሕ ሒደቱ ውስጥ ያሉ መዋቅራዊ ችግሮችና በቂ የሆነ የሕግ ዕርዳታ ያለመኖርን ይጠቅሳሉ፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖች የበቀል ዕርምጃ ሊወስድብኝ ይችላል ብሎ መፍራት፣ ከማኅበራዊና ከባህላዊ ጋሬጣዎች መካከልም እንደሚመደብም አስገንዝበዋል፡፡ እንደ ምሳሌም በሃይማኖትና በብሔር ልዩነት የተነሳ ዜጎች ፍትሕ ላላገኝ እችላለሁ ብለው ማሰባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ፍትሕ ተቋማት በፍትሕ ሚኒስቴር መሪነት በ2006 ዓ.ም. ያወጡት የጋራ ሪፖርት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ያላቸውን አፈጻጸሞች ይዳስሳል፡፡ በዚህም የሰው ኃይል ብቃትን በማጎልበት፣ የፍትሕ ዘርፍን አመራር ውጤታማነት በማሳደግ፣ የፍትሕ ዘርፍን አሠራር ቅልጥፍና በማሳደግ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማሻሻል፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግና ሥርዓቱን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን በመደገፍ የመጡትን መሠረታዊ ለውጦች ይዘረዝራል፡፡
ይሁንና የፍትሕ ዘርፉ በአመራርም ሆነ በፈጻሚው ዘንድ የለውጥ ሥራውን በመምራትና በማስፈጸም ረገድ ከግንዛቤ ጀምሮ የአስተሳሰብ፣ የክህሎትና የግብዓት ችግሮች በሰፊው እንደሚስተዋሉበትና የሰው ኃይል እጥረትና ፍልሰት የተቋማቱ የወል ችግር እንደሆነ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያም ሆነ የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በሚፈለገው መንገድ ተፈጻሚ እንዳልሆነም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ቀላል የማይባል ባለሙያና አመራር በሙስና ተግባር ተሠማርቶ የሚገኝ መሆኑንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር እነዚህን ችግሮች ከሞላ ጎደል የተቀበለ ሲሆን፣ ፍትሕ የማግኘት መብትን ከማረጋገጥ አኳያ የሚከናወኑ ተግባራትን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም ዕቅዶች በዋነኛነት መርሐ ግብሩ ከለያቸው ችግሮችና ተግዳሮቶች የተነሱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች በበቂ ሁኔታ የተደራጁ ባለመሆኑ የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት አጥጋቢ አለመሆኑ፣ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች የሚሠራጩበት ውጤታማ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤቶች በወረዳ ደረጃ ያልተቋቋሙ መሆኑና በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ደረጃም በበቂ ሁኔታ የማይገኙ መሆኑ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ የሚከናወን አለመሆኑና የኅብረተሰቡን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመገናኛ ብዙኃንንና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በሰፊው አለመሥራቱ፣ ከተጠቀሱት ችግሮችና ተግዳሮቶች መካከል ይገኛሉ፡፡
መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ጥናቶች እንደሚያከናውን፣ ተጨማሪ ምድብ ችሎቶችን እንደሚከፍት፣ ተጨማሪ አካላት እንደሚያቋቁም፣ አቅም ለማሳደግ ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ፣ የተከላካይ ጠበቆች ተጨማሪ ቅጥር እንደሚያከናውን፣ አዳዲስና ነባር ሕጎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይሆኑ ዘንድ የሽያጭ ጣቢያዎች እንዲስፋፉ እንደሚያደርግ፣ ሕጎችን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የመተርጎም፣ የማጠናከርና የማሠራጨት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚደረግ የችሎት ሥርዓት (e-litigation) በሁሉም ክልሎች ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲስፋፋ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን የሚያቀናጅ ብሔራዊ የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚያደርግና አለመግባባቶችን በሕግ የሚፈታና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት ያለው ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚያከናውን ዘርዝሯል፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ ባለፉት ወራት አብዛኛውን ዕቅድ ለመፈጸም መንግሥት መንቀሳቀሱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የተከናወኑት ተግባራት ያለውን ችግር ለመቅረፍ በቂ አለመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ቀሪ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ፍትኃዊ ሕግ የማግኘት መብት
በፓናል ውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው ፍትሕ የማግኘት መብት አፈጻጸም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ፊሊፖስ አይናለም ጠበቃና የሕግ አማካሪ እንዲሁም አስተማሪ ናቸው፡፡ አቶ ፊሊፖስ ፍትሕ የማግኘት መብት ጥሩ ወይም ፍትኃዊ ሕግ የማግኘት መብትን እንደሚጨምር ተከራክረዋል፡፡
አቶ ፊሊፖስ ፍትኃዊ ሕግ ፍትሕ ለመስጠት ተስማሚ የሆነ ሕግ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ መለያ ባህርያቱን በተመለከተ ሲያብራሩም ለሞራል የሚስማማ፣ ተፈጻሚነት ያለው፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ዘለቄታዊነት ያለው፣ ለወንጀል ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣትን የሚደነግግ፣ እኩልነትን ያረጋገጠና ወንጀል መሆን የማይገባውን በወንጀልነት የማይፈርጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማስከበር መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው የሚጠቅሱት አቶ ፊሊፖስ፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሊያስከብሩት የሚገባውን መብት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ራሳቸው ሲጥሱት እንደሚስተዋልም አመልክተዋል፡፡ ይህ ችግር በሕግ አስተርጓሚውና አስፈጻሚው አካል ጭምር የሚታይ ችግር ቢሆንም፣ አሳሳቢ የሆነው ችግር ግን በሕግ አውጪው በኩል የሚወጡና ለሕግ አስፈጻሚው ሰፊ ነፃነትን የሚሰጥበት አሠራር እንደሆነ አቶ ፊሊፖስ ያስገነዝባሉ፡፡ ሕግ አስፈጻሚው እነዚህን ክፍተቶች ተጠቅሞ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚጥሱ ደንቦችንና መመርያዎችን ማውጣቱንም ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
አቶ ፊሊፖስ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ካሏቸው አዋጆች መካከል አንዱ በባንክ በመያዣ የተያዙ ንብረቶችን የሐራጅ ሽያጭ የሚደነግገው አዋጅ ነው፡፡ ባንኮች በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን ባይወጡ፣ ፍርድ ቤቶች ጣልቃ እንዳይገቡ መከልከላቸው ፍትሕ የማግኘት መብትን እንደሚያጣብብም አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የከተማ ቦታ ይዞታ አዋጅ ለሕዝብ ጥቅም ንብረቱ የተወሰደበት ሰው ይግባኝ ሊጠይቅ የሚችለው በካሣ ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑ፣ ፍትሕ ከማግኘት መብት ጋር የሚጋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የተባረረ ተከራይ ፍርድ ቤት ሄዶ እንዳይከራከር መከልከሉ ፍትሕ የማግኘት መብትን ከመፃረሩም በላይ ሙስና እንዲበራከት ማድረጉን አቶ ፊሊፖስ አስረድተዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 639/2001 ተጠቅሞ ሕግ አውጪው አስቀድሞ የተወሰነ የሕግ ተርጓሚውን ውሳኔ በሕግ መሻሩም ፍትሕ ከማግኘት መብት መርሆዎች ጋር የሚቃረን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ፊሊፖስ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅና የግብር ሕግጋቶች እንዲሁ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ ጫና እንደሚፈጥሩ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔዎች እንደ ሕግ መቆጠራቸውን በመጥቀስ የችሎቱ አንዳንድ ውሳኔዎች ፍትሕ የማግኘት መብት ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑም አሳይተዋል፡፡
ዶ/ር አደም ካሴ በጀርመን ሃይድልበርግ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የማክስ ፕላንክ ፋውንዴሽን ዓለም አቀፍ ሰላምና የሕግ የበላይነት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር አደም እንደ አቶ ፊሊፖስ ሁሉ ፍትሕ የማግኘት መብት ከፍርድ ቤቶች ባሻገር ከአስተዳደራዊ ተቋማት ውሳኔ አሰጣጥና ሕግ አወጣጥ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ውሳኔዎችና መመርያዎች በአብዛኛው በመርህ ያልተደገፉና ከሥርዓት ይልቅ በተቋማዊ ባህል እንደሚመሩም አመልክተዋል፡፡ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቢኖር የአስተዳደራዊ ሕጎች አወጣጥና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተገማችነትና ሥርዓትን ሊፈጥር ይችል እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ሕግ ለማውጣት በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ በ1996 ዓ.ም. የተዘጋጀው ረቂቅ አልፀደቀም፡፡
ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ
አቶ ፈቃዱ ደምሌ በፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡ አቶ ፈቃዱ ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሠራው ሥራ በሕግ ከተሰጠው ሌሎች ተልዕኮዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥትን በሕግ ጉዳይ የማማከር፣ የሕግ ጥናት የማድረግ፣ ሕግ የማርቀቅ፣ ሕግን የማስረጽ፣ ወንጀል የሚቀንስበትን ስልት የመንደፍና የመከላከል ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጠበቆችን በተመለከተ ፈቃድ የመስጠት፣ የማደስ፣ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆችን ጉዳይ የመስጠት ሥልጣን ሌሎች ኃላፊነቶችን ለመወጣት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ መመርያዎችን ማውጣቱን ያስታወሱት አቶ ፈቃዱ፣ በኢትዮጵያ ጠበቆች በገዛ ፈቃዳቸው በሕግ የተጣለባቸውን በዓመት ለ50 ሰዓታት ነፃ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸውን እንደማይወጡ አመልክተዋል፡፡ ጉዳዮችን ወስደው አቅም የሌላቸውን ዜጎች ለመርዳት ሰበብ እንደሚደረድሩ፣ ከወሰዱም በኋላ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደማይከታተሉ ወቅሰዋል፡፡
ጠበቆች በተናጠል ከሚያቀርቡት ነፃ የሕግ አገልግሎት በተጨማሪ የሙያ ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሥር የተቋቋሙ የሕግ ትምህርት ቤቶች ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን አቋቁመው አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ አገልግሎቶቹን ለማቀናጀት በብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብሩ በታቀደው መሠረት ስትራቴጂ ለማውጣት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን አቶ ይበቃል አስታውቀዋል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማሻሻል መንግሥት በርካታ ሥራዎችንና ጥረቶችን እያከናወነ ቢሆንም፣ ጉድለቶች ይበልጥ ገዝፈው እንደሚታዩ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ፊሊፖስ ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት በአጠቃላይ ፈተና ላይ ነው፡፡ ፈተናውን ሙሉ በሙሉ አላለፈም፤›› ብለዋል፡፡ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሁሉም ቢስማማም፣ ፍትሕ የማግኘት መብት መሠረታዊ ችግሮች ላይ ስምምነት አለመኖሩ ችግሩ በቅርቡ ሊፈታ እንደማይችል ይጠቁማል፡፡
በአላስፈላጊ ቀጠሮዎች የተማረረው ጠበቃ ግን አንዳንድ ችግሮች በመጠነኛ ሥራዎች ሊፈታ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ‹‹በሞባይል መልዕክት፣ በስልክ ወይም በኢንተርኔት ጉዳዩ እንደማይታይ ቀድሞ ቢነገርና ባለጉዳዩ ወጪውን ቢሸፍን በጥቂት ወጪ ከድካም፣ ከገንዘብ ኪሳራና ከጊዜ ብክነት መገላገል ይቻል ነበር፤›› ሲልም ይደመድማል፡፡ አቶ ደበበ የኢትዮጵያ የፍርድ ሒደት ‹‹ሥርዓት የማብዛት ሁኔታ (Formalism) ያበዛል፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋራጭ መንገዶች ከክብሬ ጋር አይመጥንም ብሎ ይሆን ፍርድ ቤቱ ያን ሁሉ ሰዓት ቁጭ ላሉ ሰዎች በምሳ ሰዓት ዛሬ ጉዳያችሁ አይታይም የሚለው?
- EthiopianReporter By
- Hits: 15341
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ጎሮ ሰፈራ አካባቢ ለወትሮው በሚታጠፍበት ቦታ ላይ ሲደርስ ከፊት ለፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች ሲፈተሹ ያያል፡፡ ስለዚህ ትራፊክ ፖሊሶቹ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ጨምሮ ስለመሟላታቸው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄ አሽከርካሪዎች
ሲመልሱ ተራው ደርሶት በሒደቱ ውስጥ ለማለፍ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ መጠባበቁ ከምክንያታዊ ጊዜ ሲያልፍ ወጣቱ ትራፊክ ፖሊሶቹ እንዲያስተናግዱት መጣራት ጀመረ፡፡ ሰሚ አጥቻለሁ ብሎ በማሰቡ ታጥፎ ለመንቀሳቀስ መንገድ ጀመረ፡፡
ድንገት ግን ‹‹ነውር አይደለም እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ድምፁን ከፍ አድርጎ ከኋላ ከሚከተል የትራፊክ ፖሊስ ሰማ፡፡ ወጣቱም ተሽከርካሪውን ካቆመ በኋላ ‹‹ነውሬ ምንድን ነው?›› ሲል አጠገቡ የቆመውን ትራፊክ ፖሊስ ጠየቀው፡፡ ለጥያቄው ምላሽ መስጠቱን ወደ ጎን በማድረግ የሚፈልጋቸውን ሰነዶችና ጥያቄዎች አከታትሎ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ወጣቱ የተጠየቀውን ሁሉ ካሟላ በኋላ በድጋሚ የሠራው ነውር ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደሚፈልግ ገለጸ፡፡ መንጃ ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችን ለትራፊኩ ሰጥቶ የነበረው ወጣት ሳያስበው ፊቱ ላይ ተወረወሩበት፡፡ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጁና ባለቤቱን ይዞ የነበረው ወጣት በፍጥነት ከተሽከርካሪው በመውጣት ትራፊክ ፖሊሱን ተከትሎ ‹‹ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ አሁንም ያልጠበቀው ምላሽ ገጠመው፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ በቦክስ መታው፡፡
ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈጸም የሚመለከቱት የአካባቢው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባዎችም ጭምር ነበሩ፡፡ ወጣቱ ትራፊክ ፖሊሱን ለመክሰስ እንደሚፈልግ በመግለጽ አሁንም መከተሉን አላቆመም፡፡ በአካባቢው የተሰባሰቡት አራት ተጨማሪ የትራፊክ ፖሊሶች ምን እንደተከሰተ እንኳን ለማጣራት ሳይሞክሩ ወጣቱን ይበልጥ በማዋከብና በመገፈታተር መንገዱን እንዲቀጥል አዘዙት፡፡ ‹‹አለቃችሁን ማግኘት እፈልጋለሁ?›› የወጣቱ ቀጣይ ጥያቄ ነበር፡፡ የክፍል አለቃው ራሱን አስተዋውቆ በተሻለ አቀራረብ አነጋገረው፡፡ የሆነውን ሁሉ በጥሞና ከሰማ በኋላ እሱም ቢሆን ጉዳዩን በእርቅ እንዲጨርስ ጠየቀው፡፡ ወጣቱ እንደ ትራፊክ ፖሊሶቹ ሁሉ የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆነና አገሩን እንደሚያገለግል፣ የግለሰቡ ድርጊትም በምንም ዓይነት መንገድ አግባብ እንደሌለው እያስረዳ መታወቂያውን አሳየው፡፡
መታወቂያውን በማየት ብቻ የትራፊክ ፖሊሶቹ ያሳዩት የአመለካከት ለውጥ ግን ወጣቱን ይበልጥ አስደነገጠው፡፡ ያዋክቡት የነበሩት ትራፊክ ፖሊሶች ወጣቱ ክሱን በመተው በእርቅ እንዲጨርስ ይወተውቱት ጀመር፡፡ አሁን ፖሊሱ ለምን ያህል ዓመት እንደሠራ፣ ልጆችና ትዳር እንዳለው በመጥቀስ ነገሩን እንዲረሳው ይማፀኑት ጀመር፡፡ ድርጊቱን መማርያ ለማድረግ የተነሳው ወጣት ግን ጥያቄያቸውን ችላ ብሎ ወደ ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ አመራ፡፡ ወደ ቅጥር ግቢው ደርሶ ክስ የሚመሠረትበትን ክፍልና የምርመራ ኃላፊውን አገኘ፡፡ ኃላፊው የወጣቱን ጉዳይ ከሰሙ በኋላ መደብደቡን ሲገልጽላቸው ቀጣዩ ጥያቄያቸው ‹‹ከዚያስ?›› መሆኑ ወጣቱን ግራ አጋባው፡፡ ድርጊቱ በተከሰተበት ቦታ ያገኛቸው ሽማግሌ፣ የትራፊክ ፖሊሱ ባልደረቦች፣ መርማሪ ፖሊሶቹ፣ ዓቃቤ ሕጉ እንዲሁም የወጣቱ ጓደኞች ክስ መክሰሱ የበቀል ዕርምጃ እንደሆነና የሚያስተምረውም ሆነ የሚቀይረው ነገር እንደሌለ ማመናቸው ሊፈጽመው ያሰበው ነገር ትርጉም እንዲያጣ አደረጉት፡፡ ምንም እንኳን ከብዙ መንገላታት በኋላ በፖሊስ ጣቢያው ቃል መስጠትና ሚስቱን ማስመስከር ቢችልም፣ በጉዳዩ ለመግፋት ግን ተነሳሽነቱ እንዲሞት እንዳደረጉት ይገልጻል፡፡
ወጣቱ የሺዋስ ፈንታሁን ይህ አጋጣሚ የደረሰበት በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ እርግጥ ነው በፖሊስ ጣቢያዎች ሥር የተዋቀሩት የወንጀል መከላከል የሥራ ሒደት፣ የምርመራና ክትትል ሥራ ሒደት እንዲሁም የትራፊክና ደኅንነት ክፍል ባልደረቦች አደረሱት ተብሎ የሚሰማው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሺዋስን ከገጠመው በአብዛኛው ይልቃል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት ቸልተኝነትና ፍላጎት ማጣት፣ እንዲሁም በቁርጠኝነት ጥሰቶችን ለማረም ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፎች አለመኖር ሁኔታውን ማወሳሰቡ በሁሉም ጉዳዮች የጋራ ችግር እንደሆነ ኤክስፐርቶች ያስረዳሉ፡፡
ሕገ መንግሥቱን በማክበርና በማስከበር ወንጀልንና የወንጀል ሥጋትን በመከላከልና በመቀነስ፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ በየአካባቢው እንዲረጋገጥ ማድረግና የሕዝቡን ሰላማዊ ኑሮና ደኅንነት ማስጠበቅ የፖሊስ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎች ራሱ ፖሊስ በወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ሆነ ተብሎ ሲነገር ይሰማል፡፡
በተለይ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በፖሊስ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደረሰብን ማለታቸው የዜጎችን ትኩረት ከሳቡ የወንጀል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ በዘመናዊ መንገድ ተደራጅቶ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት በጥበቃ ሥር ላሉ ሰዎች የተለያዩ መብቶች ዕውቅናና ጥበቃ ይሰጣል፡፡
በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብቶች ተብለው በኢትዮጵያ ከሚታወቁት መካከል ያለመናገር ወይም ቃል ያለመስጠት መብት፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት፣ በዋስ የመለቀቅ መብት፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት፣ በሕግ ባለሙያ ወይም አማካሪ የመወከል መብት፣ ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ መብት፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ሕገ መንግሥት፣ ዝርዝር ሕጎች፣ ተቋማትና አሠራሮችን ለመቅረፅ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ በወረቀት ላይ ከፍተኛ ምቾት የሚሰጡ መብቶች በአፈጻጸም ወቅት ምቾት እንደሚነሱ የዜጎች ምስክርነት ያሳያል፡፡
በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ‹‹በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብት አከባበር በኢትዮጵያ ፖሊስ ጣቢያዎች፡- የክትትል ሪፖርት›› በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት የእነዚህ መብቶችን አፈጻጸም የዳሰሰ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በአንዳንድ የፖሊስ አባላትና መርማሪዎች ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀም ተጠርጣሪን መያዝ፣ ዛቻ፣ ስድብና ድብደባ በተጠርጣሪዎች ላይ መፈጸምና አስገድዶ ቃላቸውን መቀበል ‹‹በተወሰኑ›› ፖሊስ ጣቢያዎች መከሰቱን በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በአብዛኛው ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ጊዜ ያለመናገር መብት እንዳላቸውና የሚናገሩት ማንኛውም ቃል ራሳቸው ላይ እንደማስረጃ ሆኖ እንደሚቀርብባቸው እንደማይነገራቸውም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
በጥበቃ ሥር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ
እነዚህን ክስተቶች በመጥቀስ በኢትዮጵያ ፖሊስ በጥበቃ ሥር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የመንግሥት ይሁንታ የተቸረውና ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው ነው የሚሉ አሉ፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ሕጎችና አሠራሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚዋጉ በመሆናቸው የግለሰቦች ጥሰት አጋጣሚ እንጂ የሥርዓቱ መገለጫ አይደለም በሚል በሌላ ወገን ክርክር ይቀርባል፡፡ የእነዚህ ሁለት ጽንፍ የያዙ ክርክሮች መቋጫ ጥፋት አጥፍተው በተገኙ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡
የፖሊስ ተጠያቂነት
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ስለሚባሉ ፖሊሶች በየጊዜው ዜና የሚሰማው ዜጋ፣ ለፍርድ ቀርበው ለድርጊታቸው ተጠያቂ መደረጋቸውን ግን ሪፖርት የሚያደርግለት ካላገኘ ተቋማዊ ጥሰት እንዳለ ቢያስብ እንደማይፈረድበት ያስረዳሉ፡፡
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አሠራር ተቋማዊ ጥሰትን አይቀበልም፡፡ ግለሰቦች የሚፈጥሯቸው ችግሮች በተቋሙ መፍትሔ እየተሰጣቸው እንደሆነ ያትታል፡፡
አቶ ምትኩ መኰንን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥበቃና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኮሚሽኑ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብትን መጣስ የፖሊስ ተቋም የያዘው አቋም እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ የደረሰው በሥራ ገጠመኞች የተነሳ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በፖሊስ አማካይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ ሪፖርት ተደርጎለት ምርመራ አድርጎ ጥሰቱን ባረጋገጠባቸው ጉዳዮች ሁሉ መንግሥት ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ምትኩ ይመሰክራሉ፡፡
መንግሥት የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች ለኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ለኅብረተሰቡ መረጃውን የማድረስ ችግር እንዳለ ግን ይጠቁሉ፡፡ ‹‹ስህተት በሠሩ ፖሊሶች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ ለኅብረተሰቡ የሚገለጽበት አሠራር የለም፡፡ በዚህ የተነሳ በተቋም ደረጃ የተሠራ ሊመስል ይችላል፤›› በማለትም ያብራራሉ፡፡ ይሁንና በተቋም ደረጃ ጥሰቶቹ የሚደገፉ ቢሆን ኖሮ ጉዳዮች ይደበቁና ይድበሰበሱ እንደነበር ይከራከራሉ፡፡ ‹‹እኛ የምናውቃቸውን ጉዳዮች መርምረን፣ ጥያቄ አቅርበን ያልተከሰሰና ዕርምጃ ያልተወሰደበት አላገኘንም፡፡ ከሥራ የተባረሩ፣ የብዙ ዓመት እስራት የተወሰነባቸው ብዙ ጉዳዮችን እናውቃለን፤›› ሲሉም የተቋማቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን ለማሳለጥ ይረዳል የተባለው የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር በጥቅምት 2006 ዓ.ም. ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ባለድርሻ አካላትን የሚሠሯቸውን ሥራዎች በማቀናጀት በወረቀት ላይ ያሉ መብቶችን ወደ መሬት በማውረድ ለእያንዳንዱ ዜጋ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ያለውን ይህን ሰነድ አፈጻጸም የሚከታተለው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ እንደ አቶ ምትኩ ሁሉ የአፈጻጸም ክፍተቶችና የግለሰቦች ስህተት ቢያጋጥምም ተቋማዊ የሆነ የፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ብለው እንደማያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የወደቁ ሥርዓቶችን የተካ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ተቋማዊ አሠራር ያደርጋል ብሎ መገመት አስቸጋሪ እንደሆነም አቶ ይበቃል ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ይሄ መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር የአገር ህልውና መሠረት አድርጎ ይወስዳል፤›› ሲሉም የሰብዓዊ መብት መከበር የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ ይበቃል እንደ ሌሎች መብቶች ሁሉ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና በመስጠት ሳይገደቡ ተጽፈው ብቻ እንዳይቀሩ አፈጻጸማቸውን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ አደረጃጀቶቹ ስህተት የሚፈጽሙ የፖሊስ አባላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችሉ እንደሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በርካታ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች፣ የማረሚያ ቤቶች አመራሮች መብት መጠበቅ አልቻላችሁም ተብሎ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል›› ሲሉም የፖሊስ ተጠያቂነት በወረቀት አለመገደቡን ይመሰክራሉ፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩ ፖሊሶች በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ ተጠርጣሪዎቹ ያላቸውን መብት ሊገልጹላቸው እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን ያለማድረግ አስተዳደራዊ ዕርምጃ የሚያስወስድ እንደሆነ በፖሊስ ኮሚሽኖች የአባላት የሥነ ምግባር ደንቦች ውስጥ እንዲካተት ሥልጠናዎች እንዲሰጡም ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ አቶ ይበቃል ሁለቱንም ድርጊቶች ለማሳካት ጥረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
የወንጀል ጉዳዮችን በመያዝ ለታወቁት ጠበቃ አቶ አምሃ መኰንን ግን በዜጎች ዘንድ የፖሊስ ጥሰት ተቋማዊ እንደሆነ ተደርጎ መታሰቡ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ ‹‹ለምሳሌ ደንበኛዬ በፖሊስ ሲመረመር እንዳማክር ጥሪ ተደርጐልኝ አያውቅም፡፡ ይሄ የማይታሰብ ነገር ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በርካታ በፖሊስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ታዝቤያለሁ፡፡ ነገር ግን ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ይልቅ ጉዳዩን ስታነሳ ቂም ይያዝብሃል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ምትኩም ሆኑ አቶ ይበቃል ያጠፉ ፖሊሶችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ በሚፈለገው መልኩ እየተሠራ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ የግለሰቦች ጥፋት እየተበራከተ ሲመጣ ተቋማቱ ግለሰቦችን መቆጣጠር እንደተሰናቸው ስለሚያሳይ ኃላፊነቱን እንደሚጋሩ በመጠቆም፣ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት ሊሳብ እንደሚገባ አቶ ምትኩ ይመክራሉ፡፡
የተራዘመ የምርመራ ጊዜ
ቀልብ በሳቡ ጉዳዮች ተደጋግሞ እንደታየው በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በተራዘመ የምርመራ ሒደት ያልፋሉ፡፡ እንደ አቶ አምሃ ገለጻ፣ የችግሩ ዋና ምንጭ ፖሊሶች ወንጀል ተፈጽሟል ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸውን ማስረጃ ሳይዙ ተጠርጣሪዎችን ለማሰር የማያመነቱ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የፖለቲካ ትኩሳት ባለባቸው ጉዳዮችና የመንግሥት ልዩ ፍላጎት በሚንፀባረቅባቸው ጉዳዮች ላይ አላስፈላጊ መንዛዛቶች እንደሚስተዋሉ አቶ አምሃ ገልጸዋል፡፡
‹‹የወከልኳቸው የዞን ዘጠኝ ጉዳይ ክስ ሳይመሠረትባቸው 83 ቀናት ያህል በምርመራ ቆይተዋል፤›› ሲሉም አቶ አምሃ እንደ አንድ ማሳያ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ደንበኞቼ በጥበቃ ሥር እያሉ ለ20 ቀናት ያህል ልጎበኛቸው አይደለም በምርመራው ሒደት ላማክራቸው አልቻልኩም፤›› ሲሉም ይከሳሉ፡፡
ይህ አቶ አምሃ ከልምዳቸው በመነሳት የሚገልጹት ሁኔታ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና በዘፈቀደ የመረጣቸው ዜጎች የሚጋሩት ነው፡፡ እንደ እነዚህ ሰዎች እምነት ፖሊስ በወንጀል የጠረጠራቸውን ሰዎች ለመመርመር ካልታሰሩ ሥራውን የሚሠራ አይመስለውም፡፡ በኢትዮጵያ ሕግም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ባላቸው አሠራሮች በመርህ ደረጃ ዜጎች ነፃነታቸው ተጠብቆና በቁጥጥር ሥር ሳይውሉ የተጠረጠሩበትን ወንጀል አጣርቶ አስተማማኝ መረጃ በቅድሚያ መያዝ ያስፈልጋል፡፡
አቶ ምትኩ ሰው ታስሮ መረጃና ማስረጃ መሰብሰብ ተገቢነት የሌለው አሠራር መሆኑን ቢገልጹም፣ በተግባር ግን ፖሊስ ከእስር በኋላ መረጃና ማስረጃ የሚሰበስብበት አሠራር እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ምትኩ በኢትዮጵያ ባህል በወንጀል የተጠረጠረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው የሚል እምነት መኖሩ፣ ፖሊሶችም አልፎ አልፎ አመለካከታቸው በዚያው እንዲቃኝ ሳያደርግ እንዳልቀረ ያመለክታሉ፡፡ ይህንን ለመቀየር በርካታ ቀሪ ሥራም እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
ለአቶ ምትኩም ሆነ ለአቶ ይበቃል ችግሩን ለመቅረፍ ትልቁ ቁም ነገር የፖሊሶችን ግንዛቤ ማሳደግ ነው፡፡ ‹‹ሰብዓዊ መብት እንደ ባህል ሊዳብር ይገባል፡፡ ከግንዛቤ እጥረት የሚነሱ የአፈጻጸም ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ሰብዓዊ መብት በተፈጥሮው ሥር ለመስደድ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የሕግ ሥርዓት ተበጅቷል፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና አመለካከቶች በግልጽ ተተንትነው ቀርበዋል፣ ሕጎች ወጥተዋል፣ አሠራሮች ተዘርግተዋል፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የአመለካከት አካል ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፤›› በማለት አገሪቱ ያለባትን ተግዳሮት የጠቆሙት አቶ ይበቃል፣ በድርጊት መርሐ ግብሩ አማካይነት የተሠሩት ሥራዎች ነገሮች በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንዳሉ እንደሚያሳዩ አስገንዝበዋል፡፡ ጽሕፈት ቤታቸውም ለፖሊስ፣ ለማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለፍትሕ ቢሮዎችና ለፍትሕ ሚኒስቴር ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱንም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ግንዛቤ ማስጨበጥ ብቻ ሳይሆን እንዲፈጽሙት የቤት ሥራ እንሰጣለን፤›› በማለትም ጽሕፈት ቤቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ያገናዘበ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
አቶ አምሃ ግን ፖሊሶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙት ከግንዛቤ እጥረት እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የተጠርጣሪዎቹን መብት የማያውቅ መርማሪ አለ ብዬ አላምንም፤›› ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መርማሪዎቹ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከውጭ ካሉ መረጃዎችና ማስረጃዎች ይልቅ ጥገኛ የሚሆኑት በእምነት ቃልና በምስክሮች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የምርመራ ጊዜውን ማራዘም ብቻ ሳይሆን ለሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይጋብዛሉ፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ጥሰት ተፈጽሟል ብለው ባመኑበት አጋጣሚ ክስ ከሰው ያውቁ እንደሆነ በሪፖርተር የተጠየቁት አቶ አምሃ፣ የፖሊስ ባልደረባን ከሰው እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ ማስረጃ የማግኘት ችግርና በተጠያቂነት ሥርዓቱ ላይ እምነት ማጣት ምክንያት እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ግለሰቡ ተጠያቂ ቢሆን የተቋሙ ስም የሚጠፋ ይመስላቸዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ አቶ ምትኩ ፖሊሶችን ተጠያቂ ለማድረግ ማስረጃ ማግኘት ከባድ መሆኑን ይጋራሉ፡፡
ወጣቱ የሺዋስም ከትራፊክ ፖሊሱ ጋር በገጠመው ሁኔታ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ይህን ችግር እንዳስተዋለ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ከሥራ ባልደረቦቻቸው አንዱን ለመርዳት ማሰቤን ብቻ ነበረ ያስተዋሉት፤›› ሲልም ክስ የመክሰስ ሐሳቡን እንዲተው ያስቻለውን ነጥብ ያመለክታል፡፡
አቶ ይበቃል የዜጎችን አመለካከት መቀየር ቁልፍ በመሆኑ ከአፈጻጸም ጎን ለጎን ግንዛቤ ማስጨበጥ ተጠናክሮ እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ምትኩ በተጨማሪ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ችግርን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌሎች የመንግሥት ቁርጠኝነት የበለጠ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ያጎላሉ፡፡
- EthiopianReporter By
- Hits: 13897
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
አብዛኛዎቻችን በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረን የምንሠራ የሕግ ባለሙያዎች በተቀጠርንበት መሥሪያ ቤት ልክ የሕግ ሙያችንን እንወስነዋለን፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ስል ዓቃቤ ሕጎች፣ ነገረ ፈጆች፣ ዳኞች፣ የሕግ አማካሪዎች እና መስል የሕግ ሙያን የሚሠሩ ባለሙያዎችን ማለቴ ነው፡፡ በተቀጠርንበት የሥራ ዘርፍ ልምድና ዕውቀት ማሳደግና ማዳበር ይበል የሚያሰኝ ተግባር ቢሆንም በሌሎች የሕግ ዘርፎች መጠነኛ እውቀት እንዲኖረን ማንበብ ሁለገብ ዕውቀት እንዲኖረንና ምሉዕ እንድንሆን የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዓቃቤ ሕግ ስለወንጀል እና ስለወንጀለኛ ሕግ ሥነ ሥርዓት ብቻ ቢያውቅ ራሱን ሙሉ የሕግ ባለሙያ ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግረው ይመስለኛል፡፡ በተመሳሳይ ይህ ውስንነት በጠበቆች ላይም ሲስተዋል ይታያል፡፡
አብዛኞቹ ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በኋላ የሕግ ዕውቀታቸውን ለደንበኞች በሚሰጡት አገልግሎት ልክ ይወስኑታል፡፡ በተለይ በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች የሚተረጉሙት፣ የሚረዱት ወይም የሕግ ክፍተት የሚፈልጉት ደንበኞቻቸው ለሚፈልጉት ዓላማ ለማዋል እና እነርሱን ለማርካት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ጠበቆች ያለባቸውን ኃላፊነት ወይም የጥብቅና ሙያቸውን የሚያሳድጉበት አግባብ እጅግ ውስን ከመሆኑም ባሻገር ደንበኞች ለሚፈልጉትና ለሚጠይቁት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ብቸኛ የጠበቃ ተግባር ተደርጎ ሲወሰድ ይታያል፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ጠበቆች ደንበኞችን ለመሳብም ሆነ የደንበኞችን ጥቅም በአግባቡ ለመመለስ ካለመቻላቸውም በላይ ከፍትሕ የሚመነጭ ርካታን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከራሳቸው ወይም ከሕግ ሙያ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለማየት ይቸገራሉ፡፡
ነገር ግን አንድ ጠበቃ ደንበኛው የሚፈልገውን አገልግሎት ከመሥራትና ከዚሁ ሥራው ከሚያገኘው ጥቅም ያለፈ ታላቅ ኃላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡ ታዲያ እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ የምርጥ ጠበቃ መገለጫ ተግባሮች ምን ምን ናቸው? የሚል ይሆናል፡፡ ከአሜሪካ የጠበቆች ማኅበር የምርጥ ጠበቃ ተግባሮች እንደሚከተለው አቀናብረን አቀርበነዋል፡፡ ራስዎን ይመዝኑበት!
1. አማካሪነት
የጠበቃ የመጀመሪያና ተቀዳሚ ተግባር ርዳታ የሚፈልጉ ደንበኞች ለደረሰባቸው ችግር አስፈላጊና የተሟላ ምክር መስጠት ነው፡፡ የተሟላ ምክር ለመስጠት ደግሞ የሕጎችን መሠረታዊ መርህ በሕጎቹ እንደተደነገጉትና እንደተጻፉት እንዲሁም በተግባር አንደሚተረጎሙት ወይም ተግባር ላይ እንደዋሉት በጥልቀትና በስፋት ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር የማማከር ኃላፊነት የሰዎችን መሠረታዊ ባሕርይ፣ የፍትሕ አስተዳደሩን እንዲሁም የአንድን ኅብረተሰብ አኗኗር በሰፊው መረዳትን ያሻል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጠበቆች የሚመጡ ደንበኞች መረዳትና ማወቅ የሚፈልጉት ሕጉ ምን እንደሚል ሳይሆን ሕጉ በፍርድ ቤት በሚተረጎምበት ጊዜ የሚሰጠው ውሳኔ እነሱ ካላቸው ወይም ከሚፈልጉት ጥቅም አኳያ እንዴት እንደሚታይ ወይም ወሳኔ እንደሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ጠበቃ የደንበኞቹን ጥቅምና ፍላጎት ከመጀመሪያው መረዳትና መገመት ሳይሆን በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሰጥ ጥቅማቸው እንዴት ሊጠበቅ እንደሚችል ማወቅ መረዳት ይጠበቅበታል፡፡
በዚህም ምክንያት አንድ ጠበቃ ምርጥ ጠበቃ ለመባል የአንድን ኅብረተሰብ አኗኗር፣ የሰዎችን መሠረታዊ ባሕርይ፣ የሀገሪቱን ሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጠንቅቆ መረዳትና መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
2. መፍትሔ ሰጭነት ወይም አመላካችነት
ሁለተኛውና ቀጣዩ የምርጥ ጠበቃ ተግባር መፍትሔ ሰጭነት ወይም አመላካችነት ሲሆን በፍርድ ቤት ወይም በይግባኝ ፍርድ ቤት ስለደንበኞቹ ጥቅም በብቃት የሚከራከር ወይም ስለደንበኞቹ ሕጋዊ መብት ጥብቅና ሊቆም የሚችል ነው፡፡ አንድ የሕግ ባለሙያ ብቃት ያለውና ልምድ ያለው ጠበቃ ካልሆነ በስተቀር በግሃዱ ዓለም በፍርድ ቤት የሕግ ጉዳዮች አንዴት አንደሚተረጎሙና ተግባር ላይ እንደሚውሉ ካላወቀ በስተቀር የደንበኞቹ ጉዳዮች ወዴት እንደሚሔዱ ለማየትና ትክክለኛውን መፍትሔ ለመስጠት ወይም ለማመልከት ይቸግረዋል፡፡ ሕግ የሚተረጎመውና ተግባር ላይ የሚውለው ፍርድ ቤት/ዳኞች በሚሰጡት ትርጓሜና ውሳኔ ስለሆነ ይህንን አብይ ተግባር ቅርጽ በማስያዝና ዳኞች ትክክለኛ ትርጉምና ውሳኔ እንዲሰጡ በማድረጉ በኩል ጠበቃ የራሱን አስተዋጽዎ ያበረክታል፡፡
የመፍትሔ ሰጪነት ወይም አመላካችነት ተግባር ጠበቆች ከሚጠበቅባቸው ከባዱና አስቸጋሪው ተግባር መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንዳንድ ምርጥ ውሳኔዎች ላይ ከሚፃፉ ጥልቅ የሕግ ትርጉሞች ጀርባ የምርጥ ጠበቃ አድካሚና አሰልቺ ሥራዎች እንዳሉበት ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ መፍትሔ ሰጭነት ወይም አመላካችነት ከላይ የወረደ ጸጋ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጥረትና ልምድ የሚመጣ ክህሎት ነው፡፡ በመሆኑም የምርጥ ጠበቃ መገለጫ ተግባር ከሆኑት መካከል መፍትሔ ሰጪነት ወይም አመላካችነት አንዱና ዋንኛው ነው፡፡
3. የሕግ ሙያን፣ ፍርድ ቤትን፣ እና ሕጉን የማሻሻል ወይም የማሳደግ
የምርጥ ጠበቃ ሦስተኛው ተግባር የሕግ ሙያን፣ የፍርድ ቤት አሠራርን እና ሕጉን ለማሻሻል ወይም ለማሳደግ የራሱን ወይም የማኅበሩን (የጠበቆች ማኅበር ካለ ማኅበሩን በመወከል) አስተዋጽዎ ማበርከት ነው፡፡ “እያንዳንዱ ባለሙያ ሙያውን የማሳደግ የራሱ ኃላፊነት መወጣት አለበት፤” ይህ አባባል ሙያን ከንግድ የሚለየው አብይ ቁምነገርን የያዘ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሀገራችን የጠበቆች ሥነ-ምግባርን የሚደነግገው ደንብ (ደንብ ቁ. 57/1992) አንቀጽ 3 የሚከተለውን አጠቃላይ መርህ ይደነግጋል፡-
“ማንኛውም ጠበቃ ሕግን ለማስከበርና ፍትሕን ለማስገኘት የፍትሕ አስተዳደሩን የማገዝ ኃላፊነት አለበት፡፡ ማንኛውም ጠበቃ በተለይም ለደንበኛው፣ ለሌሎች የሕግ ሙያተኞችና ተከራካሪ ወገኖች፣ ለፍርድ ቤት፣ ለሙያው እና በአጠቃላይ ለኅብረተሰቡ ያለበትን የሙያ ኃላፊነት በቅንነት፣ በታማኝነት እና በእውነተኛነት መወጣት አለበት፡፡”
በመሆኑም ጠበቃ ደንበኛን ተቀብሎ ከማስተናገድና ከዚሁ ከሚገኘው ጥቅም ያለፈ የፍትሕ አምባሳደር መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡
4. ከራስ ተጠቃሚነት የደንበኞችን ተጠቃሚነትን የማስቀደም
ከራስ ተጠቃሚነት የደንበኞችን ተጠቃሚነትን የማስቀደም ተግባር ሌላው የምርጥ ጠበቃ መገለጫ ተግባር ነው፡፡ ጠበቆች የግል ጥቅምን ወደጎን ትተው ለትክክለኛ ፍትሕ መሥራት አለባቸው፡፡ ይህም ሲባል የጥብቅና ሙያ በኅብረተሰቡ ዘንድ መታወቅ ያለበት የግል ጥቅም ማካበቻ ተደርጎ (ንግድ ሆኖ) ሳይሆን ፍትሕ የማግኛ መንግድ ወይም ለሕዝብ ጥቅም ወይም ለሁሉም ደህንነት የሚሠራ ሙያ ሆኖ መሆን አለበት፡፡ ይህ አባባል በሁለት መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡
በአንድ በኩል ሰዎች መብታቸውን ባለማወቃቸውና የጥብቅና አገልግሎት በክፍያ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ብቻ መብታቸውን እና ጥቅማቸውን ከሚያጡ ጠበቆች የሕግ አገልግሎትን በነፃ የመስጠት ኅብረተሰባዊ፣ ሞራላዊ እና ሙያዊ ግዴታ ወይም ኃላፊነት መያዝ አለባቸው፡፡ ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎት ለሚፈልግ ሰው ተፈላጊውን አገልግሎት መስጠት ያለባቸው በክፍያ ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ የገንዘብ ክፍያ ወይም በነፃ ሊሆን ይችላል፡፡ አገልግሎት ፈላጊው የገንዘብ አቅም የሌለው ከሆነ አንድ ጠበቃ ለዚሁ ሰው ከክፍያ ነፃ የሆነ አገልግሎት ወይም አነሰኝ ሳይል በመጠነኛ ክፍያ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ሙያዊ እንዲሁም ሞራላዊ ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ መልክ በሚሰጠው አገልግሎት የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ዕውን ሊሆን የሚችለው ጠበቃው የደንበኛውን ጉዳይ በመርታቱ ሳይሆን ደንበኛው በፍትሕ መድረክ ክርክሩንና የበኩሉን መከላከያ በማቅረብ፣ በመደመጥና በመዳኘት ሕገ-መንግሥታዊ እኩል ፍትሕ የማግኘት መብቱ ሊጠቀም በመቻሉ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላውና ሁለተኛው ጉዳይ ጠበቆች በፍርድ ቤትም ሆነ በሌሎች የፍትሕ ተቋማት ፊት ሲቀርቡ ትክክለኛ ወይ ተገቢ ፍትሕን ለማስገኘት እንጂ የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ብቻ በማየት ፍርድ ቤቶችን ወይም የፍትሕ አካላትን ማሳሳት ወይም ፍትሕን ማጓደል ተገቢ አይሆንም፡፡
- Liku Worku By
- Hits: 23183
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ብዙውን ጊዜ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ክስ ያቀረበ ከሳሽ እና መልስ የሚሰጥ ተከሳሽ በክሳቸውና በመልሳቸው እንዲሁም በክርክራቸው ላይ ወጪና ኪሳራ የማቅረብ መብት ይጠበቅልኝ፣ ፍርድ ቤቱ ወጪና ኪሳራ በቁርጥ እንዲከፈለኝ ይዘዝልኝ ሲሉ፤ ፍርድ ቤቶች በበኩላቸው እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ወይም በክርክሩ የተረታው ወገን ለረታው ወገን እንዲከፍል በሚል ትዕዛዝ ሲሰጡ መመልከቱ የተለመደ ነው፡፡ ለመሆኑ ወጪና ኪሳራ ምንድን ነው? የወጪና ኪሳራ ዓላማውስ ምንድን ነው? ወጪና ኪሳራ ሊታሰብ የሚገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ሕጉ ከወጪና ኪሳራ አንፃር ለፍርድ ቤቶች የሰጠው ሥልጣን ምንድን ነው? ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በተግባር ያለው አሠራር ምን ይመስላል? የሚሉና ሌሎች ነጥቦችን በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡
ወጪና ኪሳራ ምንድን ነው?
ወጪና ኪሳራ ማለት በፍርድ ቤት ክርክር የሚያደርጉ ተከራካሪ ወገኖች ከክርክሩ ጋር በተያያዘ የሚያወጧቸው የተለያዩ ወጪዎች እና በክርክሩ ምክንያት የሚደርስባቸው ኪሳራ ማለት ሲሆን ተከራካሪ ወገኖች ከሳሹ ክስ ያቀረበው በተከሳሹ ምክንያት በመሆኑ በአንፃሩም ተከሳሹ ወደ ክስ የገባው በከሳሽ ምክንያት መሆኑን በማንሳት በክርክር ምክንያት ያወጡት ወጪና ኪሳራ በሌላኛው ተከራካሪ እንዲሸፈን የሚጠይቁበት አግባብ ነው፡፡ ክርክር በባሕርይው ወጪ የሚያስወጣና ውድ ሲሆን በክርክር ምክንያት የሚወጣ ወጪም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነው፡፡
የወጪና ኪሳራ ዓላማው ምንድን ነው?
የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከአንቀጽ 462 እስከ 466 ድረስ ወጪና ኪሳራ ስለሚጠየቅበትና ፍርድ ቤቶችም ስለሚወስኑበት እንዲሁም ሌሎች የወጪና ኪሳራ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ነጥቦች ተመክተዋል፡፡ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የሕጉ ዓላማም ያለአግባብና ከቅን ልቦና ውጪ የሚቀርቡ ክሶችን መከላከል፤ ክርክር ከሕግ ውጭ የቀረበ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ለክርክሩ ያለአግባብ የተዳረገ ወገን በክርክሩ ምክንያት ያወጣውን ወጪና ኪሳራ ለክርክር የዳረገው ወገን እንዲተካ ማድረግ መሆኑንና ከዚህ ውጪም ዓላማው የተረታውን ወገን መቅጣት አለመሆኑን ከሕጉ መንፈስና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 4 የሰበር መዝገብ ቁጥር 22260 እና በቅፅ 15 የሰበር መዝገብ ቁጥር 91103 ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ ከተሠጡ ውሳኔዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡
ተከራካሪዎች በክርክር ወቅት የሚያወጧቸው ወጪና ኪሳራዎች ምን ምን ናቸው?
የከሳሽ ወጪዎች ምንድን ናቸው?
ከሳሽ በተከሳሽ ላይ የሚያወጣቸውን ወጪዎች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡ -
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 (1) እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ.ም. በወጣው ደንብ መሠረት በክሱ እንደሚጠየቀው የገንዘብ መጠንና እንደጉዳዩ ዓይነት መዝገብ ለማስከፈት የዳኝነት ክፍያ ለፍርድ ቤቱ ለመክፈል የሚወጣ ወጪ፤
- የቴምብር ቀረጥን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 110/1990 አንቀፅ 3 እና 10 በአዋጅ ቁጥር 612/2001 አንቀፅ 14 እንደተሻሻለው ከክሱ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የሠነድ ማስረጃዎች ላይ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ተከፍሎባቸው ምልክት ሊደረግባቸው ስለሚገባ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ለመፈፀም የሚወጣ ወጪ፤
- ከክሱ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ሠነዶች ወደ ፍርድ ቤቱ የሥራ ቋንቋ መተርጎም ካለባቸው ፍቃድ ባላቸው የትርጉም ቤቶች ለማስተርጎሚያ የሚወጣ ወጪ፤
- ክስን በኮምፒውተር ማስፃፊያ፣ የኮፒ ማድረጊያ፣ በክርክር ሂደት ላይ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ መወሰድ ያለባቸው ሠነዶችን፣ ትዕዛዝና ውሳኔዎች አስገልብጦ ለመውሰድ የሚወጣ ወጪ፤
- እንደከሳሹ አድራሻና ሁኔታ ጉዳዩ ሊታይ በሚቀጠርባቸው ቀናት ከፍርድ ቤቱ እስከ ከሳሽ መኖሪያ ቤት ድረስ ለመጓጓዣ እና ተያያዥ ሁኔታዎች የሚወጣ ወጪ፤
- እንደከሳሹ ፍላጎትና ሁኔታ ጉዳዩን የምከታተለው በሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) አማካኝነት ነው ካለ ለጠበቃ አበል የሚወጣ ወጪ፤
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 112 መሠረት ምስክሮችና የሙያ ምስክሮች ወጪ ለመጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም አበል የሚከፈል ክፍያ ፍርድ ቤቱ በሚያዘው መሠረት የሚወጣ ወጪ፤
- ለተከሳሽ መጥሪያ ከማድረስ ጋር በተያያዘ እንደሁኔታው በጋዜጣ ጥሪ የሚደረግ ከሆነ የጋዜጣ ጥሪ ማስደረጊያ የሚወጡ ወጪዎች፤
- ይግባኝ የሚያስብል ነገር ካለ ለይግባኝ መዝገብ ማስከፈቻ እና ተያያዥ ወጪዎች፣ እና
- ሌሎች እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ በክርክር ሂደት ሊወጡ የሚችሉ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡
የተከሳሽ ወጪዎች ምንድን ናቸው?
ተከሳሽ ከከሳሽ ለሚቀርብበት ክስ በሚሠጠው መልስና በሚያደርገው ክርክር ላይ የሚያወጣቸው ወጪዎች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡ -
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 (2)፣ 236 እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ.ም. በወጣው ደንብ መሠረት ተከሳሽ በከሳሹ ላይ የማቻቻያ የተከሳሽ ከሳ ክስ የሚያቀርብ ከሆነ በተከሰሽ ክሱ እንደሚጠየቀው የገንዘብ መጠንና እንደጉዳዩ ዓይነት የዳኝነት ክፍያ ለፍርድ ቤቱ ለመክፈል የሚወጣ ወጪ፤
- የቴምብር ቀረጥን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 110/1990 አንቀፅ 3 እና 10 በአዋጅ ቁጥር 612/2001 አንቀፅ 14 እንደተሻሻለው ከመልስ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የሠነድ ማስረጃዎች ላይ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ተከፍሎባቸው ምልክት ሊደረግባቸው ስለሚገባ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ለመፈፀም የሚወጣ ወጪ፤
- ከመልስ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ሠነዶች ወደ ፍርድ ቤቱ የሥራ ቋንቋ መተርጎም ካለባቸው ፍቃድ ባላቸው የትርጉም ቤቶች ለማስተርጎሚያ የሚወጣ ወጪ፤
- መልስን በኮምፒውተር ማስፃፊያ፣ የኮፒ ማድረጊያ፣ በክርክር ሂደት ላይ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ መወሰድ ያለባቸው ሠነዶችን፣ ትዕዛዝና ውሳኔዎች አስገልብጦ ለመውሰድ የሚወጣ ወጪ፤
- እንደተከሳሹ አድራሻና ሁኔታ ጉዳዩ ሊታይ በሚቀጠርባቸው ቀናት ከፍርድ ቤቱ እስከ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ድረስ ለመጓጓዣ እና ተያያዥ ሁኔታዎች የሚወጣ ወጪ፤
- እንደተከሳሹ ፍላጎትና ሁኔታ ጉዳዩን የምከታተለው በሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) አማካኝነት ነው ካለ ለጠበቃ አበል የሚወጣ ወጪ፤
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 112 መሠረት ምስክሮችና የሙያ ምስክሮች ወጪ ለመጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም አበል የሚከፈል ክፍያ ፍርድ ቤቱ በሚያዘው መሠረት የሚወጣ ወጪ፤
- ይግባኝ የሚያስብል ነገር ካለ ለይግባኝ መዝገብ ማስከፈቻ እና ተያያዥ ወጪዎች፣ እና
- ሌሎች እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ በክርክር ሂደት ሊወጡ የሚችሉ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡
ኪሳራ ምንድን ነው?
በክርክር ሂደት ኪሳራ ማለት ተከራካሪዎች ለክርክሩ ከሚያወጡት ወጪ በተለየ መልኩ በክርክሩ ምክንያት ያጡትን ገቢ የሚመላክት ነው፡፡ ብዙ ጊዜም የክርክር ረቺዎች ከረቺው ላይ ኪሳራ ሲጠይቁ አይስተዋልም፡፡
ተከራካሪዎች የሚያወጧቸውን ወጪዎች የሚሸፍነው ማን ነው?
የግራ ቀኙ ክርክር ተደርጎ ፍርድ ቤት አንዱን ረቺ ሌላኛውን ተረቺ አድርጎ ውሳኔ ከሠጠ በኋላ የግራ ቀኙ ያወጧቸውን ወጪዎች በተመለከተ ተረቺው የረቺውን ወጪዎች እንዲሸፍን በሚል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 463 (1) ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲሰጥም ረቺው ያወጣቸውን ወጪዎች በሙሉ የሚያሳይ ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ እና ተረቺው አስተያየት ሰጥቶበት ፍርድ ቤቱ የሚቀበለውን ተቀብሎ የተጋነነውን አስተካክሎ ክፍያ እንዲፈፀም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ በንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ተመልክቷል፡፡
ተረቺ ሁልጊዜ የረቺን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታ አለበት?
በክርክር ሂደት ላይ የተረታ ወገን ሁሉ ሁልጊዜ የረቺውን ወገን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታ የሌለበት መሆኑን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታው የሚመጣው ተረቺው ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ረቺውን ለክርክር የዳረገው ከሆነ ብቻ መሆኑን ሕጉ እና የሰበር ውሳኔዎች ያመለክታሉ፡፡
ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት ምንድን ነው?
የሥነ ሥርዓት ሕጉ እና የሰበር ውሳኔዎቹ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በፍርድ ቤቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ኃላፊነችን ይጥላሉ፡፡ ከኃላፊነቶቹ መካከልም፡ -
- በክርክሩ ላይ አንዱን ረቺ ሌላኛውን ተረቺ አድርገው ከወሰኑ በኋላ ተረቺው ረቺውን ወገን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ረቺውን ለክርክር የዳረገ ስለመሆን አለመሆኑ በጥንቃቄ መመርመር፤
- ወጪና ኪሳራን ሲወስኑ የወጪና ኪሳራውን ልክ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ወጪና ኪሳራው የሚከፈልበትን የኃብት ምንጭ የአከፋፈሉን ሁኔታና ሌላም ተገቢ ሆኖ የሚገኝ ትዕዛዝ በተያያዥነት የመወሰን፤
- ወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብት ከተጠበቀ በኋላ ረቺው የወጪና ኪሳራ ዝርዝር እንዲያቀርብ እንዲሁም ተረቺው በዝርዝሩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥበት የማድረግ፤
- በረቺው የሚቀርበው የወጪና ኪሳራ ዝርዝር ላይ የተጋነነ እና ያልተገባ ብልፅግና ለረቺው ሊያስገኙ የሚችሉ አለመሆናቸውን በጥንቃቄ፣ በምክንያታዊነት እና በተቻለ መጠን በማስረጃ የመመርመር፤
- የወጪና ኪሣራ ዝርዝር ባልቀረበ ጊዜ የኪሳራውን መጠን የተጋነነ እንዳይሆን ክርክሩ የወሰደውን ጊዜ፣ የክርክሩ ውስብስብነትና አስፈላጊውን ዳኝነት ለመከታተል ተገቢ ናቸው የሚላቸውን ወጪዎች አመዛዝኖ ተመጣጣኝ መጠን ያለው ኪሣራ የመወሰን እና ሌሎች ተያያዥ ኃላፊነቶች ይገኙበታል፡፡
ፍርድ ቤቶች ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የሚሰሩበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ፍርድ ቤቶች በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻቻሉ በሚል የሚወስኑበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በብዙ ጉዳዮች ላይ ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ መባሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ተረቺው ረቺውን ወገን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ለክርክር ስላልዳረገው ነው ወይ የሚለው ጥያቄ በእያንዳንዱ መዝገብ ላይ ዝርዝር ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ጥቂት በማይባሉ መዛግብት ላይ ደግሞ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ የሚሉበት አግባብ አሳማኝነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ የሚሉበትንና ተረቺው ረቺውን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ለክርክር አለመዳረጉን በሚገልፅ ሁኔታም ምክንያትም አይጠቅሱም፡፡ ፍርድ ቤቶች ወጪና ኪሳራ ሲወስኑም በሁሉም መዛግብት ላይ በሚያስብል መልኩ የወጪና ኪሳራ መጠኑን ከማመላከት ውጪ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 462 በሚያዘው መሠረት ወጪና ኪሳራው የሚከፈልበትን የሀብት ምንጭ፣ የአከፋፈሉን ሁኔታና ሌላም ተገቢ ሆኖ የሚገኝ ትዕዛዝ በተያያዥነት የሚወስኑበት ሁኔታ የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በረቺ ወገን የሚቀርቡ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር ላይ በብዛት ተጋነዋል በሚል ማሻሻያ የሚደረግበት ሁኔታ ይታያል፡፡
- Abiyou Girma Tamirat By
- Hits: 21776