- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
- EthiopianReporter By
- Hits: 15631
ፍትሕ የማግኘት ፈተና
‹‹ይሄ የማይታመን ነው፡፡ ዛሬ ለስድስተኛ ጊዜ ዳኛው ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሩኝ፡፡ ከጠዋት 3፡00 እስከ 6፡30 ተቀምጬ እጠባበቃለሁ፡፡ የያዝኩት ጉዳይ ሲጣራ ዳኛው ጉዳዩ ውስብስብ ስለሆነ አይተው እንዳልጨረሱ ይነግሩኛል፡፡
የጉዳዮች ብዛትና የዳኞች ቁጥር እንደማይመጣጠን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም ላልተሠራ ነገር ደንበኛዬና ወዳጅ ዘመዶች በዚህ የትራንስፖርት ችግር በሌሊት ከቤት ወጥተውና ሥራ ፈተው እዚህ መቀመጣቸው በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ፍትሕ ለማግኘት እምነት ቋጥረው ቢመጡም፣ በየቀኑ መሠረታዊ የመብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው፡፡››
ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሪፖርተር ዘጋቢ በቅርቡ ለሥራ በሄደበት ወቅት ያገኛቸው ጠበቃ የነገሩት ቅሬታ ነበር፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት ወይም የፍትሕ ተደራሽነት ላይ ቅሬታ ያላቸው ጠበቆች ብቻ አይደሉም፡፡ በሒደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎች፣ ራሳቸው ዳኞችና የማረሚያ ቤት መኮንኖችን ጨምሮ ተገልጋዩ ማኅበረሰብ ፍትሕ የማግኘት መብት አፈጻጸም መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ይገልጻሉ፡፡ የመንግሥት ይፋዊ ሪፖርቶችም ችግሩን ለመቅረፍ የተደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ላይ ቢያተኩሩም፣ ችግሩ አሁንም ጥልቀት እንዳለው ግን ይቀበላሉ፡፡ ነገር ግን የችግሩ ምንጭና ምክንያት ላይ ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ጉዳዮችን አይጠቅሱም፡፡
ይህ መሠረታዊ ልዩነት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በኢትዮጵያ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ II በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት››ን አስመልክቶ ያዘጋጀው የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት፣ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቸርችል ሆቴል በተዘጋጀበት ወቅት በስፋት ተንፀባርቋል፡፡ ጠበቆች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተሳተፉበት በዚህ ውይይት፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ከሚያስፋፉት ይልቅ የሚገድቡት ጉዳዮች የገዘፉ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብት ይዞታ በኢትዮጵያ
በፓናል ውይይቱ ላይ ፍትሕ የማግኘት መብት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ያለውን ገጽታ አስመልክቶ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ቀደም ብሎ ዳኛና አክሽን ፕሮፌሽናል አሶሴሽን ፎር ፒፕል የተሰኘ አገር በቀል ሲቪል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቶ ደበበ ፍትሕ የማግኘት መብትን ዜጎች ወይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሕ ለማግኘት የሚጠይቁበት፣ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ መፍትሔ የሚያገኙበት ሥርዓት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡ ይህ መብት ሦስት አንኳር ክፍሎችን እንደሚያቅፍ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህም ፍትሕ የመጠየቅ ችሎታ፣ የተጠየቀውን ፍትሕ የማግኘት ዕድልና በምን ያህል ጊዜ ፍትሕ ይገኛል የሚሉት ጉዳዮች ናቸው፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብት ሦስት መሠረታዊ ባህርያት እንዳሉትም አቶ ደበበ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው ሰብዓዊ መብት መሆኑ፣ ሌሎችን መብቶች ለማስከበር መሣሪያ ሆኖ ማገልገሉና እንደ በሕግ ፊት እኩል ሆኖ የመታየት መብት ካሉ ተያያዥ መርሆዎች ተነጥሎ ለብቻው የሚቆም አለመሆኑ ናቸው፡፡
አቶ ደበበ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕገ መንግሥቷ ፍትሕ የማግኘት መብትን በአግባቡ መያዛቸውን ያስገነዝባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍትሕ የማግኘት መብት ጋር የተቆራኙ መርሆዎችን መቀበሏን ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህ መርሆዎች መካከልም ቁልፍ የሚባሉት በሕገ መንግሥቱና በሕግ የተሰጠን መብት ለማስከበር መንግሥት የገባው ኃላፊነት፣ ብቃት ያለው፣ በሕግ የተቋቋመ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት በመጠቀም ግልጽና ፍትኃዊ የፍርድ ሒደት ማደራጀት፣ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሕግ ዕርዳታ መስጠትና ተነፃፃሪ በሆነ አቅም ላይ ተከራካሪዎችን ማስቀመጥ (Equality of arms) በኢትዮጵያ ሕጎች ቦታ እንደተሰጣቸው አቶ ደበበ ያስረዳሉ፡፡
በሕጎቹ አማካይነት ኢትዮጵያ እነዚህን መርሆዎች ብትቀበልም፣ አፈጻጸማቸውን ለማሳለጥ ተቋማት ብታደራጅም፣ ሥነ ሥርዓትና አሠራሮችን ብትቀርፅም ፍትሕ የማግኘት መብትን በአግባቡ ለመፈጸም በርካታ ጋሬጣዎች ወይም መሰናክሎች እንዳሉ ግን አቶ ደበበ ይጠቁማሉ፡፡ የፍትሕ ተደራሽነትን ከሚያውኩ ዋና ዋና ጋሬጣዎች መካከል አቶ ደበበ ማኅበራዊና ባህላዊ፣ የሕግና የአስተዳደር፣ በፍትሕ ሒደቱ ውስጥ ያሉ መዋቅራዊ ችግሮችና በቂ የሆነ የሕግ ዕርዳታ ያለመኖርን ይጠቅሳሉ፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖች የበቀል ዕርምጃ ሊወስድብኝ ይችላል ብሎ መፍራት፣ ከማኅበራዊና ከባህላዊ ጋሬጣዎች መካከልም እንደሚመደብም አስገንዝበዋል፡፡ እንደ ምሳሌም በሃይማኖትና በብሔር ልዩነት የተነሳ ዜጎች ፍትሕ ላላገኝ እችላለሁ ብለው ማሰባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ፍትሕ ተቋማት በፍትሕ ሚኒስቴር መሪነት በ2006 ዓ.ም. ያወጡት የጋራ ሪፖርት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ያላቸውን አፈጻጸሞች ይዳስሳል፡፡ በዚህም የሰው ኃይል ብቃትን በማጎልበት፣ የፍትሕ ዘርፍን አመራር ውጤታማነት በማሳደግ፣ የፍትሕ ዘርፍን አሠራር ቅልጥፍና በማሳደግ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማሻሻል፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግና ሥርዓቱን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን በመደገፍ የመጡትን መሠረታዊ ለውጦች ይዘረዝራል፡፡
ይሁንና የፍትሕ ዘርፉ በአመራርም ሆነ በፈጻሚው ዘንድ የለውጥ ሥራውን በመምራትና በማስፈጸም ረገድ ከግንዛቤ ጀምሮ የአስተሳሰብ፣ የክህሎትና የግብዓት ችግሮች በሰፊው እንደሚስተዋሉበትና የሰው ኃይል እጥረትና ፍልሰት የተቋማቱ የወል ችግር እንደሆነ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያም ሆነ የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በሚፈለገው መንገድ ተፈጻሚ እንዳልሆነም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ቀላል የማይባል ባለሙያና አመራር በሙስና ተግባር ተሠማርቶ የሚገኝ መሆኑንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር እነዚህን ችግሮች ከሞላ ጎደል የተቀበለ ሲሆን፣ ፍትሕ የማግኘት መብትን ከማረጋገጥ አኳያ የሚከናወኑ ተግባራትን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም ዕቅዶች በዋነኛነት መርሐ ግብሩ ከለያቸው ችግሮችና ተግዳሮቶች የተነሱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች በበቂ ሁኔታ የተደራጁ ባለመሆኑ የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት አጥጋቢ አለመሆኑ፣ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች የሚሠራጩበት ውጤታማ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤቶች በወረዳ ደረጃ ያልተቋቋሙ መሆኑና በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ደረጃም በበቂ ሁኔታ የማይገኙ መሆኑ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ የሚከናወን አለመሆኑና የኅብረተሰቡን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመገናኛ ብዙኃንንና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በሰፊው አለመሥራቱ፣ ከተጠቀሱት ችግሮችና ተግዳሮቶች መካከል ይገኛሉ፡፡
መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ጥናቶች እንደሚያከናውን፣ ተጨማሪ ምድብ ችሎቶችን እንደሚከፍት፣ ተጨማሪ አካላት እንደሚያቋቁም፣ አቅም ለማሳደግ ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ፣ የተከላካይ ጠበቆች ተጨማሪ ቅጥር እንደሚያከናውን፣ አዳዲስና ነባር ሕጎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይሆኑ ዘንድ የሽያጭ ጣቢያዎች እንዲስፋፉ እንደሚያደርግ፣ ሕጎችን ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የመተርጎም፣ የማጠናከርና የማሠራጨት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚደረግ የችሎት ሥርዓት (e-litigation) በሁሉም ክልሎች ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲስፋፋ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን የሚያቀናጅ ብሔራዊ የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚያደርግና አለመግባባቶችን በሕግ የሚፈታና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት ያለው ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚያከናውን ዘርዝሯል፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ ባለፉት ወራት አብዛኛውን ዕቅድ ለመፈጸም መንግሥት መንቀሳቀሱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የተከናወኑት ተግባራት ያለውን ችግር ለመቅረፍ በቂ አለመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ቀሪ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ፍትኃዊ ሕግ የማግኘት መብት
በፓናል ውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው ፍትሕ የማግኘት መብት አፈጻጸም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ፊሊፖስ አይናለም ጠበቃና የሕግ አማካሪ እንዲሁም አስተማሪ ናቸው፡፡ አቶ ፊሊፖስ ፍትሕ የማግኘት መብት ጥሩ ወይም ፍትኃዊ ሕግ የማግኘት መብትን እንደሚጨምር ተከራክረዋል፡፡
አቶ ፊሊፖስ ፍትኃዊ ሕግ ፍትሕ ለመስጠት ተስማሚ የሆነ ሕግ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ መለያ ባህርያቱን በተመለከተ ሲያብራሩም ለሞራል የሚስማማ፣ ተፈጻሚነት ያለው፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ዘለቄታዊነት ያለው፣ ለወንጀል ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣትን የሚደነግግ፣ እኩልነትን ያረጋገጠና ወንጀል መሆን የማይገባውን በወንጀልነት የማይፈርጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማስከበር መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው የሚጠቅሱት አቶ ፊሊፖስ፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሊያስከብሩት የሚገባውን መብት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ራሳቸው ሲጥሱት እንደሚስተዋልም አመልክተዋል፡፡ ይህ ችግር በሕግ አስተርጓሚውና አስፈጻሚው አካል ጭምር የሚታይ ችግር ቢሆንም፣ አሳሳቢ የሆነው ችግር ግን በሕግ አውጪው በኩል የሚወጡና ለሕግ አስፈጻሚው ሰፊ ነፃነትን የሚሰጥበት አሠራር እንደሆነ አቶ ፊሊፖስ ያስገነዝባሉ፡፡ ሕግ አስፈጻሚው እነዚህን ክፍተቶች ተጠቅሞ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚጥሱ ደንቦችንና መመርያዎችን ማውጣቱንም ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
አቶ ፊሊፖስ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ካሏቸው አዋጆች መካከል አንዱ በባንክ በመያዣ የተያዙ ንብረቶችን የሐራጅ ሽያጭ የሚደነግገው አዋጅ ነው፡፡ ባንኮች በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን ባይወጡ፣ ፍርድ ቤቶች ጣልቃ እንዳይገቡ መከልከላቸው ፍትሕ የማግኘት መብትን እንደሚያጣብብም አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የከተማ ቦታ ይዞታ አዋጅ ለሕዝብ ጥቅም ንብረቱ የተወሰደበት ሰው ይግባኝ ሊጠይቅ የሚችለው በካሣ ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑ፣ ፍትሕ ከማግኘት መብት ጋር የሚጋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የተባረረ ተከራይ ፍርድ ቤት ሄዶ እንዳይከራከር መከልከሉ ፍትሕ የማግኘት መብትን ከመፃረሩም በላይ ሙስና እንዲበራከት ማድረጉን አቶ ፊሊፖስ አስረድተዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 639/2001 ተጠቅሞ ሕግ አውጪው አስቀድሞ የተወሰነ የሕግ ተርጓሚውን ውሳኔ በሕግ መሻሩም ፍትሕ ከማግኘት መብት መርሆዎች ጋር የሚቃረን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ፊሊፖስ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅና የግብር ሕግጋቶች እንዲሁ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ ጫና እንደሚፈጥሩ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔዎች እንደ ሕግ መቆጠራቸውን በመጥቀስ የችሎቱ አንዳንድ ውሳኔዎች ፍትሕ የማግኘት መብት ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑም አሳይተዋል፡፡
ዶ/ር አደም ካሴ በጀርመን ሃይድልበርግ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የማክስ ፕላንክ ፋውንዴሽን ዓለም አቀፍ ሰላምና የሕግ የበላይነት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር አደም እንደ አቶ ፊሊፖስ ሁሉ ፍትሕ የማግኘት መብት ከፍርድ ቤቶች ባሻገር ከአስተዳደራዊ ተቋማት ውሳኔ አሰጣጥና ሕግ አወጣጥ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ውሳኔዎችና መመርያዎች በአብዛኛው በመርህ ያልተደገፉና ከሥርዓት ይልቅ በተቋማዊ ባህል እንደሚመሩም አመልክተዋል፡፡ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቢኖር የአስተዳደራዊ ሕጎች አወጣጥና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተገማችነትና ሥርዓትን ሊፈጥር ይችል እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ሕግ ለማውጣት በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ በ1996 ዓ.ም. የተዘጋጀው ረቂቅ አልፀደቀም፡፡
ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ
አቶ ፈቃዱ ደምሌ በፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡ አቶ ፈቃዱ ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሠራው ሥራ በሕግ ከተሰጠው ሌሎች ተልዕኮዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥትን በሕግ ጉዳይ የማማከር፣ የሕግ ጥናት የማድረግ፣ ሕግ የማርቀቅ፣ ሕግን የማስረጽ፣ ወንጀል የሚቀንስበትን ስልት የመንደፍና የመከላከል ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጠበቆችን በተመለከተ ፈቃድ የመስጠት፣ የማደስ፣ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆችን ጉዳይ የመስጠት ሥልጣን ሌሎች ኃላፊነቶችን ለመወጣት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ መመርያዎችን ማውጣቱን ያስታወሱት አቶ ፈቃዱ፣ በኢትዮጵያ ጠበቆች በገዛ ፈቃዳቸው በሕግ የተጣለባቸውን በዓመት ለ50 ሰዓታት ነፃ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸውን እንደማይወጡ አመልክተዋል፡፡ ጉዳዮችን ወስደው አቅም የሌላቸውን ዜጎች ለመርዳት ሰበብ እንደሚደረድሩ፣ ከወሰዱም በኋላ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደማይከታተሉ ወቅሰዋል፡፡
ጠበቆች በተናጠል ከሚያቀርቡት ነፃ የሕግ አገልግሎት በተጨማሪ የሙያ ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሥር የተቋቋሙ የሕግ ትምህርት ቤቶች ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን አቋቁመው አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ አገልግሎቶቹን ለማቀናጀት በብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብሩ በታቀደው መሠረት ስትራቴጂ ለማውጣት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን አቶ ይበቃል አስታውቀዋል፡፡
ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማሻሻል መንግሥት በርካታ ሥራዎችንና ጥረቶችን እያከናወነ ቢሆንም፣ ጉድለቶች ይበልጥ ገዝፈው እንደሚታዩ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ፊሊፖስ ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት በአጠቃላይ ፈተና ላይ ነው፡፡ ፈተናውን ሙሉ በሙሉ አላለፈም፤›› ብለዋል፡፡ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሁሉም ቢስማማም፣ ፍትሕ የማግኘት መብት መሠረታዊ ችግሮች ላይ ስምምነት አለመኖሩ ችግሩ በቅርቡ ሊፈታ እንደማይችል ይጠቁማል፡፡
በአላስፈላጊ ቀጠሮዎች የተማረረው ጠበቃ ግን አንዳንድ ችግሮች በመጠነኛ ሥራዎች ሊፈታ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ‹‹በሞባይል መልዕክት፣ በስልክ ወይም በኢንተርኔት ጉዳዩ እንደማይታይ ቀድሞ ቢነገርና ባለጉዳዩ ወጪውን ቢሸፍን በጥቂት ወጪ ከድካም፣ ከገንዘብ ኪሳራና ከጊዜ ብክነት መገላገል ይቻል ነበር፤›› ሲልም ይደመድማል፡፡ አቶ ደበበ የኢትዮጵያ የፍርድ ሒደት ‹‹ሥርዓት የማብዛት ሁኔታ (Formalism) ያበዛል፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋራጭ መንገዶች ከክብሬ ጋር አይመጥንም ብሎ ይሆን ፍርድ ቤቱ ያን ሁሉ ሰዓት ቁጭ ላሉ ሰዎች በምሳ ሰዓት ዛሬ ጉዳያችሁ አይታይም የሚለው?