- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ሰላም የአቢሲኒያ ሎው ድረገጽ ተከታታዮች፤ እንዴት ናችሁ!
ከብዙ ድካምና ሀሳብ በኋላ የአቢሲኒያ ሎው አፕ አጠናቅቀን ዛሬ ገበያ ላይ አውለናል፡፡ አቢሲኒያ ሎው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሕግ መረጃ ክፍተት ለመሙላት ባለፉት 6 ዓመታት ለተጠቃሚዎች ሕግ ነክ መረጃዎችን በኢንተርኔት ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የሕግ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ መሠረታዊ ችግሮች ከሆኑት መካከል የኢንተርኔት አገልግሎት ይገኝበታል፡፡ በሀገራችን በአንድ በኩል የኢንተርኔት ስርጭት ገና እያደገ ያለ በመሆኑ ብዙ ተጠቃሚዎች መረጃውን የማያገኙ ሲሆን በሌላ በኩል የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው ቦታዎች የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ወጪ ከፍተኛ መሆን እና የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ዝቅተኛ መሆን ሕጎችን፣ የሰበር ውሳኔዎችን እንዲሁም ሕግ ነክ መረጃዎችን በቀላሉ ለማዳረስ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
እኛም ይህንን በመገንዘብ ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ሕጎችንና የሰበር ውሳኔዎችን የያዘ በፍላሽ ዲስክ ያለ ኢንተርኔት የሚሠራ አፕሊኬሽን ሠርተናል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ይህንን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ እና ፍላሽ ዲስኩ በፍጥነትና በጥራት እንዲሠራ ብዙ የደከምን ሲሆን ቤትኛውም ስፍራ ሆነው የፈለጉትን ሕግ፣ የሕጉን ሁኔታ ማለትም በሥራ ላይ ያለ ይሁን ይሻሻል ወይም ይሻር ወይም የትኛውን የሰበር ውሳኔ በተከራካሪ ወገን፣ በመዝገብ ቁጥር፣ ወይም ውሳኔ በተሰጠበት የሕግ አንቀጽ በፍጥነት ከፍላሽዎ ወይም በእጅዎ ከሚገኘው ሞባይል ማግኘት ይችላሉ፡፡
አፑ የተሠራው በራሱ በአቢሲኒያ ሎው ፍላሽ ዲስክ ነው፡፡ የሚፈልጉትን ሕግ እና የሰበር ውሳኔ ከሰከንድ በታች ያገኙታል፤ አዲስ ሕግ ሲወጣ ወይም አዲስ የሰበር ውሳኔ ሲለቀቅ ፈላሹን ከኢንተርኔት ጋር በማገናኘት አብዴት ማድረግ ይችላሉ፡፡
1. የሚፈልጉትን ማናቸውንም ሕግ ወይም የሰበር ውሳኔ መፈለጊያ ውስጥ በተየባችሁ (ታይፕ ባደረጋችሁ) በአንድ ሰከንድ ውስጥ ያገኛሉ፤
2. የአንድን ሕግ ሁኔታ ማለትም ይሻር፣ ይሻሻል ወይም ተፈፃሚ ይሁን በአንድ ሰከንድ ጊዜ ውስጥ ያገኛሉ፤
3. የሰበር ውሳኔዎችን በመዝገብ ቁጥራቸው ወይም በተከራካሪ ወገኖች ስም ብቻ ሳይሆን በክርክሩ ወይም ውሳኔው ውስጥ በተጠቀሰው አዋጅ ወይም ሕግ አንቀጽ ፈልገው ማግኘት ይችላሉ፤
4. ከላይ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ያለ ኢንተርኔት ኮኔክሽን በፍላሽ ዲስክ ላይ በየትኛውም ቦታ ማግኘት ይችላሉ፤
5. አዲስ ሕግ ሲወጣ ወይም አዲስ የሰበር ውሳኔ ሲካተት ፍላሹን ከኢንተርኔት ጋር በማገናኘት አፕዴት ማድረግ ይችላሉ፡፡
የዚህ አገልግሎት ዋጋ 900 ብር ነው፡፡ ለበለጠ በ0912168579 ይደውሉ
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 17257
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ማስታወቂያ
ፍትሕ ሚኒስቴር ለፌዴራል የማናቸውም ፍርድ ቤት የጥብቅና ፈቃድ መግቢያ ፈተና ለመቀመጥ ከዚህ በታች የተመለከተውን መስፈርት የሚያሟሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆኑ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ይገልጻል፡፡
1. በሕግ እውቅና ካገኘ የትምህርት ተቋም በሕግ ዲግሪ የተመረቀ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ሕጎች የሚያውቅና በሙያው ቢያንስ አምስት ዓመት የሥራ ልምድ ያለው ለፍትሕ ሥራ አካሄድ መልካም የሥነ ምግባር ያለውና ማቅረብ የሚችል፣
2. ምግባረ ብልሹነት በሚያመለክት ወንጀል ተከሶ ያልተቀጣ፣ የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃ ኦርጅናል እና ፎቶ ኮፒ፣ የሥራ ግብር የተከፈለበት የሥራ ልምድ፣ የቀበሌ መታወቂያ ፎቶ ኮፒ እንዲሁም የመመዝገቢያ 200.00/ሁለት መቶ ብር/
የመመዝገቢያ ቀን ከህዳር 6 ቀን እስከ ህዳር 16 ቀን 2008 መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የመመዝገቢያ ቦታ ፍትሕ ሚኒስቴር 2ኛ ፎቅ የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ቢሮ ቁጥር 205 ነው፡፡
መልካም ዕድል!
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 10211
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
“በሕግ አምላክ” ካለ ሃገሬው ውልክፍ የለም፡፡ ሕግ የማህበረሰብ የውል ገመዱ ነው፡፡ ሕግ የአንድ ሃገር ባህል፣ ልማድ፣ የኑሮ ዘይቤ ካስማና ባላ ነው፡፡ ሕግ ያለ ሰው ሰው ያለ ሕግ ምሉዕነት የለውም፡፡ ሕግ ፈራጅ ነው በዳዩን ይቀጣል፤ ተበዳዩን ይክሳል፡፡ ሕግ አድራጊ ፈጣሪ ነው ይሾማል፤ ይሽራል፡፡ ሕግ ለጋስም ንፉግም ነው ይሰጣል፤ ይነሳል፡፡ ሕግ የእግር ብረት ሆኖ እግር ከወረች ያስራል፤ ሕግ ቁልፍ ሆኖ ይፈታል፡፡ ሕግ መንገድ ነው ያገናኛል፤ ያለያያል፡፡
የአንድ ማህበረሰብ አደገኛነት ለሕግ በሚሰጠው ቦታ ይለካል፡፡ ፈሪሃ ሕግ ያለው ሰው በሕግ አምላክ ለሚለው ምልጃ ተገዥ ነው፡፡ በሕግ አምላክ እና የዳኛ ያለህ መንትዮች ናቸው፡፡ ሃገራቸውም በሚያከብራቸው ነው፡፡ ውልደታቸው በአንድ ቢሆንም በሕግ አምላክ ከዳኛ ያለህ ይቀድማል፡፡ ሁሉም ቃል ነበር፤ ሕግ ቃል ዳኛ ደግሞ ስጋ ነው፡፡ ሕግ ያለ ዳኛ፣ ዳኛ ያለ ሕግ ዱዳ ናቸው፡፡ ቃሉ ይነገር ዘንድ አንደበት ግድ ይላል፡፡ የሕጉን ቃል የዳኛው አንደበት ይናገረዋል፡፡ ሃገሬው “በሕግ አምላክ፣ ተዳኘኝ” ሲሉት በጄ ያላለውን ዳኛ ፊት ይገትረዋል፡፡ ያኔም ቃሉ ይነገራል፡፡
ዳኛ ሕግን በመተላለፍ በታሰረው ሰው ፣ በከሳሽና ተከሳሽ መሃከል ያለውን ነገር መርምሮ የሚበይን የሚፈርድ ወይም ተዳኝ ቁም ሲሉት አልዳኝም ያለውን ሰው በግድ አቁሞ በርሰት በጉልበት በሚጣሉ ሰዎች መሃከል ለሚገባው የሚፈርድ ነው፡፡ የመዳኘት ስራ ለዳኛ የተሰጠ ነው፡፡ ያኔ ዳኛው ከስሜቱ ይፋታል፡፡ ቃሉን ለመተርጎም ሰውነቱን ይረሳል፡፡ ቀልቡን ለህሊናው አንደበቱን ለህጉ ቃል ያስገዛል፡፡ በፍርድ ሥራ ዳኛው የወል ነው፡፡
ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ዳኛ የወል ዳኛ” የሚለውን የወል ምሰሶ የመሃል እንደሚባል፣ ምሰሶ በግድግዳና በግድግዳ መሃል እንደሚሆን ዳኛም ባዕድና ዘመድን ሳይለይ ለሁሉም ስለሆነ በበደለው ላይ ፈርዶ የሚቀጣ ለተበደለው የበደሉትን ነገር ዐይቶ የሚያስክስ ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ለዚህ ነው በፍርድ ሥራ ዳኛው ዙሪያውን በእኩል እንደተወጠረ ብራና ሊሆን ይገባዋል የሚባለው፡፡
“በሕግ አምላክ! በሕግ” በተባለ ማህበረሰባዊ ግንብ የታነፀ የሕዝብ ሥነ ልቦና ዳኛ የወል ዳኛ ልክ በግድግዳ መሃከል እንዳለ ምሰሶ ሚዛናዊ ሆኖ መቆም ካቃተው ግንቡ ፈራሽ ነው፡፡ ማህበረሰባዊ የሆነው ግንብ መፍረሱ ብቻ አይደለም አደጋው ዋና ጉዳቱ ፍርስራሹ የሚያዳፍናቸው እሴቶች ተመልሰው ለመገንባት የሚያዳግቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሕግ የማህበረሰብ ውል መጠበቂያ እንደመሆኑ የሕጉ አፎች በአግባቡ ካልተከፈቱ ውሉ ይፈርሳል፡፡ አንዱ የአንዱን ፍላጎት አክብሮ መንቀሳቀስ፣ የተፈቀደውን እያደረጉ የተከለከለውን መጠየፍ የውሉ አካል ነው፡፡ ውሉ ከፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ጨዋታው ፈረሰ ይሆናል፡፡ ሥርዓት ዓልበኝነት በመንገስ የነበረውን አዎንታዊ እሴት ያጠፈዋል፡፡ የፍትሕ ተገማችነት ለአንድ ማህበረሰብ ብርቱ ጉዳዩ ነው፡፡ ተገማችነቱም በባላደራው የሕግ ተርጓሚ አካል ጥንካሬ ይወሰናል፡፡ ተርጓሚው እጅ መንሻ ለሚያቀርቡና እና ኃይሉን ለተቆጣጠረው ወገን የሚያሸረግድ ከሆነ ተገማች ፍትሕ ሊኖር አይችልም፡፡
ማህበረሰቡ በሕግ አምላክ በሚለው ምልጃ ፀንቶ እንዲኖር የሕግ ተርጓሚው ወይም ዳኞች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ዳኛ ሚዛኑን ከሳተ ውሉን ያቆመው አካል ያዝናል፡፡ ዳኛ ትክክል የሕጉን ቃል እንደወረደ እየተረጎመ እንኳን ማህበረሰቡ ጥያቄ ከማንሳት ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተካራካሪው ላይ ለሕጉ አፍ ሆኖ የፈረደው ዳኛ ሕግ ፈረደበኝ ከማለት ዳኛ ፈረደብኝ የሚባልበት ጊዜ የትየሌሌ ነው፡፡ ፍርድ የሚያስደስተው ወገን ያለውን ያህል የሚያሳዝነው እልፍ ነው፡፡ በዳኝነት ያለው ጣጣ ለጉድ ነው፡፡
በድሮ ጊዜ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚነገር እና እውቁ ከበደ ሚካኤል የፃፈውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ባለእጅ ነበር፡፡ ባለእጁ የሃገሬውን ማረሻ፣ ማጭድ፣ መጥረቢያ፣ቢለዋና ሌሎች መሳሪዎችን እየሰራ እሱም በሙያው ሰውም በገንዘቡ ጥቅም እየተለዋወጡ ሲኖሩ ባለእጁ በነፍስ ግድያ ተከሶ ዳኛ ፊት ይቀርብና ይሙት በቃ ይፈረድበታል፡፡ ሃገሬውም ፍርዱን ሲሰማ ለስራ የሚያገለግል መሳሪያ እየሰራ ቀጥ አድርጎ የያዘን ሰው ይሙት ከተባለ እኛ ምን ተስፋ ይኖረናል? ማንስ የምንገለገልበት መሳሪያ ይሰራልናል? በማለት አቤት አሉ፡፡ አቤቱታውን የተቀበለው አገረ ገዡ ነፍስ የገደለ ሰው የግድ መቀጣት አለበት፡፡ ይህም የማይሻር ፍርድ ነው በማለት ሲመልሳቸው ሃገሬው እንግዲህ ፍርዱ የማይሻር ከሆነማ በእኛው ወረዳ ሁለት ሸማኔዎች አሉ፡፡ ለእኛ አንድ ሸማኔና አንድ ቀጥቃጭ በቂያችን ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥቃጩ ፋንታ ከሁለቱ ሸማኔዎች ዕጣ አውጥታችሁ የወጣበትን አንደኛውን ግደሉት እንጂ ቀጥቃጩ ምንም ቢሆን አይገደልም ብለው ዳኛውን አፋጠው ያዙት እየተባለ ይነገራል፡፡ ይሄኔ ነው ዳኛ የወልነቱን በማስመስከር ዙሪያን እንደተወጠረ ብራና መሆንን የሚጠይቀው፡፡ ዳኛው የወል ነው የሚባለው ለብዙሃኑ ጫጫታ ብቻ ጆሮ በመስጠትና ለባለጊዜዎች አፋሽ አጎንባሽ በመሆን አይደለም፡፡ የወል ዳኛ ለመሆን የተጎጅም፣ የሸማኔው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ይህንን የመሰለ የጥቅም ግጭት ነው ፈተናው፡፡ ፈተናው የሚታለፈው ስሜትን በማድመጥ፣ ጉልበትና ገንዘብ ላለው አካል ተገዥ ሎሌ በመሆን አይደለም፡፡ መንገዱ የህሊናን ብርሃን ወገግ አድርጎ ድቅድቁን የአሻጥረኝነት መንፈስ ወደ ግራ በመተው ቀኙን የህጉን ቃል መከተል መተርጎም እንጂ፡፡ ዳኝነት እንዲህ ካልሆነ “የወል ዳኛን” “ውሃ ወራጅ ዳኛ” ይተካዋል፡፡ ጊዜውም ለጭንቅ ቀን የሚሆን የወል ዳኛ ሆይ ሃገርህ ወዴት ነው? የሚባልበት የፍለጋ ዘመን ይመስላል፡፡
“ውኃ ወራጅ ዳኛ” ማንኛውም ሰው ውኃ ቀጂን፣ አልፎ ሂያጅን በግብታዊነት የሚዳኝ የጊዜ ዳኛ ነው (ከሳቴ ብርሃን የአመርኛ መዝገበ ቃላት)፡፡
- Fekadu Andargie Mekonnen By
- Hits: 10509
- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
በሕግ ሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን እና ፍትሕ ተቋማት ሥራቸውን ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም ከአዳዲስ የሕግ መረጃዎች ጋር ለማስተዋወቅ በአቢሲኒያ ሎው ድረገጽ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ጠቃሚ የሆኑ የሕግ ጽሑፎች የሚቀርቡበት የሕግ ጡመራ ክፍል ይገኝበታል፡፡
የእኛን ተጠቃሚዎች የሕግ ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ጠቃሚ ወይም አስተማሪ እንዲሁም ስለአዲስ ሕግ ወይም የሕግ መረጃ ለተጠቃሚው የሚያስተዋውቁ ጽሑፎችን እንወዳለን፤ በዚህም ምክንያት የሕግ ጸሐፊዎች ጽሑፋቸውን ለብዙዎች እንዲያካፍሉ እንደግፋለን፣ በድረገጻችን እንዲጽፉ እናበረታታለን በደስታም እንቀበላለን፡፡
አቢሲኒያ ሎው በደረገጹ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ ብዙ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት በድረገጹ ለምንጽፋቸው ጽሑፎችም ይሁን በድረገጹ ለምንለቃቸው ልዩ ልዩ መረጃዎች ከሌላው ጊዜ በበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን አስተውለናል፡፡
በመሆኑን ለአቢሲኒያ ሎው የሕግ ጡመራ ክፍል ጽሑፍ ለመጻፍ ከወደዱ የሚከተሉትን ነጥቦች ያስተውሉ፡፡
ለአቢሲኒያ ሎው መጻፍ የሚችለው ማን ነው?
በአቢሲኒያ ሎው ደረገጽ ብዙ ተጠቃሚዎች በመመዝገብ የማይጠቅሙ ወይም የማስታወቂያ የሆኑ ጽሑፎችን ብቻ በመጻፍ ዓላማቸው አንድን ድረገጽ ማስተዋወቅ ወይም ወደፈለጉት ሊንክ ተጠቃሚዎችን ማስኬድ ወይም መውሰድ አንደሆነ እናያለን፤ ለዚህ ነው ለአቢሲኒያ ሎው ድረገጽ መጻፍ ያለበት ሰው ላይ ጥንቃቄ የምናደርገው፡፡ በዚህም ምክንያት፡-
በሕግ ዙሪያ ላይ ያልተመሠረቱ ጽሑፎችን አንቀበልም፤ የጽሑፉ ዓላማ አንድን ድረገጽ ማስተዋወቅ ወይም ወደፈለጉት ሊንክ ተጠቃሚዎችን መውሰድ ብቻ ከሆነ ወዲያውኑ ጽሑፎት እናስወግዳለን፡፡
ጸሐፊዎቻችን ወይም ጦማሪያን ስለሚጽፉት ጉዳይ ዕውቀት ያላቸው ወይም ጽሑፎቻቸው ጠቃሚ እንደሆኑ እናምናለን፡፡ ነገር ግን የሕግ ትንታኔ የሌለው ወይም የሕግ ነጥቦች የሌሉት ጽሑፍ ለማስተናገድ ይከብደናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ልዩ ሁኔታ (exceptions) ሊኖረን ይችላል ነገር ግን በዚህ ጉዳይ እምነታችን ጠበቅ ያለ ነው፡፡
በአቢሲኒያ ሎው ምን ምን መጻፍ እችላለሁ?
በአቢሲኒያ ሎው በፈለጉት የሕግ ርዕሰ ጉዳይ ሊጽፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለአቢሲኒያ ሎው ከመጻፍዎ በፊት በመጀመሪያ በድረገጹ ምን ምን ዓይነት ጽሑፎችን እንደምንጽፍ ምን ምን ዓይነት የሕግ ክፍሎች እናዳሉን ይረዱ፤ በተፃፈ እና በተብራራ ጉዳይ ላይ ደግመው አለመጻፍዎን ያረጋግጡ፡፡
ጽሑፎትን በመጀመሪያ በኢሜል ለእኛ ቢልኩልን ይመረጣል፤ በኢሜል ሲልኩሉን በወርድ ፋይል ቢሆን መልካም ነው፡፡
መደረግ ያለበትና መደረግ የሌለበት
መደረግ ያለበት
ሲጽፉ ለተጠቃሚዎች ለአንባብያን ይጻፉ፤ አንባብያን ለመረጃ ወይም ለዕውቀት ጽሑፎችን ያያሉ በመሆኑም ጽሑፎት ጠቃሚ የሕግ መረጃ ወይም ዕወቀት ያለው መሆኑን ያረጋግጡ፤
ጽሑፎዎን ከስህተት የጸደ ለማድረግ የበኩሉዎን ጥረት ያድርጉ፤
ጽሑፍዎን ከ25 ገጽ ባያስበልጡ ይመረጣል፤
ጽሑፍዎ የራስዎ መሆኑን ያረጋግጡ፤ የሌላ ሰው ሥራ ወይም በሌላ ተቋም የተሠራ አለመሆኑን ያረጋግጡ፤ አስፈላጊ በሆነ ሠዓት ሁሉ ማጣቀሻ ይጠቀሙ የሌሎች ሥራን ያክብሩ፤
ጽሑፎን ለእኛ ከመላክዎ በፊት ደግመው ደጋግመው ያንብቡ፤ በአጋጣሚ የተገኙ የቃላት ግድፈት፣ የዓረፍተነገር አሰካክ ያስተካክሉ፤
መደረግ የሌለበት
ለአቢሲኒያ የሕግ ጡመራ ልዩ ልዩ ጽሑፎን ሲያቀርቡ ጽሑፉዎ፡
የሕግ ትንታኔ ያለው መሆኑን ያረጋግጡ - አቢሲኒያ ሎው የሕግ ትንታኔ የሌላቸው፣ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች አያስተናግድም፡፡
የሚያቀርቡት ጽሑፍ ከሌላ ቦታ የተቀዳ መሆን የለበትም፤ የሰው ሥራ ያለፍቃድ መውሰድ ተጠያቂነት የሚያስከትል ትልቅ ጥፋት መሆኑን ይወቁ፤
በጣም አጭር ጽሑፍ አይፃፉ፤ ከ500 ቃላት ያነሱ ጽሑፎችን አቢሲኒያ ሎው አያስተናግድም፡፡
ስም ማጥፋት ብቻ ያለበትን ጽሑፍ አይጻፉ፤
ጽሑፌን እንዴት በአቢሲኒያ ሎው የሕግ ጡመራ ክፍል (blog Category) ለመጫን (post) እችላለሁ?
በአቢሲኒያ ድረገጽ የሕግ ጡመራ ክፍል (blog Category) ጽሑፎዎን ለመጫን የሚከተሉትን ይከተሉ፡፡
ደረጃ አንድ፡ ስለርሶ ይንገሩን፤ ሙሉ ስምዎ፣ ፎቶዎን እና ስለርስዎ አጭር ነገር በ
ደረጃ ሁለት፡ እኛ account ፈጥረን እንልክልዎታለን፤ ጽሑፎንም እንለጥፋለን፡፡
ጽሑፎን ከላኩልን በኋላ ምላሽዎን በ24 ሠዓት ውስጥ እንሰጣለን፡፡
ጥያቄና አስተያየት ካለዎት ይጻፉልን፡፡
ለአቢሲኒያ ሎው ድረገጽ በመጻፍ የኢትዮጵያ የሕግ አቅዋም መሻሻልን ይደግፉ!
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 53074