- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ዳኛ የወል ዳኛ
“በሕግ አምላክ” ካለ ሃገሬው ውልክፍ የለም፡፡ ሕግ የማህበረሰብ የውል ገመዱ ነው፡፡ ሕግ የአንድ ሃገር ባህል፣ ልማድ፣ የኑሮ ዘይቤ ካስማና ባላ ነው፡፡ ሕግ ያለ ሰው ሰው ያለ ሕግ ምሉዕነት የለውም፡፡ ሕግ ፈራጅ ነው በዳዩን ይቀጣል፤ ተበዳዩን ይክሳል፡፡ ሕግ አድራጊ ፈጣሪ ነው ይሾማል፤ ይሽራል፡፡ ሕግ ለጋስም ንፉግም ነው ይሰጣል፤ ይነሳል፡፡ ሕግ የእግር ብረት ሆኖ እግር ከወረች ያስራል፤ ሕግ ቁልፍ ሆኖ ይፈታል፡፡ ሕግ መንገድ ነው ያገናኛል፤ ያለያያል፡፡
የአንድ ማህበረሰብ አደገኛነት ለሕግ በሚሰጠው ቦታ ይለካል፡፡ ፈሪሃ ሕግ ያለው ሰው በሕግ አምላክ ለሚለው ምልጃ ተገዥ ነው፡፡ በሕግ አምላክ እና የዳኛ ያለህ መንትዮች ናቸው፡፡ ሃገራቸውም በሚያከብራቸው ነው፡፡ ውልደታቸው በአንድ ቢሆንም በሕግ አምላክ ከዳኛ ያለህ ይቀድማል፡፡ ሁሉም ቃል ነበር፤ ሕግ ቃል ዳኛ ደግሞ ስጋ ነው፡፡ ሕግ ያለ ዳኛ፣ ዳኛ ያለ ሕግ ዱዳ ናቸው፡፡ ቃሉ ይነገር ዘንድ አንደበት ግድ ይላል፡፡ የሕጉን ቃል የዳኛው አንደበት ይናገረዋል፡፡ ሃገሬው “በሕግ አምላክ፣ ተዳኘኝ” ሲሉት በጄ ያላለውን ዳኛ ፊት ይገትረዋል፡፡ ያኔም ቃሉ ይነገራል፡፡
ዳኛ ሕግን በመተላለፍ በታሰረው ሰው ፣ በከሳሽና ተከሳሽ መሃከል ያለውን ነገር መርምሮ የሚበይን የሚፈርድ ወይም ተዳኝ ቁም ሲሉት አልዳኝም ያለውን ሰው በግድ አቁሞ በርሰት በጉልበት በሚጣሉ ሰዎች መሃከል ለሚገባው የሚፈርድ ነው፡፡ የመዳኘት ስራ ለዳኛ የተሰጠ ነው፡፡ ያኔ ዳኛው ከስሜቱ ይፋታል፡፡ ቃሉን ለመተርጎም ሰውነቱን ይረሳል፡፡ ቀልቡን ለህሊናው አንደበቱን ለህጉ ቃል ያስገዛል፡፡ በፍርድ ሥራ ዳኛው የወል ነው፡፡
ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ዳኛ የወል ዳኛ” የሚለውን የወል ምሰሶ የመሃል እንደሚባል፣ ምሰሶ በግድግዳና በግድግዳ መሃል እንደሚሆን ዳኛም ባዕድና ዘመድን ሳይለይ ለሁሉም ስለሆነ በበደለው ላይ ፈርዶ የሚቀጣ ለተበደለው የበደሉትን ነገር ዐይቶ የሚያስክስ ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ለዚህ ነው በፍርድ ሥራ ዳኛው ዙሪያውን በእኩል እንደተወጠረ ብራና ሊሆን ይገባዋል የሚባለው፡፡
“በሕግ አምላክ! በሕግ” በተባለ ማህበረሰባዊ ግንብ የታነፀ የሕዝብ ሥነ ልቦና ዳኛ የወል ዳኛ ልክ በግድግዳ መሃከል እንዳለ ምሰሶ ሚዛናዊ ሆኖ መቆም ካቃተው ግንቡ ፈራሽ ነው፡፡ ማህበረሰባዊ የሆነው ግንብ መፍረሱ ብቻ አይደለም አደጋው ዋና ጉዳቱ ፍርስራሹ የሚያዳፍናቸው እሴቶች ተመልሰው ለመገንባት የሚያዳግቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሕግ የማህበረሰብ ውል መጠበቂያ እንደመሆኑ የሕጉ አፎች በአግባቡ ካልተከፈቱ ውሉ ይፈርሳል፡፡ አንዱ የአንዱን ፍላጎት አክብሮ መንቀሳቀስ፣ የተፈቀደውን እያደረጉ የተከለከለውን መጠየፍ የውሉ አካል ነው፡፡ ውሉ ከፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ጨዋታው ፈረሰ ይሆናል፡፡ ሥርዓት ዓልበኝነት በመንገስ የነበረውን አዎንታዊ እሴት ያጠፈዋል፡፡ የፍትሕ ተገማችነት ለአንድ ማህበረሰብ ብርቱ ጉዳዩ ነው፡፡ ተገማችነቱም በባላደራው የሕግ ተርጓሚ አካል ጥንካሬ ይወሰናል፡፡ ተርጓሚው እጅ መንሻ ለሚያቀርቡና እና ኃይሉን ለተቆጣጠረው ወገን የሚያሸረግድ ከሆነ ተገማች ፍትሕ ሊኖር አይችልም፡፡
ማህበረሰቡ በሕግ አምላክ በሚለው ምልጃ ፀንቶ እንዲኖር የሕግ ተርጓሚው ወይም ዳኞች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ዳኛ ሚዛኑን ከሳተ ውሉን ያቆመው አካል ያዝናል፡፡ ዳኛ ትክክል የሕጉን ቃል እንደወረደ እየተረጎመ እንኳን ማህበረሰቡ ጥያቄ ከማንሳት ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተካራካሪው ላይ ለሕጉ አፍ ሆኖ የፈረደው ዳኛ ሕግ ፈረደበኝ ከማለት ዳኛ ፈረደብኝ የሚባልበት ጊዜ የትየሌሌ ነው፡፡ ፍርድ የሚያስደስተው ወገን ያለውን ያህል የሚያሳዝነው እልፍ ነው፡፡ በዳኝነት ያለው ጣጣ ለጉድ ነው፡፡
በድሮ ጊዜ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚነገር እና እውቁ ከበደ ሚካኤል የፃፈውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ባለእጅ ነበር፡፡ ባለእጁ የሃገሬውን ማረሻ፣ ማጭድ፣ መጥረቢያ፣ቢለዋና ሌሎች መሳሪዎችን እየሰራ እሱም በሙያው ሰውም በገንዘቡ ጥቅም እየተለዋወጡ ሲኖሩ ባለእጁ በነፍስ ግድያ ተከሶ ዳኛ ፊት ይቀርብና ይሙት በቃ ይፈረድበታል፡፡ ሃገሬውም ፍርዱን ሲሰማ ለስራ የሚያገለግል መሳሪያ እየሰራ ቀጥ አድርጎ የያዘን ሰው ይሙት ከተባለ እኛ ምን ተስፋ ይኖረናል? ማንስ የምንገለገልበት መሳሪያ ይሰራልናል? በማለት አቤት አሉ፡፡ አቤቱታውን የተቀበለው አገረ ገዡ ነፍስ የገደለ ሰው የግድ መቀጣት አለበት፡፡ ይህም የማይሻር ፍርድ ነው በማለት ሲመልሳቸው ሃገሬው እንግዲህ ፍርዱ የማይሻር ከሆነማ በእኛው ወረዳ ሁለት ሸማኔዎች አሉ፡፡ ለእኛ አንድ ሸማኔና አንድ ቀጥቃጭ በቂያችን ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥቃጩ ፋንታ ከሁለቱ ሸማኔዎች ዕጣ አውጥታችሁ የወጣበትን አንደኛውን ግደሉት እንጂ ቀጥቃጩ ምንም ቢሆን አይገደልም ብለው ዳኛውን አፋጠው ያዙት እየተባለ ይነገራል፡፡ ይሄኔ ነው ዳኛ የወልነቱን በማስመስከር ዙሪያን እንደተወጠረ ብራና መሆንን የሚጠይቀው፡፡ ዳኛው የወል ነው የሚባለው ለብዙሃኑ ጫጫታ ብቻ ጆሮ በመስጠትና ለባለጊዜዎች አፋሽ አጎንባሽ በመሆን አይደለም፡፡ የወል ዳኛ ለመሆን የተጎጅም፣ የሸማኔው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ይህንን የመሰለ የጥቅም ግጭት ነው ፈተናው፡፡ ፈተናው የሚታለፈው ስሜትን በማድመጥ፣ ጉልበትና ገንዘብ ላለው አካል ተገዥ ሎሌ በመሆን አይደለም፡፡ መንገዱ የህሊናን ብርሃን ወገግ አድርጎ ድቅድቁን የአሻጥረኝነት መንፈስ ወደ ግራ በመተው ቀኙን የህጉን ቃል መከተል መተርጎም እንጂ፡፡ ዳኝነት እንዲህ ካልሆነ “የወል ዳኛን” “ውሃ ወራጅ ዳኛ” ይተካዋል፡፡ ጊዜውም ለጭንቅ ቀን የሚሆን የወል ዳኛ ሆይ ሃገርህ ወዴት ነው? የሚባልበት የፍለጋ ዘመን ይመስላል፡፡
“ውኃ ወራጅ ዳኛ” ማንኛውም ሰው ውኃ ቀጂን፣ አልፎ ሂያጅን በግብታዊነት የሚዳኝ የጊዜ ዳኛ ነው (ከሳቴ ብርሃን የአመርኛ መዝገበ ቃላት)፡፡