- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት ወይም ውሳኔ ለመወሰን የሚረዱ ቀዳሚ ነገሮች
1. የሕግ ዕውቀት
ሥራንና ባለሙያን ማገናኘት (Specialization) እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሕክምና ሐኪም፣ ለሕንጻና ግንባታ መሐንዲስ እንደሚያስፈልግ ለዳኝነትም የሕግ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰየመው ችሎት ከሚካሔደው ሙግት ወይም ክርክር ጋር የተገናኘ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያለውና ስለጉዳዩ ማብራሪያ እና አስተያየት መስጠት የሚችል መሆን አለበት፡፡
2. የዳኝነት ነፃነት
የዳኝነት ነፃነት ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ የማዕዘን ራስ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ መሠረታዊ ተልዕኮውም በፍርድ ሥራ ወይም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ጥላቻና ፍራቻ፣ ስሜትና ግፊት ቦታ እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው፡፡
ይህም ዳኛው ሕጉን ዐይቶ ክርክሩን ስምቶ በሕጉ መሠረት ውሳኔ እንዲሰጥ ለማስቻል ነው፡፡ ዳኛው በቁንጽል አመለካከት ወይም በዕውቀት እጥረት የሰጠው ፍርድ/ውሳኔ በይግባኝ ተመዝኖ የሚለወጥ ወይም የሚሻሻል ቢሆን የዳኝነት ሥርዐት የሚያጠናክር እንጂ የሚያስነቅፍ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ፍርዱ በግፊት ወይም በስሜት፤ በጥላቻ ወይም በፍራቻ የተሰጠ ሆኖ በይግባኝ ሳይታረም የጸና ሆኖ ቢቀር በሁለት በኩል ለነቀፋ የተጋለጠ ይሆናል፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል ተጽዕኖው ከውስጥም ይምጣ ከውጪ በራሱ ሕገ ወጥ መሆኑ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግም ፍርዱ ወይም ውሳኔው በሕግ መሠረት ያልተሰጠ በመሆኑ ከራሱ አልፎ ሥርዓቱን ጭምር ለሥጋትና ሐሜት በመዳረግ አመኔታውን ስለሚያቃውስበት ነው፡፡ ይህም የዳኝነት ነፃነት የጥበቃ አድማስ ዳኚውንም ተዳኚውንም እንደሚያካትት ያመለክታል፡፡ ሁለቱም ካልተጠበቁ ለአደጋ የሚጋለጠው ዳኛው የሚተረጉመው፣ ተከራካሪው የሚማጸነው ሕግ ነው፡፡ ሕግ ሥርዓት ስለሆነ ለሥጋት ከተጋለጠ አመኔታ ስለሚያጣ ነፀብራቁ ከዚያ አልፎ ኅብረተሰቡን የሚያውክ ይሆናል፡፡
ስለዚህ የዳኝነት ነጻነት በቁንጽል ከተወሰነ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚታይ ሳይሆን ሰፋ ብሎ ከኅብረተሰቡ የፍትሕ አስተዳደር ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው፡፡
3. ነገርን በግልጽ ማየት
ክስን/ክርክርን ወይም ሙግትን በግልጽ መስማት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መብት ነው፡፡ ምስጢራዊነትን ስለሚያስወግድ በተከሳሹ ላይ የተነገረውን ክስ ከሳሹ እንዲያስረዳ ይገፋፋል፤ ተከሳሽም መከላከያውን ያለፍርሃትና ሥጋት ለማቅረብ ያስችለዋል፡፡ ዳኞችም በፍርሃት፣ በሥጋት ወይም በስሜት እንዳይፈርዱ የሕዝብ አስተያየት በታዛቢነት ይመለከታቸዋል፡፡ የግልጽ ችሎት ጽንሰ ሃሳብ እየዳበረና የሕግ ጥበቃ እያገኘም የመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
4. ሥርዓት
ክርክር/ሙግት የጨረባ ድግስ እንዳይሆን ሥርዓት እንዲከተል ማድረግ የተገባ ነገር ነው፡፡ ክስ እንዴት እንደሚቀርብ፣ መልስ እንዴት እንደሚሰጥ፣ ማስረጃ እንዴት እንደሚቀርብና እንዴትም እንደሚመዘን፣ ማን አስቀድሞ እንደሚናገር፣ ማን መልስ እንደሚሰጥ፣ ጥያቄ እንዴት እንደሚቀርብ፣ ወዘተ…ሥርዓት ካልተበጀ እውነትን የያዘው ተጎድቶ አፍ ያለው ረትቶ ሊሔድ ይችላል፡፡
5. ጭብጥ
ጭብጥ የሙግት ልብ ወይም እምብርት ነው፡፡ ጭብጥ ተለይቶ መውጣቱ ለግራ ቀኙና ለዳኛም እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡ ሙግት ለማገዶ እንደሚሰበሰብ ፍልጥ ቢታሰብ ጭብጡ እንደማሠሪው ልጥ ሊመሰል ይችላል፡፡ ‹‹ለሺህ ፍልጥ ማሰሪው ልጥ›› ነውና ጭብጥ የሙግት መሰብሰቢያና ማሰሪያ ነው፡፡
ማሰሪያ የሌለው ፍልጥ እንደሚበታተንና ለአያያዝ እንደሚያስቸግር ሁሉ በጭብጥ ያልተያዘ ሙግትም ወደ ጭፍጫፊ ነጥቦች እየተሰነጣጠረና እየተሰበጣጠረ ስለሚሔድ መያዣ መጨበጫ የሌለው ይሆናል፡፡
በመሆኑም ጭብጥ የሙግት/ክርክር ዳር ድንበርና ይዘት ጭምር ወሳኝ ነው፡፡ ግራ ቀኙ የተለያዩበትን ሥረ ነገርና ሕጋዊ መሠረቱን አጥርቶ ያመለክታል፡፡ ተከራካሪዎቹ ጭብጣቸውን እንዲያስረዱ፣ በጭብጣቸው እንዲረጉ፣ ፈራጅም በጭብጡ ተወስኖ ማስረጃውን መዝኖ ክርክሩን አዳምጦ ሕጉን አገላብጦ ሙግትን እንዲቆርጥ ውሳኔውን እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡
6. ማስረጃ
ፍርድን በማስረጃ ማንተራስ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አስተያየት የሚቀረጸው በማስረጃ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ማስረጃ በሁለት ወገን የሚቀርብና አልፎ አልፎም ዕውቅ ነገር ሲያጋጥም ከፈራጅ ግንዛቤ (Judicial Notice) የሚፈልቅ ነው፡፡