- Details
- Category: Sentencing and Execution
- Hits: 11459
በኢትዮጵያ የቅጣት አወሳሰን ህጉና ልምዱ
ቅጣትን የሚመለከቱ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት
በወንጀል ህጉ ሁለተኛ ታላቅ ክፍል (ልዩ ክፍል) ለእያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት መነሻና መድረሻ ቅጣት ተቀምጠዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የቅጣት መነሻና መድረሻዎች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡
- ከ1 አመት እስከ 10 አመት
- ከ3 አመት እስከ 10 አመት
- ከ5 አመት እስከ 15 አመት
በህጉ ልዩ ክፍል ከተመለከቱት ቅጣቶች በተጨማሪ አጠቃላይ የቅጣት አወሳሰን ድንጋጌዎች አሉ፡፡
- አንቀጽ 88 (የቅጣቶች አወሳሰን)
- አንቀጽ 84 (ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃዎች)
- አንቀጽ 82 (ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያዎች)
- አንቀጽ 85 (ልዩ የቅጣት ማክበጃዎች)
- አንቀጽ 83 (ልዩ የቅጣት ማቅለያዎች)
- ከአንቀጽ 179-189 (ቅጣቱ ሲከብደና ሲቀል ስለሚጣለው ቅጣት መጠን)
- ከአንቀጽ 190-200 (ቅጣትን ስለመገደብ) ናቸው፡፡
እነዚህን የተለያዩ ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ ቅጣት እንዴት ይወሰናል? በወንጀል ህግ አንቀጽ 189(1) የሚከተለው ተደንግጎ እናገኛለን፡፡
‹በአንድ ወንጀል ላይ ቅጣት የሚያከብዱና የሚያቃልሉ ጠቅላላ ምክንያቶች በተደራረቡ ጊዜ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ ማክበጃ ምክንያቶቹን ከግምት በማስገባት ያከብድና ቀጥሎ የሚያቃልሉትን ምክንያቶች መሰረት አድርጎ ቅጣቱን ያቃልላል›
ይላል፡፡
ከዚህ መረዳት እንደምንችለው መጀመሪያ ለማክበድ ከየት ይነሳል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ ስለሆነም በግልጽ ባይቀመጥም ዳኛው፣
- በቅድሚያ መነሻ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት፣
- ቀጥሎ ማክበጃ ምክንያቶች ከአሉ ቅጣቱን ማክበድ እንደሚኖርበት፣
- ቀጥሎ ማቅለያ ምክንያቶች ከአሉ ቅጣቱን ማቅለል እንደሚኖርበት፣
ያስረዳል፡፡
ይሁንና፣
- መነሻው ስንት ይሁን? በሕጉ መልስ የለም፡፡
- ማክበጃዎች ሲኖሩ በምን ያህል ሊከብድ ይገባል ? በሕጉ መልስ የለም፡፡
- ማቅለያዎች ሲኖሩ በምን ያህል ሊቀል ይገባል ? በሕጉ መልስ የለም፡፡
ስለሆነም በወንጀል ህጉ የተቀመጡትን የቅጣት ድንጋጌዎችና ስለቅጣት አወሳሰን የተቀመጡት ድንጋጌዎች በፍርድ ቤት የሚሰጡ ቅጣቶች፣
- ወጥነት፣
- ትክክለኛነት ያለው፣
ለማድረግ የሚያስችሉ አይደሉም፡፡
የቅጣት ውሳኔዎች ግምገማ
ቅጣት የተሰጠባቸው መዝገቦችን ስንመለከት፣
አቃቤ ህግ፣
- ቅጣቱ ከብዶ ይወሰን፣
- ተመጣጣኝ ቅጣት ይሰጠው፣
ከሚል ባለፈ ከብዶ ሲባል ከባዱ ምን ያህል እንደሆነ፣
- መነሻው ስንት ሆኖ ሊከብድ እንደሚገባ፣
- ተመጣጣኝ የሚሆነው ምንእንደሆነ ፣
የሚያመለክቱ አይደሉም፡፡
በተከሳሽ በኩል የሚቀርቡ የቅጣት አስተያየቶችም ጥቅል ሆነው ከሚቀርቡ በስተቀር ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ዳኛው ቅጣትን ሲወስንም፣ ቅጣትን ለማክበድ፣
- የወንጀል ሪከርድ አለው
- የወንጀል አፈጻጸሙ አደገኛነት አለው፣
- ድርጊቱ የተፈጸመው በአፍቅሮ ንዋይ በመሆኑ የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ፣
ቅጣቱን ለማቅለል
- የወንጀል ሪከርድ የለውም ስለሆነም አደገኛ አይደለም፡፡
- የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው፡፡ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ፣
ቅጣት ይወስናል፡፡
ይሁንና ዳኞች እነዚህን ምክንያቶች ይጥቀሱ እንጂ፣
- በየትኛውም መዝገብ ቅጣቱን ለመወሰን መነሻው ስንት መሆን እንዳለበት ተመልክቶ አይታይም፡፡
- በማክበጃነት የቀረቡትንና በማቅለያነት የቀረቡትን ምክንያቶች የሚቀበለውና የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን ከለዩ በኋላ፣ ከምክንያቶቹ ጋር ግንኙነቱን ለማስረዳት በማይቻል መልኩ በጥቅሉ የቅጣቱ መጠን ይቀመጣል፡፡
ስለሆነም፣
- መነሻ የቅጣት መጠኑ ስንት እንደሆነ፣
- በማክበጃነት የተቀመጡት ምክንያቶች ቅጣቱን በማክበድ ያላቸው አስተዋጽኦ እንዲሁም
- ማቅለያ ምክንያቶች እንዴት አገልግለው ቅጣቱ እንደቀለለ፣
ለማወቅ አይቻልም፡፡
ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት በአገራችን ቅጣት አወሳሰን ምክንያታዊነት የጎደለው፣ በእርግጥም የተጣለው ቅጣት አግባብነት ያለው መሆኑን ለማስረዳት አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት፣
በአንድ ዳኛ በተለያየ ጊዜ ወይም በተለያዩ ዳኞች ተቀራራቢና ተመሳሳይ ለሆኑ ወንጀሎች የሚሰጡ የተለያዩ ቅጣቶች መኖራቸው፣
ከዚህም የተነሳ በቅጣት አወሳሰን ተገማችነት የሌለው መሆኑ፣
ቅጣት አወሳሰን ግልጽነት የሌለውና በፍትህ አካላቱ ባለሙያዎች ላይ ተጠያቂ ለማድረግ የማያስችል ሆኖ እናገኘዋለን::