- Details
- Category: Property Law
- Hits: 6579
ፓትሪሞኒ (Patrimony)
በሕግ እውቅና የሚያገኙና ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች የገንዘብ ዋጋ(Pecuniary Value) ያላቸው ሆኖው ከአንድ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉና በገንዘብ ዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ተብለው በሰፊው በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። በገንዘብ ዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ መብቶች በተለያዩ የሰብአዊ መብቶችን በሚመለከት በሚወጡ ድንጋጌዎች ውስጥ የተካተቱትን የሲቪልና የፓለቲካ መብቶች የመሳሰሉትን ሊያጠቃልሉ የሚችሉ ሲሆን ፤ የገንዘብ ዋጋ ያላቸው መብቶች የምንላቸው ደግሞ ግዴታዎች በሚመለከቱ ሕጎች (Law of obligation) እና በንብረት ሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች የሚያጠቃልሉ ናቸው።
በግዴታዎች ሕግ ስር የሚካተቱት መብቶች ሊጠየቁ የሚችሉት ከተወሰኑ ተለይተው ከሚታወቁ ሰዎች በመሆኑ ግላዊ ባህሪ ያላቸው መብቶች (rights in personam) በሚል የሚታወቁ ሲሆን ፤ በንብረት ሕግ ስር የሚሸፈኑት እንደ የባሌቤትነት መብት፣ የይዞታ መብት፣ የአለባ መብት የመሳሰሉት ደግሞ ከሁሉም ሰዎች ልንጠይቃቸው የሚችሉ መብቶች በመሆናቸው ግዙፍ መብቶች (rights in rem) በመባል ይታወቃል።
በገንዘብ ሊተመኑ የሚችሉ የአንድ ሰው መብቶችና ግዴታዎች ተጠቃልለው አንድነት ሲፈጥሩ ፓትሪሞኒ (Patrimony) የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል። ፓትሪሞኒ ራሱን የቻለ ሓሳብ (Notion) እንደመሆኑ አንድ ሰው የግድ የንብረት ባለቤት ወይ ንብረት ያለው መሆን አለበት ማለት አይደለም። መብቱ ከዜሮ በታች በወረደበትና ግዴታ ብቻ በተሸከመበት ጊዜም ቢሆን ፓትሪሞኒ እንዳለው ይቆጠራል።
ፓትሪሞኒ ራሱን የቻለ ፅንስ ሓሳብ (Notion) እንደመሆኑ መጠን የዚህ ባለቤት የሆነ ሰው በህይወት እስካለ ድረስ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። በሌላ አነጋገር ለፓትሪሞኒ መኖር ንብረት ይኑሮው ኣይኑሮው ግምት ወስጥ ሳይገባ የግለሰቡ በህይወት መኖር ብቻ በቂ ያደርገዋል።
ፓትሪሞኒ አራት ባህርያት አሉት፦
- 1)እያንዳንዱ ፓትሪሞኒ የዚህ መብት ባለቤት ከሆነው የተፈጥሮ ሰው ወይም የሕግ ሰውነት ያለው ሰው ተለይቶ የማይታይ መሆኑን፣ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ዳግም ስለ ፓትሪሞኒ ስናወሳ በተጨባጭ ስለመብቶችና ግዴታዎች አብሮ መነሳቱ ስለማይቀር ነው። መብትና ግዴታ ሊኖረው የሚችል ደግሞ ሰው ብቻ በመሆኑ ነው።
- 2)እያንዳንዱ የተፈጥሮ ሰው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ፤ የሕግ ሰው ደግሞ የሕግ ሰውነት ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ የመብትና ግዴታ ባለቤት በመሆኑ ይዘቱ ወይም መጠኑ ቁጥር ሳይገባ ፓትሪሞኒ ኣለው ይባላል። ያም ሆኖ ግን የመጨረሻ ድሃ በመሆኑ ምንም ዓይነት ንብረት የሌለው ቢሆንም አንኳ ሁሉ ጊዜ ባለፓትሪሞኒ ነው። ምክንያቱም ለወደፊቱ ንብረት ሊያፈራ ይችላል ተብሎ ስለሚገመት ነው።
- 3)አንድ ሰው ምንም እንኳ ሃብታም ቢሆንም የሚኖረው ፓትሪሞኒ አንድ ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ንብረትና ፓርትሪሞኒ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸው ነው። ሁሉም መብቶችና ግዴታዎች አንድ ፓትሪሞኒ የሚፈጥሩ /የሚመሰርቱ/ መሆናቸው ለባለገንዘቦች እና (creditors) ለወራሾች ወዘተ ጥቅም ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። አንድ ሰው አንድ ፓትሪሞኒ ብቻ አለው የሚለውን መርህ እንዳለ ሆኖ እንደ ልዩ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰደው ግን አንድ ሰው ሲሞት ንብረቱን ወራሾች ስለሚከፋፈሉት በዚህ ምክንያት ከአንድ በላይ ፓትሪሞኒ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
- 4)የአንድ ሰው መብቶችና ግዴታዎች ያ ሰው በህይወት እስካለ ድረስ የሚኖሩና እሱ ሲሞት ግን ኣብረውት የሚጠፉ ናቸው። ምክንያቱም ሰው ያለ ፓትሪሞኒ ፓትሪሞኒ ደግሞ ያለ ሰው ህልውና የሌላቸው በመሆኑ ነው።
ፓትሪሞኒ በተመለከተ የተሰጠ ትርጉም የማይቀበሉ ሰዎች አሉ። የማይቀበሉበት ምኽንያት ሲገልፁም፦
ሀ/ አንድ ሰው በህይወቱ እያለ ግማሽ ንብረቱ ለሌላ ሰው ሊያስተላልፍ ስለሚችል፣
ለ/ አንድ ዕዳ የመኽፈል ግዴታ ያለበት ሰው ንብረቱን ለባለገንዘቦች ሲሰጥ/ሲያስተላለፍ/ ፤
በእነዚህ ሁለት ምኽንያቶች አንድ ሰው በህይወቱ እያለ አንድ ፓትሪሞኒ ብቻ ይኖረዋል የሚለውን ሓሳብ የሚያፈርስ ነው ይላሉ።
ይህ ነቀፊታ ቢኖርም ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው ግን ከላይ የተጠቀሱት አራት ነጥቦች ናቸው።
ፓትሪሞኒ ሊባሉ የማይችሉ (Extra-Patrimony)
በፓትሪሞኒ ሊካተቱ የማይችሉ በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ ሁሉም መብቶችና ግዴታዎች ናቸው። ለምሳሌ፦
- የፓለቲካ መብቶች
- ከጋብቻ ጋር የተያያዙ መብቶች
- ስብኣዊ መብቶች
በፓትሪሞኒና ፓትሪሞኒ ባልሆነ መብት ያለ ልዩነት ምንድነው?
- በገንዝብ ሊተመን የሚችል ወይም የማይችል መሆን
- በተለያዩ መንገዶች ከአንድ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ የሚችል ወይም የማይችል መሆንና አቤቱታ ሊቀርብበት የሚችል ወይም የማይችል መብት መሆን። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ቢኖር የደመወዝ 2/3 እና የጥሮታ አበል ላይ አቤቱታ /ክስ/ሊቀርብባቸው ይችላልን? የማይቻል ከሆነስ በፓትሪሞኒ ሊካተቱ አይችሉም ማለት ነውን? የሚል ሲሆን ፓትሪሞኒ ወደ ሌላ ሊተላለፍ የሚችል ነው የሚል መርህ እንዳለ ሆኖ ስለ 2/3 ደመወዝ እና የጥሮታ አበል በልዩ ሁነታ መታየት ያለበት ነው።
በፓትሪሞኒ ስር የሚጠቃለሉ መብቶች
ሀ/ ግላዊ ባህሪ ያለው መብት (Personal Right or right in Personam)
ለ/ ግዙፍ መብት (Real right or right in rem)
ግላዊ ባህሪ ያለው መብት (Right in personam) የሚባለው ከግዴታዎች ጋር የተያያዘ መብት ሲሆን በሁለት ወገኖች መካከል የሚኖር የመብትና ግዴታ ግንኙነት የሚገልፅ ነው። ለምሳሌ በተዋዋይ ወገኖች ያለን ግንኙነት መጥቀስ ይቻላል። ባለ ዕዳ የሆነ ወገን ለባለገንዘቡ ሲል የመስጠት፣ የማድረግ እና ያለማድረግ ግዴታ ያለበት ሲሆን ባለገንዘቡ ወይም ባለመብቱ ደግሞ በባለዕዳው ላይ ያሉት ግዴታዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑለት ለማድረግ ክስ የማቅረብ ወይም በሌላ መንገድ የመጠየቅ መብት ይኖሯል።
ግዙፍ መብት (right in rem) የምንለው ደግሞ ከንብረት ሕግ ጋር የተቆራኘ ሆኖ የዚህ ባለመብት የሆነ ሰው ሌሎች ሰዎች ጣልቃ ሳይገቡበት ሕግ በሚፈቀደው መሰረት የባለሃብትነት ወይም ሌላ መብቱን ፍፁም (absolute) በሆነ ሁነታ ተግባራዊ የሚያደርግበት፣ ሌሎች ሰዎች በመብቱ ላይ ጣልቃ የገቡበት እንደሆነም ሕጋዊ የሆነ መንገድ ተከትሎ የማስተካከል ወይም ችግሩ የማስወገድ መብት አለው። ሌሎች ሰዎች የሚጠበቅባቸው ነገር ቢኖር ያለማድረግ ግዴታ መፈፀም ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ ፓትሪሞኒ ማለት አንድ የተፈጥሮ ወይም የሕግ ሰውነት ያለው ሰው በገንዘብ ሊተመኑ የሚችሉና በመርህ ደረጃም ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉትን መብቶችና ግዴታዎች ኣጠቃልሎ የያዘ መሆኑን፣ ፓትሪሞኒ ሊኖረው የሚችል ሰው ብቻ መሆኑን፣ አንድ ሰው አንድ ፓትሪሞኒ ብቻ ያለው መሆኑን፣ ሰው ሲሞት ወይም የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሲፈርስ የነበረው ፓትሪሞኒም አብሮ የሚያከትም መሆኑን፣ በፓትሪሞኒ ሊካተቱ የሚችሉ ደግሞ ግላዊ ባህሪ ያላቸውና ግዙፍ የሆኑ መብቶች እንደሆኑ እና የገንዘብ ዋጋ የሌላቸውና ወደ ሌላ ሊተላለፉ የማይችሉ መብቶች ግን የፓትሪሞኒ አካል እንዳልሆኑ፤ ግላዊ ባህርይ ባለውና ግዙፍ በሆነ መብት መካከል ያለ ልዩነትም፤ ግላዊ ባህርይ ያለው መብት በግለሰቦች መካከል የሚኖር ግንኙነት የሚገልፅ ሲሆን ግዙፍ መብት ግን ከባለመብቱ በሰተቀር በዓለም ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ባለግዴታዎች እንዲሆኑ ያደረገ ነው።