- Details
- Category: Property Law
- Hits: 8521
ተራ የጋራ ባለሃብትነት (Ordinary Joint Ownership)
የጋራ ባለሃብትነት ምንድን ነው? የጋራ ባለሃብትነት መብት በመሰረቱ በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ውል የሚቋቋምና የሚገዛ የጋራ ንብረት ባለሃብትነት መብት ወይም ከህግ በሚመነጭ የጋራ ባለሃብትነት የሚቋቋም የንብረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብትነት መብት ከፍታብሄር ህግ አኳያ ሲታይ በሁለት ማለትም ተራ የጋራ ባለሃብትነት (Ordinary joint ownership) እና ልዩ የጋራ ባለሃብትነት (Special joint ownership) በሚል ሊከፈል ይችላል፡፡ ተራ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቱ (Subject matter) ግዙፍነት ያላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው የንብረት መብቶች እንደ የፈጠራ መብት (patent right) ፣ የቅጂ መብት (copy right) እና የኢንዱስትሪ ንድፍ (Industrial design) ያሉ የንብረት መብቶችን መሰረት በማድረግ ሊሚቋቋም የሚችል የንበረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን የንብረት መብታቸውን ንብረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ በዋስትና (mortgage) ፣ የንብረት አገልግሎት (Servitude) ፣ አላባ በመስጠት (usufruct) ወይም የቀደምትነት መብት (pre-emptive right) አለኝ በማለት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት የሚያስችላቸው የንብረት መብት ነው፡፡ ንብረቱ የሚንቀሳቀስ በሚሆንበት ግዜም በዋስትና (pledge) በአላባ (usufract) ወ.ዘ.ተ. በመስጠት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በሁለትና ከዚያም በላይ ባሉ ሰዎች መካከል የጋራ ባለሃብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የሚኖረው መስፈርት የጋራ ባለሃብቶች ነን በሚሉት ሰዎች መካከል የባለቤትነት ጥቅም (ownership interest) ያላቸው ሰዎች መሆንና የጋራ ባለሃብትነታቸው በተመሳሳይ ንብረት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል፡፡(the joint ownership must exist over the same thing) እነዚህን ሁለት መመዘኛዎች ካላሟሉ ግን የጋራ ባለሃብቶች ሊባሉ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ የንብረት ባለቤት (owner) እና የአላባ ተጠቃሚ (usufractuary) የሆነ ሰው በአንድ ንብረት ላይ የጋራ ባለሃብቶች (joint owners) ሊሆኑ አይችሉም፡፡የዚህ ምክንያትም አንደኛው በንብረቱ ያለው የሰፋ የባለቤትነት መብት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በንብረት ላይ ያለው መብት ጠበብ ያለ የአላባ መብት ስለሆነ በንብረት ላይ ያላቸው መብት የተለያየ አስከሆነ ድረስ የጋራ ባለሀብትነት (joint ownership) ሊመሰርቱ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የጋራ ባለሀብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የባለቤትነት መብትንና ይህ መብት በዚያ ተለይቶ በታወቀ ንብረት ላይ ያለ የጋራ መብት መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የጋራ ባለሃብቶች መብቶች (Rights of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት መብት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ይሄውም ስምምነቱን መሰረት ከሚያደርገው ሰነድ ወይም በጋራ ባለሃብቶች መካከል የተደረገ ስምምነት ባይኖርም እንኳ ህግ በራሱ ግዜ ያንን ንብረት የጋራ ሃብት በሚያደርግበት ግዜ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 62 መሰረት የሚታይ የባልና የሚስት የጋራ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ፣ የውርስ ንብረት እስከ ሚከፋፈል ድረስ ያለው የጋራ ባለሃብትነት መብት (የፍ/ብ/ህ/ቁ.1060-1064) ወይም በማቀላቀል ወይም በማዋሃድ መሰረት የተገኘ በጋራ ባለሃብትነት መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1183 ወይም ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1257-1277 ባሉ ድንጋጌዎች መሰረት የሚገዛ የጋራ ባለሃብትነት መብት በሚኖርበት ግዜ መብቱ የመነጨው ከህግ ይሆንና ሰዎቹ የጋራ ባለሃብቶች ይሆናሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጋራ ባለሃብቶች ከንብረት ህጉ አኳያ ሊኖራቸው የሚችል የጋራ እና የተናጠል መብቶችንና ገዴታዎችን በዝርዝር ስናይ፡-
- Øየጋራ ሃብቱን በማስመልከት የተደረገ ስምምነት ከሌለ በስተቀር የጋራ ባለሃብቶች የጋራ ንብረት በሆነው ንብረት ላይ እኩል የባለቤትነት መብት (equal ownership right) አላቸው ተብሎ የህግ ግምት (legal presumption) ስለሚወሰድ በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን ድርሻ ከመሬት በስተቀር የመሸጥ ወይም መሬትን ጨምሮ በሌላ ንብረት ላይ በዋስትና የማስያዝና የመከፋፈል መብት ይኖራቸዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1259፤ 1267፤ 1271 እና 1272) እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ፍ/ብ/ሀ/ቁ 1260 ለምን በአላባ የመስጠት መብትንስ አላከተተም? የሚል ጥያቄ ሲሆን ለዚህ በመልስነት ወይም በመከራከርያነት ሊነሳ የሚችለው ሃሳብ የእንግሊዝኛው የፍታብሄር ህግ ቅጂ "dispose" የሚል ቃልን በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) ላይ ሲለሚጠቀም እና በአላባ መስጠት የሚለውን መብት በዚሁ ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት አካቷል የሚል ሓሳብን በማንሳት ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) ለአንድ የጋራ ሃብት ባለድርሻ የአላባ መብትን የሰጠው ስለሆነ ድርሻውን በአላባ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላል የሚለው መከራከርያ ነው፡፡ ሌላው የመከራከሪያ ወይም የአተረጓጐም ስልት አንድ የጋራ ባለሃብት በድርሻው ያለውን ባለቤትነት መብት (ownership right) መሰረት በማድረግ ለሌላ ሰው የአላባ መብት ሰጠ ማለት በጋራ ሃብቱ ላይ ያለውን መብት በከፊል ለሌላ ሰው አስተላለፈ ማለት ስለሆነ ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) በአለባ የመስጠት መብትንም አካቷል ተብሎ መተርጐም አለበት የሚል ነው፡፡ አዘጋጁም በነዚህ ሃሳቦች ይስማማል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው የባለቤትነት መብት ያለው ሰው የሌላውን ሰው መብት ሳይነካ በንብረቱ ላይ እንደፈለገ የማዘዝ፤ (abusus or jus disponendi) በንብረቱ የመገልገል (usus or jus utendi) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመጠቀም(fructus or jus fruendi) መብቶች ስለሚኖሩትና አላባ ግን ከባለቤትነት መብት በጠበበ መልኩ በንብረቱ የመገልገልን ወይም ፍሬውን ሰብሰቦ የመውሰድን ወይም ሁለቱን መብቶች አዳብሎ ሊይዝ የሚችል በመሆኑ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1260(1) ደግሞ ሶስቱን መብቶች ባካተተ መልኩ የሚደነግግ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ በአላባ የመስጠትንም መብት ያካተተ ነው ብሎ መተርጐሙ የህጉን አላማ የበለጠ የሚያሳካል አተረጓጎም ስለሆነ ነው፡፡
- Øበጋራ ሃብቱ የመገልገል ወይም ፍሬውን የመሰብሰብ መብት አላቸው፡፡ ይሄውም የጋራ ሃብቱ የተፈጥሮ ፍሬ (natural fruit)፣ ሲቪል ፍሬ (Civil Fruit) የኢንዱስትሪ ፍሬ (Industrial fruit) ወይም ምርት (product ) ሊሆን ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1170፣ 1171፡ 1264 እና 1333) ስለሆነም የጋራ ሃብቱ ከሚያፈራው ፍሬ እንደየደረጃቸው ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡
- Øየጋራ ባለሃብቶቹ አንድን ባለድርሻ ነኝ የሚልን ሶስተኛ ወገን ሊከፈለው የሚገባውን በመክፈል ከጋራ ባለሃብትነቱ ለማስወጣት የሚያስችል የጋራ መብት (Concurrent right ) አላቸው፡ በዚህ ጊዜ ድርሻው ለመግዛት ገንዘብ ማዋጣት ያለባቸው ሲሆን በየድርሻቸው መጠን (pro rata basis) ማዋጣትና ገንዘቡን ለባድርሻው መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1261 እና 1386-1409)
- Øከጋራ ባለሃብቶቹ መካከል አንዱ በጋራ ሃብቱ ላይ ያለውን ድርሻ ለመሸጥ በሚፈልግበት ግዜ ከጋራ ባለሃብቶቹ አንዱ ለሱ እንዲሸጥለት የቀደምትነት መብቱን መሰረት በማድረግ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን በገበያ ዋጋው እንጂ ከዚያ ባነሰ ዋጋ እንዲሸጥለት ሊያስገድደው ይችላል ማለት አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር የጋራ ባለሃብቱ ድርሻ እገዛለሁ በሚልበት ግዜ የሻጩን በንብረቱ ተጠቃሚ የመሆን መብት መሰረት በማድረግ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በማይጥስ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(1)፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1261 እና 1386)
- Øበአንድ በጋራ ሃብትነት የተያዘ ንብረት ላይ ድርሻ ያለው ሰው ድርሻውን ለመተው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህን መብቱን መሰረት በማድረግ የነበረኝን ድርሻ ትቻለሁ በሚል ሰበብ ከመተዉ በፊት የዚህ የጋራ ሃብት ወጪዎችም ሆኑ እዳዎች ከመክፈል ወይም ለመከፈሉ ሃላፊ ከመሆን አይድንም፡፡ የተቀሩት የጋራ ባለሃብቶች ይህን የተተወን ድርሻ በእኩል የመካፈል መብት ያላቸው ሲሆን በራሱ ፈቃድ ድርሻውን ትቻለሁ ያለ የጋራ ባለሃብት ተመልሶ በድርሻየ የጋራ ባለሃብት ልሁን ብሎ መጠየቅ አይችልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1262፣ 1164)
- Øበጋራ ሃብቱ ላይ ድርሻ ያለው ሰው የሌሎችን ባለድረሻዎች መብት ሳይጥስ የጋራ ሃብቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል የማድረግ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1263)
- Øየጋራ ባለሃብቶቹ የጋራ ንብረታቸውን የማስተዳደርና ይህንን መሰረት በማድረግ ድምፅ የመስጠትና ውሳኔ የማሳለፍ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1265 እና 1266 )
- Øአንድ የጋራ ሃብት ባለ ድርሻ የጋራ ሃብቱ ሊደርስበት ከሚችል ሙሉ (total) ወይም ከፊል (partial) ጥፋት (loss) ለማዳን ሲል ያወጣውን ወጪ ከጋራ ባለሃብቶቹ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1268)
ብዙውን ግዜ ከዚህ መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚነሳው ጥያቄ ከአደጋ ለመከላከል ወጪውን የጠየቀው ስራ ውጤታማ ባይሆንና የጋራ ሃብቱ ቢወድም ሌሎቹ የጋራ ሃብት ባለድርሻዎች ይህን ወጪ የመተካት ግዴታ አላቸውን? የሚል ሲሆን ሌላውም የጋራ ሃብቱ በሙሉ ወይም በከፊል ከአደጋው ቢተርፍም ለዚህ ሲባል በአንደኛው ባለድርሻ የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ የበዛ በሚሆንበት ግዜስ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን ወጪ የመሸፈን ግዴታ አላቸውን? የሚሉ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ጥያቄ ዙሪያ የሚንሸራሸሩት ሃሳቦች የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ መታየትና መመዘን ያለበት ከድል (success) አንፃር ሳይሆን ከአላማው (purpose) አንፃር መሆን ይኖርበታል:: ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268 ቢሆንም የንብረቱ ከአደጋ ወይም ከጉዳት ስለመከላከልና ለዚህ ሲባል ስለሚወጣ ወጪ እንጂ ስለውጤቱ የሚለው ነገር ስለሌላ የመከላከሉ ግብ መምታት እና አለመምታት ወጪውን ከመሸፈንና ካለመሸፈን ጋር አያይዘን ማየት የለብንም የሚል ነው፡፡ ለዚህ የመራከሪያ ሃሳብ እንደማጠናከሪያ የሚነሱት ሌሎች ሓሳቦችም ንብረቱን ካላተረፈው ወጪውን አንሸፍንም የሚል አካሄድ መከተል የጋራ ሃብቱ እየጋየም ቢሆን በግሉ አውጥቶ የሚከላከል ሰው ስለማይኖር የጋራ ባለሃብቶች ችላ እንዲሉ ስለሚያደርግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዘን ይቸላል የሚል ነው፡፡ ሌላውም አንድን በአደጋ ግዜ ረጋ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ በሆነበት ግዜ የጋራ ሃብቱን ለማዳን ሲል አስፈላጊ የሆነውን ወጪ ያወጣ ባለድርሻ ወጪውን አንተካም ብሎ ማለት ምክንያታዊ አይደለም (unreasonable) የሚል ነው፡፡ የሁለተኛውን ጥያቄ በማስመልከት የሚሰነዘረው አስተያየትም የጋራ ንብረቱን ከአደጋ ለመከላከል የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ በላይ ቢሆንም ለዚህ የወጣን ወጪ የጋራ ባለሃብቶቹ መተካት አለባቸው የሚል ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የሚሰነዘረው አስተያየት የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ በመብዛቱ ብቻ እንዳላስፈላጊ ወጪ (unnecessary expense) መታየት የለበትም፡፡ የፍታብሄር ህጉ ይህን የሚያስብ ቢሆን ኑሮ አሁን እያነሳን ያለውን የባለ ድርሻው መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268 ያላስፈላጊ ወጪ የሚላቸውን ነገሮች በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269 ለብቻ ባላስተናገዳቸው ነበር የሚል አስተያየት ነው፡፡ ሌላው ከባለድርሻው መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ግን አንድ ባለድርሻ ይህንን ለማድረግ ስልጣን ሳይኖረውና አስፈላጊ ባልሆነ ጊዜ ወጪ አድርጎ የጋራ ሃብቱን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ከፍ እንዲል፤ (increase the economic value) እይታው እንዲያምር፤ (increase the appearances) ወይም የሃብቱ ጠቃሚነት እንዲጨምር (increase the usefulness) ቢያደርግም ወጪውን ሌሎች ባለድርሻዎች እንዲተኩለት መጠየቅ የማይችል መሆኑ ነው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269(1)) አንደዚሀ ያለ ድርጊት የፈፀመ ባለድርሻ ያለው አማራጭም ንብረቱን ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ (restoration) ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1269(2))
- Øየጋራ ባለሃብትነቱ የተመሰረተው በባለ ድርሻዎቹ ስምምነት በሆነ ግዜ የጋራ ባለሃብት ለመሆን በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ባለድርሻው ከጋራ ባለሃብትነቱ ለመውጣትም (to withdraw) ነፃ ነው፡፡ በእርግጥ ከባለድርሻዎቹ አንዱ ሽጠን እንካፈል ሲል ሌሎቹ ደግሞ በዓይነት እንካፈል የሚል መከራከሪያ በመያዝ ከአንድ ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ ፡፡ እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ ፍ/ቤት ጉዳያቸውን በማየት ወቅቱ ለመሸጥ አመቺ ነው ባላለበት ጊዜ የከፍፍል ጥያቄውን ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊያረዝመው ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1271) የሚከፋፈለው ነገር የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜም የጋራ ንብረቱ፤
-
- ከተቋቋመት አላማ ውጭ እንዳይሆን
- ክፍፍሉ የጋራ ሃብቱን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ የሚቀንሰው እንዳይሆን
- በቀጣይ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር የማይፈጥር መሆኑን ታሳቢ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1272) የጋራ ባለሃብትነት መብት ከስምምነት ሊመነጭ እንደሚችል የተገለፀ ቢሆንም የጋራ ሃብቱን መሰረት ያደረገ ስምምነት ባይኖርም ህግ በራሱ የጋራ ሃብት እንደሆኑ ግምት የሚወስድባቸው እንደ አጥር፣ የጋራ ግንብና ኮሪደር ያሉ እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1281(1) (2)
የጋራ ባለሃብቶች ግዴታዎች (Duties of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ከስምምነት የሚመነጩ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም እንዲሚኖሩት ይታወቃል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ የመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም እንደዚሁ ከህጉ የሚመነጭ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ ይኖራል፡፡ ከንብረት ህጋችን አንፃር የጋራ ባለሃብቶችን ግዴታዎች ስንመለከት፡-
በአንድ የጋራ ሃብት ላይ ድርሻ ያለው ተጋሪ የጋራ ሃብት በሆነው ንብረት የመገልገል መብት (physical enjoyment) ቢኖረውም በዚህ መብቱ በሚሰራበት ግዜ ንብረቱ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ሊገለገልበትና (shall not convert the purpose for which it was destined) የሌሎቹን ባለድርሻዎች በጋራ ንብረቱ የመገልገል መብትን በሚፃረር መንገድ (shall not impair their use rights) ሊገልገልበት አይገባም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1263)
የጋራ ባለሃብቶቹ ከውሳንያቸው ለሚመነጭ ያልተጠበቀ ውጤት (consequence) ሃላፊ የመሆን ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1267)
በባለድርሻው አማካይነት በጋራ ሃብቱ ላይ ለደረሰ ጉዳት ከባሰ ውድመት ለማዳን ሲባል በጥፋት የወጣው ወጪ አስፈላጊ ወጪ (necessary expense) ቢሆንም ጥፋቱን የፈፀመው ባለድርሻ ወጪውን የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ እንዲሁም ወጪው አላማ የሌለው (purposeless) ከሆነም ወጪውን የመሸፈን ግዴታ የሚወድቀው የዚህ ዓይነት ወጪ ባደረገው ባለድርሻ ላይ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268(2) )
የጋራ ባለሃብቶቹ በጋራ ሃብቱ አማካይነት በሶስተኛ ወገኖች ሂወትና ንብረት ለሚያደርሱት ጉዳት ሃላፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ተራ የጋራ ባለሃብትነት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ የሚችል የንብረት መብትና ግዴታ ያለበት በሰዎች መካከል የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡
የጋራ ሃብትን ስለማስተዳደር (Acts of management)
የጋራ ሃብትን ማስተዳደር ማለት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ያለውን አባባል ከፍ/ብ/ህ/ቁ.2204 ጋር አስተሳስረን ስንመለከተው የጋራ ሃብቱን ማቀብ (to preserve or maintain) ማለት ነው ብለን ልንተረጉመው እንችላለን:: ይህን ዘርዘር ባለ መልኩ ስናየው ደግሞ የጋራ ሃብትን ማስተዳደር የጋራ ሃብቱን ከሶስት ዓመት ላልበለጠ ግዜ ማከራየት፣ የተገኘውን ገቢ በሌላ ስራ ላይ ማዋል (investing the income) ምርትንና፣ የሚበላሹ ነገሮችን መሸጥን እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1266 የተዘረዘሩትን የጋራ ባለሃብቶች ሙሉ ድምፅ በማግኘት ሲወሰን የጋራ ሃብቱን መሸጥ (to dispose of) ፣ በዋስትና (mortgage or pledge) በኣላባ (usufruct) መስጠትና የጋራ ሃብቱ የተቋቋመበትን አላማ መለወጥ እንደ አስተዳደራዊ ስራ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1266 ከተዘረዘሩት ነገሮች ውጭ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ስር በሚወድቁ ጉዳዮች ላይ የጋራ ባለሃብቶቹ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ያገኘን ጉዳይ እንዲተገበር ማድረግ እንደ አስተዳደራዊ ስራ (act of management) ሊወሰድ ይችላል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ መብት መሰረት ውል በሚሆንት ጊዜ ውሉ በፅሑፍ ሆኖ ተዋዋይ ወገኖች ስለሚኖራቸው መብት፤ ግዴታና የንብረቱ አስተዳደር ምን መሆን እንዳለበት መግለፅ ይኖርበታል:: (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1277ን ከ1282 እና 1283) የጋራ ባለሃብትነት የሚመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም የጋራ ባለሃብቶቹ መብትና ግዴታ የሚመነጨው ይህን መብት ከሚያስገኘው ወይም ግዴታን ከሚጥለው ህግ ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት የጋራ ባለሃብቶች ከመጀርያው የጋራ ሃብቱን አስተዳደር መሰረት በማድረግ የሚፈጠሩትን ያለመግባባቶች በድርድር (arbitration) ለመፍታት ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1275 እና 3307-3346) ባለድርሻዎቹ ሳይስማሙ ከቀሩ ፍ/ቤት አስተዳደሪ ሊሾምላቸው ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1273) ስለሆነም የጋራ ሃብት የማስተዳደር ስልጣን ከውል ወይም ከሕግ ሊመነጭ የሚችል ሆኖ በጋራ ባለሃብቶች መካከል ያለመስማማት ማለትም ሙሉ ድምፅ (unanimous vote) ወይም አብላጫ ድምፅ (majority vote) መሰጠት ባለባቸው ጉዳይ የሚፈለገውን ድምፅ ሳይሰጡ የቀሩ እንደሆነ ጉዳያቸውን በመመስረቻ ውላቸው ባስቀመጡት የችግር አፈታት መንገድ እልባት እንዲያገኝ ይደርጋል፡፡ ይህ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ እልባት የሚያገኝ ይሆናል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1265፤1266 እና1277(2) )
የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ ስለመሆን
የጋራ ባለሃብትነት መብትና ግዴታ እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ከውል ሊመነጭና ባለ መብቶቹ ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ይህ መብትና ግዴታ ቀሪ የሚሆንበት ማለትም ህግ ፊት ዋጋ ሊያጣ የሚችልበት ጊዜ አለ፡፡ መሰረቱ ህግ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ህግ አውጪው ህጉን በሚለውጥበት ጊዜ መብቱ ህጋዊ መሰረት (legal standing) የሚያጣበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህም መሰረት የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ የሚሆኑባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ውስደን ያየን እንደሆነ፡-
ü የጋራ ባለሃብቱ ድርሻውን ለሌሎቹ ባለድርሻዎች በነፃ ፈቃዱ ሲተው (surrender) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1262)
ü የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲደረግበት፡፡ (partition) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1264)
ü ድርሻየን ትቻለሁ ሲል፡፡ (renunciation) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268(3))
ü ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም የሚንቀሳቀስ ንብረት ሲሆንና የጋራ ባለሃብቱ በሚያቀርበው ጥያቄ ንብረቱ በግልፅ ሓራጅ ሲሸጥ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1271)
ü የጋራ ሃብቱ የማይንቀሳቀስ ሆኖ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለና ለመከፋፈል የማይቻል ከሆነ ወይም ንብረቱን መሸጥ ተስማሚ አይደለም ተብሎ በፍርድ ቤት ካልተወሰነ በስተቀር የጋራ ሃብቱ ሲሸጥ ወይም ሲከፋፈል የጋራ ባለሃብትነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1272-1274)
ü የጋራ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ስምምነት ውላቸው እንዲቀር ሲያደርጉ ወይም ህጉ በሚያዘው መሰረት የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡ ለምሳሌ የጋራ ሃብቱ የውርስ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ1079(1) መሰረት የንብረቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡
ü የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ በሚሆንባቸው ሌሎች ሁኔታዎች ቀሪ ሲሆን፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1188-1192)
ü ለጋራ ባለሃብትነት መብት መኖር መሰረት የሆነው የጋራ ንብረት ሲወድም ግንኙነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1304)
ü
ስለዚህ ተራ የጋራ ባለሃብትነት (ordinary joint ownership) ከውል ወይም ከህግ የሚመጣ ንብረትን መሰረቱ በማድረግ የሚፈጠር መብትንና ግዴታን ያዘለ ግንኙነት ነው፡፡ በመሆኑም በህገ-መንግስቱና ከዚያ በታች ባሉ ሌሎች ህጐች ጥበቃ የተደረገለትና በአንድ ወቅት የጋራ ባለሃብቶቹ በመብታቸው ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ቀሪ የሚሆን ወይም መብቱም ሆነ ግዴታው ተፈፃሚነት ሊያጣ የሚችል የኢኮኖሚ ትስስር ነው፡፡