- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9867
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች (Copy Right and Neighboring Rights)
የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በማስመልከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/96 በአንቀፅ 2(8) ላይ "የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ስራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችን ይጨምራል" በማለት ሲተረጉመው ተዛማጅ መብት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ደግሞ በአንቀፅ 2(14) ላይ " ተዛማጅ መብት ማለት ከዋኝ፣ የድምፅ ሪከርዲንግ ፕሮዲሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በስራው ላይ ያለው መብት ነው" በማለት ገልፆታል፡፡ እውቁ Wikipedia free encyclopedia በበኩሉ
Generally it is "the right to copy", but also gives the copy right holder the right to be credited for the work, to determine who may adapt the work to other forms, who may perform the work, who may financially benefit from it, and others.
በማለት የቅጂ መብት ለአእምሮ ንብረት ባለቤት የሚያስገኘውን መብት ሰፋ ባለመልኩ ተርጉሞት እናገኛለን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋለ ያለብን ነገር የቅጂ መብት ሽፋን የሚሰጠው ሃሳብን (ideas) እና መረጃን (information) ሳይሆን የህግ ጥበቃ የሚሰጠው የቅጂውን መብት መሰረት በማድረግ ስለሆነ ጥበቃው ለሃሳቡና ለመረጃው ሳይሆን ለአፃፃፍ ቅርፅ (forms) ወይም አገባብ (manner) መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የቀጅ መብት ተኩረት የሚያደርገውና ሽፋን የሚሰጠው ለሀሳቡ አገላለፅ አንጂ ሀሳቡ አንዳይጣስ ማድረግ አይደለም:: Copy right usually protects the expression of an idea not the idea itself. Thus, copy right does not prohibit a reader from freely using and describing that concept to others, it is only the particular expression of that process as originally described that is covered by copy right.
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ አላማ በአገራችን ያለውን የስነ-ፅሁፍ፣ የኪነ ጥበብ እና ሌሎች ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች የህግ ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ የአገራችንን ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኒኖሎጂያዊ እድገት በማፋጠን አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ ይህን አብይ አላማ መሰረት በማድረግ አዋጁ ከአሁን ቀደም በፍታብሄር ህጉ ከቁጥር 1647- 1674 ባሉ ህጎች ለቅጅ መብት ተሰጥቶ የነበረን የጥበቃ ሽፋን በማስፋት አዳዲስ መሰረተ ሃሳቦችና መብቶች እንዲካተት ያደረገ ነው:: የማስተላለፍያ መንገዶቹ (transferability) እንዲሰፋ በማድረግ ተገቢ የሆነ ጥበቃ እንዲያገኙና ዋስትና አግኝተው ባለሙያዎቹ በልበ ሙሉነት እንዲሰሩ የማስቻል አላማን በመያዝ የወጣና በስራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከማንኛውም ግዜ በላይ በአደረጃጀትና አሰራር ተጠናክሮ በመሄድ ላይ ያለ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ ዘርፍ ነው፡፡ በቅጂ መብት ሽፋን የሚሰጣቸውን የአእምሮ ንብረቶች በማስመልከት Wikipedia ላይ ያየን እንደሆነ ፤
copy right may apply to a wide range of creative, intellectual, or artistic forms or "works" . . . can include, poems, theses, plays, other literacy works, moves, dances, musical composition, audio recordings, drawings, sculptures, photographs, software, radio and television broadcasts, and industrial designs, graphic designs.
በማለት የቅጅ መብት ጥበቃ የሚያገኙ ስራዎችን በመዘርዘር ሲያሰፍር በአገራችን የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/96 ከዚህ ጋር በተቀራረበ መልኩ ጥበቃ ስለሚደረግላቸው የቅጅ መብት ማስገኛ ስራዎች በአንቀፅ 4(1) (ሀ) (ለ) ላይ የሚከሉት ፈጠራ ስራ ጥበቃ ይደረግላቸዋል በሚል ስር፤
ትርጉም፣ የማመሳሰል ስራ፣ ቅንብርና ሌላ የስራውን ዓይነት የሚቀይር ወይም የሚያሻሻል ስራ ወይም
በይዘት፣ በቅንብር፣ ወይም በአመራረጥ የተነሳ ኦርጅናል የሆነና በሚነበብ መሳርያ ወይም በሌላ መልክ ያለ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የቅኔ ስብስብ ወይም ዳታቤዝን የመሳሰለ የስብስብ ስራ፡፡
በማለት የሽፋን አድማሱን ሲገልፅ የህግ ጥበቃ ለማግኘት ስለሚኖረው መስፈርት በማስመልከት ደግሞ በአንቀፅ 6(1) ላይ ማንኛውም የስራ አመንጪ የስራው አላማና ጥራት ከግምት ስውጥ ሳይገባ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ሊያገኝ የሚችለው ስራው ወጥ ወይም ኦርጅናል ከሆነ፣ ከተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ስራውን በማውጣት ምክንያት ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚያገኝ ሲደነግግ ስራው የፎቶ ግራፍ ስራ በሚሆንበት ግዜ ደግሞ ከፍ ብለው ከተገለፁት መስፈርቶ በተጨማሪ ስራው የአንድ ስብስብ አካል ሲሆን ወይም በመፅሓፍ መልክ ሲታተሙ ወይም የስራ አመንጪውን ወይም ወኪሉን ስምና አድራሻ ሲይዙ እንደሆነ በአንቀፅ 6(2) (ሀ) (ለ) ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ስለሆነም በአገራችን የአንድን ስራ ቅጂ መብት ለማግኘት የተጠቀመበት የአፃፃፍ ወይም የፎቶ አነሳስ ወይም የዘገባ ስርጭት ቅርፅ (form) ወይም አግባብ (manner) ኦርጅናል መሆንንና ስራዎቹ የፎቶና የብሮድካስቲን በሚሆኑበት ግዜ ደግሞ ኦጅናል ከመሆን በተጨማሪ በህጉ አንቀፅ 6(2) እና (3) የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ሟሟላት እንዳላባቸው ህጉ ያስገድዳል፡፡
የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች መብቶች
የቅጅ መብት ባለቤት ብቸኛ መብቶች (exclusive rights)
ቅጂዎችን ማባዛት ወይም እንደገና ማባዛትና መሸጥ፤
ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና ከአገር ማውጣት፤
የመጀመርያውን ስራ የሚያጠናክሩ ስራዎችን መስራት፤
ስራውን ለህዝብ ማቅረብ፤
መብቱን ለሌሎች የማስተላለፍ፤
ስራውን በሬድዮና ቴሌቪዝን ማስተላለፍ ናቸው::
የቅጅና ተዛማጅ ስራ መብት የኢኮኖሚና የሞራል መብቶች በሚል ለሁለት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን በአንቀፅ 19 ላይ ያለው ስለ ቅጂ ማሰራጨት መብትና በአንቀፅ 9 ላይ በግል አገልግሎት ስራ ስለማባዛት ያለው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የቅጂ ስራ የአእምሮ ንብረት ባለቤት የሚኖሩት የኢኮኖሚ መብቶችን በማስመልከት ህጉ በአንቀፅ 7 ላይ ማንኛውም የስራ አመንጪ ወይም የአንድ ስራ ባለቤት የሚከተሉትን ለመፈፀም ወይም ሌላ ሰው እንዲፈፅማቸው ለመፍቀድ ብቸኛ መብት ይኖረዋል በማለት ስራን የማባዛት፣ የመተርጐም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር፣ ወይም ወደ ሌላ ዓይነት የመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦርጅናል ስራን ወይም ቅጅውን የማከፋፈል፣ ኦጂናል ወይም ቅጂውን ከውጭ አገር የማስገባት፣ ኦርጅናል ወይም ቅጅውን ለህዝብ የማሳየት፣ ስራን በይፋ የማከናወን፣ ስራን ብሮድካስት የማድረግ ወይም በሌላ መንገድ የማሰራጨት መብቶች ይኖሩታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆና ህጉ ለዚህ አጠቃላይ የቅጂ የኢኮኖሚ መብት ጥበቃ ሲሰጥ ለሁለም ክንዋኔዎች እንዳልሆነ በአንቀፅ 7(2) ላይ የሚደነግግ ሲሆን በ7(3) ላይ ደግሞ ዋናው አመንጪ ወይም ወራሾች ስለሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ መብት በደንብ እንደሚወሰን ደንግጓል፡፡ አንድ የቅጂ ወይም ተዛማጅ ስራ ባለቤት የሚኖሩት የኢኮኖሚ መብቶች ከፍ ብለው የተዘረዘሩት ሲሆኑ ባለቤቱ በነዚህ መብቶች ሊሰራባችው የሚችለው ወይም መብቱ ፀንቶ የሚቆየው እስከመቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ስናይ የተለያዩ አገሮች የተለያየ የጊዜ ሰሌዳን ይጠቀማሉ ለምሳሌ በአሜሪካ መብቱ ፀንቶ የሚቆየው ከ50-70 ዓመት ሲሆን በየ 28 ዓመቱ መታደስን ይጠይቃል:: ከዚያ በኋላ የህዝብ ንብረት (public domain) ይሆናል :: በጣልያን ከሞተ በኋላ ለ6 ዓመት፤በፈረንሳይ ለ14 ዓመትና በስፔን ለ80 ዓመት መብቱ ፀንቶ የሚቆይበት ህግ አላቸው:: ወደኛ አገር ህግ ስንመጣ አዋጁ በአንቀፅ 20 ላይ
20(1) " ኢኮኖሚ መብቶች የስራ አመንጪው በሂወት በቆየበት ዘመንና ከሞተ በኃላ ለወራሾቹ እስከ ሃምሳ ዓመት ፀንተው ይቆያሉ፡፡"
20(2) " በጋራ የስራ አምንጪዎች የተሰራ ስራን በሚመለከት ጉዳይ የሃምሳ ዓመቱ ግዜ መቆጠር የሚጀምረው የመጨሻው የስራ አመንጪው ከሞተበት ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡"
20(3) " የስራው አመንጪ ከሞተ በኃላ የታተመ ስራ የሃምሳ ዓመት የጥበቃ ግዜ መቆጠር የሚጀምረው ስራው ከታተመበት ግዜ ጀምሮ ይሆናል፡፡"
20(4) " አንድ ከኦዲዮቪዥዋል ስራ ውጪ የሆነ ስብስብ ስራ አኮኖምያዊ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም መጀመርያ ለህዝብ ከቀረበበት ወይም መጀመርያ ከታተመበት ጊዜ የመጨረሻ ከሆነ አንዱ ጀምሮ ለሃምሳ ዓመት ይሆናል፡፡"
20(5) " ስራው የአመንጪውን ሰም ካልያዘ ወይም በብእር ስም የታተመ ከሆነ የስራው አመንጪ የኢኮኖሚ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም መጀመርያ ለህዝብ ከቀረበበት ወይም መጀመርያ ከታተመበት ጊዜ የመጨረሻው አንዱ ጀምሮ ለ50 ዓመታት ይሆናል፡፡"
20(6) " በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (5) ከተመለከተው ግዜ በፊት የስራው አመንጪ ማንነት ከታወቀ ወይም የማያጠራጥር ከሆነ የዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) እና (2) እንደሁኔታው ተፈፃሚ ይሆናል፡፡"
20(7) "በፎቶ ግራፍ ስራ ላይ ያሉ የኢኮኖሚ መብቶች ፀንተው የሚቆዩት ስራው ከተሰራበት ግዜ ጀምሮ ለሃያ አምስት ዓመት ይሆናል፡፡"
20(7) "በኦዲዮቪዥዋል ስራ ላይ ያለ ኢኮኖሚያዊ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም ለህዝብ ከተሰራጨበት ግዜ የመጨረሻ ከሆነው አንዱ ጀምሮ ለሃምሳ ዓመታት ይሆናል፡፡"
ከዚህ አንቀፅ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው የኢኮኖሚ መብቶች ግዜው መቁጠር የሚጀምረው ሞትን ወይም የመጨረሻ ህትመትን ወይም ከሞት በኃላ ለሚወጣ ህትመት ህትመቱ ለመጀመርያ ግዜ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ መሆኑን ነው፡፡
የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች የኢኮኖሚ መብት እንደ ማንኛውም መብት ከባለቤቱ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ የሚችል መብት ነው፡፡ የሚተላለፈውም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በማስተላለፍ ወይም ፈቃድ በመስጠት ሲሆን ውሉ መመስረት ያለበትም በፅሁፍ ነው፡፡ ይሄውም መብት በሚተላለፍበት ግዜ ፈቃድ የሰጠው ወይም የመብቱ ባለቤት የሚጠቀምባቸውን ቁሳዊ ነገሮች አያጠቃልልም፡፡ የመብት ማስተላለፊያው ሰነድ መብቱ የሚተላለፍበትን ጊዜ በግልፅ ካልያዘ የመብቱ ይተላለፍልኝ ጥያቄ መቅረብ የሚችለው በ10 ዓመት ግዜ ውስጥ ነው:: የፈቃድ ይተላለፍልኝ ጥቄያው ደግሞ በ5 ዓመት ግዜ ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በሌላ አነጋገር የተጠቀሰው ግዜ ካለፈ በኃላ የይተላለፍልኝ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም ማለት ነው፡፡ (አንቀፅ 23 እና 24) በዚህ መንገድ መብቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሳይገለገልበት ከቀረና በቅጅና ተዛማጅ መብት ባለቤት መብት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደሆነ የስራው አመንጪ የመብቱን መተላለፍ ወይም ፈቃድ መስጠትን ሊሽረው ይችላል፡፡(አንቀፅ 25)
የስራው አመንጪ የኢኮኖሚ መብቶች ባለቤት ቢሆንም ባይሆንም የሞራል መብቶች አሉት፡፡ እነዚህም:-
ወቅታዊ ሁኔታን በብሮድካስት አማካይነት ለመዘገብ ባጋጣሚ ወይም በድንገት ከተካተተ ስራ ውጪ የስራ አመንጪነቱ እንዲታወቅ የመጠየቅ መብት አለው ፡፡ (አንቀፅ 8(1) (ሀ))
ሳይታወቅ የመቆየት ወይም የብእር ስም የመጠቀምና ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጐድፍ የስራ መዛባት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም መብት ይኖረዋል፡፡ (አንቀፅ 8(1) (ለ)(ሐ))
ስራን የማሳተም ሞራላዊ መብት ይኖረዋል፡፡ አንቀፅ 8(1) (መ))
አንድ የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች ባለቤት በአንቀፅ 8 ላይ የተዘረዘሩትን የሞራል መብቶች ለወራሾች ወይም የስጦታ ተቀባዮች ካልሆነ በቀር በሂወት እያለ እነዚህን መብቶች ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገኖች ሊያስተላልፋቸው የሚችል መብቶች አይደሉም፡፡ (አንቀፅ 8(2)) የሞራል መብት የሚወረስ ወይም በስጦታ የሚሰጥ ቢሆንም የስራው አመንጪ በሂወት ባለበትና መብቱ ፀንቶ ባለበት ግዜም ሆነ ወራሾች ወይም የስጦታ ተቀባዮቹ በመብቱ የተጠቃሚነት መብታቸውን ትተነዋል ብለው ለማመልከት ይችላሉ፡፡ የሞራል መብቶች ፀንተው የሚቆዩበት የኢኮኖሚ መብቶች ፀንተው ከሚቆዩበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንቀፅ 8(3) (4))
አንድን የቅጂ መብት የተሰጠበትን ንብረት ፍትሓዊ በሆነ መንገድ መገልገልን (fair use) በማስመልከት የተለያዩ አገሮች የተለያየ አሰራርን የሚከተሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሚሰሩበት መለክያን ወስደን ስናይ፤-
የተጠቀመበት አላማና ባህሪው (purpose & characterstic)
የቅጂ መብቱ ተፈጥሮ (nature)
ከስራው የቱን ያህል ነው የተወሰደው (what amount or propertion of the whole work was taken)
በቅጂ መብቱ ላይ በገበያ የሚኖረው ዘላቂ ውጤት (the effect of the use upon the the potential market for the value of the copyrighted work) የሚሉ ናቸው::
በካናዳ ለግል አገልግሎት አባዝቶ መጠቀም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የተፈቀደ ሲሆን በአውስትራሊያ አባዝቶ መጠቀም የሚፈቀደው ለምርምር፤ ለጥናት፤ ተችቶ ለመፃፍ ፤ ለዜና ሪፖርትና የህግ ምክር አገልግሎት ለመስጠት ሲሆን ብቻ ነው:: በአሜሪካ ህግ 10 ቀጂ ማባዛት ለንግድ ስራ እንደተባዛ ይቆጠራል ከሚል በቀር ከዚያ በታች ማባዛት የተፈቀደ ስለመሆኑ በግልፅ የሚለው የለም:: የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ህግም በአንቀፅ 9(1) ላይ አንድ ቀጂ (a single copy) ለግል አገልግሎት ሲባለ ማባዛት የሚፈቅድ ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ህግ አለም አቀፍ መመዘኛ (International standards) ያሟላና ለስራ አመንጭነት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ሆኖ እንደ ሌሎቹ የአእምሮ ንብረት መብቶች ሊተላለፍ የሚችልና የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለው የኢኮኖሚና የሞራል መብት የሚያስገኝ ንብረት ነው፡፡
የመብት ጥሰት መፍትሔዎች (Remedies)
የቅጅና ተዛማች መብቶች ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 401/96 ሶስት ዓይነት መፍትሔዎችን የሚሰጥ ሲሆን እነሱም የፍ/ብሔር መፍትሔ፤ የደንበር ላይ እርምጃና የወንጀል ቅጣት ናቸው፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔ
የፍታብሔር መፍትሔን በተመለከተ ስልጣኑ የተሰጠው ለመደበኛ ፍ/ቤት ሰለሆን ፍ/ቤት የመብት ጥሰት ያለመሆኑን ከማረጋገጡ በፊትና ካረጋገጠ በኃላ ሊወስድ ከሚችለው እርምጃ ዓንፃር በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: ይሄውም ከመረጋገጡ በፊት ሊወሰድ የሚችለው በጊዚያዊነት የእግድ ትእዛዝ (interim injuction) መስጠት ሲሆን የመብት ጥስት መኖሩ ከተረጋገጠ ግን
ባለመብቱ ያወጣውን ወጭና ለደረሰበት ጉዳት ቁሳዊና ሞራላዊ ካሳ እንዲከፈለው ይወሰናል::
ያለ ባለመብቱ ፈቃድ እንዳይባዛ ወይም ከአገር ውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተባለን ነገር ያስገባ ወይም ያሰራጨ ካለ እንዲወረስ ያዛል ::
ከቅጅ መብት ጋር የተያያዙ የሂሳብ መግለጫዎች ሰነዶች፤ የንግድ ስራ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ወረቀቶችን ለመስራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችና እሽጉች እንዲያዙ ትእዛዝ ይሰጣል::
አመልካች ከካሳው በተጨማሪ ያለአግባብ በልፅጓል ሲል የከሰሰ እንደሆነ ፈቃድ ቢሰጠው ሊከፍል ይችል የነበረውን ያህል እንዲከፍለው ይወስናል ::
ባለቤቱ ከተጠርጣሪው የተገኘውን ትርፍ ብቻ እንዲከፈለው በጠየቀ ጊዜ እንዲከፍለው መወሰን፡፡ ተከሳሹ የተጠየቀው ትርፍ በሌላ ገበያ የተገኘ ሂሳብ ነው የሚል ከሆነ የማስረዳት ሸክም በተከሳሹ ላይ ይወድቃል፡፡
ይሄውም ለባለመብቱ የሚከፈለው ካሳ ለደረሰበት ጉዳትና በመጣሱ ሌላው ወገን ያገኘውን ትርፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይሆናል፡፡
የቅጅ መብት በመጣሱ ምክንያት የሚከፈል ሞራል ካሳ ከ 100.000 ብር ያላነሳ ሆኖ የደረሰውን ጉዳት መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን መብት የጣሰው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ባለማወቅ ወይም ሊያውቅ የሚችልበት በቂ ምክንያት የሌለው ከሆነ ፍ/ቤቱ ያገኝውን ትርፍ ብቻ እንዲመልስ ሊወሰን ይችላል፡፡
ቅጅዎችን ወይንም ጥቅሎቹን በቅጅ ባለመብቱ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ወይም እንዲወገዱ ወይም በሌላ ተገቢ አኳኋን እንዲጣሉ ለማዘዝ ይችላል፡፡ ይህ ቅጅዎችን በቅን ልቦና በያዘ 3ኛ ወገን ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ (አንቀጽ34)
የደንበር ላይ እርምጃ
በቅጅ ባለመብቱ በሚቀርብለት ማመልከቻ የጉምርክ ባለስልጣን ቅጅዎችን በቁጥጥር ስር ያደርጋል::
ይህን እርምጃ መውሰዱ ለአመልካቹ ወይም የዕቃው ባለቤት ወድያውኑ ያሳውቃል::
አመልካቹ በ10 ቀናት ውስጥ ህጋዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ ካልቻለ እቃውን ለመያዝ የተወሰደው እርምጃ ይነሳል ፡፡
አመልካች ያቀረበው ማመልከቻ ህጋዊ መሰረት የሌለው ሲሆን በመያዙ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናል::
በፍ/ቤቱ ትእዛዝ መሰረት የጉምሩክ ባለስልጣን መብት የጣሰን ዕቃ መውረስ ይችላል፡፡ (አንቀጽ35)
የወንጀል ቅጣት
የወንጀል ህጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር ሆን ብሎ የቅጅ መብትን የጣሰ ሰው ከ 5 ዓመት ባላነሰ እና ከ10 ዓመት ባልበለጠ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
የወንጀል ህጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር በከፍተኛ ቸልተኝነት በዚህ አዋጅ ጥበቃ የተደረገላቸው የቅጅ መብቶችን የጣሰ ከሆነ ከ 1ዓመት በማያንስና ከ 5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሰራት ይቀጣል፡፡
አግባብነት ባለው ግዜ ወንጀሉን ለመፈጸም ያገለገሉዕቃዎችን መሳሪያዎችን መብት የጣሱ ዕቃዎችን መያዝ፤ መውረስና ማውደምን ይጨምራል፡፡ (አንቀጽ36)
ስለዚህ የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ህግ አለም አቀፍ መመዘኛ (International standards) ያሟላና ለስራ አመንጭነት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ሆኖ እንደ ሌሎቹ የአእምሮ ንብረት መብቶች ሊተላለፍ የሚችልና የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለውና የአኮኖሚና የሞራል መብት የሚያስገኝ ስራ ነው፡፡ የመብቱ ተጠቃሚዎች የፍታብሄር መፍትሄ የሚያገኝ መሆናቸው በተጨማሪ የመብቱ ጥሰት የወንጀል ተግባርን ያካተተ ከሆነ በወንጀል ተጠያቂ የማስደረግን መብት የሚያጐናፅፍ ነው፡፡