- Details
- Category: Property Law
- Hits: 13422
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ
የምዝገባ አላማዎች
በኢትዮጵያ የፍ/ብሄር ፍትህ ስርዓት የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በዜጎች የንብረት መብት ጥበቃ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም እምብዛም ፍታብሄር ህጉ በሚደነግገው መሰረት ሲሰራበት አይታይም:: የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን በማስመልከት የተለያዩ አገሮች የተለያየ አሰራር ይከተላሉ:: ለምሳሌ ፈረንሳይ transcription የሚባለውን እሰራር ስትከተል አውስትራልያ matriculation የሚባለውን አሰራር ትከተላለች:: በአገራችን ያለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ስር’ዓትም በተዋዋይ ወገኖች የቀረበውን ሰነድ ቅጂ ተቀብሎ የመዝገቡ አካል የማድረግ አሰራርን የሚከተል በመሆኑ የ transcription አሰራር የሚትከተል ነው ማለት ይቻላል :: የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ምዝገባን በሚመለከት በፍ/ብሄር ህጉ ከቁጥር 1553-1646 ባሉ ድንጋጌዎችና በፍ/ብ/ህ/ቁ በ1723፤ 2878 እና 3052 ተደንግጐ የምናገኘው ሲሆን ህጉ ለማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ልዩ ጥበቃ መስጠት የፈለገበት ምክንያት እነዚህ ንብረቶች ባለይዞታው መብቱን ሲያገኝ ወይም በሆነ ምክንያት ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገን በሚያስተላልፍበት ወቅት የመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው መንግስታዊ አካል ካልተመዘገበ ህግ ፊት የሚፀና መብት እንዳይኖረው በማድረግ ዜጐች በዚህ ግዙፍነት ያለው ንብረት ያላቸው መብት ከፍላጐታቸው ውጪ በሆነ መንገድ እንዳያጡ ጥበቃ ለመስጠት ነው፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በርካታ የራሱ አላማዎች ያሉት ቢሆንም ዋና ዋናዎቹን ወስደን ያየን እንደሆነ:-
1.ዜጐች በማይንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው መብት በተለይ ወደ ሌላ ወገን በሚያስተላልፉበት ግዜ በፈቃዳቸው የተከናወነ መሆኑን ከመዝጋቢው አካል ፊት ቀርበው የሚከናወን በመሆኑ ንብረታቸው ከዚህ አሰራር ውጭ የማያጡ መሆኑን ተገንዝበው ሙሉ ዋስትና እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
2.የማይንቀሳቀስ ንበረትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ የሽያጭና ግዢ ውሎችን በምዝገባው አስረጂነት የኢኮኖሚ ግንኙነትቱን የተቀላጠፈና አስተማማኝ እንዲሆን በማድረግ በተዋዋዮቹ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖርና መጥፎ ልቦና ቢፈጠርም እንኳ አስተማማኝ ማስረጃ ሆኖ ስለሚያገለግል ሌላውን ወገን ከመጀመርያው ጀምሮ አስቦበት እንጂ ዘው ብሎ እንዳይገባ የማድረግ አላማ (refraining objective) ያለው ነው፡፡
3.የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 ይዘት አንፃር ስንመለከተው የምዝገባው ውጤት ውሉ ዋጋ እንዲኖረው (ad validitatum) የሚያስፈልግ እንጂ ለማስረጃ ብቻ (ad probtionum) የሚያስፈልግ ባለመሆኑ ከህጉ በስተጀርባ ያለው (rationale) ህዝባዊ ፖሊሲ ለማይንቀሳቀስ ንብረት መብት ከፍተኛ ጥበቃ የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
-
- 4.የማይንቀሳቀስ ንብረት ካለው የኢኮኖሚ ፋይዳ በመነሳት ህግ ልዩ ጥበቃ ሲያደርግለት የንብረት ባለይዞታነት መብት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በምናስተላልፍበት ግዜ በንብረት መዝገብ ላይ ንብረቱ በመያዣ ተይዟል አልተያዘም? በዕዳ ታግዷል ወይስ ነፃ ነው? ንብረቱ የግል ነው ወይስ የጋራ ንብረት? ንብረቱ የተገኘበት አግባብ በግዢ፣ በሊዝ፣ በውርስ፤ በስጦታ፣ በምሪት? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ዙርያ ለሶስተኛ ወገኖች ግልፅ የሆነ መረጃ (information) የመስጠት አላማም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የምዝገባው መኖር:-
የሰነድ መሰረዝ መደለዝን ያስቀራል::
ማጭበርበርን ይከላከላል::
በሀሰት የሚዘጋጁ ሰነዶችን ይከላከላል::
በንብረት ጥቅም ላይ ሊመጡ የሚችሉትን አደጋዎች ይከላከላል::
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ አላማ ከንብረት ዋስትና ጋር፣ ከህዝባዊ ፖሊሲ፤ ከማስተላለፊያ ስርዓትና የሶስተኛ ወገኞች መብት አንፃር ሲታይ የኢኮኖሚ ፋይዳው ሳንካ ያልበዛበት ምቹና የባለቤትነት ዋስትና ያለው ህበረተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ከፍ/ብሄር ህግ አንፃር
ቀደም ሲል እንደተገለፀው የማይንቀስቀስ ንብረት ምዘገባን በማስመልከት በፍ/ብሄር ህጉ ከቁጥር 1553-1646 ባሉ ድንጋጌዎችና የማንቀሳቀስ ንብረትን ከአንዱ ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍን ስርዓት መሰረት በማድረግ በፍ/ህ/ቁ. 1723፤2878 እና 3052 ላይ ተደንግጐ የምናገኘው ነው፡፡ የፍ/ብሄር ህጉ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በንጉሱ ግዜ የነበረውን አደረጃጀት ታሳቢ በማድረግ በየአውራጃው እንደሚቋቋምና ሁለት የተለያዩ መዘገቦች ማለትም አንዱ የባለቤትነት መዝገብና ሌላው የመያዣ መዝገብ እንደሚኖር ይደነግጋል፡፡ እነዚህ መዛግብት ከቦታ ቦታ መዘዋወር እንደማይፈቀድና ለህዝብ ግልፅ መሆን አለባቸው የሚል ለሶስተኛ ወገኖች ጥበቃ የሚሰጥ መርህን የተከተለ ነው፡፡
የባለቤትነትን መብት መሰረት በማድረግ የሚቋቋም መዝገብ የአንድ ወይም ብዙ ባለመብቶች መብት ለማወቅ፣ ለማስተላለፍ፣ ለመለወጥ፣ ለማስቀረት በሂወት ወይም በሞት ግዜ የተደረጉ ውሎችን በግልፅ ይሁን በግል የተደረጉ በመዝገቡ መፃፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም በባለሃብትነት መዝገቡ ላይ የተደረገ ሽያጭ፣ ኑዛዜ፣ ስጦታ፣ የኑዛዜ ስጦታ መሰረት ያደረጉ ውሎች እና እነዚህ ውሎች የተሰረዙበት፣ የተሻሩበት ወይም የሚያስቀሩ በፍርድ ቤት የተሰጡ ፍርዶች ካሉ እንዲሁም በመፋለም ክስ ላይ ፍ/ቤት የሰጠው ፍርድና ገንዘብ ጠያቂዎች ባስያዙት የማይንቀሳቀስ ንብረት የሐራጅ ሽያጭ ላይ የተሰጡ ፍርዶችን በመዝገቡ መፃፍን እንደ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአላባ ጥቅምን መስጠት፣ መቀነስ፣ መሰረዝና የንብረት አገልግሎት (servitude) ለማቋቋም፣ ለማሳወቅ፣ ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት የሚደረጉ ፅሁፎች በመዝገቡ መፃፍ ይኖርባቸዋል፡፡
በማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መዝገብ ላይም የመያዣ መብት ለማቋቋም፣ ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት የሚደረጉ ፅሁፎችና የመያዣ ዋስትና ለመረጋገጥ የተፃፈውን ፅሁፍና የዚህ መብት በህግ የታወቀበትን የቅደም ተከተል መብት ለማስተላለፍ የተፃፉትን ፅሁፎች ያካተተ መሆን አለበት፡፡
ከፍ ብሎ እንደተገለፀው የፍ/ብሄር ህጉ ሁለት ዓይነት የንብረት ምዝገባ እንደሚኖር ከመደንገጉ በተጨማሪ የአመዘጋገብ ስርዓቱን በማስመልከት የህዝብ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እና የጋራ ንብረት በሚል ይከፍላቸዋል:: አንድ የህዝብ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እላዩ ላይ ግዙፍነት ያላቸው እንደ ህንፃ ወይም ተክሎች ከሌሉበት በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ መመዝገብ እንደሌለበት ሲደነግግ የጋራ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ምዝገባ በማስመልከት በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ የእያንዳንዳቸው ሰም ያለበት በተለያየ ገፅ ላይ መመዝገብ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ንብረቱ የተፈጥሮ ሰው ሃብት በሆነበት ግዜ እንዲመዘገብለት ጥያቄ የቀረበለት ወገን፣ የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ለመለየት አስፈላጊ ከሆነ እንደ የቦታው አዋሳኝ፤ ንብረቱ የሚገኝበት የአስተዳደር ክልል፣ ወዘተ የመሰሉ መግለጫዎች፣ የንብረቱ ባለቤት ሙሉ ስም፣ የባለሀብትነት መብት ማረጋገጫ ሰነዶች ዓይነት በማጣቀሻ ቁጥራቸው እና ተያያዥነት ያላቸው ማጣቀሻ ፅሁፎች ከነቁጥራቸው ይመዘግባል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረቱ የህጋዊ ሰውነት መብት ያለው ተቋም በሚሆንበት ግዜ ደግሞ የድርጅቱ መጠርያ ስም በመዝገቡ ላይ መመዝገብ ይኖርበታል፡፡
የምዝገባ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኃላ ንብረት መዝጋቢዎች ፍ/ብ/ህ/ቁ 1562 እና 1563 በሚያዘው መሰረት ባለሃብቶቹ ስለንብረታቸው ምዝገባ በማስመልከት መግለጫ እንዲሰጣቸው በሚጠይቁበት ግዜ የተፈላጊው ሰነድ ግልባጭ መሰጠት አለባቸው፡፡ በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብቶች ይህን ሰነድ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ይህም ጠቅለል ባለመልኩ ሲታይ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ የአንድን ንብረት ባላቤትነት (ባለይዞታነት) ከማረጋገጡ ባሻገር በዚህ መብት የሚከናወኑ ስራዎችን እንደ የባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ መብት፤ ዕዳና መያዣ የመሳሰሉ በመያዝ ሶስተኛ ወገኖች ከባለንብረቱ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተና አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ እነዚህ ለህዝብ ግልፅ መሆን ያለባቸው መዛግብት የራሳቸው የአመዘጋገብ ስርዓትና ፎርም ያላቸውና ጥንቃቄን የሚጠይቁ የመሆናቸውን ያህል የሚከናወኑት በሰዎች እንደመሆኑ ለተለያዩ ግድፈቶችና ከመጥፎ ልቦና በመነሳት ችግር ለሚፈጥሩ የግል ጥቅም አሳዳጆች በእጅጉ የተጋለጡ በመሆናቸው በማስረጃነት በሚቀርቡበት ጊዜ የፍትህ አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ሊመዝኗቸው ይገባል፡፡
የምዝገባ ፅሁፎችን ማቃናትና መሰረዝ
ከአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ጋር የተያያዘ የህትመት ጉድለት ካለ ዓቃቤ መዝገቡ ማቃናት የሚችል ቢሆንም ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1622 ከሚያዘው ውጭ የሚደረግ ማቃናት ግን ፈራሽ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ውጭ የሚደረግ የማቃናት ስራ መከናወን ያለበት በፍ/ቤት ትእዛዝ ብቻ ነው፡፡ የማቃናቱ ስራ ሲከናወን የነበረውን ቃል መሰረዝ የግድ እንደሚል ሁሉ ተሰርዟል የሚል ቃልም ይፃፍበታል፡፡ የዚህ መቃናት ህጋዊነት ለማረጋገጥ በፍ/ቤት የተሰጠው ፍርድ ከአስረጂው ጋር በቤተመዛግብት መቀመጥ አለበት፡፡ የዚህ መቃናት ህጋዊ ውጤት መቆጠር የሚጀምረው የማቃናቱ ስራ ከተከናወነበት ቀን ጀምሮ ሲሆን መቃናቱ ዋጋ አልባ የሚሆነው በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1628 የተዘረዘሩት መስፈርቶች ሳይሟሉ የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ እነዚህ አንድን ምዝገባ ዋጋ አልባ ወይም ፈራሽ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በተሟሉበት ሁኔታ ማንኛውም ባለመብት ነኝ የሚል ወገን የተደረገውን መቃናት እንዲሰረዝለት ለፍ/ቤት ሲያመለክት ፍ/ቤት መቃናቱ እንዲሰርዝ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደዚህ በሆነበት ግዜ በታተመው ፅሁፍ ላይ የተሰረዘበትን ቀንና ትእዛዙን የሰጠው ፍ/ቤት ሰም በሁለት የተመሳቀሉ መስመሮች ማሃል ተሰርዟል የሚል ቃል ይፃፍበታል፡፡ ቀደም ሲል ሁለት መዘገቦች እንደሚኖሩ እንደተጠቀሰው ሁሉ የመያዣ መብትን መሰረት በማድረግ ለተወሰነ ግዜ የተደረገ ምዝገባ በሚሆኑበት ግዜና ምዝገባው በፍ/ብ/ህ/ቁ 3058(2) መሰረት ካልተራዘመና በፍ/ብ/ህ/ቁ 3068(1) መሰረት አስር ዓመት ካለፈው የአስራረዙ ስርዓት ፍ/ብ/ህ/ቁ.1632 በሚያዘው መሰረት ሲሆን ይሄውም ለመሰረዝ የፍ/ቤት ትእዛዝ ሳያስፈልገው ባለስልጣኑ በራሱ ሊሰርዘው ይችላል፡፡ ስለሆነም ዓቃቤ መዝገቡ አንድን የህትመት ቃል መሰረዝና ማቃናት የሚቻል ቢሆንም ህጉ ከሚያዘው ውጭ ማቃናት ስርዙን ዋጋ አልባ ወይም ፈራሽ ሊያደርገው እንደሚችልና ለማቃናት የፍ/ቤት ትእዛዝ መኖርን እንደሚጠይቅ ለመሰረዝም የማይንቀሳቀስ ንብረትን መሰረት ያደረገ መያዣን የሚመለከት ካልሆነ በስተቀር ስርዙ መከናወን ያለበት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1630 መሰረት በፍርድ ቤት ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ውጤት
የማይንቀሳቀስ ንብረት መመዝገብ በህግ ፊት ለሚነሳ ክርክር የማስረጃነት፣ የንብረቱን አስተዳደር የሚመለከት ለፍ/ቤት፣ 3ኛ ወገኖች፣ ባለጥቅሞች መረጃ የመስጠት ውጤት ያለው ሲሆን ከነዚህ ጠቅለል ያሉ ውጤቶች በተጨማሪ ዝርዝር ውጤቶችም ያሉት ነው፡፡ ከነዚህ ጥቂቶቹን ወስደን ያየን እንደሆነ:-
በማይንቀሳቀስ መዘገብ ላይ አንድ ፅሁፍ በመፃፍ ብቻ ሌላው ወገን የይርጋ ጥያቄ እንዳያነሳ አይከለክለውም:: ይህ የሚሆንበት ምክንያትም የዚያ ፅሁፍ መመዝገብ ብቻ የባለመብትነት መብት ስለሚያስገኝ ወይም ስለሚያሳጣ ነው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1637 እና 1639)
አንድ ተከራካሪ ወገን በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ የተመዘገበውን ፅሁፍ አላውቅም በማለት ብቻ በመከላከያነት አቅርቦ ሊከራከር አይችልም:: ሆኖም ግን ሊያውቅ ያልቻለው በአመዘጋገቡ ላይ የአቃቤ መዝገቡ ወይም በመንግስት ጉድለት ምክንያት ከሆነ ሃላፊነቱን የሚወሰዱት እነሱ ይሆናሉ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1640)
በሁለት ፅሁፎች ክርክር ቢነሳ መጀመርያ በማይንቀሳቀስ መዘገብ ያስመዘገበው ሰው የባቤትነት መብቱን የሚያገኝ ሲሆን ሁለቱ የተመዘገቡት በአንድ ቀን በሚሆኑበት ግዜ በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ የማንኛቸው ቁጥር እንደሚቀድም በማየትና የቀደመውን ቁጥር በመውሰድ መብቱ የቀደመ ቁጥር ላገኘው ሰው ይሰጣል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ1642)
የባለቤትነት፣ ግዙፍነት መብት የሚያረጋግጡ፣ የሚያስተላልፉ፣ የሚለውጡ ወይም የሚያስቀሩ ፍርዶች የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚገኝበት ስፍራ ባለ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዘገብ መመዝገብ ይኖርበታል ካልተመዘገበ ውጤት አይኖረውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1643)
በመጥፎ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ ማስመዘገብ በዚህ መመዝገብ ጉዳት ደርሶብኛል የሚል ወገን የደረሰበት ጉዳት መሰረት በማድረግ የጉዳት ኪሳራ ከሚጠይቅ በስተቀር ምዝገባውን ዋጋ አልባ የማድረግ ውጤት አያስከትልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1644)
የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመዝገብ ባለመመዝገቡ ምክንያት ሶስተኛ ወገኖች መቃወሚያ ሊሆናቸው ባልቻለበት ጊዜ ማናቸውም ሰው ለሶስተኛ ወገኖች የሚሆን መብት ካላስመዘገበው ሰው ሊያገኝ አይችልም፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ መብቱን ያገኘበት ሰነድ ከማስመዝገቡ በፊት መብቱን የሰጠው ሰው ያንን የማይንቀሳቀስ ንብረት መብት ያገኘበትን ሰነድ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1645)
የማይንቀሳቀስ ንብረት መዘገብ አቃቤ መዘገብ በባለሀብቱ የቀረበውን መዝግቦ ስለተደረገው ምዝገባ በ8 ቀን ግዜ ውስጥ ግልባጩን የማሳወቅ ግዴታ ያለው ሲሆን ይህን ባለማደረጉ በሶስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሃላፊ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ1646)
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን ከፍ/ብሄር ህጉ አንፃር ስናየው በርካታ ጥቅሞች የሚያስገኝ፣ መብቶችና ግዴታዎችን የሚጥል የራሱ የሆነ ህጋዊ ውጤት ያለው ነው:: ያለው አሰራር የቱን ያህል የህጉን አካሄድ የተከተለ ነው ብለን ያየን እንደሆነ ግን በመዝጋቢ አካልም ሆነ በፍ/ቤቶች አካባቢ እምብዛም ሲሰራበት የሚታይ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና በንብረት መብትና ግዴታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን በማጤን ስራ ላይ ልናውለው የሚገባን ነው፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 456/97 አንፃር
1. የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቓቀምን መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 የገጠር መሬት ምዝገባን መሰረት በማድረግ በአንቀፅ 6/1/ ላይ
በግል፣ በወል፣ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይዞታዎች ያሉ የገጠር መሬቶች እንደ ሁኔታው ባህላዊና ዘመናዊ የቅየሳ መሳሪያዎችን በመጠቀም የመሬት ስፋታቸውና የለምነት ደረጃቸው በክልልና በየደረጃው በተቋቋሙ የመረጃ ማእከላት እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ ሲል በአንቀፅ 6/5/ ላይም
የገጠር መሬት በማን ይዞታ ስር እንደሚገኝ ከማን መሬት ጋር እንደሚዋስን፣ ደረጃው ምን ዓይነት እንደሆነ፣ ለምን አገልግሎት እንደሚውልና ባለይዞታው ምን መብትና ግዴታዎች እንዳለበት የሚገልፅ መረጃ ተመዝግቦ አግባብ ባለው ባለስልጣን እንዲያዝ ይደረጋል፡፡
በማለት የገጠር መሬት የማይንቀሳቀስ ንብረት እንደመሆኑ መጠን በምዝገባ በአርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መካከልና መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በአጠቃላይ በአጐራባች መሬት ሊነሳ የሚችለውን ውዝግብና ከባለይዞታነት መብት የንብረት መፋለም ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በሚቀርፍ መልኩ የመሬት ባለይዞታነት መብት ምዝገባ እንደሚከናወን ይደነግጋል:: ይህን ምዝገባ መሰረት በማድረግ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር እንደሚሰጥና የማይንቀሳቀስ ንብረቱ የጋራ ንብረት በሚሆንበት ግዜም የሁሉንም ባለሃብቶች ስም ዘርዝር በመያዝ የጋራ ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጥ በአንቀፅ 6(3) (4) ላይ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አዋጅ መገንዘብ የሚቻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 40፣ 51(5)፣ 55(2) (ሀ)ን 85(5)ን መርሆች በመከተል በአሁኑ ጊዜ የዜጐች የገጠር መሬት ባለይዞታነት መብት ስለሚመዘገብበት ሁኔታ ከፍ/ብሄር ህጉ ለየት ባለ ሁኔታ ማለትም በርስትንና የመሬት ባለቤትነት መብት ምትክ በመሬት ባለይዞታነት የመጠቀም መብትን መሰረት በማድረግ የተደነገገ ህግ መሆኑን ነው፡፡
2. የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት እውቅና ያገኘውን መብት ተግባራዊ በሚያደርግ መልክ የአርሶ አደሩን፣ ከፊል አርብቶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በመሬት የባለይዞታነት መብት በሚያረጋግጥ መንገድ የወጣ ህግ በመሆኑ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ግንኙነትን ታሳቢ በማድረግ የአገሪቱ ዜጎች የመሬት አኩል ተጠቃሚነት መብት ያረጋገጠ ህግ ነው:: በፍ/ብሄር ህጉ ካለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጠቃሚነት መብትም ለየት ባለ መልኩ የወጣ ነው፡፡ በራሱ ውጤት ባይሆንም የዘላቂ ልማት መሳርያ በመሆን የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ከሚወሰኑ የልማት ግብአቶች አንዱ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በምዝገባ ጥበቃ እንዲያገኝ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም ይሄው ነው፡፡
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በዜጐች መካከል የሚከሰተውን ውዝግብ ከማስወገድ ተልእኮው በተጨማሪ ውዝግብ በሚነሳበትም ግዜ በአስተማማኝና መንግስታዊ አካል በሚሰጠው ማስረጃ ላይ ተመስርተው ዳኞች ፍትህ እንዲሰጡ የሚያስችል በመሆኑ ዜጐች በንብረት ላይ ያላቸውን ያለመደፈር መብት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዲመሰረት የሚያደርግ ነው:: በመሆኑም ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው ብቻ ሳይሆን በማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን ለማረጋገጥም ሆነ በማንኛውም ህግ በሚፈቅደው አግባብ ለማስተላለፍ ምዝገባ ማከናወን በህግ የተጣለ ግዴታም ጭምር ነው፡፡