- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 14045
በሥራ ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች የሚሰጡ ክፍያዎች
በልዩ ግዴታ ምክንያት የሚሰጡ አገልግሎቶች
የስራ ጉዳት በደረሰ ጊዜ አሠሪው ልዩ ግዴታዎች አሉበት፡፡ ይኸውም በጊዜው
- የህክምና ዕርዳታ መሥጠት
- ተስማሚ በሆነ የመጓጓዣ ዘዴ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የህክምና ጣቢያ ማድረስ እና የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የሥራ ላይ ጉዳት መድረሱን ማሳወቅ እንዲሁም ጉዳቱ
- እንዲሁም ጉዳቱ ሞትን ባስከተለ ጊዜ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጪውን መሸፈን ናቸው፡፡
የሕክምና አገልግሎቶች
- ከፍ ሲል ከተገለፁት ክፍያዎች በተጨማሪ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የሚያስፈልገው የጠቅላላ እና የልዩ ሕክምና እንዲሁም የቀዶ ህክምና ወጪዎች፣ የሆስፒታል እና የመድኃኒት ወጪዎች፤ የማናቸውም ሰው ሰራሽ ምትክ ወይም ተጨማሪ አካሎችና የአጥንት ጥገና ወጪዎች በሙሉ በአሰሪው ይሸፈናሉ፡፡ ይህ ሲሆን የህክምና አገልግሎቱ ቦርድ በሚሰጠው ውሣኔ መሰረት ካልሆነ በቀር አገልግሎት መሰጠቱ የሚቋረጥ አይሆንም፡፡
ልዩ ልዩ የጥሬ ገንዘብ ክፍያዎች
ሀ. ለጊዚያዊ የአካል ጉዳት የሚፈፀም ክፍያ
ጊዜያዊ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ጉዳቱ እስከሚወገድበት ጊዜ ድረስ በየጊዜው የሚፈፀምለት ክፍያ አለ፡፡ “ጉዳቱ እስከሚወገድበት ድረስ” የሚለው ሐረግ በየጊዜው የሚፈፀመው ክፍያ ከአንድ ዓመት የበለጠ እንደማይሆን በአንቀጽ 108(1) እና 108(3)(ሐ) ከተገለፀው አንፃር እንድምታው ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ “ጉዳቱ እስከሚወገድበት ድረስ” የሚለው ጊዜያዊ የአካል ጉዳት በባህሪው ጉዳቱ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚዘልቅና ሠራተኛው የመሥራት ችሎታውን መልሶ የሚያገኝ ስለመሆኑ ግምት መወሰዱን፤ ከዚህ በላይ የተራዘመ እንደሆነ ግን አግባብ ባለው ባለሥልጣን ወይም በአንዱ ወገን ጠያቂነት በድጋሚ በሚደረገው ምርመራ ውጤቱ ታይቶ የተጐጂ የጉዳት መጠን ደረጃ ወደ ሌላው ደረጃ በመሻገርም ቢሆን ክፍያው በዚያው አግባብ ሊፈፀምለት እንደሚችል ወይም እንደሚፈፀምለት የሚያመለክት ነው ብሎ ማሰብ ትክክል ሳይሆን አይቀርም፡፡ በየጊዜው የሚደረገው ክፍያ የተባለውም
- ጉዳቱ ከደረሰ ጀምሮ ላሉት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ሠራተኛው ያገኝ የነበረውን የአመቱ አማካይ ደመወዝ ሙሉ ደመወዝ
- ከዚህ በኃላ ላሉት ሦስት ወራት ደግሞ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ሠራተኛው ያገኝ የነበረውን የአመቱን አማካዩ ደመወዝ 75% እና
- ለቀሪዎቹ ስድስት ወራት ጉዳቱ ከመድረስ በፊት ሠራተኛው ያገኝ የነበረው የአመቱ አማካይ ደመወዝ 50% ነው፡፡
ይህ በየጊዜው የሚደረገው ክፍያ የሚያቆመው
- ሠራተኛው የደረሰበት ጉዳት የተወገደለት መሆኑን ሐኪም ሲያረጋግጥ
- ሠራተኛው የጉዳት ጡረታ ወይም ዳርጐት በሚያገኝበት ቀን
- ሠራተኛው ሥራ ለመሥራት ካቆመበት ዕለት ጀምሮ አሥራ ሁለት ወር ሲሞላው ነው፡፡
የተገለፁት ሁኔታዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ተጐጂው በማናቸውም ጊዜ ምርመራ እንዲደረግለት ሲጠይቅ እምቢተኛ ከሆነ፣ ቸል ያለና ምርመራውን ያደናቀፈ፣ ያለበቂ ምክንያት እንዲጓተት ያደረገ፤ ከጉዳቱ የሚድንበትን ጊዜ ለማራዘም በማሰብ አጉል ጠባይ ያሳየ ወይም ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰራተኞች የወጣውን መመሪያ የተላለፈ እንደሆነ በየጊዜው የሚደረግለት ክፍያ ይቋረጣል፡፡ ለጥያቄው ተገቢ መልስ እስኪሠጥም ይኸው ይቀጥላል፡፡ በዚሁ ግፊት ምክንያትም ፍቃደኛ ሲሆን በተቋረጠበት ጊዜ ያልተከፈለውን ክፍያ መልሶ አያገኝም፡፡ [አንቀጽ 107 (2) (3)]
ለዘላቂ ሙሉ ወይም ከፊል የአካል ጉዳት የሚፈፀም ክፍያ
ለዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት የሚፈፀመው ክፍያ በሕብረት ሥምምነት በሌላ አኳኃን ካልተወሰነ በቀር በአሠሪና ሠራተኛው አዋጅ መሰረት ለሚሸፈኑ የመንግሥት ድርጅት ሠራተኞች አሠሪው የገባው የመድኅን ዋስትና ካለ በዚሁ መሰረት ክፍያው ይፈፀማል፡፡ ድርጅቱ መድኀን ያልገባ እንደሆነ ደግሞ በመንግሥት የጡረታ ሕግ መሠረት ክፍያው ይፈፀማል፡፡ ይህ አከፋፈል በመንግሥት የጡረታ ህግ ለማይሸፈኑ ሠራተኞችም ተፈፃሚ ነው 109 ፡፡ ልዩነቱ በመንግሥት የጡረታ ህግ የማይሸፈኑት ተጐጂ ሠራተኞች ክፍያው የሚፈፀምላቸው በአንድ ጊዜ (in lump sum) መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ክፍያው በተገለፀው ሁኔታ በአንድ ጊዜ የሚከፈል በሚሆንበት አጋጣሚ የጉዳቱ ካሣ መጠን ለዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት የሠራተኛው የዓመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ፤ ጉዳቱ ከዛላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት መጠን በታች እንደሆነም በተመሣሣይ ሁኔታ ነገር ግን ከአካል ጉዳቱ ደረጃ ጋር የተመጣጠነ ክፍያ ይሆናል፡፡ በቀኝ እጅ ላይ የደረሰው ጉዳት 70% ቢሆን ለዚሁ ጉዳት መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ እንደማለት ነው፡፡
በሞት ምክንያት ለጥገኞች የሚፈፀም ክፍያ
በደረሰው ጉዳት ምክንያት አንድ ሠራተኛ ወይም ለማጅ ሠራተኛ የሞት አደጋ የደረሰበት እንደሆነ በዚሁ ምክንያት በሟቹ ጥገኝነት ሥር የሚተዳደሩ ሰዎች የጉዳት ካሣ ክፍያ ይፈፀምላቸዋል፡፡ በሟቹ ሥር የሚተዳደሩ የሚባሉትም
- የሟቹ ባል ወይም ሚስት
- ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች
- በሟቹ ድጋፍ ይተዳደሩ የነበሩ የሟች ወላጆች ናቸው
ሟቹ ሠራተኛ በመንግሥት የጡረታ ህግ የማይሸፈን በሆነ ጊዜ ለጥገኞቹ ለሚፈፀመው ክፍያ መሠረት የሚሆነው የሟቹ ሠራተኛ የአመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሲሆን ለሚስት ወይም ለባል የዚህ ደመወዝ 50%፣ ዕድሜያቸው 18 ዓመት ላልሞላቸው ልጆች ለእያንዳንዳቸው 10% ፣ ለሟች ወላጆች ለእያንዳንዳቸው 10% የበለጠ ወይም ያነሰ መሆን የለበትም፡፡ አንድ ልጅ ያለው ባል ቢሞት ለሚስቱ 50% ለልጁ 10% ሲሰጥ በድምሩ 60% ማለት ነው፡፡
መጠኑ 100% መሆን ስላለበት በያንዳንዱ ድርሻ ላይ እንደድርሻቸው መጠን ቀሪውን 40% ማደላደል አለብን ወይም ይኖርብናል፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታም ልጆቹ በዝተው መጠኑ ከ100% ያለፈ እንደሆነም ከፍ ሲል የተገለፀውን ዘዴ በመጠቀም መጠኑን ወደ 100% ዝቅ እንድናደርግ ይጠበቅብናል፡፡
ከዚህ በተረፈ በጉዳት ምክንያት የሚገኙ ክፍያዎች ከገቢ ግብር ነፃ ናቸው፡፡ ለሌላ የሚተላለፉ፣ ሊከበሩ ወይም በዕዳ ማቻቻያነት ሊያዙ የማይችሉ ናቸው፡፡