- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 16562
በሥራ ምክንያት ስለሚመጣ አደጋ
በሥራ ሂደት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በማናቸውም ጊዜ ያልታሰቡ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በተለይም ዘመናዊው የኢንዱስትሪ አሠራር ሂደት እያደገና እየተወሳሰበ መምጣቱ ከመሥሪያዎቹ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አደጋ የመፈጠር ዕድሉን ሠፊ ያደርገዋል፡፡ ከድኅነት ጋር ተያይዞም ችግሩ ይከፋል፡፡ ጉዳቱም ከተጎጂው ዘልቆ በሥሩ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹን የሚነካ በመሆኑ ከፍ ያለ ቀውስን በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥር ነው፡፡
ስለሆነም በአንድ በኩል የማኅበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ ተገቢ በመሆኑ፤ በሌላም በኩል ሠራተኛው ሊከሰት ከሚችለው አደጋ በስተጀርባ በርሱና በቤተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር እያሰበ በጭንቀት መስራቱ በምርታማነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ስለሚያሰድር፤ ሠራተኛው ለሚደርስበት ጉዳት የሚገባውን ካሳ የሚያገኝበትን የህግ ማዕቀፍ ማኖሩ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አገሮች ቀደም ሲል አደገኛ ተብለው በሚታወቁ (እንደ ማዕድን ማውጣት) ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩት ብቻ ይፈፀም የነበረው ካሳ የማግኘት መብት አሁን ሌሎችንም ሁሉ እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡
በዚህ የተነሳ በኛም አገር "ሠራተኛ" በሚለው ትርጉም ውስጥ የሚሸፈን ማናቸውም ሰው በሥራ ሂደት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ አደጋ የደረሰበት እንደሁ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምበት የህግ ማዕቀፍ ቀደም ሲሉ በነበሩት በአዋጅ ቁጥር 64/68፣ 42/85 እና አሁን ባለው አዋጅ ቁጥር 377/96’ም ተሸፍኗል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 95/2 ላይ እንደተገለጸው በስራ ምክንያት የሚመጡ ጉዳቶች በሚለው ርዕስ ሥር ሁለት መሰረታዊ ሀሳቦች ተካተዋል፡፡ እነኚህም በሥራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና በሥራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ናቸው፡፡ የትኛውም ጉዳይ ቢሆን ሰራተኛው የደረሰበት ጉዳት ከሥራው ጋር የተያያዘ መሆን አለበት፡፡ ከሥራው ጋር የተያያዘ የመሆን አለመሆኑ ነገር ተጎጂውን ሠራተኛ ካሳ ለማስገኘትም ሆነ ለመንሳት ወሳኝ የሆነ መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አሊያ ግን ለማንኛውም ጉዳት ሁሉ የአሠሪውን ኃላፊነት በማስከተል አንድ አሠሪ ኢንቨስት ለማድረግ የሚኖረውን ፍላጎት ይገድባል፤ በዚሁ ደረጃም ዕድገት ይቀዘቅዛል፡፡ ስለሆነም አሠሪው ኃላፊ ሊሆንበት የሚገባውን በሥራ ምክንያት የሚመጣ አደጋ እና በሽታ መለየት ተገቢ ነገር ነው፡፡ ይህን ስንል የአሠሪው የኃላፊነት አድማስ እምን ድረስ ነው ማለታችን ነው፡፡ የመጠየቁን ያህል አፋጣኝ እና ቀጥታ መልስ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡ በሥራ ሂደትም ለተለያዩ አሰራሮች መፈጠር ምክንያት በመሆን የአፈፃፀም ወጥነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
ስለሆነም በሥራ ምክንያት የሚመጡ አደጋዎችና በሽታዎችን የተሻለ ለመረዳት እንደቅደም ተከተላቸው በሚከተለው መንገድ ለመወያየት እንሞክራለን፡፡
1. በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ (during the performance of the Work)
¢በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ¢ የሚለው ሐረግ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 97 እንደተገለፀው “ማንኛውም ሠራተኛ ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ሥራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት" ማለት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም የሚከተሉት ዋና ነጥቦች ናቸው፡፡
አደጋው የደረሰው፤
- ስራን በማከናወን ላይ፤
- ከሥራው ጋር ግኑኝነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም፤
- ሥራን ለማከወን በሚደረግ ጥረት ውስጥ መሆኑ ናቸው ።
የሥራ ላይ አደጋ የሚባለውና የካሳ ሽፋን የሚሰጠው እነኚህ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው። ለበለጠ መረዳት እያንዳንዱን ነጥብ በተናጥል ማየት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሚከተለው እናያቸዋለን።
ስራን በማከናወን ላይ የሚለው ሃረግ አደጋው የደረሰው፤
- ስራው የሚከናወንበት ጊዜ፤
- ሥራው የሚከናወንበት ቦታ እና፤
- ሥራው የሚከናወንበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ‘ሥራን በማከናወን ላይ’ የሚለው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ቦታ እና ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው።
ስራው የሚከናወንበት ጊዜ
ስራው የሚከናወንበት ጊዜ የሚለው በመደበኛው ሁኔታ ሥራ የሚሰራባቸውን ከ2፡30 — 6፡30 እና ከ 7፡30 —11፡30 እና በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ከ 2—30 6፡00 እና ከ 8፡00—11፡00 እንዲሁም ቅዳሜን ግማሽ ቀን የሚሸፍን ነው። ከዚህ ውጭ ያሉት ሰዓታት ከካሳው ሽፋን ውጭ ይሆናሉ፡፡ ይህም ሲባል ከሥራው አካባቢ ጠቅላላ ሁኔታ ፣ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ እና ሥራው ከሚጠይቀው ወይም በልማድ ከሚከናወንበት ሁኔታ አንፃር ወይም ለሥራው ተቀዳሚ ወይም ተከታይ የሆኑ (incidental) ተግባሮችን ሲፈጽም በነበረበት ጊዜ አንድ ሰራተኛ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ አደጋው ሥራው ከሚሰራበት ሰዓት ውጪም ቢሆን ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሳባል። ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ውጪ ነገር ግን የአሰሪውን ትዕዛዝ በመፈፀም ላይ ባለበት ጊዜ አደጋ ቢደርስበት፣ በእረፍት ጊዜ ምሳ በመብላት ላይ እያለ አደጋ ቢደርስበት በሥራ ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል። በመጀመሪያው ነጥብ የአሰሪውን ጥቅም ለማስፈፀም ሲል በዚያ ቦታ የተገኘ መሆኑ ብቻ የሥራውን የጊዜ አድማስ ያሰፋዋል በኋለኛውም ቢሆን ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ስንነሳ ሳይበላ ስራውን ለመስራት ይቸገራል ቢሰራም እንኳን ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም ምሳ በሚበላበት፣ ሻይ በሚጠጣበት ጊዜ አደጋ ቢደርስበት፤ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሰራተኛው በአዲስ ጉልበት ስራውን መጀመር አሰሪውን የሚጠቅመው በመሆኑ በሥራ ጊዜ ላይ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሰባል። ለአንድ አፍታ እረፍት በመውሰድ ላይ እያለም ጉዳቱ ቢደርስ በተመሳሳይ ሁኔታ በሥራው ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ከካሳ ሽፋን ውጭ ማድረግ የመደበኛ ሕይወት አኗኗር ትርጉምን ማሳጣት ይሆናል።
ሥራ የሚከናወንበት ቦታ፤
አንድ ሥራ የሚሰራው ሥራውን በሚያሰራው ድርጅት ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ እያለ አንድ ሠራተኛ አደጋ ቢደርስበት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሥራ የሚሠራው ግን ድርጅቱ ያለበት ቦታ ላይ ብቻ አይደለም፤ የሥራው ባህሪ ሠራተኛው ከመደበኛው የሥራ ቦታ ላይ ተነጥሎ ወደሌላ ቦታ እንዲሄድ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ አንድ የኤሌትሪክ ወይም የቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኛ የመስመር ላይ ስራዎችን ለመሥራት ከድርጅቱ ውጭ መገኘት ሊኖርበት ይችላል ለእርሱ የሥራ ቦታው ሥራው የእርሱን መገኘት የሚጠይቅበት ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ አደጋ ቢደረስበት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ ይሆናል።
ሥራው የሚከናወንበት ሁኔታ፤
አደጋው ሠራተኛው ሲሰራ የተከሰተ መሆን አለበት። ሠራተኛው ሥራውን ሲሰራ የደረሰ አደጋ ነው የሚባለው በሥራ ዝርዝር መግለጫው ሊሠራ የሚገባው ሥራ ብቻ ሳይሆን የሥራው ባህሪ የነገሮች አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ሥራውን ተከትለው በሚመጡ አጋጣሚዎች ምክንያት፤ ከሥራ ዝርዝሩ ውጭ ያለን ሥራ እንዲሰራ ቢሆን ወይም ሥራውን ተቋርጦ ቢሆን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስ ሥራውን በመሥራት ላይ የተከሰተ አደጋ ይሆናል። ለምሳሌ አድካሚ ከሆነ ሥራ ለአንድ አፍታ አረፍ እንዳለ አደጋ ቢደርስ የውሃ ጥማቱን ለማርካት ድርጅቱ ውስጥ ወዳለው ወይም የሥራ ቦታ ላይ ወዳለው ሻይ ቤት ሲሄድ፣በምሳ የእረፍት ጊዜው ውስጥ እያለ አደጋ ቢደርስ ሠራተኛው ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ይሆናል። ሥራውን በአዲስ መንፈስ እና ጉልበት ለመቀጠል አረፍ ማለቱ፣ምሳ መብላቱ ወይም የሥራ ባልደረባውን መርዳቱ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ አሰሪውን የሚጠቅም ነው። የሚጠቅም ባይሆን እንኳን ከሥራው ጠቅላላ ባሕሪም ሆነ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ሁኔታ አንፃር ሥራው ለአንድ አፍታ የመቋረጡ አጋጣሚ ሥራው ሲሰራ የደረሰ አደጋ አይደለም አያሰኘውም። ረዘም ላለ ጊዜ ሥራው ተቋርጦ ቢሆን ለምሳሌ የሥራው ሰዐት አብቅቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ተነስቶ ከድርጅቱ ውስጥ ወይም ከሥራው ቦታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስም ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ነው መባሉን አያስቀረውም።
በአጠቃላይ ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ነው የሚባለው ሠራተኛው ሥራውን በተግባር እያከናወነ መሆኑን፣በተግባር እያከናወነ ባይሆን እንኳን ሥራውን ከፍ ሲል በተገለፁት ምክንያቶች ለጊዜው ሥራውን አቋርጦ ባለበት ጊዜ፣ የሥራ ባልደረባውን በመርዳት ላይ የአሰሪውን ትዕዛዝ በመፈጸም ላይ ሥራውን አቁሞትም ቢሆን ወደ ቤቱ ለመሄድ ነገር ግን በሥራ ቦታ ወይም በድርጅቱ ውስጥ እንዳለ አደጋ ሲደርስበት ነው።
2. አደጋው ከሥራው ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት (in connection with the performance of the Work)
ሁለተኛው ነጥብ አደጋው ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ አንድ አደጋ ተገቢውን የካሳ ክፍያ እንዲያስገኝ ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ የመሥሪያ መሣሪያዎቹ በአግባቡ ባለመስራታቸው ምክንያት፤ እየሰሩም ቢሆን በሥራው ላይ ያለውን ሠራተኛ ጉዳት ካደረሱበት ወይም ሠራተኞቹን አደገኛ ለሆነ ሁኔታ በማጋለጡ ምክንያት የተፈጠረ አደጋ ‘ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ” የተፈጠረ ስለመሆኑ መረዳት ብዙም የሚከብድ አይሆንም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ግን ጉዳቶቹ የሚመጡት ከሥራው ጋር በተያያዘ ሁኔታ መሆኑን መለየት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ በሥራ ላይ ያለ ሠራተኛ በመብረቅ ሊመታ ወይም በሥራ ላይ እያለ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ጉዳት ሊደርስበት ይችላል፡፡ በነበረበት የልብ ድካም፤የደም ብዛት ምክንያትም ሕይወቱ ሊያልፍ ወይም የአካል ጉዳተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እነኚህ ጉዳቶች በቁማቸው ሲታዩ ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ነገር ግን አደጋው ሁልጊዜ ከሥራው የመነጨ እንዲሆንም አይጠበቅም፡፡የሥራው ባህሪ ለአደጋው መከሰት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ እንደሁ ይኸው ብቻም በቂ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ያህል ቀደም ሲል የተነሳው የመብረቅ አደጋ ከሥራው ክንውን ጋር ግንኙነት ነበረው ማለት አይቻልም፡፡ ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ለዚሁ ተመሳሳይ አደጋ ተጋልጧል፡፡ የጉዳቱ ሠለባ የሆነው ሰራተኛ ሥራው ላይ የነበረ በመሆኑ ብቻ አደጋው ከሥራው ጋር (ጠንካራ) የሚያስተሳስረው ነገር አለ ማለት አይቻልም፡፡ ይሁንና የመብረቁ አደጋ በተከሰተ ጊዜ ሠራተኞቹ በመብረቁ አደጋ እንዲመቱ ያደረጋቸው ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንዲሰሩ የሥራቸው ሁኔታ ያስገደዳቸው በመሆኑ የተነሳ ከሆነ ይህ አደጋውን ከሥራው ክንውን ጋር የሚያስተሳስረው አንድ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለሆነም እንዲህ ባለ አጋጣሚ የመብረቁ አደጋ ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአንዳንድ አገሮች ደግሞ የሥራው ሁኔታ እና ግዴታ ሠራተኛውን አደጋው እደረሰበት ቦታ ባያመጣው ኖሮ በአደጋው ሊጎዳ ባልቻለም (positional risk) ነበር በማለት በአደጋው የተጎዳውን ሰው እንዲካስ ያደርጉታል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ተጎጂው ካሳ የሚያገኘው በሥራ ላይ እያለ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ አደጋውን ከሥራው ጋር የሚያስተሳስረው ይኸው ብቻ ነው፡፡
በአጠቃላይ አደጋው በህጉ ጥበቃ የተሸፈነ ነው ለማለት ከሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው አይጠበቅም፡፡ በአንድ ዓይነት ምክንያት ከሥራው ባህሪ ጋር ትስስር ያለው መሆኑ ከታወቀ ወይም የስራው ባህሪ ለአደጋው መከሰት እንኳ ባይሆን አደጋው ሲከሰት ለደረሰብን/ለሚደርስብን ጉዳት የራሱ አስተዋጽኦ ያለው/የሚኖረው ከሆነ ከስራ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
3. የአደጋው ከተጎጂው አድራጎት ውጪ በሆነ ምክንያት መከሰት
ከፍ ሲል የተገለፁት ጉዳቶች ‘የሥራ ላይ አደጋ’ እንዲሆኑ አደጋው ከተጎጂው ውጪ በሆነ ምክንያት የደረሰ መሆን አለበት፡፡ የሰው ሚስት በመድፈሩ ምክንያት በቂም ይፈልገው የነበረው ባል ተጎጂውን ሥራ ቦታ ድረስ በመሄድ ቢገድለው ይህ የግድያ አደጋ የደረሰበት ከግል ግንኙነቱ የተነሳ የመጣ እንጂ ከሥራው ባህሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም ትስስር ያለው ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡
ስለሆነም የሥራ ላይ አደጋዎች ከተጎጂዎቹ የግል ህይወት አመራር ወይም ግንኙነት ውጪ በሆነ ምክንያት እነርሱ የተፈለገውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ሊቆጣጠሩዋቸው የማይችሉ ሲሆኑ ብቻ ¢የሥራ ላይ አደጋ¢ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
4. ሥራን ለማከናወን በሚደረግ ጥረት ውስጥ የደረሰ ጉዳት
ይህ ሶስተኛው ሥራን በማከናወን ሂደት የሚደርስ የስራ ላይ አደጋ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ሥራውን ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ጉዳት ቢደርስበት የሥራ ላይ አደጋ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር ሥራውን ለማከናወን ጥረት በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል ሠራተኛው በነበረበት የልብ ድካም፤ የደም ብዛት ምክንያት ጉዳት ቢደርስበት ወይም በሌላ ሰው በደረሰበት ጥቃት ምክንያት ቢጎዳ ጉዳቱ ከስራው ጋር ያልተያያዘ ከሆነ የሥራ ላይ አደጋ ደርሶበታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይህንንም ለመረዳት ሥራው ከደረሰበት ጉዳት ጋር ያለውን ትስስር መመርመር ይጠይቃል፡፡