በመርህ ደረጃ ሲታይ አንድ ንብረት ተቀባይ የሆነ ሰው ንብረቱ ከሚያስተላልፍለት ሌላ ሰው የበለጠ መብት አይኖረውም። አንድ ሰው ራሱ የባለሃብትነት መብት ሳይኖረው ማንኛውም የንብረት መብት ለሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደማይችል ነው።

 

ንብረቱን የሚያስተላልፈው ሰው በባለሃብትነት መብቱ ላይ ጉድለት ያለበት እንደሆነ ያ ጉድለት ከንብረቱ ጋር አብሮ ወደ ተቀባዩ ይተላለፋል። በቅን ልቦና ባለይዞታ መሆን ባለሃብት ለመሆን ከሚያስችሉ መንገዶች (modalities) አንዱ ሆኖ ግዙፍነት ባላቸው መደበኛ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ ተፈፃሚነት የሚኖረውና ለሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ በሚሰጥና በሚያሽክም ውል (contract of sale of the thing under consideration) የሚገኝ ነው። ንብረቱ በቅን ልቦና የገዛ ሰው ሽያጩ ያ ንብረት ለመሸጥና ለማስተላለፍ የሚያስችል ሕጋዊ መብት እንዳለው ኣምኖ የገዛው መሆን አለበት። እዚህ ላይ ሕጉ ሁለት ተፋላሚ ጥቅሞችን (conflicting interests) ለማስማማት ወይም ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ይሞክራል። ይኸውም፤ የቀድሞው የንብረቱ ባለሃብትና የንግዱ እንቅስቃሴ /የሶሰተኛ ወገን ጥቅም/ ናቸው። በአንድ በኩል የቀድሞው ባለሃብት ብዙ ደካም፣ ጥሮግሮ ያፈራውን ንብረት ያለአግባብ እንዳይነጠቅ ጥበቃ የሰጠው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቅን ልቦና ዕቃ የገዙ ሰዎች ዕቃው ከማይመለከተው ሰው ነው የገዛችሁት የተባሉ እነሱ በማያውቁት ጉዳይ ችግር ላይ እንዳይወድቁና በዚህ ሰበብም ነፃ የንግድ እንቅስቃሴው እንዳይገታ ለማድረግ ነው።

 

ከላይ እንደተመለከተው ይህ በቅን ልቦና ባለይዞታ በመሆን የባለሃብትነት መብት የማግኘት ጉዳይ ተፈፃሚነት የሚኖረው በመደበኛ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች (ordinary corporeal chattels) ላይ ነው። መርሁ ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ ሊሆን የማይችለው፤

  1. 1.በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ
  2. 2.በልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ
  3. 3.ለህዝብ ጥቅም ተብለው በሚመደቡ ንብረቶች ላይ ነው (ፍ/ሕግ ቁ.1455)

 

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይም መርሁ ተፈፃሚ የሚሆንበትና የማይሆንበት ሁኔታ አሉ።

 

1.ተፈፃሚ የማይሆንበት ሁኔታ፤ የንብረቱ ባለሃብት በፍላጐቱና በፈቃዱ ለሌላ ሰው ያስተላለፈው እንደሆነና ተቀባዩም ወደ ሶሰተኛ ወገን በውል ያስተላለፈው እንደሆነ ኃላ የቀድሞው የንብረቱ ባለብት ከሶሰተኛው ወገን የመጠየቅ መብት አይኖረውም። ይህ ነገር ተቀባይ የሆነ ሰው ንብረቱ ካስተላለፈለት ሰው የበለጠ መብት የለውም ( “Nemo dat quod non habet,” “No one can transfer what he himself doesn’t have”)ለሚለው መርህ ልዩ ሁኔታ ነው። እዚህ ላይ የሚሰራ ወይም ተፈፃሚነት ያለው መርህ መብትህን /ንብረትህን/ በእምነት ከሰጠኸው ሰዉ ጠይቅ (“where you have put your faith there you must seek”) የሚለውን ነው። ስለዚ የንብረቱ የቀድሞ ባለሃብት መብቱን መጠየቅ ያለበት ከሰጠው ሰው እንጂ ከሶሰተኛው ወገን ሊሆን አይገባውም ማለት ነው። ለምሳሌ፦ በመያዣ (pledge) የተቀበለው፣ በብድር የወሰደው ንብረት ወደ ሶሰተኛ ወገን /በቅን ልቦና የገዛ/ ያስተላለፈው እንደሆነ ሶሰተኛው ወገን የባለሃብትነት መብት ያገኛል።

 

በቅን ልቦና ባለይዞታ በመሆን የአንድ ነገር ባለሃብት ለመሆን መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ።

ሀ/ በሻጭና በገዢ መካከል በተደረገ የሽያጭ ውል መሰረተ የተላለፈ ንብረት መሆን አለበት፣ ይኸውም ለሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች መብት የሚሰጥና ግዴተ የሚያሸክም መሆን አለበት፣ በሌላ ኣገላለፅ በስጦታ የተገኘን ንብረት በቅን ልቦና በመያዝ ባለሃብት መሆን እንደማይቻል ነው።

ለ/ በቅን ልቦና ባለይዞታ የሆነው ወደ ውሉ ሲገባ ለውሉ ምክንያት የሆነውን ንብረት ባለሃብት ለመሆን ኣስቦ ያደረገው መሆን አለበት።

ሐ/ ቅን ልቦናው ንብረቱን እጅ በሚያደርግበት ጊዜ መኖር አለበት።

መ/ ገዢው ንብረቱን ሲገዛ ከቅን ልቦ የተነሳ ከእውነተኛው ባለሃብት ነው ንብረቱ እየገዛሁት ያለሁት የሚል እምነት የነበረው መሆን አለበት፣

ሠ/ ገዢው የገዛው ንብረት ሲተላለፍለት ወይም እጅ በሚያደርግበት ጊዜ ቅን ልቦና የነበረው መሆን አለበት፣

ረ/ በቅን ልቦና የሚገዛው ንብረት መደበኛ ተንቀሳቓሽ ንብረት መሆን አለበት።

2.አንድ ሰው የሌላውን ሃብት /ነገር/ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችልም የሚል መርህ ተፈፃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ፤ ንብረቱ ከባለቤቱ እጅ ሊወጣ የቻለው ከእርሱ ፍላጐትና ፈቃድ ውጭ የሆነ እንደሆነና ተቀባዩም ወደ ሶሰተኛ ወገን ያስተላለፈው እንደሆነ የቀድሞው ባለቤት በሕግ የተደነገገን የይርጋ ጊዜ ከማለፉ አስቀድሞ ንብረቴን መልስልኝ ብሎ ሶሰተኛ ወገንን ለመጠየቅ ይችላል። የዚህ ልዩ ሁኔታ በፍ/ሕግ ቁ.1167 ላይ የተደነገገውን ነው። ይህ የሕግ ድንጋጌ ጥሬ ገንዘብንና ላምጪው የሚከፈል ሰነድ የሚመለከት ሆኖ እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) የተቀመጠበት ምኽንያት ደግሞ ገንዘብ ተመሳሳይና መለያ የሌለው /ከቁጥር በስተቀር/ በመሆኑና እንደ አጠቃላይ የመገበያያ መንገዲ (means of exchange) መጠን ነፃ ዝውውራቸው (free circulation) ጠብቀው እንዲያገለግሉ ሕጉ ጥበቃ ያደረገላቸው መሆኑን እንገነዘባለን። ከጥሬ ገንዘብና የገንዘብ ሰነዶች ውጭ ያሉትን የተሰረቁ ዕቃዎችን በተመለከተ ግን ሕጉ የባለሃበትነት መብት እንዳይደፈርና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥበቃ ያደረገለት መሆኑን ነው።     በቅን ልቦና የተሰረቀ ንብረት የገዛ ሰው ንብረቱ ለቀድሞው ባለሃብት የመመለስ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት ቢሆንም ለዚህ ንብረት ያወጣውን ገንዘብ ከሸጠለት ሰው የመጠየቅ መብት እንዳለውም ሕጉ አስቀምጧል። በመብቱ መጠቀም የሚችለው ግን ንብረቱ /ዕቃው/ የገዛው በንግድ ቤት፣ በህዝብ ገበያ ውስጥ ወይም ዕቃ በሓራጅ በሚሸጥበት አደባባይ ውስጥ የሆነ እንደሆነ ነው። በሌላ በኩል የፍ/ሕጉ የፈረንሳኛው ቅጂ ግን የተሰረቀ ንብረት በቅን ልቦና የገዛ ሰው ገንዘቡ ማስመለስ ያለበት ከንብረቱ ባለቤት እንደሆነ ነው የሚደነግገው።