በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 እና 113 መሠረት በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ በምስክርነት የሚቀርቡ ምስክሮች ለምስክርነት ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡበት ጊዜ ለመጓጓዣ እና ሌላ የቀን ወጪ የሚሆን ገንዘብ ሊከፈላቸው እንደሚገባ፤ ለምስክርነት የሚመጣው ሰውም የባለሙያ ምስክር ከሆነ የሚሰጠው ምስክርነት እንደሚፈጀው ጊዜ እና አድካሚነት ተጨማሪ አበል ሊከፈለው እንደሚገባ፤ ለምስክሮቹ ወጪ የሚከፈለው ገንዘብ አከፋፈል ፍርድ ቤቱ በሚያዘው ሁኔታና ጊዜ መሠረት እንደሚሆን እንዲሁም ለምስክሮች የሚቀመጠው ገንዘብም የማይበቃ ከሆነ ፍርድ ቤት ተጨማሪ አበል ሊያዝ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም ለምስክሮች የሚከፈለውን አበል መክፈል ያለበት አስመስካሪው ወይም እንዲመሰከርለት የሚፈልገው ተከራካሪ ወገን መሆኑንና ተከራካሪው ፍርድ ቤቱ ለምስክሮች እንዲከፍል ያዘዘውን የምስክሮች ወጪ ለመሸፈን እምቢተኛ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተከራካሪው የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ተሸጦ እንዲከፈል ወይም የተጠራው ምስክር ቃሉን ሳይሰጥ እንዲመለስ ወይም ሁለቱንም አጣምሮ ሊወስን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡  

ሆኖም በተግባር የእነዚህን ድንጋጌዎች አፈፃፀም ስንመለከት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በኩል ፈፅሞ ድንጋጌዎቹ ተግባራዊ እየተደረጉ አይደለም፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶችም ቢሆን በተወሰኑ ምድብ ችሎቶች ብቻ ተከራካሪዎች ለምስክሮቻቸው መጥሪያ ሲወስዱ አስመስካሪው ለእያንዳንዱ መጥሪያ ፖስታና አስር አስር ብር እንዲያመጣ ተደርጎ በፍርድ ቤት ሠራተኞች በኩል መጥሪያው ከአስር ብር ጋር ተደርጎ ከታሸገ በኋላ በእሽጉ ላይ የፍርድ ቤቱ ማሕተም አርፎበት ለምስክሮቹ ይላክላቸዋል፡፡ አስር ብሩ የሚላከውም ምስክሮች ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡ ለትራንስፖርት እንዲከፍሉ መሆኑን የፍርድ ቤት ሠራተኞች ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ምስክሮችን በግማሽ ቀን ብቻ አስተናግደው የሚሸኑበት ሁኔታ አጠራጣሪ በሆነበትና ብዙውን ጊዜ ተደጋጋሚ ቀጠሮ በሚሰጥበት ወይም ቀኑን ሙሉ በሚዋልበት ሁኔታ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ካለው የትራንስፖርት አቅርቦት አንፃር ምስክሮች ከሚኖሩበት አከባቢ ወደ ፍርድ ቤቶች ደርሰው ከምስክርነት በኋላ ወደ አከባቢያቸው ለመመለስ አስር ብር ብቻ ይበቃል ወይ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ድንጋጌውን ለማስፈፀም እንደ ጥሩ ጅምር ቢወሰድም ድንጋጌዎቹን በማስፈፀም ረገድ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህም፡

ለምስክሮች የመጓጓዣ ወጪ እንዲሆን አስር ብር ከመጥሪያ ጋር የመላክ አሠራር በሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶች ሳይሆን በጥቂት ምድብ ችሎቶች ብቻ መከናወኑ፤

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በኩል ለምስክሮች የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችል ተቀማጭ እንዲከፈል በፍርድ ቤቶች በኩል አለመደረጉ፤

ፍርድ ቤቶችም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 112 እና 113ን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ውጤታማ የአሰራር ሥርዓት ደካማ መሆኑ፤

ፍርድ ቤቶች ምስክሮች ለምስክርነት በሚቀርቡበት ወቅት ተገቢውንና ተመጣጣኝ የሆነ የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች የተሸፈነላቸው መሆን ያለመሆኑን ከምስክሮች አለማረጋገጣቸው እና ወጪያቸው አለመሸፈኑን ሲያረጋግጡ አስመስካሪው ወጪውን እንዲሸፍን አለማድረጋቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ድንጋጌዎቹ አለመፈፀማቸውን የሚያመላክቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በመሆኑም በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ምስክሮች ለምን ሲጠሩ አይቀርቡም? ምስክሮች የፍትሕ ሥራውን ለምን አያግዙም? ከማለታችንና ፍርድ ቤቶችም ለመቅረብ ፍቃደኛ ያልሆኑ ምስክሮች ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ከመስጠታቸው በፊት ቢያንስ በሕጉ ለምስክሮች የተረጋገጠላቸውን መብት ፍርድ ቤቶች በአግባቡ ሊያስከብሩላቸውና ሊያረጋግጡላቸው ይገባል እያልኩ የፍትሕ ሥርዓታቸው በዳበረ ሀገራት ለፍትሕ ሥራ መሳካት ለምስክሮች የሚሰጠውን ወሳኝ ሚና የሚያመላክተውን አባባል በማንሳት ሀሳቤን ላብቃ፡፡

“ምስክር ከሌለ ፍትሕ የለም”                         “No witness No justice”