ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ ኤግዚቢቶችን የሚመዘግብና በተጠበቀ ስፍራ ሊያስቀምጥ የሚችል አሠራር፣ የመዝገብ ቤት ሹም እና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጫነት የሚያገለግል የሚታወቅ የተጠበቀ ስፍራ የሌላቸው በመሆኑ ኤግዚቶችን የመመዝገብ እና የማስቀመጥ ኃላፊነት በፖሊስ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ፖሊስም በፌዴራል ደረጃ ወንጀል ምርመራን ከማጣራት ጋር በተያያዘ ኤግዚቢቶችን የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን በወንጀል መርማሪዎችና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጥና ለመንከባከብ በተመደቡ የፖሊስ አባላት በኩል የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 124 (2) መሠረት ነገሩ በሚሠማበት ቀን ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ ኤግዚቢትን ጨምሮ ያሏቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ኤግዚቢቶች ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ተመዝግበው በተጠበቀ ስፍራ ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ ኤግዚቢት ባለባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ በሕጉ በተጣለበት ግዴታ መሠረት ጉዳዩ በሚታይበት ዕለት ኤግዚቢቶችን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ይችል ነበር፡፡

ሆኖም በተግባር ዐቃቤ ሕግ ኤግዚቢት ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ኤግቪዚቱ ፍርድ ቤት ይቅረብ ብሎ ፍርድ ቤቱ ካላዘዘ በስተቀር የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 97 እና 124 (2) በሕጉ በሚያዝዘው መሠረት እየተፈፀሙ ባለመሆናቸው ይህ ቢታሰብበት ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል፡፡