- Details
- Category: General - ልዩ ልዩ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርኃ-ግብር
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ /ኢፌዴሪ/ መንግስት፤ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩበትና የሚረጋገጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሰብዓዊ መብቶችን የበለጠ ለማስከበር እና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስልቶችን መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ፤ ከመሠረቱ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብርን ማዘጋጀትና ለተግባራዊነቱ መትጋት በአንድ ሀገር ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን በተቀናጀ ሁኔታ በማስከበርና በማረጋገጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የማዘጋጀቱ ጉዳይ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በተካሄደው በ2ኛው የቪየና የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮንፈረንስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በሀገራት መካከል መግባባት የተደረሰበት አጀንዳ ነው፡፡ የዚሁ ኮንፈረንስ ውጤት በሆነው የቪየና ዴክላሬሽንና የትግበራ ፕሮግራም ክፍል ሁለት አንቀጽ 71፤ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶችን በማስፋፋት፣ በማስጠበቅና በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን አፈፃፀም ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊወስዱት የሚገባውን እርምጃ በግልፅ የሚያመለክት ሀገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የማዘጋጀትን አስፈላጊነት በአፅንዖት እንዲቃኙት አሳስቧል፡፡ ከዚህ አኳያ፤ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር ማዘጋጀትና መተግበር በዓለም አቀፍ ደረጃ መግባባት የተፈጠረበትን ጉዳይ መፈፀም ዓለም አቀፍ ኃላፊነትን መወጣት ጭምር ነው፡፡ የድርጊት መርሐ-ግብሩ፤ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ጥበቃ ረገድ እስካሁን ከተገኘው መሻሻል የበለጠ ውጤት የሚያመጣ የአመለካከት ለውጥ እንዲፈጠር ለማድረግ፤ ትምህርትና ስልጠናን ለማስፋፋት፤ ነፃ የህግና የዳኝነት ስርዓትን ለማጎልበት፤ እንዲሁም የህግ የበላይነትን በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤትና በማኅበራዊ ዋስትና መስኮች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ አመቺ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ቀርፆ ማስፈፀሚያ በጀት ለመመደብና ለመተግበር የተዘጋጀ የፖለቲካ ፈቃደኛነትና ቁርጠኛነት ያለው አመራር መኖሩን ታሳቢ አድርጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል፤ ሀገራት ሰብዓዊ መብትን በማረጋገጥ በኩል ያላቸውን አፈፃፀም የሚገመገምበት በየአራት ዓመቱ የሚካሔድ ሁል-አቀፍ ግምገማ መድረክ አመቻችቷል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ “ዩኒቨርሳል ፔርዮዲክ ሪቪው” ተብሎ በሚጠራው በዚህ የግምገማ መድረክ ባቀረበችው ሪፖርት ላይ በመመስረት ከተሰጡትና ሀገሪቱ ከተቀበለቻቸው አስተያየቶች መካከል የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ-ግብር ማዘጋጀትና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም አስተያየት አንዱ ነበር፡፡ ይህንን የድርጊት መርሐ-ግብር ማዘጋጀት፤ ሰብዓዊ መብትን በይበልጥ ለማረጋገጥ ረገድ በመንግስት ረገድ ያለውንፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነትማረጋገጫ ከመሆኑም በተጨማሪ“በዩኒቨርሳል ፔሪዮዲክ ሪቪው” ለመንግስታችን የተሰጡ አስተያየቶችን የመፈፀምም አካል ነው። ይህን ሰነድ ማዘጋጀትና መተግበር በራሱ በዚሁ ስርዓት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት ነው፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩን የማዘጋጀት ውሳኔ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብርን የማዘጋጀቱ ሂደት በተጠናከረ ሁኔታ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር ‘‘የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር ለማዘጋጀት የተጠራ ብሔራዊ የምክክር ወርክሾፕ’’ በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ መጋቢት ወር 2002 ዓ.ም ባዘጋጀው የመንግስት አካላት፣ ሲቪል ማህበራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተሳተፉበት ሀገራዊ መድረክ ነበር። ከዚህ መድረክ በመቀጠል በህዳር ወር 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደውና ሀገራችን በአጠቃላይ ወቅታዊ ግምገማ (ዩኒቨርሳል ፔርዮዲክ ሪቪው) ስርዓት ባቀረበችው ሪፖርት በተሰጡ አስተያየቶች ላይ ለመመካከር በተካሄደው ብሔራዊ የምክክር ወርክሾፕ በመንግስት ተቀባይነት ያገኙ በርካታ አስተያየቶች ላይ በመመስረት ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የማዘጋጀት ጠቃሜታ ላይ አጠቃላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡ የምክክር መድረኩ የድርጊት መርሐ-ግብሩን ለማዘጋጀት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለመንግስት የመነሻ ሀሳብ እንዲያቀርብ የሚለው የመፍትሄ ሀሳብ ላይም መግባባት ላይ ደርሷል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት የምክክር መድረኮች መሰረት በማድረግ የድርጊት መርሐ-ግብሩ በምን መልኩ ሊዘጋጅ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከር የመነሻ ሃሳብ ተዘጋጅቶ ለመንግስት ቀርቧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የማዘጋጀቱ ጉዳይ በመስኩ እየተደረጉ ያሉት ከፍተኛ ፍሬ ያፈሩ አፈፃፀሞችን በሀገራዊ ዕቅድ በመምራት ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የሚቻል መሆኑን በመገንዘብ የድርጊት መርሐ-ግብሩ እንዲዘጋጅ ወስኗል፡፡ በመሆኑም የድርጊት መርሐ-ግብሩን አዘገጃጀት በበላይነት የሚመራ ብሔራዊ የአመራር ኮሚቴ፤ የመርሐ-ግብሩ አቀራረፅ በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳታፊ በሆነ ሂደት እንዲዘጋጅ የሚያስችል ብሔራዊ የአስተባባሪ ኮሚቴ እንዲሁም የድርጊት መርሐ-ግብሩን ረቂቅ አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ባለሙያዎችን ያካተተ ጽሕፈት ቤት በመንግስት ውሳኔ መሰረት ተቋቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ-ግብርን ለማዘጋጀት መንግስት መወሰኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ነሐሴ 26 ቀን 2003 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ የዝግጅት ሥራው በይፋ ተጀምሯል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ ዓላማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር ዋና ዓላማ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀናጀና ከሌሎች ዕቅዶች ጋር በተጣመረ አኳኋን፤ በሕገ መንግስቱ ለተረጋገጡት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የበለጠ ጥበቃ የሚያበጁ ስልቶችንና አቅጣጫዎችን መቀየስ ነው፡፡
ድርጊት መርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ በመዳሰስ መሻሻልና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት፤ የሚሻሻሉበትንና የሚስተካከሉበትን አቅጣጫ ተልሞ የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎች ያሳካል፡-
Øየሀገራችንን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ባሕል የሚያጎለብቱ ስትራቴጅያዊ አቅጣጫዎችን ያመለክታል፡፡
Øለሚቀጥሉት ሦስት አመታት በሀገሪቱ የተቀናጀና ቀጣይነት ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች የማስከበሪያ አቅጣጫዎችን ያመለክታል፡፡
Øየሰብዓዊ መብቶች የግንዛቤ ማስፋፊያ ስራዎች የሚካሄዱበትን ስልቶችን ያመለክታል፡፡
Øሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበሩና በማረጋገጡ እንቅስቃሴ መንግስት በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 እና ሌሎች ሁኔታዎች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በተለይም ከብዙሃን ማህበራት እና ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲሁም ከልማት አጋሮች ጋር በትብብርና በቅንጅት መስራት የሚችልበትን አቅጣጫዎችን ያመላክታል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ ግብ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር ግብ፤ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ዋስትና ያገኙትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ በማስፋፋትና በማሟላት ረገድ ሲከናወኑ የነበሩትን ፍሬያማ ተግባራት በዚህ ብሔራዊ ሰነድ አማካይነት በተቀናጀና በተዋሀደ መንገድ እንዲጠናከሩ በማድረግ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሻለ ሀኔታ ማረጋገጥ ነው፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት አደረጃጀት
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እና ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን በአባልነት የያዘውና በክቡር የፍትህ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ የአመራር ኮሚቴ የድርጊት መርሐ-ግብሩን ዝግጅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በበላይነት ሲመራ ቆይቷል፡፡
በብሔራዊ አመራር ኮሚቴው ስር የተደራጀው ሌላው መዋቅር፤ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ መስተዳድሮች ከፍተኛ ኃላፊዎችን በአባልነት ይዞ በክቡር የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሰብሳቢነት የተመራው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ የዘጠኙን ክልሎች ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮችን፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ምክትል ከንቲባዎችን፣ የክልል/ከተማ መስተዳድሮች ቢሮ ኃላፊዎችን እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አመራሮችን በአባልነት የያዘ ሲሆን ከ200 በላይ አባላትን ያካተተ አካል ነው፡፡ የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ ከሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችን የያዘ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የነበረው ሲሆን ከድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በቅርበት ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘበ፣ ሊተገበር የሚችል እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የድርጊት መርሐ-ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ባለሙያዎች ያሉበት የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር ዝግጅት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተደርጅቷል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ሕገ መንግስቱን፣ የሀገሪቱን ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ስትራቴጅዎችና ፕሮግራሞች መነሻ በማድረግ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያዘጋጀውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር መመሪያ በማጣቀስ የድርጊት መርሐ-ግብሩን የማዘጋጀት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስፈላጊው የፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍ እየተደገለት በኮሚሽኑ ቢሮ ውስጥ ተደራጅቶ መርሐ-ግብሩን የማዘጋጀት ስራውን አከናውኗል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተመደቡ እንዲሁም ለዚሁ ስራ የተቀጠሩ ሌሎች ባለሙያዎችን በአባልነት አካቷል፡፡ ጽሕፈት ቤቱንና አጠቃላይ የዝግጅቱን ሂደት የሚያማክሩ በሙያቸውና ተሞክሯቸው ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተመረጡ አማካሪዎችም ተመድበው በድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በብሔራዊ ደረጃ ካሉት አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት የየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ በድርጊት መርሐ-ግብሩ መካተቱን ለማረጋጋጥና በክልሉ የሚደረገውን የዝግጅት ሂደት ለመደገፍ የሚችሉ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ደረጃ የተዋቀሩ የየክልሎች/ከተማ መስተዳድሮች የብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ-ግብር አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ኮሚቴዎች በምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ወይም በምክትል ከንቲባዎች የሚመሩ ሲሆን የክልል/የከተማ መስተዳድር የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች፣ በክልል የሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸውን አደረጃጀቶችና አካላት በአባልነት አካተዋል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ የዝግጅት አካሄድና ስልት
የብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ-ግብር የማዘጋጀቱ ውሳኔ በመንግስት ይፋ ከተደረገበት ነሐሴ 26 ቀን 2003 ዓ.ም በኋላ የብሔራዊ አመራር ኮሚቴው በዝግጅቱ ውስጥ ያሉ አደረጃጀቶችን የስራ ሃላፊነት የሚዘረዝር ቢጋር በማፅደቅ፣ ከክልሎች ጋር ሊኖር ስለሚገባው ቅንጅት እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት እንዲጀመር አድርጓል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩን ለማዘጋጀት በቅድሚያ ሀገሪቷ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ከእያንዳንዱ መብት አንፃር ያለችበትን ደረጃ ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ሁኔታ ሊያሳይ የሚችል ጥናት በፌዴራልና በክልል/ከተማ መስተዳድር ደረጃ ከሁሉም ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችን በማሰባሰብ እንዲዘጋጅ ተደርጎ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተት የመነሻ ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡
በብሔራዊ አመራር ኮሚቴው የተቀመጠው ዋነኛ አቅጣጫ፤ የድርጊት መርሐ-ግብሩ ከተዘጋጀ በኋላ በትግበራው ሂደት ህብረተሰቡ በባለቤትነት የሚረባረብበት እንዲሆን፤ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን ያንፀባረቀና ደረጃውን የጠበቀ ዕቅድ ይሆን ዘንድ የዝግጀቱ ሂደት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ተሳትፎን ያረጋገጠና መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን ሀሳብ ያካተተ ሊሆን እንደሚገባና ይህም ተሳትፎ የድርጊት መርሐ-ግብር ሰነዱን ከማዘጋጀቱ ባልተናነሰ ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት በድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት ላይ ግብዓት የሚሰጡበት መንገድ ተመቻችቶ የተለያዩ የግብዓት የማሰባሰቢያ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው የመጀመሪያውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በህዳር 17 እና 18 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያካሄደ ሲሆን በዚሁ መድረክ በሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሐ-ግብር ምንነት፣ ዝግጅት እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት አፈፃፀም አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ መነሻነትም የድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት በሁሉም አካላት ግንዛቤ እንዲያዝበት በማድረግ ለዝግጅቱ የጋራ ትብብር የሚደረግበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡
በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከክልሎቹ/ከተማ መስተዳድሮቹ አመራሮች፣ መረጃ ከሚሰበስቡ ባለሙያዎች እና ከሲቪል ማህበራትና ከህብረተሰቡ ጋር 33 (ሰላሳ ሦስት) የሚሆኑ የውይይት ወርክሾፖችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ መድረኮችም ለመርሐ-ግብሩ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ ሕብረተሰቡና ሲቪል ማህበራት ስለጉዳዩ ግንዘቤ እንዲኖራቸውና አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም የመንግስት አመራሮች በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው በዝግጅቱ ሂደት ያላቸውን ሁነኛ ሚና እንዲረዱ ለማድረግ፤ የሚያስችሉ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮች የተደረጉት የውይይት መድረኮች በዋናነት የሚከተሉት ናቸው፡-
· በክልሎች ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮችና በከተማ መስተዳድሮች ደግሞ ምክትል ከንቲባዎች የሚመሯቸው አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚህም ከኮሚቴዎቹ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር አቅጣጫዎቸን ለማስቀመጥ ተችሏል፡፡ ይህም የመርሐ-ግብሩ ዝግጅት በየክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እና በየከተማ መስተዳድሩ ምክር ቤት እውቅና አግኝቶ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጥኝነት የሚፈፀምበትን መሰረት ሊጥል የቻለ ነው፡፡
· የየክልሉ/ከተማ መስተዳድሩ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላትም በየክልል/ከተማ መስተዳድር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በድርጊት መርሐ-ግብሩ ለማካተት እንዲቻል መረጃዎችን ለይተው ለጽሕፈት ቤቱ የሚሰጡና ከጽሕፈት ቤቱ ጋር በጋራ እንዲሰሩ ለመደቧቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች ስለ አጠቃላይ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች፣ ስለ መርሐ-ግብሩ ፅንሰ ሃሳብ፣ ስለ ዝግጅቱና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ስልጠና እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በተዘጋጁት የመረጃ ማሳባሰቢያ የፅሁፍ መጠይቆች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ባለሙያዎቹ መጠይቆችን በመረጃ እየሞሉ እንዲሁም የየመስሪያ ቤቶቹን ዕቅዶች፣ የአፈፃፀም ሪፖርቶች፣ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጅዎች እና ሌሎች አስፈላጊ የተባሉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ለጽሕፈት ቤቱ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡
· በየክልሎች/በየከተማ መስተዳድሮች ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከሀይማኖት መሪዎች፣ ከመንግስት ሰራተኞች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በድርጊት መርሐ-ግብሩ ዙሪያ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህም ሲቪል ማህበራቱና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ስለ ድርጊት መርሐ-ግብሩ ግንዛቤ እንዲኖረውና ሃሳቡን እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡
በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮች በተደረጉት መድረኮች የተገኙት ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችም ተሰብስበው ተቀምረዋል፡፡ እነዚህም የምክክር መድረኮች በየክልሎቹ/ከተማ መስተዳድሮቹ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ከፍተኛ ሽፋን እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን የሚዲያ አካላትም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲይዙ በየመድረኮቹ ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ከምክክር መድረኮቹ በተጨማሪ ማንኛውም ግለሰብ፣ የሚመለከተው በጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በድርጊት መርሐ-ግብሩ ውስጥ ሊካተቱ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ሃሳቦች ለጽሕፈት ቤቱ በስልክ፣ በኢሜይል፣ በደብዳቤ እንዲሁም በአካል ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደርጓል፡፡ ለዚህ መሰሉ ተሳትፎ የተዘጋጁና በተለያዩ የሀገሪቱ ቋንቋዎች የቀረቡ የጥሪ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ ሃሳቦች ለጽሕፈት ቤቱ ቀርበውና ተቀምረው እንደየአግባቡ በድርጊት መርሐ-ግብሩ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በመላ ሀገሪቱ ከተለያዩ ምንጮች በተለያዩ መንገዶች የተገኙትን መረጃዎችና ግብዓቶች በመቀመር የድርጊት መርሐ-ግብሩን አዘጋጅቷል፡፡ የድርጊት መርሐ-ግብሩ የመጀመሪያ ረቂቅ ከተዘጋጀ በኋላ በየደረጃው በብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ስራ አስፈፃሚ ቀጥሎም በብሔራዊ አመራር ኮሚቴው በተለያዩ ጊዜያት ሰፋ ያለ ጊዜን በመውሰድ ውይይቶች እየተደረጉበት የተሰጡ ማስተካከያ ሀሳቦችን በማካተት እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
ሀገሪቷ ከሰብዓዊ መብት አፈፃፀም አንፃር ያለችበት ሁኔታ፣ ያሉት ችግሮችና ተግዳሮቶች፣ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት፣ ተግባራቱን ሊያከናውኗቸው የሚገቡ አካላት እንዲሁም መርሐ-ግብሩ የሚፈፀምበትን ስልት እና መሰል ጉዳዮችን አካትቶ የድርጊት መርሐ-ግብሩ ከተረቀቀ በኋላ በግንቦት 6 እና 7 ቀን 2004 ዓ.ም የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ሁለተኛው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ቀርቧል፡፡ በዚህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ በጽሕፈት ቤቱ ተዘጋጅቶ በብሔራዊ አመራር ኮሚቴ፣ በብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴና በአማካሪዎች በየደረጃው ሰፊና ጥልቅ ውይይት ተደርጎበት የዳበረው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብሩ ረቂቅ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ጉባኤውም የድርጊት መርሐ-ግብሩን ሊያዳብሩ የሚችሉ ግብዓቶችን በመስጠትና የማስፈፀሚያ ስልቱን በመወሰን የተቀበለው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የድርጊት መርሐ-ግብሩ በዚህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በተሰጡ ግብዓቶች፣ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች የመንግስት ተቋማት በፅሁፍ አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ በተገኙት አስተያየቶች ሰነዱ እንዲዳብር ከተደረገ በኋላ በብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ስራ አስፈፃሚ እና በብሔራዊ አመራር ኮሚቴው በጋራ መድረክ ታይቶ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአመራር ኮሚቴው ሊፀድቅ ችሏል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ ግብዓቶች
የፌዴራልና የክልል ሕግጋተ መንግስት፣ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ስትራቴጅዎች፣ ፕሮግራሞች፣ የእድገትና የትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ፣ የፌዴራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች ዕቅዶች፣ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች፣ በመንግስት በይፋ የወጡ አሀዛዊ መረጃዎች፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ፖሊሲ አስፈጻሚ የመንግስት አካላት የተገኙ መረጃዎች፣ በመንግስት የተከናወኑ ጥናታዊ ፅሁፎች፣ በተለያዩ የህዝብ መድረኮች የተነሱ ሃሳቦች፣ በግለሰቦች፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እና በተለያዩ አካላት የተሰባሰቡ ሃሳቦች፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁሉ-አቀፍ የግምገማ መድረክ (ዩኒቨርሳል ፔሪዮዲክ ሪቪው) የተሰጡ አስተያያቶች፣ ለተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት አካላት በመንግስት የቀረቡ ሪፖርቶችና የተሰጡ ግብረ መልሶች እና ሌሎችም ጠቃሚ የሆኑ ፅሁፎች ለድርጊት መርሐ-ግብሩዝግጅት እንደግብዓት አገልግለዋል፡፡
በዚህ መሰረት የተለያዩ መረጃዎች ከተለያዩ አካላት ከተሰበሰቡ በኋላ ከእያንዳንዱ መብት አፈፃፀም አንፃር የሚኖራቸውን ፋይዳ፣ መብቶቹ ሊያካትቷቸው ከሚገቡት መለኪያዎች ወይም አመላካቾች አኳያ ተጠናቅሮና ተቀምሮ የሀገሪቱን የአቅም ሁኔታና የዕቅድ ዘመኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ችግር ፈቺ ሊሆኑ የሚችሉና በተግባር ሊተገበሩ የሚችሉ ተግባራትን የያዘ የድርጊት መርሐ-ግብር ሊዘጋጅ ችሏል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ ወሰን
ይህ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን፣ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች መብቶችን (የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአረጋውያን፣ ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች መብቶች) በዝርዝር የዳሰሰ እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰነዱ የልማትና የአካባቢ ደህንነት መብቶችን ይሸፍናል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ በዕቅድ ዘመኑ ከመንግስት አቅም አንፃር ሊከናወኑና ሊፈጸሙ የሚችሉ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በመምረጥ የተዘጋጀ ሲሆን “ሰብዓዊ መብቶች የተሳሰሩ፣ ተደጋጋፊና የማይነጣጣሉ ናቸው” በሚለው መርህ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫን ተከትሏል፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ፈርጆችን ሁለንተናዊና ያልተከፋፈለ አፈፃፀም ለማረጋገጥ የተከናወኑና የሚከናወኑ ተግባራትን ፋይዳ ታሳቢ ያደረገና ተጨባጭ የሆኑና ተለይተው የታወቁ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ያተኮረ መርሐ-ግብር መሆኑን በማስመር ሊደረስበት የሚችል ግብን በማስቀመጥ፤ የመብቶቹን ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም መብቶቹን የበለጠ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ወደ አንድ ተጨባጭ ግብ የሚያደርሱ እርምጃዎችን ያካተተ እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡
የድርጊት መርሐ-ግብሩ በስድስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ምዕራፍ አንድ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መሰረታዊ ገፅታዎችን ሲዳስስ፤ ምዕራፍ ሁለት ደግሞ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን በዝርዝር ይመለከታል፡፡ ምዕራፍ ሦስት በአንፃሩ፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የባሕል መብቶችን ሲቃኝ፤ ምዕራፍ አራት ደግሞ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት መብቶቻቸውን ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከት ነው፡፡ የአካባቢ ደህንነትና የልማት መብቶች በምዕራፍ አምስት ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ የመርሐ-ግብሩ የማስፈፀሚያ፣ የክትትልና የግምገማ ስርዓት በምን መልኩ ሊዘረጋ እንደሚገባ ዝርዝር ጉዳዮችን በማካተት ተዘጋጅቷል፡፡
በድርጊት መርሐ-ግብሩ በተለይ ስለ እያንዳንዱ መብት ሁኔታ በተዳሰሰበት በምዕራፍ ሁለት፣ ሦስትና አራት በይዘት ረገድ የሚከተሉት ጉዳዮች ተካትተዋል፤
· የእያንዳንዱን የሰብዓዊ መብት ወሰንና ሽፋን እንዲሁም የመብቱ መሰረት የሆኑት የሕገ መንግስትና የዓለም አቀፍ ህጎች ማዕቀፍን ማመላከት፤
· ከመብቱ አኳያ በሀገሪቱ የወጡ ፖሊሲዎችና ከመብቶቹ ጋር ቀጥታ ተዛማጅነት ያላቸው ህጎች፤
· የተጠቀሰውን መብት ለማስከበር፣ ለማስጠበቅና ለሟሟላት በመንግስት የተወሰዱ ዋና ዋና አስተዳደራዊና ተቋማዊ እርምጃዎችን ማመላከት፤ ከዚህ አኳያ ሰብዓዊ መብቶችን በማስጠበቅ ረገድ መንግስት የወሰዳቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችና ያስከተሏቸውን ከፍተኛ ውጤቶች ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለዚህ የድርጊት መርሐ-ግብር አመላካች ሊሆኑ የሚችሉ ዋና ዋና ክንዋኔዎች ተመላክተዋል፤
· መብቶቹን በማክበር፣ በማስጠበቅና በሟሟላት ረገድ የተስተዋሉ ችግሮችና ተግዳሮቶችን መለየትና ማስቀመጥ፤
· በመጨረሻም እነዚህን ችግሮችና ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና በዕቅዱ ዘመን ውስጥ መብቶቹን ለማክበር፣ ለማስጠበቅና ለሟሟላት መከናወን የሚገባቸውን ዋና ዋና ተግባራት በዕቅድ መልክ በማስቀመጥ፤ የተግባራቱ ፈጻሚ አካላትንና የአፈፃፀሙን የክትትልና ግምገማ ስርዓትን በማስቀመጥ የተሰናዳ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርኃ-ግብር ሙሉን ሰነድ ከዚህ ያውርዱ