By muluken seid hassen on Friday, 08 March 2019
Category: Labor and Employment Blog

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት በተሰጠ የፍርድ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ የአፈጻጸም ክስ በይርጋ ቀሪ ስለሚሆንበት የሕግ አግባብ

መግቢያ

አፈጻጸም ማለት አንድ መብቱ በፍርድ ውሳኔ እንዲከበር ለፍርድ ቤት ክስ ያቀረበ ሰው የፍርድ ውሳኔ አግኝቶ በፍርዱ መሰረት ሳይፈጸምለት ሲቀር ፍርዱ የተፈረደበት ወገን እንደ ፍርዱ እንዲፈጽም የሚገደድበት የሕግ ሥርዐት ነው፡፡ ይህ ስርዐት የሚመራውም በፍትሐብሔር ሥነ- ሥርአት ሕግ ቁጥር 375 ጀምሮ በተደነገጉ ድንጋጌዎች መሰረት ሲሆን በእነዚህ የሕግ ማእቀፎች ተንተርሶ መብቱ እንዲፈጸምልት ሚጠይቅ ወገን የፍርድ ባለመብት ሲባል እንዲፈጽም የሚገደደው ደግሞ የፍርድ ባለእዳ ተብሎ ይጠራል፡፡

የፍርድ ባለእዳው እንደፍርዱ ሊፈጽም ካልወደደ የፍርድ ባለመብት የሆነው ወገን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 378 መሰረት ፍርዱ እንዲፈጸም አቤቱታውን ፍርዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት  አልያም በሥነ-ሥርአት ሕጉ አንቀጽ 375/1/ በተገለጸው መሰረት ፍርዱን እንዲያስፈጽም የታዘዘ ፍርድ ቤት ያለ እንደሆነ ለዚያው ፍ/ቤት የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

የፍርድ ባለመብት የሆነው ወገን ባለእዳው ላይ የአፈጻጸም ክስ የሚያቀርብበት የጊዜ ገደብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 384 ላይ የተመለከተ ሲሆን የጊዜ ገደቡም “ፍርድ እንዲፈጸም ማመልከቻ ቀርቦ አስር አመት ከቆና ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሌላ ማመልከቻ በማቅረብ ነገሩን ለማንቀሳቀስ ፍርድ እንዲፈጸም ለመጠየቅ አይቻልም” በማለት በሥነ ሥርዐት ሕጉ ተመልክቷል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 377/96 እንዲሁም በማሻያው አዋጅ ቁጥር 494/98 መሰረት ተደርጎ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ አቤቱታዎች በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የፍርድ ውሳኔ እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡ ይህን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በውሳኔው ተጠቃሚ የሆነ ወገን እንደ ፍርድ ባለመብትነቱ ባለእዳው እንደፍርዱ አልፈጽምም ያለው እንደሆነ ፍርዱ ይፈጸምለት ዘንድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 378 መሰረት ፍርዱን ለፈረደው አልያም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 375/1/ መሰረት ፍርዱን ያስፈጽም ዘንድ በተለይ የታዘዘ ፍርድ ቤት ያለ እንደሆነ ለዚያው ፍርድ ቤት የአፈጻጸም ክሱን ያቀርባል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ የሚቀርቡ የአፈጻጸም ክሶችን በተመለከተ በተግባር አከራካሪ ሲሆን ሚስተዋለው ጉዳይ የፍርድ ባለመብት የሆነ ወገን የአፈጻጸም ክሱን ሊያቀርብ የሚችልበት የጊዜ ገደብ /የይርጋ ደንብ/ የሚመራው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 384 በተገለጸው በ10 አመት የይርጋ ደንብ ነው ወይስ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162 ላይ በተገለጸው የአንድ አመት ይርጋ ጊዜ ነው የሚለው ሲሆን ይህን ሁኔታ በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ችሎቱ ከሠጠው አስገዳጅ ውሳኔ አንጻር የግል ምልከታዬን በማከል እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡  

አዋጅ ቁጥር 377/96 እንዲሁም ማሻሻያ አዋጁ 494/98 መሰረት ተደርጎ በተሰጠ የፍርድ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ የአፈጻጸም ክስ በይርጋ ቀሪ ስለሚሆንበት የሕግ አግባብ

በአዋጅ ቁጥር 377/96 እና ማሻሻያ አዋጁ 494/98 መሰረት በማድረግ ከስራ ማስወጣትን ጨምሮ ሌሎች የዲሲፒሊን እርምጃዎች ላይ፤ የሥራ ውሉ መቋረጥ ወይንም መሰረዝን የሚመለከቱ ጉዳዮች፤የስራ ሰአትን ፤የተከፋይ ሂሳብን ፤ፈቃድንና እረፍትን የሚመለከቱ ክሶች፤የቅጥርና ስንብት ማስረጃን ሰርተፍኬት መስጠትን የሚመለከቱ፤የጉዳት ካሳን የሚመለከቱ ክሶች ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥራ ክርክር ችሎት በማቅረብ የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኝ  ማድረግ የሚቻል መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 138 ላይ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ አግባብ የክስ አቤቱታው ለፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ውሳኔው በፍርድ ቤት አስገዳጅነት ይፈጸም ዘንድ የአፈጻጸም ክሱ መቼ መቅረብ አለበት የሚለውን የጊዜ ገደብ በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ላይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይህን መሰል የይርጋ ደንብ በአዋጁ የተቀመጠ ባለመሆኑ በአፈጻጸም ረገድ አስቸጋሪ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

በአንድ አንድ ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ እንዳስተዋልኩት የስራ ክርክርን መሰረት በማድረግ በተሰጠ ፍርድ ላይ ፍርዱ እንዲፈጸምለት የሚፈልገው ባለመብት የአፈጻጸም ክሱን ማቅረብ ያለበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 384 መሰረት የአፈጻጸም ክሱ የሚቀርብበት ፍርድ ውሳኔ ካገኘ ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር በ10 አመት የይርጋ ጊዜ ውስጥ ነው የሚል አቋም ያለ ሲሆን በሌላ በኩል የሚቀርበው መከራከሪያ ነጥብ አዋጅ ቁጥር 377/96 እንደሁም ማሻሻያ አዋጁን 494/98 መሰረት በማድረግ በተሰጠ ፍርድ ላይ የሚቀርበው የአፈጻጸም ክስ ሊቀርብ ሚገባው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 384 ላይ በተገለጸው በ10 አመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይሆን በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162 ላይ በተገለጸው ከፍተኛው የአንድ አመት የይርጋ ገደብ ውስጥ ነው የሚል ነው፡፡    

እንደ እኔ እምነት ከዘህ በላይ የገለጽኳቸውን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት ተደርጎ በተሰጠ ፍርድ ላይ የሚቀርብ የአፈጻጸም ክስ ሊቀርብ ሚገባው በአዋጁ አንቀጽ 162 ላይ በተገለጸው ከፍተኛ በሆነው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም÷ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ላይ የተሰጠ ፍርድ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ አፈጻጸም ሊቀርብበት ይችላል የሚለውን ጉዳይ መመክከት ያለብን ከአሰሪና ሰራተኛ ሕግ አላማ አንጻር ነው፡፡ በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ አላማ አሰሪና ሰራተኛ ግንኙነታቸውን መሰረታዊ በሆኑ መብቶችና ግዴታዎች ላይ መስርተው የኢንዱስትሪ ሰላምን በመፍጠር ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት በመተባበር በጋር እንዲሰሩ በማድረግ ላቅ ያለ ሚና መጫወት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 53527 በቅጽ 11 አስገዳጅ ውሳኔ የሰጠ ውሳኔ ሲሆን በውሳኔውም ላይ እንደገለጸው “በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ባለመብት የሆነ ወገን የአፈጻጸም ክሱን የሚያቀርብበት የይርጋ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ላይ ያልተገለጸ በመሆኑ ጉዳዩ ትርጓሜ የሚያሻው ነው በማለት ሕግ ሊተረጎም የሚገባው የሕጉን አይነተኛ አላማ በአዋጁ ከተካተቱ ድንጋጌዎች ጋር በማጣጣም ሊሆን ይገባል ሲል አንድ ሰራተኛ በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርአት ሕጉ ስር በተመለከተው የአስር አመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የአፈጻጸም መዝገብ ማስከፈት ይችላል ከተባለ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ሊያሳካ ያሰበውን ግብ ችግር ውስጥ የሚከተው ይሆናል፡፡ ሰራተኛው በጊዜውና በቦታው ተገኝቶ  ስራውን ካልሰራ አሰሪው ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል ተብሎ አይገመትም፡፡ በመሆኑም ለጉዳዩ አግባብነት የሚኖረው በአዋጅ ቁጥር 377/96 ስር የተመለከተው ከፍተኛው የአንድ አመት የይርጋ ጊዜ ለአፈጻጸም ማመልከቻ ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረጉ የአዋጁ አላማ ከማሳካት ረገድ ግድ የሚል ነው፡፡ አፈጻጸም የሚቀርብበት ፍርድ ቤትም የፍርድ ይፈጸምልኝ ጥያቄው በዚሁ ጊዜ ውስጥ የቀረበ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት” የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ አላማን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሠጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ መሰረት በማድረግ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት የተሰጠ ፍርድ እንዲፈጸም የሚቀርብ የአፈጻጸም ክስ ፍርዱ ከተሰጠ ቀን አንስቶ በሚቆጠር አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያልቀረበ እንደሆነ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡

 

መደምደሚያ

የስራ ክርክርን መሰረት ተደርጎ የሚቀርብ የአፈጻጸም ክስ የይርጋው ጊዜ መቆጠር ያለበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 384 ላይ የተቀመጠውን አጠቃላይ የአፈጻጸም ይርጋ ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ሳይሆን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የተቀረጸበትን መንፈስ መሰረት በማድረግ የሕጉን አላማ በጠበቀ መልኩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162 ላይ በተገለጸው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ይፈጸምልኝ ክስ ያልቀረበ እንደሆነ መብቱ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡  

Related Posts

Leave Comments