የአንድ ተሸከርካሪ ቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ እንዴት ይተመናል?
የመኪና ቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ የሚተመነው በመኪናው የሲ.ሲ መጠን፣ መኪናው በተመረተበት ጊዜ እና መኪናው በተገዛበት ዋጋ ነው፡፡ እነዚህን ሦስት መተመኛዎች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. የሲ.ሲ መጠኑን መሠረት በማድረግ
ይህ የተሸከርካሪውን የሞተር ጉልበት/የሲሊንደር አቅም/ መሠረት ያደረገ ነው፡፡
1.1 የተሸከርካሪው የሲሊንደር ይዘት ከ1300 ሲ.ሲ በታች ከሆነ
· ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 125.0075%
· ለመገጣጠም የሚገባ 59.975%
1.2 የተሸከርካሪው የሲሊንደር ይዘት ከ1300 – 1800 ሲ.ሲ ከሆነ
· ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 176.24%
· ለመገጣጠም የሚላክ 96.2%
1.3 የተሸከርካሪው የሲሊንደር ይዘት ከ1800 በላይ ከሆነ
· ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 244.55%
· ለመገጣጠምየሚላክ 100.05
2. የተመረተበት ጊዜ
ለማነፃፀሪያ ሲባል አንድ ዓመት ወደፊትና ወደኋላ የሆነ የምርት ዘመን ማለት ነው፡፡
ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ሲገቡ የእርጅና ቅናሽ ከተሸከርካሪው የምርት ዘመን በመነሳት እስከ ሦስት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከፎብ /Free on Board or FOB/ ላይ በየዓመቱ የሚደረግ የ10 በመቶ ቅናሽ ሲሆን ቅናሹ ከ30 በመቶ አይበልጥም፡፡
ተ.ቁ |
ተሸከርካሪው ከተመረተበት ቀን ጀምሮ የቆየበት የአገልግሎት ዘመን |
የሚደረገው የእርጅና ቅናሽ መጠን በመቶኛ (ከዋጋ ላይ) |
1 |
ከአንድ አመት በታች |
0% |
2 |
አንድ ዓመት |
10% |
3 |
ሁለት ዓመት |
20% |
4 |
ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ |
30% |
ይህ በአንቀፅ የተደነገገ ሲሆን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሸከርካሪዎች ከተመረቱ በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት ወይም ጥቅም ላይ ሳይውሉ ከአንድ አመት በኋላ የቆዩ ቢሆንም የእርጅና ቅናሽ ሳይደረግባቸው አዲስ በነበሩበት ጊዜ ያለው ዋጋ የቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
3. የተገዛበት ዋጋ
በጉምሩክ ተቀባይነት ሲያገኝ የተገዙበት ዋጋ ላይ በአስመጪ እስከ ኢትዮጵያ መግቢያ በር ድረስ የተከፈሉ/የሚከፈሉ አጠቃላይ ወጪዎችን በአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 96 መሰረት በመደመር እና የተሸከርካሪ የታሪፍ ምጣኔን በማባዛት ማስላት ነው፡፡
ሆኖም የተገዙበት ዋጋ (FOB price) በጉምሩክ ተቀባይነት በሚገኝበት ጊዜ በመረጃ ተቋም ካለው ተመሳሳይ (አንድ ዓይነት) ተሸከርካሪዎች ጋር በማነፃፀርያ ዋጋ በመውሰድ ተጨማሪ ወጪዎችን በመደመርና ከታሪፍ አመዳደቡ ጋር በማነፃፀር የተገኘውን ውጤት ባለው ወቅታዊ የወጭ ምንዛሬ በመቀየር ቀረጥና ታክሱን ማስላት ይቻላል፡፡
ተሸከርካሪዎች የዋጋ አተማመን ስሌት
1. ለአዲስ ተሸከርካሪዎች (For new car)
Duty paying value = FOB + Freight + insurance + other cost
2. ላገለገሉ ተሸከርካሪዎች (For used car)
DPV = (FOB - depreciation)+ Freight + insurance + others
ተጨማሪ ክፍያዎች በተጨባጭ መረጃ እና ማስረጃ ሊተመኑ ካልቻሉ በአዋጁ አንቀፅ 96 በተደነገገው መሠረት በሚከተሉት ሁኔታዎች በማስላት በቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ይካተታሉ፡፡
የትራንስፖርት ወጪ /Freight/ = 5% of FOB value
የኢንሹራንስ ወጪ /Insurance/ = 2% of FOB value
መግለጫ
ያገለገሉ ተሸከርካሪ የምንለው በተመረተበት የምርት ዘመን በኋላ ጥቅም ላይ የቆየ ባለሞተር ተሸከርካሪ ነው፡፡
የፎብ ዋጋ (FOB price) ማለት የዕቃው መሸጫ ዋጋ እና በላኪ ሀገር እስከ የመጨረሻ መጫኛ ቦታ (ወደብ) ድረስ ለዕቃው የተከፈለ/የሚከፈል ወጪ ድምር የሚያመለክት አንዱ የአለምአቀፍ የንግድ ስምምነት ዓይነት (INCOTERM) ሲሆን በመርከብ ለማስጫን፣ ለማጓጓዝ፣ ለማራገፍ፣ ለመንከባከብ የወጣ ሲሆን ለኢንቨስትመንትና ሌሎች የሚወጡ ወጪዎችን አይጨምርም፡፡
የሲ.አይ.ኤፍ ዋጋ (CIF price) ማለት የዕቃው የመጫኛ ዋጋ እና በላኪ አገር እስከ የመጨረሻ ቦታ (ወደብ) ድረስ ለዕቃው የተከፈለ/የሚከፈለ ወጪ፣ የኢንሹራንስ፣ ዕቃውን ለማጓጓዝ የወጣ ወጪ ድምር የሚያመለክት አንዱ የዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ዓይነት (INCOTERM) ሲሆን እስከ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ክልል የመጀመሪያ መግቢያ በር ድረስ ዕቃውን ለማስጫን፣ ለማራገፍ፣ ለመንከባከብ እና ለዕቃው የተከፈሉ/የሚከፈሉ ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡
Originally written by: ዳንኤል ታደሰ እና ትግስት ሙሉጌታ