በህዝባዊ ሥፍራዎች ሲጋራ ማጨስ በሕግ መከልከሉ፤ ከፍተኛ ታክስ በሲጋራ ምርቶች ላይ መጣሉ፣ የሲጋራ ማስታወቂያዎች እንዳይሠራ መከልከሉና የሲጋራን የጤና ጠንቅነት ለዜጐች በስፋት ማስተማር ባደጉ አገራት ላይ የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የየአገሮቹ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የገቢ አቅማቸው እያደገ መምጣት፣ ግዙፎቹ የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ታዳጊ አገራት ማዞር፣ የዜጐች ግንዛቤ አናሣ መሆኑና በትምባሆ ምርቶች ግብይትና አጠቃቀም ላይ ገዳቢ ሕጐች አለመኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም ከትምባሆ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመቅረፍ በዓለም አቀፉ መድረክ ስምምነት (ኮንቬንሽን) ስታጸድቅ በሃገር ደረጃ ደግሞ የተለያዩ ሕጎችን አውጥታለች፡፡ እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች በቅደም ተከተል የሚከተሉት ናቸው፡፡
አዋጅ ቁጥር 661/2002 - የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ፤
ደንብ ቁጥር 299/2006 - የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፤
አዋጅ ቁጥር 822/2006 - የዓለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን ማጽደቂያ አዋጅ
መመሪያ ቁጥር 28/2007 - የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ
ዛሬ መብትና ግዴታዎን ይወቁ በሚለው ክፍል ውስጥ ይህንን ርዕስ ለማንሳት የወደድነው የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያወጣውን የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 28/2007) መሠረት በማድረግ ከትንባሆ ጋር የተገናኙ መብትና ግዴታዎችን ለመዳሰስ በማሰብ ነው፡፡
የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያው የወጣው የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ማጽደቂያ አዋጅ አንቀጽ (4)፣ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀጽ 55(3) እና በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 98 መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ዓላማውም ትምባሆን በመጠቀምና በትምባሆ ጢስ መጋለጥ ምክንያት በኅብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን የጤና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ጉዳቶች ለመከላከል፤ እና ኢትዮጵያ በአለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን፣ የኮንቬንሽኑ ማስፈጸሚያ ጋይድላይኖች፣ እና አግባብ ባላቸው የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ፕሮቶኮሎች ውስጥ የገባችውን ግዴታዎች እንደአግባቡ ለማስፈጸም ነው፡፡
በደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 36 እና በመመሪያ ቁጥር 28/2007 አንቀጽ 4 ትምባሆን በማንኛውም ሕዝብ በሚሰበሰብበት ወይም በሚገለገልበት ቦታ ማጨስ ክልክል ነው በማለት ይደነግጋሉ፡፡
በእነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች መሠረት ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ከበር መልስ ያሉ ቦታዎች፣ ከበር መልስ ያለ የሥራ ቦታ፣ እና በሕዝብ መጓጓዣዎች ውስጥ ማጨስ የተከለከለ ነው፡፡
ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ቦታዎች ማለት ለሕዝብ ክፍት የሆነ ወይም የማህበረሰቡ አባል የሆነ ሰው ሊገባበት የሚችል ማንኛውም ስፍራ ሲሆነ ከበር መልስ ያለ ቦታ (indoor place) ማለት ደግሞ የተሰራበት ቁሳቁስ ዓይነት እና መዋቅሩ ቋሚ ወይም ጊዜያዊ መሆኑ ሳይወስነው ማንኛውም በጣሪያ የተሸፈነ እና አንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆነ ግድግዳ የተከለለ ስፍራ ማለት እንደሆነ ከሕጎቹ ለመረዳት ይቻላል፡፡ የሥራ ቦታ ማለት ደግሞ በክፍያም ይሁን ካለ ክፍያ አንድ ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የሥራ ኃላፊነታቸውን የሚያከናውኑበት ስፍራ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚጠቀሙበት የጋራ ስፍራን አንደሚጨምር መመሪያው ይደነግጋል፤
መመሪያው በተለይ በሚከተሉት የሕዝብ ቦታዎች ማጨስ የተከለከለ መሆኑን ያብራራል፡፡
በጤና ተቋማት እና በትምህርት ተቋማት፤
በምግብ ቤቶች፣ በሆቴሎች ወይም በሌላ የመመገቢያ ቤቶች፣ በመጠጥ ቤቶች፣ በምሽት ክለብ፣ በካፌዎች፣ በመዝናኛ ክበብ፣
ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና በየትኛውም ዓይነት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤
በመሥሪያ ቤት ኮሪደሮች፣ እንግዳ መቀበያ ቦታዎች፣ በሊፍት እና ደረጃዎች ላይ፣
በመጸዳጃ እና መታጠቢያ ቦታዎች፤
በፋብሪካዎች እና የንግድ መደብሮች፤
ሲኒማ፣ ቲያትር እና ቪዲዮ ቤቶች፣ የሙዚቃ ማሳያ አዳራሾች፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች እና ሌሎች ትዕይንት የሚደረግባቸው ቦታዎች፤
የመስህብ ቦታዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፤
ባቡር ጣቢያ፣ አውሮፕላን ጣቢያ እና አውቶቢስ ጣቢያ፤
ለህፃናት ወይም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች አገልግሎትን በሚሰጡ እንደ ህፃናት መጫወቻ ስፍራ፣ መዋለ ህጻናት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ማንኛውም ህፃናት የሚሰበሰቡበት ቦታ እና ወጣት ማዕከላት በመሳሰሉት ቅጥር ግቢ ውስጥ፤
በሕዝብ ማጓጓዣ አውቶብስ፣ ታክሲ፣ ባቡር፣ አየር መጓጓዣ፣ አምቡላንስ ወይም በማንኛውም ሕዝብን ለማጓጓዝ የሚያገለግል መጓጓዣ ውስጥ ማጨስ የተከለከለ ነው፡፡
ህፃናት ወይም ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች ለሆኑ ልጆች አገልግሎት በሚሰጡ ቦታዎች፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከትምህርት እና ጤና ተቋም ክፍሎች በስተቀር ከላይ በተመለከቱት ሥፍራዎች ላይ ማጨስ የሚቻለው ለዚሁ ዓለማ ተብሎ የተከለለ ወይም የተለየ የማጨሻ ቦታ ካለ ብቻ ነው፡፡ ይህ ለማጨስ የተከለለ ወይም የተሰየመ ክፍል ለብቻው የአየር ማናፈሻ (ventilation) የተገጠመለት መሆን ያለበት እንደሆነም መመሪያው ይደነግጋል፡፡ ይህ የማጨሻ ክፍል የማያጨሱ ሰዎች ለማንኛውም አገልግሎት ወይም ዓላማ እንዲያልፉበት፣ እንዲዘዋወሩበት ወይም በየትኛውም መልኩ እንዲገቡበት በሚያደርግ ሁኔታ ያልተሰራ መሆን ያለበት ሲሆን ትምባሆ ለሚያጨሱ ተገልጋዮች ተብሎ ካልሆነ በስተቀር በዋናነት የትምባሆ ምርትን ለማስጨስ ታስቦ የተከለለ መሆን እንደሌለበትም መመሪያው በግልጽ ይደነግጋል፡፡
ክፍት የሆነ የሕዝብ ቦታ ወይም ማጓጓዣ ባለንብረት ወይም ሌላ ኃላፊነት ያለበት ሰው ወይም የሥራ ቦታን በተመለከተ አሰሪ ወይም ሌላ ኃላፊነት ያለበት ሰው በመመሪያ በተፈቀደው የተከለለ ቦታ ካልሆነ በስተቀር የሲጃራ መተርኮሻ ሳህን እንዲቀመጥ መፍቀድ እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡
ለሕዝብ ክፍት የሆነ ቦታ ወይም ማጓጓዣ ባለንብረት ወይም ሌላ ሀላፊነት ያለበት ሰው ወይም የሥራ ቦታን በተመለከተ አሰሪ ወይም ሌላ ሀላፊነት ያለበት ማንኛውም ሰው በጉልህ የሚታይ ማጨስ በሕግ የተከለከለ ነው የሚል ማሳሰቢያ ከነምልክቱ በአማርኛ እና/ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ወይም በአካባቢው የሥራ ቋንቋ እና በአማርኛ መለጠፍ አለበት፡፡
ለሕዝብ ክፍት የሆነ ቦታ ወይም ማጓጓዣ ባለንብረት ወይም ሌላ ኃላፊነት ያለበት ሰው ወይም የሥራ ቦታን በተመለከተ አሠሪ ወይም ሌላ ኃላፊነት ያለበት ማንኛውም ሰው የትምባሆ ምርት በማይጨስበት ቦታ ላይ የመመሪያውን ድንጋጌዎች የማስከበር እና እንዳይጣስ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች መመሪያው እርምጃዎችንም እንዲወስዱ ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከሥልጣናቸው መካከል ማጨስ በሕግ ያለመፈቀዱን የሚገልጽ ምልክት በመግቢያና በሌላ አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ መለጠፍ፣ ደንቦች በአግባቡ እየተተገበሩ መሆናቸውን መከታተል እንዲሁም ሰዎች እንዳያጨሱ መከልከል፣ ፈጽመው የተገኙ እንደሆነ አካባቢውን ወይም የሕዝብ መጓጓዣውን ለቀው እንዲወጡ ማድረግ፣ አግባብ ከሆነ አገልግሎቱን ማቋረጥ እና ለሕግ አካል ማሳወቅ ይገኙበታል፡፡
ከትምባሆ ሽያጭ ጋር ተያይዞ መመሪያው ከከለከላቸው ድርጊቶች መካከል የትምባሆ ምርትን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች ማቅረብ ወይም መሸጥ መከልከሉ ዋናውና አንዱ ነው፡፡ ዕድሜን ለማጣራት ሻጩ የገዢውን ዕድሜ ከተጠራጠረ ሕጋዊ ፓስፖርት፣ መንጃ ፈቃድ ወይም የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ በማየት ማረጋገጥ እንደሚችልም መመሪያው ይደነግጋል፡፡ የትምባሆ ምርቶችን በድረ-ገጽ መሸጥን ጨምሮ የትንባሆ ምርትን ለመሸጥ ወይም እንዲሸጥ ለማድረግ ወይም ሽያጩን ለማቀላጠፍ ገዢ እና ሻጭ በአንድ ተመሳሳይ ቦታ ፊት ለፊት ሳይገናኙ የሚደረግ የትንባሆ መገበያ መንገድ መጠቀም መመሪያው በጥብቅ የከለከለው ድርጊት ነው፡፡
መመሪያው አስፍሮት ከሚገኘው ድንጋጌዎች መካከል “ሲጋራን በነጠላ ስለ መሸጥ” የሚል ይገኝበታል፡፡ በመመሪያው አንቀጽ 18 መሠረት የትንባሆ ምርት የሚሸጠው በመመሪያው መሠረት የጤና ማስጠንቀቂያ ይዞ እንደ አግባቡ የተወሰነውን የሲጃራ ወይም ትንባሆ ቁጥር ወይም ክብደት በያዘ ባልተከፈተ ፓኬት ወይም ማሸጊያ ታሽጎ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የሲጋራ ምርትን በነጠላ መሸጥ የተከለከለ ነው፡፡ “ነጠላ” ማለት በሲጋራ ፓኬት ውስጥ ከሚገኙ ሲጋራዎች ውስጥ በቁጥር አንዷን የሚገልጽ መሆኑንም መመሪያው በግልጽ ይደነግጋል፡፡
እንደ ድንጋጌው ከሆነ ሱቅ ሄደው አንድ ወይም ሁለት ወይም ማናቸውንም ቁጥር ነጠላ ሲጋራ መግዛት አይችሉም፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሲጋራ ለመግዛት ወደ ሱቅ ቢሔዱ ሻጩ አልሸጥም የማለት መብት አለው፤ ግዴታም አለበት፡፡
እንዴት ነው ይህንን ለማስፈጸም ይቻላል? እስቲ ሃሳባችሁን ጣል ጣል አድርጉ