- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4025
የኮ/መ/ቁ 172869 - አቶ በረከት ታደገኝ እና እነ አቶ ሳሙዔል አርከበ
የመ/ቁጥር 172869
ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- አቶ በረከት ታደገኝ ፡-ወኪል ማንያህልሻል ንቦ፡- ቀረቡ
ተከሳሾች፡- 1ኛ) አቶ ሳሙኤል አርከበ፡- ቀረቡ
2ኛ) ቢም አይቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ ጠበቃ ማቲያስ ግርማ፡- ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነው ከሳሽ ሰኔ 25 ቀን 2010 አሻሽለው ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽና 1ኛ ተከሳሽ እያንዳንዳቸዉ 50/100 የሆነ ድርሻ በመያዝ ዋናው ሥራው በዌብሳይት አማካኝነት የጨረታ መረጃዎች የሚሰጠዉን 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ቢም አይቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ የመሰረቱ መሆኑን፤በማህበሩ መመስረቻ ደንብ እንዲሁም ህደር 13 ቀን 2001 ዓ/ም እና ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ/ም በተደረገዉ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በጣምራ ሥራ አስኪያጅነት ለመምራት በሙሉ ድምጽ የወሰኑ መሆኑን በዚህም መሰረት የማህበሩን የባንክ ሂሳብ መክፈት ማንቀሳቀስ፤መዝጋት እንዲሁም የማህበሩን ንብረት አስይዞ የመበደር ስልጣን የከሳሽ እና የ1ኛ ተከሳሽ የጋራ ስልጣን መሆኑን ስራቸዉንም በጋራ ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን፡፡ ነገር ግን ከመስከረም 2009 ዓ.ን ጀምሮ በከሳሽ እና በ1ኛ ተከሳሽ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዉስጥ ያላቸዉን ተሳትፎ ያቆሙ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ አለመግባባቱ ከተከሰተ ጀምሮ ማስጠንቀቂ በመስጠት እና በማስፈራራት ተጽእኖ ሲያሳድሩባቸዉ የነበረ መሆኑን፤1ኛ ተከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር አግልግሎት በመስጠት የሚገኘዉን የአገልግሎት ክፍያ በቼክ እየሰበሰቡ በማህበሩ ስም ወደተከፈተ የባንክ የሂሰብ /Account/ ገቢ ማድረግ ሲገባቸዉ ከአሰራር ውጪ በጥሬ ገንዘብ እየተቀበሉ በካዝና ሲያስቀምጡ የቆዩ መሆኑን ከዚህም በላይ ያለከሳሽ ፈቃድ በጣምራ ሊንቀሳቀሱ የሚገባውን ገንዘብ ያለከሳሽ እውቅና 1ኛ ተከሳሽ አላግባብ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያባከኑ ከመሆኑም በላይ ከሳሽ ሊከፈላቸዉ የሚገባዉን የወር ደሞዝ እና የትርፍ ድርሻ ለመከፈል ፈቃደኛ ሊሆኑ ያልቻሉ መሆኑን፤1ኛ ተከሳሽ ከመደበኛው የማህበሩ ሂሳብ አሰራር ውጪ የማህበሩን ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ የነበረ መሆኑን በዚህም ምክንያት የማህበሩ ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ እንዲመረመር ጠይቀዉ 1ኛ ተከሳሽ ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ መሆኑን እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽ የማህበሩን ዌብሳይት እንዳይጠቀሙ ፓስዋርድና ዩዘር ኔም የቀየሩ መሆኑን ገልጸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከማህበሩ ሥራ አስኪያጅነት ተሽረው ከማህበሩ ባለአክሲዮኖች ውጪ የሆነ ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ እንዲሾም እንዲወሰንላቸዉ፤1ኛ ተከሳሽ የማህበሩን ዌብሳይት ዩዘር ኔምና ፓስዋርድ መቀየራቸው ተገቢ አይደም ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ፣ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ገቢ በቼክ እየተሰበሰበ በባንክ መቀመጥ ሲገባው በጥሬ ገንዘብ እየተሰበሰበ በቀጥታ ወጪ መደረጉ ተገቢ አይደለም ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ፣ያለ ከሳሽ ተሳትፎ በተናጠል በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት የተፈፀሙ ክፍያዎች በሙሉ ሕገወጥ ናቸው ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ፣ከመስከረም 2009 ጀምሮ ያለዉ የማህበሩ ሂሳብ በገለልተኛ ባለሙያ እንዲመረመር እንዲወሰንላቸዉ፤1ኛ ተከሳሽ በተናጠል የኢተዮጵያ ንግድ ባንክ፣ህብረት ባንክ እና ከወጋገን ባንክ ገንዘብ ማውጣት ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ጥፋት ምክንያት በማህበሩ ላይም ሆነ በከሳሽ ላይ የደረሰዉን ጉዳት፤ያልተከፈላቸዉውን ደሞዝ እንዲሁም ያልተከፈላቸውን የትርፍ ደርሻ አስመልክቶ ክስ የማቅረብ መብታቸዉ እንዲጠበቅላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ ተከሳሾች እንዲተኩ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰነድ ማስጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስከሮች ቆጥሯል፡፡ ተከሳሾች የከሳሽ ክስ ከነ አባሪዎቹ ደርሷቸዉ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልሳቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት መከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዉ ላይ ግራ ቀኙን ከከራከረ በኃላ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ውድቅ ያደረጋቸዉ በመሆኑ እና ዝርዝሩም ከመዝቡ ሰፍሮ የሚገኝ ስለሆነ ከዚህ ማሰፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡
ተከሳሾች በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ 1ኛ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ ዛቻና ማስፈራራት ያልፈጸሙ መሆኑን ከሳሽ ስራቸዉን የለቀቁት በገዛ ፈቃዳቸዉ መሆኑን ከከሳሽ ጋር አለመግባባት የተፈጠረበት ምክንያት ከሳሽ ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ/ም ግብርን ለመሰወር ያቀረቡትን ሀሳብ ባለመቀበላቸዉ መሆኑን ከሳሽ ከሰኔ 20-26 2008 ዓ/ም ባለው ግዜ የማህበሩን ድህረገጽ ኮድ ቀይረው 1ኛ ተከሳሽ እንዳይከፍተው እና እንዳይቆጣጠረው ያደረጉ መሆኑን እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ከደንበኞቹ የኢሜል መልዕክት እንዳይደርሰው ጠልፎ በማስቀረት ህገወጥ ድርጊቶችን የፈጸሙ መሆኑን ከሳሽ አስከ 2009 ዓ/ም ሲያስተዳድረው ከነበረው 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ስራ የሚሰራ ቢቲኤ ቴክኖሎጂ የተባለ ድርጅት አቋቁሞ የጥቅም ግጭት የፈጠረ መሆኑን ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ ማናቸዉንም ስራ በእንደነት ለማከናወን ተስማምቷል በማለት ከሳሽ የገለጹት ሀሰት መሆኑን ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም የተደረገው የባለአክሲዮኖች ስብሰባ አላማ ስራ አስኪያጆችን ለመሰየም ብቻ ሲሆን ይህ ማለት ደግሞ ሁለቱም ስራ አስኪያጆች በየራሳቸው የስራ ድርሻ እንዲወጡ መሆኑን፣ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ በጋራ የሚያከናውኑትን ስራ በተመለከተ ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ ጉባዔ ላይ በገልጽ የሰፈረ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽን የዕለት ተዕለት ተግባር በቅንነት ከማከናውን በስተቀር የማህበሩን ገንዘብ ብቻውን ያላንቀሳቀሰ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ህግን ተላልፎ ያከናወነው ሕገወጥ ተግባር የሌለ መሆኑን ከስራ አስኪያጅነት ለመሻር የሚያበቃ ጥፋት ያልፈጸመ መሆኑን ከሳሽ ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2006 ዓ/ም ድርስ በየዓመቱ የትርፍ ክፍፍል እየወሰደ የነበረ መሆኑን ከሳሽ በተደጋጋሚ ስበሰባ ተጠርተዉ ሳይመጡ የቀሩ መሆኑን የማህበሩ የአገልግሎት ክፍያ በቼክም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ሲሰበሰብ የነበረ መሆኑን የተሰበሰበዉንም ገንዘብ 1ኛ ተከሳሽ ለማህበሩ ስራ ሲያውል የነበረ መሆኑን ከባንክ ገንዘብ ወጪ የተደረገዉ ከሳሽም ራሳቸው ፈርመው በነበሩት ሲፒዮች መሆኑን እንዲሁም ማህበሩ ኦዲት ሊደረግ የሚገባዉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እንጂ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ መሆን የሌለበት መሆኑን ፍርድ ቤቱ በሚመድበው ሰብሳቢ አማካኝነት ባለአክሲዮኖቹ ሥራአስኪያጅ አንዲመርጡ የቀረበው ጥያቄም የሕግ መሠረት የሌለዉ ስለሆነ ውድቅ ሊደረግ የሚገባዉ መሆኑን ከሳሽ ወደፊት ክስ ለማቅርብ እንዲፈቀድላቸዉ የጠየቁትም ከሥነሥርዓት ውጭ ስለሆነ ውድቅ ሊደረግ የሚገባዉ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱም ጥቅምት 5/2012 ዓ.ም ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሣሽ ባቀረቡት ክርክር ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ በማሻሻል የጋራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ እንዲሰሩ የተወሰነ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽ ስራ እንዲያቆም በማድረግ የማበሩን ስራ ለብቻዉ እየሰራ መሆኑን የማህበሩ ሂሳብም በከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ በጋራ እንዲንቃሳቀስ በቃለ ጉባኤ የተወሰነ መሆኑን ገንዘብ ወጪ ሲደረግበት የነበረዉ ሲፒዮ ላይ ያረፈዉ ፊርማ የከሳሽ አለመሆኑን ይህ ክስ በቀረበበት ጊዜ በማህበሩ ሂሳብ ላይ የሚገኘዉ ገንዘብ ብር 552,979(አምስት ሀምሳ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ) ብቻ መሆኑን ይሁን እንጂ በማህበሩ ሂሳብ ላይ ብር 3.4 ሚሊዮን መገኘት የነበረበት መሆኑን ከ2009 ዓ/ም ጅመሮ የማህበሩ ትርፍ ክፍፍል ተፈጸሞ የማያውቅ መሆኑን የከሳሽ ደመዉዝም ተከፍሎ የማያውቅ መሆኑን ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ የስራ አስኪያጅነቱን ስራ ተግባብተዉ መስራት የማይችሉ መሆኑን በዚህም ምክንያት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ከውጭ ሊሰየም የሚገባዉ መሆኑን የማህበሩ ሂሳብ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ ያልተሰራ መሆኑን የተሰራዉም በማህበሩ የሂሳብ ሰራተኛ መሆኑን ከሳሽ ስራ ካቆመ በኃላ የማህበሩ ገንዘብ በሲፒዮ ወጪ ሲደረግ የነበረ መሆኑን በዚህ ሲፒዮ ላይ ያረፈዉ ፊርማ የከሳሽ አለመሆኑን ገልጸዉ ያቀረቡትን ክስ አጠናክረዉ ክርክራቸዉን ሲያቀርቡ ተከሳሾች በበኩላቸዉ ከሳሽ ስራ ያቆሙት ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ስራ የሚሰራ ቢቲኤን የተባለ ድርጅት ስለቋቋሙ መሆኑን የ2ኛ ተከሳሽን ደንበኞችም አዲስ ወደ አቋቋሙት ማህበር ወስደዉ ስራ የሰሩ መሆኑን ከሳሽ ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸዉን ሲፒዮች ፈርመዉ የነበረ መሆኑን ሲፒዮም አገልግሎቱ ለመንግስት ክፍያ መፈጸሚያ መንግድ መሆኑን ከሳሽ ከመስከረም 2009 ዓ/ም ጀምሮ ስራ ላይ ያልነበሩ በመሆኑ ደመዉዝ ሊከፈላቸዉ የማይገባ መሆኑን ከከሳሽ ጋር አብረዉ የማህበሩን ስራ መስራት የማይችሉ መሆኑን ከማህበሩ አባላት ወጪ የሆነ ሰዉ የማህበሩን ጥቅም የሚያስከብር እስከሆነ ድረስ በስራ አሰኪያጅነት ቢሾም ተቃውሞ የሌላቸዉ መሆኑን ለማህበሩ የውጭ ኦዲተር ተሰይሞ የማያውቅ መሆኑን የማህበሩ ሂሳብ ይጠራ ከተባለ መጣራት ያለበት ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ መሆኑን የተፈጸሙት ክፍያዎች አግባብነት ያላቸዉ በመሆኑ ህግ ወጥ ሊባሉ የማይገባ መሆኑን ከሳሽ እስከ 2009 ዓ/ም ድረስ ማህበሩን ለብቻቸዉ ሲመሩ የነበረ ስለሆነ 1ኛ ተከሳሽ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ማህበሩን ለብቻቸዉ መምራታቸዉ ህገ ወጥ ሊባል የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን ማህበሩ ግልጽ የሆነ የሂሳብ መመሪያ የሌለዉ መሆኑን ገንዘብ ወጪ የተደረገዉ በሲፒዮ ላይ ያለዉ ፊርማ የከሳሽ ፊርማ መሆኑ ተረጋግጦ መሆኑን ከሳሽ በሲፒዮ ላይ ያረፈዉ ፊርማ የተጨበረበረ ነዉ በሚል ያቀረቡት ክስ የሌለ መሆኑን ይህም የሚያሳየዉ በሲፒዮ ላይ ያረፈዉ ፊርማ የከሳሽ ስለመሆኑ መሆኑን ከሳሽ ማህበሩ ጠቅላላ የሰበሰበዉ ገንዘብ በሂሳብ ላይ መታየት አለበት ያሉት አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ማህበሩ ገቢ ብቻ ሳይሆን ወጪም የሚያወጣ መሆኑንበመግለጽ የመከላከያ መልሳቸዉን አጠናክረው ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ቀጥሎ የተመለከቱትን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡
1ኛ) 1ኛ ተከሳሽ ከጋራ ስራ እሰኪያጅነት ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም ?
2ኛ) ከ1ኛ ተከሳሽ ማህበር አባላት ወጪ የሆነ ሰዉ በስራ አስኪያጅነት ሊሾም ይገባል ወይስ አይገባም ?
3ኛ) የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ አዲት ሊደረግ ይገባል ወይስ አይገባም ?
4ኛ) በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ የወጡ ወጪዎች እና የተፈጸሙ ክፍያዎች ህግ ወጥ ሊባሉ ይገባል ወይስ አይገባም ?
5ኛ) 1ኛ ተከሳሽ ማህበር የአገልግሎት ክፍያ በጥሬ ገንዘብ ሰብስቦ በቀጥታ ወጪ አድርጓል አላደረግም አድጓል የሚባል ከሆነ አግባብነት አለዉ ወይስ የለዉም
1ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ኃ/የተ/ግ/ማህበር በአንድ ወይም ብዙ ሥራ አስኪያጆች ሊተዳደር አንደሚችል እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ ከማህበሩ አባላት ወይም ከማኅበረተኞች ውጭ ሊምረጥ እንደሚችሉ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 525 እና 526 ይደነግጋል፡፡በዚሁ ድንጋጌ አግባብ 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሰየሙ መሆኑን ማህበሩ ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም የያዘዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ይህ ቃለ ጉባኤም የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አካል እንደሆነ በቃለ ጉባኤዉ ላይ ተመልክቷል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ የጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሾሙ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በማህበሩ የመመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ሥራ አስኪያጅ ከሥራ አስኪያጅ ስልጣኑ ሊሻር የሚችለዉ በንግድ ህጉ 527(1) እና 536(2) መሰረት ከማህበሩ ባለአክሲዮኖች መካከል በሶስተኛ አራተኛ ድምጽ ባላቸዉ ባለአክሲዮኖች ስር አስኪያጁ እንዲሻር ድጋፍ ሲያገኝ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌም ተፈጻሚነት ያለዉ የማህበሩን ሥራ አስኪያጅ በጠቅላላ ጉባኤ ለመሻር በቀረበ ጊዜ ሲሆን በሌላ በኩል እንድ ስራ አስኪያጅ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ቢሆንም ስራ አስኪያጁ ከስልጣኑ እንዲነሳ ሊያደረጉ የሚችሉ ጥፋቶች እስካሉ የማህበሩ አባላት ስራ አስኪያጁ በፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲሻር መጠየቅ እንደሚቻሉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት የማህበር አባል የሚገባ ምክንያት(good cause) እስካለ ድረስ ስራ አስኪያጁ እንዲሻር ክስ ሊያቅርብ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ተጠቃሹ ደንጋጌ የሚገባ ምክንያት (good cause) ምን ምን እንደሆነ በዝርዝር የሚያስቀምጠዉ ነገር የለም በንግዱ ህጉ አንቀጽ 528(1) የሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ የማህበሩን ዓላማ ወሰን ሳያልፍ በማናቸዉም ሁኔታዎች ሁሉ በማህበሩ ስም ለመስራት ስልጣን ያለዉ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን የአንድ ማህበር ዓለማ እና ግብ የሚታወቀዉ ከማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ነዉ፡፡ በመሆኑም ስራ አስኪያጅ የማህበሩን ዓላማ ለማሳካት የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ፤መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም ህግን መሰረት አድርጎ የመስራት ግዴታ እና ሃላፊነት አለበት፡፡ከእነዚህ ማዕቆፎች ወጭ በስራ አስኪያጅ የተፈጸመ ተግባርም የማህበሩን ዓላማ ለማሳካት ተድርጎ የማይወሰድ ጥፋት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ከጣምራ ስራ አስኪያጅነቱ ሊሻር ይገባል በማለት በዋንኝነት የሚከራክሩት የማህበሩን ሂሳብ ለብቻዉ አንቀሳቅሷል የትርፍ ክፍፍል እንዳይፈጸም አድርጓል፤በማህበሩ ሂሳብ ላይ መገኘነት የነበረበት የገንዘብ መጠን እንዳይገኝ አድርጓል የማህበሩ ዌበሳይት ዩዘር ኔምን ቀይሯል እንዲሁም የማህበሩን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸዉ አውለዋል በማለት ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽ ከጋራ ስራ አስኪያጅነት ስራዉ ሳይሻር ከሳሽ ወደ ቢሮቸዉ እንዳይገቡ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበርን ቁልፍ እና የማህበሩን ዌብሳይት ፓስዋርድ መቀየራቸዉ የተመሰከረ መሆኑ ሲታይ ከሳሽ የማበሩን ሰነዶች መመለከት በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 የተጠበቀለት መብት ሆኖ እያለ 1ኛ ተከሳሽ ይህን በመተላላፍ ክልከላ ማድረጋቸዉ፤የማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ በሚደነግገዉ መሰረት በየአመቱ እንደ ስራ አስኪያጅነታቸዉ እና በተግባር ማህበሩን ከ2009 ዓ/ም እንደመምራቸዉ የትርፍ ክፍፍል እንዲደርግ ያለማድረጋቸዉ፤ሰብሰባ እንዲጣራ ከሳሽ ጠይቀዉ 1ኛ ተከሳሽ ምላሽ አለመስጠታቸዉ መመስከሩ ሲታይ እንዲሁም የማህበሩ የሂሳብ ሪፖርት በ2009 እና በ2010 ዓ/ም ካሽ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ያለዉ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ነገር ግን በተግባር በማህበሩ የባንክ ሂሳብ ዉስጥ የሚገኘዉ አራት መቶ አርባ ሺህ ብቻ መሆኑ የተመሰከረ ከመሆኑ አንጻር 1ኛ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 528 መሰረት እንዲሁም በማህበሩ መመስረቻ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለማህበሩ ጥቅም እየሰራ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ሲጠቃለልም በከሳሽ በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች 1ኛ ተከሳሽ ከስራ አስኪያጅነት ስልጣን ሊያሰነሳቸዉ የሚችል በቂ ምክንያት መኖሩን፤የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ፤መመሰረቻ ጽሁፍ እና የንግድ ህጉን በመተላላፍ ጥፋት የፈጸሙ መሆኑን በአግባቡ ያስረዱ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች 1ኛ ተከሳሽ የፈጸሙትን ጥፋቶች የሚያስተባብሉ አይደሉም፡፡ ስለሆነም 1ኛ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የጋራ ስራ አስኪያጅነት እንዲሻር ተወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ የማህበር ሥራ አስኪያጆች እንደ ማህበሩ ወኪል የሚቆጠሩ መሆኑን የንግድ ህጉ አንቀጽ 33 የሚደነግግ በመሆኑ፤የንግድ ህጉ ከአንድ በላይ የሆኑ ሥራ አስኪያጆች ማህበሩን የሚመሩ እና የተሰጣቸዉም ስልጣን በጋራ አንድ አይነት ጉዳይ ለመከናወን እንዲችሉ ከሆነ የአንዱ ሥራ አስኪያጅ ከሥራ አሰኪያጅነት መሻር ያላዉን ዉጤት የማያሰቀምጥ ስለሆነ በንግድ ህጉ አንቀጽ 1 በተደነገገዉ መሰረት የፍ/ህ/ቁ 2231ን መጠቀም አሰፈላጊ ነዉ፡፡ከዚህ አንጻር ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩን የባንክ ሂሳብ በጋራ ለመከፈት፤ለማንቀሳቀስ፤ለመዘጋት የማህበሩን ንብረት በዋስትና ለማሲያዝ ከባንክም ሆነ ከድርጅት ገንዘብ በብድር ለመውሰድ በጣምራ እንዲሰሩ የተሰየሙ መሆኑን ማህበሩ ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ/ም እና ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም ከያዘዉ ቃለ ጉባኤ መረዳት የሚቻል ሲሆን በፍ/ሕ/ቁ 2231(1) ድግሞ ከአንድ በላይ የሆኑ ተወካዮች ተመሳሳይ ጉዳይ በጋራ እንዲያከናውኑ ስልጣን ተሰጥቷቸዉ እያለ አንደኛዉ የተሰጠዉን ስልጣን መከናወን እንዳይችል ከተደረገ ለሌላኛዉም ወኪል የተሰጠዉ ስልጣን ቀሪ እንዲሆን የተመለከተ ስለሆነ 1ኛ ተከሳሽ ከጣምራ ሥራ አስኪያጅነቱ በመሻሩ ከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በጣምራ የተሰጠዉን ስልጣን ለብቻዉ ለማከናወን አያስችለዉም፡፡
2ኛ ነጥብ በተመለከተ ምንም እንኳን ተከሳሾች ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር አባላት ወጭ ገለልተኛ ስራ አሰኪያጅ የሚሾመበት የህግ መሰረት የለም በማለት መልሳቸዉን ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ክስ በሰማ ዕለት ለማህበሩ ጥቅም የሚሰራ እስከሆነ ድረስ ከማህበሩ አባላት ውጭ የሆነ ስራ አስኪያጅ ቢሾም የማይቀወሙ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ከማህበሩ አባላት ወጭ የሆኑ ሰዎች በስራ አስኪያጅነት ሊመሩት እንደሚችሉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 525(1) የተመለከተ በመሆኑ እንዲሁም የማህበሩ አባልት በንግድ ህጉ አንቀጽ 526 የተጠበቀላቸዉን መብት በአከበረ መልኩ የማህበሩ አባላት ስበሰባ ፍርድ ቤቱ በሚመድበዉ ባለሙያ ጥሪ ተድርጎ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህብር ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ ሊሾም ይገባል ተብሎ ተወሰኗል፡፡
3ኛዉን ነጥብ በተመለከተ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በገለልተኛ ኦዲተር ኦዲት ተድርጎ የማያውቅ መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም ተከሳሾችም የማህበሩ ሂሳብ በገለልተኛ ኦዲተር ሊመረመር አይገባም በሚል ያቀረቡት ክርክር የለም ተከሳሾች ያቀረቡት ክርክር ቢኖር የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ መመርመር ያለበት ማህበሩ ከተመሰረተበት ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ ሊሆን ይገባል በማለት ነዉ ይሁን እንጂ ከሳሽ የማህበሩ ሂሳብ እንዲመረመር ዳኝነት የጠየቁት የጋራ ስራ አስኪያጅነት ስራቸዉን ካቆሙበት ከመስከረም 2009 ዓ/ም ጀምሮ በመሆኑ እንዲሁም ተከሳሾች የማህበሩ ሂሳብ ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ እንዲመረመርላቸዉ ያቀረቡት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የሌለ በመሆኑ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ ከመስከረም 2009 ዓ/ም ጀምሮ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ ኦዲት እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
4ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ወጪ የተደረገ ገንዘብ እና የተፈጸሙ ክፍያዎች ህገ ወጥ ሊባሉ ይገባል በማለት ከሳሽ ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በበኩላቸዉ የተፈጸሙት ክፍያዎችም ሆነ ወጪ የተደረገዉ ገንዘብ ለመንግስት ከፍያ የዋለ መሆኑን ገንዘቡም ወጪ ተድርጎ ክፍያ የተፈጸመዉ ከሳሽ በፈረመዉ ሲፒዮ መሆኑን በመግለጽ ክርክር አቅርቧል፡፡
በተከሳሾች በኩል የቀረቡት ምስክሮች ከማህበሩ ሂሳብ ላይ ወጪ ተድርጎ ክፍያ ሲፈጸም የነበረዉ በከሳሽ ተፈርመዉ የተቀመጡ ሲፒዮችን በመጠቀም መሆኑን ከሳሽ በሌለ ጊዜ ሲፒዮ ፈርሞ ትቶ የሚሄድ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ በሌለ ጊዜ ሲፒዮ ፈርሞ ትቶ የሚሄድ መሆኑን ከሳሽ የስራ አስኪያጅነት ስራቸዉን ካቆሙ በኃላ የማህበሩ ቢሮ መጥተዉ ሲፒዮ እና ቼኮች የፈረሙ መሆኑን በነዚህ ቼኮች እና ሲፒዮች ገንዘብ ወጪ ተደርጎ የደመዉዝ፤የቫት፤የተርፍ ገብር፤የጡርታ፤ዊዝሆልዲንግ እንዲሁም የኪራይ ክፍያ የተፈጸመ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን በከሳሽ በኩል የቀረቡት 1ኛ ምስክር ሲፒዮችንም ሆነ ቼኮቹን ከሳሽ ያልፈረመ መሆኑን የነገራቸዉ መሆኑን ገልጸዉ መመስከራቸዉ ሲታይ ምስክሯ ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸዉን ሲፒዮች ከሳሽ ይፈረሙ አይፈርሙ የማያውቁ መሆኑን የሚያስረዳ ከመሆኑም በላይ ገንዘቡ ለምን ጥቅም እንደዋለ አላውቅም ማለታቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ገንዘቡን ለግል ጥቅሙ ያዋለ መሆኑን አያስረዳም፡፡ከዚህም በላይ ከሳሽ በሲፒዮዎቹ ላይ ያረፉት ፊርማዎች የእኔ አይደለም ከሚሉ በቀር አግባብነት ባለዉ አካል ፊርማዉ እንዲመረመርላቸዉ አልጠየቁም፡፡ ይህ ሁሉ ሲታይ 1ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ/ም እና ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም በተያዘዉ ቃለ ጉባኤ መሰረት በጋራ የ2ኛ ተከሳሽን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ የተጣለባቸዉን ግዴታ ጥሷል ሊያስብል አይችልም ይልቁንም ወጪዎች እና ክፍያዎች የተፈጸሙት ከሳሽ በፈረሙት ሲፒዮች እና ቼኮች መሆኑ ሲታይ 1ኛ ተከሳሽ በዚህ ረግድ ጥፋት ያልፈጸሙ መሆኑን መረዳት የሚቻል ከመሆኑም በላይ ከሳሽ በደፈናዉ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ የተደረጉ ወጪዎች እና ክፍያዎች ህገ ወጥ ይባልልኝ ከሚሉ በቀር ሀገ ወጥ ሊባሉ የሚችሉት ክፍያዎች ምን ምን እንደሆኑ እንዲሁም ህገ ወጥ የሚባልበትን ህገዊ ምክንያት ያላስረዱ ስለሆነ ከሳሽ በዚህ ረገድ የጠየቁትን ዳኝነት ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል፡፡
5ኛዉን ነጥብ በተመከተ ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር የማህበሩ የአገልግሎት ክፍያ በቼክ እየተሰበሰባ በቀጥታ ወደ ማህበሩ ሂሳብ ገቢ ከተደረገ በኃላ ነዉ ከማህበሩ ሂሳብ ላይ ገንዘብ ወጪ የሚደረገዉ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩን የአገልግሎት ክፍያ ቀጥታ በካሽ እየሰበሰቡ ወጪ አድርጓል ይህም አግባብነት የለዉም ሊባል ይገባል በማለት ክርክር ያቀረቡ ቢሆንም ከሳሽ ይህን ፍሬ ነገር በማስረጃ ያላረጋገጡ ሲሆን ተከሳሾች በበኩላቸዉ ከ2006 ዓ/ም በፊትም ሆነ በኃላ ማህበሩ የሰበሰበዉ የአግልግሎት ክፍያ ቀጥታ ወደ ባንክ ሳይገባ ለተለያዩ ወጪዎች ይውል የነበረ መሆኑን የሂሳብ አወጣጥን በተመለከተ ማህበሩ መመሪያ የሌለዉ መሆኑን እንዲሁም ወጪዎች ስራ አስኪጆቹ በፈለጊት መንግድ ወጪ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ይህም የማህበሩ የተለመደ አሰራር መሆኑን የቀረቡት ምስክሮች አስርድቷል፡፡ ማህበሩ የሂሳብ አያያዘን በተመለከተ መመሪያ የሌለዉ በሆነበት ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩን የአገልግሎት ክፍያ በካሽ ሰብስቦ ቀጥታ ወጪ ማድረጉ ተገቢ አይደለም የሚባልበት ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ ፍርድ ቤቱ በዚህ ረገድም ከሳሽ ያቀረቡትን ክርክር ውድቅ አድርጎታል፡፡
ዉሳኔ
1ኛ) ተከሳሽ ከ2ኛ ከሳሽ ማህበር የጣምራ ሥራ አስኪያጅነት ሊሻር ይገባል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ከማህበሩ አባላት ወጪ የሆነ ገለልተኛ ባለሙያ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በስራ አስኪያጅነት እንዲሾም ታዟል፡፡
2ኛ) የምድቡ ሬጄስተራር ጽ/ቤት ከዳኛ ረዳቶች መካከል የንግድ ህግ ገንዘቤ ያለዉን የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር አባላትን ሰብሰባ ጠርቶ ስራ አስኪያጅ የሚያስመርጥ የዳኛ ረዳት እንዲመድብ ታዟል፡፡
3ኛ) የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ በገለልተኛ ኦዲተር ኦደት እንዲደረግ ስለተወሰነ የምድቡ ሬጅስተራር ጽ/ቤት ገለልተኛ ኦዲትር አንዲመብ ታዟል፡፡
3ኛ) ከሳሽ ያልተከፈላቸዉን ደመዉዝ፤የትርፍ ክፍፍል እንዲሁም በ1ኛ ተከሳሽ ጥፋት የደረሰባቸዉ ጉዳት ካለ ወደፊት ክስ አቅርበዉ የመጠየቅ መብታቸዉ ተጠብቋል፡፡
4ኛ) ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ ገልባጭ ይሰጥ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡