የኮ/መ/ቁ፡- 179280

ቀን፡- 30/04/2012

ዳኛ፡ አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሾች፡- 1ኛ) ዶ/ር ጌተሁን ይትባረክ ከጠበቃ ኢሳያስ ከልሌ፡- ቀረቡ

        2ኛ) ሲሣይ አበበ

ተከሳሾች፡- 1ኛ) ዶ/ር አከዛ ጠዓመ፡- ጠበቃ ግርማ ሀይሌ፡- ቀረቡ

          2ኛ) ቅዱስ ያሬድ ኃ/የተ/የግል/ማህበር ፡- አልቀረቡም

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነው ከሳሾች ጥቅምት12/2011ዓ.ም ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሾች የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ባለአክሲዩኖች መሆናቸዉን 1ኛተከሳሽ ከከሳሾች እውቅና ውጪ፤ያለ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ለብቻው ቃለጉባኤ በመያዝ ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ እና ከሕግ ውጪ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር  ሥራ አስኪያጂ የሾመ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚሰራ ተቋም ከባለቤታቸው ጋር ከፍተው የ2ኛ ተከሳሽን ደንበኞችና አሰራሮች ወደራሳቸው ተቋም አየወሰዱ መሆኑን፤በ2ኛ ተከሳሽ ሥም ከአምቦ እና ኢኳተርያል የህክምና ዕቃ አቅርቢዎች ወስደዉ እራሳቸዉ በመሰረቱት የህክምና ተቋም ዉስጥ የህክምና መሳሪያዎች እየተገለገሉበት የሚገኙ መሆኑን፤የ2ኛ ተከሳሽ አካል የሆነው ሴንቸሪ ፓርማሲ እንዲዘጋ በማድረግ ከዱሹስ በሚል ስም ፓርማሲ የከፈቱ መሆኑን፤የ2ኛ ተከሳሽ ማህበርን መኪና ለግል ጥቅማቸው የሚገለገሉበት መሆኑን፤ስራ ለማህበሩ ሳይሰሩ በወር ብር 159,230.09( አንድ መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ሺ ሁለት መቶ ሰላሳ 09/100) የሚከፈላቸዉ መሆኑን በተመሳሳይ ባለቤታቸዉ ወ/ሮ ሜላት አባተ ሌላ ቦታ ሥራ እያላቸዉ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሥራ አስኪያጅ በሚል ስም ወራዊ ደሞዝ ብር 27,615.38(ሃያ ሰባት ሺ ስድስት መቶ አስራ አምስት 38/100 )እንዲሁም ብር 5000.00( አምስት ሺ) የነዳጅ አበል እንዲከፈላቸዉ ያደረጉ መሆኑ፤የ1ኛ ተከሳሽ ወንድም የ2ኛ ተካሳሽ ሒሳብ ክፍል ኃላፊ በመሆን በወር ብር 14,690.00(አስራ አራት ሺ ስድስት መቶ ዘጠና) የሚከፈላቸዉ መሆኑን የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር  የውጭ ኦዲተር በመሆን በዓመት 162,800.00( አንድ መቶ ስልሳ ሁለትሺ ሰምንት መቶ ብር) እንዲከፈላቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ያደረጉ መሆኑን ማህበሩ አለአግባብር 12,000,000.00( አስራ ሁለት ሚሊዮን) ግብር እንዲከፍል ያደረጉ መሆኑን በቂ እዉቀት ሳይኖረዉ የአጎታቸዉን ልጅ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በማድረግ በወር ብር 66,258.62( ስልሳ ስድስት ሺ ሁለት መቶ ሀምሳ ስምንት 62/100) የተጋነነ ክፍያ እንዲከፈል ያደረጉ መሆኑን ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ብር 2,727,030.00( ሁለት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃያሰባት ሺ ሰላሳ) አለ አግባብ ወጪ ያደረጉ መሆኑን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የህንድ ሆስፒታል እና የኢንተርናሽል ላብራቶሪ ዕዳ ሳይኖርበት  ዕዳ አለበት በማለት በድምሩ ብር 4,875,200.00( አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሰባ አምስት ሺ ሁለት መቶ) ወጪ አድርገዉ የወሰዱ መሆኑን እንዲሁም ማህበሩ ትርፍ ቢያተርፍም የትርፍ ክፍፍል ተድርጎ የማያወቅ መሆኑን ገልጸዉ 1ኛ ተከሳሽ 01/13/2010ዓ.ም በውልና ማስረጃ ያፀደቁትን ቃለጉባኤ የከሣሾችን መብት እና ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ቃለ ጉባኤዉ እንዲሻር እንዲወሰንላቸዉ፤1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ሥራ በግል በመክፍት እየሰሩ ስለሆነ እና ማህበሩ ላይ ጉዳት እያደረሱ ስለሆነ ድርሻቸው ተከፍሏቸው ከማህበሩ እንዲወጡ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጩና ኪሳራ እንዲተከላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሉዋቸውን የሠነድ ማስረጃ አያይዘው አቅርበዋል እንዲሁም የሰው ምስክር  ቆጥረዋል፡፡

ከሳሾች ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎች ለተከሳሾች ደርሶቸው መልስ የሰጡ ሲሆን ተከሳሾች በሰጡት የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር በቀረበዉ መቃወሚያ ላይ ካደመጠ በኃላ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት በተከሳሾች የቀረበዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ወድቅ ያደረገዉ በመሆኑ ከዚህ ማስፈር ሳይፈልግ ታልፏል፡፡ ተከሳሾች በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ 1ኛ ተከሳሽ እና 1ኛ ከሳሽ የህክምና ባለሙያዎች በመሆናቸዉ በጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔ መሰረት 2ኛ ተከሳሽ በየወሩ ደሞዝ ይከፈላቸው የነበር መሆኑን ነገር ግን ከሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የደሞዝ ክፍያዉ እንዲቀር የተደረገ መሆኑን በተመሳሳይ ለ2ኛ ከሳሽም በኃላፊነታቸው ልክ በጉባኤው ውሳኔ መሠረት ደመዉዝ ሲከፈላቸዉ የነበረ መሆኑን ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ለመቅጠር ከሳሾች ተስማምተው መረጣ ከተካሄደ በኃላ በባለአክሲዩኖች ስብሰባ ላይ ከሣሾች እንዲገኙ ጥሪ ቢደረግም ከሳሾች ሊገኙ ያልቻሉ መሆኑን በዚህም ምክንያት የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የስራ አስኪያጅ ቅጥር ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ያልተቻለ መሆኑን ለከሳሾች በተለመደው የማህበሩ የስብሰባ አጠራር በ14/10/2010 በስብሰባ እንዲገኙ በ1ኛ ተከሳሽ በደብዳቤ እና ኤሚል ጥሪ ቢደረግላቸውም ባለመገኘታቸው እና ለመገኘት እንደማይፈልጉ ለ2ተኛ ተከሳሽ በመሳወቃቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የህግ አማካሪ ጋር በመሆን በማህበሩ መተዳደሪ ደንብ መሠረት 2ኛ ተከሳሽ ያለ ሥራ አስኪያጅ መቆየት ስለማይገባው የተሻለ የተባለው ሰው በሥራ አስኪጂነት እንዲቀጠር የወሰኑ መሆኑን ዉሳኔዉ የተላለፈበት ቃለጉባኤም የተመዘገበ መሆኑን የ1ኛ ተከሳሽ ወንድም የ2ኛ ተከሳሽ ማህበርን ኦዲት ያልሰራ መሆኑን ነገር ግን ለማህበሩ ለሰጠዉ አግልግሎት ህጋዊ ክፍያ የተከፈለዉ መሆኑን 2ኛ ተከሳሽ በውጪ ኦዲተሮች በየጊዜው ኦዲት የሚደረግ መሆኑን የኦዲት ሪፖርትም ለባለአክሲዮች በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ የጸደቀ መሆኑን የማህበሩ የ2018 ኦዲት ሪፖርት እንዲሰራ ትዕዛዝ የተላለፈ መሆኑን 2ኛ ተከሰሽ 12,000,000.00( አስራ ሁለት ሚሊዮን) የግብር ዕዳ እንዲከፍል ተደርጓል የተባለው በማስረጃ ሀሰት መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ተፎካካሪ ድርጅት አቋቋመዋል የተባለው 2ተኛ ተካሳሾችን ለመፎካከር ተብሎ የተቋቋመ ድርጅት ስለመኖሩ የማያውቁ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ አቋቋሟል የተባለው ድርጅት  2ኛ ተከሳሽ ካለበት ክ/ከተማ ውጪ የሚገኝ መሆኑን 1ኛ ተካሳሽ ከህግ አግባብ ውጪ ገንዘብ ወስዷል የተባለው ሐሰት መሆኑን የ1ኛ ተከሳሽ አጎት የ2ኛ ሥራአስኪያጅ ሆነው ሰራተዋል የተባለዉ ሀሰት መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ትዕግስት ደጀኔ የምትባል ዘመድ የሌላቸዉ መሆኑን ከአምቦ እና ኢኳተርያል የህክምና ዕቃ አቅርቢዎች የህክምና ዕቃ ግዢ በግል ባቋቋመዉ ድርጅት እየተገለገለበት ይገኛል የተባለዉን በተመለከተ ከእነዚህ ተቋማት የተገዛ የህክምና መገልገያ የሌለ መሆኑን የአሁኑ ሥራ አስኪያጅ የደመዉዝ ክፍያ ቀድሞ ከነበሩት የሥራ አስኪያጂዎች ክፍያ በእጅጉ የሚያንስ መሆኑን አፖሎ ሆስፒታል ከ2ኛ ተከሳሽ ብር 551,000.00( አምስት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ)የሚፈልግ መሆኑን ይህ ዕዳ ሳይከፍል የቀረዉ በውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን 2ኛ ተከሳሽ የኢንተርናሽል ላብራቶሪ እንዲሁም የሌሎች መድሐኒት አቅራቢዎች ዕዳ ያለበት መሆኑን የትርፍ ድርሻን በተመለከተ የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ የተደረገበት መሆኑን ገልጸዉ የመካለከያ መልሳቸዉን አቅርበዋል፡፡

ተከሳሾች ክሱን ይከላከሉልኛል ያሏዋቸውን የሠነድ ማስረጃ አቅርቧል የሰው ምስክርም  ቆጥረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ/ም  በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት  ከሳሾች ባቀረቡት ክርክር 1ኛ ተከሳሽ ለከሳሾች የሰብሰባ ጥሪ ሳያደርጉ ለብቻቸዉ  ቃለ ጉባኤ በመያዝ  የማህበሩን ስራ አስኪያጅ የሾሙ መሆኑን  ስራ አስኪያጅ የመሾም ስልጣን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን በ1ኛ ተከሳሽ ብቻ ተይዞ የጸደቀዉ ቃለ ጉባኤ መብትና ጥቅማቸዉን የሚናካ በመሆኑ ሊሻር የሚገባዉ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ሆነዉ ሳለ የራሳቸዉን ጥቅም በማስቀደም ከማህበሩ ጋር ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ሶስት የህክምና ተቋም ከፍተዉ የሚሰሩ መሆኑን የ2ኛ ተከሳሽ ማህበርን ደንበኞች በመወስድ በእራሳቸዉ ተቋም አገለግሎት እየሰጡ የሚገኙ መሆኑን  የማህበሩ የዉስጥም ሆነ ውጭ ኦዲትር የ1ኛ ተከሳሽ ወንድም መሆናቸዉን የማህበሩን ተሽከርካሪ ለግል ጥቅማቸዉ የሚገለገሉበት መሆኑን  ከማህበሩም 4 ሚሊዮን ብር በብድር የወሰዱ መሆኑን የማህበሩ ፈርማሲ እንዲዘጋ አድርገዉ እራሳቸዉ ፋርማሲ ከፍተዉ ይህ ፋርማሲ ለ2ኛ ተከሳሽ መድሃኒት እንዲያቀርብ በማድረግ የ የማህበሩን ገንዘብ አለ አገባብ ወደ ራሳቸዉ እየወሰዱ የሚገኙ መሆኑን፤አፖሎ እና አንተርናሽናል ሆስፒታል ከ2ኛ ተከሳሽ የሚፈለጉት ክፍያ ተከፍሏቸዉ እያለ 1ኛ ተከሳሽ ዕዳዉ እንዳልተከፈለ እንዲመዘገቡ ያደረጉ መሆኑን የማህበሩንም ሰራተኞች እየወሰዱ በግል ባቋቋሙት የህክምና ተቋም እያሰሩ የሚገኙ መሆኑን  በመገልጽ ያቀረቡትን ክርክር አጠናክረዉ የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሾች በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር 1ኛ ተከሳሽ በከሳሾች ላይ ያደረሰዉ ጉዳት የሌለ መሆኑን በ1ኛ ተከሳሽ ተፈጽሟል ተብለዉ የተገለጹት በማስረጃ ያልተደገፉ መሆኑን የ1ኛ ተከሳሽ  ወንድም የማህበሩን ሂሳብ ሰርቶ ለውጭ ኦዲትር ከሚያቀርብ በቀር የማህበሩ የውጭ ኦዲተር አለመሆኑን ቀደም ሲል ሁሉም የማህበሩ አባላት ደመዉዝ ሲከፈላቸዉ የነበረ መሆኑን አሁን ግን እንዲቀር የተወሰነ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ በግላቸዉ የከፈቱት የህክምና ተቋማት በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር አለመሆኑን በዚህ ረገድም የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን ከሳሾች ስበሰባ ሲጠሩ የማይገኙ መሆኑን የማህበሩ ዕዳ ተከፍሎ እያለ እንዳልተከፈለ ተመዝገቧል የተባለዉ ሀሰት መሆኑን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን አባል የንግድ ህጉን አንቀጽ 261ን መሰረት በማድረግ ማሰናበት የማይቻል መሆኑን በማህበሩ የመተዳደሪያ ደንብና መመሰረቻ ጽሁፍ የማህበሩ አባል እንዲሰናበት የተደነገገ ድንጋጌ የሌለ መሆኑን 1ኛ ተከሳሽ ለማህበሩ ስራ አሰኪያጅ የሾሙት በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሆኑን ስራ አሰኪያጅ ለመሾም በማህበሩ የጋራ ስራ አሰኪያጅ እና በ1ኛ ተከሳሽ የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ የተደረገ መሆኑን ለከሳሾች በደብዳቤ እና በኢሜል ጥሪ ተደርጎላቸዉ ያልቀረቡ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሳቸቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡

በመዝገቡ ላይ የቀረበዉ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም 01/13/2010ዓ.ም በውልናማስረጃ የጸደቀዉ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር አባልነት ሊሰናበቱ ይገባል ወይስ አይገባም የሚሉትን ነጥቦች በጭብጥነት በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንደመሆኑ መጠን ተፈጻሚነት ያላቸዉ የንግድ ህጉ ደንጋጌዎች ከአንቀጽ 510-543 ድርስ ያሉት መሆናቸዉ ገልጽ ነዉ፡፡ በንግድ ህጉ አንቀጽ 525(1) ስር አንደተመለከተዉ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአንድ ወይንም ከአንድ በላይ በሆኑ ስራ አስኪያጆች ሊተዳደር እና ሊመራ እንደሚችል የተመለከተ ሲሆን ነገር ግን የማህበሩ አባላት ከ20 በላይ በሆኑ ጊዜ ዉሳኔዎች በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሊወሰኑ አንደሚገባ በንግድ ህጉ አንቀጽ 525(2) ስር ተመልክቷል፡፡የማህበሩ አባላት ከ20 በሚበልጡ ጊዜ በማህበሩ የመተዳዳሪያ ደንብ በተወሰነዉ ቀን በየዓመቱ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ ያለበት መሆኑን የንግድ ህጉ አንቀጽ 532(1) የሚደንገግ ሲሆን ከጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች ወጭ ሌሎች ስብሰባዎች በማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በሌለበት ጊዜ በማህበሩ ኦዲተር፤ኦዲትር በሌለ ጊዜ በማህበሩ ላይ ከግማሽ በላይ ድርሻ ያለዉ አባል ጥሪ ሊደረግ እንደሚችል በንግድ ህጉ አንቀጽ 532(2) ተድንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ማህበሩ በህግም በማህበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ስብሰባ እንዲያካሂድ የማይገደድ ከሆነ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሊወሰኑ የታሰቡትን ዉሳኔዎች ለአባላቱ በመላክ የማህበሩ አባላት ድምጽ እንዲሰጡበት ሊደረግ የሚገባ ስለመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 533 ስር ተደንግጓል፡፡ የማህበሩ አባላት በስብሰባ ላይ የመገኝት እና በማህበሩ ላይ ባላቸዉ ድርሻ ልክም ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸዉ መሆኑም የንግድ ህጉ አንቀጽ 537 ስር ተደንግጓል፡፡

በንግድ ህጉ ስለ ሃላፊነቱ የግል ማህበር በሚደነገግገዉ ክፍል በንግድ ህጉ አንቀጽ 535 መሰረት ማለትም ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ የሚገደድ ከሆነ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ የሚወሰናቸዉ ዉሳኔዎች እንዲሁም የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሊተላላፍ የታሰባዉን ዉሳኔ ለማህበሩ አባላት በመላክ የሚወሰኑ ዉሳኔዎች ዉጤታቸዉ ምን እንደሆነ የተመለከተ ባይሆን የንግድ ህጉ ስለ አክሲዮን ማህበር በተደነገገዉ ክፍል ዉስጥ የተመለከተዉን አንቀጽ 388 በማመሳሰል መጠቅም አሰፋላጊ ሲሆን በዚህ ደንጋጌ መሰረት በህግ አግባብ  የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ተድርጎ የተላላፉ ዉሳኔዎች ሁሉንም የማህበሩ አባላት ሊያስገደዱ እንደሚችሉ የተመለከተ ሲሆን ባለአክስዮኖች የማህበሩ ባለአክሲዮን በመሆናቸዉ የተገናጸፉትን መብቶች ማለትም በጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚተላላፉ ዉሳኔዎች ላይ ድምጽ የመስጠት መብታቸዉን ሊነፈጉ የማይገባ ስለመሆኑ የንግድ ህጉ አንቀጽ 534/389 ያስገነዝባል፡፡

ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት አስፈላጊ ሲሆን ጥሪ  የሚደረገዉ ለአባላቱ የተመዘገበ ደብዳቤ በመላክ መሆኑን ከንግድ ህጉ አንቀጽ 535(2) መረዳት የሚቻል ሲሆን ነገር ግን ለማህበሩ አባላት ጥሪ የሚላክላቸዉ ጉባኤዉ ወይንም ዉሳኔ ከሚወሰንበት ስንት ቀናት ቀደም ብሎ እንደሆነ የተመለከተ ነገር የለም እንዲሁም የጥሪ ደብዳበው ምን ምን ማካተት እንዳለበት የተመለከተ ነገር የለም፡፡በመሆኑም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከአክሲዮን ማህር በጋራ የሚጋራዉ ባህሪ ያለዉ በመሆኑ እና ከዓላማቸዉ አንጻር  በአክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት የተቀመጡትን ቅደመ ሁኔታዎች መጠቀም አሰፈላጊ ነዉ፡፡ በዚህም መሰረት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባላት በንግድ ህጉ አንቀጽ 535(1) በተመለከተዉ መሰረት ዉሳኔ ለመስተላላፍ የሰብሰባ የጥሪ ማስታወቂያ ከ15 ቀናት በፊት ቀድሞ ብሎ ሊደረሳቸዉ የሚገባ መሆኑ እንዲሁም በሰብሰባ ላይ ወይይት የሚደረግባቸዉ አጀንዳዎች በጥሪ ማስታወቂያ ላይ መገለጽ ያለባቸዉ ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 395፤396 እና 397 መረዳት የሚቻል ሲሆን አንድ ስበሰባዉ አይነት ምለዓት ጉባኤ  ካልተሟለ እና አሰፈላጊዉ ደምጽ ካላተገኘ በአጀንዳ ላይ የተገለጹትን የዉሳኔ ሀሳቦች ለማጽደቅ የማይቻል ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ 399(1) መረዳት ይቻላል፡፡

ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ በህግ ወይም በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ ግዴት የተጣለበትም ሆነ ጠቅላላ ጉባኤ የማድርግ በህግም ሆነ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ግዴታ ያልተጣለበት ማህበር ዉሳኔዎች ማስተላላፍ ያለበት ከማህበሩ ካፒታል ላይ ከግማሽ በላይ ድርሻ ባላቸዉ አባላት ድጋፍ ሲያገኝ መሆኑ በመርህ ደራጃ በንግድ ህጉ አንቀጽ 535 የተደነገገ ሲሆን በልዩ ሁኔታ ደግሞ የማህበሩን ዜግነት ለመቀየር የማህበሩን አባላት ሙሉ ደምጽ የሚልግ መሆኑን እንዲሁም ሌሎች ማሻሻዎችን በማህበሩ መተዳዳሪያ ደንብ ለማድረግ በማህበሩ ላይ የሶስተኛ አራተኛ ድርሻ ባላቸዉ አባላት ዳግፍ ሊያገኝ የሚገባ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 536 ስር ተመልክቷል፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ሰንመለስ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቃለ ጉባኤ የጸደቀዉ በቀን 1/13/2010 ዓ/ም ሲሆን ተከሳሾች ለከሻሾች የሰብሰባ ጥሪ ተደርጎ ከሳሾች ባለመገኘታቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከማህበሩ ካፒታል ላይ ከግማሽ በላይ ድርሻ ያላቸዉ በመሆኑ በቃለ ጉባኤዉ ስራ አስኪያጅ በመሾም ዉሳኔ አስተላልፏል ዉሳኔዉም በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍም ሆነ በንግድ ህጉ የተደገፈ ነዉ፡፡ በመሆኑም ቃለ ጉባኤ ሊሻር አይገባም  በማለት ተከሳሾች ተክርክረዋል፡፡

ቃለ ጉባኤዉ ሊሻር ይገባል አይገባም የሚለዉን ነጥብ ለመመለሰ ቃለ ጉባኤዉን ለማጸደቅ የተጠራዉ ጠቅላላ ጉባኤ አጣራሩን እና አካሄዱን መመርመር አሰፈላጊ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር አባላት ሶስት በመሆናቸዉ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድርግ ግዴታ የሌለባቸዉ መሆኑን ከንግድ ህጉ አንቀጽ 532(1) መረዳት የሚቻል ቢሆንም የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያድርግ መሆኑን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤም የማህበሩ የበላይ አካል መሆኑን እንዲሁም የማህበሩን ዋና ስራ አስኪያጅ የሚሾመዉም ሆነ የሚሸረዉ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 5.2.1 ስር ሰፍሯል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅ ለመሾም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደርግ በመተዳዳሪያ ደንቡ ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል ከተባለ ደግሞ ከሳሾች በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ በህጉ አግባብ ጥሪ ተድርጎላቸዋል ወይ የሚለዉን መመልከቱ ጠቀሚ ነዉ፡፡ ተከሳሾች ለከሳሾች በህጉ አግባብ ጥሪ ተድርጎላቸዋል በማለት የሚከራከሩ እንደመሆኑ መጠን ይህን ፍሬ ነገር የማስረዳት ሽከም አለባቸዉ፡፡

2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጳጉሜ 1/13/2010 ዓ/ም በአካሄደዉ ጠቅላላ ጉባኤ የተገኙት የማህበሩ አባል 1ኛ ተከሳሽ ሲሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ከማህበሩ ካፒታል ላይ ከግማሽ በላይ ድርሻ ማለትም 54% ድርሻ ያላቸዉ በመሆኑ ምንም እንኳን ሌሎች የማህበሩ አባላት በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያልተገኙ ቢሆንም የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በማድረግ አቶ መዘምር ከተማን በስራ አስኪያጅነት የሾሙ መሆኑን የቀረበዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡

በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 5(1) የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩ የበላይ አካል መሆኑን የማህበሩን ዋና ስራ አስኪያጅ የሚሾመዉም ሆነ የሚሻረዉ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 5.2.1 ስር ተመልክቷል፡፡

2ኛ ተከሳሽ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲደረግ ጥሪ አድርጊያለሁ ይበል እንጂ እራሱ በማስረጃት ያያዘዉ  በቀን 13/10/2010 ዓ/ም በቁጥር ኤስዋይጂኤች/1013/18 የተጻፈ ደብዳቤ ቋሚ ዋና ስራ አስኪያጅ እና ሌሎች አጀንዳዎች ዉሳኔ ለማሰለፍ የማህበሩ አባለት በቀን 14/10/2010 ዓ/ም እንዲያገኙ የሚያሳስብ ድብዳቤ ሲሆን በዚህ ዕለት 1ኛ ተከሳሽ እና ሌሎች የማህበሩ አባላት ያልሆኑ የማህበሩ ጠበቆች ተገኝተዉ 1ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንዲሾሙ ለ1ኛ ተከሳሽ ስልጣን መስጠቱ የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ የማሻሻል ዉጤት ያለዉ ነዉ፡፡

የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 5 መሰረት ስራ አስኪያጅ የመመረጥ ስልጣን የጠቅላላ ጉባኤዉ እንደመሆኑ መጠን የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ ለመሻሻል ¾ ድምጽ የሚያስፈልግ ከመሆኑ አንጻር 1ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጁን እንዲመርጡ መወሰኑ ህገወጥ እና አስገዳነት የሌለዉ ነዉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቃለ ጉባኤ የተያዘዉ በ1/13/2010 ዓ/ም ሆኖ ሳለ ለከሳሾች በቀን 13/10/2010 ዓ/ም የተጻፈዉ ደብዳቤ በቀን 14/10/2010 ዓ/ም ለሚደረገዉ ስብሰባ እንደመሆኑ መጠን ተከሳሾች ይህኑኑ ደብዳቤ በማስረጃነት በማቅርብ ቃለ ጉባኤዉ ከመያዙ በፊት ለከሳሾች ጥሪ አድርገናል በማለት ያቀረቡት ክርክር ተገቢነት ያለዉ ካለመሆኑም በላይ ከ15 ቀናት በፊት የሰብሰባ ጥሪዉ ለከሳሾች ያልደረሰ በመሆኑ ተቀባይነት ያለዉ አይደለም፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተላኩት ደብዳቤዎቹ ለከሳሾች የደረሱ መሆኑን የተከሳሽ 2ኛ ምስክር የገለጹ ቢሆንም ምስክሯ ደብዳቤዉ ለከሳሾች ሲሰጥ በቦታዉ ላይ ያልነበሩ እና ደብዳቤዉ ለከሳሾች የደረሳቸዉ መሆኑን ከሌላ ሰዉ የሰሙ መሆኑ፤ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የስጋ ዝምድና ያላቸዉ መሆኑ ሲታይ እንዲሁም በቀን 1/13/2010 ዓ/ም ለተደረገዉ ስብሰባ ቀደም ብሎ በህጉ አግባብ ለከሳሾች ጥሪ የተደረገላቸዉ መሆኑን አለማስረዳታቸዉ ሲታይ ምስክሯ የሰጡት ምስክርነት እምነት የሚጣልበት ካለመሆኑም በላይ ምስክሯ ለከሳሾች ጥሪ ድርሷል የሚሉት ለሰኔ 14 ቀን 2010 ዓ/ም የተጠረዉን ስብሰባ ሲሆን ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ቃለ ጉባኤ የጸደቀዉ በዚህ ዕለት ባለመሆኑ እና ስራ አስኪያጁም የተሾሙት በዚህ ዕለት በተያዘ ቃለ ጉባኤ ባለመሆኑ በዚህ መልኩ በተከሳሾች የቀረበዉ ክርክር ተቀባይነት ያለዉ አይደለም፡፡

በቀን 14/10/2010 ዓ/ም ለሚደረገዉ ጠቅላላ ጉባኤ ከሳሾች የጥሪ ማስታወቂያ ደርሷቸዋል እንኳን ቢባል በተያዘዉ አጀንዳ መሰረት ስራ አስኪያጅ በመምረጥ ጉባኤዉ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 535(2) መሰረት ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ዉሳኔ ከሚሰጥ በቀር በቀን 14/10/2010 ዓ/ም ለሚደረግ ጠቅላላ ጉባኤ ቀደም ሲል ለከሳሾች ጥሪ ተድርጎላቸዋል በሚል ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ሳይደረግ 1ኛ ተከሳሽ ለብቻቸዉ ቃለ ጉባኤ  በመያዝ ስራ አስኪያጅ ሊሾሙ የሚችሉበት የህግ አግባብ የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሚያዚያ 1 ቀን 2010 ዓ/ም የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የጋራ ስራ አስኪያጅ የነበሩት በወ/ሮ ሕይወት ትርፍነህ ጥሪ የተደረገዉ የጠቅላላ ጉባኤ ጉባኤዉ አንደሚከናወን የሚገልጸዉ እ.ኤ.አ አፕሪል 12  በመሆኑ በቀን 1/13/2010 ዓ/ም ለተካዴዉ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ሊያገልግልበት የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ስለሆነም በቀን 1/13/2010 ዓ/ም በውልና ማስረጃ መዝገባ ጽ/ቤት የተመዘገበዉ ቃለ ጉባኤ ለከሳሾች በንግድ ህጉ እና በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ እና ተካሂዶ ያልተወሰነ ዉሳኔ በመሆኑ በከሳሾች ላይ አሰገዳጀነት ሊኖረዉ ሰለማይገባ በንግድ ህጉ አንቀጽ 416(5) መሰረት ተሽሯል፡፡

2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን ይህን ማህበር የሚገዛዉ የንግድ ህጉ ክፍል ከአንቀጽ 510-543 ስር የተገለጹት ድንጋጌዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ደንጋጌዎች ደግሞ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባል የሆነ ሰዉ ከማህበሩ ሊሰናበት የሚችልበትን አግባብ አያስቀምጡም፡፡በርግጥ ሃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር የሽርክና ማህበር እና የአክሲዮን ማህበራት የተቀላቀለ ባህሪ ያለዉ ማህበር መሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡

በሽርክና ማህበራት ዉስጥ የአባሉቱ ማንነት እና ባህሪ (personality of members) ለማህበሩ ቀጣይነት ዋሳኝ ነዉ ይህም የሆነዉ የሽርክና ማህበራት የሰዎች ስብስብ (association of persons) ስለሆነ ሲሆን የአክሲዮን ማህበር ዉስጥ ደግሞ የአባላቱ ማንንትም ሆነ ባህሪ ለማህበሩ ቀጣይነት ጠቃሚ አይደለም ይህም የሆነበት ምክንያት የአክሲዮን ማህበራት የካፒታል ስብስብ(association of capital) በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር ተከሳሽ ከማህበሩ ሊሰናበት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ ሃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማህበር ያለዉን የተቀላቀለ ባህሪ መሰረት በማድረግ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ከሳሾች ተከሳሽ ከማህበሩ እንዲሰናበት መሰረት አድርገዉ የሚከራክሩት የንግድ ህጉን አንቀጽ 261 እና 279 ሲሆን እነዚህም ድንጋጌዎች እንደየቅደመተከተላቸዉ የሚገኙት በንግድ ህጉ ስለ ተራ ሽርክና እና ስለ እሽሙር ማህበር በሚደነግገዉ የህግ  ክፍል ነዉ፡፡ የነዚህንም ድንጋጌዎች ይዘት ስንመለከተ ፍርድ ቤት በቂ ምክንያት ሲኖር እንዱን ማህበርተኛ ከማህበሩ እንዲወጣ ሊፈርድ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡እነዚህ ድንጋጌዎችም የሚገኙት ስለ ተራ የሽርክና ማህበር እና ስለ እሽሙር ማህበር በሚደነግገዉ የህግ ክፍል እንደመሆኑ መጠን እና ስለ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚደነግገዉ የንግድ ህጉ ክፍል ተጠቃሾቹ ድንጌዎች አገልግሎት ላይ ሊውል እንደሚችል የተመለከተ ገልጽ ነገር ባለመኖሩ ደንጋጌዉ በሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የሌለዉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡በመሆኑም በንግድ ህጉ አንቀጽ 261 የተራ ሽርክና ማህብርተኞችን እና በአንቀጽ 279(1) ላይ የእሽሙር የሽርክና ማህበር አባልን በፍርድ ቤት ከሽርክና ማህበር እንዲወጣ ለመወሰን የሚያስችል በግልጽ ተደንግጎ እያለ ስለ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባልን ፍርድ ቤት ከአባልነት እንዲሰርዝ ለመወሰን እንደሚቻል ያለመደነገጉ ተጠቃሾቹ ደንጋጌዎች በሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የሌላቸዉ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በ1ኛ ከሳሽ ማህበር የመመሰረቻ ጽሁፍም ሆነ የመተዳደሪያ ደንብ የማህበሩ አባል ከማህበሩ አባል ሊሰናበት የሚችልበትን አግባብ አልተቀመጠም፡፡ እንዲሁም ተራ የሽርክና ማህበር በንግድ ህጉ አንቀጽ 5 ስር በተዘረዘሩት የንግድ ስራዎች ላይ መሳተፍ እንደማይችል እንዲሁም ተራ የሽርክና ማህበር የንግድ ማህበራት ባህሪ የሌለዉ መሆኑን ከንግድ ህጉ አንቀጽ 213 እና 227 መረዳት የሚቻል ሲሆን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዓላማዉ ምንም ቢሆን የንግድ ማህበር መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 10(2) ስር የተቀመጠ በመሆኑ እና ሁሌም የንግድ ስራ የሚስራ  ከመሆኑ አንጻር እና ተራ የሽርክና ማህበር እንደ ንግድ ድርጅት የማይቆጠረ ከመሆኑ አንጻር በተራ የሽርክና ማህበር ስር የተደነገገን ደንጋጌ አመሳሰሎ(analogy) በግልጽ የንግድ ማህበር መሆኑ የተቀመጠ የንግድ ማህበር ላይ ተፈጻሚ ማድረግ አግባብነት የለዉም፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሊሰናበት የሚችልበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የከሳሾች በዚህ ረገድ የጠየቁትን ዳኝነት ውድቅ አድርጓል፡፡

ውሳኔ

1ኛ) በቀን 1/13/2010 ዓ/ም በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ተይዞ የጸደቀዉ ቃለ ጉባኤ ተሽራል፡፡

2ኛ) ወጪና ኪሳራ ከሳሾች ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 90፤የጠበቃ አበል ብር 50,000.00(ሃምሳ ሺህ) እንዲሁም ለቀረጥ ቴምብር የተከፈለ ብር 45(አርባ አምስት) ተከሳሾች ለከሳሽ ይክፈሉ፡፡

 

ትዕዛዝ

ይግባኝ መጠየቅ መብት ነው፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡