By muluken seid hassen on Friday, 10 September 2021
Category: Succession Law Blog

ስለ ኑዛዜ ከውርስ ሕግና ከሰበር ውሳኔዎች ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ኑዛዜ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሰጠው ትርጉም ባይኖርም አንድ ኑዛዜ ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር የሚያስቀምጡ የሕግ ድንጋጌዎችን ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 857 እስከ 908 ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ጽሁፍ ኑዛዜ በምን አግባብ ቢደረግ በሕግ ዘንድ ውጤት ይኖረዋል፤በውርስ ሕጋችን ላይ የተቀመጡት የኑዛዜ አደራረግ ስርዓቶች አስገዳጅነታቸው እስከምን ድርስ እንደሆነና ኑዛዜ በፍርድ ቤት ቢጸድቅ ሊያስገኝ የሚችለው ውጤትና ባለመጽደቁ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ ከውርስ ሕግ እና አስገጋጅ ከሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ውሳኔዎች አንጻር  በአጭሩ ዳሰሳ ለማድርግ ተሞክሯል፡፡ 

ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የስረ ነገር ሁኔታዎች    

በፍትሐ ብሔር ህግ ከአንቀጽ 857 እስከ 879 የተደነገጉት ድንጋጌዎች ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የሥረ ነገር ሁኔታዎች (essential condition of wills) አካትተው ተደንግገዋል፡፡ ከእነዚህ አጠቃላይ ደንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ለኑዛዜ ዋጋ መኖር አስፈላጊ የሆኑ የሥረ ነገር ሁኔታዎች በሁለት ከፍሎ ማየትና መተንተን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የኑዛዜ ሁለንተናዊ ወይም ተፈጥሯዊ አስፈላጊ ነገር( inherent or intrinsic elements of will) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኑዛዜው ይዘት ላይ የሚያተኩርና ለሕግና ሞራል ተቃራኒ መሆን ወይም አለመሆኑን የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡

    ሀ) ተናዛዡ ራሱ በሙሉ ሀሳቡ ኑዛዜ የፈጸመ መሆኑ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 857 በተገለጸው መሰረት ሟች ኑዛዜ የማድረግ ሀሰብና ፍላጎት ኖሮት እንደዚሁም የኑዛዜው ይዘት በመረዳት ኑዛዜ ማድረግ ያለበት እሱ ራሱ ብቻ መሆን እንዳለበት በግልጽ ደንግጓል፡፡ ህጉ የሟች ሀሳብ በሌሎች ሰዎች ማለትም በወኪሎች በኩል በኑዛዜ ላይ መግለጽ እንደማይገባው በመከልከል ኑዛዜውን የሟች የግል ስራና የራሱ የሀሰብ መግለጫ መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አንድ ሰው በሌላ ሰው በስሙ ኑዛዜ እንዲያደረግ ፤እንዲለውጥ ወይም እንዲሽር ስልጣን ሊሰጠው እንደማይችል አንድ ሰው ሌላ ሶስተኛ ወገን ወራሹን እንዴት እንደሚወስንና ውርሱ ለማን መተላለፍ እንዳለበት እንዲፈጽም ሊያደርግ እንደማይችል የውርስ ህግ ደነግጋል፡፡ 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁጥር 134836 በቅጽ 22 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ ላይ እንደተመላከተው “ ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው እና በሟች ብቻ የሚፈጸም በመሆኑ ብዙ ሰዎች አንድ በሆነ ጽሁፋ በጋራ ማናዘዝ የማይቻልና ኑዛዜው ፈራሽ የሚያደርገው ነው፡፡ በመሆኑም በተደረገው ኑዛዜ በሟች የግል ንብረት ላይ ሌላ ሰው ጭምር በአንድ የኑዛዜ ሰነድ ላይ ተናዘው ከተገኙ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 858፤857 እና 880 እና ተከታዩ ድንጋጌዎች አንጻር ፍርድ ቤቶች ኑዛዜውን ፈራሽ ነው በማለት የሚሰጡት ውሳኔ የሚነቀፍበት ሕጋዊ መክንያት የለም” ሲል የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

     ለ  የተናዛዡ ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ  

በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጲያ ሕግ የተናዛዡን ኑዛዜ የመፈጸም ሀሳብ (animus testandi) እያለው ኑዛዜ የፈጸመ መሆኑን ለማረጋገጥና ለኑዛዜው ዋጋ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት እንደ መስፈርት የያዘው የተናዛዡን ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ (capacity make a will) ነው፡፡

የተናዛዡ ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ የሚመዘነው የተናዛዡ የሚፈጽመው ተግባር ኑዛዜ መሆኑንና የሚፈጽመው ኑዛዜ ይዘት በአግባቡ የሚረዳ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በመመዘን ነው፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ነገር አንድ ሰው በሕግ ችሎታ ያለው መሆኑ አለመሆኑ ጉዳይ ኑዛዜ ለመፈጸም ካለው ችሎታ ጋር በቀጥታ ማይገናኝ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ኑዛዜ ለመፈጸም ችሎታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሌላው ኑዛዜ ለመፈጸም የሚያስፈልገው እድሜ አስራ አምስት አመት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት ማንኛውም አስራ አምስት አመት ያደረገ ሰው ያለማንም ሰው አመራር ሰጪነትና ተቆጣጣሪነት በሕግ ፊት ውጤት ያለው ኑዛዜ ለመፈጸም እንደሚችልና አስራ አምስት አመት ሳይሆነው የፈጸመው ኑዛዜ ግን በሕግ በኩል ውጤት እንደማይኖረው ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 308 ለመረዳት ይቻላል፡፡

በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች በፍርድ ከመከልከላቸው በፊት ያደረጉት ኑዛዜ ውጤት የሚኖረው ሲሆን በፍርድ ክልከላ ከተደረገለት በኋላ የሚያደርጉት ኑዛዜ ውጤት እንደማይኖረው የኢትዮጲያ የፍ/ብ/ሕግ አንቀጽ 368 ይደነግጋል፡፡ የአዕምሮ መጓደል የአንድ ሰው ኑዛዜ የመፈጸም ችሎታ ለማሳጣት ምክንያት አይደለም፡፡ በውርስ ሕጋችን መሰረት ኑዛዜውን ሲፈጽም የአዕምሮ ጉድለቱ (ህመሙ)  በግልጽ የታወቀ ሰው ካልሆነ በስተቀር ሌሎች የአዕምሮ ጉድለታቸው በግልጽ ያልታወቀ ሰዎችን የሚፈጽሙት ኑዛዜ ሕጋዊ ውጤት ይኖረዋል ይህንንም ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 863 ለመረዳት ይቻላል፡፡

    ) ኑዛዜ በመገደድ ወይም በሥህተት ወይም በመንፈስ መጫን ያልተደረገ መሆኑ  

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 867 እና 877 በተገለጸው መሰረት ሟች ኑዛዜ ያደረገው በሀይል ተገድዶ ወይም በስህተት ምክንያት ከሆነ ኑዛዜው ሊፈርስ ይችላል፡፡ ሟች በወቅቱ በደረሰበት የመንፈስ መጫን ምክንያት የተደረገው ኑዛዜ ለመቀነስ ወይም ለመሻር ዳኞች የሚከተሏቸው ሕጋዊ መሰረቶች በፍ/ብ/ህ/ቁ 875 ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

   መ) ኑዛዜው ህጋዊ መሆን  

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 865 እና 866 በግልጽ መረዳት የሚቻለው አንድ የኑዛዜ ቃል ለህግ ወይም ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ ከሆነ ሕጋዊ ውጤት አይኖረውም፡፡    

ኑዛዜ ዋጋ ያለው ይሆን ዘንድ በሕግ አስፈላጊ የሆነውን ፎርም አሟልቶ መገኘት ይኖርበታል፡፡ የኑዛዜ ፎርም ከተናዛዡ ውጪ በሆነ ሌላ ሀይል በሕግ አውጪው ኑዛዜው በምን መልክ መዘጋጀት እንዳለበት በሕግ የሚደነግግ ነው፡፡

የውርስ ሕጋችንም ኑዛዜ በሶስት አይነት ፎርም ሊፈጸም እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይኸውም

በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ፡

በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ ማለት አንድ ሰው ኑዛዜውን ሲፈጽም ሌሎች ሰዎች ( እማኞች) ባሉበት የተደረገ ሲሆን በዚህም ምክንያት ለአከባቢው ህብረተሰብ ግልጽ የሆነ ማላት ነው፡፡  በፍ/ሕ/ቁ 880 መሰረት ግልጽ ኑዛዜ የሚከተሉትን ሟሟላት አለበት፡፡

ግልጽ ኑዛዜ ለማድረግ ከዚህ በላይ በሕግ አስገዳጅነት የተቀመጠ መስፈርቶች መሰረት በማድረግ በአተገባበር ረገድ ዘርፈ ብዙ ክርክሮች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን አሰገዳጅ የሕግ ትርጓሜ እንመልከት…ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰበር መዝገብ ቁጥር 47917 በቅጽ 11፤በመ/ቁ 36777 በቅጽ 10 በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ኑዛዜ የተደረገው ከሁለት ሰዎች ምስክርነት በተጨማሪ ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው ሰው ፊት ስራውን በሚያከናውንበት ክፍል ውስጥ ከሆነ ውል ለማዋዋል ስልጣን የተሰጠው ሰው በምስክርነት ባይጠቀስም ሟች ኑዛዜውን ሲያደርግ በነጻ ፈቃዱ መሆኑን አይቶ እና ኑዛዜው ሲነበብ አይቶ ከፈረመ ስሙ ምስክር ተብሎ ባለመገለጹ ብቻ ምስክር አይደለም የሚባልበት ህጋዊ ምክንያት የለም ”  በማለት የሕግ ተርጓሜ ሰጥቷል፡፡ 

በሰ/መ/ቁ 70057 ቅጽ 13 እንዲሁም በሰ/መ/ቁ 147331 ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ ውል አዋዋይ ወይም ዳኛ ፊት የተደረገ ኑዛዜ በህጉ የተመካከተውን የኑዛዜ መነበብ ስርዓት ያላሟላ ከሆነ ህጋዊ ፎርማሊቲን እንደሚያሟላ መቁጠር አይቻልም፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881 ስር ከተመላከቱት የኑዛዜ ፎርማሊቲዎች መካከል ለይቶ ያወጣው የምስክሮችን ቁጥር ብቻ  ሆኖ ሁለት ምስክሮች በቂ የሚሆኑበትን አግባብ የሚያሳይ እንጂ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881/2/ ስር ኑዘዜ በምስክሮችና በተናዛዡ ፊት ስለመነበቡ የሚለው ስርዓት ውል አዋዋይ ወይም ዳኛ ፊት ለማድረግ ግልጽ የኑዛዜ ፎርማሊቲ የማይፈልግ መሆኑን የሚገልጽ አይደለም በማለት ኑዛዜው እስካልተነበበ ድረስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881/2/ ስር የተመለከተውን ፎርማሊቲ አያሟላም ተብሎ ፈራሽ እንዲሆን የግደ ነው ሲል” ውሳኔ ሰጥቷል፡፡     

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 193067 በቀን 30/11/2013ዓ.ም ( ያልታተመ) በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ላይ እንደተመላከተው  በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 881/2/ ስር ኑዛዜው በተናዛዡና በአራት ምስክሮች ፊት መነበብ ይኸው ስርዓት መፈጸሙንና የተፈጸመበትን የሚያመላክት መሆን አለበት የሚለው መስፈርት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 882 መሰረት በውል አዋዋይ ፊት ለተደረገ ግልጽ ኑዛዜ ጭምር ሊፈጸም የሚገባ ስርዓት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት “ኑዛዜ ወይም የስጦታ ውል በሕግ ስልጣን በተሰጠው አካል ወይም በውል አዋዋይ ፊት የተደረገ በሆነ ጊዜ ከዚህ ድንጋጌ ጋር ግንኙነት ያለውን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 922/2008 እና ይህን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ሰነድ ለማረጋገጥ ከተዘረጋው ስርዓት ጋር ተገናዝቦ መታየት አለበት፡፡ በዚህ አዋጅ መግቢያ ላይ እንደተመላከተው በሰዎች መካከል የሚደረጉ ሌሎች መስተጋብሮች በሚመለከት የሚፈጸሙ የውል እና ሌሎች ግንኙነቶች በሕግ አግባብ በማረጋገጥ እምነት የሚጣልበት ሰነድ ማመንጨት በአዋጁ በተዘጋው ስርዓት ለማሳካት የታለመ አላማ ነው፡፡ በተጨማሪም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7/3/ ስር እንደተመላከተው ማንኛውም ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ ተግባር እንዲፈጽም በአዋጁ ስልጣን የተሰጠው አካል የዜጎችን የግል ንብረት የማፍራት፤ የመጠቀምነ በሕጋዊ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን በማክበር የፍትሕ ስርዓቱን በማገዝ የሕግ የበላይነትን የማስጠበቅ አላማ ከግብ የማድረስ ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 2(2) እና 5፤8(5) እና 10(2) ስር ሰነድ አረጋጋጩ አዲስ ሰነድ በአዘጋጁ ወይም ጉዳዩ በሚመለከተው ሲፈረም ማየትና ይኸው መፈጸሙን ማረጋገጥ ወይም በትክክል መስፈሩን በማረጋገጥ እንዲፈጸም ማድረግ ፤ለማረጋገጥ የሚቀርቡ ሰነዶች ህጋዊነት ማረጋገጥ እንዲሁም አንቀጽ 17 ስር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አግባብ ባላቸው ህጎች የተደነገገውን ስርዓት መከተል የሰነድ አረጋጋጩ ተግባርና ኃላፊነት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ሰነድ አረጋጋጩ ሰነድ ከማረጋጋጡና ከመመዝገቡ በፊት የሰነዱን ይዘት የመለወጥ ወይም የማስለወጥ ሥልጣን ባይኖረውም የሰነዱን ይዘት ትክክለኛነት የማረጋገጥ የሰነዱ ይዘት ሕግንና ሞራልን የማይቃረን መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 13 ላይ የተደነገገው ያሳያል፡፡ ሰነድ አረጋጋጩ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ በሚል እምነት ሕግ አውጪው በአዋጁ አንቀጽ 17 ስር የስጦታ ውል ወይም ኑዛዜ የማረጋገጥና የመመዝገብ ተግባር በሚፈጽምበት ጊዜ ሁለት ምስክሮች እንዲፈርሙ ማድረግ እንደሚገባ ከመደንገጉ በስተቀር በዚህ አዋጅ አንቀጽ 17 ላይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881/2/ በተደገገው መሰረት ሰነድ አረጋጋጭ ኑዛዜ መነበብ እንዳለበት ይኸው ስለመፈጸሙ በኑዛዜው ሰነድ ላይ መመልከት አለበት የሚለው በኑዛዜ ሰነዱ ወይም በስጦታ ውሉ ላይ መመልከቱን ማረጋገጥ ይኖርታል በሚል አይደነግግም፡፡ሕግ አውጪው ይህንን መስፈርት በዝምታ ያለፈበት ምክንያት የስርዓቱ መፈጸም አስፈላጊ አይደለም በሚል ሳይሆን ሰነድ አረጋጋጩ ኑዛዜ ወይም የስጦታ ውል ከማረጋገጡና ከመመዝገቡ በፊት የሰነዱን ይዘት ትክክለኛነት የማረጋገጥና ይዘቱን ለሕግና ለሞራል የማይቃረን መሆኑን የማጋገጥ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣል በሚል እምነት ሰነዱ ላይ በቃላት ባይገለጽም አረጋጋጩ የማረጋገጥ ተግባሩን ሲወጣ የታለመው አላማ ከግብ ይደርሳል በሚል ነው፡፡ በመሆኑም የኑዛዜ ሰነድ ወይም የስጦታ ውል ላይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881/2/ በተደነገገው መሰረት ኑዛዜ መነበብ እንዳለበት ይኸው ስለመፈጸሙ በኑዛዜው ሰነድ ላይ መመልከት አለበት የሚለው ስርዓት ስለመፈጸሙ በግልጽ ያልተገለጸ ቢሆንም እንኳ ይህ ተግባር የኑዛዜ ውል ከመረጋገጡና ከመመዝገቡ በፊት በሰነድ አረጋጋጭ እንደተፈጸመ ሊቆጠር ይገባል እንጂ ይህ ስርዓት ስለመፈጸሙ የሚያመላክት ቃል ወይም ሀረጋት በኑዛዜ ሰነዱ ወይም በስጦታ ውሉ ላይ አልተመለከተም በሚል ኑዛዜው ወይም የስጦታ ውሉ ፈራሽ ሊሆን አይገባም ” በማለት ከዚህ ቀደም በቅጽ 13 በሰበር መዝገብ ቁጥር 70057 እና በሰበር መ/ቁጥር 177331 የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ በመሻር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡           

ለ) በተናዛዡ ጽሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ

በተናዛዡ ጽሁፍ የሚደረግ ኑዛዜን በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 884 የተደረገገ ሲሆን በዚህም መሰረት÷

ሐ) የቃል ኑዛዜ

የቃል ኑዛዜን በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 892 ላይ የተደነገገ ሲሆን በዚህም መሰረት የቃላ ኑዛዜ ማለት አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡ የቃል ኑዛዜም ማድረግ የሚቻለው÷

በአጠቃላይ ኑዛዜ በሕግ ፊት የሚጸናው ከዚህ ላይ የተጠቀሱትን ሕግ ያስቀመጣቸው መለኪያዎች አሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 17058 በቅጽ 4 እንዲሁም በመ/ቁጥር 42482 በቅጽ 10 ላይ ሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ መሰረት “ ኑዛዜ ህጉ ያስቀመጠውን ስርዓት እና መስፈርት አሟልቶ ከተገኘ በራሱ በሕግ ረገድ ውጤት የሚሰጠው ሰነድ ነው እንጂ በፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ ኑዛዜ በፍርድ ቤት ጸድቆ ከሆነ የኑዛዜው መጽደቅ ሌሎች ባለመብቶች ክርክር ወይም መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ሊገድባቸው አይችልም፡፡ኑዛዜ በፍርድ ቤት መጽደቁ በራሱ በኑዛዜ በተሰጠው ንብረት ላይ የኑዛዜ ተጠቃሚዎች ባለሀብት ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ብቸኛ ማስረጃ አይደለም ” ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

መደምደሚያ

ከዚህ በላይ በሰፈረው ጽሁፍ ለአንድ ኑዛዜ ህጋዊ መሆን በፍ/ብ/ሕጉ በአስገዳጅነት የተመላከቱ ድንጋጌዎችን ባካተተ መልኩ መዘጋጀት እንደሚኖርበት መረዳት ይቻላል፡፡ ከአሁን ቀደም ክርክር ሲነሳባቸው የነበሩ ሁኔታዎች በተለይም በውል አዋዋይ ፊት የተደረገ ኑዛዜ በተናዛዡ ፊት ስለመነበቡ በተመለከተ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል በሰበር መዝገቦቹ በሰጠው ውሳኔ ኑዛዜው እስካልተነበበ ድረስ በፍ/ብሕ/ቁ 881/2/ ሥር የተመለከተውን አያሟለም በሚል ሊፍርስ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ አሁን ላይ በመ/ቁጥር 193067 በቀን 30/11/2013ዓ.ም( ያልታተመ) በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የኑዛዜ ሰነድ ወይም የስጦታ ውል ላይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 881/2/ በተደነገገው መሰረት ኑዛዜ መነበብ እንዳለበት ይኸው ስለመፈጸሙ በኑዛዜው ሰነድ ላይ መመልከት አለበት የሚለው ስርዓት ስለመፈጸሙ በግልጽ ያልተገለጸ ቢሆንም እንኳ ይህ ተግባር የኑዛዜ ውል ከመረጋገጡና ከመመዝገቡ በፊት በሰነድ አረጋጋጭ እንደተፈጸመ ሊቆጠር ይገባል እንጂ ይህ ስርዓት ስለመፈጸሙ የሚያመላክት ቃል ወይም ሀረጋት በኑዛዜ ሰነዱ ወይም በስጦታ ውሉ ላይ አልተመለከተም በሚል ኑዛዜው ወይም የስጦታ ውሉ ፈራሽ ሊሆን አይገባም  በማለት ከዚህ ቀደም በቅጽ 13 በሰበር መዝገብ ቁጥር 70057 እና በሰበር መ/ቁጥር 177331 የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ በመሻር ውሳኔ መስጠቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ኑዛዜ በፍርድ ቤት ባይጸድቅም በሕግ የተመላከቱ አስገዳጅ መስፈርቶችን አሟልቶ የተደረገ እስከሆነ ድረስ የሚጸና መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ 

 

Related Posts

Leave Comments