By Filipos Aynalem on Monday, 23 September 2024
Category: Constitutional Law Blog

ፍትሕ እና ጤና

በሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ራሳቸውን በተለየ መልኩ የፍትሕ አካላት በማለት በየዓመቱ ሚያዝያ/ግንቦት ወር የፍትሕ ሣምንት የሚያከብሩ የፖሊስ፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ዐቃቤ ሕግ እና ፍ/ቤቶችን እንመለከታለን፡፡ በየዓመቱም በአዲስ አበባ ከተማችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ቅጥር ገቢ ድንኳን እየተተከለ ሥራዎቻቸውን በፎቶ ግራፎች፣ በጽሑፎችና በውይይት በተደገፈ ለሕዝብ በተለይም ለፍ/ቤቱ ባለጉዳዮች ያስጎበኛሉ፡፡ ነገር ግን ፍትሕ ተቋሞቻችን በመሠረታዊነት ከሚመዘኑበት የሥራዎቻቸው ቅልጥፍና፣ ውጤታማነትና ተገማችነት ባሻገር በአካል ለሚመለከታቸው ህንፃዎቻቸው፣ ግቢያቸው፣ የችሎት አዳራሾቻቸው/ክፍሎቻቸው፣ ቢሮዎቻቸው፣ መጸዳጃ ቤቶቻቸው ቢጎበኙ በተለይም ለጤና ተስማሚነታቸው ምን ይመስላሉ? የሚለው ጉዳይ ለዚህ ጽሁፍ ዐብይ መነሻ ምክንያት ነው፡፡

“ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡” የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 44(1)

ፍትሕ ብቻውን የሚቆም ወይም የሚነገርለት ቃል/ፅንሰ ሃሳብ ሳይሆን ከሰዎች ልጆች ሁሉአቀፍ መብቶች፣ ከሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ከፖለቲካዊ፣ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር ዕድገትና ምቹነት፣ ከእስረኞች፣ ከህፃናት፣ ከሴቶች … መብቶች ጋር በንፅፅር የሚታይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የሀገራችን የፍትሕ አሠራር ማለትም የፍትሕ አካላቱ አካባቢያዊ ምቹነት በደረጃ መዳቢዎች ባይለካም በተገልጋዩ ማህበረሰብ ሲገመገም ከሰዎች ጤና ወይም ደህንነት አንጻር ተደራሽነታቸው እንዴት ይታያል? የሰዎች ልጆች ደህንነት/ጤና ምን ዓይነት የሕግ ጥበቃ ተሰጥቶታል? የሚሉት ጉዳዮች ምልከታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የንጽህና እና የጤና ጉዳይ ከላይ በጽሁፉ መግቢያ እንደተመለከተው በኢፌዲሪ ሕገመንግስትም ሆነ በክልሎች ሕግጋተ መንግስት ዕውቅና የተሰጠውና የህግ ጥበቃ የሚደረግለት ሕገመንግስታዊ መብት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 44 “የአካባቢ ደህንነት መብት” በሚለው ርዕስ ሥር ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው በሚል የተደነገገ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛው ንባብ ደግሞ All persons have the right to a clean and healthy environment. በሚል ተደንግጓል፡፡

ከሕገመንግስቱ የድንጋጌው ርእስ፣ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ድንጋጌ ጣምራ ንባብ እንደምንረዳው የመኖር መብት… የሚገልጸው መኖሪያ ቤትን፣ ሥራችንን ስንሰራ ወይም ጉዳይ ስንፈጽምና ስናስፈጽም የምንቆይበትን፣ የምንወልበትን፣ የምንዝናናበትን፣ የምንጓጓዝበትን፣ ትምህርት ቤትን፣ ፍርድ ቤትን፣ ፖሊስ ጣቢያን፣ ማረሚያ ቤትን፣… ማንኛውንም አካባቢ እንደሚያካትት ነው፡፡ ሕገመንግስቱ ስለ አካባቢ ደህንነት መብት ከደነገገው በተጨማሪም የወንጀል ሕጉን ጨምሮ የተለያዩ ሕግጋትና ጤና ነክ ፖሊሲዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለጤና ያወሳሉ፡፡ ለምሳሌ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 514 እስከ 524 በጤና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በአንቀጽ 830 በህዝብ ጤና እና በፅዳት ጥበቃ ላይ ስለሚፈጸሙ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች የሚያስቀጡ መሆን በዝርዝር ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ የፍትሕ ተቋሞቻችንን በተለይም ዘወትር ከሰኞች እስከ ዐርብ በተለያዩ ባለጉዳዮች ሲጨናነቁ የሚውሉትን ፍርድ ቤቶቻችንን ጥቂት መመዘኛዎችን በመለኪያነት በመውሰድ ከሰዎች ንጹህና ጤናማ አካባቢያዊ መብት አንጻር ቀጥሎ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡


1. ከመታጠቢያና መፀዳጃ ቤት አቅርቦት አንጻር፡-


ከላይ ከተጠቀሰው የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ የምንረዳው ነገር የሰው ልጆች የሚውሉበት፣ የሚያድሩበት፣ የሚዝናኑበት፣ የሚሰሩበት… አካባቢ ሁሉ ለጤና ተስማሚ በሽታ አምጭ ነገሮችን የሚከላከል መሆን እንደሚገባው ነው፡፡ ከዚህም ዓላማ አንፃር በጤና ተቋማት ለሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች፣ ንግድ ቤቶች … የንግድ ሥራ ፈቃድ ሲሰጥም ሆነ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት ያላቸው መሆኑና አካባቢው ለጤና ምቹ መሆኑን ግምገማና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ መለኪያውን አሟልቶ ካልተገኘ የንግድ ድርጅቱ ይታሸጋል፣ ይዘጋል፣ ፈቃዱ ይሰራዛል፣ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል … ታዲያ የፍትሕ ተቋሞቻችን ለምሳሌ የፌደራል ፍ/ቤቶቻችን በአዲስ አበባ ከተማ የሚያስችሉት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ከዋናው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጀምሮ ሲመለከቷቸው ለባለጉዳዮች መታጠቢያና መፀዳጃ ቤቶች የሌሏቸው፣ ቀድሞ የነበሩት በተለያዩ ምክንያት በመፍረሳቸው አለመተካታቸው፣ በተለይም ወደ ሆቴሎች መንቀሳቀስ ለማይችሉት እስረኞች ወገኖቻችን ወንድም እህቶቻችን፣ እናት አባቶቻችን የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ አለመኖራቸው፣ አልፎ አልፎ ያለውም ሽታው በአካባቢው የማያስደርስና በዓይን ለማየትም በእጅጉ የሚዘገንን የመሆኑ ጉዳይ መፍትሄ ሰጭው አካል ማነው? በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማረሚያ ቤቶች ያለውስ ተቋማዊ ለጤና ተስማሚነት ምን ይመስላል? የሚለው ጉዳይ ዕይታን ይፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ የፍርድ ቤቶችን ባለጉዳዮች ልዩ የሚያድርጋቸው በሕገመንግስቱ አንቀጽ 25 ስለ እኩልነት እንደተደነገገው የታዳሚዎቹ ዓይነት በዘር፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በፖለቲካ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ሳይደረግ በርካታ ሰዎችን ባልሥልጣን፣ ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ኢንቨስተሮች፣ ባለሙያዎች፣ እሥረኞች፣ የውጭ ሀገር ዜጎች…የሚያካትት በመሆኑ የፍርድ ቤት ሁለነገሩ ልዩ ትኩረትን የሚጠይቅ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በየምድቡ በልደታ፣ በቂርቆስ፣ በየካ፣ በቦሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲ የፍ/ቤቶች ህንፃዎችን ማስገንባቱ ይበል የሚያሰኝና የሚያስመሰግን ለፍትሕ አሰጣጡም በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን የሚያሳድግ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ታዲያ እንደጉድለት ከሚነሱት መካከል የተሰሩት ህንፃዎች ለባለጉዳዮች መታጠቢያና መፀዳጃ ቤቶች የሌላቸው፣ በውጭ ከመፀዳዳት ያላዳኑ መሆናቸው፣ ብዙዎቹ ችሎቶች መስኮትና አየር አልባ መሆናቸው፣ አንዳንዶቹም መስታዎቶቹ ለፀሐይ የተጋለጡና የሚያቃጥሉ መሆናቸው፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት የሌላቸው መሆናቸው ከጤና አንፃር ሊገመገሙ ይገባል፡፡ በየፍርድ ቤቶቹ በእውነታው የሚታየው የመታጠቢያና የመፀዳጃ ቤቶች ችግር በትልልቅ የፍትሕ ባለሙያዎች ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር እንደ አንድ ትልቅ ችግር እየተነሱ መሆኑን ይስተዋላል፡፡

በሀገራችን ትልቁን የፍትሕ ተቋም በሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሚሰጥበትን የመጨረሻው የሞት ሽረት ፍርድ የሚሰጥበትን የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤትን ጨምሮ የአካባቢ ደህንነትን የሰዎች መብት ጉዳይ ቸል ማለታቸውና ቢያንስ አነስተኛውን የመታጠቢያና ንፁሕ መፀዳጃ ቤትን አቅርቦት ለባለጉዳዮች አለማሟላታቸው አብዛኞቹ ተቋማት በአዋጅ የተደነገገ ይመስል ለጤና ተስማሚ አለመሆናቸውን ለተመለከተ ተቋማቱ በንፅህና ጉዳይ ራሳቸውን እንዲጥሉ አስገዳጅ ሕገ ደንብ ይኖር ይሆን? ያስብላል:: በዘመናችን የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ የንግድ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ደረጃውን የጠበቀ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው ተፈጥሮአዊ ግዴታቸውን አሟልተው የሚታዩ ከመሆኑ አንጻር ከመንግስት የሦስቱ አካላት አንደኛው የሆነው ሕግ ትርጓሚው አካል በየዕለቱ ሕግ የሚተረጎምበትና የሚፈፀምበት አካል ተቋማትስ ይህ አንሷቸው ነው? ወይስ የሁሉም ሰዎች ተፈጥሮአዊ ግዴታን የመፈጸሚያው ነገር የፍትሕ ጉዳይ አይደለም ተብሎ ነው?

2. የፍርድ ቤቶች ግቢዎች፣ ክፍሎችና ህንጻዎችን በተመለከተ፡-

ብዙዎቹ ፍርድ ቤቶች የሚያስችሉባቸው ህንጻዎችና ክፍሎች በወቅቱ ዕድሳት የማይደረግላቸው፣ የተሰበሩ የመስተዋት መስኮቶች የማይጠገኑላቸውና ከነፋስ/ብርድ የማያድኑ መሆናቸው፣ የጽዳት ንጽህናቸው በአግባቡ የማይጠበቅላቸው፣ በየህንጻው ግድግዳ ላይ ዓመታት ያሳለፉ ለአንድ ቀን/ለቀናት ብቻ የሚያገልግሉ ወደ ቆሻሻነት የተለወጡ አቧራ የጠገቡ የወረቀት ማስታወቂያዎች የሚታዩባቸው፣ በግቢያቸው አሮጌ ተሽከርካሪዎችን ሳይቀር መወገድ የሚገባቸው ልዩ ልዩ ቆሻሻዎች የሚታይባቸው፣ አንዳንዶቹ በኪራይ የተያዙ ህንጻዎች በቂ የችሎት አዳራሽ የሌላቸው በኮምፐልሳቶ የተካፋፈሉ፣ ችሎት አዳራሽ የለም ተብሎ ቀጠሮ የሚለወጥባቸው፣ የፎቅ መውረጃ መውጫቸው ከላይና ከታች የሚጓዙ ሰዎችን የማያስተላልፉና እስረኞችን በፖሊስ አጅቦ ለመጓዝ ፍጹም የማያስችሉ መሆናቸው፣ ችሎት መጠበቂያ ኮሪደር እንኳን የሌላቸው፣ የዳኞች ጽ/ቤቶች የተጨናነቁ መሆናቸው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ሰበር ሰሚ ችሎቶችን ጨምሮ ችሎት በፈረቃ መሆኑና በጽ/ቤት ለመስተናገድ ለሰዓታት ያለበቂ ማረፊያ ባለጉዳዮች እንዲቆሙ የመገደዳቸው ነገር ከሚባክነው ወርቃማ ጊዜ ባሻገር በጤና ላይ ከሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት አንጻር አስቸኳይ መፍትሔ ሰጭ አካል እና መፍትሔ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡

የፍርድ ቤቶችን የችሎት አዳራሾች ለምሳሌ በልደታ ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ብዙዎቹን ችሎቶች ለተመለከተ መስኮትና አየር አልባ መሆናቸው፣ መብራት ሲጠፋ ብርሃን የለሽ የመሆናቸው ነገር በዚህ የሰለጠነ ዘመን ከአርክቴክቸሩ ጀምሮ ተወቃሹ ብዙ ነው፡፡ በቂ አየር በሌለው ክፍል ውስጥ ለሰዓታት ተጨናንቆ መቀመጡ ለዳኛው፣ ለፍ/ቤቱ ሠራተኞችም ሆነ ለባለጉዳዮች የሚፈጠረውን የጤና ጉድለት መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ የጤና ጉዳይ በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የዓለም ጤና ድርጅትን፣ በሀገር ደረጃ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን፣ ልዩ ልዩ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማትን እስከመቋቋም ያደረሰ ጉዳይ መሆኑ የቱን ያህል ትኩረት የሚሻ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ለነገሩ በሀገራችን ከአካባቢያዊ ንጽህና እና ደህንነት ጋር ያለን ልማዳዊ የአመለካከት ችግርም ለተቋማቱም አንዱ የችግሩ ሁሉ መነሻ ይመስላል፡፡ በከተማችን ቀድሞ የነበሩ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች አለመተካታቸውና የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ችግሩ የበለጠ እየከፋና የፈጠጠ መሆኑ፣ በኃይማኖትና በትምህርት ተቋማት ጭምር ለጤና ነክ ጉዳዮች ትኩረት የማይሰጥ መሆኑ፣ በየመንገዱ ባለመኪኖች ሳይቀሩ ቆሻሻን በየአስፋልቱ ሲጥሉ ማየቱ፣….በጥቅሉ ስለ አካባቢያዊ ደህንነትና ንፅህና ጉዳይ አመለካከታችን የሚሻሻለው/የሚለወጠው መቼ ይሆን? ያስብላል? እንቆቅልሻዊ ጥያቄም ይመስላል፡፡ የፍትሕ ሳምንት 7 ዓመታትን አስቆጥሮ ከጤና ጋር በተያያዘ ግን ያነሳው ነገር አልተሰማም ወይም ያመጣው ለውጥ አልታየም፡፡ ለቀጣዩ ዓመት 8ኛው የፍትሕ ሳምንት አንዱ የፍትሕ ተቋማቱ የሚመዘኑበት ነገር የጤና ጉዳይ እንዲሆን ከወዲሁ መሥራት ይኖርብናል፡፡

በየፍ/ቤቶቻችን የሚታደሙት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ዜጎችም በመሆናቸው ሀገራችንንም ለትዝብት እያጋለጣትና ችግሩ የፍርድ ቤቶቻችንን መልካም ገጽታም የሚጎዳ በመሆኑ ጉዳዩ ቀላል ነገር ሲመስል ከጤና አንጻር ወሳኝ ነገር በመሆኑ ለመፍትሔው እንደመዝገቦቹ ያልተወሰነ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጠውና ሊዘገይ አይገባም እንላለን፡፡ በሀገራችን አበባል “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንደሚባለው ፍርድ ቤቶች ባለጉዳዮችን አካባቢያዊ ደህንነት መብታቸው በመጓደሉ ምክንያት ታምመው ከመማቀቅ ይታደጓቸው፡፡ በአንዳንድ ምግብ ቤቶች አካባቢዎች “የምግብ ንፅህና ጉድለት የጤና ጠንቅ ነው” የሚል ጥቅስ ተጽፎ ይነበባል፡፡ የፍትሕ አካላት የአካባቢ ንፅህና ጉድለትስ የጤና ጠንቅ አይሆንምን?
ታዲያ በፍ/ቤቶቻችን የሚስተዋሉትን ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ነገሮችን መቆጣጠርና ማስተካከል ያለበት ማነው? ደረጃ መዳቢዎች፣ ጤና ጥበቃ ሚ/ር፣ የፍ/ቤቶች ኃላፊዎች፣ ዳኞች፣ ማህብረሰቡ …? የአካባቢ ደህንነት የሰዎች መብትን ለማስከበር መፍትሔው በፍርድ ቤቶቹ በራሳቸው ክስ አቅርቦ ዳኝነት መጠየቅ፣ የሕግ አስፈጻሚው አካል ለሆነው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቤቱታ ማቅረብ፣ ጉዳዩን በተለየ ባለቤትነት የሚከተታልና የሚያስፈጽም ክፍል በየፍርድ ቤቱ እንዲኖር ማድረግ፣ ሥራውን ከፍ/ቤቶቹ ውጭ አካላት የሆኑ ባለድርሻ አካላት እዲሳተፉበት ማድረግ፣ ወይስ ሌላ ….?

3. የቀጠሮ ሰዓት አለመከበርና በሰዓቱ አለመስተናገድ፡-

ሌሎች ከፍትሕ ጋር በተያያዘ ከጤና ጋር ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው ነገሮችም አሉ፡፡ በሰዓቱ ካለመስተናገድ ጋር በተያያዘ ጠበቆችና ባለጉዳዮች ለሰዓታት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ በየግቢው፣ በየኮሪደሩ መቀመጫም በሌለበት ቆመውና ከተገኘም በየድንጋዩ ላይ ተቀምጠው ለሰዓታት በጽ/ቤት ጥሪ መጠበቁ በግልጽ ችሎት የመዳኘትን መብት ትተነው በጤና ላይ የሚፈጥረው ጫና (stress) ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስከትለው የእግር፣ የወገብ፣ የስኳር፣ የደምብዛት፣ የሥነልቦና … ሕመሞች ይኖራሉ፡፡ በእርግጥም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰዓት መቅጠር የተለመደ ሲሆን ነገር ግን በሰዓት የመቀጠሩ ዓላማ ከቀጠሮው ሰዓት በፊት ከተጠራ አልቀረበም ላለመባል እንጅ የቀጠሮውን ሰዓት ለማክበር እንዳልሆነ በግልጽና በተግባር የሚታይ ነገር ነው፡፡ በዘመናችን በሰዓታት፣ በደቂቃዎችና በሰከንዶች ብዙ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮች ይከወናሉ፡፡ ይህንን ከሀገራችን ብርቅዬ አትሌቶች ስኬት በስተጀርባ ያለው ሚስጥር ደቂቃዎችንና ሰከንዶችን በአግባቡ መጠቀማቸው ከመሆኑ አንጻር ለኢትዮጵያውያን የጊዜ ዋጋንና ጠቀሜታን መረዳቱ ቀላል ነው፡፡ ሕግም ለጊዜ ትልቅ ዋጋ የሰጠ ሆኖ ባለበት ውዱን ነገር የፍትሕ ተቋማት ግን ሰዓታትና ደቂቃዎችን ብቻ ሳይሆን ቀናት፣ ወራትንና ዓመታትን ሳይቀር እንደቀላል ነገር የጊዜን ዋጋ ቸል በማለት በተበላሸ ሁኔታ በሥራ ላይ የሚያውሉትና መሠረታዊ የመሻሻል ለውጥ የማይታበት ልማድ የሆነው የጊዜ ጉዳይ ፍትሕን ከማዘግየቱ በተጨማሪ በባለጉዳዮች ሥነልቦናዊና አካላዊ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ልብ ሊባልና መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

4. ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ከመሰጠቱና ፈጣን ውሳኔ ካለማግኘት አንጻር፡-

ጉዳዮች በተፋጠነ ሁኔታ ሳይቋጩ ለብዙ ዓመታት ሲጓተቱም በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ጉዳዮች ጠበቆችን ጨምሮ በባለጉዳዮች ጤና ላይ አሉታዊ ውጤት እንዳለው መገመቱ ቀላል ነው፡፡ ለምሳሌ በፍቺ የተለያዩ ባልና ሚስት የፍቺ ውጤት የሆነውን ንብረቶቻቸውንና የልጆቻቸውን ጉዳይ በአጭር ጊዜያት ዕልባት ማግኘት ካልቻሉና የመጨረሻ ፍትሕ ለማግኘት በአማካይ ለ4 እና 5 ዓመታት በላይ የሚቆይ ከሆነ፣ ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ የሚገኙ ባለጉዳዮች ፍርድ ለማግኘት ለዓመታት የሚመላለሱ፣ ከሚፈረድባቸው በላይ የሚታሰሩ፣ ለዓመታት ታሥረው ነፃ የሚባሉ፣ በተጨማሪም የሚታሰሩበት ክፍል/አዳራሽ የጤናን ጉዳይ ከግምት የማያስገባ ከሆነ…. በዜጎቻችን በሕይወታቸው፣ በአካላዊና በሥነልቦናዊ ጤንነታቸው ላይ የሚያስከትለውን ውጤት መገመት ቀላል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ሲታሠሩም ሆነ በእሥር ላይ እያሉ የጤና እክል ለሚገጥማቸው ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት ጥበቃ አስተዳደር ሥር ለሚገኙ እስረኞችም በአካባቢያዊ ደህንነት መብትም ሆነ በቀጠሮ አሰጣጡ ልዩ ትኩረትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡

ሕግን መሠረት ያደረገ ውታጤማና ቀልጣፋ ውሳኔ ከመስጠት አንጻር፡- ይህ ንዑስ ርዕስ ራሱን በቻለ በየአንዳንዱ ጽንሰ ሃሳብ ብዙ ገጾችን ሊያጽፍ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን የተቋቋሙበት ዓላማ በዜጎች መካከል ወይም በመንግስት አካላትና በዜጎች መካከል የፍትሐብሄርም ሆነ የወንጀል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ሕግን በመተርጎምና የዜጎችን መብት በማክበረና በማስከበር ፈጣንና ውጤታማ መፍትሔ በመስጠት የሕዝቦችን ሰላም ማረጋገጥ ነው፡፡ በዘንድሮው ዓመት በተከበረው 7ኛው የፍትሕ ሣምንት የበዓሉ መሪ ቃል “የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የሕዝቦች አንድነት” በሚል እንደተገለጸውና በየቦታው በፍርድ ቤቶች ቅጥር ግቢ ተለጥፎ እንዳነበብነው ፍርድ ቤቶች ዕለታዊ ተግባሮቻቸውን የፍርድ ቤቶቹን ራእይ፣ ተልዕኮና ዓመታዊ ዕቅድን መሠረት አድርገው ዜጎችና የሚያረካ፣ የሕዝቦች ታማኝነትን ያተረፈ ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተገማች ውጤትን ሊያሳዩን ይገባል፡፡ የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል እንደሚባለው ፍትሕ የሚዘገይና ቅልጥፋና የሚጎድለው ከሆነ ለመዘግየት ምክንያት የሆኑትን ቀላሎቹን ችግሮች ለምሳሌ የዚህ ዓመት አንደኛውን በቃል ክርክርና በምስክሮች መስማት የችሎት ውሎዎች በድምጽ የተቀዳን ወደ ጽሁፍ ለመለወጥ በርካታ ወራትን እያስቆጠረ ለቀጠሮዎች መለወጥና ለጉዳዮች መዘግየት ምክንያት ሆኖ የሚታየውን ቀላል ችግር እንኳን በወቅቱ ለመፍታት ካልተቻለ የውጤታማነትና የቅልጥፍና እጥረት እስከ ይግባኝ እና ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ለበርካታ ዓመታት በመሟገት ወቅታዊ ፍትሕን ከማሳጣቱ በሻገር በተዘዋዋሪ የባለጉዳዮቹንም ሆነ የሰራተኞችን ጤናንም እንደሚጎዳ ግልጽ ነውና ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንሻለን፡፡

ስለዚህ አዕምሮአዊ፣ ሥነልቦናዊ እና አካላዊ ጤንነትን ያገናዘበ፣ የአካባቢ ደህንነት ህገመንግስታዊ መብትን ያከበረና ያስከበረ የፍትሕ ተቋማት ሊኖሩን ይገባል/ እንዲኖረን መብታችንም ነው፡፡

Related Posts

Leave Comments