By muluken seid hassen on Tuesday, 05 April 2022
Category: Contract Laws Blog

የሽያጭ ውልን የተመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች ከሰበር ውሳኔ ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

መግቢያ

በዚህ ጽሑፍ የሽያጭ ውል ምንነት፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ስላለው መብትና ገዥው ስለሚኖርበት ግዴታ፣ የሽያጭ ውልን መሰረት አድርገው የሚቀርቡ ክርክሮች ይዘታቸው እና  የይርጋ ገደባቸው ምን እንደሚመስል እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ንብረቱን ሊለቅ የሚችልባቸው የሕግ አግባብ ምን ምን እንደሆኑ ከፍትሐብሔር ሕግ እና ከሰበር ውሳኔዎች አንጻር ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡   

1. የሽያጭ ውል ማለት ምን ማለት ነው

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2266 ላይ እንደተገለተው የሽያጭ ውል ማለት በሻጭና በገዥ መሀከል አንድን ነገር አስመልክቶ አደኛው ወገን የተወሰነ ገንዘብ (price) ለመክፈል ሌላኛው ወገን ደግሞ ዕቃውን ከነ ባለሀብትነቱ ለማስረከብ የሚገቡት ውል ነው፡፡

በዚህ የሽያጭ ውል ትርጉም ውስጥ ጎልተው የሚወጡ ነጥቦች

በሌላ አነጋገር የሽያጭ ውል በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የግዴታ መቋቋምና መፈጸም የሚያስከትል ሆኖ ይህም ባህሪው በአንደኛው ወገን ላይ ብቻ ግዴታ ከሚጥሉ እንደ የስጦታ ውል ካሉ ልዩ ውሎች የሚለየው ነው፡፡ የሽያጭ ውል በባህሪው የችሮታ (gratuitous) ባህሪ የለውም፡፡

ከሽያጭ ውል አይነተኛ ባህሪያት አንዱ ባለሀብትነትን ለገዥ ማስተላለፉ ነው፡፡ ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2281-86 ተመላክቶ ይገኛል፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም የሽያጭ ውል አላማ ገዥን ባለቤት ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ሻጩ ዕቃውን ለገዥ ከማስረከቡ በተጨማሪ ባለቤትነትን ማስተላለፍ አለበት፡፡ ባለቤትነት በዋናነት በሕግ ወይም በውል ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ባለቤትነት በሕግ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1161 ላይ የተጠቀሰው የቅን ልቦና ባለይዞታነት (good faith acquisition) መሰረት ነው፡፡ ባለቤትነት በውል ሲተላለፍ የተላለፈለት ወገን ገዥ ከአስተላላፊው ሻጭ ያነሰ መብት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ ሀሳብ በላቲት nemo dat qua non habet የሚባለው ሲሆን ትርጉሙ ማንም የሌለውን መብት ( ባለቤትነት) ሊያስተላልፍ አይችልም ነው፡፡ በመሆኑም ሻጭ መብቱን ከማስተላለፉ በፊት በርግጥ የባለቤትነት መብት ያለው መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡   

2. የማይንቀሳቀስ እና ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት ገዥ ስላለው መብቶች እና የሻጭ ግዴታዎች

ሻጭ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሶስተኛ ወገን ይዞታና ቁጥጥር ነጻ በማድረግ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ ገዥ ለሻጭ ከሚሰጠው የመነቀል ዋስትና ግዴታ የተለየ ነው፡፡ ሻጭ ንብረቱ ላይ የሰፈሩትንና በንብረቱ መዝገብ የተመዘገበ መብት የሌላቸውን ሰዎች የማይንቃቀስ ንብረት እንዲለቅቁ በማድረግ ለሻጭ የማስረከብ ግዴታ የማይንቀሳቀስ ንብረት ውል በመፈጸም ሂደት ገዥ ለሻጭ ሊያከናውነው የሚገባ የመጀመሪያ ግዴታ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2882 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት ሻጭ ለገዥ የሸጠለት የማይንቀሳቀስ ንብረት የማይንቀሳቀስ ስለመሆኑ የሚሰጠው ዋስትና ገዥ የገዛውንና የተረከበውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ነጻ ሆኖ ከተረከበ በኋላ ንብረቱ የእኔ ነው ባይ ቢመጣ ሻጭ በዋቢነት ሊቆምለት የሚገባ መሆኑን የሚያመላክቱ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡

ገዥ የቤቱ ባለሀብትነት መብት በሽያጭ ውል ከሻጭ የተላለፈለት መሆኑን የሚያሳይ የሽያጭ ውል ሰነድና በሽያጭ ውሉ መሰረት በማይንቀሳቀሰው ንብረት ባለኃብትነት የተዛወረለት መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በማያያዝ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1206 መሰረት ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብትና ጥቅም አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጉዳይ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ክርክር ሲካሄድ ይስተዋላል፡፡ በአንድ አንድ ችሎቶች ገዥ የቤቱን ሻጭ ከመክሰስ በስተቀር በቀጥታ በተሸጠው ቦታ ላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሰዎች ቤቱን እንዲለቅቁ ክስ ማቅረብ አይችልም በማለት ውሳኔ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 100395 በቅጽ 21 ላይ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን ትርጓሜውም “ገዥ ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሰረት የተሸጠውን ቤት የያዙትን አስለቅቀው ያስረክቡኝ በሚል ክስ ሲያቀርቡ በማይስቀሳቀሰው ንብረት ላይ በማናቸውም ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን በተከሳሽነት አጣምረው መክሰስ እንዳለባቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 36(4) አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ ይህም ሻጭን በሚከሱበት ጉዳይ የተሸጠውን ቤት የያዙትን የግድ በተከሳሽነት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚገባ ነው፡፡ በፍርድ ቤቶች ገዥ ሻጭን ከመክሰስ በስተቀር በተሸጠው ቦታ ላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሰዎች ቤቱን እንዲለቅቁ ክስ ማቅረብ አይችልም በማለት የሚሰጡት ውሳኔ ሻጭ በሽያጭ በተላለፈው ንብረት ላይ ያለውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ገዥው ከውል የመነጨ መብት ያለው መሆኑን ያላገናዘበና በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195 ፣1206 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33(2) ድንጋጌዎች ያላገናዘበ በመሆኑ ስህተት ያለበት ነው” በማለት ወስኗል፡፡

የመኪና ሽያጭ፡ የመኪና ሽያጭን በተመለከተ ሻጭ ከመኪናው ጋር በተገናኘ ከመኪናው ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ሰነዶችን ለገዥ አሟልቶ ያስረከበ መሆኑ ከተረጋገጠ ገዥ ስመ ኃብቱ በስሜ አልተዘዋወረም በሚል ምክንያት ብቻ ውሉ እንዲፈርስ የሚያቀርበው አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ስመ ሀብቱን ለማዞር አስፈለጊ ሁኔታዎችን አሟልቶ ስም እንዲዘዋወርለት ለሚመለከተው የአስተዳደር አካል ጥያቄ አቅርቦ መብቱ ሊረጋገጥለት ያልቻለ ሰው መብቱን የሚያስጠብቀው በሚመለከተው አከል ላይ በፍርድ ቤት ክስ በመመስረት እንጂ ውሉ እንዲፍርስለት በመጠየቅ አይደለም በማለት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 56569 በቅጽ 12 ላይ የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡   

 

3. የሽያጭ ውል አለመፈጸም ስለሚያስከትለው ውጤት

ተዋወይ ወገኖች ያቋቋሙት ውል አለመፈጸሙ ልዩ ልዩ ውጤቶችን ያከትላል፡፡ አንድ ግዴታ እንደውሉ አልተፈጸመም የሚባለው

እንደ ውሉ አልተፈጸመም የሚል ወገን ሁለት መፍትሔዎች ይኖሩታል፡፡

1ኛ) ውሉን በግዴታ ማስፈጸም

2ኛ) ውሉን ማፍረስና ካሳ መጠየቅ (1784-1789) ይህም በነጠላ ማለትም በአንደኛው ወገን ከሳሽነት ወይም በፍርድ ቤት አጽዳቂነት ሊፈጸም ይችላል፡፡

ጉድለት ያለበት ንብረት ወይም ደግሞ ሙሉ የባለቤትነት መብት ለመገልገል የማያስችል ጉድለት ያለበት ንብረት የተረከበ ገዥ ያለው የማስተካከያ መብት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2336 ቀጥሎ ባሉት ድንጋጌዎች የተጓደሉትን ነገር አሟልቶ ይፈጸም ዘንድ ወዲያውኑ መጠየቅ ሲሆን ከዚህ ጋር ጎን ለጎንም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2360 እንደተመለከተው ከላይ ከተመለከቱት የህግ መፍትሔዎች በሻጭ ግዴታ መጓደል ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት በገንዘብ አስልቶ መጠየቅ እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡

ገዥ የሽያጭ ውል በግድ አንዲፈጸምለት ለመጠየቅ የሚችለው ልዩ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝለት ሆነ ሲገኝ ሲሆን ገዥው ውሉ ላይ ልዩ ጥቅም አለው የሚባለው እና የሽያጭ ውሉን ፍርድ ቤቶች ሻጭ በፍርድ ሀይል እንዲፈጽም ለመወሰን የሚችሉት የሽያጭ ስምምነት የተደረገበት እቃ በልምድ ምትክ ሊገኝለት የማይችል የሆነ እንደሆነ ወይም የተባለውን ምትክ ለመግዛት ገዥው ላይ ከፍ ያለ ወጪና ችግር የሚያስከትል አንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2329 እና 2330 ተደንግጓል፡፡ ገዥውም ውሉ በግዴታ እንዲፈጸምለት የማስገደድ ሀሳብ ያለው መሆኑን በመግለጽ ለሻጭ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት አለበት፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ገዥ የሽያጭ ውሉ በፍርድ ኃይል ይፈጸምልኝ ለማለት አይችልም፡፡

የማይንቀሳቀስ ንብረት የሸጠ ሰው ሁለት ግዴታዎች አሉበት፡፡ እነርሱም 1ኛ) የማይንቀሳቀሰውን ንብረት ከሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ከሻጭ ቁጥጥር ነጻ በማድረግ ለገዥ ማስረከብ ( የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2875 እና 2247)፣ 2ኛ) የ3ኛ ወገኖች መብት ካለ ገዥ ማስታወቅ፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2880 እና 2888 ናቸው፡፡ በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት ገዝቶ የንብረቱ ባለሀብትነት ማስረጃ ተሰጥቶት ያለ ገዥ በማስረጃው ከተመለከተው ንብረት ውስጥ የተወሰነው በሌሎች ሰዎች እጅ ስር ከሆነ ገዥው እነዚህ ሰዎች ቦታውን እንዲለቅቁ ክስ ሲያቀብባቸው ከውል የመነጨ መብት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ሻጭ ቦታውን ከ3ኛ ወገን ነጻ አድርጎ የማስረከብ ግዴታ ስላለበት በክርክሩ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡ ( ሰ/መ/ቁ 100395 ቅጽ 20)    

ስለዚህ ከዚህ መረዳት አንደሚቻለው ተዋዋይ ወገኖች የሽያጭ ውልን በተመለከተ ያላቸውን አለመግባባት ለመዳኘት አቤቱታ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህ አቤተታ በየትኛው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለፍርድ ቤት ሊቀርብ አንደሚገባ ከዚህ በታች ባለው ርዕስ ስር እንመለከታልን፡፡

4. የሽያጭ ውል ይርጋ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2892 በተጠቀሰው መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ውሉ እንደ ቃሉ ዓይነት እንዲፈጸምለት ለማድረግ የተለየ ጥቅም እንዳለው ሆኖ ይገመታል፡፡ ስለዚህ ውሉ እንደ ቃሉ ዓይነት እንዲፈጸምለት ለማስገደድ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሻጩ ውሉን አንደ ውሉ ቃል ከመፈጸም መዘግየቱ ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ውሉ እንዲፈጸምለት ካልጠየቀ በቀር ገዥው ውሉን በግዴታ አንዲፈጽም የማድረግ መብቱን ያጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ የእንግሊዘኛው ትርጓሜ the buyer shall lose the right to demand the specific performance of the contract where he fails to demand it within one year after he has ascertain the delay of the seller በማለት ይደነግጋል፡፡ በአማርኛው መዘግየቱን ከተረዳበት በሚለው ቃል እና በእንግሊዘኛው ascertained በሚለው መካከል ልዩነት ያለ ሲሆን የድንጋጌው መንፈስ ገዥው በአንድ አመት ውስጥ አንዲፈጸምለት ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ያለበት ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሰረት ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኑን ካረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የእንግሊዘኛውን የቃል አጠቃቀም በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ጉዳት በተመለተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 38935 በቅጽ 8 ላይ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ትርጓሜውም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1731(1) እና 1732 መሰረት ተዋዋይ ወገኖች የውል ቃል መሰረት በማድረግ ውሉን የመፈጸም ፍላጎትና ቅን ልቦና ያላቸው መሆኑ የውል ሕግ ግምት የሚወስድበት ጉዳይ በመሆኑ ገዥ በሽያጭ ውሉ በገባው የውል ቃል መሰረት አንዲፈጸም የተለያዩ የተስፋ ቃሎችን ሲሰጠው የቆየ መሆኑ የማስረዳት ግዴታ የለበትም፡፡ በተቃራኒው የፍ/ብ/ህ/ቁ 2892(3)  ን ጠቅሶ የሚከራከር ሻጭ ከገዥ ጋር ባደረገው የሽያጭ ውል መሰረት ለመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑ ገዥ በማያሻማ ሁኔታ እንዲያውቅና አንዲረዳው ያደረገ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ በአጠቃላይ ሻጭ በገባው የሽያጭ ውል ቃል መሰረት ለመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑን በማሻማ ሁኔታ ለገዥ ካሳወቀውና ገዥም ይህንኑ ከተረዳው እና ካረጋገጠ ከአንድ ዓመት በኋላ የውል ይፈጸምልኝ ክስ ገዥ ያቀረበ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ የለበትም፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2892(3) ላይ ያለው ይርጋ ተፈጻሚነት የሚኖረው ገዥ ለሻጭ በውሉ መሰረት የመፈጸም ፋላጎት የሌለው መሆኑን በማያሻማ ሀኔታ ገዥ እንዲያውቀው ያደረገበት ቀን መነሻ በማድረግ መሆን ይገባዋል፡፡ አንዲሁም የፍ/ብ/ህ/ቁ 2875፣2892(3) እና 2331 ተጣምረው ሲታዩ ውሉ የሚፈጸምበት ቀን በጥብቅ ወይም በቁርጥ የተወሰነ መሆኑ በተገለጸ ጊዜ ነው፡፡ በመሆኑም ሻጭ በውሉ መሰረት የመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ለገዥ በማያሻማ ሁኔታ ያሳወቀ መሆኑን ባላስረዳበት ሁኔታ ወይም የሽያጭ ውሉ የሚፈጸምበትን ጥብቅ የጊዜ ገደብ ባልገለጸበት ሁኔታ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2892(3) የተገለጸው ሳይሆን በ1845 የተገለጸው ነው በማለት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡        

4. የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ንብረቱን የሚለቅቅበት የሕግ አግባብ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ ከ2882-2285 የተደነገጉት ድንጋጌዎች እንዲሁም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2284(2) ላይ ያሉት ድንጋጌዎች ተያይዘው በአንድነት ሲታዩ የተሸጠው የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የሻጩ ኃብት ሳይሆን የሌላ ሰው ኃብት ሆኖ ከተገኘ ገዥው አንደሚነቀል ወይም አንዲለቅቅ የሚደረግ ስለመሆኑ የሚጠቅሱ ናቸው፡፡ ገዥው በህጉ ያለው መፍትሔ ሻጩን መጠየቅ ነው፡፡ የሌላ ሰው ንብረት ንብረቴ ነው ብሎ መሸጥ ከህጉ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ህገ ወጥ ነው፡፡ ህገ ወጥ ውል ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1716 መሰረት ፈራሽ ነው፡፡ ገዥውም በዚህ ምክንያት ከንብረቱ ይነቀላል ወይም ለሕጋዊ ባለመብቱ እንዲለቅቅ ይደረጋል፡፡ ሻጩ በማጭበርበር ስመ-ንብረቱ በራሱ ስም አስመዝግቦ ቢሆን እንኳ ሻጩ ትክክለኛ ባለይዞታ እስካልሆነ ድረስ ገዥው ንብረቱን ከመልቀቅ አያድነውም፡፡       

5.መደምደሚያ

የሽያጭ ውል ማለት በሻጭና በገዥ መሀከል አንድን ነገር አስመልክቶ አደኛው ወገን የተወሰነ ገንዘብ (price) ለመክፈል ሌላኛው ወገን ደግሞ ዕቃውን ከነ ባለሀብትነቱ ለማስረከብ የሚገቡት ውል ነው፡፡ ሻጭ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሶስተኛ ወገን ይዞታና ቁጥጥር ነጻ በማድረግ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ ገዥ ለሻጭ ከሚሰጠው የመነቀል ዋስትና ግዴታ የተለየ ነው፡፡ ሻጭ ንብረቱ ላይ የሰፈሩትንና በንብረቱ መዝገብ የተመዘገበ መብት የሌላቸውን ሰዎች የማይንቃቀስ ንብረት እንዲለቅቁ በማድረግ ለሻጭ የማስረከብ ግዴታ የማይንቀሳቀስ ንብረት ውል በመፈጸም ሂደት ገዥ ለሻጭ ሊያከነውነው የሚገባ የመጀመሪያ ግዴታ ነው፡፡  ሻጩ ውሉን አንደ ውሉ ቃል ከመፈጸም መዘግየቱ ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ውሉ እንዲፈጸምለት ካልጠየቀ በቀር ገዥው ውሉን በግዴታ አንዲፈጽም የማድረግ መብቱን ያጣል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የሻጩ ኃብት ሳይሆን የሌላ ሰው ኃብት ሆኖ ከተገኘ ገዥው እንደሚነቀል ወይም አንዲለቅቅ የሚደረግ ስለመሆኑ የሚጠቅሱ ናቸው፡፡ ገዥው በህጉ ያለው መፍትሔ ሻጩን መጠየቅ ነው፡፡

Related Posts

Leave Comments