By Mulugeta Belay on Friday, 19 June 2020
Category: Opinion/Critiques/Case Comment/Public Lecture

ስለቅድመ ሳንሱር

ቅድመ ሳንሱር በማንኛውም ቅርፅ በማንኛውም አካል ክልል ነው። ሰሞኑን ዎልታ ቴሌቪዥን ለማሰራጨት ያዘጋጃቸውን ፕሮግራሞች እንዳያሰራጭ የፍርድ ቤት ትእዛዝ እንደተሰጠ አድምጠናል። የመናገር ነፃነትና የሚዲያ ነፃነት የሕግ እና የአሰራር ገደቦች የትላንት ከትላንት ወዲያ የጭቆና አርእስቶች ነበሩ። ምንም አስብ፣ ምንም አቅድ መናገርና ሀሳብህን በስእል፣ በፅሁፍ፣ በሙዚቃ እና በየትኛውም ራስን የመግለፅ ጥበብ መግለጽ ተፈጥሮአዊ እና ህገመንግስታዊ መብት ነው።

በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 29 ላይ ቅድም ሳንሱር በየትኛውም መልክ ክልክል ስለመሆኑ ተደንግጓል። ሚዲያዎች የህዝብን ሀሳብ የዴሞክራሲ ሀሳቦችን ማንሸራሸሪያና የግለሰቦች የመናገር ነፃነት መድረክ በመሆናቸውም ነፃነታቸው በሕግ ተረጋግጧል።

ህገ-መንግስቱን ተከትለው የወጡ አዎጆች ማለትም እንደ መገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዎጅ ያሉ ህጎችም ሚዲያዎች ነፃ ስለመሆናቸው፤ ቅድመ ሳንሱር ስለመከልከሉ፤ መረጃ እና ትችት የማቅረብ መብታቸው በሕግ ከሚቀመጡ ገደቦች ውጭ ስለመከበራቸው ደንግገዋል።

ከመናገር በፊት መናገርን መከላከል፤ ከመፃፍ በፊት መፃፍን ከመዘገብ በፊት መዘገብን፤ ከመሳል በፊት መሳልን …መከላከል አይቻልም።

ግን ደሞ እንደፈለጉ መናገር እና መዘገብ ያለገደብ በብላሽ አልተሰጡም። ይህን ገደብ ማተላለፍ ሀላፊነት ያስከትላል። ባጭሩ እንዳሻህ ዝለል እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ ነው። በልብህ ያሰብከውን መናገር ትችላለህ ገደብህን ከሳትክ የጅህን ታገኛለህ እንደ ማለት ነው። በሚዲያዎች ላይ የሚጣል ማናቸውም ገደብ በሕግ አስቀድሞ የተደነገገና ዋና ጉዳይ ሳይሆን ልዮ ሁኔታ ወይም በስተቀር ሲሆን ሲተረጎምም በጠባቡ እና እኔብስ እኔብስ የሚሉትን የመናገር ነፃነት እና የህዝብ ጥቅምን ለማስታረቅ በሚያስችለው መጠን ብቻ የተደረገ ሊሆን ይገባል።

በተለይ ደግሞ ሚዲያንና የህትመት ስራን በተመለከተ አንድ ጉዳይ በሚዲያ ከመሰራጨቱ ወይም ለህትመት ከመብቃቱ አስቀድሞ እንዳይሰራጭ ወይም እንዳይታተም መከላከል አይቻልም።

 

ቅድመ ሳንሱር በማንኛውም ቅርፅ ክልክል ነው ማለት አንድ ነገር ከመሆኑ ቀድመህ እንዳይሆን ልትከለክለው አትችልም ማለትን ይጨምራል።

ከፍ ሲል እንደተገለፀው ሚዲያዎች ያሻቸውን ለመፈፀም ነፃ ቢሆኑም በስራቸው የጥላቻ ንግግር፣ ስም ማጥፋት፣ የጦርነት ቅስቀሳ ወይም በሕግ የተከለከለ የፍታብሄር ወይም የወንጀል ሀላፊነት የሚያስከትል ድርጊት ከፈፀሙ ይጠየቁበታል ያበላሹትን እንዲያስተካክሉ የበደሉትን እንዲክሱ ይገደዳሉ።

ለምን እንዲህ አይነት ነፃነት

አስቀድሞ መከልከል እኔ አይቸው መዝኘው ካልሆነ አይተላለፍም አይታተምም ወይም አትናገርም እንደማለት ነው። እንዲህ አይነቱ ድርጊት ደግሞ ያለአግባብ የመናገር እና የሚዲያ ነፃነትን ይገድባል፤ የፈጠራ ስራን ያቀጭጫል። ብሎም ሚዲያዎች በትችታቸውና የተሸሸገውን በማሳየት ስራዎቻቸው የሕግ ጥሰትን እና የህዝብ ችግሮችን እንዳያጋልጡ ስለሚከለክል ገደባቸውን በመንገር ከገደቡ ሲያልፉ በሕግ መጠየቅ የተሻለው መንገድ ሆኖ ተገኝቷል።

ቅድመ ሳንሱር አለመኖሩ የምርመራ ጋዜጠኝነትን አስፋፍቷል በዚህ ምክንያት አለም የአሜሪካን የጓንታናሞ ጉድ የብዙ ፖለቲከኞች እና ሀብታሞችን ጉድ የዘረገፈውን The Panama Papers የክትባት ሴራዎች የሙስና ቅሌቶችን ብሎም የሴት ህፃናትን ስቃይ ለአለም የገለጡ ስራዎች ተገኝተዎል። በዛው ልክ የግለሰቦች ማጥቂያ የፖለቲካ መሳሪያ የሆኑ ዘገባዎች የሚሊዮኖችን ሀሳብ በማሳከር ግለሰቦችን በማጥቃት የሀገራትን ስም በማጥፋት ተጠናቀዎል።

ሳንሱር የደራሲዎችን የሀሳብ በመሸሸግ ለጥበብ ልኳ ያልሆነ ልብስ በማልበስ ለዘመናት የጥበብ እና የሀሳብ ፀር ሆኖ ኖሯል። ሳንሱር ቢኖር ጥበብ ዛሬም በህገወጥ ሳንሱር አንካሳ የሆነችው ጥበብ ማንከሷ ሳያንስ ለመታወርም ባበቃት ነበር።

ለፅሁፉ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳይ ስንመጣ ፍርድ ቤቱ ገና በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ እግዱን የሰው የግለሰብ ስም ሊያጠፉ ይችላሉ ካጠፉ ደግሞ የማይተካ ጉዳት በግለሰቡ ላይ ያደርሳሉ በሚል ነው።

የግለሰቦችን ስም ማጥፋት ጥፋትም ወንጀልም ነው። ነገርግን ጥያቄ ጥፋት የሚሆነው መቼ ነው? የሚለው ነው።

ያልተላለፈ ነገር ከተከደነ ነገር ጋር መሳ ነውና ካልተከፈተ አይታወቅም። ስለዚህ ሀላፊነት የሚመጣው ከክዳኑ መከፈት ብሗላ ነው።

ቅድመ ሳንሱርበ ሕግ ክልልክ የሆነው በማናቸም ቅርፅ እና በማንኛውም የመንግሥት አካል ሲከወን ስለመሆኑ የህገመንግሥቱ አንቀፅ 29 እና ከፍሲል የተገለፀው የአዎጁ አንቀፅ 4 ያስገነዝባሉ። በአንድ በኩል የመንግሥት አካል ሲባል ፍርድ ቤቶችን ወይም ሕግ ተርጓሚውንም ይጨምራል

በሌላ በኩል ቅድመ ሳንሱር በማናቸውም ቅርፅ ተከልክሏል ማለት በፍርድ ቤት ትእዛዝም ቢሆን የሚደረግ ገደብን ይመለከታል።

ሕግን ማክበር ደግሞ በፍርድ ቤቶችም ላይ መጣሉን ሲያጠይቁ ራሱ ህገመንግስቱም ሆነ አዎጆቹ ሕግ ተርጓሚው መብቶችን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር ይጠይቃሉ።

በመሆኑም ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም በሚዲያ ነፃነት ላይ የተቀመጡ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ከሚጠየቅ በቀር አስቀድሞ ስራውን እንዳይሰራ ሊከለከል አይችልም።

አስቀድሞ መከልከል ለፍርድ ቤቶች ከተፈቀደ ዜና በተሰራ፣ ሙዚቃ በቀረበ፣ ትችት እና ውይይት በተደረገ ጊዜ ሁሉ ሁኔታው ያልተመቸውም በርግጥ ስሙ ሊጠፋ ያለው ሁሉ ፍርድ ቤትን ከማጨናነቁ በተጨማሪ የሚዳያ ነፃነት መቃብር መፈፀሚያ ስልት ሊሆን ይጀምራል።

ገና ያልተላለፉ ፕሮግራሞች በቂ ማስረጃ ያላቸሁ ይሁኑ አይሁኑ እንዲሁም ስም አጥፊ፣ አገር አጥፊ ወይም ጦርነት ጎሳሚ እንዲሁም ጥላቻ ሰባኪ መሆናቸው ሊታወቅ አይችልም።

እንዲህ መሆናቸውን ለማወቅ ብቸኛው መንገድ ስራዎቹን አስቀድሞ ማየት ወይም መመርመር ነው። ይህ ደግሞ በግልፅ እና በማያሻማ መልኩ የተከለከለውን ቅድመ ሳንሱር መከወን ነው። ፍርድ ቤቶች አንድን ስራ በመመርመር ሕግ መጣስ አለመጣሱን መመርመር ተፈጥሮአዊ ስሪታቸው ቢሆንም ገና ከመተላለፉ በፊትግን ሊሆን አይችልም።

በርግጥ ሚዲያዎች ሚዲያውን ለጥላቻ ለስም ማጥፋት ወይም ለአንድ ወገን ጥቅም ስብከት አያዎሉትም የሚል ድፍረት የለኝም።

እነሱ እንዲያ ስለሆኑ ግን የሚዲያ ነፃነትን መገደብ ፍፁም ስህተት ነው። ይልቁኑ መለማመድ ያለብን ገደባቸውን ያለፉ ሚዲያዎች ካሉ በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው። ያልቻልነው እና የሰለጠነብን ጉዳይ ቢኖር እንደውም ይህ አጥፍቶ አለመጠየቅ ይመስለኛል።

ቢሆንልን እና በወጉ ቢከወን ኖሮ የምርመራ ጋዜጠኝነት የመንግስትን፣ የተቋማትንም ሆነ የግለሰቦችን አለሌነት መቆጣጠሪ ለወደፊቱም ማንቂያ ደወሎቻችን በሆኑ ነበር።

እንዳለመታደል እውነታው በተቃራኒው ነው። ሚዲያዎች ዘመኑን የሚመስሉ አሸርጋጆች በመሆናቸው ለዚህ አልታደልንም።

 

Related Posts

Leave Comments