በተለምዶ የሕግ ባለሙያዎች በንግዱ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱት ተወዳዳሪ ኃይሎች የተጋለጡ አልነበሩም፡፡ ይህ በሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ሃገራት በአድቮኬቶችና ላቲን ኖታሪዎች እንዲሁም በኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ሃገራት በባሪስተሮች፣ ሎሊሳይቶሮች እና ኮንቬሮች መካከል ተመሳሳይ እውነታ ነበር፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ሥርዓት የሕግ ሙያ ቁጥጥር የሚተገበረው በቀጥተኛ የመንግሥት ቁጥጥርና በላቀ ሁኔታ ደግሞ በራስ አስተዳደር (self regulation) ባለሙያዎች በተቀረፁ ሕጎች በመተዳደር ነው፡፡ ይህ የሕግ ሙያ ቁጥጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ሥርዓቶች በፈጠረው የፀረ-ውድድር ተፅዕኖ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተተቸ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ ተንታኞች የሕግ አገልግሎቱ ፀባይ የተወሰነ የግል ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው ቢስማሙም በተመሳሳይ ሁኔታ ቁጥጥሩ በተለይ የራስ አስተዳደር ሕጎች (rules of Self Regulation) ውድድርን አብዝቶ በመገደብ እና ለሕጉ ሙያ ጥቅም በመቆርቆር የብዙኃኑን ሕዝብ ጥቅም ከግምት ላያስገባ ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው::
በዚህ አጭር ጽሑፍ የጥብቅና ሙያ አገልግሎትን ለመቆጣጠር ምክንያት የሆኑ ትንታኔዎችን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
ቁጥጥርን የሚመለከቱ የሕዝብ ጥቅም ንድፈ ሀሳቦች (Public interest theories of regulation)
ሰፊ የኢኮኖሚ ጥናት እንደሚያሳየው ለሕግ ሙያ አገልግሎት የሚሰጥ ነፃነት (free market for legal services) አጥጋቢ ውጤት ላያመጣ ይችላል፡፡ የተጠቃሚውን ርካታ የሚያጓድሉ ሦስት ዓይነት የገበያ ጉድለቶች አሉ፡፡ እነዚህም ያልተመጣጠነ መረጃ (Information asymmetry)፣ ውጫዊ አሉታዊ ተፅዕኖዎች (Negative Externalities) እና የአቅርቦት ዝቅተኛ መሆን (public goods under supply) ናቸው፡፡ ከገበያ ውድቀት ባሻገር ተጠቃሚነትን የማዳረስ ግቦች (distributional goals) ወይም መልካም ማሕበራዊ ግንኙነት (paternalism)፣ የውድድር ሕግ (competition Law) የመሳሰሉት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የጥብቅና ሙያ አገልግሎትን ለመቆጣጠር ምክንያቶች ናቸው፡፡
ሀ. የመረጃ አለመመጣጠን (Information asymmetry)
ምንም እንኳን ጠበቆች ስለሚሰጡት የሕግ አገልግሎት ምሉዕ የሆነ መረጃ ቢኖራቸውም ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ከማግኘታቸው በፊት ጥራቱን የሚለኩበት መንገድ ስለማይኖራቸው ምርጫቸው አብዛኛውን ጊዜ ዋጋን መሠረት ያደርጋል፡፡ ተጠቃሚዎች የሚያገኙትን አገልግሎት ጥራት መለካት ካልቻሉ ከፍተኛ ጥራት ያለውን አገልግሎት በከፍተኛ ዋጋ ለማግኘት ፈቃደኞች አይሆኑም፡፡
እ.ኤ.አ. በ2001 በኢኮኖሚክስ የሽልማት ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ ከነበሩት አንዱ ጆርጅ አኪርሎፍ እንደሚሉት ያገለገሉ መኪኖች በሚሸጡበት ገበያ ገበያው ምቹ አይደለም፤ ምክንያቱም በሻጩና በገዢው መካከል ስለመኪናው ያለው ያልተመጣጠነ መረጃ ነው፡፡ የመኪናው ሻጭ ከመኪናው ጋር አብሮ ስለነበር ስለመኪናዋ ብቃት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በተቃራኒው ገዥ ስለመኪናዋ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ይህም ሻጭ አንድ ብልጫ አለው፡፡ ገዢ የሚያውቀው ነገር ስለሌለ ለመኪና አማካኝ ዋጋ ብቻ ከፍሎ ለመግዛት ይፈልጋል፡፡ መኪናቸው ከአማካኝ ዋጋ የተሻለ እንደሚያወጣ የሚያውቁ ሻጮች ገበያውን ለመልቀቅ ይገደዳሉ፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ዋጋቸው ከአማካኝ ዋጋ በታች የሆኑ መኪኖች ብቻ ገበያው ውስጥ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሂደት ምንም ሊሠሩ የማይችሉ መኪኖች ብቻ ገበያ ውስጥ እስኪቀሩ ይቀጥላል፡፡ ባጭሩ መጥፎዎቹ መኪኖች ጥሩዎችን ከገበያ አስወጧቸው ማለት ነው፡፡
የኢኪርሎፍ ምሳሌ ሙሉ ታሪኩን አስረግጦ ላያስረዳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠው ዕቃ ሲገዛ በደንብ ሳያይ እንደማይገዛ ዕሙን ነው፡፡ ለምሳሌ ጫማ የሚገዛ ሰው ጫማውን አጥልቆ ራመድ ራመድ እያለ በመስታወትም እያየ የሻጩንም አስተያየት ከመጠየቅ አይቦዝንም፡፡ ተመሳሳይ ጫማ የገዙትን ወዳጆቹንም ሊያማክር ይችላል፡፡ ጥሩ ዕቃን ለማግኘት ይህን ያህል ጥረት የሚደረግ ከሆነ የመረጃ ችግር ያን ያህል አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፡፡ በፍለጋ የተገኘው ዕቃ ግን መለዮውን አይተን፣ ቀለሙን፣ ቅርፁን፣ ሽታን ወይም አስተሻሸግን ብቻ በሚመለከት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም የፍለጋ ሂደት የጥሩ ዕቃን ሙሉ ገጽታ ሊያሣይ ይችላል፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ ዕይታ ብቻውን ሊሸውድ ይችላል፡፡ ጥሩ ዕቃን ለምሳሌ ሹራብም ሆነ ጫማ ለብሶ በማየት መሞከር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ምግብ ቤት ምሣ ከመብላቱ በፊት ምግቡን እንዲቀምስ ይፈቀድለታል?
የመረጃን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከነዚህም ውስጥ ቁጥጥር (regulation) አንዱ ነው፡፡ መንግሥት የጥራት ደረጃዎችን ወይም ምርት ማስገቢያ መመዘኛዎችን ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ከዚህም በመነሳት መንግሥት ከምርቱ ደረጃ አንፃር አይቶ አምራቾችን ሲዘጋ ይታያል፡፡ ስለዚህ የታሸገ ውኃ የሚሸጡ ድርጅቶች የምርታቸውን ጥራት ለማሳየት የተለያየ መለኪያዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ገዢውም እነዚህን መለኪያዎች በማየት ውሃውን ይገዛል፡፡ ነገር ግን አንድ የሕግ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልግ ደንበኛ የጠበቃውን ብቃት እንዴት ማወቅ ይችላል? በሚለብሰው ልብስ? በሚያሽከረክረው የመኪና ዓይነት? በአነጋገሩ ዘይቤ? ደንበኛውን በሚያናግርበት ወቅት ስልኩ በጮኸበት ብዛት? ቢሮው በሚገኝበት ሠፈርና ህንፃ ጥራት? የተማረበት ዩንቨርሲቲ? በጥብቅና የሠራው የሥራ ልምድ? እነዚህ ሁሉ የፍለጋ መለዮዎች (search qualities) ናቸው፤ በተወሠነ መልኩም የጥራት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ውድ መኪና የሚያሽከረክር እና ምርጥ ልብሶችን የሚለብስ ሠው ሀብታም ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ሀብታም የሆነው በሰጠው ግልጋሎት ባገኘው ብዙ ገንዘብ ሊሆን ይችላል፤ ሀብቱን ወርሶ ልብስና መኪናውን ደግሞ ተውሶም ሊሆን ይችላል፡፡ ስልኩ ደጋግሞ ስለጠራ ሰውዬው እጅግ ተፈላጊ ነው ሊባል ይችላል፤ ወይም ደግሞ ለአንድ ሰው በየሁለት ደቂቃው እንዲደውልለት በክፍያ ተስማምቶም ሊሆን ይችላል፡፡ ውጪዓዊ መለዮዎች የትኛው ጠበቃ ምርጡ እንደሆነ ለመለየት አያመቹም ወይም አያስችሉም፡፡ በተደጋጋሚ በማይገዙት እና በማይዋዋሉት አገልግሎቶች ላይ ይህ ጉዳይ የምርጫ መዛባትን እንዲሁም አጠቃላይ የጥራት መዛባትን ያስከትላል፡፡
በመረጃ አለመመጣጠን ሊከሠት የሚችለው ሌላው ችግር የሞራል ጥፋት (moral hazard) ነው፡፡ በሕግ ባለሙያዎች የሚሰጠው አገልግሎት ታማኝነትን የሚጠይቅና ከባለጉዳዩ ጋር በቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ የገንዘብ ተኮር ግንኙት ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ የሞራል ጥፋት በወካይና በተወካይ ግንኙነት ላይ የተለመደና ከመረጃ እጥረት ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚመጣ ነው፡፡ ይህም አገልግሎት ሰጪው ጠበቃ (ተወካይ) ሊያሳካው ካሰበው ግብና በደንበኛው (በወካዩ) ዓላማ መካከል ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል፡፡ ደንበኛው ወይም ወካዩ የሚፈልገውን የዋጋ-ጥራት ተዛምዶ መግለጽ ስለማይችል ጠበቃው (ተወካዩ) ለሚሰጠው የሕግ ሙያ አገልግሎት ከፍተኛ ዋጋዎችን ለማስከፈል እንዲያመቸው በማሰብ አገልግሎቱ ከፍተኛ ጥራት ያለው በማስመሰል ያቀርባል (ምንም እንኳን ደንበኛው (ወካዩ) በደህና ጥራትና በመጠነኛ ዋጋ አገልግሎቱን ማግኘት የሚበጀው ቢሆንም)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደንበኛው (ወካዩ) የማይፈልገውን የአገልግሎት ዓይነት ጠበቃው (ተወካዩ) የሚያቀርብበት አደጋም ይስተዋላል፡፡ በአንዳንድ የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ላይ ይህ የመረጃ ችግር #ደጋግሞ የመግዛት$ (“Repeat purchase”) ዘዴን ሊቀንስ ይችላል፡፡ ተጠቃሚዎች የሠለጠኑ (professional) ገዥዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አገልግሎቱ በአጥጋቢ ሁኔታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን በየቤታቸው የሕግ አማካሪ ያላቸው ደንበኞች የሚሠጣቸውን የጥብቅና አገልግሎት ጥራት መለካት ቢችሉም በወቅታዊነት ጠበቃን የሚጠቀሙ ደንበኞች ላይ ይህ እውነታ ነባራዊ አይደለም፡፡
ትክክለኛ በጠበቆች የሚሰጥን የሕግ አገልግሎት ከሦስት የጥራት መመዘኛ አቅጣጫዎች ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህም፡-
ሀቀኝነት፣ ሚዛናዊነትና ታማኝነት (Integrity, Impartiality and trustworthiness)
የሕግ ጥራት:- የሚሰጠው የሕግ ምክር ጥራት እና ጉዳዮን በፍ/ቤት በሚገባ የማድረስ ብቃት (Legal quality:- quality of given advice, adequacy of legal representation in courts)
ደንበኛን ከገንዘብም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመንከባከብ ሁኔታ ወይም የደንበኛ አያያዝ (commercial quality or treatment of consumers) ናቸው፡፡
ከደንበኛ አያያዝ በስተቀር የመጀመሪያውቹ ሁለቱን መመዘኛዎች ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ የሕግ ምክር ሥራን በተመለከተ ደንበኛው ስለጠየቀው የሕግ ምክር ጠበቃው የተቻለውን ሁሉ እንዳደረገና የተሰጠውም ምክር አግባብ ስለመሆኑ አያውቅም፡፡ የደንበኛውን ጥቅም በፍ/ቤት ማስጠበቅን በተመለከተም ጠበቃው የደንበኛውን ጥቅም ከማስከበር አንፃር ሊነሱ የሚገባቸውን ሁሉንም የመከላከያ ሀሳቦችና ክርክሮችን ማንሳቱን ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጠበቆች የደንበኞቻቸውን ጉዳይ ለማጥናትና ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ እንደወሰደባቸው ወይም በተገቢውና በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸው በምን ይታወቃል? ደንበኞችስ ያገኙትን የሕግ አገልግሎት ጥራት ደረጃ በምን ይለካሉ? እነዚህ ነገሮች ካልታወቁ ተጠቃሚዎች ለጠበቃ ለመክፈል ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ያገለገለው መኪና ምሳሌ እዚህ ጋር ነው እንግዲህ የሚመጣው፡፡ ምንም ብቃት የሌላቸው ጥሩ መሣይ ግን ምንም የማይጠቅሙ ሙያውን ይመሩታል፡፡ ብቃት ያላቸውና እምነት ሊጣልባቸው የሚገቡ ጠበቆች ግን አገልግሎቱን ለቀው ይወጣሉ፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ጠበቆችን እና የሕግ አገልግሎቱን ለመቆጣጠር ደፋ ቀና የሚለው፤ ለዚህ ነው መንግሥት ወደ ጥብቅና ሙያ አገልግሎት ከመገባቱ በፊት የተለያዩ ሊታለፉ የማይገባቸው መስፈርቶችን የሚያስቀምጠው፡፡ የትምህርት ደረጃ፣ አግባብ ባለው አካል የተዘጋጀ ፈተናን ማለፍ፣ የሕግና የሥነ-ምግባር ደረጃዎች ማጤንና የመሳሰሉት፡፡ እነዚህ የሙያ ቁጥጥሮች በራስ አስተዳደርም ሆነ ቀጥተኛ በሆነ በመንግሥት ቁጥጥር በሁለቱ የሕግ ሥርዓት ተከታይ ሃገሮች ደረጃውና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ተመሳሳይ ነው፡፡ የዚህ የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ቁጥጥር ደካማ ጎን የቁጥጥር ደረጃውና ዓይነት በጣም ዝቅ ወይም በጣም ከፍ ሊል መቻሉ ነው፡፡ ከፍ ሲል በአውሮፓ ሕብረት አባል ሃገራት እንደተስተዋለው ጥቂት ጠበቆች፣ አነስተኛ የውድድር መንፈስና የተጠቃሚዎች ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት መገደድ ነው፡፡ ዝቅ ሲል ከላይ የተገለፁት ችግሮች መስተዋላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የጥብቅና ሙያ አገልግሎት የቁጥጥር መስፈርቶች በጣምም ከፍ በጣምም ዝቅ ያላለና ለጥብቅና ሙያ አገልግሎት እንደሃገሩ ተጨባጭ ሁኔታ የጠበቆችን ብቃትና ችሎታ ሊለይ የሚችል እንዲሁም ሕብረተሰቡ ከጥብቅና ሙያ አገልግሎት ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት ሊያስገኘው በሚችል አኳኋን መስፈርቶቹ መቀረጽና ተግባር ላይ መዋል አለባቸው፡፡
ለ. አሉታዊ ውጫዊ ተጽዕኖዎች (Negative externalities)
ጠበቆች ከደረጃ በታች የሆነ የጥብቅና ሙያ አገልግሎትን ሲያቀርቡ ወይም ሲሰጡ ደንበኞች ብቻ ሣይሆኑ ለጉዳዩ ሦስተኛ የሆነ ወገንም ሊጎዳ ይችላል፡፡ ለአሉታዊ ውጫዊ ተጽዕኖ ችግር የመጀመሪያው ሕጋዊ የመፍትሔና የመከላከያ ዕርምጃ በተጠያቂነት ሕግ (liability law) ይመለሳል፡፡ ለጥፋቶች ተጠያቂ የመሆን አሠራር ጥፋትን ለሚያቅዱ ግለሰቦች አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ትልቅ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ የሕግ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ እንደሚያሳየው የተጠያቂነት ሕጎች በውስን ሁኔታዎች ላይ ብቻ የጥፋት ርምጃዎችን ለማስጠንቀቅ (deterrence) ይረዳሉ፡፡ በቀጥተኛ ተጠያቂነት ሕግ ጊዜ ካሣ የሚከፈለው በደረሠው ጉዳትና በጉዳት አድራሹ መካከል ምክንያታዊ ግንኙት (causal link) ሲኖር ነው፡፡ ይህ ሕግ እንደ ማስጠንቀቂያ (deterrence) የሚያገለግለው የሚከፈለው የካሣ መጠን ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል/ተመጣጣኝ ሲሆን ነው፡፡ ነገር ግን ዳኛው የአሉታዊ ውጫዊ ተፅዕኖን መጠን በትክክለኝነት መመዘን ካልቻለ ይህ ጉዳይ ተግባራዊ አይሆንም፡፡ በቸልተኝነት ሕግ ጊዜ አጥፊው በሕግ የሚፈለገውን የጥንቃቄ ደረጃ መምረጡን ዳኛው መወሰን አለበት፡፡ በድጋሚም የካሣው መጠን በርግጥ ከደረሠው ጉዳት ጋር እኩል መሆን አለበት፡፡
ዳኛው ጥቃቅን ጥቅሞችን (Marginal benefit) እና የተጨማሪ ጥንቃቄን ዋጋ (costs of additional care) የሚለይበት በቂ መረጃ ከሌለው በቸልተኝነት ሕጉ ላይ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል፡፡ በተጨማሪም በቸልተኝነትም ይሁን በቀጥተኛ ተጠያቂነት (negligence and strict liability) ምክንያታዊ ግንኙነት በቀላሉ ላይሟላ ይችላል፡፡ በመሆኑም የተጠያቂነት ሕጎች በሕግ ባለሙያዎች ደካማ አፈፃጸም (performance) የተፈጠሩትን ውጫዊ ተፅዕኖዎች በተሟላ ሁኔታ እንዲረዳ ሊያደርግ አይችልም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የተጠያቂነት ሕግ ድክመቶች በአጠቃላይ በጥብቅና ሙያ አገልግሎት ላይ እየተስተዋሉ በመሆኑ ቁጥጥርን የሚያስገድዱ ጉዳዮች ሆነዋል፡፡ በጥብቅና ሙያ አገልግሎት ሊፈጠር የሚችለውን የጥራት ማሽቆልቆል ቁጥጥር ሊታደገው ይችላል፡፡ ከተጠያቂነት ማለትም ጉዳት ከደረሰ በኋላ ወደ ርምጃ ከሚሔደው የተጠያቂነት ሕግ በተቃራኒ ቁጥጥር በቅድሚያ የጥራት መስፈርቶችን በመቀመር ብቁ ያልሆኑ ባለሙያዎች ወደ ጥብቅና አገልግሎት እንዳይገቡ ያግዳል፡፡ የሕግ ኢኮኖሚ ትንታኔ ቁጥጥር ከተጠያቂነት ሕግ የተሻለ የሚሆንባቸውን አያሌ ምክንያቶች ያስቀምጣል፡-
አጥጋቢ የጥንቃቄ ደረጃን ለመወሰን አስፈፃሚ አካል ከዳኞች የተሻለ መረጃ ሊኖረው ስለሚችል፣
ቁጥጥር በወንጀል ተጠያቂነት ተፈፃሚ ስለሚሆን (regulation is enforced by criminal sanctions) ከካሣ ግዴታ የተሻለ የመቀጣጫ /deterrence/ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡
የደረሰው ጉዳት በግለሰቦች ላይ በብዛት የተስፋፋ ሲሆን ወይም ምክንያታዊ ግንኙት (causation) ማረጋገጥ ሳይቻል ሲቀር ተጠያቂነት ሊነሣ ወይም ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርብ አይችልም፡፡
ነገር ግን በሕግ ሙያ አገልግሎት የመረጃ እጥረት በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይም ሊከሠት ይችላል፡፡ የጥራት መስፈርቶችን የማስቀመጥ አስተዳደራዊ ወጪም በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ አጥጋቢ የጥራት መስፈርቶችን ለማስቀመጥ ሕግ አውጪው ጥራትን እንዴት እንደሚለካ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ለፍርድ ቤቶች የዝቅተኛ ኢ-ሙያዊ አሠራር (malpractice cases) ጉዳዮችን የመቆጣጣር ያህል የከበደ ይሆናል፡፡
ስለዚህም ከግብዓት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የቁጥጥር ርምጃዎች ማለትም ተገቢ የትምህርት ደረጃን መጠየቅንና በሥራ ላይ ሥልጠናን የማድረግ ርምጃዎች ከውጤት ጋር ተዛማጅነት ላላቸው የጥራት መለኪያዎች ተመራጭ ይሆናሉ፡፡
ሐ. የአቅርቦት ዝቅተኛ መሆን (under-Provision of public goods)
የማይከፍሉ ተጠቃሚዎችን ወይም ደንበኞችን አገልግሎት ሰጪው ከተጠቃሚነት ማስወጣት ባለመቻሉ ምክንያት በነፃ ገበያ ውስጥ የሕዝብ አገልግሎት አቅርቦት ከመጠን በታች የመሆን ባሕርይ አላቸው፡፡ የሕዝብ የአገልግሎት አቅርቦትን ለማረጋገጥ መንግሥት የሕዝብ አገልግሎቶችን አቅርቦት የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ሊያወጣ ይችላል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ለጠቅላላው ሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውን አዎንታዊ ውጤቶችን ስለሚያስመዘግቡ መንግሥት የጥብቅና ሙያ አገልግሎት በገንዘብ ማግኘት ለማይችሉ ዜጎች ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ጠበቆች አግባብ ያለውን የፍትሕ አመራር ግዴታዎች በመወጣት ረገድ ወሣኝ ሚናን እንዲጫወቱ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ፣ ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትና ለሃገሪቱ ሕጎች ተፈፃሚነት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መንግሥት በተለይ አቅም የሌላቸውን ወገኖች የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ በጠበቆች ላይ ሙያዊ ግዴታ በመጣልና ይህን ሙያዊ ግዴታ መወጣት አለመወጣታቸውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አፈጻፀሙን መከታተል አለበት፡፡
መ. ሌሎች የሕዝብ ጥቅም መገለጫዎች
የጥቅብና ሙያ አገልግሎትን መቆጣጠር ከላይ የተገለፁትን የገበያ ጉድለቶች (የመረጃ አለመመጣጠን፣ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እና ዝቅተኛ አቅርቦቶች) ከማስተካከል ባሻገር ሌሎች ሕዝባዊ ግቦች (Public Interest goals) አሉት፡፡
መንግሥታት ተጠቃሚነትን በማዳረስ ግቦች ወይም መልካም ማሕበራዊ ግንኙነት ግቦች ሊነሳሱ ይችላሉ፡፡ የዋጋ ቁጥጥር ወይም የዋጋ ጣራን መወሰን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የጥብቅና አገልግሎትን እንዲያገኙ እና ሕገ-መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቅላቸው ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ተጠቃሚነትን ከማዳረስ ባሻገር መንግሥት የሕግ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ሕጋዊ ልውውጥ (Legal transaction) ሲያደርጉ የሕግ እገዛን እንዲያገኙ ማስገደድን አስፈላጊ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል፡፡
ይህ ሁኔታ ግን የጥብቅና ፈቃድ አስተዳደርና አሰጣጥን አስመልክቶ በተደረገው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናትም ሆነ ተዘጋጅቶ በቀረበው ረቂቅ ሕግ ውስጥ የተባለ ነገር የለም፡፡ ጠበቆች የሚሰጡትን የሕግ አገልግሎት አስመልክቶ ከደንበኞች ጋር ሲዋዋሉ የዋጋ ቁጥጥር አልተደረገባቸውም ወይም የዋጋ ጣራ አልተቀመጠላቸውም፡፡ በተመሳሳይም የሕግ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ሕጋዊ ልውውጥ (Legal transaction) ሲያደርጉ የሕግ እገዛን እንዲያገኙ እስካሁን ባለው የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አልተገደዱም፡፡ ይህ ምናልባት በአሁን ሠዓት አሳሳቢ ሆኖ ስላልተገኘ ይሆናል፡፡
ሠ. የውድድር ሕግ (Competition Law)
የውድድር ሕግ የግል ጥቅምን ብቻ ዓላማ ያደረጉ ገደቦችን በማስወገድ ረገድ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡ በጥብቅና ሙያ አገልግሎት ዘርፍም የመንግሥት ርምጃ ከግል ወይም ከማሕበራት ርምጃ የበለጠ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ መንግሥት በተደነገጉ ሕጎችና ደንቦች ላይ የውድድር ድንጋጌዎች በማካተት በተጠቃሚው ላይ አደጋን ሊያደርሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሊያስወግድ ይችላል፡፡ በሌላ አገለላፅ ውድድርን የሚያበረታቱ ድንጋጌዎችን በሕግ ውስጥ በማካተት መንግሥት ሕብረተሰቡ ከሙያው ዘርፍ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም ማስከበር ይችላል፡፡ በተለይ በራስ አስተዳደር (Self regulation) ባለሙያዎች የሚቀረፁ ሕጎች ፀረ-ውድድርን ያበረታታሉ የሚል ከፍተኛ ትችት አለ፡፡ ይህም የጠበቆች ማህበር ወደ ጥብቅና ሙያ አገልግሎት ብቅ ብቅ የሚሉ አዳዲስ ጠበቆች ላይ ሙያው ጥራት ያለው ጠበቃ ይፈልጋል በሚል ሽፋን ጥብቅ ቁጥጥሮችን በማድረግ አብዛኛውን ጊዜ በጣም ከባድ ፈተናዎችን በመፈተን በአገልግሎቱ ውስጥ ጥቂት ጠበቆች እንዲኖሩና አገልግሎቱን ጥቂቶቹ ጠበቆች እንደፈለጉ የሚመሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
ወደ ጥብቅና ሙያ አገልግሎት ከመገባቱ በፊት የሚደረግ የሙያው ቁጥጥር በጣም መጥበቅና መላላት በሙያው አገልግሎት ጥራት ላይ አሉታዊው ተፅዕኖ ከማድረጉም በላይ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የውድድር መንፈስን ይቀንሳል፡፡ የሙያው ቁጥጥር በጣም ከፍ ሲል በአገልግሎቱ የሚሳተፉ ጠበቆች ጥቂት መሆንን ያስከትላል፡፡ ጥቂት ጠበቆች ሲኖሩ ደግሞ ውድድር ባለመኖሩ የጥብቅና ሙያ አገልግሎትን ማግኘት የሚፈልጉ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ከፍተኛ ዋጋን ይከፍላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገልግሎት ዘርፍ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሙዎች ዕድሉን ይነፈጋሉ፡፡ ይህም በሁለቱም በኩል ማለትም ሙያውን መቀላቀል የሚፈልጉ የሕግ ባለሙያዎችም ሆነ ለጠቅላላው ሕብረተሰብ ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ወደ ሙያው ከመገባቱ በፊት የሚደረግ የሙያው ቁጥጥር የላላ መሆን ብቃት የሌላቸውንና እምነት የማይጣልባቸው ወይም ለጥብቅና ሙያ አገልግሎት የማይመጥኑ የሕግ ባለሙያዎች ወደ አገልግሎት ዘርፉ በመግባት ጥራት የሌለው አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት ሕብረተሰቡ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደርጋሉ፡፡ በአገልግሎት ዘርፉም ብዛት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች በመቀላቀላቸው ለበርካታ ችግሮች አገልግሎቱን ከማጋለጥ ባሻገር በሙያው ውስጥ ከሚገኙ ብቃትና ችሎታ እንዲሁም ሥነ-ምግባር ካላቸው ጠበቆች ጋር በመዳበል አገልግሎቱን ያጥለቀልቁታል፡፡ ይህም ተጠቃሚዎች ላይ የማንነት (Identity) መዛባትን በማስከተል የአገልግሎቱን በጥራት ተደራሽነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡታል፡፡