የሂሳብ መዝገብ መያዝ ለመልካም የንግድ አሠራር ሥርዓት በጣም ጠቃሚና ከማንኛውም ግብር ከፋይ የሚጠበቅ፤ የንግድ አሠራር ሥርዓቱም የሚጠይቀው በመሆኑ በንግድ ሥራ ውስጥ ያለ አብይ ተግባር ሲሆን ለግብር አሰባሰብና አስተዳደር አመቺ እንዲሆን ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ማለትም የቁርጥ ግብር ከሚከፍሉት በስተቀር ማንኛውም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ወይም የሚከራዩ ህንፃዎች ባለቤት የሆነ ሰው የሂሳብ መዝገቦችንና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታ እንዳለበት በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 48 ላይ በግልጽ ተደንግጓል።
ይህም ማለት ግብር ከፋዮች ተጨባጭ ወደሆነ የግብርና ታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ስርዓት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ አዋጁና ይሄንኑ ለማስፈጸም የወጣው ደንብ የሂሳብ መግለጫዎችና ደጋፊ ሰነዶችን የደረጃ "ሀ " እና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች ከደረጃ "ሐ" ከተመደቡት የቁርጥ ግብር ከፋዮች የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴና ዓመታዊ ሽያጭ እንደሚኖራቸው ታሳቢ በማድረግ ተቀባይነት ያገኘውን የሂሳብ አያያዝ መርህን መሰረት በማድረግ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከብር አንድ መቶ ሺህ ያለበለጠ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች በስተቀር ዓመታዊ ሽያጫቸው ከብር አምስት መቶ ሺህ በላይ የሆኑት የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች እና ዓመታዊ ሽያጫቸው እስከ ብር አምስት መቶ ሺህ የሚደርስ የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዛግብቶችና ሰነዶችን እንዲይዙ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል፡፡ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮችም ቢሆኑ ምንም እንኳን መዝገብ የመያዝ ግዴታ ባይጣልባቸውም ለግብርና ታክስ አወሳሰን፤ የገቢያቸውን ልክ ለማወቅና ትርፍና ኪሳራቸውን ለመገንዘብ ያስችላቸው ዘንድ የሂሳብ መዝገብ ቢይዙ ተቀባይነት ያለው አሰራር ይሆናል፡፡
የግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ አያያዝ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ መርሆዎችን መሰረት ያደረገና በግብር ባለሥልጣኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አያያዝ ሆኖ:
· የደረጃ "ሀ "ግብር ከፋዮች በየዓመቱ መጨረሻ ላይ የዓመቱን የዕዳና ሀብት መግለጫ እንድሁም የትርፍና ኪሣራ መግለጫ፤ ያልተጣራውን ትርፍ የተሰላበትን የሂሳብ አሰራር ዘዴ የሚያሳይ ሰነድ፤ የሥራ ማስኬጃና የአስተዳደር ወጪን የሚያሳይ ሰነድ፤ ስለእርጅና ቅናሽ የሚያሳይ ሰነድ እና ሌሎች ደጋፊ የሆኑ ሰነዶችን በመያዝ ለ10 ዓመታት ጠብቀው የማቆየት ግዴታ ሲኖርባቸው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሰው የሚያስቀሩ ድርጅቶች /withhold Ajents/ ደግሞ የሂሳብ መዝገብና ደጋፊ ሠነድ በመያዝ ለ5 ዓመታት ጠብቀው የማቆየት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
· የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የትርፍና ኪሣራ መግለጫ በዓመቱ መጨረሻ ለግብር አስገቢው መ/ቤት በማቅረብ ገቢያቸውን በማስታወቅ ባስታወቁት ልክ ግብሩን መክፈል አለባቸው፡፡
· የደረጃ "ሐ" ግብር የሚወሰነው የቁርጥ ግብር አወሳሰን ዘዴን በስራ ላይ በማዋል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ውስጥ በተመለከተው በንግድ ስራው ዓይነት፤ በንግድ ስራው ስፋት፤ የንግዱ ሥራው በሚገኝበት ቦታ ማለትም ለስራው ያለው አመችነትን ግምት በሰጠ የቁርጥ ግብር አወሳሰን ሰንጠረዥ መሠረት በማድረግ የሚወሰን የግብር መጠን ነው፡፡
በአጠቃላይ የየዘመኑ ሂሳብ በሚሰራበትና ሰነድ በሚዘጋጅበት ወቅት ሰነዱ ትኩረት ሊያደርግባቸው ሚገባው አንዳንድ ነጥቦች ስንመለከት፡-
· ያለተጣራ ትርፍ የተሰላበት የሂሳብ አሰራር ዘዴ የሚያሳይ መሆን
· ለዕቃ ሽያጭ ምርት ተግባር የሚውሉ ዕቀዎች ዝርዝር የያዘ
· የማምረቻና ሌሎች ዕቃዎች የዕርጅና ቅናሽ ሀብቶቹን ለመስራት ወይም እነዚሁኑ ሀብቶች ለማሻሻል፤ ለማደስ መልሶ ለመገንባት የተደረገ ወጪ፤የተወገዱ እቃዎች የሽያጭ ዋጋ፤ በተፈጥሮ አደጋ ለወደሙ ንብረቶች የተገኘ ካሣ፤ ለንግድ ስራው ንብረት የተደረገ የጥገና እና የማሻሻያ ትክክለኛ ወጪ፤ የሚያሳይ መዝገብና ሰነድ
· ማንኛውንም ግብይት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የተከናወነበት ሰነድ ወይም የንግድ ዕቃን ወደ ውጭ ለመላክ ወይም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያገለግል አንድ ህጋዊ ስነ-ሥርዓት የተፈጸመበት ሰነድ….ወዘተ የያዘ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ገቢን ስለማስታወቅ
ማናቸውም ግብር ከፋይ በህግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ግብሩን አስታውቆ የመክፈል ግዴታ አለበት ፡፡
ማናቸውም ግብር ከፋይ ሲባል የሦስቱም ደረጃ ግብር ከፋይ ሲሆን የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ የማሳወቅ ግዴታን በተመለከተ ሁለት አይነት አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ይታያል አንደኛው ሀሳብ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋይ የማስታውቅ ግዴታ አለበት ሲል ሌላኛው ክፍል ግን ይህ ደረጃ የቁርጥ ግብር ከፋይ በመሆኑ ገቢው ለውጥ እስከሌለው ድረስ ማስታውቅ ግዴታ ሳይኖርበት በቁርጥ ግብሩ ልክ ግብሩን መክፈል ሆኖ የማስታወቅ ግዴታ የተጣለበት ግን የገቢ ግብሩ ደንብ ቁጥር 78/1994 አንቀጽ 22 መሠረት ሦስት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ማለትም በበጀት ዓመቱ ያገኘውን ጠቅላላ ገቢ፤ ከመደበኛ ስራው በስተቀር ከሌላ ምንጭ ያገኘውን ገቢ እና ይሠራው የነበረውን መደበኛ የንግድ ሥራውን የለወጠ ከሆነ አዲሱን የንግድ ስራ ዓይነት ለግብር አስገቢው ባለሥልጣን የማስታወቅ ግዴታ ተጥሎበታል እንጂ በገቢ ግብር አዋጁ መሰረት ለሚጣልበት ቁርጥ ግብር ግን የማስታወቅ ግዴታ ሊኖርበት አይገባም የሚል ልዩነት ነው፡፡
እዚህ ላይ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ደንቡ ‹‹በበጀት ዓመቱ ያገኘውን ጠቅላላ ገቢ›› ሲል የቁርጥ ግብሩን ገቢ ብቻ ማለቱ አለመሆኑን እና ሌላ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ሲችል ማስታወቅ እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ ግብር ከፋዩ ግብሩን በቁርጥ ግብር እንዲከፍል ውሳኔ ላይ ደርሶ የቁርጥ ግብር ከፋይ ሊስት ውስጥ ካስገባው ከግብር ከፋዩ የሚጠብቀው በተጣለበት ቁርጥ ግብር ልክ የቁርጥ ግብሩን መክፈል ሲሆን ማስታወቅ የሚገባው ከቁርጥ ግብሩ በላይ ገቢ ስለማግኘቱ ወይም ገቢው ከሚከፍለው የቁርጥ ግብር በታች ሆኖበት ኪሳራ ያጋጠመው ሲሆን እንጂ በገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ ተጠንቶ የተጣለበትን ቁርጥ ግብር መልሶ እንዲያስታውቅ ሊሆን አይገባውም፡፡ ግብር ከፋዩ በቁርጥ ግብር ከተወሰነበት በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን በራሱ ካወቀ ከቁርጥ ግብሩ በላይ ያገኘውን ገቢ እና ቁርጥ ግብሩን በመለየት ማስታወቅ ያለበት መሆኑን ለማመልከት ሆኖ በቁርጥ ግብሩ ልክ ከሆነ ግን የማስታወቅ ግዴታ የሌለበት ሊሆን ይገባል፡፡ግብር ከፋዩ የዘመኑ ገቢው ከቁርጥ ግብሩ በታች ከሆነበትም ሊያስታውቅ ይችላል ይህም ማለት የዘመኑ ገቢው ማነሱንና ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ ከተወሰነበት የቁርጥ ግብር ሊቀነስለት እንዲያስችለው በራሱ አነሳሽነት ሊያስታወቅ እንደሚገባም ነው፡፡ይህም የሚያገለግለው ለሁለት አላማ ሲሆን አንደኛው ግብር ከፋዩ የቁርጥ ግብር ተወስኖልኛል በሚል ግብሩን አሳንሶ እንዳይከፍልና የተሻለ ገቢ መኖሩን እያወቀ ገቢውን ደብnል ተብሎ ቅጣት እንዳይጣልበት ለመከላከል እና ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱም የተሻለ ገቢ ግብር ከፋዩ ማግኘቱን ካወቀ የግብር ከፋዩን ደረጃ ሊያሻሽል እንዲያስችለው ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ ግብር ከፋዩ ገቢው ከወትሮው ያነሰ መሆኑን ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ በተጨባጭ ከተረዳ ተወስኖበት የነበረውን ቁርጥ ግብር በማሻሻል ከታወቀው ገቢ ጋር የተመጣጠነ ቁርጥ ግብር ለመወሰን እንዲያስችለው እንደሆነ የፀሀፊው እምነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ግብር ከፋዩ ከተጣለበት ቁርጥ ግብር በላይ ግብር ሊያስከፍል የሚያስችል ገቢ አግኝቶ ይሄንኑ ገቢ ሳያስታውቅ ቀርቶ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ በራሱ መረጃ ደርሶበት ከቁርጥ ግብሩ በላይ ያለበትን ግብር በሚጠይቅበት ጊዜ ግብር ከፋዩን ገቢን ባለማስታወቅ አይቀጣውም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡
ለሁሉም ግብር ከፋይ ግብሩ የመሰላው በግብር ዓመቱ በተገኘው ገቢ መጠን ሲሆን የግብር ከፋዮች የግብር ዓመት የሚባለው
ሀ. ግለሰቦችን እና የሽርክና ማህበሮች የበጀት ዓመቱ ሲሆን ለነዚህ ግብር ከፋዮች የበጀት ዓመት የሚባለው የዓመቱ የበጀት ዓመት ማለት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡
ለ. ድርጅት የድርጅቱ የሂሳብ ዓመት ሲሆን የድርጅቱ የሂሳብ አመት የሚባለው ድርጅቱ የተቋቋመበትና በንግድ መዝገብ ተመዝግቦ በግብር ከፋይነት የታወቀበት ጊዜና ቀን ነው፡፡
ይህን ለመገንዘብ በደረጃ አመዳደባቸው እና እንደግብሩ አይነት ስንመለከት፡-
1. የደረጃ "ሐ" የቁርጥ ግብር ከፋይ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ ከሐምሌ 01-30 ባለው ጊዜ፡፡
2. የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ ከሐምሌ 01-ጳጉሜ 5/6
3. የደረጃ "ሀ' ግብር ከፋዮች የበጀት ዓመቱ ወይም በታክስ ባለሥልጣኑ የታወቀ የሂሣብ ዘመናቸው በተጠናቀቀ ከሐምሌ 01-ጥቅምት 30 ወይም ከጥር 01-ሚያዝያ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ገቢያቸውን እያስታወቁ ግብር መክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
4. የሠንጠረዥ "መ" ግብር ከፋዮች የመክፈያ ጊዜ ከላይ ከተገለጹት የሚለይ ሲሆን የሚለዩበት ምክንያትም የገቢ መሰረታቸውን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የዚህ ሠንጠረዥ ግብር ከፋዮች ዋና ዋና የገቢ አይነታቸው የፈጠራ መብትን በማከራየት የሚገኝ ገቢ፤ የቴክኒክ አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ ገቢ፤ ከአክስዮን ትርፍ ድርሻ የሚገኝ ገቢ፤ ንብረትን አልፎ አልፎ በማከራየት የሚገኝ ገቢ፤ ከተቀማጭ ገንዘብ ላይ ከሚከፈል ወለድ የሚገኝ ገቢ፤ የካፒታል ንብረቶችን ከማስተላለፍ የሚገኝ ገቢ ሲሆኑ ይሄንኑ ግብር የሚከፈልበትን ገቢ ለባለመብቱ የሚከፍል ሰው የሚከፍለውን ግብር ከተከፋዩ ሂሳብ ላይ ቀንሶ በማስቀረት ግብሩ ከተቀነሰበት ወር የመጨረሻ ቀን አንስቶ ባሉት 15 ቀናት ውሰጥ ለግብር ባለሥልጣኑ አስታውቆ ገቢ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
5. የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ማስታወቅን በተመለከተ የታክሱ ዓላማ ገቢ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ በተደራጀ የሒሳብ አያያዝና የደረሰኝ አጠቃቀም ላይ በተመሰረተ ለገቢ ግብሩ በመረጃ ምንጭነትም ማገልገል በመሆኑ በሂሣብ ጊዜው ማለትም ግብይቱ በተከናወነበት ወር ቀጥሎ ባለው ወር ሽያጫቸውን እያስታወቁ ታክሱን የመክፈል ወይም የሚከፍሉት ታክስ ባይኖርም እንካÿን የወሩን የሂሣብ እንቅስቃሴ በማቅረብ ማስታወቅ ግዴታ ሲኖርባቸው
6. የተርን ኦቨር ታክስ ግብር ከፋዮች ደግሞ የደረጃ "ሀ' ግብር ከፋዮች በየወሩ የደረጃ "ለ'ግብር ከፋዮች ከኢትዮጵያ በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በሚቆጠር ወይም በባለሥልጣኑ ሲፈቀድ በአውሮጳ ዘመን አቆጣጠር ከዓመቱ መጀመሪያ ቀን ጀምሮ በየሦስት ወሩ እንድሁም የደረጃ "ሐ'ግብር ከፋዮች በየዓመቱ ማስታወቂያ እያቀረቡ ባስታቁት ልክ ወዲያውኑ መክፈል፤
7. የኤክሳይዝ ታክስ በተመለከተ ወደአገር ለሚገቡ ዕቃዎች ዕቃው ከጉምሩክ ክልል ሲወጣ በአገር ውሰጥ ለሚመረት ዕቃ ከተመረተበት ወር ቀጥሎ ባለው 30ቀን ውስጥ በመጋዘን እንዲቀመጡ የተፈቀዱ ዕቃዎች ከመጋዘን እንዲወጡ በማስታወቅ ወዲያውኑ ገቢ ማድረግ፤
8. የቴምብር ቀረጥን በተመለከተ ሰነድ እንደተሰራ ወዲያወኑ ወይም በሰነዱ ለመጠቀም የፈለገው አካል ሰነዱን ከመጠቀሙ በፊት መከፈል አለበት፡፡ በማለት የበኩሌን ብያለሁ ይህንን ያያችሁ ሁሉ ያላችሁን ጨምሩበት፡፡