ለምንድነው ግን በየመንገዱ፣ በየአጥሩ፣ በየሥርቻውና በየጉራንጉሩ ሽንት መሽናት ልምድ ሆኖ የቀረው? ምናልባት የከተማ አስተዳደሮች በቂ የሆነ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በየቦታው ስላላኖሩልን ይሆናል፡፡ መንገድ ላይ ሽንት መሽናት ነውር መሆኑስ ለምን ቀረ? መንገድ ላይ ቆሞ መሽናት ወይስ መንገድ ላይ እየበሉ መሔድ? የቱ ነው ነውር? ይህ ሞራላዊ ጥያቄን ለጊዜው ትቼ ሕጉ በዚህ ዙሪያ ምን ይላል የሚለውን እንመልከት፡፡
የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 661/2002) አንቀጽ 31 ‹‹ማንኛውም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ንጽህናው የተጠበቀ በቂ የመጸዳጃ ቤት የማዘጋጀትና ለደንበኞች ክፍት የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡›› ብሎ ደንግጓል፡፡
በዚህም መሠረት፡-
- አገልግሎት በሚያገኙበት ሆቴል፣ ካፌ፣ ባር ወይም ሬስቶራንት ጽዳቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት የማግኘትና የመገልገል መብት አልዎት፡፡ በመሆኑም መንገድ ላይ ላለመሽናት አገልግሎት ባገኙበት ተቋም ተጸዳድተው መውጣት እንዳለብዎ አይዘንጉ፡፡
- በመንገድ ላይ ሆነው ሽንት የያዘዎ እንደሆን አቅራቢያዎ ወደሚገኝ የአገልግሎት ተቋም ለምሳሌ፡ ካፌ፣ ሆቴል፣ ሬስቶራንት በመግባት መጠቀም ይችላሉ፡፡
ሕጉ በእነዚህ የአገልግሎት ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን ‹‹ማንኛውም የከተማ ወይም የገጠር አስተዳደር የሕዝብ መጸዳጃ ቤት እንዲኖርና ንጽህናውም ሁልጊዜ የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡›› በማለት የከተማ እና የገጠር አስተዳደሮች ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡ ይህንን ግዴታ የከተማና የገጠር አስተዳደሮች እንዳልተወጡት ማስተዋል እንችላለን፡፡ የሌሎቹን ትተን በአዲስ አባባ ምን ያህል የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች አሉን? ይህንን የሕግ ግዴታ የከተማው አስተዳደር ያስብበት!
ሕጉ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በከተማና ገጠር አስተዳደሮች ላይ መጸዳጃ ቤት ስለማዘጋጀት የተደነገገውን ግዴታ መተላለፍ ከብር 3ሺ እስከ 5ሺ መቀጮ ይቀጣል ብሎ በአንቀጽ 53/ቸ በግልጽ ደንግጓል፡፡