ዛሬ የምናነሳው ርዕስ አያድርሰውና ከሥራ ጋር ተያይዞ ስለሚደርስ አደጋ እና ከዚህ ጋር ተያይዘው ማወቅ ስላለብን መብትና ግዴታዎች ለማውሳት ነው፡፡ መቼስ አብዛኞቻችን ይብዛም ይነስም፣ ያስደስት አያስደስትም፣ ያዝናና አያዝናናም ተቀጥረን ሠራተኛ የሚለውን ማዕረግ ይዘን እንቀሳቀሳለን፡፡ ታዲያ ከሥራ ጋር ተያይዘው የሚደርሱ አደጋዎችን የሀገራችን ሕጎች እንዴት አይተውታል እንዴትስ አስተናግደውታል የሚለውን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!
‘በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ’ ማለት ማንኛውም ሠራተኛ ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ሥራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ወይም በአካሉ ማንኛውም ክፍል ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የሚደርስ ጉዳት ማለት ነው፡፡ (የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 97ን ይመልከቱ)፡፡
ያስተውሉ ሠራተኛ ሆነው ተቀጥረው አደጋ የደረሰበዎት እንደሆነ እና አደጋው የደረሰው፡
ሀ) ሥራዎትን በማከናወን ላይ እንደሆነ፤ ወይም
ለ) ከሥራው ጋር ግኑኝነት ባለው ሁኔታ ሆኖ ከእርስዎ ውጭ በሆነ ምክንያት፤ ወይም
ሐ) ሥራዎትን ለማከናወን በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ
ከሆነ ካሳ የማግኘት ሙሉ መብት አለዎት፡፡
የሥራ ላይ አደጋ የሚባለውና የካሳ ሽፋን የሚሰጠው ከላይ ከተመለከቱት ሁኔታዎች አንዱ ሲሟላ ነው። አደጋው የደረሰበዎት ‘ሥራዎትን በማከናወን ላይ እንደሆነ’ የሚለው አገላለጽ
ሥራው የሚከናወንበት ጊዜ፤
ሥራው የሚከናወንበት ቦታ እና፤
ሥራው የሚከናወንበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ‘ሥራዎትን በማከናወን ላይ’ የሚለው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ቦታ እና ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው።
ሥራው የሚከናወንበት ጊዜ
ሥራው የሚከናወንበት ጊዜ የሚለው በመደበኛው ሁኔታ ሥራ የሚሠራባቸውን ከ2፡30 — 6፡30 እና ከ 7፡30 —11፡30 እና በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ከ 2—30 6፡00 እና ከ 8፡00—11፡00 እንዲሁም ቅዳሜን ግማሽ ቀን የሚሸፍን ነው። ከዚህ ውጭ ያሉት ሰዓታት ከካሳው ሽፋን ውጭ ይሆናሉ፡፡
ነገር ግን ከሥራው አካባቢ ጠቅላላ ሁኔታ፣ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ እና ሥራው ከሚጠይቀው ወይም በልማድ ከሚከናወንበት ሁኔታ አንፃር ወይም ለሥራው ተቀዳሚ ወይም ተከታይ የሆኑ (incidental) ተግባሮችን ሲፈጽም በነበረበት ጊዜ አንድ ሠራተኛ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ አደጋው ሥራው ከሚሠራበት ሰዓት ውጪም ቢሆን ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሳባል። ለምሳሌ እርሶዎ ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ውጪ ነገር ግን የአሠሪዎን ትዕዛዝ በመፈፀም ላይ ባሉበት ጊዜ አደጋ ቢደርስበዎት፣ በእረፍት ጊዜ ምሳ በመብላት ላይ እያሉ አደጋ ቢደርስብዎት በሥራ ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል ማለት ነው።
በመጀመሪያው ነጥብ የአሠሪውን ጥቅም ለማስፈፀም ሲሉ በዚያ ቦታ የተገኙ መሆኑ ብቻ የሥራውን የጊዜ አድማስ ያሰፋዋል በኋለኛውም ቢሆን ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ ስንነሳ አንድ ሰው ሳይበላ ሥራውን ለመሥራት ይቸገራል ቢሠራም እንኳን ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም ምሳ በሚበላበት፣ ሻይ በሚጠጣበት ጊዜ አደጋ ቢደርስብዎት፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሥራዎትን በአዲስ ጉልበት መጀመር አሠሪውን የሚጠቅመው በመሆኑ በሥራ ጊዜ ላይ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሰባል። ለአንድ አፍታ እረፍት በመውሰድ ላይ እያሉም ጉዳቱ ቢደርስብዎት በተመሳሳይ ሁኔታ በሥራው ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ከካሳ ሽፋን ውጭ ማድረግ የመደበኛ ሕይወት አኗኗር ትርጉምን ማሳጣት ይሆናል።
ሥራ የሚከናወንበት ቦታ
አንድ ሥራ የሚሠራው ሥራውን በሚያሠራው ድርጅት ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ እያሉ አደጋ ቢደርስብዎት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሥራ የሚሠራው ግን ድርጅቱ ያለበት ቦታ ላይ ብቻ አይደለም፤ የሥራው ባሕርይ ሠራተኛው ከመደበኛው የሥራ ቦታ ላይ ተነጥሎ ወደሌላ ቦታ እንዲሔድ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ አንድ የኤሌትሪክ ወይም የቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኛ የመስመር ላይ ሥራዎችን ለመሥራት ከድርጅቱ ውጭ መገኘት ሊኖርበት ይችላል ለእርሱ የሥራ ቦታው ሥራው የእርሱን መገኘት የሚጠይቅበት ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ አደጋ ቢደረስበት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ ይሆናል።
ሥራው የሚከናወንበት ሁኔታ
አደጋው ሥራዎትን ሲሠሩ የተከሰተ መሆን አለበት። አንድ ሠራተኛ ሥራውን ሲሠራ የደረሰ አደጋ ነው የሚባለው በሥራ ዝርዝር መግለጫው ሊሠራ የሚገባው ሥራ ብቻ ሳይሆን የሥራው ባሕርይ የነገሮች አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ሥራውን ተከትለው በሚመጡ አጋጣሚዎች ምክንያት፤ ከሥራ ዝርዝሩ ውጭ ያለን ሥራ እንዲሠራ ቢሆን ወይም ሥራውን ተቋርጦ ቢሆን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስ ሥራውን በመሥራት ላይ የተከሰተ አደጋ ይሆናል።
ለምሳሌ አድካሚ ከሆነ ሥራ ለአንድ አፍታ አረፍ እንዳሉ አደጋ ቢደርስብዎት፤ ውኃ ለመጠጣት ድርጅቱ ውስጥ ወዳለ ወይም የሥራ ቦታ ላይ ወዳለ ሻይ ቤት ቢሔዱ፣ በምሳ የእረፍት ጊዜዎት ውስጥ እያሉ አደጋ ቢደርስብዎት ሥራውትን እየሠሩ የተከሰተ አደጋ ይሆናል። አንድ ሠራተኛ ሥራውን በአዲስ መንፈስ እና ጉልበት ለመቀጠል አረፍ ማለቱ፣ ምሳ መብላቱ ወይም የሥራ ባልደረባውን መርዳቱ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ አሠሪውን የሚጠቅም ነው። የሚጠቅም ባይሆን እንኳን ከሥራው ጠቅላላ ባሕርይም ሆነ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ሁኔታ አንፃር ሥራው ለአንድ አፍታ የመቋረጡ አጋጣሚ ሥራው ሲሠራ የደረሰ አደጋ አይደለም አያሰኘውም። ረዘም ላለ ጊዜ ሥራው ተቋርጦ ቢሆን ለምሳሌ የሥራው ሰዓት አብቅቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ተነስቶ ከድርጅቱ ውስጥ ወይም ከሥራው ቦታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስም ሥራውን ሲሠራ የተከሰተ አደጋ ነው መባሉን አያስቀረውም።
በአጠቃላይ አንድ ሠራተኛ ሥራውን ሲሠራ የተከሰተ አደጋ ነው የሚባለው ሠራተኛው ሥራውን በተግባር እያከናወነ መሆኑን፣ በተግባር እያከናወነ ባይሆን እንኳን ሥራውን ከፍ ሲል በተገለፁት ምክንያቶች ለጊዜው ሥራውን አቋርጦ ባለበት ጊዜ፣ የሥራ ባልደረባውን በመርዳት ላይ የአሠሪውን ትዕዛዝ በመፈጸም ላይ ሥራውን አቁሞትም ቢሆን ወደ ቤቱ ለመሄድ ነገር ግን በሥራ ቦታ ወይም በድርጅቱ ውስጥ እንዳለ አደጋ ሲደርስበት ነው።