1. የቃብድ ክፍያ ማለት ምን ማለት ነው?
የቃብድ ክፍያ ማለት ተዋዋይ ወገኑ በውሉ ለመገደድ ወይም ውሉን እስከመጨረሻው ተከታትሎ ለመጨረስ ያለውን ፍላጎት ለማሳየት ሲል በመያዣነት ለሌላኛው ወገን የሚሰጠው ክፍያ ነው:: እንዲህ ዓይነቱ ክፍያ የሚፈጸምበት ዓላማም ተደራዳሪው ወገን ውሉን አስመልክቶ ከልቡ መሆኑን ወይም በውሉ ለመገደድ ያለውን ፍላጎት የሚገልጽበት ስልት ነው:: የሚከፈለውም የክፍያ መጠን እንደየ አከባቢው ሁኔታ ወይም እንደስራው ዓይነት እና ስምምነት የሚለያይ ሲሆን በአማራጭም /earnest/ a Good-faith deposit በመባል በሌላ ሃገር ይጠራል:: እንዲህ ዓይነቱ የክፍያ ሥርዓት ከድሮ ጀምሮ ያሉ ስለመሆናቸው የተለያዩ ጹፎች ያመለክታሉ:: በእኛም ሃገር ቢሆን በባህልም ህብረተሰቡ ሲገለገልበት የነበረ ስለመሆኑ ይታወቃል:: የፍትሐ ነግስት ሕግም ይህንኑ አስመልክቶ የሚደነግጋቸው አንቀጾች ነበሩት::
2. የቃብድ ክፍያ እና ቅድመ ክፍያ /advance payment/ ልዩነት ምንድነው?
የቃብድ ክፍያ እና ቅድመ ክፍያ /advance payment/ ልዩነት አስመልክቶ በፍ/ብሔር ሕግ ቁጥር {tip ፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1884 (የውሉ አፈጻጸም)::ቃብድ የተቀበለው ወገን ሌላ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር መመለስ ወይም ውሉ ሲፈጸም ከሚገባው ገንዘበ ላይ መታሰብ አለበት}1884{/tip} መሠረት ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ቃብድ ተቀባይ ውሉ ከተፈፀመ በኋላ የቀብዱን ገንዘብ መመለስ ወይም ከጠቅላላ ክፍያው መቀነስ ያለበት መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ ውል ከተፈፀመ በኋላ ቃብድ እንደ ቅድሚያ ክፍያ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡
አንድ ክፍያ ቃብድ ከሆነ ከፋይ ውሉ ቀሪ ቢሆን የሚያስመልሰው የቀብዱን እጥፍ ሲሆን አንድ ክፍያ ቅድመ ክፋያ ከሆነ ግን ከፋይ አካል ገንዘቡን የሚያስመልሰው በፍ/ብ/ወ/ሕጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት መጀመሪያ ውሉን በፍ/ቤት አስርዞ በዛው ካሣ እና የወጣውን ወጪ ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር የምንመለከተው ነገር ቃብድ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳት መኖሩን ሳያመለክት ውሉ ሲፈርስ ውል ካፈረሰው ሰው ገንዘቡን በእጥፍ መቀበል ይችላል ሆኖም የተከፈለው ገንዘብ ቅድመ ክፍያ በሚሆንበት ወቅት ከፋይ የሚቀበለው ገንዘብ የከፈለውን ያክል ብቻ ሲሆን ተጨማሪ ክፍያዎችን ለመቀበል ጉዳት መኖሩን ማመልከት ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ውሉን ያፈረሰው ገንዘብ ከፋይ በሚሆንበት ጊዜ ቃብድ ከሆነ የከፈለውን ቃብድ በመተው ውሉን ሲሰርዝ ቃብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቃብድ እንዲመልስ አይገደድም ሆኖም በቅድመ ክፍያ ወቅት ይህ ተፈፃሚ አይሆንም ስለዚህም ጉዳት ወይም ለዚሁ ውል ብሎ ያወጣቸው ወጪዎች ካሌሉ በስተቀር እንዲመልስ ይገደዳል፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛውን ጊዜ ቃብድ ሰጪ አካል ውል ሲያፈርስ ገንዘቡን ማስመለስ ሲፈልግ የሰጠሁት ቅድመ ክፍያ እንጂ ቃብድ አይደለም የሚሉት የሁለቱን የክፍያ አይነት ጥቅም በምንመለከትበት ወቅት ቃብድ የፍርድ ቤት እንግልትና ወጪ የሚቀንስ እና በአብዛኛው በእርግጠኝነት የሚገኝ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ የሚከፈለው በውሉ ለመገደድ ያለን ፍለጐት ለመግለፅ ሳይሆን ወደ ፊት የሚመጣውን የእዳ መጠን ለመቀነስ ታስቦ የሚከፈል ክፍያ ነው፡፡ ቃብድ ግን በውሉ ለመታሰር እና ውል ስለመኖሩም ለማስረዳት በማሰብ የሚደረግ የውል አይነት ነው፡፡
3. የቃብድ ክፍያ ውጤት ምንድነው?
የአሁኑ የፍትሐብሔር ሕግም ከአንቀጽ 1883 እስከ 1885 ድረስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ይደነግጋል:: አንቀጽ 1883 የአንዱ ወገን ለአንዱ ወገን ቃብድ መስጠት ውል መደረጉን ያረጋግጣል ይላል:: ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ውል በጽሁፍ ሊደረጉ የሚገባቸውን ውሎችን በጽሑፍ ሳይደረጉ ቀርተው ቃብድ በመሰጠቱ ብቻ ውል መደረጉን ያረጋግጣል ማለት አይደለም:: በፍ/ብ/ሕ/ ቁጥር 1885 መሰረት ደግሞ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ቃብድ የሰጠው ወገን የሰጠውን ቃብድ በመልቀቅ ውለታውን በራሱ ፈቃድ ለማፍረስ የሚችል ሲሆን እንዲሁም ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ቃብድ የተቀበለው ወገን የተቀበለውን ቃብድ አጠፌታ በመክፈል ውለታውን ለማፍረስ ይችላል ይላል:: ይህም በሚታይበት ጊዜ ቃብድ ሰጪ ቃብድ ባይሰጥ ኖሮ ያገኝ የነበረውን መብት ማለትም በፍ/ቤት ውሉ እንዲፈጸም የማስገደድ መብትን ገንዘቡ በእጥፍ እስከተመለሰ ድረስ ሊጠቀሙበት የማይችል በመሆኑ የውልን አስገዳጅነት ሁኔታ ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡