- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 5126
የኮ/መ/ቁ 173282 - ወ/ሮ ሙሉእመቤት ፀጋዬ (ሞግዚት) እና የምነዉሸዋ ኢንተርቴመንት ባለቤት አቶ ሸዋቀና በንቲ ኢታና
የኮ/መ/ቁ 173282
ሚያዚያ 24 ቀን 2011 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- ወ/ሮ ሙሉእመቤት ፀጋዬ
የህጻን ቦንቱ ናንሲ ሚካያ ተሾመ ሞግዚት
ተከሳሽ፡- የምነዉሸዋ ኢንተርቴመንት ባለቤት አቶ ሸዋቀና በንቲ ኢታና
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ/ም አሻሽለዉ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ህጻን ቦንቱ ናንሲ ሚካያ የወ/ሪት ሚካያ ኃይሉ ወራሽ መሆኗን ከሳሽ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ጻጋዬ የህጻን ቦንቱ ናንሲ ሞግዚት መሆኗን ይህም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 1644/06 በቀን 26/6/06 ዓ/ም የተረጋገጠ መሆኑን ተከሳሽ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ ውል የአርቲስት ሚካያ ባኃይሉን ጊዜ ቢነጉድም የሚለዉን የሙዚቃ ስራ ከሀገር ዉጪ የሙዚቃ ስራዉን በሲዲ ለማሰራጨት መብቱን ከከሳሽ በብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የገዛ መሆኑን ለዚህም ክፍያ ይሆን ዘንድ ቁጥሩ ኤቢዋይ 5935402 የሆነ ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የያዘ ቼክ የሰጧቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ በቼኩ ክፍያ እንዳይፈጸም ተከሳሽ ለባንኩ ትዕዛዝ በመስጠቱ በቼኩ ላይ የተመለከተዉ ገንዘብ ሳይከፈላቸዉ የቀረ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ብር 200,000.00(ሁለት መቶ ሺህ) ከነ ህጋዊ ወለዱ እንዲከፈላቸዉ እንዲወስንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ እንደ ክስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡
ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ለተከሳሽ እንዲደርስ ተደርጎ ተከሳሽ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ በቃለ መሕላ በተደገፈ አቤቱታ የቀረበባቸዉን ክስ ለመከላከል የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ የቀረበዉን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኋላ ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ በከሳሽ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ አቅርቧል፡፡ ይዘቱም ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተፈረመዉ ውል ላይ የውል ተቀባይ የሆነዉ አቶ ጌዲዮን አማረ የተከሳሽ ድርጅት የአይቲ ባለሙያ እንጂ ስራ አስኪያጅ ያለመሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማራ ከተከሳሽ የተሰጣቸዉ ምንም አይነት ውክልና የሌላቸዉ መሆኑን፤ ተከሳሽን ወክለዉም ምንም አይነት ውል መፈጸም የማይችሉ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማራ ለአነስተኛ ስራዎች ለዋስትና የተቀመጠ ቼክን ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን፤ ተከሳሽ ዉሉ ላይ በተመለከተዉ መልኩ የከሳሽን ካሴት በውጭ ሀገር ያላሰራጨ፣ ያላሳየ እና ለሽያጭ ያላቀረበና ጥቅም ያላገኘ መሆኑን፤ ከሳሽ የሙዚቃ ስራዉ ዉጭ ሀገር ሳይሰራጭ ቀድመዉ በሀገር ዉስጥ በማሰራጨታቸዉ ስራዉ በዉጭ ሀገር ያልተሰራጨ መሆኑን፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ የድርጅቱ ተወካይ ፈርመዉ ባስቀመጡበት ሁኔታ ኦቶ ጌዲዮን አማረ ያለ አግባብ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን ቼኩም ለዋስትና የተሰጠ መሆኑን ገልጾ ተከሳሽ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸዉ ጠይቋል፡፡
ተከሳሽ አንደ መከላከያ መልስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰዉ ምስክሮች ቆጥሯል፡፡
ተከሳሽ ካቀረበዉ የመከላከያ መልስ በተጨማሪ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱም በተከሳሽ ከሳሽ ስም እና በከሳሽ ተከሳሽ ስም ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገ ውል መኖሩን የተከሳሽ ከሳሽ የተረዱ መሆኑን ይሁን እንጂ በተከሳሽ ከሳሽ ስም በውሉ ላይ የፈረሙት ግለሰብ የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያ እንጂ ስራ አስኪያጅ አለመሆናቸዉን፤ የተሰጣቸዉ ውክልናም የሌለ መሆኑን፤ የተከሳሽ ከሳሽ በውሉ ላይ የተጠቀሰዉን ካሴት በውጭ ሀገር ያላሰራጨ፤ ያላሳየ እና ጥቅም ያላገኘ መሆኑን ገልጸዉ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተከሳሽ ከሳሽ ስም እና በከሳሽ ተከሳሽ ስም የተፈጸመዉ ውል እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸዉ ጠይቋል ፡፡
እንድ ክስ አቀራረቡ ያስዱልኛል ያሏቸዉንም የሰዉ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡
የተከሳሽ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ለከሳሽ ተከሳሽ ደርሶ የከሳሽ ተከሳሽ ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም የተከሳሽ ከሳሽ እንዲፈረስ የጠየቁት ውል የተፈረመዉ በተከሳሽ ከሳሽ ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ እና ተወካይ መሆኑን፤ ዉሉም የድርጅቱ አርማ ባረፈበት ወረቀት እና ማህተም የተረጋገጠ እና በድርጅቱ ዉስጥ የተፈረመ በመሆኑ የተከሳሽ ከሳሽ ውሉን አላቀዉም በማለት ያቀረቡት ክርክር ሀሰት መሆኑን፤ ይህን ክስም የተከሳሽ ከሳሽ ያቀረቡት የሙዚቃ ስራዉን ኦንላይን ላይ ጭነዉ ገቢ ማግኝት ከጀመሩ በኃላ መሆኑን፤ ይህም የተከሳሽ ከሳሽ ቅን ልቦና የሌለዉ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፤ የተከሳሽ ከሳሽ ውሉ ከመፈረሙ በፊት ድርድር ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን፤ ዉሉ ሲፈረምም ሙሉ ፈቃዳቸዉን ሰጥተዉ የተፈረመ መሆኑን፤ ዉሉ ከተፈረመ በኃላም ከከሳሽ ጋር ስለ ዉሉ መልካም አፈጻጸም ሲነጋገሩ የነበረ መሆኑን፤ የከሳሽ ተከሳሽ ዉሉን የፈጸሙት በቅን ልቦና መሆኑን፤ የተከሳሽ ከሳሽ ዉሉን በውጭ ሀገር አለማስራጨቱ ዉሉ እንዳይጸና ሊያደርግ የሚችል አለመሆኑን ገልጸዉ የተከሳሽ ከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ተከሳሽ የአርቲስት ሚኪያ በሀይሉን የሙዚቃ ስራ በውጭ ሀገር ለማሰራጨት በብር 200,000 የገዛ መሆኑን፤ ለዚህም ክፍያ ይሆን ዘንድ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን፤ ይህንም ቼክ ለክፍያ ባቀረቡ ጊዜ ሊከፈላቸዉ ያልቻለ መሆኑን፤ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገዉ ውል ሁለት ዘርፍ ያለዉ መሆኑን አንዱ የወጭ ሀገር ስርጭትን የሚመለከተ ሲሆን ሌላዉ ደግሞ የኦንላይን ስርጭትን የሚመለከት መሆኑን፤ በዚህ መዝገብ ክስ ያቀረቡት የውጭ ሀገር ካሴት ስርጭትን በተመለከተ መሆኑን የኦንላይን ስርጭቱን በተመለከተ ያልበሰለ በመሆኑ ክስ ያላቀረቡ መሆኑን፤ ውክልና በዝምታ ወይም በግልጽ ሊሰጥ ይችላል በመሆኑም ተከሳሽ ዉሉን የፈረሙት አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና የላቸዉም በማለት ያቀረበዉ ክርክር የህግ መሰረት የሌለዉ መሆኑን፤ ውክልና በግድ በጽሁፍ መሰጠት የሌለበት መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን ከሌሎች አርቲስቶች ጋርም ድርጅቱን ማህተም ተጠቅሞ ውል ሲፈጸም የነበረ መሆኑን፤ ተከሳሽ ክፍያዉን ለመፈጸም የሚገደደዉ ጥቅም በማግኘቱ ብቻ አለመሆኑን፤ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ ላይ የወንጅል ክስ ማቅረበባቸዉ የቀረበባቸዉን ክስ ለመከላከል የማያበቃ መሆኑን፤ ቼኩን የፈረመዉ ሁለት ሰዉ መሆኑን አንደኛዉ ፈራሚ አቶ ጌዲዮን አማረ መሆኑን፤ ማህተሙ የድርጅቱ መሆኑን፤ ተከሳሽ ያልካደ መሆኑን የሀገር ዉስጥ ስርጭቱን ከሳሽ በፈለገዉ መልኩ የማሰራጨት መብት ያለዉ መሆኑን፤ ይህን አስመልክቶም በውሉ ላይ የተቀመጠ ገደብ የሌለ መሆኑን ገልጸዉ ያቀረቡት ክስ እና የከሳሽ ተከሳሽነት መልስ አጠናክረዉ የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር ለአቶ ጌዲዮን አማረ በውልና ማስረጃም ሆነ በድርጅቱ የፕሮቶኮል ደብዳቤ የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸመዉን ውልም በዝምታ ያልተቀበሉ መሆኑን፤ ውል እንዲፈጽሙም የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የድርጅቱን ሄደር እና ማህትም አለ አግባብ በመጠቀሙ የወንጅል ክስ ያቀረቡበት መሆኑን፤ ቼኩም ተቀምጦ የነበረዉ ለከሳሽ ክፍያ አለመሆኑን፤ የሙዚቃ ስራዉንም ያልገዙ መሆኑን፤ ያገኙት ጥቅም የሌለ መሆኑን፤ በተጨማሪ ማስረጃነት የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስረዱት ዩቲዩብን በተመለከተ እንጂ የካሴት ስርጭትን የሚመለከቱ አለመሆናቸዉን በመግልጽ ያቀረቡትን የመከላከያ መልስ እና የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በማጠናክር ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት በተለየዉ ጭብጭ ላይ የግራ ቀኙን ምስክር ሰምቷል፡፡ በዚህም መሰረት በከሳሽ በኩል የቀረቡትም ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ተከሳሽ ጊዜዉ ቢነጉድም የሚለዉን በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የሙዚቃ ስራ ከ1ኛ እና ከ3ኛ የከሳሽ ምስክሮች ጋር በመሆን ሰምቶት የወደደዉ በመሆኑ የውጭ ሀገር ስርጭቱን ለመግዛት ፈቃደኛ የነበረ መሆኑን ሀገር ዉስጥም አቶ ጌዲዮን አማረ የተባለ ወኪል ያለዉ በመሆኑ ዋጋዉን በተመለከተ ከእሱ ጋር ጨርሱ ያለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ በተከሳሽ ድርጅተ ዉስጥ የሚሰራ መሆኑን ስራዉ በሲዲ ሊታተም ሲልም የከሳሽ ቤተሰብ የሆነዉ 1ኛ ምስክር የሚኪያ በሀይሉን ፎቶ ግራፍ ለዲዛይን በተከሳሽ ጥያቄ መሰረት ለተከሳሽ የላኩ መሆኑን፤ የሙዚቃ ስራዉ ውል በተከሳሽ ቢሮ ዉስጥ የተፈጸመ መሆኑን፤ ተከሳሽ የሙዚቃ ስራዉ በቅርብ ጊዜ የሚወጣ መሆኑን በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ ሲያስተዋውቁ የነበረ መሆኑን፤ ለክፍያ የተሰጠዉ ቼክ የታገደ በመሆኑ ተከሳሽ ሲደወልላቸዉ ድርጅቱ ችግር ዉስጥ ነዉ ትንሽ ታገሱ ይከፈላችኋል ሲሉ የነበረ መሆኑን፤ በወቅቱ ስለ አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና ያነሱት ነገር አለመኖሩን፤ ተከሳሽ ሀገር ዉስጥ በመጡ ጊዜም የከሳሽ ቤተሰብ ከሆነዉ ከ1ኛ ምስክር ድርጅት ቢሮ ዉስጥ ተገናኝተዉ የአንድ ወር ጊዜ ስጡኝ እከፍላለዉ ያሉ መሆኑን፤ በዚህ ወቅትም አቶ ጌዲዮን አማረ ቢሮ ዉስጥ ሲገባ እና ሲወጣ የነበረ መሆኑን፤ ከአንድ ወር ተከሳሽ ክፍያዉን ሳይከፍሉ ቀርተዉ ሲጠየቁ እኔ ለጌዲዮን ሰጥቻለሁ ከፈለጉ ከጌዲዮን ይጠይቁ ያሉ መሆኑን፤ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ክፍያ አስመልከቶ ከ1ኛ ምስክር ጋር የኢሜል ልውውጥ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ፤ ዉሉን የፈረሙት አቶ ጌዲዮን አማረ የተባሉትም የከሳሽ ምስክር ዉሉን የፈረሙት ከተከሳሽ ጋር ተነጋገረዉ መሆኑን፤ ስራዉም የመጣዉ በተከሳሽ በኩል መሆኑን፤ በዚህ መልኩም ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር ውል ሲፈጽሙ የነበረ መሆኑን፤ ቼኩም ለከሳሽ የተሰጠዉ ለክፍያ መሆኑን፤ ይህንም የተከሳሽ ወኪል የሚያውቁ መሆኑን፤ ቼኩንም ቆርጠዉ የሰጡት የተከሳሽ ወኪል አቶ አሸናፊ መሆናቸዉን አቶ አሸናፊ እንዲህ አይነት ስራ ሰርተዉ የማያውቁ መሆኑን፤ የሚገናኙትም በቼክ ጉዳይ መሆኑን ከያሬድ ነጉ እና ከሳሚ ዳን ጋርም የተፈጸመዉን ውል የፈረሙት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ በተከሳሽ የተሰጣቸዉ የጹሁፍ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ በመተዳደሪያ ደንቡን ላይ ምክትል ስራ አስኪያጅ ተብለዉ ያልተሰየሙ መሆኑን ከተከሳሽ ጋር የተጋጩት ከድርጅቱ ከሚገኘዉ ጥቅም አካፈለኝ በሚል መሆኑን ጸቡም የተፈጠረዉ ውሉ ከተፈጸመ ከስድስት ወር በኃላ መሆኑን ገልጸዉ መስክረዋል፡፡
በተከሳሽ በኩል የቀረቡት 1ኛ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል የተከሳሽ ድርጅት ስራ አስኪያጅነት በውክልና የተሰጣቸዉ መሆኑን፤ በክፍያ ጉዳይ ላይ ከባለሙያዎች ጋር የሚነጋገሩት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ በክፍያ የሚሰሩትን ስራዎች ውል የሚዋዋሉት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የሚዋዋሉት ክፍያ የማይፈጸምባቸዉን የነጻ ውሎች መሆናቸዉን፤ አቶ ጌዲዮን ከሙያ ስራቸዉ ውጭ ሌላ ሃላፊነት የሌላቸዉ መሆኑን ፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ ለአነስተኛ ወጪዎች በሚል ፈርመዉ አስቀምጠዉ የሄዱ መሆኑን፤ በቼኩ ላይ የሰፈረዉም ጽሑፍ የእርሳቸዉ አለመሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የተባሉት የከሳሽ ምስክር እና ተከሳሽ የተጣሉት በዚህ ውል መሆኑን፤ ተከሳሽ ድርጅት የሚሰራዉ የኦንላይን ሽያጭ እና ኮንሰርት መሆኑን፤ የውጭ ሀገር ስርጭት የማይሰራ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ በተከሳሽ የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ የከሳሽ ስራ በሀገር ዉስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያላሰራጩ መሆኑን፤ ከሳሽ አዲስ አበባ ዉስጥ በሌላ ድርጅት ካሴቱን ያሰራጩ መሆኑን፤ ከሌሎች አርቲስቶችም ጋር ውል የፈጸሙት እሳቸዉ መሆናቸዉን፤ ከያሬድ ነጉ እና ሳሚ ዳን ጋር የተደረገዉን ውል እርሳቸዉ ያልፈጸሙ መሆኑን ገልጸዉ ሲመሰክሩ 2ኛ የተከሳሽ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል 1ኛ የተከሳሽ ምስክር አቶ ጌዲዮን አማረ የአይቲ ባለሙያ መሆኑን የነገራቸዉ መሆኑን፤ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል በተፈጠረዉ አለመግባባት ሽምግልና ተቀምጠዉ የነበረ መሆኑን፤ ሽምግልናዉም የተደረገዉ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን የዩቲዩብ አካዉንቴን ሃክ አድርጎብኛል አስመልሱልኝ በማለታቸዉ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አካዉንቱን ሃክ ማድረጋቸዉን አምነዉ በሽምግልናዉ ወቅት ገንዘብ ያንሰኛል ይጨመርልኝ ሲሉ የነበረ መሆኑን ገልጸዉ የምስክርነት ቃላቸዉን ሰጥቷል፡፡
የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ እና በአቶ ጌድዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግንኙነት አለ የለም? የሚለውን እና ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በከሳሽ እና በተከሳሽ መከካል የተደረገዉ ውል ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት በመያዝ እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡
የመጀመሪያዉን ጭብጥ በተመለከተ ተከሳሽ የሚከራከረዉ ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነዉ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገዉ ውል አያስገድደኝም:: አቶ ጌዲዮን ውክልና የለዉም፤ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅም አይደለም፡፡ በከሳሽና ተከሳሽ መካከል የውል ግኑኘነት ስለሌለ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ልከፍል አይገባም በማለት ሲሆን ተከሳሽ ለአቶ ጌዲዮን አማረ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት ቀርበዉ የሰጡት ውክልና የሌለ መሆኑን፤ የተከሳሽ ምስክር አስረድቷል፡፡ ከዚህም በላይ ይህ ፍሬ ነገርም በከሳሽ የተካደ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የወካይ ተወካይ ግኑኝነት በጽሑፍ ከተሰጠ ውክልና ብቻ የማይመንጭ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 2180 መረዳት ይቻላል፡፡ አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸሙት ውል የግድ በጽሁፍ መደረግ ያለበት የውል ስምምነት አይነት አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰዉ ድንጋጌ መሰረት በጹሑፍ የተሰጠ ውክልና መኖር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይልቁንም ተከሳሽ ዉሉን በተመለከተ ከጌዲዮን አማረ ጋር ጨርሱ፤ ሀገር ዉስጥ ወኪሌ አቶ ጌዲዮን አማረ ናቸዉ ማለታቸዉ ሲታይ፤ ከከሳሽ 1ኛ ምስክር ጋር ባደረጉት ንግግር በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ እከፍላለዉ ትንሽ ታገሱኝ ማለታቸዉ፤ ከከሳሽ 1ኛ ምስክር ጋር ያደረጉት የኢሜል ልዉዉጥ ተከሳሽ ውሉን የሚያዉቁት መሆኑን መረዳት የሚስችል በመሆኑ፤ ከሌሎች አርቲስቶች ጋርም ድርጅቱን ወክሎ ውል የሚፈጽመዉ አቶ ጌዲዮን አማረ መሆኑ የተመሰከረ ከመሆኑም በላይ ከቀረበዉ የቪዲዮ ማስረጃ መረዳት የተቻለ በመሆኑ፤ ተከሳሽ ክፍያዉን እንዲፈጽሙ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ጊዜ ስጡኝ ከማለት ዉጭ አቶ ጌዲዮን አማረ ድርጅቱን ወክሎ ውል መዋዋል የሚያስችል ስልጣን የለዉም የሚል ነጥብ አንስተዉ የማያውቁ መሆኑን ሲታይ ተከሳሽ በዉሉ ላይ የተመለከተዉ ሙዚቃ በቅርብ የሚወጣ መሆኑን በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ መለጠፋቸዉ መመስከሩና ይህም በተከሳሽ ያለመካዱ ሲታይ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግኑኘትም መኖሩን ከላይ ከተገለጹት የተከሳሽ ግልጽ ተግባራት እና ዝምታ የሚያሳይ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 2180 እና ከፍ/ሕ/ቁ 2195(ሐ) መረዳት የሚቻል በመሆኑ እና የተከሳሽ ምስክሮች የሰጡትም ቃል እርስ በእራሱ የሚጣረስ እና እምነት የሚጣልበት ሆኖ ስላልተገኘ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና የለዉም በዉሉም አንገደድም በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት ያለዉ ሆኖ ስላልተገኘ እና ዉሉም ተከሳሽን ከላይ በተገለጸዉ ምክንያት የሚያስገድድ ሆኖ ስለተገኘ ፍርድ ቤቱ የተከሳሽን ክርክር አልተቀበለዉም፡፡
2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ ዉል እንዲፈርስላቸዉ የጠየቁት አቶ ጌዲዮን አማረ ተከሳሽን ወክሎ ውል ለመፈጸም ችሎታ የለዉም በማለት ሲሆን ከላይ እንደተገለጸዉ ተከሳሽ ባደረጉት ንግግር፤ በፈጸሙት ተግባር እና ዝምታ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግኑኘነት የፈጠረ በመሆኑ እና ተከሳሽ በፈጸሙት ተግባር፤ ባደረጉት ንግግር እና በዝምታቸዉ አቶ ጌዲዮን አማረ የተከሳሽ ወኪል ሆነዉ በፍ/ሕ/ቁ 2195(ሐ) የሚቆጠሩ በመሆኑ ተከሳሽ ወክለዉ ውል ማድረግ የሚችሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ እኔን ወክለዉ ውል ለመግባት ችሎታ የላቸዉም የተሰጣቸዉም ውክልና የለም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡
ሌላዉ ተከሳሽ ዉሉን ለማፍረስ የጠቀሱት ምክንያት ከዉሉ የሚገባንን ጥቅም አላገኘንም የሚል ሲሆን ይህ ምክንያት ዉሉን ለማፍረስ የሚያበቃ ምክንያት ካለመሆኑም በላይ ከሳሽ በዉሉ መሰረት ያልተወጡትን ግዴታ በማስረጃ አላረጋገጡም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ 1784 እና 1784 ስር የተገለጹት የውል ማፍረሻ ምክንያቶች የሌሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ/ም የተደረገዉ ውል ይፍረስልኝ በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም ፡፡
ሲጠቃለልም አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸሙት ውል ተከሳሽን የሚያስገድድ በመሆኑ እና ዉሉም የሚፈርስበት ህጋዊ ምክንያት ስላልተገኘ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፍል ይገባል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ውሣኔ
- ተከሣሽ ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ከ1/8/2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
- ወጪና ኪሣራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 5,850፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 40፣ እንዲሁም የጠበቃ አበል ብር 20,000 ተከሣሽ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡