ተጠሪዎች 1. አቶ ተስፋዬ ደርበው ረዳ         

አቶ አሸናፊ መንግስቱ አፈወርቅ

አቶ ልዑልቃል መለሰ ውብሸት በሌሉበት

አቶ ታሪኩ እሸቱ ቱርፋት

አቶ ታሪኩ አለማየሁ ለማ    

       መዝገቡ ተመርምሮ ተከታይ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

አመልካቾች በመስከረም 21 ቀን 2012 ዓ∙ም ጽፈዉ ባቀረቡት የክስ መመልከቻ አመልካቾች እና ተጠሪዎች በቁጥር ቅ/10/4758/40/10 በታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል የሠነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ በተመዘገበ የመመስረቻ ጽሁፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ አብርሃም፣ ቢኒያም፣ ታሪኩ እና ጓደኞቻቸው ሰብቤዝ እና ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ህብረት ሽርክና ማህበር የሚል የህብረት ሽርክና ማህበር በመቋቀም ሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ተጠሪዎች ማህበሩ በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባም ሆነ ድንገተኛ ስብሰባ ተጠርተው አድራሻቸው ባለመታወቁ እና የእጅ ስልካቸውንም የማያነሱ በመሆኑ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ 

ተጠሪዎቹ ማህበሩ ሊያሳልፍ በሚገባው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ውሳኔ ለመስጠት አለመቻላቸው በመመስረቻ ጽሁፉ አንቀጽ 8.2 እና በሌሎች ሕጎች መሠረት የማህበርተኞችን ሁሉ ስምምነት የሚፈልግ ውሳኔ በማሳለፍ የራሳቸዉም ሆነ የማህበሩን መብት እና ጥቅም ለማስከበር አልተቻለም፡፡  በዚህ ምክንያትም ማህበሩ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት የሚገኝ ሲሆን በዚህ መልክ ከቀጠለም ወደፊት በማህበሩ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ፣ የማይካስ እና የማይተካ በመሆኑ ተጠሪዎች ከማህበሩ አባልነት እንዲወጡ ውሳኔ እንዲሰጥልን በማለት አመልክተዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ እና የሰዉ ማስረጃዎችን አያይዘው አቅርበዋል፡፡

 

    ተከሳሾች በሕግ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው በፅሑፍ መልስ ያላቀረቡ በመሆኑና ክሱ እንዲሰማ በተቀጠረበት እላትም ያልቀረቡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ የሰጠ በመሆኑ ክስ የተሰማ ሲሆን አመልካቾች በጽሁፍ ያቀረቡትን ክርክር በመጠናከር አስረድቷል።

    ፍ/ቤቱም ተጠሪዎች ከማህበሩ አባልነት እንዲሰናበቱ ሊደረግ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ አመልካቾች ያቀረቡትን ክስ ከሕጉ አንጻር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምሯል፡፡

አመልካቾች በተጠሪዎች  ላይ ባቀረቡት ክስ የጠየቁት ዳኝነት ተጠሪዎች ማህበሩ በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባም ሆነ ድንገተኛ ስብሰባ ተጠርተው አድራሻቸው ባለመታወቁ እና የእጅ ስልካቸውንም የማያነሱ በመሆኑ ሊገኙ ያልቻሉ ሲሆን ተጠሪዎቹ ማህበሩ ሊያሳልፍ በሚገባው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ውሳኔ ለመስጠት አለመቻላቸው ጥሪ ቢደረግላቸውም ሊቀርቡ ያልቻሉ ስለሆነ ወደፊት በማህበሩ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ፣ የማይካስ እና የማይተካ በመሆኑ ተጠሪዎች ከማህበሩ አባልነት እንዲወጡ እንዲወሰንላቸው ሲሆን ማህበሩ በህግ አግባብ የተቋቋመ የንግድ ማህበር ስለመሆኑ፤ ተጠሪዎች የማህበሩ አባል ስለመሆናቸዉ  አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህንኑ የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃም ከክሱ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡

   ከሳሽ ማህበር የሕብርት ሽርክና ማህበር ሲሆን አንድ በህግ አግባብ የተቋቋመ የንግድ ማህበር የተመሰረተበትን አላማ ማለትም በማህበሩ መመስረቻ ጽሑፍ አሳካቸዋለሁ ብሎ ያስቀመጣቸውን የንግድ አላማዎች በአግባቡ በማሣካት ማህበርተኞችንና ሦስተኛ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችል ዘንድ፣ ጉዳትም እንዳይደርስባቸው መከላከል ይችል ዘንድ የንግድ ማህበሩ በህጉና ህጉን መሠረት በማድረግ ሊመራ ይገባል፡፡ ማህበሩ አላማውን በማሳካት አባለቱን እና ሦስተኛ ወገኖችን ለመጥቀም እና ጉዳት እናዳይደርስባቸው ለመከላከል የንግድ ማህበሩ በህጉ፣ በመመስረቻ ጽሑፍ እና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሊመራ እና ሊተዳደር፣ ማህበርተኞችም በህግ በመመስረቻ ጽሑፍ ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ  የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እና በግዜው ሊፈጽሙ ይገባል፡፡ የማህበሩ አባላት በህግ፣ በማህበሩ መ/ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በግዜው እና በአግባቡ መፈፀም ሲኖርባቸው ካልፈፀሙ በዚህ ምክንያትም በማህበሩ ስራ ላይ ጉዳት ከደረሰ ወይም ሌላኛው ማህበርተኛ በማህበሩ ውስጥ ያለውን መብት መጠቀም ካልቻለ ማህበሩ ሌሎች አባላትን እና ማህበሩን ከለጉዳት ለመታደግ ጥያቄውን ለፍ/ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡

  ከላይ ከገለጽነው ሁኔታ አኳያ የያያዝነውን ጉዳይ ስንመለከት ማህበሩ የህብረት ሽርክና ማህበር ሲሆን የማህበሩ አባላት ለማህበሩ ጉዳዮች በጥንቃቄና በትጋት መስራት እንዳለባቸው ከን/ሕ/ቁ 303 ፤ 243/1/ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በያዝነዉ ጉዳይም የማህበሩ አባላት በማናቸውም ስብሰባ ላይ የመሳተፍ እና ሁሉም የማህበሩ አባላት በማህበሩ ስራ ላይ የመሳተፍ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ በማህበሩ መ/ደብ አንቀፅ 4∙1 ስር ተመልክተዋል።

 አምልካቾች ተጠሪዎች ከማህበሩ አባልነት ሊሰናበቱ ይገባል በማለት ያቀረቡት ምክንያት ተጠሪዎቹ ማህበሩ ሊያሳልፍ የሚገባው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ውሳኔ ለመስጠት ባለመቻላቸው የማህበርተኞችን ሁሉ ስምምነት የሚፈልግ ውሳኔ በማሳለፍ የራሳቸዉም ሆነ የማህበሩን መብት እና ጥቅም ለማስከበር ያልቻሉ በመሆኑ ማህበሩ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን በመግለጽ ነዉ።

ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ለመስራት ይችል ዘንድ የአመልካቾችን ምስክሮች አስቀርቦ የሰማ ሲሆን የቀረቡት ሶስት ምስክሮች ተጠሪዎች ማህበሩ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተሳትፈው የማውቁ ስለመሆኑ እና በስልክ ጥሪ ሲደረግላቸውም ያልቀረቡ፣ አድራሻቸዉ የማይታወቅ  ስለመሆኑ በዚህ ምክንያትም ስራ ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሆነ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ አስረድተዋል፡፡

 ፍ/ቤቱ ከማህበሩ አባላት መካከል አንዱ እንዲወጣ በቂ ምክንያት ሲኖር ፍርድ ሊሰጥ እንደሚችል በን/ህ/ቁ 261 ስር የተመለከተ ሲሆን ተጠሪዎች ማህበሩ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተሳትፈው የማውቁ ስለመሆኑ እና አድራሻቸዉ የማይታወቅ  ስለመሆኑ በዚህ ምክንያትም ማህበሩ ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ የማህበሩ ቀሪ አባላትም እንደ ማህበር አባልነታቸው ከማህበሩ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በተከሳሾች አማካኝነት ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን ፍ/ቤቱ ተገንዝቧል። ስለሆነም በማህበሩ ሳይሳተፉ መቅረትና የአባልነት ግዴታን አለመወጣት እና ጥሪ ሲደረግላቸውም አለመቅረባቸው ከማህበር አባልነታቸው እንዲሰናበቱ ለማድረግ እንደ በቂ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ፤ተጠሪዎችም  ከአባልነት መውጣት የሌለባቸው መሆኑንም በመግለጽ ያቀረቡት ክርክርም ሆነ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ ተጠሪዎች ከማህበሩ አባልነታቸው እንዲወጡ ሊደረግ እና ማህበሩ በቀሪዎቹ አባላት እንዲቀጥል ሊደረግ ይገባል ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ውሳኔ

  1. ተጠሪዎች ከአብርሃም፣ ቢኒያም፣ ታሪኩ እና ጓደኞቻቸው ሰብቤዝ እና ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ህብረት ሽርክና ማህበር አባልነታቸው እንዲሰናበቱ እና የማህበሩ ሕልውና በቀሪዎቹ አባላት መካከል ሊቀጥል ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
  2. ተከሳሾች ከማህበር አባልነት እንዲወጡ የተወሰነ በመሆኑ ከማህበሩ ስም የአቶ ታሪኩ ስም እንዲወጣና የማህበሩ ስያሜ እንዲቀየር በን/ህ/ቁ 281/2 መሰረት ተወስኗል፡፡
  3. ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

ትዕዛዝ

  1. የውሳኔው ግልባጭ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ፡፡
  2. ይግባኝ መብት ነዉ፡፡
  3. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡