ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ 6ተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ የፌደራል መንግሥቱ ማራዘሙን ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ ብሔራዊ መንግሥት ምርጫውን በክልሉ ለማካሔድ በመወሰን የምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫውን ለማድረግ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ዝግጅት በማድረጉ ሲሆን የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫውን ማድረግ ይችላል አይችልም? ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቁጥጥር ውጭ የሆነና ራሱን የቻለ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም ይችላል አይችልም? ምርጫውስ ከተካሄድ ሊኖረው የሚችለው ውጤት ምን ድን ነው? የሚሉትንና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲሁም የትግራይ ክልል ምርጫውን ማድረግ መቻሉ ጋር የምርጫውን በክልል ደረጃ መደረጉን የሚደግፉ ፖለቲከኞችና አስተያየት ሰጭዎች ራስን በራስ ከማስተዳደርና የራስን እድል በራስ ከመወሰን ሕገ መንግሥታዊ መብት ጋር ስለሚያያይዙት ከነዚህ መብቶች ጋር ምርጫ ማድረግ እንዴት ሊታይ ይገባል? የሚለውን ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት እና ከምርጫ አዋጆች (አ/ቁ. 1133/2011 እና አ/ቁ. 1162/2011) አኳያ ለማብራራትና ሃሳብ ለማቅረብ በሚል የተዘጋጅ አጭር ጽሑፍ (Article) ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ ማንኛውም አስተያየት ሰጭ ለሚሰጠው አስተያየት ጸሐፊው ለማስተናገድና ሃሳብ ለመለዋወጥ ዝግጁ መሆኔን ከወዲሁ ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
1. የትግራይ ክልል ምርጫ ምንነትና ዓይነት
የፌደራል መንግሥቱ 6ተኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለማድረግ ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ አይፈቅድም በማለት የምርጫ ጊዜውን ማራዘሙን ተከትሎ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫውን አደርጋለሁ በማለት ቀን ቆርጦ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫውን አደርጋለሁ ካለ የሚያደርገው ምርጫ ክልላዊ ነው ወይስ ሀገራዊ ምርጫ? ምርጫው ምን ዓይነት ነው? የሚለው ትርጉምና ማብራሪያ ሀገሪቱ ካላት ሕገ-መንግሥትና የምርጫ አዋጆች (አ/ቁጥር 1133/2011 እና አ/ቁጥር 1162/2011) ላይ ለምርጫ ከተሰጠው ትርጉምና ከተዘረዘሩት የምርጫ ዓይነቶች የምርጫውን ምንነትና ዓይነት ማወቅ እንችላለን፡፡ በነዚህ አዋጆና የሕግ መንግሥት ድንጋጌዎች ላይ ከተሰጡት ትርጉሞች ላይ ትርጉሙንና ምንነቱን ማግኘት ካልቻልን የትግራይ ክልል መንግሥት ሕግ የማያውቀው ምርጫ እያካሄደ መሆኑን መረዳትና ማረጋገጥ ይቻላል ማለት ነው፡፡
በአ/ቁ. 1162 አንቀጽ፣ 2(5)፣ 6 እና 7 ላይ የምርጫ ዓይነቶችና ትርጉማቸው ተዘርዝረው እናገኛለን እነሱም፡ አጠቃላይ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ድጋሚ ምርጫ፣ የማሙያ ምርጫ እና የሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ናቸው፡፡ እነዚህ የምርጫ ዓይነቶች እያንዳንዳቸው በአ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 2(5) እና አንቀጽ 7 ላይ (የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደርገዋለሁ ያለው ምርጫ ከነዚህ የምርጫ አዋጁ ከዘረዘራቸው ውስጥ የአንዳቸውንም ዓይነት አይደለም፡፡ በርግጥ ክልላዊ መንግሥቱ አደርጋለሁ ያለው 6ተኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ መሆኑን ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄድ የነበረው 6ተኛ ዙር ምርጫ ደግሞ ጠቅላላ ምርጫ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጠቅላላ ምርጫ ደግሞ በየ5 አመቱ አንድ ግዜ የሚካሄድ የፌደራል የህዝብ ተወካዮችንና የክልል ምክር ቤቶች አባላትን ለመምረጥ በተመሳሳይ ግዜ በመላ ሀገሪቱ የሚካሄድ መሆኑን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና ከአ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 2(6)፣ 7(1፣2) መረዳት ይቻላል፡፡ በርግጥ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ ሁኖ ሲያገኘውና ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለ አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 7(2) ላይ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን የትራይ ክልል ምርጫ በተለየ ሁኔታ አስፈላጊነቱ ታምኖበትና በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተቀባይነት አግኝቶ እንዲደረግ የተወሰነ አይደለም፡፡ እንዳውም በተቃራኒው ምርጫው እንዳይደረግ የተባለና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው ነው፡፡ ጠቅላላ ምርጫ በመካሄድ ላይ ከሆነ ጠቅላላ ምርጫ ለማለት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መደረግ የነበረበት ሲሆን አሁን እየተደረገ ያለው በትግራይ ክልል ብቻ ስለሆነ 6ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ አይደለም ማለት ነው፡፡ 6ተኛው ይሁን የክልል ምርጫም ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ከዚህ በፊት በክልል ደረጃ ሀገራዊ ምርጫ ተደርጎ ስለማያውቅ ሲሆን 1ኛው የትግራይ ክልል ምርጫ እንዳይባልም የክልል ምርጫ የሚባል የሕግ ማእቀፍ ያለው የምርጫ ዓይነት የለም፡፡
በሌላም በኩል ካየነው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮችንና የክልል ም/ቤቶችን አባላት ለመምረጥ የሚደረግ ምርጫ ነው፡፡ የክልል ም/ቤት አባላቱን በክልሉ ውስጥ ስለሆነና ከሌላ ክልል የሚመረጥም ሆነ የሚመረጥ ስለሌለ የክልሉን ም/ቤት እንዳሻው ማድረግ ይችል ይሆናል (ቢያንስ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሃላፊነት ያለበት የፌደራል መንግሥቱ ሃላፊነቱን እስኪወጣ ድረስ) ነገር ግን የፌደራል ም/ቤቶች ተወካዮችን በተመለከተ በዚህ ምርጫ ለፌደረል ም/ቤቶች የተመረጡት ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች እጣፈንታቸው ምን ድን እንደሚሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ከተቀሩት የምክር ቤት አባላት ጋር ተቀላቅለው እንዳይቀጥሉ የሚመረጡት ተወካዮች የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ስለሌላቸው እንዲሁም የሌሎች ክለክሎች የም/ቤት ቤት አባላት ነባሮች ስለሆኑና አዲስ ምርጫ ተደርጎ ስላልተመረጡ ተቀላቅለው የም/ቤት አባላትን ወንበር በመያዝ መንግሥት ሊመሰርቱ አይችሉም አስቀድሞ የተመሰረተ መንግሥት ስላለ እንዲሁም ወንበሩን ይያዙ ከተባለና ምርጫውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ከሰጣቸው (ተቀባይነት የማግኘት እድሉ ዝቀተኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ) በፌደራል መንግሥቱ የሚካሄደውን አጠቃላዩን ምርጫ ውጤት ውጭ ሁነው መጠበቅ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የምርጫው ምንነት በሕግ ያልታወቀና የሚመለከተው አካል እውቅና ያልሰጠው መሆኑን ነው፡፡
2. ክልሎች ምርጫ የማድረግ ሥልጣን ሕገ መንግሥታዊነት
ምርጫ ማድረግ (ምርጫ ማካሔድና ማዘጋጀት) እና የራስን ምርጫ ቦርድ ማቋቋም አንዱ የአንዲት ሀገር ሉአላዊነት መገለጫ ነው፡፡ የትግራይ ክልል የፌደራሉ መንግሥት አንድ አካል እስከሆነ ድረስ ከፌደራል መንግሥት እውቅናና ፍቃድ ውጭ ራሱን ችሎ ምርጫ ማድረግ አይችልም፡፡ ምርጫ ከተደረገ ክልሉ ራሱን እንደ አንድ ነፃና ሉአላዊት አገር እየቆጠረ ሲሆን የሕገ መንግሥቱ አነቀጽ 8 ሕገ መንግሥቱ የብሔርች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉአላዊነት መገለጫ መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን የሉአላዊነት መገለጫቸው በሆነው ሕገ መንግሥት ምርጫን በተመለከተ የሚወስንላቸው የፌደራል መንግሥት መሆኑን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አስቀምጠዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ ሕዝቦች እንተዳደርበታለን ይገዛናል በማለት በጋራ ያጸደቁት የመግባቢያና የቃልኪዳን ሰነድ ሲሆን ከዚህ ማእቀፍ ለመውጣትም ይሁን አብሮ ለመቆየት የሚቻባቸውን ሁኔታዎች ሕግ መንግሥቱ ካስቀመጠው ድንጋጌ ውጭ በመውጣት መንቀሳቀስ የሕዝቦችን እርስ በርስ የመተማመንና የአብሮነትና እኩልነት መርህ የሚጥስ ተግባር ነው፡፡ በዚህም ምክንያ ሀገራዊና ክልላዊ ቀውስና አለመረጋጋት ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ርእስ ለመግቢያ ያክል ይህን ካልኩ ይህን የአገሪቱንና የሕዝቦች የሉአላዊነት መገለጫ የሆነውን ሕገ መንግሥት የአንድ ክልል ምርጫ ማድረግ እንዴት ይጥሳል የሚለውንና ክልሉ ምርጫ ማድረግ መብት የሌለው መሆኑን በተከታዩ ሁኔታ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
- በምርጫ ላይ የመወሰን ሥልጣን ለክልል መንግሥታት ያልተሰጠ ነው
ሌላው ከዚሁ ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ ነጥብ ሁኖ የቀረበው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ የወሰነበት አግባብ ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱንና የክልል መንግሥቶችን ሥልጣንና ተግባር በሚደነግጉት አንቀፆች ውስጥ ምርጫ ማድረግን ጨምሮ ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎች ማውጣት፣ መወሰን፣ ምርጫን ማስፈጸም እንደሚችል ሥልጣን የተሰጠው ለፌደራል መንግሥት መሆኑን ከሕገ መንግሥት አንቀጽ 51(15)፣ 55(2)(መ)፣ 60፣ 102፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አ/ቁ. 1133/2011 አንቀጽ (3)፣ 7(1)፣ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝባና የምርጫ ሥነምግባር አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 3(1)፣ 7፣ 8፣ 9፣ 10 እና 11 መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችና የምርጫ አዋጆች ምርጫ የማድረግና በምርጫ ላይ የመወሰንና ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌደራል መንግሥት በግልጽ የተሰጠ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ሲሆን የክልል መንግሥታት (ምክር ቤት) ይህ ሥልጣን ሊኖረው ይችል የነበረው በግልጽ ለፌደራል መንግሥ ያልተሰጡ ቢሆን እንደነበር ሲሆን ካልሆነ ደግሞ በግልጽ የክልሎችን ሥልጣንና ተግባራትን በሚወስነው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 52 ላይ ተሰጥቷቸው የነበር ቢሆን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ለፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ሰጥቶ ባለበት ሁኔታ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑ ሕገ-መንግሥቱን የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
- የክልል ምርጫ ቦርድ መቋቋም ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው
ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አ/ቁ. 1133/2011 አንቀጽ 2(2)፣ 3 እና የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 2(4) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለው በአገሪቱ አንድ ምርጫ ቦርድ የተቋቋመ ሲሆን እሱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ቦርዱም በፌደራልና በክልሎች ምርጫ (ጠቅላላ ምርጫ፣ አካባቢ ምርጫ፣ የሟሟያ ምርጫ፣ ድጋሚ ምርጫ፣ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ) እንዲያካሂድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ ሥልጣን ደግሞ የክልሎች ሥልጣን እንዳልሆነና ክልሎች ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የማክበር ሃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ክልሎች ምርጫ ቦርድ ካቋቋሙ ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረን ተግባር ነው፡፡ ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ቦርድ ማቋቋም ቢችሎ ኖሮ የክልሎችን ሥልጣንና ሃላፊነት በሚወስነው የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ አንቀጽ 52 ውስጥ ያካትተው የነበረ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ ምርጫ ማድረግንም ይሁን የምርጫ ሕግ ማውጣት እና ቦርድ ማቋቋም ለክልሎች የተሰጠ ሥልጣን መሆኑን አይገልጽም፡፡ ስለዚህ የትግራይ ክልል የምርጫ ቦርድ መቋቋም የኢፌደሪ ሕገ መንግሥትን የጣሰና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡
- የመምረጥና የመመረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ይጥሳል
እንደሚታወቀው ምርጫው የሚደረገው አንድ ክልል ውስጥ ብቻ በመሆኑና በክልሉ ውስጥ የሚካሄደውም ምርጫ የፌደራል መንግሥቱ እውቅና ያልሰጠው በመሆኑ ክልሉ ውጭ የሚኖሩ መራጮች ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮች፣ ሲቪል ሰራተኞችና ቤተሰቦቻው፣ በከፍተኛ ት/ት ተቋማት የሚማሩ ዜጎች (አሁን ባው ወቅታዊ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ ውጥ የሚማሩ አለመኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሁም በእስር ቤት የሚገኙ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ ዜጎች፣ በማናቸውም ምክንያት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 17 በሚያስቀምጠው አግባብ ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞላቸው እንዲመርጡ የሚደረግበትና የሚመቻችበት ሁኔታ የለም፡፡ ከዚህ አኳያ የነዚህ ዜጎች ተወካዮቻቸውን የመምረጥ መብታቸውን አጥተዋል፡፡
በሌላም በኩል የክልሉን ህዝብ እንወክላለን በሚል ከክልሉ ውጭ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የግል ተወዳዳሪ ተመራጮችን እንዲሁም ሀገራዊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በክልሉ ምርጫ እንዳይሳተፉ የማድረግ ውጤት ስላለው የነዚህን አካላት የመመረጥ መብት የሚጎዳና የሚጥስ ሲሆን ህዝቡም አማራጮችን እንዳያገኝና ምናልባትም ይወክሉኛል የሚላቸውን ትክክለኛ ወኪሎቹን ሳይመርጥ የሚቀርበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ የክልሉን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች (አረናንና ብልጽግና ፓርቲ) የክልሉ ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ባለመሆኑ በምርጫ አንሳተፍም ማለታቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡
- በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ይጥሳል
የኢትዮጵያ ፖለቲካና የመንግሥት አወቃቀር በቋንቋና በዘር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ አብዘኞቹ ክልሎች የተመሰረቱት የአንድን ብሔር ብዛትና አሰፋፈር ከግምት በማስገባት ሲሆን በክልሎቹ ውስጥ የሚኖሩ አናሳ የሆኑ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያካተቱ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ የነዚህን በየክልሉ ውስጥ የሚገኙ አናሳ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የክልሉ ባለቤት እንዲሆን በተደረገውና አብዛሃኛውን ቁጥር በያዘው አንድ ብሔር እንዳይዋጡ ለመከላከልና ትክክለኛ ወኪሎቻቸውን መምረጥ እንዲችሉ በማሰብ አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 13 ላይ የህዝብን ብዛትና አሰፋፈራቸውን መሠረት ያደረገ ራሱን የቻለ የምርጫ ክልል እንዲቋቋምላቸው መደረግ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (1)፣(5) ላይም በየ10 ዓመቱ የህዝብ ቆጠራ እንደሚደረግና በውጤቱን መሠረት የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ጥናት መሠረት እንዲቋቋም ይደነግጋል፡፡ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያየ ምክንያት እስካሁን በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው የግዜ ገደብ መሠረት የህዝብ ቆጠራ አልተደረገም፡፡ የህዝብ ቆጠራ የሚደረገው የህዝቡን አሰፋፈርና ብዛት መሠረት በማድረግ የምርጫ ክልል ለማቋቋምና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ለማስጠበቅ እንዲሁም ከላይ እንደተጠቀሰው አናሳ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በብዙሃኑ እንዳይዋጡና የራሳቸውን ወኪሎች በመምረጥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ለማረጋገጥ በሚልነው (አ/ቁ. 1133/2011 እንቀጽ 7(6)፣ 23(1,2,3,) እና 1162/2011 አንቀጽ 2(15)፣13(1(ሀ፣ለ፣ሐ፣መ፣ሠ)) ይመልከቱ)፡፡ በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ የራያ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ኢሮብ፣ ኩናማ፣ ተንቤን አገው፣ እንደርታና ዋጅራት እና ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንደሚያነሱና እስካሁን እንዳልተመለሰላቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ አናሳ ብሔሮችና ሕዝቦች የአሰፋፈራቸውና የመሬት አቀማመጥ ሁኔታ፣ የህዝብ ብዛታቸውና ፍላጎታቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ የምርጫ ክልል ለማቋቋም እንዲሁም የተለየ ውክልና የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ለመለየት ይቻል ዘንድ የሕዝብ ቁጥራቸው ሊታወቅ ይገባ ነበር፡፡ የትግራይ ክልል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ላይ እንደተቀመጠው የሕዝብ ቆጠራ ሳይደረግ ምርጫ ማድረጉ የህዝቦቹን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጎዳና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
- ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራስን እድል በራስ መወሰን መብትን ምርጫ ከማድረግ መብትና ሥልጣን ጋር እንዴት ልንገነዘባቸው ይገባል
ህወሓትን ጨምሮ በትግራይ ክልል ይሁን በሌሎች የአገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አገራዊና ክልላዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ ክልል ምርጫን ለማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ያለው መሆኑን አጥብቀው የሚከራከሩት ራስን በራስ የማስተዳደር መብትንና የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብትን በመጥቀስ ምርጫ የማድረግ መብታቸው ከዚህ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የመነጨ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦችና ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች አሁን ባለን ሀገራዊ ሁኔታና ሕገ-መንግሥት መሠረት ለክልሎች ምርጫ የማዘጋጀትን (የማካሔድን) መብት የማይሰጡና የማይገናኙ እንዲሁም አንዱ የአንዱ መገለጫ አይደሉም፡፡ ለዚህም ተከታዮቹን ነጥቦች ማንሳት ይቻላል፡፡
- ራስን በራስ ማስተዳደር እና የራስን እድል በራስ መወሰን (….እስከ መገንጠል) መብቶች የሚረጋገጡት የመምረጥና የመመረጥ መብትን በመጠቀም ስለመሆኑ
ከፌደራል መንግሥቱ እውቅና ውጭ ምርጫ ማድረግ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠልን የራስን እድል በራስ መወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ነው የሚል ክርክር የሚያቀርቡት አካላት የመምረጥና የመመረጥ መብትን ከምርጫ ማድረግ መብት (ሥልጣን) ጋር አንድ ዓይነት ትርጉምን በመስጠትና የተለያዩ መብቶች ለተለያዩ አካላት የተሰጡ መሆናቸውን ባለመረዳት ይመስላል፡፡ ምርጫ የማድረግ መብት እና የመምረጥና የመመረጥ መብት ለተለያየ አካል የተሰጡ ሁለት የተለያዩ መብቶች ናቸው፡፡ ምርጫ የማድረግንና የምርጫ ቦርድን በፌደራል መንግሥት ደረጃ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ሃላፊነት ሲሆን የመምረጥና የመመረጥ መብት ደግሞ የዜጎች መብት ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚረጋገጠው ምርጫ በማድረግ መብት ሳይሆን በመምረጥና በመመረጥ መብት ነው (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38 (1(ሀ))፡፡
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ምርጫ የማድረግ መብተንም የሚያካትት ቢሆን ምርጫን በሚመለከት ወይም ራስን በራስ ማስተዳደር መብትን በሚመለከት የሚደነግጉት የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ላይ ተካቶ ይቀመጥ ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38(1)(ሀ)፣ 39 (3)፣ 50 (4)፣ 52(2)(ሀ) እና 88 ላይ ራስን በራስ ማስተዳደር መብቶች የሚገለጹትና የሚረጋገጡት በየትኛውም የመንግሥት የአስተዳደር አካላትና ሥልጣን ላይ በቀጥታና በነፃ በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት በመሳተፍ፣ በክልልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና ማገኘት፣ ህዝቡ በሰፈረበት መልክአ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት ማቋቋም፣ ህዝቡ በቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆንባቸው ለዝቅተኛ አስተዳደሮች በቂ ሥልጣን መስጠት፣ ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር መርህን በጠበቀ ሁኔታ እንዲዋቀሩ በማድረግ ነው፡፡
ነገር ግን ክልሎች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፌደራል መንግሥት ያቋቋመው ብሔራው ምርጫ ቦርድ በሚያዋቅራቸው የክልልና የወረዳ እንዲሁም የቀበሌ የምርጫ ክልሎችና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና የምርጫ አስፈፃሚ አካላት ውስጥ የመወከልና የመሳተፍ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሆነው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አላቸው፡፡ ለዚህም ሲባል አ/ቁ. 1133/2011 አንቀጽ 6(2)፣7(8)፣ 7(14)፣ 9(8)፣ 23(2)፣ 23(3)፣ እና በአ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 12(1)፣ 13(3፣5፣6)፣ 15(1፣2፣8፣9፣10) ላይ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የክልሉ ኗሪ የሆነ ሰው መሳተፍ እናዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ይህም ማለት ከላይ እንደተገለጸው የክልሉ ኗሪ የሆነ ሰው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያቋቁመው የምርጫ ክልል እና የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትና የምርጫ አስፈፃሚ ውስጥ እንዲሳተፍ በማድረግ ራስን በራስ የማስተዳደርና የመወሰን መብት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ እነዚህ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት የሚቋቋሙ የክልል ምርጫ ጽ/ቤቶች፣ የምርጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች፣ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ጣቢያዎች በቦርዱ በሚሰጣቸው መመሪያና አቅጣጫ መሠረት ምርጫ ማካሔድና የምርጫውን ውጤት መወሰን የመሳሰሉት ሥልጣን የተሰጣቸው ሲሆን ይህን ስልጣናቸውን በሚከውኑበት ግዜ ነፃና ገለልተኛ በመሆን ስለሆነ፡፡
ሌላው ምርጫ የማድረግ መብት አለን የሚሉት ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39(1) ላይ የተጠቀሰውን የራስን እድል በራስ መወሰን (….እስከ መገንጠል) መብትን በመጥቀስ ነው፡፡ አንድ ክልል የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ሥልጣን ሕገ መንግሥቱ ስለሰጠው ምርጫ ላድርግ ወይም አላድረግ ብሎ መወሰን ይችላል፡፡ ምርጫ ይደረግ አይደረግ ብሎ መወሰን አንዱ የራስን እንድል በራስ መወሰን መብት ነው ፤ ምርጫ ማድረግና አለማድረግ ደግሞ የክልሉ ጉዳይ ሲሆን መወሰንም የሚችለው የክልሉ መንግሥትና ህዝብ ብቻ ነው የሚል ክርክር በምክንያትነት ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወገን ያሉት ተከራካሪዎች ሊገነዘቡ ያልቻሉት ነጥብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የራስን እድል በራስ መወሰን መብት የሚረጋገጡትና የሚተገበሩት በሁለት የተለያየ የምርጫ ዓይነትና ዘዴ እንዲሁም ሁኔታ መሆኑን ነው፡፡ የመጀመሪያው አገሪቱ በምታዘጋጀው በጠቅላላ ምርጫ (General Elections) በመሳተፍ የሚተገበር ሲሆን የሁለተኛው መብት ደግሞ በህዝበ ውሳኔ ምርጫ (Referendum) የሚተገበር ነው፡፡ ሁለቱም የምርጫ ዓይነቶችና ሂደቶች የዜጎች፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ቢሆኑም የሚፈጸሙትና የሚዘጋጁት ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል በሚዘጋጅ ምርጫ ነው፡፡
ምርጫ ላድርግ አላድርግ ብሎ መወሰን አንዱ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አካል አለመሆኑን የኢፊድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (1 እና 4) ፤ በአ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 2(10) እና አንቀጽ 11 ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት ተሰጥቷል ሲባል ክልል ወይም ብሔር ብሔረሰቡና ሕዝቡ አሁን ባለው የአስተዳደር መዋቀር መካተቱን በመቃወም በልዩ ወረዳ፣ በልዩ ዞን፣ በክልልነት ወይም ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና ሀገር ለመመስረት ሲፈልግ የሚነሳ መብት ሲሆን ይህንንም ፍላጎቱን የሚያረጋግጠው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያዘጋጀው የሕዝበ ውሳኔ (referendum) ምርጫ ነው፡፡
የራስን እድል በራስ መወሰን ሲባል ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ማንንነት ማን ነው ቋንቋው ምንድን ነው፣ የሚኖረው የት ነው፣ ታሪኩ ምንድን ነው፣ ባህሉና እምነቱ ምንድን ነው፣ የስራ ቋንቋው ምን ሊሆን ይገባል፣ ከኢትዮጵያ ሊገነጠል ይገባል ወይስ አብሮ መኖር አለበት፣ ከአንድ ክልል ጋር መኖር አለበት ወይስ ራሱን ችሎ ክልል፣ ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ ሁኖ ይኑር ወይስ አሁን ካለበት ጋር ሳይሆን ሌላ ክልል ጋር ተቀላቅሎ ይኑር፣ የሚያስተዳድሩት እነማን ሊሆኑ ይገባል፣ የመንግሥት መዋቅሩና አስተዳደሩ ምን ሊመስል ይገባል፣ ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ አወቃቀሩ ምን ይመስላል፣ ከቀሪው የኢትዪጵያ ሕዝብና ብሔር ብሔረሰብ ጋር እንዴት ባለሁኔታ ሊኖር ይገባል የመሳሰሉትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ያለማንም ጣልቃ ገብነት መወሰን እንዲችል ሕገ መንግሥቱ መብት የሰጠ ሲሆን እነዚህን ለመወሰን የሚያስችለው በህዝበ ውሳኔ (Referendum) ምርጫ ነው፡፡
አንድ ክልል ወይም ብሔር ወይም ህዝብ የራስን እድል በራስ መወሰን (…እስከ መገንጠል) መብት አለው ማለት ከመገንጠሉ አስቀድሞ የሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ምርጫ የማድረግ መብት አለው ማለት አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (3) እና አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 11 ላይ በግልጽ ተደንግጎ እንደሚገኘው የራስን እድል በራስ መወሰን (….እስከ መገንጠል) መብትን ለማረጋገጥ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ እንዲደረግ የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ጥያቄውን ያቀረበው የክልል፣ የብሄርሰብ፣ ብሄረሰቦች ወይም የህዝቦች ምክር ቤትና ተወካዮች ሳይሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን ነው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ሲወስን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ ያደርጋል (አ/ቁ. 1162/2011 አንቀጽ 11)፡፡ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ጥያቄ ያነሳው ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ወይም ክልል በምርጫ ቦርድ በተዘጋጀው ምርጫ በመሳተፍና የመምረጥና የመመረጥ መብቱን በመጠቀም በምርጫው ውሳኔውንና ፍላጎቱን ማሳወቅ ሲሆን የህዝበ ውሳኔ ምርጫው እንዲካሄድ የመወሰንም ይሁን የማካሔድ ሥልጣን የለውም፡፡
ራስን በራስ ከማስተዳደር መብትና የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ጋር በተያያዘ በአብዛኞቻችን የሚታወቀውን የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄንና የተሰጠውን መፍትሄ መጥቀስ ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት ያለው ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ራሴን በራሴ ላስተዳድር በማለት ለሚመለከተውና ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ላለው አካል ጥያቄውን አቀረበ እንጂ ምርጫ አደርጋለሁ (በራሴ ምርጫ አስፈጽማለሁ)፣ ምርጫ ማድረግና አለማድረግ የራሴ ጉዳይ ስለሆነ በራሴ ጉዳይ የሚመለከተው አካል የለም አላለም፡፡ ጥያቄውም ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ እንዲደረግ የፌደራል መንግሥት በወሰነው መሠረት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔውን ምርጫ አዘጋጀ ህዝቡም የመምረጥና የመመረጥ መብቱን በመጠቀም (ምርጫ የማድረግ መብትና ሥልጣን ሳይሆን) የራሱን እድል በራሱ ወስኖ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ክልል በመሆን አረጋግጧል፡፡ አሁን የሲዳማ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ያረጋገጠ ሲሆን ይህን መብቱን ያረጋገጠው ምርጫ ማድረግና ምርጫ እንዲደረግ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ ሳይሆን የመምረጥና የመመረጥ መብቱን ተጠቅሞ ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርና የመወሰን መብቱ ተረጋግጧል ሲባል ከፌደራል መንግሥትና ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅናና ቁጥጥር ውጭ ምርጫ በራሱ ክልል እንዲካሄድ ይወስናል / ያስፈጽማል / ማለትም አይደለም፡፡ ከዚህ የምንረዳው ራስን በራስ የማስተዳደርና የመወሰን መብት አለ ማለት የምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫ ማድረግ፣ መፈጸም፣ ማዘጋጀት፣ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰን መብትና ሥልጣን አለ ማለት አለመሆኑን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የኢፌድሪ ሕገ - መንግሥት ታሪክ የሲዳማ ህዝብ በምርጫና በራሱ ፍቃድ የራሱን ክልል የመሰረተ የመጀመሪያው ሕዝብ ነው፡፡ ሌሎች ዘጠኝ ክልልሎች በራሳቸው ምርጫና ፍላጎት ሳይሆን ክልል የሆኑት በመንግሥት ምርጫና ፍላጎት ነው፡፡ ለዚያም ነው አሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚያስብል ደረጃ የኔ ነው ያንተ አይደለም መጤነህ አገርህ አይደለም የሚል አመለካከት የተፈጠረውና አንዱ ባለቤት ሌላው መጤ (ባይተዋር) ተብሎ ብዙ መፈናቀሎች፣ የህይወት መጥፋት፣ የሃብትና ንብረት ውድመት ሊከሰት የቻለው፡፡
- የክልሎች /ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች/ ምርጫ የማድረግ መብትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የማይነጣጠሉ መብቶቻቸው የሚሆኑበት ሁኔታ
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ምርጫ በማድረግ መብት የሚረጋገጠውና ሁለቱ መብቶች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሚሆኑት በአንዲት ሉአላዊት ሀገር ላይ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ምርጫ የማድረግ ሉአላዊ መብቷ ሲሆን ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ እንድታደርግ ወይም እንዳታደርግ የሚያዛትም ይሁን የሚያስገድዳት ወይም የሚከለክላት ሀገር ወይም መንግሥታት ሊኖር አይችልም፡፡ የፌደራል መንግሥቱ አካል የሆነ አንድ ክልል ራሱን ችሎ ምርጫ ለማድረግ መወሰንና ምርጫ ማድረግ ግን አይችልም፡፡ የፌደራል መንግሥቱ አካል የሆኑት ክልሎች ምርጫ ማድረግና በምርጫ ላይ ሊወስኑ የሚችሉት ከኢትዮጵያ ሲገነጥሉና ራሳቸውን የቻሉ ሀገር ሲሆኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ ኤርትራን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኤርትራ ሀገር ከመሆኗ በፊት ምርጫ እንዲካሄድ ሲወሰን የነበረው በኢትዮጵያ መንግሥት ነበር፡፡ ኤርትራ የራሷን እድል በራሷ ወስና ተገንጥላ ሀገር ለመሆን ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የወሰነውም ይሁን ያስፈጸመው በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት እንጂ የኤርትራ ክፍለሃገር አልነበረም፡፡ የኤርትራ ክፍለ ሃገር የመገንጠል ጥያቄውን አቀረበ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኖ ምርጫውን በምርጫ ቦርድ አማካኝነት እንዲፈጸም አደረገ እንጂ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ምርጫው እንዲደረግ ወስኖና ምርጫውን አድርጎ የኤርትራን እድል በራሷ እንዲወሰን አላደረገም፡፡ አሁን ግን ከኢትዮጵያ የተገነጠለችና ራሷን ችላ ሀገረ መንግሥት የመሰረተች ሉአላዊት ሀገር ስለሆነች ምርጫ ላይ የመወሰን ስልጧኗ ራሷን በራሷ ከማስተዳደር ጋር የተዋሃደና የማይነጣጠል መብቷ ነው፡፡
- ክልሎች ራሳቸውን ችለው ምርጫ ቢያካሂዱ የሚኖረው ሕጋዊ ውጤት
ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው ክልሎች በማናቸውም ሁኔታና በየትኛውም የሕግ አግባብ ራሳቸውን ችለው ምርጫ ማድረግ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ምርጫ ቢደረግ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በአጭሩ በተከታዩ ማስቀመጥና መገመት ይቻላል፡፡
- ምርጫው ሕገ-መንግሥቱን የሚጥስ በመሆኑ ተፈፃሚነት የማይኖረው እንደተደረገ የማይቆጠርና ሕጋዊ ውጤት የሌለው (VOID) ነው፡፡
- ምርጫው በመደረጉ አስቀድሞ የክልሉን መንግሥት ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ስልጣኑን ያጣል ምክንያት
- ከምርጫው ቡሃላ የሥልጣን ዘመኔን ጨርሻለሁ በሚል ምርጫ ስላካሄደ በፌደራልና በክልል የያዛቸውን የውክልና እና የሥልጣን ወንበሮች በራሱ ፍቃድ እንደለቀቀ ያስቆጥራል ፤
- ምርጫ ያካሄደው የመንግሥት አካል፣ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ሕገ መንግሥቱን ስለጣሱና ሕገ መንግሥቱን በሚጥስ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል ይህም የፖለቲካ ድርጅቶችን ህጋዊ ሰውነት እስከማሳጣት ሊደርስ የሚችል ቅጣትን ሊያካትት ይችላል ፤
- የርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ምርጫው በመደረጉ
- ሕገ መንግሥቱን በማስከበርና ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረግ እንቅስቃሴ ግጭት ይፈጠራል፣
- ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሲደረግ በክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግሥት ምርጫ እንዲካሄድ ስለሚያደርግ እና እንዳይደረግ የሚፈልጉ ወገኖች ስለሚኖሩ በመካከላቸው ግጭትና አለመግባባት ይፈጠራል፤
- የፌደራል መንግሥቱ ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫውን በክልሉ ውስጥ ስለሚያደርግ በአንድ ክልል ውስጥ ሁለት ምርጫ ለአንድ ወንበር ስለተደረገ ሁለት ተመራጭ፣ ሁለት ተወካይ ያለው ሁለት መንግሥት በክልሉ ውስጥ የመፈጠር እድሉ ሰፊ ስለሆነ የክልሉን መንግሥት ሥልጣን ማን ሊይዝ ይገባል እንዲሁም በፌደራል ሕዝብ ተወካዮችና በፌደሬሽን ምክር ቤት ወንበሮች የክልሉን ሕዝብ የሚወክለው ህጋዊ ተወካይ ማን ሊሆን ይገባል በሚል አለመግባባት ያስከትላል፤
- በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ይፈጥራል፤ የፌደራል ሥርአቱን የሚያፈርስና ከፌደራል ሥርዓት ወደ ኮንፌደሬሽን ሥርዓት ሊቀይር የሚችል ማሳያ ይሆናል፡፡
- ሌሎች ክልሎችንና ሕዝቦችን ለተመሳሳይ ፍላጎትና ድርጊት ያነሳሳል (የምርጫው ውጤት ስጋት)፤
- የፌደራል መንግሥቱን ሕገ መንግሥትንና ሕግን የማስከበር አቅምን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፣
- በአገርና በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመግለጽ እነደተሞከረው አንድ ክልል በየትኛውም ሁኔታ ራሱን ችሎ የፌዴራል መንግሥትና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድና እውቅና ሳይሰጠው ምርጫ የማድረግ ሥልጣንና መብት የለውም፡፡ ምርጫ አደርጋለሁ ካለም የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ተግባር ነው፡፡ የትግራይ ክልል ራሱን ችሎ ምርጫ ማካሔድ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ምርጫው ኢትዮጵያ ጋር እንደ ሃገር ለመቀጠል የሚያስችል ሳይሆን ራስን ችሎና ተገንጥሎ ለመኖር የሚያስቸል የሚመስል ነው፡፡ ምርጫው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ አይደለም፡፡ ምርጫው በሕግ ረገድ ውጤት የሌለውና ተፈፃሚነት የማይኖረው ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ምርጫው ቢደረግ (ማድረግ) የትግራይ ክልል ተመራጮችና የተመረጠው የፖለቲካ ድርጅት የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን ወይም የፌደራል የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ም/ቤት ወንበሮችን የሚይዝበት ሁኔታ የለም፡፡ ብቻውንም ም/ቤትና መንግሥት ሊመሰርት አይችልም፡፡ የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የሚጠቅመውም ሆነ የሚጎዳው በዋናነት የክልሉን ሕዝብ ነው፡፡
በቀድሞ ታሪኮቻችንና ስራዎቻችን ላንግባባ እንችል ይሆን ይሆናል ነገር ግን እንዴት ራሳችን በራሳችን ባዘጋጀነውና በፃፍነው እንዲሁም በምክር ቤት ቁጭ ብለን እጅ አውጥተን ባጸደቅነው ሕግና ሕገ መንግሥት መግባባትና መገዛት ያቅተናል? በታሪኮቻችን አለመስማማትና ሳይስማሙ መኖር ይቻል ይሆናል በሕግ ላይ ሳይስማሙና ባለመስማማት ሕግን እየጣሱ መኖር የማይቻል ነው፡፡ የትግራይን የምርጫ ውጤት ወደፊት የምናየው ይሆናል በእኔ በኩል የሚገባኝና የተረዳሁት ነገር ምርጫው ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ፣ የሕዝቦችን አብሮነትንና አንዱ ከሌላው ጋር በመተማመን መኖርን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ (ያስገባ)፣ የፌደራል ሥርዓቱን ወደ ኮንፌደሬሽን ሥርዓት የሚቀይር በተለይ ትግራይ ክልልን ለመገንጠል በሂደት ላይ መሆንን የሚያሳይ፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እንዲሁም የዜጎችን መብት የሚጎዳና ፍላጎታቸውን የሚቃረን፣ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሳይሆን የአንድ የተለየ ዓላማ ያለው ቡድንን ዓላማን ለማራመድ የተዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ጸሐፊው የሕግ ባለሙያና ጠበቃ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው