አንድ ግብር ከፋይ በንግድ እንቅስቃሴው ያመነበትን ወስኖ ያቀረበውን የሂሣብ መግለጫዎችን የታክስ ባለስልጣኑ የግብር ኦዲት በመስራት ግብር ከፋዩ ሊከፍል የሚገባውን ግብር ይወስናል፡፡ በአገራችን የግብር አወሳሰን ዘዴዎች ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህም በሂሳብ መዝገብ ወይም በግምት መሠረት ናቸው፡፡
ግብር ከፋዩ ለግብር አወሳሰን ያቀረበው የሂሳብ መዝገብ ሰነዶች ከተጣራ /ከተመረመረ/ በኋላ በመዝገቡ መሠረት ሊከፈል የሚገባው ግብር የሚወሰን ሲሆን፤ በሌላ በኩል የታክስ ባለሥልጣኑ ግብር ከፋዩ ሊከፍል የሚገባውን ግብር በግምት ሊወስን ይችላል፡፡
በግምት የሚወሰን ግብር በሦስት አይነት ዘዴዎች የሚከናወን ሲሆን እነዚህም፤
1. የእለት/ቀን/ ገቢን በመገመት የሚወሰን፤
2. በመረጃ መሠረት የሚወሰን እና
3. በቁርጥ የሚወሰን ግብር
ናቸው፡፡
ከእነዚህ የግምት ግብር አወሳሰን ስልቶች መካከል የዚህ ፅሁፍ ዓላማ የቀን ገቢን በመገመት /Estimated Assessment/ በሚወሰን የገቢ ግብርን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋዮች አመካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ ማሰባሰቢያ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 123/2009 በሕጉና በአፈጻጸም ረገድ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡
1. የግምት ግብር ስልቶች
በፌዴራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 26 በግልጽ እንድተቀመጠው ማንኛውም ታክስ ከፋይ በታክስ ሕግ መሠረት በማንኛውም የታክስ ጊዜ ማቅረብ የሚገባውን የታክስ ማስታወቂያ ያላቀረበ እንደሆነ ባለሥልጣኑ በማንኛውም ጊዜ የሚያገኘውን ማስረጃ መሠረት በማድረግ ለታክስ ጊዜው ታክስ ከፋዩ ሊከፍል የሚገባውን ታክስ በግምት (“የግምት ስሌት” ተብሎ የሚጠራ) ማስላት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የታክስ ባለሥልጣኑ በአንድ ግብር ከፋይ ላይ ከታች ከተመለከቱት የግምት ግብር ስልቶች መካከል በአንዱ ግብር ሊወስን ይችላል፡፡
በእለት ገቢ የሚወሰን ግብር /Estimated Assessment/፡- የግብር ከፋዮችን የንግድ እንቅስቃሴ መሠረት ያደረገ በገቢ መርማሪዎች የህሊና ዳኝነት ላይ ተመስርቶ የቀን ገቢ ይገመታል፡፡ ይህም የቀን ገቢ ግምት ወደ አማካኝ ዓመታዊ ገቢ መቀየር ለዚህ በተዘጋጀው ትርፋማነት ምጣኔ ተለይቶ ባለው የገቢ ማስከፈያ ተመን መሠረት ግብሩ ይጠየቃል፡፡
በመረጃ የሚወሰን ግብር፡- የግብር ከፋዩ መዝገብ ከሂሳብ አያያዝ ስርዓትና ከግብር ሕጉ አኳያ ተመርምሮ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ከሶስተኛ ወገን በሚገኝ የግዥ ወይም የሽያጭ መረጃ ላይ በመመሥረት ግብሩ ይወሰናል፡፡
በቁርጥ የሚወሰን ግብር /Presumptive Taxation/:- ግብር ከፋዮች መዝገብ ሳይዙ ሲቀሩ ወይም መዝገቡ ተመርምሮ ውድቅ ሲሆን ወይም መዝገብ የመያዝ የሕግ ግዴታ የሌለባቸው የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ግብር ወይም ስለ ግብር ከፋዩ በቀን ገቢ ግምት ወይም ከሶስተኛ ወገን መረጃ ማግኘት ሳይቻል ሲቀር ግብሩ በቁርጥ/Presumptive/ይወስናል፡፡
2. የእለት/የቀን/ ገቢ ግምት አፈጻጸም መመሪያ
የቀን ገቢ ግምትን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋዮች አመካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ ማሰባሰቢያ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መመሪያ አንቀጽ አንቀጽ 2/7/ መሰረት የቀን ገቢ ማለት አንድ ግብር ከፋይ ከፋይ በቀን ዕቃ ሸጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ የሚያገኘው አማካኝ እለታዊ ገቢ ማለት እደሆነ ይደነግጋል፡፡
አማካይ የቀን ገቢ ግምት ዳግም የሚጠናበትን ጊዜ በተመለከተ መመሪያው በአንቀጽ 5 ላይ ቢያንስ በየ3 ዓመቱ የመረጃ ማሰባሰብ ስራ በማከናወን እንደሚከለስ የሚደነግግ ቢሆንም፤ የከተማ አስተዳደሩ የቀን ገቢ ግምት ከተገመተ ከ2009 ዓ.ም በሃላ ዳግም ጥናት ሳያከናውን 3 ዓመታት ያለፈ በመሆኑ፤ በ2009 ዓ.ም በተከናወነው የቀን ገቢ ግምት መሰረት ግብራቸውን የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ያሉበትን ወቅታዊ ደረጃ ለማወቅ የሚያስቸግር እና ከ2009 ዓ.ም በሃላ ወደ ንግድ ስርዓቱ የገቡና ግምት ያልተጠናላቸውን አዳዲስ ግብር ከፋዮች የማያካትት በመሆኑ፤ በጸሃፊው እምነት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ የበጀት ዓመት አማካይ የቀን ገቢ ግምት ዳግም ማጥናት ይኖርበታል፡፡
3. የመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን
በአንቀጽ 3 ላይ የመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ መመሪያ በአንቀጽ 3 በንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ አማካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ የሚጠናላቸው እና የማይጠናላቸው ግብር ከፋዮች በማለት ለሁለት ከፍሏቸዋል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግምት የሚጠናላቸው እና የማይጠናላቸው ግብር ከፋዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የቀን ገቢ ግምት የማይጠናላቸው፤
- የፌዴራል ግብር ከፋዮች በሙሉ፤
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋይ ሆነው፤
- ግብር በመረጃ የሚወሰንላቸው ግብር ከፋዮች፤ በመደበኛ ቁጥር የሚወሰንላቸው ግብር ከፋዮች እና የጎዳና ንግድ እና ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡
- የቀን ገቢ ግምት የሚጠናላቸው፤
- የከተማ አስተዳደሩ ግብር ከፋይ ሆነው ከላይ በቁጥር 3.1.2. የተመለከቱትን ሳይጨምር፤
- ሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ግብር ከፋዮች፤
- አመታዊ ጠቅላላ ገቢ ከብር 500ሺ በታች የሆኑ የደረጃ“ሐ” የቁርጥ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡
በመሆኑም ከመመሪያው አንቀጽ 3 የተፈጻሚነት ወሰን በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው አማካይ የቀን ገቢ ግምት በሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋዮች ላይ የሚጠና አይደለም፡፡ ስለሆነም አማካይ የቀን ገቢ ግምት በሚጠናላቸው ግብር ከፋዮች ላይ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ተፈጻሚነት ያለው ሲሆን፤ በማይጠናላቸው ግብር ከፋዮች ላይ ግን መመሪያው አስገዳጅነት የለውም፡፡
የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ የሕግ ግዴታ የሌለባቸው በመሆኑ ግብራቸውን ከላይ በቁጥር 1 ላይ ከተዘረዘሩት ከሦስት የግምት ግብር ስልቶች መካከል በአንደኛው የሚከፍሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ የግምት ግብር ስልቶች መካከል በቁርጥ በሚወሰን የግምት ግብር /Presumptive Taxation/ እና በመረጃ መሠረት በሚወሰን የግምት ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣው መመሪያ ቁጥር 123/2009 ተፈጻሚነት የለውም፡፡ መመሪያው አስገዳጅነት ያለው በቀን ገቢ ግምት ግብር /Estimated Assessment/ ላይ ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥራ ላይ ያዋለውን አመካይ የቀን ገቢ ግምት ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 123/2009 በተመለከተ ጸሃፊው በከተማ አስተዳደሩ በተለይም በአንዳንድ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤቶች መመሪያውን በተግባር በመፈጸም ረገድ የሚታዩ ችግሮች እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ያቀርባል፡፡
4. አመካይ የቀን ገቢ ግምት መመሪያ በአፈጻጻም የሚታዩ ችግሮች፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ያዋለው አመካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ ማሰባሰቢያ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 123/2009 በአፈጻጸም ረገድ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ መመሪያው ለማስፈጸም ካለመው ዓላማ በተቃራኒ የሚታዩ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ግብርን በመዝገብ በሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ላይ መመሪያው ተፈጻሚ መሆኑ፤
የግብርና የታክስ አሰባሰቡን ለአከፋፈልና ለክትትል እንዲያመች በሚያስችል መንገድ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ መነሻ በማድረግ በፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 3 መሠረት ግብር ከፋዮች በ3 ደረጃ ይህም ደረጃ “ሀ” ደረጃ “ለ” እና ደረጃ “ሐ”በማለት ይከፈላሉ፡፡ ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ ጠቅላላ አመታዊ ገቢው ብር 1,000,000 ብርና በላይ ጥቅል ሽያጭ ሲሆን፤ ደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ አመታዊ ጠቅላላ ገቢው ከብር 500,000 አስከ 1000,000 የሆነ አመታዊ ጥቅል ሽያጭ ነው፤ ደረጃ “ሐ” ደግሞ አመታዊ ጠቅላላ ገቢው እስከ ብር 500,000 ጥቅል ሽያጭ ያለው ነው፡፡
የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የንግድ ትርፍ ግብራቸውን የሚከፍሉት በሂሳብ መዝገብ መሰረት ነው፡፡ አንድ ግብር ከፋይ ለግብር አወሳሰን ያቀረበው የሂሳብ መግለጫዎችና ሰነዶች በግብር ሰብሳቢው መ/ቤት ከተመረመሩ በኋላ በመዝገቡ መሠረት ሊከፈል የሚገባው ግብር ይወሰናል፡፡ ግብር ሰብሳቢው መ/ቤት የግብር ምርመራውን /tax audit/ በዋናነት በአራት ስልቶች ይህም፡- በልዩ ምርመራ ኦዲት (Investigation audit)፣ በአጠቃላይ መርመራ /Comprehensive Audit/፤ በዴስክ ኦዲት /Desk Audit/ ወይም በውስን ምርመራ /Spot Audit/ ሊያከናውን ቢችልም፤ አንድ ግብር ከፋይ በሂሣብ ጊዜ ያቀረበውን የሂሣብ መግለጫዎችና ሰነዶችን ገቢ ሰብሳቢው መ/ቤት ትክክለኛነቱን የሚረጋገጠው ወይም ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውን የሂሳብ መዝገቦችና ሰነዶች ማስተካከያ የሚያደርገው በዴስክ ኦዲት /Desk Audit/ ምርመራ ነው፡፡
በመሆኑም የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በሂሳብ መዝገብ ያቀረብትን የንግድ ትርፍ ግብር መግለጫ የግብር ሰብሳቢው መ/ቤት ኦዲተር በዴስክ ኦዲት /Desk Audit/ የግብር ምርመራ ስልት በመጠቀም ከመረመረ በሃላ በግብር ከፋዩ ላይ የኦዲት ግኝቶች (Audit findings) ከተገኙ ግብር ከፋዩ ስለ ኦዲት ግኝቶቹ ዝርዝር ይዘት እንዲያውቀውና እንዲረዳው ማድረግና ግብር ከፋዩ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተባበል የሚያስችል ማስረጃ ካለው እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አገላለጽ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በሂሳብ መዝገብ ያሳወቁትን ግብር /Self-Assessment/ ግብር ሰብሳቢው መ/ቤት የዴስክ ኦዲት በመስራት ግብር ከፋዩ በተሠራው የዴስክ ኦዲት ላይ ሊታይለት የሚገባ ፍሬ ነገር ካለ ሐሳብና አስተያየት በማድመጥ ዕድል በመስጠት ግብር ሰብሳቢው መ/ቤት /Official assessment/ ኦዲት በመስራት ለግብር ከፋዩ ያሳውቃል፡፡
ነገር ግን በከተማ አስተዳደሩ አንዳንድ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በሂሳብ መዝገብ ያሳወቁትን ግብር የዴስክ ኦዲት በማድረግ ስለተገኘው የኦዲት ግኝትና በዚሁ መሠረት የተደረገ ማስተካከያ ለግብር ከፋዩ መግለጽ ሲገባቸው፤ ያለ በቂና አሳማኝ ምክንያት የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የንግድ ትርፍ ግብራቸውን በሂሳብ መዝገብ ሳይሆን፤ በግምት ግብር አወሳሰን ሦስት ስልቶች መካከል በተለይም በቀን ገቢ ግምት እንዲከፍሉ መደረጉ ከመመሪያው አንጻር ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ድርጊቱ ከግብር ከፋዩ አቅም በላይ ግብርና ታክስ በመጫን አላስፈላጊ የሆነ ገቢ እንዲሰበሰብ የሚያደርግ ነው፡፡
- መመሪያው የታክስ መሠረታዊ መርሆዎች የሚጥስ መሆኑ፤
የቀን ገቢ ግምት መመሪያ ቁጥር 123/2009 ግብርን በመዝገብ በሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ላይም ጭምር ተፈጻሚ እንዲሆን መደረጉ መመሪያው በአገራችን የታክስ ህግና ሥርዓት ውስጥ ተካተው የሚገኙት የታክስ መሠረታዊ መርሆችን መካከል በተለይም የመክፈል አቅም (Ability to pay) እና ፍትሃዊነት (equitability) የሚቃረን ነው፡፡
- የመክፈል አቅም (Ability to pay):- አንድ ግብር ከፋይ ግብር እንዲከፍል የሚገደደው ባገኘው ገቢ ልክ ብቻ ነው (tax only income) በህግ አግባብ መሰረት ከገቢ ግብር ነጻ ከተደረጉ ግብር ከፋዮች በስተቀር ማንኛውም ሰው ባገኛው ገቢ ልክ ግብር የሚጣልበት ሲሆን፤ የግብር ከፋዩ ገቢ እያደገ ሲሄድ በተመሳሳይ የግብር ማስከፈያ ምጣኔውም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
- ፍትሃዊነት (equitability):- ግብር የመክፈል አቅም ያለው ሁሉ እንደየአቅሙ ግብር እንዲከፍል ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሁሉም ግብር ከፋዮች ላይ የሚያርፈው የግብር ጫና እኩል ወይም ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ በግብር ከፋዮች መካከል በሚጣል ግብር እና የግብር ማስከፈያ ምጣኔ ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት መደረግ የለበትም፡፡
በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ አንዳንድ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በሂሳብ መዝገብ ያሳወቁትን ግብር ያለ በቂና አሳማኝ ምክንያት ግብራቸውን በሂሳብ መዝገብ ሳይሆን በቀን ገቢ ግምት እንዲከፍሉ ማድረጉ መመሪያ ቁጥር 123/2009 የሚጻረር እና የታክስ መሠረታዊ መርሆችን የሚቃረንና የግብር ከፋዮችን መሰረታዊ መብቶች የሚጥስ ከመሆኑም በተጨማሪ እነዚህ ግብር ከፋዮች የሂሳብ ሰነዶችን የመያዝ ግዴታ፤ ደረሰኝ የመጠቀም ግዴታ እና ተያያዥ ግዴታዎችን ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥረት ከንቱ የሚያስቀር ነው፡፡
5. የመፍትሄ ሃሳቦች፤
በቀን ገቢ ግምት መመሪያ ቁጥር 123/2009 በአንቀጽ 3 ላይ አማካይ የቀን ገቢ ግምት የሚጠናላቸው እና የማይጠናላቸው ግብር ከፋዮች በግልጽ ተለይተው የተቀመጡ በመሆኑ፤ የፌዴራል ግብር ከፋዮች በሙሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋይ ሆነው ግብር በመረጃ የሚወሰንላቸው ግብር ከፋዮች፤ በመደበኛ ቁጥር የሚወሰንላቸው ግብር ከፋዮች እና የጎዳና ንግድ እና ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግምት የማይጠናላቸው በመሆኑ የከተማው አስተዳደር በተለይም የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት በእነዚህ ግብር ከፋዮች ላይ መመሪያውን ተፈጻሚ ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው፡፡
ግብራቸውን መዝገብ የሚከፍሉ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ለግብር አወሳሰን የሚያቀርብትን የሂሳብ መዝገብና ሰነዶች የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ያለበቂና አሳማኝ ሕጋዊ ምክንያቶች የግብር አወሳሰን ዘዴውን ከሂሳብ መዝገብ ወደ ግምት ግብር አወሳሳን በመለወጥ ግብራቸውን በቀን ገቢ ግምት ግብር ወይም በመረጃ መሠረት በሚወሰን ግብር ወይም በቁርጥ በሚወሰን ግብር እንዲከፍሉ ማደረጉ የሕግ መሰረት የሌለው በመሆኑ፤ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የሚያቀርቡትን የሂሳብ መዝገቦች በዴስክ ኦዲት በመመርመርና በግኝቶች ላይ ለማስተባበል ዕድል በመስጠት በገቢያቸው ልክ ብቻ መወሰን አለበት፡፡
6. ማጠቃለያ
ደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ግብርን በሂሳብ መዝገብ መሰረት የመክፈል ጉዳይ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በሕግ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡ ግብርን በሂሳብ መዝገብ መሰረት መክፈል በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል ግብር ከፋዩ የሚያወጣቸው ወጭዎች በተቀናሽ እንዲያዝ ያግዛል፣ በገቢ ሰብሳቢው መ/ቤት እና በግብር ከፋዩ መካከል መተማመንን ይፈጥራል፣ ግብር ከፋዩ ገቢና ወጭውን አሰርቶ ስለሚቀርብ ፍትሀዊነት ያሰፍናል፣ ግብር ከፋዩ የግብር በዛብኝ ጥያቄዎችን ያስቀራል፡፡
ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይም አንዳንድ የወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤቶች የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮችን የንግድ ትርፍ ግብራቸውን በሂሳብ መዝገብ መሰረት ከማስከፈል ይልቅ ያለበቂና አሳማኝ ምክንያት እነዚህ ግብር ከፋዮች በቀን ገቢ ግምት መሰረት ግብር እንዲከፍሉ ማስገደዳቸው አማካኝ የቀን ገቢ መመሪያ ቁጥር 123/2009፤ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እና የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 የተጻረረ ነው፡፡