መግቢያ
አንድን የወንጀል ተግባር በሕግ አግባብ አጣርቶና መርምሮ ወደ ፍርድ ሂደቱ ለማስገባትና ውሳኔ ለማሰጠት አስቀድመው ከሚከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል የመጀመሪያው የወንጀል የምርመራ ሥራ ነው። በመሰረታዊነት የወንጀል የምርመራ ተግባርን የማከናወን ኃላፊነትና ሥልጣን የፖሊስና የዐቃቤ ሕግ መሆኑ ቢታወቅም በብዙ የሂደቱ ደረጃዎች ፍርድ ቤቶች ያላቸው ሚና ላቅ ያለ መሆኑም የሚታወቅ ነው። መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪውን በሕግ አግባብ መያዙን፣ ከያዘውም በኋላ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረቡን፣ የአቆያየት ሁኔታውን በተመለከተም በአግባቡ አይቶና መርምሮ ተገቢ ናቸው ያላቸውን ሕጋዊ ትዕዛዛትና የማስረጃ አሰባሰብ ጉዳዮችን (ለምሳሌ፡- የቀዳሚ ምርመራ፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዛት…) ኹሉ በበላይነት በመምራትና በመቆጣጠር የግለሰቦችንና የህዝብን መብትና ጥቅም የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው።
በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጊዜ ወይም ቅድመ ክስ ወቅት ጠርጥሮ የሚይዛቸውን ሰዎች አቆያየት በተመለከተ በፍርድ ቤቶች የሚደረገው ተሳትፎ የፍትሕ ሥርዓቱ የሕዝብን ጥቅም እና በዓለም፣ በአህጉርና አገር ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የታወቁ የተጠርጣሪ ሰዎችን መሰረታዊና ሥነ ሥርዓታዊ መብቶችና ነጻነቶች የሚያስከብር በመሆኑ የፍርድ ቤቶች ተሳትፎና ውጤታማነቱ ከፍተኛ ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤት እንደአንድ ዋነኛ የፍትሕ አስተዳደር አካልነቱ በወንጀል ምርመራ ወቅት የሚያደርገውን ይሄን መሰሉን ተሳትፎውን ሲያከናውን የሂደቱን ሕጋዊነት በማረጋገጥ ፍትሕን ከማስፈን፣ የሕዝብና የዜጎችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር በፍትሕ አስተዳደር ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባውን የግልጸኝነትና የተጠያቂነት አሰራር ለማረጋገጥ (check and balance) በማለም መሆኑም ሊዘነጋ የማይገባው ነው።
በዚህ ጽሁፍ (Article) ዓላማም በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች[2] በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ምን ምን ዓይነተኛ ተግባርና ኃላፊነት አሉባቸው፣ ፍርድ ቤቶች ከወንጀል ምርመራ ጋር ተያይዞ ተግባርና ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ በተግባር እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችስ ምንድን ናቸው የሚሉትን ፍሬ ጉዳዮች ከመረመረ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና በጉዳዬ ዙሪያ ተጨማሪ የክርክርና የውይይት መነሻ ነጥብ ለመፍጠር ነው። ጽሁፉ በሁለት ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን በመጀመሪያው ክፍል ‹‹በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በተለይም በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ምን ምን ዓይነተኛ ተግባርና ኃላፊነት አሉባቸው›› የሚለው የሚቀርብ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ‹‹የወንጀል ምርመራን ከመምራትና ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤቶች በኩል ምን ምን ችግሮች ይስተዋላሉ፣ ለችግሮቹ በመፍትሔነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሃሳቦችን›› የሚነሱበት ይሆናል።
- የወንጀል ምርመራ ምንነት፤ ትርጉም
የወንጀል ምርመራ ምንነትን በተመለከተ ብዙ ገለጻዎችና ብያኔዎች የተሰጡ ቢሆንም ከጽንሰ ሃሳቡ ሰፊነት የተነሳ የተሰጡት ትርጓሜዎችም በዚያው ልክ ሰፊና የተለያዬ ይዘት ያሏቸው ናቸው። ይሁን እንጅ ትርጓሜዎቹ በይዘት ደረጃ ብዙም ልዬነት የሌላቸው በመሆናቸው በዚህ ጽሑፍ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ የወንጀል ምርመራ ምንነቱን ከዓላማው ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው እንመለከተዋለን።
ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ የተባለው የሃሳብ ቋት ‹‹የወንጀል ምርመራ ወንጀሎች የሚመረመሩበት ወይም የሚጠኑበትና ወንጀለኞች የሚያዙበትን ሥነ ዘዴዎች የሚያመለክት›› ነው በማለት ይገልጸዋል። ብሪታኒካ ጨምሮም ‹‹የወንጀል መርማሪ በምርመራ ሥራው ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈጸመበትን መንገድ፣ ገፊ የመነሻ ምክንያቱን እና የወንጀለኛውን ማንነት እንዲሁም ደግሞ በወንጀሉ ተጎጂ (ተጠቂ) የሆነውን ሰው ማንነት የመለየትና ስለድርጊቱ አስረጂ የሆኑ ምስክሮችን የመፈለግና ቃላቸውን የመቀበል ተግባራትን የሚያከናውን›› ስለመሆኑ ይገልጻል።
ዊኪፒዲያ በበኩሉ የወንጀል ምርመራ ተግባራዊ ሳንይንስ መሆኑን ገልጾ በወንጀል ክርክሮች የሚቀርቡ ፍሬ ነገሮች የሚጠኑበት ክዋኔ እንደሆነ ያትታል። የተሟላ የወንጀል ምርመራ ብርበራን፣ ቃለመጠይቆችን፣ የምርመራ መጠይቆችን፣ ማስረጃ ማሰባሰብንና መጠበቅን እና የተለያዩ የምርመራ ሥነ ዘዴዎችን ማካተት ይኖርበታል። ዘመናዊው የወንጀል ምርመራ ተግባር ደግሞ ዘመኑ የደረሰባቸውን የምርመራ ዘዴዎች ወይም ቴክኒኮች በነሲብ ቃሉ ደግሞ የፎረንሲክ ሳይንስ ተብሎ የሚጠራውን አዘውትሮ የሚጠቀም ነው። የወንጀል ምርመራ ጥንታዊ ሳይንስ ሲሆን ከክርስቶስ መወለድ 1700 ዓ.ዓ በፊት በነበረው የሃሙራቢ ኮድ መነሻውን እንዳደረገ ይታመናል። የሃሙራቢ አዋጅ (ኮድ) ከሳሽና ተከሳሽ ሁለቱም የሰበሰቡትን ማስረጃ የማቅረብ መብት እንደነበራቸው ያሳያል። ዘመናዊው የወንጀል ምርመራ ተግባር ደግሞ በመንግስት የፖሊስ ዓባላት የሚከናወን ሲሆን የግል መርማሪዎችም በፖሊስ የሚደረገውን ምርመራ በማጠናቀቅ ወይም በመርዳት ይሳተፋሉ። ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ምርመራዎችን በበላይነት በመምራትና በመቆጣጠር በዋናነት የሚሳተፍ ሲሆን ፍርድ ቤቶችም ተጠርጣሪውን ጨምሮ ከሁለቱ አካላት በሚቀርብላቸው ጥያቄዎች በብዙ የሂደቱ ደረጃዎች ጣልቃ በመግባት ወሳኝ ተግባራትን የሚያከናወኑበት ሂደት ነው።
ከላይ ከተገለጹት ብያኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የወንጀል ምርመራ ተግባር አስቀድሞ የወንጀል ተግባር ስለመፈጸሙ ለመለየት፤ ወንጀል መፈጸሙ ከተለየ በኋላ ደግሞ የተፈጸመውን የወንጀል ዓይነት፣ የአፈጻጸሙን ሁኔታ፣ የፈጻሚውን ማንነት የሚያስረዱ ፍሬ ነገሮች ወይም ማስረጃዎች የሚሰበሰቡበት፣ የሚተነተኑበትና በመጨረሻም ለወንጀል ክስ መሰረታዊ የውሳኔ ግብዓት ሆነው የሚቀርቡበት ሂደት ነው።
- ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ተግባር ውስጥ ለምን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ይሳተፋሉ?
ከተፈጥሯዊ አደረጃጀታቸው አንጻር የፍርድ ቤቶች ዋነኛ ተግባር ለክርክር በሚቀርብ ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠት መሆኑ የሚታወቅ ነው። ፍርድ ቤት በተፈጥሮው ውሳኔ ሰጭ እንዲሆን ተደርጎ የተዋቀረ አካል ነው። ፍርድ ቤት በወንጀል ፍትሕ አስተዳዳር ውስጥ ከሳሽ የሆነው ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ የሚያቀርበውን ክስ መነሻ በማድረግና የሚቀርበውን ጉዳይም የተለያዩ የክርክር ደረጃዎችን እንዲያልፍ በማድረግ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ ይሰጣል። ይሁን እንጅ የፍርድ ቤቶች የተለመደ ተሳትፎ ከክስ መቅረብ በኋላ (up on trial) ቢሆንም ከቅድመ ክስ በፊት (pretrial) ወይም በወንጀል ምርመራ ወቅትም ደግሞ በብዙ ሁኔታዎች የሚሳተፉ መሆናቸው የተለመደ ነው። በተለይም ደግሞ አንግሎ አሜሪካን ወይም ኮመን ሎው ተብሎ የሚታወቀውን የሕግ ሥርዓት በሚከተሉ እንደ አሜሪካና እንግሊዝን በመሳሰሉ አገራት ፍርድ ቤቶች ከክስ በፊት ባለው የወንጀል ሙግት ሂደት ውስጥ በተደራጀ ሁኔታ የመሳተፍ ሕጋዊ ስልጣንን የተጎናጸፉ ናቸው። አኅጉራዊ ወይም ደግሞ ሲቪል ሎው ተብሎ በሚጠራውና ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጀርመን የመሳሰሉት አገራት በሚከተሉት የሕግ ሥርዓት ውስጥ ፍርድ ቤቶች በቅደመ ክስ የወንጀል ክርክሮች ውስጥ በብዙ ጉዳዮች ይሳተፋሉ። በአንጻራዊነት የሁለቱን የሕግ ሥርዓቶች ያካተተ እንደሆነ የሚታሰበው የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓትም ፍርድ ቤቶች በወንጀል ምርመራ ወቅት ወሳኝ ተሳትፎ እንዳላቸው በሕግ ተደንግጎ ይገኛል። እዚህ ላይ የሚነሳው መሰረታዊ ነጥብ ታዲያ ፍርድ ቤቶች በወንጀል ምርመራ ሂደት ለምን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ይሳተፉሉ? የሚለው ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ የውሳኔ ሰጭነት ስልጣናቸው ተሻግረው በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ለምንና እንዴት ይሳተፋሉ የሚሉትን ነጥቦች በተመለከተ ቀጥለን እንመለከታለን።
- ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ተግባር ውስጥ ለምን ይሳተፋሉ?
3.1 የሕዝብና የግለሰቦችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ፤
ከፍትሐብሄር ጉዳዮች በተቃራኒ የወንጀል ጉዳዮች የማኅበረሰቡን አጠቃላይ ሰላምና ደኅንነት በቀጥታ የሚነኩ ሲሆን የፍትሕ አስተዳደር አካላት የወንጀል ጉዳዮችን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ የሚያከናውኗቸው ተግባራት የግለሰቦችን መሰረታዊና ሥነ ሥርዓታዊ መብቶችና ነጻነቶች የሚጋፋ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። ፍርድ ቤቶች እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ ሕዝባዊ ተቋም የሚቀርብላቸውን ክርክር ተመልከተው ውሳኔ የሚሰጡት ውሳኔ እንዲሰጡ በሕግ ስልጣን ስለተሰጣቸው ብቻ አይደለም። በመሰረታዊነት ከላይ በተጠቀሰው አካኋን ከወንጀል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሕዝብን ጥቅም እንዲሁም ደግሞ በወንጀል ተግባር የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን መብትና ነጻነት ለማስከበር እንዲችሉ ነው።
ከላይ ስለወንጀል ምርመራ ምንነት ለመግለጽ እንደተሞከረው የወንጀል ምርመራ በአንድ ተፈጸመ ከተባለ የወንጀል ተግባር ጋር ተያይዞ በርግጥም ወንጀል ስለመፈጸሙ፣ ወንጀሉን የፈጸመውን ሰው ማንነት እንዲሁም በድርጊቱ ተሳትፏል የተባለን ሰው ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ወይም ደግሞ በተቃራኒው ስላለመፈጸሙ በፍሬ ነገር ለማረጋገጥ የሚደረግ ክንውን ነው። የወንጀል ምርመራ የማጣራት ሥራ እንደመሆኑ መጠን በሚደረገው ምርመራ ወንጀለኛውን አጣርቶ በመለየት ለፍርድ በማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ በማድረግ በአንድ በኩል ያለውንና በመንግስት የሚወከለውን የሕዝብ ጥቅምን ለማስከበር ጥረት ሲደረግ በሌላ በኩል ደግሞ የምርመራ ሂደቱ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ስህተትን በሚሰሩ ሰዎች የሚመራ በመሆኑ ሂደቱ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን መሰረታዊና ሥነ ሥርዓታዊ መብቶቻቸውን ሊጥስ የሚችል መሆኑ የሚጠበቅ ነው። ከዚያም ባሻገር የምርመራ ሂደት በሚገባ ካልተመራ ንጹኃን ሰዎች ጥፋተኛ የሚባሉበትና ከፍተኛ የሆነ የፍትሕ መዛባትን (miscarriage of justice) ሊያከትል እንደሚችልም የሚገመት ነው። በፍትሕ አስተዳደር ሂደቱ ያለአግባብ ጉዳት የሚደርስባቸውና ጥፋተኛ የሚባሉ ሰዎችን ከሂደቱ በአስቸኳይ የሚያስወጣና የሚክስ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ባልተዘረጋበት ኢትዮጵያን መሰል አገር ደግሞ የወንጀል ፍትሕ አስተዳዳር ክንዋኔዎች ከፍተኛ የሆኑ ጥንቃቄዎችን የሚሹ ናቸው።
ስለሆነም እነዚህን የመሰሉ መሰረታዊ ጉዳዮችን በሚያጠናቅረው የምርመራ ሂደት ውስጥ ከፖሊስና ከዐቃቤ ሕግ በተጨማሪ በአንጻራዊነት በአደረጃጀት አወቃቀሩም ገለልተኛ እንደሚሆን የሚታሰበው ፍርድ ቤት መሳተፉ ጠቃሜታው በእጅጉ ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። ባጭሩ በወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ ፍርድ ቤቶች የሚሳተፉበት አንዱ ምክንያት የሕዝብንና የግለሰቦችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።
3.2 ተጠያቂነትን፣ ግልጸኝነትን፣ ፍትሕንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፤
ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉበት ሌላው መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ በሦስቱ የመንግስት አካላት መካከል ሊኖር የሚገባውን ተቋማዊ የርስበርስ የተጠያቂነትና የግልጸኝነት አሰራር እንዲሁም ደግሞ ፍትሕንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ነው። ፍርድ ቤት ለብቻው የሚቆምና ሕግን የሚተረጉም የመንግስት አካል ነው። ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ደግሞ በሕግ አውጭው አካል የሚወጡትን የወንጀል ሕጎች የሚያስፈጽሙ የአስፈጻሚው አካል እጆች ናቸው። እነዚህ አካላት ከቆሙበት ምድብ አንጻር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ በተለይም ደግሞ የወንጀል ምርመራ ሂደቱ ሕግን ያከበረ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ እንዲሆን በማድረግ በኩል የተቀመጠላቸው የሕግና የአሰራር አካሄድ ያለ ቢሆንም የሥራ ክንውናቸው በርግጥም በተቀመጠላቸው ሕጋዊ አካሄድ መሰረት መከናወኑን ሊያረጋገጡ የሚችሉ ሌሎች የመንግስት አካላት አሉ። እነዚህም ፍርድ ቤትና የሕግ አውጭው አካል ናቸው። ለምሳሌ፡- በወንጀል ምርመራ ወቅት ፖሊስ በወንጀል የጠረጠረውን ሰው ከመያዙ በፊት የመያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት መጠየቅ አለበት። የተጠርጣሪውን የግል ይዞታ ለመበርበርና ንብረቶችን ለመያዝም እንዲሁ የፍርድ ቤት የፈቃድ ትዕዛዝ ያስፈልገዋል። የተጠርጣሪውን ሀብትና ንብረት ለማሳገድ እንዲሁ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያሻዋል። ፖሊስ በወንጀል ጠርጥሮ የያዘውን ሰው በያዘ በ48 ሰዓት ውስጥ አቅራቢው ወደሚገኝ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት። በእነዚህና በሌሎች የምርመራ ሂደቶች ውስጥ ፍርድ ቤት ጣልቃ የሚገባው የምርመራ ሂደቱ አፈጻጸም በሕግ አግባብ መከናወኑንና በዚህም በተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባውን የርስበርስ መጠያየቅ ለማረጋገጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ የሚያደርጉት የምርመራ ሥራ መሰረታዊ የሆኑትን የግለሰቦችን የነጻነት መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ የንብረት መብት፣ የግላዊነት መብትና በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የተቀመጡ ሥነ ሥርዓታዊ መብቶቻቸውን፤ ለምሳሌ፡- ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት፣ ተገደው ቃላቸውን ያለመስጠት መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ የተያዙበትን ምክንያት የማወቅ መብት፣ የዋስትና መብት፣ በታወቀ ቦታ የመቆየትና የመሳሰሉትን መብቶቻቸውን ሊጥሱ የሚችሉበት ዕድል በመኖሩ ሁለቱ የፍትሕ አስተዳደር አካላት ሥራቸውን ሲያከናውኑ በዘፈቀደ ሳይሆን በሕግ ብቻ እንዲሆን ፍርድ ቤት ያስገድዳቸዋል። ፍርድ ቤቱ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በምርመራ ሂደቱ ውስጥ ፍትሕን ሊያዛቡ የሚችሉ የምርመራ ተግባራትን ለመቆጣጠርና በዚህም ፍትሕን ለመጠበቅ ያስችለዋል። ለዚህም ነው ፍርድ ቤቶች በተለምዶ የፍትሕ ጠባቂ ዘብ (guardian of justice) እየተባሉ የሚጠሩት።
- ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ተግባር ውስጥ በምን በምን ሁኔታዎች ይሳተፋሉ?
4.1 የመያዣ ትዕዛዝ በመስጠት፤
ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ተግባር ውስጥ ከሚሳተፉባቸው ሂደቶች መካከል አንዱና ወሳኙ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን እንዲያዙ የመያዣ ትዕዛዝ በመስጠት ነው። በዓለም ዓቀፍ፣ በአህጉር አቀፍና በአገር ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የታወቀው የሰዎች የነጻነት መብት የወንጀል ጉዳይን በመሰሉ ልዩ ሁኔታዎች ጣልቃ የሚገባባት ቢሆንም ጣልቃገብነቱ በዘፈቀደና ያለበቂ ምክንያት እንዳይሆን የፍርድ ቤቶች ተሳትፎ ወሳኝነት አለው።
ስለሆነም ፖሊስ በወንጀል የጠረጠረውን ሰው ከመያዙ በፊት የመያዣ ትዕዛዝ እንዲሰጠው በቂ ምክንያቱን ገልጾ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት በማመልከቻ ሲጠይቅ ፍርድ ቤቱም ‹‹የምርመራ ሂደቱ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ አመቺነት ይረዳ ዘንድ›› ስሙ ተጠቅሶ የቀረበለት ተጠርጣሪ እንዲያዝ ለፖሊስ ፈቃድ ይሰጣል። ፍርድ ቤት ይህን የፈቃድ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ወቅት ሊረዳውና በተጨማሪነት እንዲሟሉ የሚያዛቸው ሁኔታዎችም አሉ። ከነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው።
ፍርድ ቤቱ የመያዣ ትዕዛዝ የሚሰጥበት ተጠርጣሪ በተጠረጠረበት ወንጀል ምክንያት ፍርድ ቤት መቅረቡ ፍጹም አስፈላጊና (የወንጀሉን ክብደት፣ ተጨማሪ ወንጀል የመፈጸም ዕድሉን መረዳት) በሌላ መልኩ ሊቀርብ የማይችል (ለምሳሌ፡- በመጥሪያ) መሆኑን ማመን፣ ተጠርጣሪውን የሚይዘው ፖሊስም የሚይዘውን ተጠርጣሪ በሚገባ እንዲያረጋግጥ፣ የመያዣ ትዕዛዙን ይዘት የፖሊስ መኮንኑ ለተጠርጣሪው እንዲያነብና ለማየት ሲጠይቅም እንዲያሳየው፣ ተጠርጣሪውን በሚይዝበት ወቅትም ሁኔታው ከሚጠይቀው በላይ የሆነ ኃይል እንዳይፈጽም እንዲሁም ደግሞ ፖሊስ የያዘውን ተጠርጣሪ ከያዘው በኋላ ሰብዓዊ መብቱንና ክብሩን ጠብቆ በያዘ በ48 ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲያቀርበው የሚገልጹ ትዕዛዛትን ይሰጣል። ከእነዚህ ትዕዛዛት ውስጥ አንዱ የሆነውን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብትን ብንመለከት የተያዘው/የታሰረው ሰው በዚህ ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረቡ የተያዘበትን ምክንያት የመጠየቅ፣ በአያያዝ ሂደቱ ወይም በቆይታው ያጋጠመው የመብት ጥሰት ካለ እሱን የመግለጽና መፍትሔ እንዲያገኝ የመጠየቅ፣ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለትና ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል እንዲፈቀድለት የመጠየቅ ዕድልን የሚፈጥር መሰረታዊ ጉዳይ ኾኖ እናገኘዋለን።
ከዚህ ፈቃጅ የመያዣ ትዕዛዝ በተቃራኒ በፖሊስ በኩል የቀረበው የመያዣ ትዕዛዝ ይሰጠኝ አቤቱታ በበቂና አሳማኝ ሁኔታ ተደግፎ ካልቀረበ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በወንጀል ምርመራ ውስጥ አንዱ ተግባር የሆነውን ተጠርጣሪውን የመያዝ ሂደት ላይ ከላይ በተገለጸው አግባብ የሚቀርብለትን የማስፈቀጃ አቤቱታ በሚገባ በመመርመር የሕዝብንና የግለሰቦችን መብትና ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችለውን ትዕዛዝ መስጠት ይኖርበታል ማለት ነው።
4.2 የጊዜ (የቀነ) ቀጠሮ ክርክሮችን በመምራትና በመቆጣጠር፤
ሌላውና ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ በሚገባ የሚሳተፉበት ሁኔታ በጊዜ ቀጠሮ ክርክሮች ወቅት ነው። በተለምዶ ‹‹የጊዜ ቀጠሮ›› እየተባለ የሚጠራው ተጠርጣሪውን አስሮ የመመርመር ሂደት ተጠርጣሪውን ግለሰብ ከውሳኔ በፊት እንዲታሰር የሚያደርግ፣ ነጻነቱን የሚገድብና ዘርፈብዙ ፍትሐዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያስነሳ ሂደት በመሆኑ የፍርድ ቤቶች ተሳትፎ አይተኬ ሚና ያለው ነው።
በጊዜ ቀጠሮ ወቅት አከራካሪ የሆኑትና ፍርድ ቤቶችም ዳኝነት የሚሰጡባቸው ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መሰረታዊ ጉዳች ውስጥ የመጀመሪያው ፖሊስ የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት ተጠርጣሪው ግለሰብ በምርመራ ሥራው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ያደናቅፋል ወይ የሚለው ነው። ይህን ጉዳይ በተለመከተ ፖሊስ ለጉዳዩ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን፣ የአሰባሰብ ሂደታቸውንና ተጠርጣሪው ግለሰብ ሊያደርግ የሚችለውን ተጠባቂ ጣልቃ ገብነት ሁሉ ተጨባጭና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ በመግለጽ ፍርድ ቤቱን ሊያሳምን ይገባዋል።
ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በሚያቀርበው አቤቱታ፣ ምክንያትና የማሳያ ማስረጃ ላይ የተጠርጣሪውን/የጠበቃውን አስተያየት ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የጊዜ ይፈቀድልኝ አቤቱታው ተቀባይነትን ካገኘ በሕግ በተቀመጠው መሰረት ለተጠየቀው ጉዳይ መፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ምክንያታዊ ጊዜ ወስኖ በመፍቀድ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ያዛል። ነገር ግን በፖሊስ በኩል የቀረበው ምክንያት በቂነት የሚጎድለው ከሆነ ማለትም አሳማኝነት የሌለው ከሆነ ደግሞ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን ይዘጋል። ተጠርጣሪው ግለሰብም የነጻነት መብቱን ለማስከበር የሚያስችሉትን የዋስትና ወይም ደግሞ የአካል ነጻ ማውጣት ጥያቄውን እንዲያቀርብ ዕድል ያገኛል ማለት ነው።
ፍርድ ቤቶች ይሄን ሂደት በሚገባና በልዩ ትኩረት ካልመሩት ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ እንዲበደሉ፣ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች እንዲጋለጡና ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ በፍትሕ አስተዳደር አካላቱ ላይ አመኔታ እንዲያጡ ያደርጋል።
4.3 ማስረጃ በማሰባሰብ፤
ፍርድ ቤቶች በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ከሚሳተፉባቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ሌላኛው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ ማስረጃ ማሰባሰብ ነው። ፍርድ ቤቶች ከዚህ ቀጥሎ በሚቀርቡት ሁኔታዎች መሰረት በፖሊስ ወይም በዐቃቤ ሕግ በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሰረት ቀዳሚ ምርመራ በማድረግ፣ የእምነት ቃል በመቀበል፣ የአካል/የሰውነት ምርመራ ፣ የብርበራ እና የዕገዳ ትዕዛዛትን በመስጠት ለወንጀል ጉዳዮች እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ ተግባራትን ያከናውናሉ። የእያንዳንዱን ጉዳይ ዝርዝር ቀጥለን እንመለከታለን።
4.4 ቀዳሚ ምርመራ በማድረግ፤
ቀዳሚ ምርመራ በወንጀል ጉዳዮች ላይ መደበኛ ክስ ከመቅረቡ በፊት በተጠርጣሪው ላይ ሊቀርብ የሚችለውን ክስና ክሱን ያስረዳሉ ተብለው የተለዩ ማስረጃዎች በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው የሚሰሙበት/የሚመዘገቡበት/የሚያዙበትና ግልባጩ ለሚመለከተው ዐቃቤ ሕግ/ፍርድ ቤት የሚሰጥበት ሥነ ሥርዓታዊ ክንውን ነው። ቀዳሚ ምርመራ በዋና ክርክር ወቅት ለሚደረገው የፍሬ ነገር አቀራረብ እንደዋና አስረጅ ፍሬ ነገር ኾኖ ሊቀርቡ የሚችሉ ማስረጃዎች እንዳይጠፉ፣ እንዳይበላሹ፣ እንዳይሸሹና በተለያዩ ምክንያቶች በማስረጃነት እንዳይቀርቡ ከሚያደርጉ ተግባራት ለመከላከል የሚያስችል የማስረጃ መጠበቂያ ተግባር በመሆኑ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ትኩረትን የሚሻ ነው።
ልክ እንደመደበኛው የወንጀል ክርክር ወይም ሙግት ፍርድ ቤቱ በዚህ የክርክር ሂደት ወቅት ከሳሽ ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ (ከጠበቃው ጋር) የሚያደርጉትን የፍሬ ነገር ክርክር በሥነ ሥርዓት ሕጉ በተቀመጠው አግባብ በመምራት ማከናወን ይጠበቅበታል። ቀዳሚ ምርመራውን የሚያከናውነው ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ይዘት ሕጋዊነት በመመርመርና ማስተካከያም ካስፈለገ ያንኑ እንዲከናወን ተገቢውን ትዕዛዝ በመስጠት፣ የምስክር አሰማም ሂደቱን በተለይም የዋና ጥያቄ፣ የመስቀለኛ ጥያቄ፣ የድጋሜና የማጣሪያ ጥያቄዎችን አቀራረብ እንዲሁም ደግሞ የተከሳሹን ቃል አሰጣጥ ሕጉን የተከተሉ፣ ግልጽና እውነትን/ፍትሕን ለመስጠት በሚያስችሉ አኳኋን ማስፈጸም ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት በዚህ የክርክር ሂደት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በነጻ የማሰናበት ውጤት ያለው ውሳኔ የማይሰጥበት ቢሆንም ከላይ እንደተገለጸው በኋላ ላይ ስልጣን ባለው አካል በሚቀርበው ክስ የፍሬ ነገር ክርክሩ ግልባጭ በሙሉ ወይም በከፊል ቀርቦ የሚመረመርና ለፍርድ አሰጣጥ ወሳኝ በኾነ ሁኔታ የሚረዳ በመሆኑ ሂደቱን ከሕዝብና ከግለሰቦች መብትና ጥቅም እንዲሁም ደግሞ ፍትሕን ከመጠበቅ አንጻር ተመልክቶ በሚገባ መምራትና መቆጣጠር ያስፈልጋል።
4.5 የእምነት ቃል በመቀበል፤
ፍርድ ቤቶች በወንጀል ምርመራ የማስረጃ አሰባሰብ ወቅት የሚሳተፉበት ሌላኛው ተግባር ደግሞ የተጠርጣሪውን ቃል ወይም የእምነት ቃሉን በመቀበል ነው። ፖሊስ በወንጀል ተግባር ጠርጥሮ የያዘውን ሰው በሥነ ሥርዓት ሕጉ በተቀመጠው አካሄድ መሰረት የተከሳሽነት ቃሉን ከተቀበለው በኋላ የሚሰጠው ቃል የቀረበበትን የወንጀል ተግባር በማመን ከኾነ የእምነት ቃሉ በፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ በድጋሜ መሰጠት የሚኖርበት በመሆኑ ፖሊስ በተጻፈ ማመልከቻ ተጠርጣሪው የእምነት ቃሉን እንዲሰጥለት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ያቀርበዋል። ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን ማመልከቻ ይዘት ሕጋዊነት (የእምነት ቃሉና የተጠቀሰው ድንጋጌ መጣጣሙን) የመመርመር፣ ተጠርጣሪው ቃሉን ያለመስጠት መብት ያለው መኾኑን፤ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ከኾነም በሚሰጥበት ወቅት በፍጹም ነጻ ፈቃዱ (ሳይገደድ፣ ፈልጎና ውጤቱን አውቆ) መሆኑን እንዲሁም የሚሰጠው የእምነት ቃል በቀጣይ በሚቀርብብት ክስ በማስረጃነት ሊቀርብብት እንደሚችል በአግባቡ የማስገንዘብ ሥራዎችን ኹሉ ይፈጽማል።
በተጠርጣሪው የሚሰጠው የእምነት ቃል ወይም ቃል በኋላ ላይ በምርመራ መዝገቡ ላይ በዐቃቤ ሕግ ለሚሰጥ ውሳኔም ኾኘ በፍርድ ቤት ለሚቀርብ ክስ በታማኝነት ደረጃው ከፍ ያለ አስረጅ ፍሬ ነገር ኾኖ የሚቀርብ በመሆኑ በፍርድ ቤቱ የሚመዘገበው የእምነት ቃል ወይም ቃል ይዘት በሕግ እንዲሟሉ የተቀመጡትን ሥነ ሥርዓታዊ የመብት ጥበቃ ሁኔታዎችን (procedural safeguarding) የያዘ፣ ቃሉም ግልጽና ዝርዝር መኾን ይጠበቅበታል። የእምነት ቃሉ ወይም ቃሉ ግልጽና ዝርዝር እንዲሆን ለማድረግ ሲባል ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ የማብራሪያ ጥያቄዎችን በሚገባ መጠየቅና መመዝገብ ይኖርበታል። ስለሆነም የተጠርጣሪውን የእምነት ቃል መቀበል የተዘጋጀ ፎርምን ሞልቶ ተጠርጣሪውን አስፈርሞ መዝገቡን በግብር ይውጣ ከመዝጋት ያለፈ እጅግ ጠቃሚ ተግባር መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል።
4.6 የብርበራ ትዕዛዝ፤
ከወንጀል ምርመራ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤቶች ከሚደረጉ ተግባራት ሌላኛው ደግሞ የብርበራ ትዕዛዝ መስጠት ነው። የብርበራ ትዕዛዝ ሊፈጸም በዝግጅት ላይ ባለ ወይም ተፈጸመ ከተባለ የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ ለወንጀሉ መፈጸሚያነት ያገለገሉ ወይም የወንጀል ፍሬ የኾኑ ቁሶችን ወይም ንብረቶችን ለመያዝና በሚቀርበው የወንጀል ክስ ገላጭ ማስረጃ ለማድረግ በማሰብ ቁሶቹ ወይም ንብረቶቹ ከባለቤቱ/ባለይዞታው እጅ ወጥተው በፍርድ ቤት እንዲቀመጡ ለማድረግ የሚያስችል ትዕዛዝ ነው። ይህ ትዕዛዝ በግለሰቦች የንብረት መብትና የግላዊነት መብት (right to privacy) ላይ ጣልቃ መግባትን የሚያስከትል በመኾኑ በፍርድ ቤቱ የሚሰጠው የብርበራ ትዕዛዝ በጥብቅ የአፈጻጸም ቅድመና ድህረ ሁኔታዎች የታጠረ ነው። የሚበረበረው ቤት፣ ቦታ ወይም ይዞታ የተጠርጣሪው መኾኑን፣ በብርበራ የሚያዘውን ቁስ/ንብረት ዓይነትና ብዛት፣ ብርበራው የሚደረግበት ጊዜ፣ የብርበራው ውጤት ሪፖርት አደራረግና የመሳሰሉት ጉዳዮች ኹሉ በትዕዛዝ ሰጪው ፍርድ ቤት ትኩረት የሚደረግባቸው ሁኔታዎች ናቸው።
4.7 ልዩ የምርመራ ዘዴዎች እንዲከናወኑ መፍቀድ፤
ከወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ የፍርድ ቤቶችን ጣልቃ ገብነት ከሚጠይቁ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ሌላኛው ደግሞ ልዩ የምርመራ ዘዴዎች እንዲከናወኑ ትዕዛዝ መስጠት ወይም መፍቀድ ነው። ከስማቸው እንደምንረዳው ልዩ የምርመራ ዘዴዎች አፈጻጸማቸውና ውጤታቸው ከመደበኛው የወንጀል ምርመራ ሥነ ሥርዓት የተለዩ ናቸው። ዘዴዎቹ የግለሰቦችን የግላዊነት መብት፣ ግንኙነትና እንቅስቃሴ በስውር በመከታተል ማስረጃ የሚሰበሰብባቸው አሰራሮች ናቸው። አሰራሮቹ የግለሰቦችን የግላዊነት መብትና ነጻነት የሚጥሱ በመሆናቸው አፈጻጸማቸው በዘፈቀደ ሳይኾኑ በበቂ ምክንያት ተደግፈው በፍርድ ቤት ፈቃድ ብቻ የሚከናወኑ ናቸው። በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እነዚህን መሰል ልዩ የምርመራ ዘዴዎች የደነገጉ አዋጆች ያሉ ሲሆን በተለይም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ስለልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን የያዘ ኾኖ እናገኘዋለን። ስለኾነም ፍርድ ቤቶች እነዚህን መሰል ልዩ የምርመራ ዘዴዎች እንዲከናወኑ በፖሊስ በኩል የፈቃድ ጥያቄ በማመልከቻ ሲቀርብላቸው ጉዳዩን በሚገባ በመመርመር አስፈላጊነቱን ካመኑበት ከዘዴዎቹ አንዱ ወይም ሌላኛው ተፈጻሚ እንዲኾን ትዕዛዝ የሚሰጡ ሲሆን አስፈላጊነቱ አሳማኝ ካልኾነ ደግሞ ማመልከቻውን ውድቅ ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው። ፍርድ ቤቶች ልዩ የምርመራ ዘዴዎች እንዲከናወኑ ለፖሊስ የሚፈቅዱ ከኾነ ስለምርመራ ዘዴዎቹ አፈጻጸም፣ ስለማስረጃዎቹ አሰባበሰብ/አያያዝና አቀራረብ ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ዝርዝር የአፈጻጸምና የክትትል ተግባራትን ማከናወን ይኖርባቸዋል።
4.8 የእግድ ትዕዛዝ መስጠት፤
በወንጀል ምርመራ ወቅት ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ተያያዥ የኾኑ በተለይም የወንጀል ፍሬ የኾኑ ወይም ደግሞ በወንጀል ድርጊቱ ለደረሰው ጉዳት ካሳ ሊሆኑ የሚችሉ የተጠርጣሪው ንብረቶች እንዳይሸጡ ወይም እንዳይለወጡ ወይም በዕዳና በዕገዳ እንዳይያዙ ወይም እንዳይሸሹ ወይም የሌላ ወንጀል ፍሬ እንዳይሆኑና ምናልባትም እንዳይወድሙ ሲባል ታግደው እንዲቆዩ (እና አስፈላጊም ሲሆን በአስተዳዳሪም ጭምር እንዲጠበቁ) የሚያስችለውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤት ይሰጣል። ይህ ትእዛዝ ልክ እንደብርበራ ትዕዛዝ ኹሉ በግለሰቦች የንብረት መብት ላይ ጣልቃ መግባትን የሚያስከትልና እገዳው የሚተላለፍበትን ተከሳሽ አስተያየት ሳያካትት በአንድ ወገን በሚቀርብ አቤቱታ የሚሰጥ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የዕገዳ ትዕዛዙን በሚሰጥበት ጊዜ አመልካቹ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ የሚያቀርበውን አቤቱታ አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንጻር በሚገባ መመርመር ይኖርበታል። ይሄን የመሰለው በሌላ ሰው ሀብትና ንብረት ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ሰዎች በንብረት መብታቸው ላይ እንዳይጠቀሙበት የሚገድብ ወይም የሚከለክል በመሆኑ በፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ትዕዛዝ የማይታገዱ ንብረቶችን እንዳያካትት (ዕግዱ የሚሰጥበትን ገንዘብ መጠን ጨምሮ)፣ ያለበቂ ወይም ተጨባጭ ምክንያት እንዳይሰጥ በተለይም ደግሞ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት የሌላቸውን ሦስተኛ ወገኖች መብትና ጥቅም ያለአግባብ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። በሌላ አነጋጋር ፍርድ ቤቱ የእግድ ትዕዛዙ አሰጣጥና አፈጻጸም የሰዎችን መሰረታዊ የኑሮ ፍላጎት በማይገድብና የሀብት መፈጠርንና አስተዳደርንም በማይከለክል አኳኋን ከፍ ሲል የተጠቀሰውን ዓላማ ለማሳካት በሚያስችል መንገድ ብቻ እንዲከናወን ማድረግ አለበት።
4.9 የዋስትናና አካልን ነጻ የማውጣት (habeas corpus) ክርክሮችን አስደርጎ ውሳኔ በመስጠት፤
ፍርድ ቤቶች በወንጀል ምርመራ ወቅት ከሚሳተፉባቸው ወሳኝ ተግባራት መካከል የዋስትናና አካልን ነጻ የማውጣት ክርክሮችን አስደርጎ ውሳኔ መስጠት ነው። በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በሕግ አግባብም ሆነ ከሕግ ውጭ በሆነ ሂደት የተያዙ/የታሰሩ ሰዎች መሰረታዊ የሆነውን የነጻነት መብታቸውን የሚያጡ በመሆናቸው የተያዙት ሰዎች ራሳቸው ወይም ጠበቆቻቸው በሚያቀርቡት የአቤቱታ ማመልከቻ (ክስ) መነሻነት ፍርድ ቤቶች የግራቀኙን ተከራካሪዎች ክርክር መርምረው ተገቢ ነው ያሉትን ውሳኔ ይሰጣሉ። ከእነዚህ ውሳኔዎች ውስጥ ሁለቱ መሰረታዊ ጉዳዮች የዋስትና መብትና አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ዋነኞቹ ናቸው። ጉዳዮች ነጣጥለን እንመልከታቸው።
ሀ) የዋስትና ክርክር፤
በወንጀል ምርመራ ወቅት ከሚነሱና የፍርድ ቤትን ውሳኔ ሰጪነት ከሚጠብቁ ጉዳዮች አንዱ የዋስትና ክርክር ነው። የዋስትና ክርክር ተጠርጣሪው ግለሰብ ከተከሰሰበት የወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለወደፊቱ በሚኖረው የክርክር ሂደት ባለመቅረብ የፍርድ ሂደቱን እንዳያሰናክል ግለሰቡን በተወሰኑ የሁኔታ ግዴታዎች መሰረት ከእስራት እንዲለቀቅ በሚቀርበው ክርክር ላይ የአመልካቹን የዋስትና መብት በመፍቀድ ወይም በመከልከል የሚሰጥ ውሳኔ ነው። ይህ ክርክር በአንድ በኩል በተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊት የተነሳ ሰላሙና ደኅንነቱ የተናጋውን የማኅበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተጠርጣሪውን ግለሰብ የነጻነት መብት ለማስጠበቅ የሚደረግ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከእነዚህ መሰረታዊ ጥቅሞችና አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንጻር መርምሮ ውሳኔውን ይሰጣል።
በነዚህ የሕጉ ንዑስ ድንጋጌዎች መሰረት በዋስትና ወረቀት ያልተለቀቀ ተከሳሽ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 64 በተቀመጠው መሰረት በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱን ለመጠየቅ ይችላል። ፍርድ ቤቱም በዋስትና ለመለቀቅ የሚቀርበው ማመልከቻ ሲደርሰው ማመልከቻውን ያለ መዘግየት ወዲያውኑ በማየትና ስለጉዳዩ የሚመለከተውን ዐቃቤ ሕግ ወይም ፖሊስ አስተያየት እንዲሰጥ በማድረግ ውሳኔውን በ48 ሰዓት ውስጥ መስጠት አለበት። በዋስትና ክርክር በፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ አመልካቹን በዋስትና የመለቀቅ ከኾነ የትዕዛዙን መፈጸም በሚገባ መከታተልና ማረጋገጥ ይኖርበታል። የክርክሩ ውጤት በተቃራኒው የተጠርጠሪውን የዋስትና መብት የሚከለክል ከኾነ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቂ መሰረታዊ አገልግሎቶች በሚገኙበትና ከማረሚያ ቤት ውጭ ወደኾነ ሕጋዊ የማረፊያ ቤት እንዲወስደው ማድረግ ይኖርበታል። ፍርድ ቤቱ ልክ እንደፈቃጅ ትዕዛዙ ሁሉ በዚህ ውሳኔ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተፈጻሚነትም መከታተል ይኖርበታል።
ለ) አካልን ነጻ የማውጣት ክስ (Habeous Corpus) ፤
አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ሕገ ወጥ እስርን ለመቆጣጠር ሲባል የፍትሐብሄር ክስ በፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ የሚሰጥበት የክስ አቤቱታ ነው። ፍርድ ቤቱ ልክ እንደዋስትና ክርክር ኹሉ በተጠርጣሪው ወይም በጠበቃው አማካኝነት የሚቀርብለትን የክስ ማመልከቻ ከተቀበለ በኋላ ተጠርጣሪውን የያዘውን አካል በቀረበው ክስ ላይ ያለውን አስተያየት እንዲሰጥ በማስደረግ ጉዳዩን መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጣል። በዚህ ክርክር በፍርድ ቤቱ የሚያዘው መሰረታዊ ጭብጥ የአመልካቹ ‹‹የእስር ሕገወጥነት›› ጉዳይ ነው። ለፍርድ ቤቱ በሚቀርበው ማመልከቻና ማስረጃ መሰረት ተጠርጣሪው/ግለሰቡ የታሰረበት ሂደትና አግባብ በሕግ ከተቀመጡ መብቶችና ነጻነቶች እንዲሁም የአፈጻጸም ሥነ ሥርዓቶች በተቃራኒ ከኾነ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ወይም ግለሰቡ ከተያዘበት ወይም ከታሰረበት እንዲለቀቅ የሚያስችለውን ውሳኔና የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ ይሰጣል። የትዕዛዙን አፈጻጸምም ይከታተላል። በፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ ከላይ ከተገለጸው በተቃራኒ ከኾነም መዝገቡ ላይ ምክንያቱን ገልጾ ውሳኔውን ይሰጣል።
4.10 የወንጀል ምርመራ እንዲጣራ ትዕዛዝ መስጠት እና የሕሊና ካሳ መወሰን፤
በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በሕግ ተደንግገው ለፍርድ ቤቶች ከተሰጡ አዳዲስ ስልጣኖች ውስጥ የወንጀል ምርመራ እንዲጣራ ትዕዛዝ መስጠትና የሕሊና ካሳ መወሰን የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው። በ2012 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የሽብር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ፍርድ ቤቶች በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘው/የተሰሰሰው ሰው ከአያያዙ ጋር በተያያዘ በሚያነሳው የመብት ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት መመርመር እና ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ አግባብነት ያለውን ትዕዛዝ መስጠት እንዳለባቸው ይደነግጋል። አዋጁ በአንቀጽ 41(3) መሰረት ‹‹ፍርድ ቤት በወንጀል ክርክር ሂደቱ የሕግ አስፈጻሚ አካላት የሕግ ጥሰት የፈጸሙ መሆኑን ያረጋገጠ እንደሆነ የወንጀሉ ጉዳይ እንዲጣራ ትእዛዝ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስጠይቅ ካልሆነ በስተቀር ጥሰት የፈጸመው ሰው ወይም ተቋም ለተጎጂው ከአስር ሺህ ብር እስከ መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የህሊና ጉዳት ካሣ እንዲከፍል በያዘው የክርክር መዝገብ ለመወሰን እንደሚችል›› ስልጣን ተሰጥቶታል። የህሊና ጉዳት ካሳው አወሳሰን ልክ እንደችሎት መድፈር የቅጣት አወሳሰን በአመልካቹ ክስ መቅረብን የማይጠይቅና ማስረጃዎቹም እንዲሁ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ፣ ግንዛቤና መረዳት የሚቀርቡና የሚመረመሩ መሆናቸው የሕጉን ተፈጻሚነት ቀላል የሚያደርግ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል።
4.11 ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብ ትዕዛዝ መስጠት፤
በዘመናዊ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እድገት ውስጥ ከተዋወቁና በግራቀኙ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ያለውን የማይመጣጠን የኃይል አሰላለፍ (inequality of arms) ለማስታረቅ ከሚረዱ አስቻይ የተከሳሽ ሥነ ሥርዓታዊ መብቶች ውስጥ በተከላካይ ጠበቃ የመታገዝ መብት ዋነኛው ነው። ይህ መብት ከፍተኛ የሕግ ሙያ ክህሎትና ልምድ ያላቸው ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ የሕግ እውቀት ከሌለው ተከሳሽ ጋር በፍርድ ቤት ፊት የሚያደርጉት የሕግና የፍሬ ነገር ክርክር ሊፈጥረው የሚችለውን የፍትሕ መዛባት ለመከላከል የሚያስችል ነው። የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ይህን መብት በዝርዝር የሕግና የአፈጻጸም አካሄድ በሚገባ ከማስጠበቅ አንጻር በጉልህ የሚታዩ ክፍተቶች፤ ለምሳሌ፡- ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ወሳኝ የሆነውን የቅድመ ክስ/ክርክር (የወንጀል ምርመራ ሂደት) ወቅት አለማካተቱ፣ በአፈጻጸም ረገድም በውስንና በፍርድ ቤቶች ‹‹ከባድ›› ተብለው በሚለዩ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ብቻ ተግባራዊ መደረጉና መብቱም በፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ ብቻ የሚከናወን መሆኑ ተከሳሾች መብቱን በተሟላ ሁኔታ እንዳይጠቀሙበት ሊያደርግ የሚችል ቢሆንም ፍርድ ቤቶች መብቱን ለማስጠበቅ በሚያስችል አግባብ በተለይም በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሰረት ከተጠበቁ የተከሰሱ ሰዎች መብቶች አንጻር ክርክሮችን በመመልከት የተጠረጠሩ ሰዎች በወንጀል ምርመራ ወቅትም በጠበቃ የመታገዝ መብታቸው እንዲከበርላቸው/እንዲሟላላቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።