መጠይቅ ደግ ነው፡፡ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባራትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16(6) ፍትሕ ሚኒስቴር በቂ ምክንያት ሲኖር በሕግ መሠረት ሂደት ላይ ያለን ክስ ያነሳል በሚል ይደነግጋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጠው ክስ የማንሳት ሥልጣን እስከምን ድረስ ነው? ክስ ማንሳት በማንኛውም ጊዜ ይቻላል? ክሱን ሲያነሳስ በቂ ምክንያቱን ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል? በቂ ምክንያትስ የምንለው ምንድን ነው? የክስ መነሳትስ ተከሳሾች ላይ ያለው ውጤት ምንድን ነው? በዚህ ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚና ምን መሆን ይገባዋል? የሚለው ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ነው፡፡
ክስ ማንሳት ለምን?
ፍትሕ ሚኒስቴር ከሳሽ አካል እንደመሆኑ ወንጀል ጉዳይ ተፈፅሟል ብሎ ሲያመን ክስ እንደሚመሰርተው ሁሉ ምክንያት ሲኖረው ክሱን ሊያነሳ እንደሚችል በአዋጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ክስ የሚነሳባቸው ምክንያቶች በሕግ ተዘርዝረው ያልተቀመጡ በመሆናቸው ለክርክር ምክንያት መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ክስ ለማንሳት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ በአንድ በኩል ቀጥታ ከክሱ ጋር በተገናኘ ቀጥተኛ ምክንያት ሲሆን ሕጋዊ ምክንያት በማለት ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ በሌላ በኩል ከክሱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ፖለቲካዊ ምክንያት ነው፡፡ ሕጋዊ ምክንያት የምንለውን ከስሩ የሕግ ፍልስፍና ስናስበው ነፃ ሰው ጥፋተኛ እንዳይባል ወይም ወንጀል አድራጊ መቀጣት እያለበት ከሕግ እንዳያመልጥ የሚቀርብ ነው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ቀጥታ ከሳሹ አካል ከሚያቀርባቸው ማስረጃ ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ከሳሽ ማስረጃ በደንብ ወይም በአግባቡ ካለመሰብሰቡ በትክክል ወንጀል የሠራ ተከሳሽ ነፃ ሊባል የሚችልበት ሁኔታ ስለሚኖር ማስረጃ አሰባሰብ ላይ እርምት በማድረግ ለዳግም ክስ ለመዘጋጀት ትንፋሽ መግዣ ነው፡፡ ልብ ልንለው የሚገባው ክስ የሚነሳው ፍርድ ከመስጠቱ በፊት በመሆኑ ዳግም ክስ ከማቅረብ የሚከለክል አይደለም፡፡ ክስ ማንሳት ከዳግም ክስ ካልገደበ ከሳሽ ጎደለ የሚለውን ማስረጃ እንደገና ለማጠናከር እንዲያውም ክሱ ከተጀመረ በኋላ ማስረጃ ይሆነኛል የሚለው አዲስ ማስረጃ የተገኘ ሲመስለው ክሱን አንስቶ እንደገና ክንዱን አፈርጥሞ ለመመለስ መሽሎኪያ የሚሆነው መንገድ ነው፡፡ በተጨማሪም ነፃ ሰው ባልሠራው ወንጀል ጥፋተኛ እንዳይባልም ክስ ለማንሳት መነሻ ምክንያት ይሆናል፡፡ ነፃን ሰው ለማዳን ክስ ለማንሳት የሚበረቱት እንኳ አንድ ነፃ ሰው ጥፋተኛ ከሚባል ሺህ ወንጀለኞች ቢያመልጡ ይሻላል የሚል መርህ ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡
ሁለተኛውንና ፖለቲካዊውን ምክንያት እንመልከት፡፡ በሃገሪቱ የመንግሥት አካላት አወቃቀር ከሳሽ የሆነው ፍትሕ ሚንስቴር አደራጃጀቱ በአስፈፃሚው ክንፍ ሲሆን ከሕግ ተቋምነቱ ፖለቲካዊ ተቋምነቱ ይጎላበታል ለማለት ይቻላል፡፡ በሃገሪቱ ሁለት ዓይነት ተከሳሾች አሉ በማለት መፈረጅ ይችላል፡፡ እንዲቀጡ የሚፈለጉ ስህተት የሚፈልግባቸው እና እንዲቀጡ የማይፈለጉ ስህተት የሚደበቅላቸው በማለት መክፈል ነገሩን ግልፅ ያደርገዋል፡፡ ለጊዜው ስህተት የሚደበቅላቸውን እንመልከት፤ እነዚህ በአብዛኞቹ የመንግሥት ሹመኞች እንደመሆናቸው የእለት ውሏቸው ሆነ የህይወት ዳራቸው በወንጀል የተጨማለቀ ነው፡፡ ከሳሹ አካል ስለወንጀላቸው ማስረጃውን አሰባስቦ ክስ ቢመሰርት በመንግሥት ላይ የሚያስነሳውን ተቃውሞ በመመልከት አስፈፃሚው ረጅም እጁን ሰዶ ክስ ለማስቆም ይቻለዋል፡፡ ይሄ የውስጥ ገፅታን ከመጠበቅ የሚደረግ ክስ የማንሳት ሂደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ምክንያት የተከሰሱ ሰዎች ካላቸው የሕዝብ ተቀባይነት እና ዓለም ዐቀፍ ታወቂነት አንፃር የሚታይ ነው፡፡ መንግሥት የውጪ ገፅታውንም መጠበቅ ስለሚፈልግ የሕዝብ ተቀባይነት እና ዓለም ዐቀፍ ታዋቂነት ያላቸውን ሰዎች ክስ በማቋረጥ የክስ ማንሳቱን ምክንያት ፖለቲካዊ ያደርገዋል፡፡
የክስ ማንሳት ገደብ?
ሂደት ላይ ያለን ክስ ማንሳት ፍትሕ ሚኒስቴር አዋጅ ያጎናፀፈው ሥልጣን ቢሆንም ለሁሉም ሥልጣን ልጓም አለው፡፡ የተከሳሾች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም የፍርድ ቤቶች ሥልጣን በልጓምነት የተቀመጠ ቢሆንም እሱም አከራካሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ የክስ ማንሳት አንዱ ልጓም የተከሳሽ መብት ነው፡፡ ክስ የሚነሳው ከፍርድ በፊት ነው ሲባል ክስ የሚያነሳው አካል ስለፈለገ ብቻ ክስ ማንሳት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ማስረጃ ተከሳሽ ጥፋተኛ አይባልም ብሎ ባሰበ ቁጥር ክስ ላንሳ በማለት ቢቀርብ አሳማኝ የተከሳሽን ነፃ የመባል መብት የሚጋፋ ይሆናል፡፡ ሲጀመር አንድ ሰው ክስ ሊቀርበብበት የሚገባው በቂ ማስረጃ ሲገኝበት ነው፡፡ በቂ ማስረጃ አለ ተብሎ ክስ የቀረበበት ወገን የተፋጠነ ፍትሕ ሊሰጠው የሚገባ በጊዜ ውሳኔውን አውቆ ምን ይፈረድብኝ ይሆን ከሚል ስጋት እና ቀውስ ለማዳን ነው፡፡ ሆኖም ግን አንድ ሰው በቂ ማስረጃ ቀርቦበታል ተብሎ ከተከሰሰ በኋላ ክሱ ቢነሳ ዳግም አዲስ ክስ ከማቅረብ የማያግድ እስከሆነ ድረስ ተከሳሹን የባሰ ስጋት እና ሰቀቀን ውስጥ ሊጥል ይችላል፡፡
በዚህም ምክንያት ክስ ሊነሳ የሚገባው ለጊዜው ተከሳሹ ክስ በመቋረጡ የሚያገኘውን ከእስራት መፈታት እና ክስ መቆም ሳይሆን ዘላቂ ዋስትና በሚሰጥ ሁኔታ ነው፡፡ ሌላው ክስ የሚነሳው በሁሉም ወንጀሎች ላይ አለመሆኑን ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ስለክስ ማንሳት ዐቃቤ ሕግ ከባድ የግፍ አገዳደል እና ከባድ ወንበዴነት ተግባር ከተከሰሰ ሰው ውጪ በፍርድ ቤት ፈቃድ ክሰ ሊያነሳ እንደሚችል ይናገራል፡፡ እንግዲህ የቀድሞውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት አድርጎ የወጣው እና አሁንም በሥራ ላይ ያለው ሥነ ሥርዓት ሕግ ክስ ሊነሳባቸው የማይችሉ ወንጀሎች ያሉ መሆኑን ያስቀመጠበት ምክንያት ከወንጀሎች ከባድነት እና ክስ ማንሳቱ በተከሳሾች ላይ ሊኖረው ከሚችለው ውጤት አንፃር መሆኑን የሕግ አውጭውን ዓላማ በመረዳት መልሱን ማግኘት ይችላል፡፡ ክስ የማንሳቱ ገደብ በወንጅሉ ክብደት መለየቱ ከሳሹ አካል በከባድ ወንጀሎች ክስ ከመመሥረቱ በፊት በቂ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በተዘዋዋሪ ሲያስቀምጥ ነው፡፡ በተጨማሪም በከባድ ወንጀል የተከሰሰ ሰው በቀላል ከተከሰሰ ሰው የበለጠ የመቀጣት ስጋት የሚፈጥርበት በመሆኑ ክስ በተነሳ ቁጥር ዳግም እከሰሳለሁ የሚል ስጋትን ሊኖር ስለሚችል በከባድ ወንጀሎች ላይ ገድብ ያስፈለገበት ምክንያትም ይሆናል፡፡
ክስ ሲነሳ ፍርድ ቤቶች ሊኖራቸው ሚችለው ሚና?
ክሱን ማንሳት ይቻላል ብሎ የፈቀደው አዋጅ በቂ ምክንት ሲኖር ጥያቄው ሊቀርብ እንደሚችል ሲናገር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከሳሹ ባቀረበው ጥያቄ ክሱ የሚነሳው ፍርድ ቤቱ ሲፈቅድ ነው ይላል፡፡ እንግዲህ ፍርድ ቤቶች ነፃ በማለት ሊያሰናብቱት የሚችሉትን ሰው ከሳሹ በክስ ማንሳት ሰበብ ዳግም ስጋት ውስጥ እንዳይገባ የመጠበቅ የሕግም የሞራልም ግዴታ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በቂ ማስረጃ የሚለውን እንደጉዳዩ ሊመለከቱት የሚገባ ቢሆንም በራቸውን ክፍት ሊያደርጉ የሚገባቸው ለአሳማኝ ሕጋዊ ምክንያት እንጅ ለፖለቲካዊ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡ የክሱ መቋረጥ ተከሳሾች ነፃ የመባል እና የወደፊት ኑሯቸው ላይ ወሳኝነት ያለው እንደመሆኑ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ምክንያት በቂ ብሎ ክሱን ሲያነሳ ሁለቱንም ወገኖች አከራክሮ መሆን አለበት፡፡ ከሳሽ ክሴን ላንሳ ስላለ ተከሳሽን ሳይጠሩ ክስ ማንሳት መዘዙ ወደኋላ ነው፡፡ ለጊዜ ተከሳሽ እፎይ ያለ ቢመስልም ዕዳው ከራሱ የሚወርድ ባለመሆኑ የክስ መነሳት ሂደት የክርክር አካል ሆኖ ሊቀርብ የሚገባ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የመደመጥ መብትን በጠበቀ መልኩ ሊወስን ይገባል፡፡
የዞን ዘጠኞች ክስ መቋረጥ አንድምታ
በግሌ ተፈተው ማየቴ ደስ ብሎኛል ብልም ብዥታ ውስጥ እንዳለሁ ግን ይሰማኛል፡፡ አንድ ክሱ የተነሳበት ምክንያት አለመታወቁ የፈጠረው ሲሆን ሌላው ክሱ ከተነሳ በኋላስ የሚለው ስጋት ሰቅዞ ይዞኝ ነው፡፡ ከሳሹ ምክንያቱን ሳይገልፅ ክሱ እንዲቋረጥ ፍርድ ቤቱ ፈቅዶ ከሆነ የተለመደው የቁልቁለት መንገድ ነው፡፡ ክሱ የተነሳው በሁለት መንገድ ሊሆን እንደሚችል መናገር ይቻላል፡፡ አንድ እንደ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ጉዳዩን የያዙት ዳኞች ልብ አግኝተው አምስቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማስረጃ በቂ ባለመሆኑ በነጻ ሊሰናበቱ ነው፤ አለ የምትሉ ከሆነ ማስረጃ አምጡ በማለት ለአለቃቸው አቅርበው ይሆናል፡፡ ይህን ምክንያት ለማቅረብ የቻልኩት ክሱ የተቋረጠው ይከላከሉ ወይም ነፃ ናቸው ተብሎ ለመወሰን በተቀጠረበት የክርክር ሂደት በመሆኑ ነው፡፡ ከሳሹ አካል ወይም መንግሥት ደግሞ ማስረጃ ከሥሩ እንዳላቀረበ ስለሚያውቀው በፍርድ ቤት ነፃ ተብለው ከሚለቀቁ እና እንደተሳሳተ ለሕዝብ ከመጋለጡ በፊት ክሱን አንስቶ ተከሳሾችንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በስጋት ቢያኖር የሚሻለው ነው፡፡ ይሄን ምክንያቴን ጎደሎ የሚያደርገው ነፃ በማለት በብይን የሚያሰናብቱ ዳኞች አናሳ በመሆናቸው ነው፡፡
ሌላው ምክንያት ያው የተለመደው ፖለቲካዊ ምክንያት ነው፡፡ ይሔ ከመንግሥት የውጪ ገፅታ ግንባታ አንፃር የሚታይ ነው፡፡ ብዕር ያነሳውን ሁሉ በመሣሪያ ዓይን እያዬ የሚያስረው መንግሥት ከኃያላኑ የሚቀርብበት ነቀፌታ አንዱ ሲያስር አለመመርጡን ነው፡፡ በቁጥር ለሚያምነው ስንኩል መንግስት ዘጠኝ ጦማሪና እና ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ተባሉ ከሚባል አምስቱን ፈቶ አራት ጥፋተኛ ቢል ጫናው ይቀንሳል ብሎ ያምናል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች ከፋፍሎ በመፍታት እና ጥፋተኛ በማለት በለውጥ ሃይሉ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማስቻል አንዱ መሰሪ ዓላማውም ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ለተፈቱት ወገኖች ፈንጠዝያ ማድረጉ ባይከፋም፤ የተፈቱት ሰዎች የወደፊት ሕይዎት ዋስትና የሌለውና በስጋት የተሞላ መሆኑንም ልናስብ ይገባል፡፡ ክስ ተነሳ ማለት ነፃ ተባለ ማለት አይደለም፤ በአንፃሩ ለዳግም ክስ ትንፋሽ መግዣና ሃይልን ማጠናከሪያ እንጅ፡፡ በተፈቱት ተከሳሾች ላይ ማስረጃ ለማግኘት የማይፈነቀል ነገር እንደማይኖር መገመት አይከብድም፡፡ የነገ የተከሳሾች ሕይዎት በዳግም እከሰስ ስጋት እና ቀውስ እንዲገባ ማድረግ ሌላው የከሳሹ እኩይ ዓላማ ነው፡፡ ሰዎች በእስር መንፈሳቸው አልደክም ሲል የተረጋጋ ማህበራዊ ሕይዎት እንዳይኖራቸው በማድረግ ስጋት ውስጥ ማኖር እና የፍርኃት ማኅበረሰብ መፍጠር የአምባገነኖች ባህሪ ነው፡፡
የክሱን መነሳት ውጤት አብሮ መከታተሉ አይከፋም፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው!! እስቲ አስተያየት ስጡበት