በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ የወንጅል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ስለመዋል ወይም ስለመያዝ የሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማብራራት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የሰዎች የነፃነት መብትና በፖሊስ በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ስለመዋል መካከል ስላለስ ግንኙነት በትንሹ ገለፃ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች የሚያዙባቸውን መንገዶችና እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ የሚደነግገውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ክፍል በጥልቀት ለመርመር ሙከራ ተደርጓል፡፡
የመያዝና የሕገ መንግሥቱ የነጻነት መብት ግንኙነት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 (1) ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ነፃነቱን እንደማያጣ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ይህም ማለት በንዑስ አንቀጽ (2) እንደተብራራው ማንኛውም ሰው ክስ ሳይቀርብበበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር እንደማይችል ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ሕጎች በግልፅ በተደነገጉ ሁኔታዎች የዜጎች የነፃነት መብት ሊገደብ እንሚችል የሕገ መንግሥቱ ‹‹በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ›› የሚለው አገላለፅ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ማንኛውም የወንጀል ድርጊት የፈፀመ ሰው ወይም በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው በፖሊስ የሚያዝበት አግባብ ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ሲሆን ወንጀሉን የፈፀመው ሰው የሕገ መንግሥቱን ዓላማና መንፈስ በጠበቀ መልኩ ነፃነቱ መገደቡን መረዳት እንችላለን፡፡ ከዚህ በመቀጠል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እውቅና የተሰጣቸውና በአሁኑ ሰዓት በማገልገል ላይ የሚገኙትን ወንጀለኛን የመያዣ መንገዶችን እንዲሁም የአያያዝ ሥርዓቶች እንቃኛለን፡፡
በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ወንጀለኛን የመያዣ መንገዶች