መግቢያ
የወንጀል ክስን በማስረጃ አስደግፎ በማረጋገጥ እና ተከሳሽን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጥፋተኛ ማስደረግ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ትልቅ ጥረትና ድካም የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ አንድ ወንጀል ማህበረሰቡ ላይ ሲፈጸም ወንጀሉን የፈጸመን አካል ነቅሶ በማውጣት ለፍርድ በማቅረብ ማስቀጣት የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ አንድ መንግሥት የሕዝብን ሥልጣን ሲቀበል የማህበረሰቡን ሰላም መጠበቅ ከሕዝቡ የተጣለበት ግደታው ነው፡፡ ይህንን ሰላም ለመጠበቅ ደግሞ ወንጀል እንዳይፈፀም ይከላከላል፡፡ ከተፈፀመ በኋላ ፈፃሚውን ለሕግ ያቀርባል፣ ወንጀል ለመፈፀሙ ሊያሥረዱ የሚችሉ ማስረጃወችን አብሮ ያቀርባል፡፡
ቀዳሚ ምርመራም መንግሥት ወንጀል መፈፀሙን ለማሥረዳት የሚችሉ ማስረጃወችን የሚሰበስብበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ቀዳሚ ምርመራ ክስ ከመሰማቱ በፊት በፍርድ ቤት የሚደረግ የማስረጃ መስማት እና ለክስ መስማት የሚቀርበውን ጉዳይ የመለየት ሂደት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በሦስተኛ መጽሐፉ ከአንቀፅ 80 እስከ 93 ድረስ ስለ ቀዳሚ ምርመራ የሚያትቱ ድንጋጌዎች አካትቶ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው በሃገራችን ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ይዘት እና የተግባር አሠራር የሚመለከት ነው፡፡ በአተገባበር ደረጃ ግድፈት አለባቸው ተብለው በጸሐፊው እይታ የታዩ ደንጋጌዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እስከተቻለ ድረስ የሕጉን መንፈስ እና በተግባር ምን እየተሠራ እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡