- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4606
የመ/ቁ 275249
ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ሣሽ፡- አቶ አብደና በቀለ ቀነአ- ጠበቃ ደጀኔ
ተከሳሾች 1ኛ. አቶ ጠቀሳ ባይሳ ቀልቤሳ ጠበቃ ጋሻሁን
2ኛ. ወ/ሪት ገልገሌ ባይሳ ቀልቤሳ
መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ተገቢውን ለመስራት ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
በመዝገቡ ላይ ተከሳሾች ያቀረቡት የመከላከያ ማስፈቀጃ ውድቅ ተደርጎ ውሳኔ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን የፌ/ከ/ፍ/ቤት የመ/ቁ 242914 በሆነው መዝገብ ላይ ተከሳሾች ያቀረቡትን ይግባኝ ቅሬታ መርምሮ ተከሳሾች የመከላከያ መልሳቸውን እንዲያቅርቡ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ እንዲወስን በሰጠው ውሳኔ መሰረት መዝገቡ ወደ ስር ፍ/ቤቱ የቀረበ ነው፡፡ በመዝገቡ ላይ የቀረበውን ክስ ስንመለከት ከሣሽ በግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከሳሽ ከተከሳሾች ጋር በጥር 4 ቀን 2011ዓ.ም ባደረግነው የእርቅ ስምምነት ቀድሞ በነበረን የሽርክና ማኅበር ግንኙነት የድርሻዬን በተለያዩ የጊዜ ገደብ ገንዘብ ከፍለውኝ ከሽርክና ማህበሩ እንደምወጣ የተስማማን ሲሆን በዚሁ መሰረት ከማህበሩ የወጣሁና በስምምነታችን መሰረትም የመጀመሪያውን ክፍያ ብር 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) በቼክ ቁጥር ኢጂ 25014011 የተቀበልኩ ሲሆን ሁለተኛው ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቂርቆስ ቀበሌ ቅርጫፍ በቼክ ቁጥር EG 25014012 በጥር 04 ቀን 2011ዓ.ም የሚመነዘር ተከሳሾች ቼክ ቆርጠውና ፈርመው ሰጥተውኛል፡፡
ተከሳሾች እንዲከፈል በማለት የጻፈውን ቼክ ለክፍያ ዝግጁ በሆኑበት ቀን ክፍያውን ለመቀበል ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቂርቆስ ቀበሌ ቅርንጫፍ ብመላለስም በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ እንደሌለ በ21/08/2011ዓ.ም በማረጋገጥ ማስረጃ የሰጠኝ ከመሆኑም በላይ የተከሳሾች ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆንም ከሳሽ ግን በሆደ-ሰፊነት ወደ 1ኛ ተከሳሽ በመደወል የባንኩ ሂሳብ በቂ ስንቅ እንደሌለውና ገንዘቡን እንዲከፍል ለማሳወቅ ጥረት ቢያደርግም እንቢተኛ የሆነ ሲሆን ከእኔም አልፎ የቅርንጫፍ ባንኩ ማናጀር ጭምር ደውሎለት ቼኩ ከተመታ በኋላ ገንዘብ ገቢ ያደረገ ቢሆንም ክፍያ እንዲፈጽም ቢጠይቀውም ፍቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲሁም ወጪና ኪሳራን ጨምሮ እንዲከፍሉ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ተከሳሾች በህዳር 24 ቀን 2012 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ክስ የቀረበበት ቼክ በተከሳሾች የተፃፈ ቢሆንም ጥር 24 ቀን 2011 ዓ/ም እንዲመነዘር የተሠጠ አይደለም፡፡ ቼኩ የተሰጠው ለዋስትና ሲሆን የጉዳዩ መነሻም ተከሳሾች ከከሳሽ ጋር የመሰረትነው አብደና እና ገልገሌ የኤሌክትሪክ ሜካኒካል ሶሉሽን ሽርክና ማህበር ነበር፡፡ ከሳሽ ማህበሩ እንዲፈርስ የመ/ቁ 265253 በሆነው መዝገብ ላይ ክስ አቅርበው የነበረ ሲሆን ጉዳዩ ክርክር ላይ እንዳለ ጉዳዩ በእርቅ አልቋል፡፡ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ/ም ከከሳሽ ጋር በተደረገው ስምምነትም ተከሳሾች በአጠቃላይ ብር 1,300,000 (አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ) ለከሳሽ ከፍለን ከሳሽ ከማህበሩ እንዲሰናበቱ የተስማማን ሲሆን በውሉ መሰረትም ክፍያው የሚፈመው በሶስት ዙር ሲሆን የክፍያው ጊዜ አልተገለፀም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ተከፋዩ ገንዘብ ቀጥታ ከማህበሩ ወይም ተከሳሾች የሚከፈል ሳይሆን ኦሮሚያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ከተባለው መንግስት ተቋም በተለያዩ ጊዜያት የሚለቀቅ በመሆኑ ነው፡፡ በውሉ መሰረትም የከሳሽን መብት ለማስጠበቅ ክስ የቀረበበትን ቼክ ጨምሮ ሶስት ቼኮች በሽማግሌ እጅ የነበሩ ሲሆን ይህ ሶስተኛ የሆነው ወገን ገንዘብ ሳይለቅ የቼኮቹ የመክፈያ ጊዜ ሊያበቃ ቢሆን በግራ ቀኙ ቃለ ጉባኤ ተይዞ ተለዋጭ ቼክ እንደሚሰጥም ተስማምተናል፡፡
ከሳሽ ይህንን ስምምነት በመጣስ ከአስታራቂ ሽማግሌዎች ጋር በመመሳጠር ቼኮቹን በመውሰድ ክስ ያቀረቡ ሲሆን ክፍያውን የይለቃል የተባለው ተቋምም የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ክፍያውን ሲያዘገይ ከቆየ በኋላ የተወሰነ ገንዘብ የለቀቀ ሲሆን ይህ ገንዘብም ለሰራተኞች ደሞዝ ፣ ለመኪና ኪራይና ለመንግስት ግብር ወጪ ተሰርቶ የሚቀረው ገንዘብ በቼኩ ላይ እንደተገለፀው ለመክፈል ባለመቻሉ የተወሰነ ገንዘብ ወስደው ቀሪውን በትእግስት እንዲጠባበቁ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆን ክስ አቅርበዋል፡፡
ከሳሽ እንደውሉ ያልተፈፀመላቸው ከሆነ ውሉን መሰረት በማድረግ በአፈፃፀም መጠየቅ ከሚችሉ በስተቀር ለዋስትና የተሰጠውን ቼክ መነሻ በማድረግ ክስ ማቅረብ አይችሉም፡፡ እንደ ውሉ ያልተከፈለ ገንዘብ አለ ካሉም ለወደፊት ከሚለቀቅ ክፍያ ከሚወስዱ በስተቀር በቼኩ ላይ የተመለከተውን ገንዘብ በውሉ መሰረት እንድንከፍል አንገደድም፡፡ በዚህም ከሳሽ ወጪና ኪሳራ እንዲከፍሉ ተወስኖ ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት ቀንም ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ቼኩ ከሽማግሌ እጅ ለከሳሽ የተሰጠው በውሉ መሰረት ሁለተኛ ክፍያ ከብር 1.9 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ የተለቀቀ በመሆኑ ሲሆን በውሉ ላይ ክፍያ ሲከፈል የሚከፈል በመሆኑ ያለ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ነው፡፡ ለሰራተኛ ለመብራት የሚል ስምምነት በውሉ ላይ የሌለ ሲሆን ክፍያ የተለቀቀ መሆኑንም ተከሳሾች አምነዋል በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሾች ባቀረቡት ክርክር ሁለተኛ ክፍያ ብር 1.9 ሚሊየን ተከፍሎናል ነገር ግን በውሉ ላይ ስንት ገንዘብ ሲለቀቅ ክፍያ እንደሚፈፀም አልተገለፀም በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
በግራ ቀኙ በኩል የተነሱት የመከራከሪያ ነጥቦች ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት
በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡
ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሾች ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡
በያዝነው ጉዳይ ከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሾች ለከሳሽ የሰጡት ከተከሳሾች ጋር በጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረጉት የእርቅ ስምምነት ውል መሰረት ቀድሞ በነበራቸው የሽርክና ማኅበር ግንኙነት የድርሻቸውን በተለያዩ የጊዜ ገደብ ገንዘብ ተከፍሏቸው ከሽርክና ማህበሩ እንዲወጡ የተስማሙ በመሆኑ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ይህንን በከሳሽ የቀረበውን መከራከሪያ በማጠናከር ነው ተከሳሾችም የተከራከሩት፡፡ ሆኖም ተከሳሾች ቼኩ ለዋስትና የተሰጠ ኦሮሚያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ከተባለው መንግስት ተቋም በተለያዩ ጊዜያት ክፍያ ሲለቀቅ እንዲከፈል በሽማግሌ እጅ እንዲቀመጥ የተደረገ ሆኖ ሳለ ይህ ቅድመ ሁኔታ ባልተሟላበት ቼኩ ለከሳሽ እንዲሰጥ የተደረገ መሆኑን የገለፁ ናቸው፡፡
በዚህም ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነው ጉዳይ ግራ ቀኙ በጥር 4 ቀን 2011 ዓ/ም ያረጉት የእርቅ ስምምነት ውል በመሆኑ የውሉን ይዘት መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ በውሉ ላይ ከሳሽ ብር 1,300,000 (አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ) ተከፍሏቸው ከተከሳሾች ጋር ካቋቋሙት ማህበር ለመውጣት የገንዘብ አከፋፈሉን በተመለከተ በሶስት ዙር ሆኖ በመጀመሪያ ዙር ብር 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) በቼክ የተሰጣቸው ሲሆን 2ኛ ዙር ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) አሰሪው ተቋም በሁለተኛ ዙር ከኦሮሚያ ሪጅን አ/አ/ኤ/አ/ፕ ከሚከፈለው ክፍያ ውስጥ ሊከፈል እንዲሁም ቀሪው 3ኛው ዙር ክፍያ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ደግሞ ተቋሙ ለሶስተኛ ዙር ከሚለቀቅለት ክፍያ የሚከፈል መሆኑ ተመልክቷል፡፡
እንግዲህ ይህንን ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ በተመለከተ ግራ ቀኙ ካደረጉት የውል ስምምነት አኳያ ክፍያ ሊፈፀምበት የሚገባ ነው ወይ ክፍያ ሊፈፀም የሚገባው ከሆነስ መቼ ነው? የሚለውን ነጥብ ፍ/ቤቱ እንደመረመረው ከላይ እንደተመለከትነው በውሉ ድንጋጌ ላይ ተከሳሾች ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ለመክፈል የሚገደዱት ማህበሩ ለሰራው ስራ የሁለተኛ ዙር ክፍያ ሲለቀቅለት መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ተከሳሾች ለፍ/ቤቱ እንዳስረዱትም ይህ የሁለተኛ ዙር ክፍያ ብር 1.9 ሚሊየን ብር የተለቀቀላቸው ሲሆን በውሉ ላይ ተከሳሾች ምን ያህል ገንዘብ ሲለቀቅላቸው ይህንን ገንዘብ ለከሳሽ እንደሚከፍሉ የተገለፀበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህም ከሳሽ የሁለተኛ ዙር ክፍያ የተለቀቀ እንደሆነ ክፍያ የሚፈፀምላቸው መሆኑን ግራ ቀኙ የተስማሙ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን ምን ያህል ገንዘብ ሲለቀቅና ተከሳሾች ይህንን የተለቀቀውን ገንዘብ ምን ምን ላይ አውለው ሲተርፍ ለከሳሽ የሚከፍሉ ስለመሆኑ በውሉ ላይ ያልተመለከተ በሆነበት ሁኔታ ተከሳሾች ሁለተኛ ዙር ገንዘብ የተለቀቀ መሆኑን በማመን እየተከራከሩ ባለበት ሁኔታ የተለቀቀው ገንዘቡ ለሰራተኞች ደሞዝ ፣ ለመኪና ኪራይና ለመንግስት ግብር ወጪ ተሰርቶ ለከሳሽ ገንዘቡን ለመክፈል ያልበቃ መሆኑን በመግለፅ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ሊከፍሉ የማይገባ መሆኑን ያቀረቡት መከራከሪያ ግራ ቀኙ ያደረጉትን የውል ስምምነት ቼኩ እንዲከፈል ከተሰጠበት ምክንያት ውጪ በመሆኑ መከራከሪያቸውን ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነው ግራ ቀኙ ያደረጉት የእርቅ ስምምነት ውል መሆኑ በግራ ቀኙ በኩል ያለውን የቼክ ግንኙነት ከሚያመለክት በስተቀር ቼኩን መሰረት በማድረግ በቀጥታ ክስ ሊቀርብ አይገባም ሊባል የሚችልበት የህግ አግባብ የሌለ ሲሆን በዚህም ተከሳሾች ከሳሽ በአፈፃፀም መጠየቅ ከሚችሉ በስተቀር ለዋስትና የተሰጠውን ቼክ መነሻ በማድረግ ክስ ማቅረብ አይችሉም በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡
በዚህም ተከሳሾች በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ሊከፍሉ የማይገባበት ምክንያት ያለ መሆኑን ያላስረዱ በመሆኑ ገንዘቡን ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ውሳኔ
- ተከሳሾች ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ) ቼኩ ለክፍያ ባንክ ከቀረበበት ከሚያዚያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
- ወጪና ኪሣራ በተመለከተ ከሣሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 7,850 ፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 30 ፣ የጠበቃ አበል በጥብቅና ውሉ መሰረት ብር 50,000 ፣ ልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 1,000 ተከሳሾች ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 5582
የመ/ቁ. 270967
ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ/ም
ልደታ ምድብ 5ኛ ፍ/ብ ንግድ ችሎት
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ከሣሽ፡- መክሊት የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አ.ማ)
ተከሣሾች፡- 1ኛ. አቶ በፍቃዱ ጋረደዉ መስቀሌ
2ኛ. አቶ መሐሪ የማነ አብረሃም
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የብድር ገንዘብ ለማስከፈል የቀረበ ክስን የሚመለከት ሲሆን ከሣሽ በአጭር ሥነ-ሥርዓት ታይቶ እንዲወሰን ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የክስ አቤቱታ በከሳሽ እና በተከሳሾች መካከል ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል ስምምነት 1ኛ ተከሳሽ ብር 2,5000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ከከሳሽ ተበድረው የወሠዱ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ በብድር ለወሠዱት ገንዘብ ዋስ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ በውሉ መሰረት የተበደሩትን ገንዘብ ባይከፍሉ በአንድነት እና በነጠላ በመሆን የማይከፋፈል ኃላፊነት በመግባት ውሉ ፈርመዋል፡፡ 1ኛተከሳሽም ከወሰዱት ገንዘብ ከወለድና ቅጣት ጋር ብር 16,243∙53 የቀሪባቸዉ በመሆኑ የተበደሩትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ፍቃደኛ ሆነዉ ሊከፍሉ አልቻሉም፡፡ በመሆኑ ከተበደሩት ገንዘብ ውስጥ ዋና ገንዘብ ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 4,183∙29 ከወለድ ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 9,703∙38 ከቅጣት ቀሪ የሆነ ዕዳ ብር 2,356∙86 በድምሩ ብር 16,243∙53 (አሥራ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሶስት ከ38/100) እንደሚቀርባቸው በዚህም ወጪና ኪሳራን ጨምሮ ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ የዚህ ክስ ዉሳኔ እስከ ሚሰጥበት ድረስ ያለዉን ከሚታሰብ 17% ወለድ እንዲሁም ቅጣት 7% እንዲከፍሉ እንዲወሰንለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል፡፡
ተከሳሾች በህግ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው 1ኛ ተከሳሽ ክሱን እንዲከላከሉ በተፈቀደላቸው መሰረት መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የመከላከያ መልሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ መጥሪያ የደረሳቸው ቢሆንም የመከላከያ ማስፈቀጃ ያላቀረቡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ የመከላከል መብታቸውን አልፎታል፡፡
1ኛ ተከሳሽ በሰጡት መልስ ከከሳሽ ብር 25000(ሀያ አምስት ሺህ ብር) ሊከፍሉ ዉል የገቡ መሆናቸዉን በማመን ከተበደሩት ዋና ገንዘብ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ብር 20,816∙71 (ሀያ ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ስድስት ብር ከ71/100) እና ወለድ ብር 7,825 (ሰባት ሺህ ስምንት ሀያ አምስት ብር) የከፈሉና ቀሪ ዕዳ ብር 4,183∙29 (አረት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) ሲሆን ከዚህም 1ኛ ተከሳሽ ተቀማጭ ቀሪ የተገኘዉን ብር 1,549∙92 ከከሳሽ ካዝነ ያለ በመሆኑ ስቀነስ ከዋና እዳ ቀሪ ብር 2,633∙37 ብቻ የቀረባቸዉ መሆኑን ገልጾ ከሳሽ መጠየቅ የሚችለዉ በዉሉ አንቀጽ 1∙2∙6 እና 2∙7 መሰረት ተከሳሽ ለመክፈል በተስማማበት የጊዜ ገደብ ዉስጥ ሳይከፍል በቀረዉ የብድር ገንዘብ ብር 2,633∙37ና ከግንቦት 22 ቀን 2009 እስከ መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ/ም ያለ የ22 ወራት ወለድ ብር 869 እንዲሁም የዚህ ወለድ ወለድ ብር 286∙77 እና ቅጣት ብር 434∙50 በድምሩ ብር 4223∙64 ብቻ ከሳሽ መጠየቅ ሲገባ ብር 16,243∙53 ተከሳሾችን ለማስከፈል ያቀረቡት ክስ ዉድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ጠይቋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል፡፡
ፍ/ቤቱ ክስ በሰማበት እለት ከሳሽ ባቀረበው ክርክር 1ኛ ተከሳሽ ብር 20,816∙71 ከፍያለሁ በማለት የገለፁ ቢሆንም ይህ ስለማሆኑ ያቀረቡት ማስረጃ የለም። ያልተከፈለ ጠቅላላ ገንዘብ ብር 16,243∙53 ነዉ። ወለዱ ፍላት ሬት ነዉ። የሚቀረዉ ገንዘብ አንድ ብር እንኳን ቢሆን ወለዱ የሚሰላዉ በአጠቃለይ በተበደሩት ገንዘብ ላይ ነዉ። ወለዱ መታሰብ ያለበት በዉሉ 1∙2∙6 መሰረት ከዋናዉ ገንዘብ ላይ ነዉ። 1ኛ ተከሳሽ በተቋሙ ያለዉ ተቀማጭ ቁጠባ ገንዘብ ለማካካስ 1ኛተከሳሽ ቀርቦ ፎርማሊቲዉን ሟሟለት እያለባቸዉ አልቀረቡም። ለ3 ወር በላይ ያልከፈሉ በመሆኑ ዉሉ ተቋርጣል በማለት የገለፀ ሲሆን 1ኛተከሳሽ በበኩሉ ብር 20,816∙71 በየወሩ በዉሉ መሰረት ስከፍል ነበር። በዉሉ አንቀጽ 1∙2∙6 መሰረት ወለዱ መታሰብ ያለበት በቀሪዉ ዕዳ ላይ ነዉ። በዉሉ መሰረት ያስቀመጥኩት ቁጠባ ገንዘብ ብር 1,549∙92 ለዕዳ ማካካሸነት ሊታሰብ ይገባል። የሚቀረዉ ብር 2,633∙37 ነዉ በማለት አስረድተዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ በተከሳሾች ላይ ክስ ያቀረቡት 1ኛ ተከሳሽ ተበድረው የወሠዱትን ገንዘብ በብድር ውሉ መሠረት ያልመለሱ ስለሆነ ተበድረው ከወሠዱት ቀሪ ገንዘብ ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት ሲሆን ከሳሽ እና 1ኛ ተከሳሽ ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል ስምምነት 1ኛተከሳሽ ብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ከከሳሽ ተበድረው የወሠዱ መሆናቸዉን 2ኛተከሳሽ 1ኛተከሳሽ በብድር ለወሠዱት ገንዘብ ዋስ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ በውሉ መሰረት የተበደሩትን ገንዘብ ባይከፍሉ በአንድነት እና በነጠላ በመሆን የማይከፋፈል ኃላፊነት በመግባት ውሉ የፈረሙ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ ቀርቧል፡፡
በህግ አግባብ የተደረጉ ውሎች ማለትም በህግ ፊት የሚፀና ህጋዊ ውጤትን የሚያስከትል ውል ለመዋዋል መሟላት አለባቸው ተብለው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1678 ስር የተቀመጡትን መስፈርቶች በሙሉ ባሟላ መልኩ የተደረጉ ውሎች በተዋዋይ ወገኖች ላይ ህግ ናቸው ይህም ከላይ በገለጽነው ህግ በቁጥር 1731/1/ ስር ተመልክቷል፡፡
ግራ ቀኙ ተዋዋይ ወገኖች ያደረጉት ውል የብድር ውል ከሆነ ተበዳሪው ወገን በብድር ውሉ መሠረት ተበድሮ የወሠደውን ገንዘብ በብድር ውሉ ላይ የብድር ገንዘቡን መክፈያ ጊዜ ተወስኖ ከተቀመጠ ይህ የመክፈያ ጊዜ ሲደርስ፣ በብድር ውሉ ላይ መክፈያ ጊዜው ካልተወሠነ አበዳሪው ወገን ያበደረው ገንዘብ እንዲመለስለት በጠየቀ በ30 ቀናት ውስጥ ተበዳሪው ወገን ለአበዳሪው የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2482፣ 2483 ስር ተመልክቷል፡፡ ተበዳሪው ወገን በዚህ ግዴታው መሠረት ተበድሮ የወሠደውን ገንዘብ ካልመለሰ አበዳሪው ወገን ውሉን እንዲሁም ህጉን መሠረት በማድረግ ተበዳሪው ወገን በብድር የወሠደውን ገንዘብ እንዲመልስለት መጠየቅ ይችላል፡፡
ከሳሽ እና ተከሳሾች ያደረጉት ውል የብድር ውል ሲሆን በዚህ የብድር ውል 1ኛ ተከሳሽ ከከሣሽ ላይ ብር 25,000 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) ተበድረው ወስደው በውሉ መሰረት ባይከፈል በብድር የወሰዱት ገንዘብ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በአንድነት እና በነጠላ ለከሳሽ ለመመለስ ውል ያደረጉ ስለመሆኑ የቀረበዉ ማስረጃ የሚያስረዳ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የተበደሩት ከዋናዉ ብድር እንዲሁም ወለዱን በየወሩ ሲከፍሉ የነበሩና ከዋና ቀሪ ዕዳ ብር 4,183∙29 (አራት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) ብቻ ሳይከፈል የቀረ መሆኑን እንዲሁም ተቀማጭ ቀሪ የተገኘዉን ቁጠባ ብር 1,549∙92 ከከሳሽ ካዝና ያለዉ መሆኑን የቀረበዉ የሰነድ ማስረጃ ያስረዳል። በግራቀኙ የተደረገው የብድር ዉል አንቀጽ 1∙2∙6 እና 1.2∙7 መሰረት ተበዳሪዉ ለመክፈል በተስማማበት የጊዜ ገደብ ዉስጥ ክፈያዉን ያላጠናቀቀ እንደሆነ ሳይከፍል በቀረዉ ዋና ገንዘብ በተጨማሪ ዕዳዉን አጠናቅቆ እስከሚከፍል ድረስ በ18% ተሰልቶ ወለድና የወለድ ወለድ ሊከፍል እንደሚገባ ተደንግጓል። ከዚህ አንጻር ተከሳሽ እንድከፍል የሚገደደዉ ሳይከፍል በቀረዉ ከዋና ገንዘብ ቀሪ ዕዳ እና በ18% ተሰልቶ የዚህኑ ወለድና የወለድ ወለድ በመሆኑ መረዳት የሚቻል ሲሆን ከሳሽ ወለዱ የሚታሰበዉ በፍላት ሬት ከተበደረዉ ዋና ገንዘብ ላይ እንጅ ከቀሪ ዕዳ አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር ፍ/ቤቱ አልተቀበለም።
ከዚህ በተጨማሪም የዉሉ አንቀጽ 1∙2∙7 መሰረት ተበዳሪዉ በዉሉ መሰረት ያልከፈለዉ ዉዝፍ ዕዳ ቢኖር በተቋሙ ዉስጥ ያስቀመጠዉ ማንኛዉም ቁጠባ ያለምንም ክርክር ለእዳዉ ማካካሸነት የሚዉል መሆኑ የተደነገገ ሲሆን ይህም የባለእዳ ፈቃድ ላይ ያልተመሠረተና ከሳሽ በማንኛዉም ጊዜና ያለቅድመ ሁኔታ ላልተከፈለዉ ዉዝፍ ዕዳ ማካካሸነት መዋል እንደሚችል የሚያስረዳ ሲሆን ከሳሽ ተከሳሽ ቀርቦ ፎርማሊትዉን ማሟላት ስላለበት ከቀሪዉ እዳ አልተቀነሳም በማለት ተከሳሽ በዉሉ መሰረት ከቀሪ ዕዳ ሊቀነስለት የሚገባ በተቋሙ ቁጠባ እያለ ሳይቀነስለት ከዋና ቀሪ ዕዳዉን ከነወለዱ ተሰልቶ ለማስከፈል ያቀረቡት ክርክር ፍ/ቤቱ ተገቢ ሆኖ አላገኘውም። ስለሆነም ክስ የቀረበበት ገንዘብ ከዋና ቀሪ ዕዳ ከብር 4,183∙29 (አራት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ከ29/100 ብር) 1ኛተከሳሽ ከከሳሽ ላይ ያሉት የቁጠባ ገንዘብ ብር 1,549∙92( አንድ ሸህ አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር ከ92/100) ቅናሽ ተደርጎ 1ኛተከሳሽ ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ በቀሪነት የሚፈለግባቸው ብር 2,633∙37 (ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ሶስት ብር ከ 37/100) እና የ22 ወራት ወለድ ብር 869 (ስምንት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ብር) እንዲሁም የወለድ ወለድ ብር 286∙77 (ሁለት መቶ ሰማንያ ስድስት ብር ከ 77/100) በድምሩ ብር 3,789∙19 (ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር ከ19/100) የሚሆን ሲሆን ተከሳሾችም ይህንን የገንዘብ መጠን በአንድነት እና በነጠላ ኃላፊነት ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ከሳሽ ለ1ኛ ተከሳሽ በብድር ውሉ መነሻነት ባበደሩት ገንዘብ ላይ ስምምነት ያደረጉበት 18% ወለድ አስልተው ዳኝነት ጠይቀው እያለ ገንዘቡ በውሉ መሰረት በወቅቱ ባለመከፈሉ ቅጣት ብር 2,356∙86 (ሁለት ሺህ ሶስት መቶ አምሣ ስድስት ብር ከ586/100) እንዲከፍሉ እንዲሁም ክስ በቀረበበት ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቅጣት 7% እየተሰላ ጭምር ከሳሽ እንዲከፈለው ዳኝነት ጠይቋል፡፡ ተበዳሪው የተበደረውን ነገር ከመመለስ ወይም የሚገባውን ወለድ ከመክፈል የዘገየ እንደሆነ ጊዜ በማስተላለፍ የሚከፈለውን ወለድ እንዲከፍል እንደሚገደድ እና ይህን ግዴታ የሚያከብድ ማንኛውም የውል ቃል ፈራሽ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2489(2) ስር ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም ከሳሽ እና ተከሳሾች ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ/ም ባደረጉት የብድር ውል ተከሳሾች የብድር ገንዘቡ ለመመለስ ስምምነት በተደረገበት ጊዜ ባለመመለሳቸው ወለድ ተሰልቶ ዳኝነት ተጠይቆ እያለ ከላይ የተጠቀሰዉ ቅጣት ተከሳሾች ለከሳሽ እንዲከፍሉ የተደረገው ተከሳሾቹ ሙሉ በሙሉ ባይቃወሙ እንኳን የውሉ ክፍል የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2489(2) ይዘትን ያልተከተለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ው ሳ ኔ
- ተከሳሾች ክስ ከቀረበበት ገንዘብ ውስጥ ብር 3,789∙19 (ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር ከ19/100) ክስ ከተመሰረተበት ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከ ሚጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር በአንድነት እና በነጠላ ለከሳሽ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
- ከሳሽ የብድር ገንዘቡ እና ወለዱ በመዘግየቱ ቅጣት እንዲከፈል ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
- በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት የወጣ ወጪና የደረሰ ኪሣራ በተመለከተ ለዳኝነት ፍርድ በተሰጠበት የገንዘብ ልክ ብር 162 ፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 20 እንዲሁም ለልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 500 ተከሳሾች በአንድነትና በነጠላ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነዉ፡፡
2∙ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡
- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4573
የመ/ቁ 270687
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ከሣሽ፡- አቶ አበራ አግዛ
ተከሣሽ፡- አቶ አንድአምላክ ሳህሌ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ከሣሽ በታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ተከሣሽ የቼክ ቁጥሩ ኤኤ2899517 የሆነ ብር 50,000.00 (ሀምሳ ሺህ) ያዘዘ ቼክ እንዲሁም የቼክ ቁጥሩ ቢኤፍ3779809 የሆነ ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ያዘዘ ቼክ ባለን የንግድ ግንኙነት ወይም እቁብ አብረን እንሰራ የነበረ በመሆኑ ፈርመው የሠጡኝ ቢሆንም ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ ሳቀርብ ባንኩ በቂ ገንዘብ እንዲሁም ሂሳቡ ተዘግቷል በማለት ቼኮቹ ሣይከፈልባቸው የተመለሱ በመሆኑ ተከሣሽ በቼኮቹ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ተከሣሽ የመ/ማስፈቀጃ አቅርበው ፍ/ቤቱ የመ/መልሳቸውን እንዲያቀርቡ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት በሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ/ም በሰጡት መልስ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መሰረት ከሳሽ ክስ ያቀረቡበት የቼክ ቁጥር ኤኤ2899517 የሆነውን ቼክ በተመለከተ ክስ ለማቅረብ መብታቸው በይርጋ ቀሪ መሆኑን ፍ/ቤቱ ብይን ሰጥቶበታል፡፡
ተከሳሽ በፍሬ ጉዳዩ ላይ የሰጡትን መልስ ስንመለከት ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጠሁት በየካቲት ወር 2007 ዓ/ም በተጀመረው ባለን የእቁብ ግንኙነት ነው ፤ ተከሳሽ ያለብኝን የእቁብ ገንዘብም በከሳሽ ስም በተከፈተ ሂሳብ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም በተከፈተ ሂሳብ ገቢ በማድረግ ጨርሼ ከፍያለሁ ያላግባብ ለመበልፀግ ያቀረቡት ክስ በመሆኑም ክሱ ውድቅ እንዲደረግና ወጪና ኪሳራ የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት ቀንም ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ለክሱ መነሻ የሆነው ቼክ ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በ2010 ዓ/ም በመጨረሻ ላይ ለወጣው እቁብ ክፍያ ይሆን ዘንድ ለመተማመኛ ነው ፤ ያቀረቡበት የሰነድ ማስረጃ በ2008/9 ዓ/ም ለወጣ እቁብ የተከፈለበት ነው ያሉ ሲሆን የመዝጊያ ክርክር ባቀረቡበት ጊዜ ደግሞ ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጡት ተከሳሽ ሊጥሉት ይገባ የነበረውን የእቁብ ገንዘብ ከሳሽ እከፍልላቸው የነበረ በመሆኑ ለዚህ ክፍያ ይሆን ዘንድ ነው ካሉ በኋላ ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በእቁብ ምክንያት ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 200ሺህ ለተከሳሽ ያበደርኳቸው በመሆኑ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ተከሳሽ በበኩላቸው ከከሳሽ ጋር የእቁብ ግንኙነት የለኝም ቼኩ ከሳሽ እጅ ሊገባ የቻለው ከሳሽ በ2009 ዓ/ም እቁብ ይሰበስቡ የነበረ በመሆኑ ለዋስትና ቀን ሳይፃፍበት የተሰጠ ሲሆን በወቅቱም እቁቡ አልቆ ተለያይተናል፤ ከሳሽም በወቅቱ ቼኩን ሊመልሱ አልቻሉም በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡
ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሽ ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ ሂሳቡ የተዘጋ መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡
በያዝነው ጉዳይ ተከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ቼኩን ለከሳሽ የሰጠሁት በየካቲት ወር 2007 ዓ/ም በተጀመረው ባለን የእቁብ ግንኙነት ነው ፤ ተከሳሽ ያለብኝን የእቁብ ገንዘብም በከሳሽ ስም በተከፈተ ሂሳብ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም በተከፈተ ሂሳብ ገቢ በማድረግ ጨርሼ ከፍያለሁ ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን ያቀረቧቸው የሰነድ ማስረጃዎችም በተለያየ ቀን በከሳሽ ስም በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም በከሳሽ ባለቤት ስም ወ/ሮ ሰልፍነሽ ግዛው ስም በወጋገን ባንክ በተከፈተ ሂሳብ ገንዘብ ገቢ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከሳሽ በፅሁፍ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ላይ ለክሱ መነሻ የሆነው ቼክ በእቁብ አማካኝነት በተከሳሽ የተሰጣቸው መሆኑን የገለፁ ሲሆን ክስ በተሰማበት ቀን ደግሞ በአንድ በኩል ቼኩ በእቁብ አማካኝነት ለክፍያ ይሆን ዘንድ የተሰጠኝ ነው ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሽ ቼኩን ለከሳሽ የሰጡት ተከሳሽ ሊጥሉት ይገባ የነበረውን የእቁብ ገንዘብ ከሳሽ እከፍልላቸው የነበረ በመሆኑ ለዚህ ክፍያ ይሆን ዘንድ የተሰጠ ነው ያሉ ሲሆን እንዲሁም በድጋሚ ለፍ/ቤቱ ሲያስረዱም ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት በእቁብ ምክንያት ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 200ሺህ ለተከሳሽ ያበደርኳቸው በመሆኑ ነው በማለት እርስ በርሱ የሚጣረስ ክርክር አቅርበዋል፡፡ ይህም በከሳሽ የቀረበው መከራከሪያ ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ያገኙት ከተከሳሽ ጋር በነበራቸው የንግድ ግንኙነት አማካኝነት ክፍያ ይፈፀምበት ዘንድ የተሰጠ መሆኑንም ሆነ ከከሳሽ ጋር የብድር ውል ግንኙነት የነበራቸው ስለመሆኑም የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ያስረዱበት አግባብ የለም፡፡ በዚህም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ በተመለከተ ከተከሳሽ ጋር ባላቸው ግንኙነት የተሰጣቸው መሆኑን ያስረዱበት አግባብ በሌለበት ሁኔታ በቼኩ የተመለከተው ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ሊጠይቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ በመስጠት ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ውሳኔ
- ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም፡፡
- ተከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 5223
የመ/ቁ 261663
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳኛ፡- ሀዲስ ነቃጥበብ
ከሣሽ ፡- ወ/ሪት ኢለን ንጉስ
ተከሳሽ ፡- አቶ ገ/ፃድቅ ካህሳይ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡
ፍርድ
ከሣሽ በመጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም በአጭር ስነ-ስርዓት ፅፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ተከሳሽ ለከሳሽ የቼክ ቁጥሩ 61206575 የሆነ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ያዘዘ ቼክ ፈርመው የሠጡኝ ቢሆንም ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ ሳቀርብ ባንኩ ሂሳቡ በቂ ስንቅ የለውም በማለት ቼኩ ሣይከፈልበት ተመልሷል፤ በመሆኑም ተከሣሽ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰብኝን ወጪና ኪሣራም እንዲተኩ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ተከሣሽ የመከላከያ ማስፈቀጃ አቅርበው ክሱን እንዲከላከሉ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት በጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ከሳሽ በተከሳሽ የተሰጠኝ ነዉ ያሉት ሰነድ ክፈል በሚለዉ ሁለት መስመሮች ቦታ የተፃፈዉ ካሽ የሚል እና በዚሁ መስመር ላይ በድጋሚ አራት መቶ ሺ ብር የሚል ተፅፏል ፡፡ በዚህ ክፍት ቦታ የሚፃፈዉ የተከፋይ ስም እንደሆነ ከቼኩ ማንም ሰዉ መረዳት ይችላል፡፡ ከዚህ ዉጪ የብር መጠን በአኃዝ የሚፃፍበት ቦታ ምንም ነገር አልተፃፈም፡፡ የብር መጠን የሚፃፍበት ሁለት መስመሮች ላይ የብሩን መጠን በአኃዝ የሚገልፅ ወይም በዚህ ሰነድ ላይ በተከሳሽ መፃፍ በነበረበት ቦታ የተፃፈ የብር መጠኑን የሚያሳይ ምንም ነገር ያልተፃፈበት ሰነድ ነዉ፡፡ በመሆኑም ይህ ሰነድ በንግድ ህጉ የተዘረዘሩትን አንድ ቼክ መያዝ የሚገባዉን መስፈርቶች ያልያዘ ሰነድ በመሆኑ እንደ ቼክ ሊቆጠር ስለማይገዉ የከሳሽ ክስ ተቀባይነት የለዉም፡፡
ተከሳሽ ይህንን ቼክ ያዘጋጀሁት አቶ ዳንኤል ገ/ሕይወት ከተባሉት ግለሰብ ላይ ለተበደርኩት ገንዘብ ክፍያ ለመፈፀም ነዉ፡ ይህንን ቼክ አዘጋጅቼ ለአቶ ዳንኤል ገ/ሕይወት ስሰጣቸዉ በዚህ ቼክ ላይ በፊደል የተፃፈዉ ገንዘብ መጠን ብር በሚለዉ ቦታ መፃፍ ሲገባኝ በስህተት የተከፋይ ስም በሚፃፍበት ቦታ መፃፌንና የገንዘብ መጠኑ በፊደል መፃፍ በሚገባዉ ቦታ ደግሞ ባዶ መሆኑን አቶ ዳኒኤል ገ/ሕይወት ቼኩን ተቀብለዉኝ ካዩ በኋላ ሲነግሩኝ ቼኩ የፎርም አሞላል ችግር ያለበት ስለሆነ ክፍያ በዚህ ሰነድ ስለማይፈፀምልኝ ቀይርልኝ በማለት ሲጠይቁኝ፤ እኔም የአሁን ተከሳሽ ይህ ሰነድ የፎርም አሞላል ችግር ያለበት መሆኑን ተገንዝቤ በዚሁ ሰነድ ክፍያ ሊፈፀምበት አይችልም የሚል ከቅንነት የመነጨ እምነት አድሮብኝ ሰጥቻቸዉ የነበረዉን ሰነድ ተቀብያቸዉ የመኪናዬ ኪስ ዉስጥ በማስቀመጥ በምትኩ ብር 400,000.00 / አራት መቶ ሺ/ የተፃፈበትን ቁጥር 61206576 የሆነ ሌላ ቼክ ቀይሬ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ተከሳሽ ለከሳሽ በዚህ ቼክ ላይ የተፃፈዉን የገንዘብ መጠን ፅፎ ለመስጠት የሚያበቃ ሕጋዊ ግዴታ ወይም ግብይት (transaction) የሌለን ሲሆን ከሳሽ የሴት ጓደኛዬ የነበሩ በመሆኑ ብዙ ጊዜ በእኔ በተከሳሽ ተሽከርካሪ አብረን ስንጓዝ የነበረ በመሆኑ አጋጣሚዉን በመጠቀም ከቅን ልቦና ውጪ ለክሱ ምክንያት የሆነዉን ቼክ ከተሸከርካሪዬ ኪስ ዉስጥ የወሰዱ መሆኑን ተከሳሽ ያወኩት ከሳሽ በቂ ስንቅ የለዉም በማለት ማስመታታቸዉን ካወኩ በኋላ ነዉ፡፡
በመሆኑም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን የገንዘብ መጠን ለመፃፍ የሚያበቃ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግዴታ ግብይት (transaction ) በመካከላችን ሳይኖር ያለአግባብ ለመበልፀግ በማሰብ ያቀረቡት ክስ በመሆኑ ወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብቴ ተጠብቆ ክሱ ዉድቅ እንዲደረግላቸው በመጠየቅ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ክሱን በሰማበት እለት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ቼኩ የፎርም ችግር የሌለበት መሆኑ በከፋዩ ባንክ ተረጋግጧል፤ ቼኩን ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡበት ምክንያት ለመኪና ሽያጭ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ከከሳሽ ወስደው የመኪናው ስም እስኪዛወር ለዋስትና እንዲሆን ታስቦ የተሰጠ ነው ተከሳሽም ቼኩ ከተመታ በኋላ የባንኩ ስራ አስኪያጁ ዘንድ ቀርበው እከፍላለሁ ብለው ድርድር ሲያደርጉ ነበር በማለት የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸው ባንኩ የፎርም ችግር እያለበት መሆኑን እያወቀ ይህንን አለመግለፁ ቼኩን ህጋዊ አያደርገውም፤ ከከሳሽ ጋር ግብይት የለንም ፤ የመኪና ሽያጭን በተመለከተም በክሱ ላይ ያልተገለፀ ነው በማለት በፅሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይ? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለጉዳዩ ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች አኳያ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ከሣሽ ለክሱ መሠረት ያደረጉት ጉዳይ ቼክ ሲሆን ቼክ ደግሞ በን/ህ/ቁ 732/2 እንደ ንግድ ወረቀት ይቆጠራሉ ተብለው ከተዘረዘሩት የንግድ ወረቀቶች አንዱ ሲሆን ሀተታ የሌለበት ለክፍያ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት ስለመሆኑም በን/ህ/ቁ 827/ሀ እና 854 ስር ተመልክቷል፡፡ የቼኩ አምጪ ቼኩን ለክፍያ ለከፋዩ ባንክ አቅርቦ ቼኩ ሳይከፈልበት ከተመለሰ የቼኩ አውጪ ስለ ቼኩ አከፋፈል ዋስ በመሆኑ እና ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ በቼኩ ላይ የተፃፈውን ገንዘብ የቼኩ አውጪ እንዲከፍለው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ይህም በን/ህ/ቁ 840 እና 868 ስር ተመልክቷል፡፡
ክስ የቀረበበት ቼክ የተከሳሽ ሲሆን ቼኩ ለባንክ ለክፍያ በቀረበ ጊዜ በሂሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ የሌለው መሆኑን በመግለፅ ባንኩ የእንቢታ ማስታወቂያ የሰጠ በመሆኑ ቼኩ ክፍያ ሳይፈፀምበት የተመለሰ መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስዱ ናቸው፡፡ የቼክ አውጪ እንዲከፈልበት የወጣ ቼክ ሳይከፈልበት የተመለሰ እንደሆነ ገንዘቡን የመክፈል ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የቼክ አውጪ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ በተመለከተ ሊከፍል የማይገባበትን መከላከያ ማለትም ከቼኩ አምጪ ጋር ያለውን የግል ግንኙነት መሠረት ያደረገ በን/ህ/ቁ 717/1//3/፣ 849፣ 850 መሰረት እንዲሁም በን/ህ/ቁ 717/1/2/ ስር በተመለከቱት ከቼኩ አወጣጥ፣ ፎርም፣ የተፃፋ ቃላት ፊርማ መሠረት ያደረጉ ቼኩን የሚመለከቱ መከላከያዎች በማቅረብ ያስረዳ ሲሆን ነው ገንዘቡን እንዳይከፍል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው፡፡
በያዝነው ጉዳይ ከሳሽ ባቀረቡት መከራከሪያ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጡት ለመኪና ሽያጭ ሲሆን ተከሳሽ በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ከከሳሽ ወስደው የመኪናው ስም እስኪዛወር ለዋስትና እንዲሆን ታስቦ የተሰጠ መሆኑን ገልፀው የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ደግሞ ቼኩን ለከሳሽ ለመስጠት የሚያስችል ግንኙነት የሌላቸውና ቼኩ የፎርም ችግር ያለበት መሆኑን ከሳሽ ቼኩን ያገኙት ከቅን ልቦና ውጪ መሆኑን በመግለፅ የተከራከሩ ናቸው፡፡
ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ለመስራት ይችል ዘንድ የግራ ቀኙ ምስክሮችን አስቀርቦ የሰማ ሲሆን 1ኛየከሳሽ ምስክር ከሳሽ ራሳቸው ሲሆኑ በሰጡት የምስክርነት ቃል ተከሳሽ የልብስና ሽቶ ደንበኛዬ ናቸው ስራ ቦታ መጥተው መኪናዬን ልሸጣት ስለሆነ አንቺ በብር 600ሺህ ግዢኝ አሉኝ ተከሳሽም በጥር 9 ቀን 2010 ዓ/ም ፒክ አፕ የሆነች መኪና ይዘው መጥተው አሳዩኝ ሊብሬው የታለ ስላቸው አመጣለሁ ቤት ረስቼው ነው አሉኝ በእለቱም በጥሬ ገንዘብ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ ሰጠኋቸው መኪናው መጥቷል ያሉኝ በመሆኑ ሊብረውን ረስቼዋለሁ ያሉ በመሆኑ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ሰጥተውኝ በ20ቀን ውስጥ ስሙን አዞርልሻለሁ አሉኝ ውል እንዋዋል ስላቸው ችግር የለም መኪናው ገብቷል ዛሬ ነገ እያሉ ቆዩ ብሩን መልሱልኝ ስላቸው እሰጥሻለሁ እያሉ የቆዩ በመሆኑ ቼኩን አስመታሁ ብር 200ሺህ ስም ሲዞር ለመጨመር ነበር የተነጋገርነው ፤ ብሩን ለተከሳሽ ስሰጥም አቶ ይበቃል ገ/እግዚአብሔር የተባለ ግለሰብ ነበር ሲሉ መስክረዋል፡፡ 2ኛየከሳሽ ምስክር የባንኩ ሰራተኛ ሲሆኑ ቼኩ በቂ ስንቅ የለውም በማለት የመታሁት እኔ ነኝ የባንኩ ኦፊሰሮች ቼኩን በተመለከተ ደውለው ተነጋግረው ነበር ምን እንደተነጋገሩ ግን አላወኩም ብለዋል፡፡ 3ኛየከሳሽ ምስክርም የባንኩ ሰራተኛ ሲሆኑ ከሳሽ ይዘው የመጡት ቼክ በሂሳቡ ገንዘብ አልነበረውም በዚህም ምክንያት ለተከሳሽ ደወልኩ ተከሳሽም ጠብቀኝ ብለው ስልኩ ተዘጋ ተከሳሽ ባንኩ ዘንድ መጥተውም ቼኩን ተሰርቄ ነው ለፖሊስ አመለክታለሁ ሲሉ ነበር በማለት መስክረዋል፡፡
1ኛ የተከሳሽ ምስክር ተከሳሽ ሲሆኑ በሰጡት የምስክርነት ቃል ቼኩን ለአቶ ዳንኤል የፃፍኩት ነበር በመንደር ውል ብር 400ሺህ አበድረውኝ የነበረ በመሆኑ አቶ ዳንኤል ቼኩን ከወሰዱ ከ1 ሰአት በኋላ ደውለው ቼኩ በስም ቦታ ብር የተፃፈበት በመሆኑ ችግር አለበት ና አሉኝ እኔም ሄጄ ቼኩን በመቀበል ቀየርኩላቸው የተቀበልኩትን ቼክም መኪና ውስጥ አደረኩት ከሁለት ወር በኋላ በ18/07/2010 ዓ/ም ከባንክ ሲደወል ነው ቼኩ የጠፋ መሆኑን ያወኩት በእለቱም ከከሳሽ ጋር ነበርን ለባንኩም የጠፋ ቼክ ነው እንዳትከፍሉ አልኳቸው ከባንክ እንደተነገረኝም ለፖሊስ አመለከትኩ ከዚህ በኋላ ነው ከሳሽ በ19/07/2010 ዓ/ም ሄደው ያስመቱት ከሳሽ የሴት ጓደኛ እጮኛዬ በመሆናቸው መኪና ውስጥ አብረን እንሄድ ነበር የንግድ ግንኙነት የለንም ብለዋል፡፡ 2ኛየተከሳሽ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል ለተከሳሽ በታህሳስ 27 ቀን በተደረገ የብድር ውል ብር 400ሺህ ሰጥቻቸው ተከሳሽ ቼክ ሰጡኝ ከተከሳሽ ጋር ከተለያየን በኋላ ቼኩን ሳየው ክፈል በሚለው ላይ ካሽ ከታች ደግሞ በፊደል ብር 400ሺህ ይላል ብር በሚለው ላይ አልተፃፈም ነበር ወጋገን ባንክ ሄደን ስጠይቅ መስተካከል አለበት ስላሉን ለተከሳሽ ደውዬላቸው የሰጡኝን ቼክ መልሼላቸው ሌላ ቼክ ሰጡኝ ያሉ ሲሆን 3ኛየተከሳሽ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል ከ2ኛየተከሳሽ ምስክር ጋር በእለቱ የነበሩ መሆኑን በመግለፅ 2ኛየተከሳሽ ምስክር ከሰጡት የምስክርነት ቃል ተመሳሳይ የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል፡፡ 4ኛየተከሳሽ ምስክር በበኩላቸው ከሳሽ የተከሳሽ ሴት ጓደኛ ናቸው ብዙ ጊዜ ሶስታችንም አብረን ምግብ እንበላ ነበር ተከሳሽም ከሳሽን በመኪና ይሸኟቸው ነበር ሲሉ መስክረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም መዝገቡን እንደመረመረው ተከሳሽ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ ለከሳሽ ያልሰጡና የግል ግንኙኘት ሳይኖራቸው ከሳሽ ከቅን ልቦና ውጪ ያገኙት መሆኑን የማስረዳት ሸክም ያለባቸው ሲሆን በተከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ይህ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ቼክ ተከሳሽ ለነበረባቸው እዳ ለመክፈል አዘጋጅተውት የነበረ መሆኑንና ስህተት ያለበት በመሆኑም ተከሳሽ ቼኩን እንዲቀይሩላቸው ጠይቀዋቸው ሰጥተዋቸው ከነበረው ግለሰብ (2ኛየተከሳሽ ምስክር) ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ የተቀበሉ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ተከሳሽ ቼኩን ለ2ኛምስክራቸው የሰጠሁት የነበረ ነው ባሉበት በታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ/ም ም ከ2ኛምስክራቸው ጋር የብር 400ሺህ የብድር ውል ያደረጉ መሆኑን የሚያስረዳ የብድር ውል ስምምነት ያቀረቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ ቼኩን በተመለከተ የጠፋባቸው መሆኑን በመግለፅ በመጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ/ም ለፖሊስ ያመለከቱ ስለመሆኑ ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ ያረዳል፡፡
ከላይ ከተመለከትናቸው የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም ከቀረቡት ምስክሮች ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ክስ የቀረበበትን ቼክ ለመስጠት የሚያስችል ግንኙነት እንደሌላቸው ቼኩም ለ2ኛየተከሳሽ ምስክር ተሰጥቶ የነበረ መሆኑን ፍ/ቤቱ ለመገንዘብ የቻለ ሲሆን ከሳሽ ራሳቸው ቀርበው በሰጡት የምስክርነት ቃል ከተከሳሽ በብር 600ሺህ ለመግዛት ለተስማሙት ተሽከርካሪ ክፍያ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ የከፈሉና ለዋስትናም ይህንን ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ ተከሳሽ እንደሰጧቸው ተሽከርካሪውንም ተከሳሽ በስምምነቱ መሰረት ያላስረከቧቸው በመሆኑ ለተከሳሽ የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ክሱን ያቀረቡ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ሆኖም ከሳሽ ይህንን የሰጡትን የምስክርነት ቃል በሌላ ገለልተኛ በሆነ ምስክርም ሆነ የመኪና ሽያጭ ውል ከተከሳሽ ጋር አድርገው የነበረ መሆኑን በሰነድ ማስረጃ ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ገንዘቡን ለተከሳሽ ሰጠሁ ባሉበት ቀን ነበሩ በማለት የጠቀሷቸውን አቶ ይበቃል ገ/እግዚአብሔር የተባሉትን ግለሰብ እንኳን በማስረጃ ዝርዝር መግለጫቸው ላይ ያልጠቀሷቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ ቼኩ ከተመታ በኋላ ተከሳሽ የባንኩ ስራ አስኪያጁ ዘንድ ቀርበው እከፍላለሁ ብለው ድርድር ሲያደርጉ ነበር በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ከባንኩ ዘንድ የቀረቡት ምስክሮች በዚህ አግባብ ተከሳሽ ለመክፈል የተደራደሩ መሆኑን ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ይልቁንም 3ኛየከሳሽ ምስክር ተከሳሽ ባንኩ ዘንድ መጥተው ቼኩን ተሰርቄ ነው ለፖሊስ አመለክታለሁ ሲሉ እንደነበር የሰሙ መሆኑን ያስረዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ ከተከሳሽ ሊገዙት ያሉትን ተሽከርካሪ ተከሳሽ ይዘው መጥተው ያዩት መሆኑን እየገለፁ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሽን ውል እንዋዋል ስላቸው ችግር የለም መኪናው ገብቷል በማለት መኪናው ገና አገር ውስጥ ሳይገባና መኪናውን ሳያዩ ገንዘብ እንደከፈሉ በሚያስረዳ መልኩ የምስክርነት ቃል በስጠታቸው ሲታይም የሰጡት የምስክርነት ቃል እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ በዚህም ይህ በሆነበት አግባብ ከሳሽ ከተከሳሽ ለመግዛት ለተስማሙት ተሽከርካሪ ክፍያ ብር 400,000 (አራት መቶ ሺህ ) ለተከሳሽ የሰጡ በመሆኑ የተሰጣቸው ቼክ መሆኑን በመግለፅ ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚህም ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆነውን ቼክ በተመለከተ ከተከሳሽ ጋር ባላቸው ግንኙነት የተሰጣቸው መሆኑን ከተከሳሽ በተሻለ ያስረዱበት አግባብ የሌለ ሲሆን ይህ ከሆነ ደግሞ በቼኩ የተመለከተው ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ሊጠይቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ በመስጠት ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ውሳኔ
- ተከሣሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ አይገባም፡፡
- ወጪና ኪሣራን በተመለከተ ከሳሽ ለተከሳሽ የጠበቃ አበል ብር 40,000 ፣ የቴምብር ቀረጥ ብር 10 ፣ ልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 1,000 ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ መብት ነው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4727
መ/ቁ 181609
ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- ጎስፕላ ትሬዲንግ ኃ. የተ.የግል.ማህብር ስራ አስኪያጅ ፡- ሽመልስ አበበ፡- ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አቶ ፍቃዱ ተስፋሁን፡- ጠበቃ በላይነዉ አሻግሬ፡- ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርማራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ/ም በተፋጠነ ስነ ሰርዓት ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ ዕቁብ በሚሰበሰቡበት አቤነዘር ብራንድ የህጻናት አልባሳት ስም በተዘጋጀ የዕቁብ ደብተር ከሳሽ በመ/ቁ 01 መደቡ የብር 440/አራት መቶ አርባ/ ለሆነዉ 22 ጊዜ፤ በመ/ቁ 02 መደቡ የብር 2,200(ሁለት ሺህ ሁለት መቶ) ለሆነዉ 32 ጊዜ፤ መ/ቁ 03 መደቡ የብር 2,200 (ሁለት ሺህ ሁለት መቶ) ለሆነዉ 32 ጊዜ፤መደቡ የብር 1,100(አንድ አንድ መቶ) ለሆነዉ 22 ጊዜ እንዲሁም እንጎቻ ባህላዊ ምግብ ቤት ዉስጥ ተከሳሽ ለሚሰበስበዉ ባለ 440 (አራት መቶ አርባ)15 ጊዜ በአጠቃላይ ብር 181,000.00 (አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ከላይ ለተጠቀሱት የዕቁብ መደቦች የጣሉ መሆኑን ከሳሽ በዕቁቦቹ ተሳታፊ የሆኑት ተከሳሽ የዕቁቡን 2ኛ ዕጣ ያለውድድር የሚሰጧቸዉ መሆኑን ቃል ስለገቡላቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ቃል በገባላቸዉ መሰረት የ2ኛዉን ዙር ዕቁብ ሊሰጣቸዉ ያልቻለ በመሆኑ ዕቁቡን ያቋረጡ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ብር 181,000.00 (አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) እንዲከፈላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥሯል፡፡ ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አአባሪዎቹ ለተከሳሽ ደርሶ ተከሳሽ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ ያቀረቡትን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኃላ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡትም የመከላከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርቧል በፍሬ ነገሩ ላይ መልስ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ከሳሽ የህዳር ወር የ30 ቀናት የእቁብ ክፍያ ሳይፈጽሙ የበሰለ ክፍያ በተከሳሽ ላይ ያላቸዉ በማስመሰል በተፈጠነ ስነ ሰርዓት ክስ ማቅረባቸዉ አግባብብነት የለዉም የቀረበዉ ክስም ውልን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ክሱ መቅረብ ያለበት ዉሉ በተደረገበት ወይም በሚፈጽመበት ስለሆነ የተከሳሽ የንግድ ቦታ ቦሌ ክፍለ ከተማ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል የግዛት ክልል ስልጣን የለዉም እንዲሁም ከሳሽ በእቁቡ ደንብ መሰረት የእቁብ ተመላሽ ገንዘብ ሊጠይቁ የሚገባዉ እቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወር በኃላ በመሆኑ የቀረበዉ ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸዉን ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስም ደግሞ ከሳሽ ለመጀመሪያዉ ዕጣ መክፈል የነበረበት ብር 191,400(አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ ከሳሽ የከፈለዉ ብር 181,000(አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) መሆኑን ተከሳሽ ምንም እንኳን የእቁቡ ደንብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዕጣ ለእቁቡ አከፋፈል ዋስትና እንዲሆን የሚደነግግ ቢሆንም ከሳሽ የነበረበትን ችግር ከግምት ዉስጥ በማስገባት የባለ 1,100/አንድ ሺህ አንድ መቶ) የሆነዉን ዕቁብ ሁለተኛዉን ዕጣ ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ መሆኑን፤ከሳሽ ለ2ኛ ዕጣ የሚሆነዉን ክፍያ በየቀኑ መክፍል የነበረበት መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ ይህን ክፍያ ከሳሽ ያልፈጸሙ መሆኑን ፤ከሳሽ የህዳር ወር የ30 ቀናት የዕቁብ ክፍያ የሆነዉን ብር 191,400( አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) ያልከፈለ ቢሆንም ከሳሽ ክፍያዉን ቢፈጽም ኖሮ ከሚያገኘዉ ብር 240,000.00(ሁለት መቶ አርባ ሺህ) ላይ ያልከፈለዉን ብር 191,400(አንድ መቶ ዘጠኛ አንድ ሺህ አራት መቶ) ተቀናሽ በማድረግ ብር 60,000.00 (ስልሳ ሺህ) እንዲወስድ ሲጠየቅ አምቢተኛ የሆነ መሆኑን፤ከሳሽ የዕቁብ ተመላሽ ገንዘብ መጠየቅ የሚቻለዉ በዕቁብ ደንብ መሰረት ዕቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወር በኃላ መሆኑን ከሳሽ በአሁኑ ጊዜ የእቁቡ ገንዘብ ሊመለስለት ይገባል እንኳን ቢባል በዕቁቡ ደንብ አንቀጽ 6 መሰረት ብር 36,200.00( ሰላሳ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ) ቅጣት እንዲሁም የሰብሳቢ የአግልግሎት ክፍያ ብር 139,200(አንድ መቶ ሰለሳ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ) በድምሩ ብር 175,400.00( አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ አራት መቶ) ከሳሽ በአጠቃላይ ከከፈለዉ ብር 181,000.00(አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ላይ ተቀናሽ ተድርጎ ለከሳሽ ሊከፈል የሚገባዉ ብር 5,600/አምስት ሺህ ስድስት መቶ) ብቻ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሱን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሚያዚያ 16 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ተከሳሽ የዕቁቡን ዕጣ 2ኛ ዙር ያለውድድር ሊሰጣቸዉ ቃል የገባ መሆኑን ተከሳሽ በገባዉ ቃል መሰረት የ2ኛዉን ዙር ዕቁብ እንዲሰጣቸዉ ሲጠይቁ ተከሳሽ እምቢተኛ የሆነ መሆኑን የ2ኛዉን ዙር ዕቁብም ለማግኝት ከሳሽ መክፍል የሚጠበቅበት ብር 33,000.00(ሳላሳ ሶስት ሺህ) መሆኑን ከሳሽ ብር 35,200(ሰላሳ አምስት ሺህ) የከፈለ መሆኑን በቀንም መጣል ይጠበቅባቸዉ የነበረዉ ብር 1,100 (አንድ ሺህ አንድ መቶ ) መሆኑን የሰብሳቢ የአገልግሎት ክፍያ የተባለዉን የማያውቁ መሆኑን፤ በማስረጃነት የቀረበዉንም የእቁብ መተዳደሪያ ድንብ የማያውቁት መሆኑን ተከሳሽም ዕቁቡን ሲቀላቀሉ ያላሳያቸዉ መሆኑን የሰብሳቢ የአግልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ሊከፍሉ የማይገባ መሆኑን በመግለጽ ሲከራከሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ዕቁቦቹ አምስት መደቦች ያላቸዉ መሆኑን በአያንዳንዱ ዙርም ከሳሽ ብር 191,400.00(አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መከፍል የሚጠበቅባቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ከሳሽ የመጀመሪያዉን ዙር እንኳን ሙሉ ክፍያ ያልከፈሉ መሆኑን 2ኛዉን ዙር ምንም አይነት ክፍያ ያልከፈሉ መሆኑን ነገር ግን ሙሉዉን ክፍያ የመክፍል ግዴታ ያለባቸዉ መሆኑን እንዲሁም ከሳሽ የዕቁቡን መተዳደሪያ ድንብ አናውቀዉም በማለት ያቀረቡት ክርክር አግባብነት የሌለዉ መሆኑን በመግለጽ ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡
የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ተከሳሽ ያቀረባቸዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ክርክሩ ወደ መደበኛ ክርክር የተለወጠ በመሆኑ ጉዳዩ በተፋጠነ ስነ ስርዓት መቅረቡ አግባብነት የለዉም በማለት ተከሳሽ ያቀረበዉ መቃወም አግባብነት ያለዉ ባለመሆኑ እንዲሁም ይህ ፍርድ ቤትም በአዋጅ ቁጥር 25/88 መሰረት ጉዳዩን ለማየት የግዛት ክልል ስልጣን ያለዉ በመሆኑ የተከሳሽን የመጀመሪያ ደረጃ መቃሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል፡፡
በመቀጠል ፍርድ የመረመረዉ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፈል ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ ነዉ፡፡
እንደመረመረዉም ከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን ገንዘብ ክፍያ የፈጸሙ መሆኑን ተከሳሽ ካለመካዳቸዉም በላይ ከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀዉን ገንዘብ የከፈሉ መሆኑን የቀረቡት የእቁብ ክፍያ ደብተሮች ያስረዳሉ፡፡
ተከሳሽ ለከሳሽ በ2ኛ ዙር ባለ 1,100( አንድ ሺህ አንድ መቶ) መደቡን ዕቁብ ያለውድድር ለከሳሽ ለመሰጠት ቃል የገባ መሆኑን በመከላከያ መልሱ ላይ ከማመኑም በላይ ክስ በተሰማ ጊዜም ለችሎቱ ገልጸዋል ፡፡
ተከሳሽ የ2ኛ ዙሩን አቁብ ለከሳሽ ያልሰጠሁት በክሱ ላይ ለተጠቀሱት ለአምስቱም አይነት የዕቁብ መደቦች በአጠቃላይ ብር 191,400 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መክፍል ይጠበቅባቸዋል በማለት የተከራከረ ቢሆንም አምሰቶቹም በክሱ ላይ የተጠቀሱት የዕቁብ መደቦች እራሳቸዉን ችለዉ የሚቆመ መሆኑን ግራ ቀኙ በክርክር ሂደት የገለጹ ከመሆኑ አንጻር እና ተከሳሽም ለከሳሽ ያለውድድር ሊሰጥ የነበረዉ ባለ 1,100 የሆነዉን መድብ ከመሆኑ አንጻር ተከሳሽ በ2ኛ ዙር ዕጣዉን ያለውድድር ለማገኝት ብር 191,400 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) መከፈል ነበረባቸዉ በማለት ያቀረበዉ ክርክር እርስ በእርሱ የሚጣርስ ነዉ፡፡
በተለመደዉ የዕቁብ አሰራርም ከሳሽ የሚጠበቅባቸዉ ያለውድድር ለሚያገኙት የዕቁብ ክፍያ ዕጣዉ እስኪሰጣቸዉ ድረስ የሚፈለግባቸዉን ክፍያ መክፈል ነዉ፡፡ ከሳሽ ለባለ 1,100 መደብ ብር 35,200(ሰላሳ አምሰት ሺህ ሁለት መቶ) የከፈሉ መሆኑን ክርክር አቅርቧል በማስረጃም አረጋግጧል ተከሳሽ በበኩሉ ለዚህ መደብ እቁብ በተከሳሽ ብር 35,200 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ) ያልተከፈለ መሆኑን በመግለጽ ያቀረበዉ ማስተባበያ የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ባለ 1,100 መደቡን እቁብ ለማገኝነት ተገቢዉን ክፍያ የከፈሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሽ በገባዉ ቃል መሰረት ባለ 1,100 ዉን መደብ ለከሳሽ በ2ኛ ዙር ለመስጠት እምቢተኛ መሆኑን አልካደም፡፡ ይህም የተከሳሽ ተግባር አይነተኛ የውል መጣስ በመሆኑ እና ከሳሽም ተከሳሽ 2ኛዉን ዙር ዕቁብ ያለ ውድድር ለማግኝት በዕቁቡ ታሳፊ የሆኑ በመሆኑ እና ተከሳሽም ባቀረበዉ ክርክር ከሳሽ ወደ ዕቁብ የገቡት 2ኛዉን ዙር ዕቁብ ያለውድድር የሚሰጧቸዉ መሆኑን በማመን መሆኑን ያልካዱ በመሆኑ ከሳሽ ዕቁቡን ማቋረጡ በአገብቡ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ለከሳሽ ተመላሽ ሊደረግ የሚገባዉ ገንዘብ ብር 5,600 ነዉ ከሳሽ አጠቃላይ ከከፈሉት የገንዘብ መጠን ላይ የሰብሳቢ ጠቅላላ አግልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ብር 175,400(አንድ መቶ ሰባ አምስት ሺህ) በዕቁቡ ደንብ መሰረት ተቀናሽ ሊደረግ ይገባል በማለት ክርክር አቅርቧል ከሳሽ በበኩላቸዉ በማስረጃነት የቀረበዉን የዕቁብ ደንብ አናወቀወም የሰብሳቢ ጠቅላላ የአገልግሎት ክፍያ እና ቅጣት ተቀናሽ ሊደረግ አይገባም በማለት ነዉ፡፡
የእቁብ ደንብ የአባላቱን መብትና ግዴታ የሚገዛ እንደመሆኑ መጠን ድንቡ በአባላቱ ላይ አስገዳጅ እንዲሆን የዕቁቡ አባላት ደንቡን አይተዉ ተመልክተዉ ፈቃዳቸዉን መሰጠት ያለባቸዉ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 1678 እና 1679 መረዳት የሚቻል ሲሆን አንድ የእቁብ ደንብ እንደ ውል የሚቆጠር በመሆኑ አባላቱ እንዲገደዱበት ፈቃዳኛቸዉን መስጠት አለባቸዉ፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ተከሳሽ ከሳሽ የእቁቡ አባል ሲሆኑ የዕቁቡን ደንብ ያልተመለከቱ መሆኑን የእቁቡ ድንብ ላይ ፈቃዳቸዉን ሰጥተዉ ያልፈረሙ መሆኑን አልካዱም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ፈቃዳኛዉን ባለሰጡበት ደንብ የሚገደዱበት የህግ መሰረት የለም፡፡በመሆኑም
ተከሳሽ ከሳሽ አጠቃላይ ከከፈሉት የገንዘብ መጠን ላይ የሰብሳቢ ጠቅላላ የአግልግሎት ክፍያ እንዲሁም ቅጣት ተቀናሽ ሊደረግ ይገባል በማለት ያቀረቡት ክርክር የማስረጃ ፤የህግ እንዲሁም የተለመደ አሰራር ድጋፍ የሌለዉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ሌላዉ ተከሳሽ ያቀረቡት ክርክር ከሳሽ የእቁብ ተመላሽ ገንዘብ ሊጠይቁ የሚገባዉ ዕቁቡ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወራት በኃላ ነዉ በማለት ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ተከሳሽ ለዚህም መሰረት ያደረጉት በማስረጃት ያቀረቡትን የእቁብ ደንብ ነዉ ይሁን እንጂ ይህ ደንብ በከሳሽ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ ከሳሽ ፈቃዳኛዉን ያልሰጡትበት በመሆኑ ሊስገድዳቸዉ አይችልም፡፡ ይልቁንም ተከሳሽ የገባዉን ቃል በማጠፉ እና የዕቁብ ሂደትም ውልን መሰረት የሚደረግ በመሆኑ እና ተከሳሽም 2ኛዉን ባለ 1,100 ዕጣ ዕቁን ለከሳሽ ለመስጠት እምቢተኛ መሆኑ ሲታይ ተከሳሽ አይነተኛ የውል ጥስት የፈጸመ መሆኑን የሚያስረዳ ስለሆነ እና እንዲህ በሆነ ጊዜም ዉሉ ቀሪ ሆኖ ግራ ቀኙ ወደነበሩበት ሊመሰለሱ የሚገባ መሆኑን መረዳት የሚቻል ስለሆነ ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊመልስ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ ብር 181,000.00( አንድ መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ) ከጥር 27 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታስብ 9% ወልድ ጋር ለተካሳሽ ይክፈሉ፡፡
- ወጪና ኪሳራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 4,545፤ለቴምብር ቀረጥ ብር 30 እንዲሁም የጠበቃ አበል ብር 18,000 ተከሳሽ ለከሳሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ፡፡
መዝገቡ ተዝግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 3657
መ/ቁ 180219
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- አቶ ኃይለስላሴ አስርስ ደሳለኝ ከጠበቃ መለስ ግርማይ ጋር ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አቶ አብርሃም ጌታሁን ደያም፡- ጠበቃ ሳሙኤል ደመቀ ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ መርምሮ ተገቢዉን ለመስራት ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤተታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃልና ምስል በንግድ ምልከትነት ያስመዘገቡ መሆኑን ከ25/1/2009 ዓ/ም እስከ 25/1/2016 ዓ/ም ድርስ የሚቆይ የአዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ የተሰጣቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ያለ እርሳቸዉ ፈቃድ እና እውቅና ያስመዘገቡትን የንግድ ምልክት እየተጠቀሙበት የሚገኙ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ይህን ድርጊታቸዉን እንዲያቁሙ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ እንድ ክስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰንድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡
ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ድርሶ ተከሳሽ ጥር 3 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልሳቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍርሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ያቀረባቸዉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ፍርደ ቤቱ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች መርምሮ ውድቅ ያደረጋቸዉ በመሆኑ ከዚህ ማስፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡
ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ስም Sun land international Hotel የሚል ሳይሆን Sun land Hotel የሚል መሆኑን international የሚለዉ ቃልም በተከሳሽ የንግድ ስም ዉስጥ የሌለ መሆኑን በጋዜጣ ላይ የወጣዉ የከሳሽ የንግድ ምልክት በኢታሊክስ አጻጻፍ Sun land የሚል መሆኑን ነገር ግን የተከሳሽ የንግድ ስም በካፒታል ሌተር SUN LAND HOTEL የሚል በመሆኑ ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተቀራራቢ እንጂ ተመሳሳይ ነዉ ሊባል የማይችል መሆኑን በጋዜጣ የወጣዉ የከሳሽ የንግድ ምልክት ምስል እና ከሳሽ ከክሱ ጋር አያይዞ በማስጃነት ያቀረበዉ ምስል ተመሳሳይነት የሌላቸዉ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልክቱን በስማቸዉ ያስመዘገቡ ስለመሆኑ የምስክር ወረቀት ያላቀረቡ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልከቱን የምስክር ወረቀት ባላቀረቡበት ሁኔታ የንግድ ምልከቱ በሶስተኛ ወገኖች ላይ ተፈጻሚነት የሌለዉ መሆኑን ተከሳሽ suland hotel የሚለዉን የንግድ ስም ስልጣን ባለዉ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት ያስመዘገቡ መሆኑንአዕምሮዊ ንብረት የንግድ ምልክትን ምዘገባ የሚያካሂድ መሆኑን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደግሞ የንግድ ስም ለመመዘገብ ስልጣን የተሰጠዉ መሆኑን በዚህም ምክንያት አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ ሊሆን የሚችልበት አግባብ የሌለ መሆኑንአንዱ በሌላኛዉ ላይ የበላይነት አለዉ የሚባል ከሆነምመብቱን ቀድሞ ያገኘዉ ማን ነዉ የሚለዉ ነጥብ መተያት ያለበት መሆኑን ተከሳሽ የንግድ ስም የምስር ወረቀትያገኘዉ በ10/5/2009 ዓ/ም መሆኑን ከሳሽ በዚህ ጊዜ የንግድ ምልዕክቱንበጋዜጣ ማስታወቂያ አሳውጆ ተቃዋሚ የሚቀርብ ከሆነ ሲጠባበቅ የነበረ መሆኑን የምስከር ወረቀት ሊያገኝ የሚችለዉም ከዚህ ጊዜ በኃላ መሆኑን ከሳሽ የንግድ ምልክት አስመዝገቢያለሁ በማለት የሚከራከሩ ቢሆንም በንግድ ስሙ የከፈተዉ ሆቴል ወይም የሚንቀሳቅሰዉ ንግድ የሌለ መሆኑን በአንጻሩ ደግሞ ተከሳሽ ባስመዘገበዉ የንግድ ስም በስራ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከሳሽ በንግድ ስሙ እንዳይጠቀም የሚከለከል ከሆነ ያገኘዉን መልካም ስም የሚያጣ መሆኑንበመገለጽ የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልዕክት ከሳሽ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ የሚሰጡት አገልግሎት ተመሳሳይ መሆኑን የእዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ ጽ/ቤት በሰጠዉ ማስረጃ ተከሳሽ የሚጠቀምበት የንግድ ምልክት የከሳሽ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን፤ sun land hotel የሚለዉ ቃል እና የከሳሽ የንግድ ምልክት በተከሳሽ ሆቴል ላይ በተሰጠቀለዉ ቦርድ ላይ ያለ መሆኑን የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀትም የተሰጣቸዉ መሆኑን ተከሳሽ የንግድ ምልዕክቱን የተጠቀሙት ያለፈቃዳቸዉ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር sun land hotel የሚል የንግድ ስም ለተከሳሽ መስጠቱ ህገወጥ መሆኑን በእዕምሮ ፈጣራ ዉጤት የተያዘን ስም በንግድ ስምንነት ለተከሳሽ መስጠቱ አግባብነት የሌለዉ መሆኑንተከሳሽ የቀደምነትነት መብት የሌላቸዉ መሆኑንየቅድምትንት መብት ያለዉ ከሳሽ መሆኑን ተከሳሽ የተጠቀመዉ የንግድ ምልዕክቱ ላይ ያለዉን ስም እና መስሉን ጭምር መሆኑን በመግለጽ ክርክራቸዉን ያቀረቡ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር የንግድ ምልዕክት ያስመዘገበ ሰዉ በመብቱ መስራት የሚችለዉ የምስክር ወረቀቱ በእጁ በገባ ጊዜ መሆኑን እዕምሮዊ ንብረት በተቀመጠ የምስክር ወረቀት መብት ሊቋቋም የማይችል መሆኑን የንግድ ምልክቱን በጋዜጣ ሊወጣ የሚገባ መሆኑን ክሱም መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር መሆኑንገልጸዉ የመከላካያ መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክሯል፡፡
የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡
ከሳሽ የሚከራከረዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት ስለተጠቀም እና ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን ከሳሽ ከሚሰጠዉ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መሳከርን የሚያስከትል ስለሆነ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀም ሊወሰንልን ይገባል በማለት ነዉ፡፡
ከከሳሽ ክርክር አንጻር ምላሽ ሊያገኝ የሚገባዉ ጉዳይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 501/2000 ያገኘዉን የብቸኝነት መብት(exclusive right) የሚጠስ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉ ሲሆን ይህ መልስ ከመስጠታችን በፊት የንግድ ስምን እና የንግድ ምልከት አገልግሎታቸዉ/ጥቅማቸዉ ምን እንደሆነ መለየቱ ተገቢ ነዉ፡፡
ከዚህ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 2(12) እንደተመለከተዉ የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰዉ ዕቃዎች ወይም አገለግሎቶቸ ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን የንግድ ምልክቱም ቃላቶችን፤ዲዛይኖችን፤ ፊደሎችን፤ቁጥሮችን፤ቀለሞችን ወይም ዕቃዎችን ወይም የመያዣቸዉን ቅርጾችወይም የነዚህን ቅንጅቶች ሊይዝ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
የንግድ ምልክትን ለመመዘገብም ስልጣን የተሰጠዉ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ስለመሆኑ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ዓ/ም አንቀጽ 2(10) እንደተደነገገዉ የንግድ ስም ማለት አንድ ነጋዴ ለንግድ ስራዉ የሚጠቀምበት እና በህብረተሰቡ ዘንድበግልጽ የሚታወቅበት ስም ነዉ በሚል ተደንግጓል፡፡ ማንኛዉም ነጋዴ የንግድ ስሙን በግለጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ እንዳለበትም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ዓ/ም አንቀጽ 18(1) ተድንግጓል፡፡
የንግድ ስም የመመዘገብ ስልጣንም የንግድ ሚኒስቴር እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ስር ተመልክቷል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለዉ የንግድ ምልክት የሚያገለግለዉ የአንድን ድርጅት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚሰጡት አገልግሎት/ከሚያቀርቡት ዕቃዎች ለመለየት ሲሆን የንግድ ስም ደግሞ አምራቹ ወይም አገልግሎት ሰጪዉ አገልግሎቱን ወይም ዕቃዎቹን ለህበረተሰቡ የሚያቀርብበት ስም መሆኑን እንዲሁም ነጋዴው በንግድ ቦታዉ የንግድ ስሙን በሚታይ ቦታ መለጠፍ በህግ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የከሳሽ የንግድ ምልክት በምዝገባ ቁጥር LTM/4386/2009 E.C የተመዘገበ መሆኑን፤ከሳሽምከ25/1/2009 ዓ/ም አስከ 25/1/2016 ዓ/ም ድረስ ለንግድ ምልክቱ ጥበቃ የተሰጠዉ መሆኑን የንግድ ምልከቱም ለሆቴል አገልግሎት በዓለም አቀፍ ምድብ 43 የተመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ሚያዚያ 15 ቀን 2011 ዓም ለፍርድ ቤቱ የላከዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ ይህም የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት በአዋጅ ቁጥር አንቀጽ 501/98 አንቀጽ 15 መሰረት የተሰጠ መሆኑን እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረበዉ የንግድ ምልክት ባለቤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የንግድ ምልከቱ የተመዘገበለት ሰዉ የንግድ ምልከቱን ከተመዘገበበት ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር አያይዞ የመጠቀም ወይም ሌላ ሰዉ እንዲጠቀምበት የመፈቀድ መብት የሚኖረዉ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(1) ስር ተመልክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ምልከት ባለቤት የሆነ ሰዉ ሌሎች ሰዎች የንግድ ምልክቱን ወይም ህዝብን ሊያሳስት የሚችል ማናቸዉንም የንግድ ምልከቱን የሚመስል መለያ የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበባቸዉ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ወይም ህዝብን ሊያሳስት በሚችል አኳን ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ እንዳይጠቀሙ፤የንግድ ምልከቱን ወይንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ ያለ በቂ ምክንያቶች ጥቅሙን በሚጎዳ አኳን እንዳይጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለማገድ የሚችል ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 26(2)(ሀ)(ለ)(ሐ) የሚደነግግ ሲሆን አንድ አይነት መለያ ለአንድ አይነት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ሲውል የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት መውስድ የሚቻል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 26(3) ስር ተመልክቷል፡፡
ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረቡት የንግድ ምልክትከላይ የተጠቀሱት የብቸኘነት መብት (exclusive right) ያላቸዉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተከሳሽ የሚጠቀመዉየንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ፤ተከሳሽ የተሰማራበት የስራ ዝርፍም የሆቴል አገልግሎት መሆኑን እንዲሁም ተከሳሽ በንግድ ምልክትነት ያስመዘገበዉን ስም እና መስል በሆቴሉ ላይ ሰቅሎ ሲጠቀም የነበረ መሆኑን በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች አስረድቷል እንዲሁም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃል በንግድ ምልክትነት ለሆቴል አገልግሎት ያስመዘገቡ መሆኑን የአዕምሮዊ ንብረት ለፖሊስ በቀን 25/12/2009 ዓ/ም የሰጠዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ ከዚህ አንጻር አማካኝ (average) የሆነ ተጠቃሚን ብንወስድ ተከሳሽ SunlandHotel የሚለዉን ቃል ከሳሽ በንግድ ምልክትነት ካስመዘገቡት መስል ጋር በሆቴሉ ላይ መጠቀሙ ተጠቃሚዉን ሊያሳስት የሚችል መሆኑን መረዳት የሚችል ከመሆኑም በላይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክትም ሆነ ስም በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(3) መሰረት የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት ሊያስወስድ የሚችል ነዉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ የሚጠቀሙበትን የንግድ ስም ያስመዘገቡት በቀን 10/5/2009 ዓ/ም መሆኑን በማስረጃነት ያቀረቡት የምስክር ወረቀት የሚያስረዳ ሲሆን ከሳሽ በበኩላቸዉ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት በ25/1/2009 ዓ/ም መሆኑን የእዕምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት የሰጠዉ ማስረጃ ያስረዳል፡፡ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት መኖሩን ነዉ፡፡ይሁን እንጂበንግድ ምልከት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት በተፈጠረ ጊዜ እንዴት እንደሚፈተ ህጋችን ያስቀመጠዉ የህግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰዎች ድርጊቶችን በቀን ልቦና እንዲፈጽሙ የሚጠበቅ ሲሆን ከሳሽ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የንግድ ምልክት ያስመዘገቡት በቀን 21/1/2009 ዓ/ም መሆኑ እና የንግድ ምልክቱን የሚቃወም ካለም እንዲቀርብ በጋዜጣ ጥሪ የተደረገ መሆኑ ሲታይ በሌላ በኩል ተከሳሽ የንግድ ስሙን ያስመዘገቡት እና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ/ም መሆኑ ሲታይ ምንም እንኳን በአዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 17(1) የንግድ ስም በመዝገብ መግባት የንግድ ስሙን ለመጠቀም መብት የሚሰጥ ተቀዳሚ ማስረጃ መሆኑን የሚደነግግ ቢሆንም ተከሳሽ የንግድ ስሙን በማስመዘገብ ከቅን ልቦና ውጪ ሊጠቀሙት አይችሉም ቀን ልቦና አላቸዉ ሊባልም አይችልም፡፡በመሆኑም ከሳሽ Sunland international Hotel የሚለዉን ቃል ከሚሰጡት የሆቴል አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለመጠቀም የቀዳሚነት መብት አላቸዉ ተብሏል፡፡
ሲጠቃለልም ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት/ስም አማካይ የሆነ ተጠቃሚን ሊያሳስት የሚችል በመሆኑ፤ከሳሽ እና ተከሳሽ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን የሚያሳክር በመሆኑ፤ከሳሽ የንግድ ምልክታቸዉን ያስመዘገቡት ለሆቴል አገልግሎት በመሆኑ ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘም የንግድ ምልክቱን ቃልም ሆነ መስል መጠቀም የብቸኝነት መብት ያላቸዉበመሆኑ ተከሳሽ ይህ ዉሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ የከሳሽን የንግድ ምልክት እንዳይጠቀሙ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት የፈጸሙ ስለሆነ የከሳሽን የንግድ ምልከት እንዳይጠቀሙ የሰቀሉትንም የከሳሽ የንግድ ምልክት ከሆቴላቸዉ ላይ እንዲያነሱ ተወስኗል፡፡
- ተከሳሽ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈለዉን ብር 90፤የጠበቃ አበል ብር 16,000 እና ለሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች ብር 200 ለከሳሽ ይክፈል፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡