የንግድ ችሎት ውሳኔዎች

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከአቢሲኒያ ሎው ጋር በመተባበር በፍርድ ቤቱ ሥር የሚገኙ የንግድ ችሎቶች የሰጧቸው የተመረጡ ውሳኔዎችን በዚህ ክፍል ያቀርባል፡፡ ዓላማውም ችሎቶቹ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ሥልጣን ባላቸው የበላይ ፍርድ ቤቶች መታየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለንግድ ማህበረሰብ እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች ውሳኔዎቹን ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡

የመ/ቁጥር 161457

ቀን 29/04/12

 

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡-የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፡- ነ/ፈ ምህረቱ መኮንን፡- ቀረቡ  

ተከሳሽ፡- አፍሪካ ጁስ  ቲቪላ አ/ማ፡- አልቀረቡም  

 መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰቷል፡፡

ፍርድ

በዚህ መዝገብ የነበረዉን ክርክር ይህ ፍርድ ቤት ተመልክቶ ሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ/ም ዉሳኔ የሰጠ ቢሆንም ከሳሽ በተሰጠዉ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኛዉን ለፌዴራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዉ የፌ/ከ/ፍ/ቤትም ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ይህ ፍርድ ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ በመ/ቁ 202266 በቀን 21/10/2010 ዓ/ም በመሻር በነጥብ የመለሰዉ በመሆኑ በድጋሚ ለችሎት ቀርቧል፡፡  

ከሳሽ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከአፍሪካ ጁስ ቢቪ ጋር በፈጸሙት የኢንቨስትመንት ውል መሰረት አፍሪካ ጁስ ቲቪላ አ/ማህበርን ህዳር 16/2001 ዓ/ም የመሰረቱ መሆኑን ከሳሽ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በእጁ የነበረውን ቲቪላ የእርሻ ልማት ንብረቶችን በአይነት ያዋጣ መሆኑን አፍሪካ ጁስ ቢቪ የተባለው የተከሳሽ ባለአክሲዮን ደግሞ በአሜሪካ ዶላር ሊያዋጣ ከሚጠበቅበት ጠቅላላ ክፍያ ውስጥ 25 በመቶዉን በቅድሚያ ከፍሎ ቀሪውን መዋጮ ደግሞ ኩባንያው ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ዶላር በተከታታይ ዓመታት ለመክፈል የተስማማ መሆኑን ይሁን እንጂ አፍሪካ ጁስ ቢቪ በገባዉ ግዴታ መሰረት ግዴታዉን ያልተወጣ መሆኑን ተከሳሽ ከንግድ ህጉና ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ለከሳሽ ጥሪ ሳያደርግ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ተድርጎ የተከሳሽ ማህበር ካፒታል ከህግ አግባብ ወጭ እንዲያድግ ዉሳኔ የተሰጠ መሆኑን፤ስብሰባዉ የተጠራው በከሳሽ እና በአፍሪካ ጁስ ቢቪ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በኦዲተሮች የተጠራ ስብሰባ ሆኖ ሳለ የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ መደረጉ አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዉ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ሕገወጥ ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ፤ተከሳሽ ማህበር እንዲያድግ ዉሳኔ የተሰጠዉ ከህግ አግባብ ወጭ ስለሆነ እንዲሻር እንዲወሰንላቸዉ፤የተከሳሽ ማህበር የኦዲት ሪፖርቱ ባለሰክሲዮኖች በጠቅላላ ጉባኤ ባልተገኙበት የፀደቀ በመሆኑ እንዲሻር እንዲወሰንላቸዉ፤በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ የፀደቀው የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ እንዲታገድ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ እንዲተከላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሾች ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርበዋል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡

ተከሳሽ በከሳሽ የቀረበዉ የክስ አቤቱታ ከነአባሪዎቹ ድርሶት የመከላከያ መልሱን  ያቀረበ ሲሆን ባቀረበዉ የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የስር ነገር ስልጣን  የለዉም እንዲሁም ክሱም የቀረበዉ ቃለ ጉባኤዉ ከጸደቀ ከሶስት ወር በኃላ ስለሆነ የቀረበዉ ክስ በይርጋ ቀሪ ነዉ በማለተ  የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ በከሳሽ ህገ ወጥ ነዉ የተባለዉ ስብሰባ ባሰክሲዮኖች ሰዓትና ቦታው ላይ ተስማምተውበት በኦዲተሮች የተጠራ ስብሰባ መሆኑን አፍሪካ ጁስ ቢቪ የሚጠበቅበትን ክፍያ ታህሳስ 2006 ዓ/ም የተከፈለ መሆኑን እንዲሁም ክፍያውም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በብሄራዊ ባንክ እውቅና ያገኘ መሆኑን በከሳሽ እንዲሻር የተጠየቀዉ ቃለ ጉባኤ የከሳሽ ተወካዮች በተሳተፉበት በሙሉ ድምጽ የፀደቀና የተመዘገበ በመሆኑ ስለሆነ ሊሻር አይገባዉም በማለት መልሱ ሰጥቷል፡፡

ፍ/ቤቱም ሕዳር 29 ቀን 2012 ዓ/ም በዋለው ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡  

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍ/ቤቱም ተከሳሽ ማህበር ሕዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በደረገዉ ሰብሰባ የማህበሩን ካፒታል በማሳደግ፤የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በመጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር በመተካት ዉሳኔ ያስተላለፈበት ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡

እንደመረመረዉም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 212/1/ሠ ላይ ከተዘረዘሩት የንግድ ማህበራት መካከል አንዱ አክሲዮን ማህበር ሲሆን አክሲዮን ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የላቸዉ ድንጋጌዎች ድግሞ በንግድ ሕጉ በጠቅላለዉ ስለ ንግድ ማህበራት የተደነገጉት ድንጋጌዎች ማለትም ከአንቀጽ 210-218 እንዲሁም አክሲዮን ማህበርን ብቻ የሚመለከቱ በንግድ ህጉ ከአንቀጽ 305-509 የተመለከቱት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡

ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የጸደቀዉ ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም ለሚለዉ ነጥብ ምላሽ ከመስጣታችን በፊት ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የተካሄደዉ ለባለ አክሲዮኖች በሕግ አግባብ  ጥሪ ተድርጎ ነዉ ወይስ አይደለም እንዲሁም ዉሳኔዎቹ የተላላፉት በንግድ ህጉ የተቀመጡት ቅደመ ሁኔታዎች ተሟልተዉ ነዉ ወይስ አይደለም  የሚሉትን ነጥቦች ማየቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡

በአክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮች ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አይነቶች ሲሆነ እነርሱም የባለአክሲዮኖች መደበኛ እና ደንገተኛ የባለአክሲዮች ጠቅላላ ጉባኤ ስለመሆናቸዉ  በንግድ ሕጉ 390 ተደንግጓል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 388 እንደተደነገገዉ በህግ አግባብ  የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ተድርጎ የተላላፉ ዉሳኔዎች ሁሉንም የማህበሩ አባላት ሊያስገደዱ እንደሚችሉ የተመለከተ ሲሆን ባለአክስዮኖች የማህበሩ ባለአክሲዮን በመሆናቸዉ የተገናጸፉትን መብቶች ማለትም በጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚተላላፉ ዉሳኔዎች ላይ ድምጽ የመስጠት መብታቸዉን ሊነፈጉ የማይገባ ስለመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 389 ተደንግጓል፡፡

በንግድ ሕጉ አንቀጽ 391/1 መሰረት ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማድረግ የሚችሉት ዳይሬክተሮች፣ ኦዲተሮች፣ሂሳብ አጣሪዎች ወይም አስፈላጊ ሲሆን ፍ/ቤቱ የሚሰይማቸዉ አካላት ስለመሆናቸዉ ተመልክቷል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሰረት በመርህ ደረጃ የባለአክሲዮኖችን ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት  ግዴታና ስልጣን ያላቸው ዳይሬክሮች ሲሆኑ ኦዲተሮች፤ሂሰብ አጣዎች እና በፍርድ ቤት የሚሰየሙ አካላት በልዩ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ እንዲችሉ አግባብነት ያላቸዉ የንግድ ህጉ ድንጋዎች የሚያስረዱ ሲሆን ኦዲተሮች በንግድ ሕጉ አንቀጽ 377/1 እና 351/4 የተገለጹት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ማለትም ዳይሬክተሮች ጠቅላላ ጉባኤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ስብሰባ ሳይጠሩ የቀሩ እንደሆነ ኦዲተሮች በዳይሬክቶረቹ ቦታ ተተክተው ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ እንደሚችሉ ዳይሬክተሮች በተለያዩ ምክንያቶች ስልጣን ላይ ከሌሉ የማህበሩ ኦዲተሮች የባለአክሲዮኖን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንደሚችሉ ተድንግጓል፡፡

ዳይሬክተሮች የማህበሩ የሂሳብ ዓመት በተጠናቀቀ በአራት ወር ጊዜ ዉስጥ መደበኛ ጠቅላላ የባለአክሲዮች ስብሰባ መጥራት ያላባቸዉ መሆኑን ይህ የአራት ወር ጊዜ አስከ ስድስት ወር በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ሊራዘም እንደሚችል በንግድ ህጉ አንቀጽ 418 ተመልክቷል፡፡ የባለአክሲዮች ጠቅላላ መደበኛ ስብሰባ ከመደረጉ አስራ አመስት ቀናት ቀደም ብሎ የማህበሩ ባለ አክሲዮኖች ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርበዉን የማህበሩን የሂሰብ ሚዛን፤የትርፍ እና ኪሳራ መገልጫ እንዲሁም የኦዲተር ሪፖረት ማግኝት ያለባቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 418 የተመለከተ ሲሆን በመደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በንግድ ህጉ አንቀጽ 419 የተገለጹ ሲሆን እነዚህም የማህበሩን ሂሳብ ሚዛን፤የትርፍ እና የኪሳራ መገለጫ እንዲሁም የኦደተሮችን ሪፖርት መርምሮ ማጽደቅ ወይም ወድቅ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 419(2) ሰር የተገለጹት ሌሎች ተግባሮችም ይከናወናሉ፡፡

ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ከመደረጉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ የማህበሩ ባለአክሲዮኖች በደንገተኛ ጠቅላላ  ጉባኤዉ ሊተላላፉ የታሰቡትን የዉሳኔ ሀሳቦችሰ እና የኦዲተር ሪፖርት ሊያገኙ የሚገባ ስለመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 422 የተደነገገ ሲሆን የአክሲዮን ማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ሊሻሻሉ የሚችሉት በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 423 በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በተለይም የማህበሩን ዜገነት ለመቀየረ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸዉን እንዲያሳደጉ በቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ሁሉም ባአክሲዮች መገኝት ወይንም መወከል ያለባቸዉ መሆኑን እነዚህን የዉሳኔ ሀሳቦችም በባለአክሲዮኖች በሙሉ ደምጽ ካልተደገፉ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ  425 ተድንግጓል፡፡

የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ ደንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ የሚደረገበት መንግድ በንግድ ህጉ አንቀጽ 392 የተደነገገ ሲሆን ለባለአክሲዮኖች የሰብሰባ የጥሪ ማስታወቂያ ከ15 ቀናት በፊት ቀድሞ ብሎ ሊደረሳቸዉ የሚገባ መሆኑ እንዲሁም በሰብሰባ ላይ ወይይት የሚደረግባቸዉ አጀንዳዎች በጥሪ ማስታወቂያ ላይ መገለጽ ያለባቸዉ ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 395፤396 እና 397 መረዳት የሚቻል ሲሆን አንድ ስበሰባዉ አይነት ምለዓት ጉባኤ  ካልተሟለ እና አሰፈላጊዉ ደምጽ ካላተገኘ በአጀንዳ ላይ የተገለጹትን የዉሳኔ ሀሳቦች ለማጽደቅ የማይቻል ስለመሆኑ በንግድ ህጉ 399(1) ተመልክቷል፡፡

ሌላዉ መነሳት ያለበት ነጥብ በንግድ ህጉ አንቀጽ 415 የማህበሩ ባለአክሲዮኖች የሚያካሂዱት ኢንፎርማል ጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን ይህም የማህበሩ ሁሉም ባለአክሲዮኖች የተገኙ እንደሆነ ወይንም የተወከሉ እንደሆነ በስምምነት ምንም አይነት ቀድመ ሁኔታ ሳያስፈልግ ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካሂዱ የሚችሉ መሆኑን በዚህ አይነት ሁኔታ በሚካሄድ ጠቅላላ ጉባኤም ማናቸዉንም አይነት ዉሳኔ ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ 

ከላይ ለማብራረት ከተሞከሩት ደንጋጌዎች አንጻር የተያዘዉን ጉዳይ ስንመለከተ ተከሳሽ  ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በተደረገዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከሳሽ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርጊያለሁ በማለት ክርክር ያቀረበ ቢሆንም እራሱ ተከሳሽ ካቀረበዉ ማስረጃ ለመመለከት እንደሚቻለዉ ጥሪ የተደረገዉ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም ሲሆን ሰብሰባዉ የተካሄደዉ ድግሞ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም ነዉ፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 395 እና በማህበሩ መተዳዳሪያ ደንብ መሰረት ከሳሽ በጠቅላላ ጉባኤዉ ላይ እንዲሳተፍ በህጉ አግባብ ከስበሳዉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ ጥሪ ያላደረገ መሆኑን ነዉ፡፡ ተከሳሽ ለከሳሽ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት የጥሪ ማስታወቂያዉ እንዲደርሰዉ ያልተደረገዉ ቀደም ሲል ሁሉም ባለአክሲዮኖች በተገኙበት ሰብሰባ ላይ የሰብሰባዉ ቦታ እና ሰብሰባዉ የሚካሄደበት ቀን በመወሰኑ ነዉ በማለት ክርክር ያቀረበ ቢሆንም ይህን ፍሬ ነገር በማስረጃ ከላማረጋገጡም በላይ ከላይ የተጠቀሰዉ ደንጋጌ ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት ከ15 ቀናት በፊት በህጉ በተመለከተዉ ሁኔታ ጥሪ ሊደረግላቸዉ የሚገባ መሆኑን በአስገዳኝነት የሚደነግግ በመሆኑ ባለ አክሲዮኖቹ ቀደም ብሎ በነበረዉ ስበሰባ ላይ የሰብሰባ ቀኑን መወሰናቸዉ ተከሳሽ ከላይ በተጠቀሰዉ ድንጋጌ መሰረት እና በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ መሰረት ከስበሰባዉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ  ለባለአክሲዮኖች ጥሪ የማደረግ ግዴታዉን የሚያስቀር አይደለም፡፡

ተከሳሽ ማህበር በጠራዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ወይይት የሚደረግባቸዉ አጀንዳዎች በጥሪ ማስታወቂያ ላይ መገለጽ ያለበት ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 395፤396 እና 397 መረዳት የሚቻል ቢሆንም ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በአካሄደዉ ጠቅላላዉ ጉባኤ የማህበሩን ካፒታል በማሳደግ፤የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በመጽድቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር በመሻር በሌላ ዳሬክትር ተክቷል፡፡ እነዚህን የስብሰባ አጀንዳዎች ተከሳሽ ለከሳሽ በላከዉ የጥሪ ማስታወቂያ ላይ ያልተገለጹ መሆናቸዉን ተከሳሽ ካቀረበዉ ማስረጃ መረዳት የሚቻል ሲሆን በማህበሩ ኦዲተሮች ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም የተጠራዉ ሰብሰባ አጀንዳም በባአክሲዩኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትን ለመፈታት ስለመሆኑ በጥሪ ማስታወቂያዉ በግልጽ  ስፍሯል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ ተከሳሽ ማህበር ከላይ የተገለጹትን ዉሳኔዎች ያስተላለፈዉ በንግድ ህጉ እና በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡትን ቅደመ ሁኔታዎች ሳያሟላ መሆኑን መገንዘብ ይቻልል፡፡  

ተከሳሽ የማህበሩን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ አድርጊያለሁ በማለት የሚከራከረዉ  የማህበሩ ኦዲተሮች ጥቅምት 24/2009 ዓ.ም ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች ጥሪ ያደረጉትን ደብዳቤ መነሻ በማደረግ ሲሆን ኦዲተሮቹ ስብሰባ የጠሩት በባአክሲዩኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት የኦዲት ሪፖርት ለመስራት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኦዲተሮች በንግድ ሕጉ አንቀጽ 377/1 እና 351/4 መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ  የሚችሉት የማህበሩ ዳይሬክተሮች በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ስብሰባ ሳይጠሩ የቀሩ እንደሆነ ወይንም የማህበሩ ዳይሬክተሮች በተለያዩ ምክንያቶች ስልጣን ላይ በሌሉ ጊዜ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ቢሆንም ተከሳሽ የስብሰባ ጥሪ በኦዲተሮች የተከናወነዉ ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ተክስተዉ ስለመሆኑ ያቀረበዉ ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በኦዲተሮች የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ የተደረገ ስለሆነ ስብሰባዉ ህጋዊ ነዉ በማለት ያቀረበዉ ክርክር የህግ መሰረት ያለዉ አይደለም፡፡

አንድ ባለአክሲዩን በባአክሲዩኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመገኘት ድምፅ የመስጠት የማህበሩን ውሳኔ የመቃወም ካልፈለገ በስተቀር ፍጽማዊ መብቱ (Inherent right) መሆኑን የንግድ ሕጉ አንቀጽ 389 የሚደነግግ ሲሆን የንግድ ሕጉ አንቀጽ 388 ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ገዥ የሚሆነው በሕግ አግባብ ሲደረግ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ማህበር የከሳሽ  መብትን በመገድብ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ/ም የተለያዩ ዉሳኔዎች ያስተላላፈ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በመጨረሻም የአክሲን ማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ሊሻሻሉ የሚችሉት በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 423 በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በተለይም የማህበሩን ዜገነት ለመቀየረ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸዉን እንዲያሳደጉ በቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ሁሉም ባአክሲዮች መገኝት ወይንም መወከል ያለባቸዉ መሆኑን እነዚህን የዉሳኔ ሀሳቦችም በባለአክሲዮኖች በሙሉ ደምጽ ካልተደገፉ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ  425 ተድንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በተያዘዉ ጉዳይ ከሳሽ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኘ ስለመሆኑ እንዲሁም የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ ድምጽ የሰጠ ስለመሆኑ በተከሳሽ በኩል የቀረበ ማስረጃ የለም ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ ተከሳሽ ማህበር የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ ያደረገዉ የንግድ ህጉ አንቀጽ 425ን በሚቃረን መልኩ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ  በንግድ ህጉ አንቀጽ 467 እንደተደነገገዉ የማህበሩ ሙሉ ካፒታል ክፍያ ሳይፈጸም የማህበሩን ካፒታል አዳዳስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ በማቅርብ ማሳደግ የማይቻል ስለመሆኑ ገልጽ ከልከላ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ የተከሳሽ ማህበር ሙሉ ካፒታል በባለአክሲዮኖች ሙሉ ለሙሉ ሳይከፍል አዳዳስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ በማቅርብ የማህበሩ አክሲዮን እንዲያድግ መደረጉ አግባብነት የሌለዉ በመሆኑ ተቀባይነት የለዉም፡፡  

ሲጠቀለልም ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የማህበሩን ካፒታል በማሳድግ፤ የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በማጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር አንዲሻሩና በምትካቸዉ ሌላ ዳሬክተር በመሾም  ዉሳኔዎች  ያስተላለፈዉ በንግድ ህጉ ስለ ጠቅላላ ጉባኤ አጠራር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች የማህበሩን መተዳዳሪያ ደንብ ሳያከብር በመሆኑ፤ዉሳኔዎቹ የተላላፉት ዉሳኔዎቹን ለማስተላላፍ የሚያስፈልገዉ ምላዓት ጉባኤ እና የሚያሰፈልገዉ ድምጽ ሳይሟል በመሆኑ እንዲሁም የሰብሰባ ጥሪ ለማድረግ ስልጣን የተሰጠዉ አካል ጥሪ ሳያድርግ የተላላፉ ዉሳኔዎች በመሆናቸዉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በአካደዉ ስበሰባ ያስላለፋቸዉ ዉሳኔዎች እና የተያዘዉ ቃለ ጉባኤ በንግድ ህጉ አንቀጽ 416(5) መሰረት ተሸሯል፡፡

ዉሳኔ

 • ተከሳሽ የማህበሩን ካፒታል በማሳድግ፤vየማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በማጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር አንዲሻሩና በምትካቸዉ ሌላ ዳሬክተር በመሾም ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም ያስተላላፋቸዉ ዉሳኔዎች እና ቃለ ጉባኤዉ እንዲሻር ተወሰኗል፡፡
 • ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ ለከሳሽ በቁርጥ ብር 3,000 (ሶስት ሺህ) ይክፈል፡፡

ትዕዛዝ

 1. ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ፡፡
 2. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የኮ/መ/ቁ 178843

ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- ብሩክ ሳህሉ ከጠበቃ ስራብዙ ሲራክ ጋር ቀረቡ

ተከሳሽ ፡- ኤርዝ ዋርክ ጂኦቴክ ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጠበቃ አሸናፊ ሀይሌ ቀረቡ  

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ  ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ ኩባንያ በ16/01/2010 ዓ/ም በደብዳቤ ቁጥር EWG/01/270/17 ብር 135,000 የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድ የሰጧቸዉ መሆኑን በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን በሶስት ወር ጊዜ ዉስጥ ለመክፈል ግዴታ የገቡ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ላለፉት ሁለት አመታት ገንዘቡን ሳይከፍላቸዉ የቀረ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታስብ ህጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡ በማስረጃነትም ሰነዱን አያይዘዉ አቅቧል፡፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ድርሶ ተከሳሽ ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ ያቀረበዉን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኃላ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ ክሱን እንዲከላከል ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ በቀን 09/4/11ዓ/ም በተጻፈ የመካለከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ የሰጠ ሲሆን ተከሳሽ ያቀረበዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ወድቅ ያደረገዉ ስለሆነ ከዚህ ማስፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡

ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት የመከላከያ መልስ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የመተማመኛ ሰነድ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ የማህበሩ ተወካይ የተሰጠዉ ውክልና ጠቅላላ ውክልና መሆኑን የመተማመኛ ሰነዱ እንደ የሚተላለፉ ሰነዶች የሚቆጠር በመሆኑ ሰነዱን ለመፈርም ልዩ ውክልና የሚያስፈልግ መሆኑን የዕዳ አለብኝ ሰነዱን ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ ግለሰብ ተራ የድርጅቱ ተወካይ ወይም ጉዳይ አስፈጻሚ መሆኑን ግለሰቡም በደርጅቱ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ስልጣን የተሰጠዉ ዳሬከክተር አለመሆኑን ተከሳሽ ስልጣን ባልተሰጠ ሰዉ የሚገደድበት ህጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን፤ተከሳሽ ከሳሽ ስራ የሰራ መሆኑን የማያውቅ መሆኑን እንዲሁም ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የገባዉ ውል የሌለ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሱን አቀርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ የፈረሙት ህጋዊ የተከሳሽ ስራ አስኪያጅ መሆናቸዉን የመተማመኛ ሰነዱን የፈረመዉም ግለሰብ በዬትኛዉም መስሪያ ቤት ቀርቦ ውል ለመዋዋል የሚያስችለዉ ውክልና የተሰጠዉ መሆኑን እንዲሁም ክፍያዎችን እንዲፈጽም በተከሳሽ ውክልና የተሰጠዉ መሆኑን ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የመተማመኛ ሰነድ ግለሰቡ መፈረም የሚችሉ መሆኑን ገልጸዉ ሲከራከሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ግለሰቡ ውክልና ያላቸዉ መሆኑን ነገር ግን ሁሉንም ነገሮች የመፈረም ስልጣን የተሰጣቸዉ አለመሆኑን ውል መዋዋል የሚችሉ መሆኑን ክፍያ መፈጸም የሚችሉ መሆኑን ነገር ግን የዕዳ መተማመኛ ሰነድ መስጠት የማይችሉ መሆኑን ግለሰቡ የመተማመኛ ሰነዱን የፈረሙት በፍ/ሕ/ቁ 2205(2) መሰረት የተሰጠ ልዩ ውክልና ሳይኖራቸዉ መሆኑን በተፈረመዉም የመተማመኛ ሰነድ ተከሳሽ ሊገደድ የማይችል መሆኑን ከሳሽ ስራ ሰርተናል ከሚል በቀር ሰራ የሰሩ ስለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጃም ሆነ ውል የሌለ መሆኑን በመግለጽ የከሳሽ ክርክር ወድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡   

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ለክርክሩ መነሻ በሆነዉ  ሰንድ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን ተከሳሽ የመክፈል ሃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

እንደመረመረዉም ከሳሽ የሚከራከረዉ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ ሰነድ ነዉ በመሆኑም ለክርክሩ መነሻ በሆነዉ ሰነድ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ተከሳሽ ሊከፍለኝ ይገባል በማለት ሲሆን ተከሳሽ የሚከራከረዉ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ ግለሰብ ከተከሳሽ የተሰጠዉ ልዩ ውክልና የለም ሰነዱም እንደሚተላላፉ ሰነዶች የሚቆጠር በመሆኑ ሰነዱን ለመፈረም በፍ/ሕ/ቁ 2205(2) መሰረት ልዩ ውክልና ያስፈልጋል በመሆኑም ይህ አይነት ውክልና ባልተሰጠበት የተፈረመ ሰነድ ሊያስገድድን አይገባም በማለት ነዉ፡፡

ወደ ዋናዉ ጭብ ከመግባታችን በፊት ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ እንደሚተላላፉ ሰነዶች(የተስፋ ሰነድ /የሐዋላ ወረቀት)  የሚቆጠር ሰነድ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን ነጥብ መየቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 715(1) እንደተመለከተዉ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ ማለት መብቱ ከሰነዱ ተለይቶ ሊሰራበት ወይም ሊተላለፍ የማይችል ያገልግሎት መብት ያለበት ሰነድ ሁሉ ስለመሆኑ የተመለከተ ሲሆን የድንጋጌዉ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ የንግድ ወረቀቶችም እንደሚተላለፉ ሰነዶች የሚቆጠሩ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 732(1) ደግሞ የንግድ ወረቀቶች ማለት በገንዘብ መክፈል የሚሆነዉን ግዴታ የሚናገሩ ሰነዶች ስለመሆናቸዉ የተመለከተ ሲሆን የድንጋጌዉ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ የተሰፋ ሰነድ ከንግድ ወረቀቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 823 እንደተደነገገዉ አንድ ሰነድ የተሰፋ ሰነድ ለመባል በሰነዱ ዉስጥ የተስፋ ወረቀት የሚል ቃል መገኝትና ሰነዱ በተጻፈበት ቋንቋ መገለጽ ያለበት መሆኑን  የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ሀተት የሌለበት መሆን አንዳለበት፤የሚከፈልበት ጊዜ መገለጽ ያለበት መሆኑን ገንዘቡ ሊከፈልበት የሚገባዉ ቦታ መገለጽ ያለበት መሆኑን ገንዘቡ የሚከፈለዉ  ሰዉ ስም ወይም የታዘዘለት ሰዉ ስም ወይም ወረቀቱ ለአምጪዉ መክፈል የሚገባዉ መሆኑ መገለጽ ያለበት መሆኑን ሰነዱ የተጻበት ቀንና ቦታ እንዲሁም ሰንዱን ያወጣዉ ሰዉ ፊርማ በሰነዱ ላይ መኖር ያለበት መሆኑን ይደንግጋል፡፡ ከነዚህ ከላይ ከተገለጹት ነገሮች አንዱ እንኳን ቢጎል ሰነዱ እንደ ተስፋ ሰነድ የማይቆጠር መሆኑን የንግድ ህጉን አንቀጽ 824 ይደነግጋል፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ ስንመለከተ የተስፋ ሰነድ መገለጫዎች ከሆኑት መካከል ሰነዱ ላይ የተስፋ ወረቅት በሚል የተመለከተ ነገር የለም፤ገንዘቡ ሊከፈልበት የሚገባዉ ቦታ በሰነዱ ላይ አልተገለጸም እንዲሁም ሰነዱ የተጻፈበት ቦታ አልተገለጸም፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ በንግድ ህጉ አንቀጽ 823 እና 824 ጣምራ ንባብ (cumulative reading) ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ / የቃልኪዳን ሰነድ ሊባል አይችልም ፡፡

በተመሳሳይ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ በንግድ ህጉ 735 የተቀመጡትን ቀድመ ሁኔታዎች የማያሟላ በመሆኑ እንድ ሐዋለ ወረቀት (bill of exchange) ሊቆጠር እንደማይችል ከንግድ ህጉ አንቀጽ 735 እና 736 መረዳት ይቻላል፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ ሰነድ/የሐዋለ ወረቀት አይደለም የሚተላላፉ ሰነዶች ባህሪም የለዉም ከተባለ ደግሞ ሰነዱን ለመፈረም ልዩ ውክልና አያስፈልግም ከሰነዱ ላይ ለመመለከት የሚቻላዉ ሰነዱን ፈርሞ የሰጠዉ ግለስብ ያረጋገጠዉ ነገር ቢኖር ከሳሽ ያለዉን ቀሪ ተከፋይ ገንዘብ ነዉ ግለሰቡም በማህበሩ ስም ክፍያ እንዲፈጽም፤ሰነዶችን እንዲፈርም እንዲሁም ውል እንዲዋዋል ስልጣን የተሰጠዉ ስለመሆኑ የቀረበዉ የውክልና ሰነድ ያረጋግጣል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ የተከሳሽ ማህበር ተወካይ አቶ አያልነህ አበበ ቀሪ ተከፋይ ገንዘብ መኖሩን ማረጋገጡ በተሰጠዉ ውክልና ውል የማዋዋል እና ሰነዶችን የመፈረም ሰልጣኑ  በማህበሩ ላይ ግዴታን የሚያስከትሉ ተግባራት መፈጸም የሚችል መሆኑን መረዳት አያዳግትም፤ለክርክሩ መነሻ የሆነዉም ሰነድ በተከሳሽ ላይ ግዴታን የሚፈጥር ነዉ ይህ ደግሞ አንደ ውል የሚቆጠር መሆኑ ገልጽ ነዉ፡፡

ሲጠቃለልም የሚተላላፉ ሰነዶችን ለመፈረም ልዩ ውክልና የሚያስፈልግ መሆኑ በተለይም ከአንግሊዘኛዉ የፍ/ሕግ 2205 (2) በተለይም to signs bill of exchange ከሚለዉ ሀረግ  መረዳት የሚቻል ቢሆንም ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የሚተላላፉ ሰነዶች ባህሪ የሌለዉ እና ከሚተላላፉ ሰነዶች መካከል አንዱ ባለመሆኑ ተከሳሽ ሰነዱን የፈረመዉ ሰዉ ልዩ ውክልና የሌለዉ ስለሆነ በሰነዱ ልንገድድ አይገባም በማለት ያቀረበዉን ክርክር ፍርድ ቤቱ  አልተቀበለዉም ሰነዱን ለፈረመዉ ግለሰብ የተሰጠዉን ውክልና ይዘትም ስንመለከተ ግለሰቡ ውል ለመዋዋል፤ ሰነዶችን ለመፈረም እና ክፍያ ለመፈጸም ስልጣን የተሰጠዉ ከመሆኑ አንጻር ቀሪ ተከፋይ ገንብብ መኖሩን በማረጋገጥ ለከሳሽ የሰጠዉ ሰነድ ከስልጣኑ ውጭ የተሰጠ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ በክሱ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን ሊከፍል ይገባል ተብሎ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡   

   ውሣኔ

 1. ተከሣሽ ብር 135,000.00(አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ) ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ከ16/4/2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
 2. ወጪና ኪሣራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 3,875፣ለቴምብር ቀረጥ ብር 15፣ እንዲሁም የጠበቃ አበል 13,500 ተከሣሽ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

ትዕዛዝ

 • ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
 • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የኮ/መ/ቁ 173282

ሚያዚያ 24 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- ወ/ሮ ሙሉእመቤት ፀጋዬ

       የህጻን ቦንቱ ናንሲ ሚካያ ተሾመ ሞግዚት

ተከሳሽ፡- የምነዉሸዋ ኢንተርቴመንት ባለቤት አቶ ሸዋቀና በንቲ ኢታና

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ/ም አሻሽለዉ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም  ህጻን ቦንቱ ናንሲ ሚካያ የወ/ሪት ሚካያ ኃይሉ ወራሽ መሆኗን ከሳሽ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ጻጋዬ የህጻን ቦንቱ ናንሲ ሞግዚት መሆኗን ይህም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 1644/06 በቀን 26/6/06 ዓ/ም የተረጋገጠ መሆኑን ተከሳሽ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ ውል የአርቲስት ሚካያ ባኃይሉን ጊዜ ቢነጉድም የሚለዉን የሙዚቃ ስራ ከሀገር ዉጪ የሙዚቃ ስራዉን በሲዲ ለማሰራጨት መብቱን ከከሳሽ በብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የገዛ መሆኑን ለዚህም ክፍያ ይሆን ዘንድ ቁጥሩ ኤቢዋይ 5935402 የሆነ ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የያዘ ቼክ የሰጧቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ በቼኩ ክፍያ እንዳይፈጸም ተከሳሽ ለባንኩ ትዕዛዝ በመስጠቱ በቼኩ ላይ የተመለከተዉ ገንዘብ ሳይከፈላቸዉ የቀረ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ብር 200,000.00(ሁለት መቶ ሺህ) ከነ ህጋዊ ወለዱ እንዲከፈላቸዉ እንዲወስንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ እንደ ክስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ለተከሳሽ እንዲደርስ ተደርጎ ተከሳሽ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ በቃለ መሕላ በተደገፈ አቤቱታ የቀረበባቸዉን ክስ ለመከላከል የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ የቀረበዉን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኋላ ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ በከሳሽ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ አቅርቧል፡፡ ይዘቱም  ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተፈረመዉ ውል ላይ የውል ተቀባይ የሆነዉ አቶ ጌዲዮን አማረ  የተከሳሽ ድርጅት የአይቲ ባለሙያ እንጂ ስራ አስኪያጅ ያለመሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማራ ከተከሳሽ የተሰጣቸዉ ምንም አይነት ውክልና የሌላቸዉ መሆኑን፤ ተከሳሽን ወክለዉም ምንም አይነት ውል መፈጸም የማይችሉ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማራ ለአነስተኛ ስራዎች ለዋስትና የተቀመጠ ቼክን ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን፤ ተከሳሽ ዉሉ ላይ በተመለከተዉ መልኩ የከሳሽን ካሴት በውጭ ሀገር ያላሰራጨ፣ ያላሳየ እና ለሽያጭ ያላቀረበና ጥቅም ያላገኘ መሆኑን፤ ከሳሽ የሙዚቃ ስራዉ ዉጭ ሀገር ሳይሰራጭ ቀድመዉ በሀገር ዉስጥ በማሰራጨታቸዉ ስራዉ በዉጭ ሀገር ያልተሰራጨ መሆኑን፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ  የድርጅቱ ተወካይ ፈርመዉ ባስቀመጡበት ሁኔታ ኦቶ ጌዲዮን አማረ ያለ አግባብ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን ቼኩም ለዋስትና የተሰጠ መሆኑን ገልጾ ተከሳሽ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸዉ ጠይቋል፡፡

ተከሳሽ አንደ መከላከያ መልስ አቀራረቤ ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰዉ ምስክሮች ቆጥሯል፡፡

ተከሳሽ ካቀረበዉ የመከላከያ መልስ በተጨማሪ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱም በተከሳሽ ከሳሽ ስም እና በከሳሽ ተከሳሽ ስም ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገ ውል መኖሩን የተከሳሽ ከሳሽ የተረዱ መሆኑን ይሁን እንጂ በተከሳሽ ከሳሽ ስም በውሉ ላይ የፈረሙት ግለሰብ የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያ እንጂ ስራ አስኪያጅ አለመሆናቸዉን፤ የተሰጣቸዉ ውክልናም የሌለ መሆኑን፤ የተከሳሽ ከሳሽ በውሉ ላይ የተጠቀሰዉን ካሴት በውጭ ሀገር ያላሰራጨ፤ ያላሳየ እና ጥቅም ያላገኘ መሆኑን ገልጸዉ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተከሳሽ ከሳሽ ስም እና በከሳሽ ተከሳሽ ስም የተፈጸመዉ ውል እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸዉ ጠይቋል ፡፡

እንድ ክስ አቀራረቡ ያስዱልኛል ያሏቸዉንም የሰዉ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡

የተከሳሽ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ለከሳሽ ተከሳሽ ደርሶ የከሳሽ ተከሳሽ ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም የተከሳሽ ከሳሽ እንዲፈረስ የጠየቁት ውል የተፈረመዉ በተከሳሽ ከሳሽ ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ እና ተወካይ መሆኑን፤ ዉሉም የድርጅቱ አርማ ባረፈበት ወረቀት እና ማህተም የተረጋገጠ እና በድርጅቱ ዉስጥ የተፈረመ በመሆኑ የተከሳሽ ከሳሽ ውሉን አላቀዉም በማለት ያቀረቡት ክርክር ሀሰት መሆኑን፤ ይህን ክስም የተከሳሽ ከሳሽ ያቀረቡት የሙዚቃ ስራዉን ኦንላይን ላይ ጭነዉ ገቢ ማግኝት ከጀመሩ በኃላ መሆኑን፤ ይህም የተከሳሽ ከሳሽ ቅን ልቦና የሌለዉ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፤  የተከሳሽ ከሳሽ ውሉ ከመፈረሙ በፊት ድርድር ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን፤ ዉሉ ሲፈረምም ሙሉ ፈቃዳቸዉን ሰጥተዉ የተፈረመ መሆኑን፤ ዉሉ ከተፈረመ በኃላም ከከሳሽ ጋር ስለ ዉሉ መልካም አፈጻጸም ሲነጋገሩ የነበረ መሆኑን፤ የከሳሽ ተከሳሽ ዉሉን የፈጸሙት በቅን ልቦና መሆኑን፤ የተከሳሽ ከሳሽ ዉሉን በውጭ ሀገር አለማስራጨቱ ዉሉ እንዳይጸና ሊያደርግ የሚችል አለመሆኑን ገልጸዉ የተከሳሽ ከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ተከሳሽ የአርቲስት ሚኪያ በሀይሉን የሙዚቃ ስራ በውጭ ሀገር ለማሰራጨት በብር 200,000 የገዛ መሆኑን፤ ለዚህም ክፍያ ይሆን ዘንድ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ ለከሳሽ የሰጠ መሆኑን፤ ይህንም ቼክ ለክፍያ ባቀረቡ ጊዜ ሊከፈላቸዉ ያልቻለ መሆኑን፤ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገዉ ውል ሁለት ዘርፍ ያለዉ መሆኑን አንዱ የወጭ ሀገር ስርጭትን የሚመለከተ ሲሆን ሌላዉ ደግሞ የኦንላይን ስርጭትን የሚመለከት መሆኑን፤ በዚህ መዝገብ ክስ ያቀረቡት የውጭ ሀገር ካሴት ስርጭትን በተመለከተ መሆኑን የኦንላይን ስርጭቱን በተመለከተ ያልበሰለ በመሆኑ ክስ ያላቀረቡ መሆኑን፤ ውክልና በዝምታ ወይም በግልጽ ሊሰጥ ይችላል በመሆኑም ተከሳሽ ዉሉን የፈረሙት አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና የላቸዉም በማለት ያቀረበዉ ክርክር የህግ መሰረት የሌለዉ መሆኑን፤ ውክልና በግድ በጽሁፍ መሰጠት የሌለበት መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን ከሌሎች አርቲስቶች ጋርም ድርጅቱን ማህተም ተጠቅሞ ውል ሲፈጸም የነበረ መሆኑን፤ ተከሳሽ ክፍያዉን ለመፈጸም የሚገደደዉ ጥቅም በማግኘቱ ብቻ አለመሆኑን፤ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ ላይ የወንጅል ክስ ማቅረበባቸዉ የቀረበባቸዉን ክስ ለመከላከል የማያበቃ መሆኑን፤ ቼኩን የፈረመዉ ሁለት ሰዉ መሆኑን አንደኛዉ ፈራሚ አቶ ጌዲዮን አማረ መሆኑን፤ ማህተሙ የድርጅቱ መሆኑን፤ ተከሳሽ ያልካደ መሆኑን የሀገር ዉስጥ ስርጭቱን ከሳሽ በፈለገዉ መልኩ የማሰራጨት መብት ያለዉ መሆኑን፤ ይህን አስመልክቶም በውሉ ላይ የተቀመጠ ገደብ የሌለ መሆኑን ገልጸዉ ያቀረቡት ክስ እና የከሳሽ ተከሳሽነት መልስ አጠናክረዉ የተከራከሩ ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር ለአቶ ጌዲዮን አማረ በውልና ማስረጃም ሆነ በድርጅቱ የፕሮቶኮል ደብዳቤ የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸመዉን ውልም በዝምታ ያልተቀበሉ መሆኑን፤ ውል እንዲፈጽሙም የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የድርጅቱን ሄደር እና ማህትም አለ አግባብ በመጠቀሙ የወንጅል ክስ ያቀረቡበት መሆኑን፤ ቼኩም ተቀምጦ የነበረዉ ለከሳሽ ክፍያ አለመሆኑን፤ የሙዚቃ ስራዉንም ያልገዙ መሆኑን፤ ያገኙት ጥቅም የሌለ መሆኑን፤ በተጨማሪ ማስረጃነት የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስረዱት ዩቲዩብን በተመለከተ እንጂ የካሴት ስርጭትን የሚመለከቱ አለመሆናቸዉን በመግልጽ ያቀረቡትን የመከላከያ መልስ እና የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በማጠናክር ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት በተለየዉ ጭብጭ ላይ የግራ ቀኙን ምስክር ሰምቷል፡፡ በዚህም መሰረት በከሳሽ በኩል የቀረቡትም ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ተከሳሽ ጊዜዉ ቢነጉድም የሚለዉን በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የሙዚቃ ስራ ከ1ኛ እና ከ3ኛ የከሳሽ ምስክሮች ጋር በመሆን ሰምቶት የወደደዉ በመሆኑ የውጭ ሀገር ስርጭቱን ለመግዛት ፈቃደኛ የነበረ መሆኑን ሀገር ዉስጥም አቶ ጌዲዮን አማረ የተባለ ወኪል ያለዉ በመሆኑ ዋጋዉን በተመለከተ ከእሱ ጋር ጨርሱ ያለ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ በተከሳሽ ድርጅተ  ዉስጥ የሚሰራ መሆኑን ስራዉ በሲዲ ሊታተም ሲልም የከሳሽ ቤተሰብ የሆነዉ 1ኛ ምስክር የሚኪያ በሀይሉን ፎቶ ግራፍ ለዲዛይን በተከሳሽ ጥያቄ መሰረት ለተከሳሽ የላኩ መሆኑን፤ የሙዚቃ ስራዉ ውል በተከሳሽ ቢሮ ዉስጥ የተፈጸመ መሆኑን፤ ተከሳሽ የሙዚቃ ስራዉ በቅርብ ጊዜ የሚወጣ መሆኑን በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ ሲያስተዋውቁ የነበረ መሆኑን፤ ለክፍያ የተሰጠዉ ቼክ የታገደ በመሆኑ ተከሳሽ ሲደወልላቸዉ ድርጅቱ ችግር ዉስጥ ነዉ ትንሽ ታገሱ ይከፈላችኋል ሲሉ የነበረ መሆኑን፤ በወቅቱ ስለ አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና ያነሱት ነገር አለመኖሩን፤ ተከሳሽ ሀገር ዉስጥ በመጡ ጊዜም የከሳሽ ቤተሰብ ከሆነዉ ከ1ኛ ምስክር ድርጅት ቢሮ ዉስጥ ተገናኝተዉ የአንድ ወር ጊዜ ስጡኝ እከፍላለዉ ያሉ መሆኑን፤ በዚህ ወቅትም አቶ ጌዲዮን አማረ ቢሮ ዉስጥ ሲገባ እና ሲወጣ የነበረ መሆኑን፤ ከአንድ ወር ተከሳሽ ክፍያዉን ሳይከፍሉ ቀርተዉ ሲጠየቁ  እኔ ለጌዲዮን ሰጥቻለሁ ከፈለጉ ከጌዲዮን ይጠይቁ ያሉ መሆኑን፤ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ክፍያ አስመልከቶ ከ1ኛ ምስክር ጋር የኢሜል ልውውጥ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ፤ ዉሉን የፈረሙት አቶ ጌዲዮን አማረ የተባሉትም የከሳሽ ምስክር ዉሉን የፈረሙት ከተከሳሽ ጋር ተነጋገረዉ መሆኑን፤ ስራዉም የመጣዉ በተከሳሽ በኩል መሆኑን፤ በዚህ መልኩም ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር ውል ሲፈጽሙ የነበረ መሆኑን፤ ቼኩም ለከሳሽ የተሰጠዉ ለክፍያ መሆኑን፤ ይህንም የተከሳሽ ወኪል የሚያውቁ መሆኑን፤ ቼኩንም ቆርጠዉ የሰጡት የተከሳሽ ወኪል አቶ አሸናፊ መሆናቸዉን አቶ አሸናፊ እንዲህ አይነት ስራ ሰርተዉ የማያውቁ መሆኑን፤ የሚገናኙትም በቼክ ጉዳይ መሆኑን ከያሬድ ነጉ እና ከሳሚ ዳን ጋርም የተፈጸመዉን ውል የፈረሙት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ በተከሳሽ የተሰጣቸዉ የጹሁፍ ውክልና የሌለ መሆኑን፤  በመተዳደሪያ ደንቡን ላይ ምክትል ስራ አስኪያጅ ተብለዉ ያልተሰየሙ መሆኑን ከተከሳሽ ጋር የተጋጩት ከድርጅቱ ከሚገኘዉ ጥቅም አካፈለኝ በሚል መሆኑን ጸቡም የተፈጠረዉ ውሉ ከተፈጸመ ከስድስት ወር በኃላ መሆኑን ገልጸዉ መስክረዋል፡፡

በተከሳሽ በኩል የቀረቡት 1ኛ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል የተከሳሽ ድርጅት ስራ አስኪያጅነት በውክልና የተሰጣቸዉ መሆኑን፤ በክፍያ ጉዳይ ላይ ከባለሙያዎች ጋር የሚነጋገሩት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ በክፍያ የሚሰሩትን ስራዎች ውል የሚዋዋሉት እርሳቸዉ መሆናቸዉን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የሚዋዋሉት ክፍያ የማይፈጸምባቸዉን የነጻ ውሎች መሆናቸዉን፤ አቶ ጌዲዮን ከሙያ ስራቸዉ ውጭ ሌላ ሃላፊነት የሌላቸዉ መሆኑን ፤ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ቼክ ለአነስተኛ ወጪዎች በሚል ፈርመዉ አስቀምጠዉ የሄዱ መሆኑን፤ በቼኩ ላይ የሰፈረዉም ጽሑፍ የእርሳቸዉ አለመሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ የተባሉት የከሳሽ ምስክር እና ተከሳሽ የተጣሉት በዚህ ውል መሆኑን፤ ተከሳሽ ድርጅት የሚሰራዉ የኦንላይን ሽያጭ እና ኮንሰርት መሆኑን፤ የውጭ ሀገር ስርጭት የማይሰራ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን አማረ በተከሳሽ የተሰጣቸዉ ውክልና የሌለ መሆኑን፤  የከሳሽ ስራ በሀገር ዉስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያላሰራጩ መሆኑን፤ ከሳሽ አዲስ አበባ ዉስጥ በሌላ ድርጅት ካሴቱን ያሰራጩ መሆኑን፤ ከሌሎች አርቲስቶችም ጋር ውል የፈጸሙት እሳቸዉ መሆናቸዉን፤ ከያሬድ ነጉ እና ሳሚ ዳን ጋር የተደረገዉን ውል እርሳቸዉ ያልፈጸሙ መሆኑን ገልጸዉ ሲመሰክሩ 2ኛ የተከሳሽ ምስክር  በሰጡት የምስክርነት ቃል 1ኛ የተከሳሽ ምስክር አቶ ጌዲዮን አማረ የአይቲ ባለሙያ መሆኑን የነገራቸዉ መሆኑን፤ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል በተፈጠረዉ አለመግባባት ሽምግልና ተቀምጠዉ የነበረ መሆኑን፤ ሽምግልናዉም የተደረገዉ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን የዩቲዩብ አካዉንቴን ሃክ አድርጎብኛል አስመልሱልኝ በማለታቸዉ መሆኑን፤ አቶ ጌዲዮን  አካዉንቱን ሃክ ማድረጋቸዉን አምነዉ በሽምግልናዉ ወቅት ገንዘብ ያንሰኛል ይጨመርልኝ ሲሉ የነበረ መሆኑን ገልጸዉ የምስክርነት ቃላቸዉን ሰጥቷል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ እና በአቶ ጌድዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግንኙነት አለ የለም? የሚለውን እና ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም በከሳሽ እና በተከሳሽ መከካል የተደረገዉ ውል ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት በመያዝ እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡

የመጀመሪያዉን  ጭብጥ በተመለከተ ተከሳሽ የሚከራከረዉ ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነዉ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ/ም የተደረገዉ ውል አያስገድደኝም:: አቶ ጌዲዮን ውክልና የለዉም፤ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅም አይደለም፡፡ በከሳሽና ተከሳሽ መካከል የውል ግኑኘነት ስለሌለ በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ልከፍል አይገባም በማለት ሲሆን ተከሳሽ ለአቶ ጌዲዮን አማረ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት ቀርበዉ የሰጡት ውክልና የሌለ መሆኑን፤ የተከሳሽ ምስክር አስረድቷል፡፡ ከዚህም በላይ ይህ ፍሬ ነገርም በከሳሽ የተካደ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የወካይ ተወካይ ግኑኝነት በጽሑፍ ከተሰጠ ውክልና ብቻ የማይመንጭ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 2180 መረዳት ይቻላል፡፡ አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸሙት ውል የግድ በጽሁፍ መደረግ ያለበት የውል ስምምነት አይነት አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰዉ ድንጋጌ መሰረት በጹሑፍ የተሰጠ ውክልና መኖር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይልቁንም ተከሳሽ ዉሉን በተመለከተ ከጌዲዮን አማረ ጋር ጨርሱ፤ ሀገር ዉስጥ ወኪሌ አቶ ጌዲዮን አማረ ናቸዉ ማለታቸዉ ሲታይ፤ ከከሳሽ 1ኛ ምስክር ጋር ባደረጉት ንግግር በቼኩ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ እከፍላለዉ ትንሽ ታገሱኝ ማለታቸዉ፤ ከከሳሽ 1ኛ ምስክር ጋር ያደረጉት የኢሜል ልዉዉጥ ተከሳሽ ውሉን የሚያዉቁት መሆኑን መረዳት የሚስችል በመሆኑ፤ ከሌሎች አርቲስቶች ጋርም ድርጅቱን ወክሎ ውል የሚፈጽመዉ አቶ ጌዲዮን አማረ መሆኑ የተመሰከረ ከመሆኑም በላይ ከቀረበዉ የቪዲዮ ማስረጃ መረዳት የተቻለ በመሆኑ፤ ተከሳሽ ክፍያዉን እንዲፈጽሙ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ጊዜ ስጡኝ ከማለት ዉጭ አቶ ጌዲዮን አማረ ድርጅቱን ወክሎ ውል መዋዋል የሚያስችል ስልጣን የለዉም የሚል ነጥብ አንስተዉ የማያውቁ መሆኑን  ሲታይ ተከሳሽ በዉሉ ላይ የተመለከተዉ ሙዚቃ በቅርብ የሚወጣ መሆኑን በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ መለጠፋቸዉ መመስከሩና ይህም በተከሳሽ ያለመካዱ ሲታይ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግኑኘትም መኖሩን ከላይ ከተገለጹት የተከሳሽ ግልጽ ተግባራት እና ዝምታ የሚያሳይ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 2180 እና ከፍ/ሕ/ቁ 2195(ሐ) መረዳት የሚቻል በመሆኑ እና የተከሳሽ ምስክሮች የሰጡትም ቃል እርስ በእራሱ የሚጣረስ እና እምነት የሚጣልበት ሆኖ ስላልተገኘ ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ ውክልና የለዉም በዉሉም አንገደድም በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት ያለዉ ሆኖ ስላልተገኘ እና ዉሉም ተከሳሽን ከላይ በተገለጸዉ ምክንያት የሚያስገድድ ሆኖ ስለተገኘ ፍርድ ቤቱ  የተከሳሽን ክርክር አልተቀበለዉም፡፡

2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ ዉል እንዲፈርስላቸዉ የጠየቁት አቶ ጌዲዮን አማረ ተከሳሽን ወክሎ ውል ለመፈጸም ችሎታ የለዉም በማለት ሲሆን ከላይ እንደተገለጸዉ ተከሳሽ ባደረጉት ንግግር፤ በፈጸሙት ተግባር እና ዝምታ በተከሳሽ እና በአቶ ጌዲዮን አማረ መካከል የወካይ ተወካይ ግኑኘነት የፈጠረ በመሆኑ እና ተከሳሽ በፈጸሙት ተግባር፤ ባደረጉት ንግግር እና በዝምታቸዉ አቶ ጌዲዮን አማረ የተከሳሽ ወኪል ሆነዉ በፍ/ሕ/ቁ 2195(ሐ) የሚቆጠሩ በመሆኑ ተከሳሽ ወክለዉ ውል ማድረግ የሚችሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ አቶ ጌዲዮን አማረ እኔን ወክለዉ ውል ለመግባት ችሎታ የላቸዉም የተሰጣቸዉም ውክልና የለም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡

ሌላዉ ተከሳሽ ዉሉን ለማፍረስ የጠቀሱት ምክንያት ከዉሉ የሚገባንን ጥቅም አላገኘንም የሚል ሲሆን ይህ ምክንያት ዉሉን ለማፍረስ የሚያበቃ ምክንያት ካለመሆኑም በላይ ከሳሽ በዉሉ መሰረት ያልተወጡትን ግዴታ በማስረጃ አላረጋገጡም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ 1784 እና 1784 ስር የተገለጹት የውል ማፍረሻ ምክንያቶች የሌሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ/ም የተደረገዉ ውል ይፍረስልኝ በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም ፡፡

ሲጠቃለልም አቶ ጌዲዮን አማረ የፈጸሙት ውል ተከሳሽን የሚያስገድድ  በመሆኑ እና ዉሉም የሚፈርስበት ህጋዊ ምክንያት ስላልተገኘ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፍል ይገባል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ውሣኔ

 1. ተከሣሽ ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ከ1/8/2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
 2. ወጪና ኪሣራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 5,850፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 40፣ እንዲሁም የጠበቃ አበል ብር 20,000 ተከሣሽ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

ትዕዛዝ

 • ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
 • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

የኮ/መ/ቁ ፡- 171853

ቀን ፡- 21/10/11 ዓ.ም

ፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ንግድ ችሎት

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ    

ከሳሽ ፡-    ወ/ሮ ሙሉ አጥናፍ ታዬ - ጠበቃ ዘውዱ ተሾመ - ቀረቡ

ተከሳሾች ፡-  1) ማራኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር -

ሥ/አስኪያጅ አቶ አስራት ጥላሁን ቀረቡ

2ኛ አስራት ጥላሁን አሸንጎ - ቀረቡ

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርመሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል::

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነው ከሳሽ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ጋብቻ ፈፀመው ለ20 ዓመት አብረው ሲኖሩ የነበረ መሆኑን፤ በዚህ ወቅትም 1ኛ ተከሳሽ ማህበርን በ25/10/2007 ዓ.ም በጋራ አቋቁመው የፔንሲዮን አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ መሆኑን፤ ከጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ በመካከላቸው ከፍተኛ ያለመግባባት የተፈጠረ በመሆኑ ከቤታቸው ወጥተው ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ያላቸው ጋብቻ እንዲፈርስ አመልክተው ጋብቻው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ በመ/ቁ 40455 በተሰጠ ውሳኔ የፈረሰ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም የከሳሽ ወኪል ነኝ በማለት ማህበሩ ስለከሰረ እንዲፈርስ ተስማምተናል የሚል የሐሰት ቃለ ጉባኤ በፌደራል የሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አቅርበው በማስመዝገባቸው በጋራ የሰሩትን ባለ 16 ክፍል ቤት በእናቱ ስም በማስመዝገቡ ስለ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር ገቢ ወጪና ትርፍ ምንም የማያሳውቃቸው በመሆኑ የ1ኛ ተከሳሽ ማህበርን ንግድ ፈቃድ አሰርዞ የማህበሩ ዓላማ እንዳይሳካ በማድረጉ የ1ኛ ተከሳሸ ማህበርን ገንዘብ በማህበሩ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ማድረግ ሲገባው ለግል ጥቅሙ በማዋሉ የጋራ የሆነው ቤታቸው ተሸጦ ለማህበሩ ካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል የተቀበለውን ብር 930,000 ለማህበሩ ገቢ ሳያደርግ ለግል ጥቅም በማዋሉ ለ1ኛ ተከሳሽ ማህበር የተገዛውን በሰሌዳ ቁጥር አአ-02-95088 የሚታወቀውን ተሽከርካሪ በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ ከሳሽ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የነበራቸውን አክሲዮን በመሸጥ የተገኝውን ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ ከዕቁብ የተቀበለውን ብር 480,000 ለ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ገቢ ማድረግ ሲገባው ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ ከ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ብር 2 ሚሊዮን ወጪ አድርጎ ለእናቱ ቤት የገነባበትን ገንዘብ ለማህበሩ ሳይመለስ 2ኛ ተከሳሽ ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች የፈፀመ በመሆኑ በከሳሸ እና በ2ኛ ተከሳሽ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ የተፈጠረ መሆኑን ገልፀው ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም በፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የፀደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው እንዲወሰንላቸው፣ 2ኛ ተከሳሽ በፈፀመው ጥፋት የደረሰባቸውን ጉዳት በሌላ መዝገብ ከሰው ለመጠየቅ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው፣ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸው፣ የሂሳብ አጣሪ ተሹሞ የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራላቸው እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸው ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርበዋል የሰው ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የተሻሻለ ክስ ለከሳሾች ደርሶ ተከሳሾች ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ  እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሾች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከሳሽ ያቀረቡት ክርክር የጋራ ንብረትን ጉዳይ ከማህበሩ ክርክር ጋር ደበላልቀው ያቀረቡት በመሆኑ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው የጠየቁት በህጉ የተቀመጠው የሦስት ወር ጊዜ ካለፈ በኋላ በመሆኑ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ነው፡፡ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ማህበር በስምምነት የፈረሰ በመሆኑ ክሱ የቀረበው በስምምነት ባለቀና በተፈፀመ ጉዳይ ስለሆነ የከሳሽ ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ በውልና ማስረጃ ማስረጃ ምዝገባ ፅ/ቤት የፀደቀው ቃለ ጉባኤ በህጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተሻረ ስለሆነ ስምምቱ ህጋዊ መሆኑን፤ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው ይሻርልኝ ከሚሉ በቀር ቃለ ጉባኤው የሚሻርበትን ህጋዊ ምክንያትን ያላስረዱ መሆኑን፤ ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ በቀን 14/10/1992 ዓ.ም የሰጠሁትን ውክልና ሽሪያለሁ ቢሉም ውክልናው የተሻረ ስለመሆኑ ያልደረሳቸው መሆኑን፤ ውክልናው የተሻረ መሆኑን ሌላ የሚያውቁበት መንገድ የሌለ መሆኑን፤ ይህ ሆኖ ሳለ ከሳሽ ማህበሩ የፈረሰው ውክልናው ከተሻረ በኋላ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ከሳሽ በቀን 14/10/1992 ዓ.ም የሰጡት ውክልና ተሽሯል እንኳን ቢባል ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ በቀን 15/9/1999 ዓ.ም የሰጡት ውክልና መኖሩን፣ ይህ ውክልናም ያልተሻረ መሆኑን፣ በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ የአብላጫ አክሲዮን ባለ ድርሻ ስለሆኑ ማህበሩ እንዲፈርስ መወሰን የሚችሉ መሆኑን፣ ቃል ጉባኤውም ስልጣን ባለው አካል የተመዘገበ ስለሆነ የሚሻርበት ህጋዊ ምክንያት የሌላ መሆኑን፣ ማህበሩ የፈረሰው የተቋቋመበትን ጉዳይ መፈፀም ባለመቻሉ እና በገንዘብ እጥረት መሆኑን፣ ማህበሩ በኪሳራ የፈረሰ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የማህበሩን መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ በመተላለፍ የፈፀሙት ጥፋት የሌለ መሆኑን ገልፀው የመከላከያ መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተሻሽሎ በቀረበው ክስ ላይ ሚያዝያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር በክሱ ላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮች የገለፁት በከሳሽ እና በ2ኛ ተከሳሽ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ መኖሩን ለማሳየት መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ለብርቱ ጭቅጭቅ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ያልካዱ መሆኑን፤ ተከሳሾች የቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ያቀረቡትን ክርክር በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በብይን ውድቅ ያደረገው መሆኑን፤ የንግድ ህጉ አንቀፅ 416 ኃላፊነቱ ለተወሰነ የግል ማህበር ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን፤ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የፈፀሙት እርቅ ስምምነት የሌለ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ቃለ ጉባኤውን ያፀደቁት በተቃራኒ ዘንግ ቆመው በፍርድ ቤት የጋራ ንብረትን አስመልክቶ በክርክር ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን ይህም 2ኛ ተከሳሽ ቅን ልቦና የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፤ ያፀደቀው ቃለ ጉባኤውም ሊሻር የሚገባው መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም ማህበሩን ማፍረስ የማይችሉ መሆኑን፤ ማህበሩም ሊፈርስ የሚገባው በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ግዴታቸውን ተወጥተው የማያውቁ መሆኑን ገልፀው ሲከራከሩ፤ ተከሳሾች በበኩላቸው ባቀረቡት ክርክር ከሳሽ ቀደም ሲል ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው ያልጠየቁ መሆኑን ከሳሽ ቃለ ጉባኤውን ያወቁት በ29/6/2010 ዓ.ም መሆኑን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተሻሽሎ የቀረበው ክስ እስከቀረበበት ጊዜ ከሶስት ወር በላይ መሆኑን፤ በዚህም ምክንያት የቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ መሆኑን፤ ማህበሩ በስምምነት የፈረሰ መሆኑን፤ የፈፀሙት ጥፋትም የሌለ መሆኑን፤ ገልፀው የመከላከያ መልሳቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተውን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ነው ወይስ አይደለም? የቀረበው ክስ በእርቅ ስምምነት ያለቀና የተፈፀመ ነው ወይስ አይደለም? ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ውልና ማስረጃ መዝገባ ጽ/ቤት የፀደቀው ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይጋባል ወይስ አይገባም? 1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ ሊጣራ ይገባል ወይስ አይገባም? እንዲሁም ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስዳደር ረገድ በፈፀሙት ጥፋት ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ነጥቦች እንደሚከተለው መርምሯል::

የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ የሚከራከሩት ከሳሽ የፀደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው የጠየቁት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሳሽ የፀደቀውን ቃለ ጉባኤ ያወቁት በ29/6/2010 ዓ.ም ነው፡፡ በመሆኑም የቀረበው ክስ በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) መሰረት በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) እንደተደነገገው ህግን፣ የማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍና መተዳደሪያ ደንብን ባለመከተል የተደረጉትን ውሳኔዎች ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ በሦስት ወር ውስጥ ወይም በንግድ ምዝገባ ተመዝግቦ እንደሆነም ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ በሦስት ወር ውስጥ ማንኛውም ባለጥቅም ሊቃወመው እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው ድንጋጌው ተፈፃሚነት የሚኖረው የማህበሩ አባላት በተገኙበት ወይንም በህጋዊ ወኪል አማካኝነት ተወክለው በተሰጠ ውሳኔ ላይ ከመሆኑም በላይ የማህበሩ አባላት ውሳኔው ከመስጠቱ በፊት አግባብነት ባለው ህግ፣ በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የሰበሰበው አጀንዳ ተገልፆ ጥሪ የተደረገላቸው እንደሆነ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል (የንግድ ህጉ አንቀፅ 416(1)) ይመለከታል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ማህበርን የማፍረስ ስልጣን በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ እንቀፅ 8.6 መሰረት ለማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የተሰጠ ሲሆን የጠቅላላ ጉባኤ አጠራርም በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር መመስረቻ ፅሁፍ አንቀፅ 6.2 እንደተመለከተው የማህበሩ ስብሰባ ከመደረጉ ከአስር/አስራ አምስት ቀናት በፊት በአባላቱ በአደራ ደብዳቤ የስብሰባውን ጥሪ ማሳወቅና ለውሳኔ ወይም ለውይይት ቀርበው ሀሳባቸው ምን እንደሆነ በግልፅ ማስረዳት ያለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ አጀንዳ የተያዘ መሆኑን በመግለፅ ለከሳሽ በፅሁፍ ያሳወቁ እና ስበሰባ የጥሩ መሆኑን በመግለፅ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ይህም የሚያሳየው ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ተይዞ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የፀደቀው ቃል ጉባኤ ከሳሽ በህጉ አግባብ ማለትም በንግድ ህጉ አንቀፅ 391፣ 392 እና 532 እና በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ አንቀፅ 6.2 መሰረት ጥሪ ሳይደረግላቸው የፀደቀ ቃለ ጉባኤ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ የፀደቀው ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀፅ 543 የተጠበቀላቸው ድምፅ የመስጠት መብት ሳይከበርላቸወ መሆኑን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ከሳሽን በመወከል ድምፅ ሰጥቻለሁ በማለት የሚከራከሩት በንግድ ህጉ አንቀፅ 409(1) ስር የተመለከተውን ገደብ በመተላለፍ ከከሳሽ ጋር በጉዳዩ ላይ የጥቅም ግጭት እያላቸው እና በፍቺ ተለያይተው በክርክር ላይ እያሉ እና ከሳሽንም ወክለው ድምፅ ለመስጠት የህግ ክልከላ በተቀመጠበት ሁኔታ ነው፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ የፀደቀው ለከሳሽ ጥሪ በአግባቡ ሳይደረግላቸው እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የጥቅም ግጭት እያላቸው ከሳሽን በመወከል ድምፅ የሰጡ በመሆኑ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው መኖሩን እያወቁ ግራ ቀኙ በፍቺ ከተለያዩ በኋላ በነበራቸው የጋራ ንብረት  ክርክር በመሆኑ የንግድ ህጉ አንቀፅ 416 (2) ተፈፃሚነነት የሚኖረው በቃለ ጉባኤው የተወሰነው ውሳኔ የተወሰነው አባሉ በአካል ወይም የጥቅም ግጭት ሳይኖር በአግባቡ ተወክሎ ወይንም በአግባቡ ጥሪ ተድርጎላቸው በስብሰባው ላይ ሳይገኝ የተሰጠ ውሳኔ ከሆነ ብቻ መሆኑን መረዳት የሚቻል በመሆኑ እና ድንጋጌው ከላይ በተገለፁት ምክንያቶች በተያዘው ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት የሌለው ከሆነ በፍ/ሕ/ቁ 1677(1)እና 1885 መሰረት ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ደንብ የአስር ዓመት ጊዜ በመሆኑ ተከሳሾች ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

     የንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) ለተያያዘው ጉዳይ ተፈጻሚነት አለው እንኳን ቢባል ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የነበራቸው ጋብቻ እዲፈርስ ለፍርድ ቤት ያመለከቱት ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም መሆኑን በማስረጃት ከቀረበው የፍቺ ውሳኔ መረዳት የሚቻል ሲሆን ከሳሽ ከጥቅምት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከ2ኛ ተከሳሽ መኖርያ ቤት ወጥተው መኖር የጀመሩ ስለመሆኑም በተከሳሾች የተካደ ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው ከሳሽ በቀን 27/5/2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀውን ቃለ ጉባኤ የሚያውቁት መንገድ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ በቀን 17 /8/ 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ በሰማ ዕለት ከሳሽ ቃለ ጉባኤውን በቀን 29/6/2010 ዓ.ም ያውቁ መሆኑን ገልጸው ክርክራቸውን አቅርቧል፡፡ ይህ ደግሞ ይርጋ የሚቆጠረው በፍ/ሕ/ቁ 1846 እንደተደነገገው በመብቱ መስራት ከሚችልበተ ቀን አንስቶ በመሆኑ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው ሊጠይቁ የሚችሉበት ቃለ ጉባኤው መኖሩን ካወቁበት ከቀን 29/6/2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል በዚህ መዝገብ በቀን 30/6/2011 ዓ.ም ያቀረቡ መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) መሰረት የፀደቀውን ቃለ ጉባኤ በአወቁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ማቅረባቸውን መረዳት የሚቻል በመሆኑ በዚህ ረገድም ተከሳሾች ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች ያቀረቡት ክርክር ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ ከሳሽ እንዲሻርላቸው የጠየቁት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ነው፤ ቀደም ሲል ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ላይ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው አልጠየቁም እንዲሁም ከሳሽ የጸደቀ ቃለ ጉባኤ መኖሩን በቀን 29/6/2010 ዓ.ም አውቀዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው ቃለ ጉባኤው መኖሩን በአወቁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መጠየቅ ሲገባቸው አልጠየቁም እንዲሻርላቸው የጠየቁት ቃለ ጉባኤው መኖሩን ካወቁ ከሶስት ወር በኃላ ነው በማለት ያቀረቡተትንም ክርክር በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ከመሻሻሉ በፊት ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ይዞ የተከሳሾችን የይርጋ መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው የጠየቁ መሆኑ ቀደም ሲል ባቀረቡት ክስ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ግልጽ የሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ከሳሽ ቀደም ሲል ባቀረቡት ክስ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው አልጠየቁም በማለት ያቀረቡት ክርክር ፍርድ ቤቱ የሚቀበለው አይደለም፡፡

   2ኛውን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በእርቅ ያለቀና የተፈፀመ ጉዳይ ስለሆነ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 244(2)(ረ) እንደተደነገገው ክሱ የተነሳበት ነገር በሽምግልና ታይቶ በስምምነት የተፈፀመ መሆኑን የሚገልፅ መቃወሚያ ቀርቦ በማስረጃ ከተጋገጠ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ ባለጉዳዮችን ማሰናት ያለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከሳሽ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ የጠየቁት ዳኝነት በቀን 27/5/2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ እንዲጣራ እንዲወሰንላቸው እንዲሁም ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስተዳደር ረገድ በፈጸሙት ጥፋት ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ሲሆን እነዚህን ጉዳቶች ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሰረት በሽምግልና ታይተው በስምምነት የተፈፀሙ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሾች ጉዳዩ በእርቅ ያለቀ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት ያለው ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

   3ኛውን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ የሚከራከሩበት በከሳሽ የተሰጠኝ ውክልና ስለነበረ በተሰጠኝ ውክልና 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ አድርጊያለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ቃለ ጉባኤው የሚሻርበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት ነው፡፡ በርግጥ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ በቀን 15/9/1999 ዓ.ም እና 14 /10/ 1992 ዓ.ም የሰጡት ስለመኖሩ ወይም ውክልና ከሳሽን ወክለው ስለማህበሩ ጉዳይ ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸው መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም፡፡ ይሁን እንጂ ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የፍቺ ክስ አቅርበው በክርክር ላይ የነበሩ መሆኑን የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ከማስረዳታቸውም በላይ ግራ ቀኙ የተካካዱት ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ ተወካይ የሆነ ሰው ከወካዩ ጋር በሚያስተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው የሚገባ መሆኑን፤ ተወካዩ ስራውን የሚፈፅመው ለወካዩ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ መሆኑን እንዲሁም ተወካዩ በውክልና ስራው በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልናው የተሰጠውን አደራ እንደ መልካም ቤተሰብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንዲሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ ያለበት ስለመሆኑ በፍ/ሕ/ቁ 2208፣2209 እና 2211 ስር ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም ተወካዩ ከወካዩ ጋር የጥቅም ግጭት ያለው እንደሆነ ወካዩን በመወከል ድምጽ መስጠት የሌለበት ስለመሆኑ በንግድ ህግ አንቀፅ 409(1) ስር ተመለክቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከላይ የሰፈሩትን ድጋጌዎች በመተላለፍ ከከሳሽ ጋር በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እያለ ከሳሽን በመወከል ማህበሩ እንዲፈርስ ድምጽ መስጠቱ ቅን ልቦና የሌለው መሆኑን እና ከላይ የተጠቀሱትን ግዴታዎቹን ያላከበረ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ቃለ ጉባኤ እንዲሻር በንግድ ህጉ አንቀፅ 416 መሰረት ተወስኗል፡፡

  ሌላው 2ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት ክርክር በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ አብላጫ ድምጽ ያለኝ በመሆኑ ማህበሩ እንዲፈርስ መወሰን እችላለው፡፡ በመሆኑም ቃለ ጉባኤው ሊሻር አይገባም በማለት ያቀረቡት ክርክር በተመለከተ ማህበሩን ለማፍረስ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት ስለመሆኑ የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀፅ 6.2 ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን ለማፍረስ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ 2ኛ ተከሳሽ ይህን ስለማድረጋቸው ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ በመሆኑም 2ኛ ተከሳሽ በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

    4ኛውን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማፍረስ የጸደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻር ከላይ የተወሰነ ስለሆነ እና ውጤቱም ማህበሩ እንዳልፈረሰ የሚቆጠር (የንግድ ሕግ አንቀፅ 416 (5) እና (6)) ይመለከታል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ማህበሩ እንዲፈረሰ የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ብርቱ ጭቅጭቅ የተፈጠረ ስለሆነ ማህበሩ ሊፈርስ ይገባል በማለት ክርክር አቅርበዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ብርቱ ጭቅጭቅ የሌለ መሆኑን ክደው አልተከራከሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማህበሩ አባላት ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ እንደመሆናቸው መጠን በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት በፍቺ ፈርሷል፡፡ ይህም በአባላቱ መካከል የማህበሩን እንቅስቃሴ እና ዓላማ ከግብ ለማደረስ የሚያስችል መልካም ግንኙነት አለ ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ማህበር በአባላቱ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ ያለ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ያረጋገጠ ስለሆነ በንግድ ህጉ አንቀፅ 218 እ 542 መሰረት እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡

  5ኛውን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ የተወሰነ በመሆኑ እና ማህበሩ እንዲፈርስ ከተወሰነ ደግሞ የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ የሚገባ መሆኑን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 189 የተደነገገ ስለሆነ የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡

  6ኛውን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ጉዳት ያደረሱ መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው የማህበሩ ሂሳብ ከተጣራ በኃላ በመሆኑ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስተዳደር ረገድ በፈጸሙት ጥፋት ያደረሱት ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቋል፡፡

ው  ሳ  ኔ

 1. በቀን 27 /5/ 2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ቃለ ጉባኤ ተሽሯል፡፡
 2. 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡
 3. የ1ኛ ተከሳሽ ማህበርን ሂሳብ የሚያጣራ ባለሙያ የምድቡ ሬጅስትራር ይመድብ፡፡
 4. ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ላይ ወይም በእርሳቸው ያደረሱት ጉዳት ካለ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
 5. ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡

ት  ዕ  ዛ  ዝ

 • ይግባኝ ለጠየቀ ተገልብጦ ይሰጠው፡፡
 • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የኮ/መ/ቁ 171664

የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- እንደራስ ናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር ፡- ጠበቃ ጀሚላ ክብረት ቀረቡ

ተከሳሽ፡- እንደራስ የንብረት አስተዳደር ኃ/የተ/የግል/ማህበር ፡- ጠበቃ ከበደ ደራራ ቀረቡ

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ የካቲት 20 ቀን 2011 ዓ/ም  በተጻፈ ያቀረበዉ የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከሳሽ እንደራስ ናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር በሚል የንግድ ስም በ17/02/1998 ዓ/ም የተቋቋመ መሆኑን ይህ የከሳሽ ማህበርም የሪል እስቴትና ሌሎች ንብረቶችን የማስተዳደር፤ የንግድ እንደራሴነት ስራ፤ የሪልስቴት ልማት ስራዎች፤ የንብረት አቻ ግምት ስራዎች የሚሰራ መሆኑን፤ ከሳሽ የሚሰጣቸዉን አገልግሎቶች ከሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ለመለየት እንደራስ ናሽናልስ አሴት ማኔጅመንት የሚል ቃል እና ምስል ያለበት የንግድ ምልክት በአለም አቀፍ ምድብ 36 እንዲመዘገብለት ለኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት አመልክቶ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱ እንዳይመዘገብ ተቃውሞ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የተከሳሽ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጎ የንግድ ምልክቱ በምዝገባ ቁጥር LTM/3042/2009 ተመዝግቦ የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ሳለ ከሳሽ ባስመዘገበዉ የንግድ ምልክት የተካተተዉን ቃል እና ምስል በንግድ ስምነት የሚጠቀም መሆኑን እንዲሁም ከከሳሽ ጋር አንድ አይነት የሆነ የንግድ ስም የሚጠቀም መሆኑን እንዲሁም አሳሳች የንግድ ምልክት የሚጠቀም መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት በንግድ ስም ስያሜነት እና የንግድ ምልክትነት መጠቀሙን እንዲያቆም እንዲወሰንላቸዉ፤ በአዋጅ ቁጥር 40 መሰረት ካሳ ብር 400,000 እንዲከፈለላቸዉ፤ የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል የሰዉ ምስክርም ቆጥሯል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ደርሶ ተከሳሽ ሚያዚያ 1 ቀን 2010 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክትም ሆነ የንግድ ስም  ያልተጠቀመ መሆኑን፤ እንደራስ ከሚለዉ ቃል ውጪ የከሳሽ እና የተከሳሽ የንግድ ስም የማይመሳሰል መሆኑን ተከሳሽ የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች ከሳሽ ከሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች የተለዩ መሆናቸዉን፤ የተከሳሽ የንግድ ምልክት እንደራስ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎት ኃ.የተ.የግል ማህበር በሚለዉ የንግድ ስም እና የጣት አሻራ ምስል በቅንጅት የተፈጠረ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ተከሳሽ የከሳሽ የንግድ ምልክት እንዳይመዘገብ ያቀረበዉን ተቃውሞ ውድቅ አድርጎ የከሳሽን የንግድ ምልክት መመዝገቡ የከሳሽ እና የተከሳሽ  የንግድ ምልክቶች ተመሳሳይ ናቸዉ የሚል መደምደሚያ ላይ የማያደርስ መሆኑን፤ ከሳሽ የደረሰበትን ጉዳት ያላስረዳ መሆኑን፤ ከሳሽ እንዲከፈለዉ የጠየቀዉ ካሳ ከደረሰበት ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚገባ መሆኑን እንዲሁም የሮያሊቲ ክፍያ ለጉዳዩ አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዉ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግላቸዉ ጠይቋል፡፡

ተከሳሽ እንድ መከላከያ መልሳችን ያስረዱልኛል ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡   

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም? ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሰዉን የጉዳት ካሳ ሊከፍል ይገባል ወይስ አይገባም? እንዲሁም ተከሳሽ የሞራል ካሳ ሊከፍል ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ነጥቦች  እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡

የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ የሚከራከረዉ ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት በንግድ ስምነት ስለተጠቀመ እና ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን ከሳሽ ከሚሰጠዉ አገልግሎት ጋር በተያያዘ መሳከርን የሚያስከትል ስለሆነ ተከሳሽ የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀም ሊወሰንልን ይገባል በማለት  ነዉ፡፡

ከከሳሽ ክርክር አንጻር ምላሽ ሊያገኝ የሚገባዉ ጉዳይ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ስም እና የንግድ ምልክት ከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 501/2000 ያገኘዉን የብቸኝነት መብት (exclusive right) የሚጥስ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉ ሲሆን ይህ መልስ ከመስጠታችን በፊት የንግድ ስምን እና የንግድ ምልከት አገልግሎታቸዉ/ጥቅማቸዉ ምን እንደሆነ መለየቱ ተገቢ ነዉ፡፡

ከዚህ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 2(12) እንደተመለከተዉ የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰዉ ዕቃዎች ወይም አገለግሎቶቸ ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን የንግድ ምልክቱም ቃላቶችን፤ ዲዛይኖችን፤ ፊደሎችን፤ ቁጥሮችን፤ ቀለሞችን ወይም ዕቃዎችን ወይም የመያዣቸዉን ቅርጾች ወይም የነዚህን ቅንጅቶች ሊይዝ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

የንግድ ምልክትን ለመመዝገብም ስልጣን የተሰጠዉ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት ስለመሆኑ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በአዋጅ  ቁጥር 980/2008 ዓ/ም አንቀጽ 2(10) እንደተደነገገዉ የንግድ ስም ማለት  አንድ ነጋዴ ለንግድ ስራዉ የሚጠቀምበት እና በህብረተሰቡ ዘንድ በግልጽ የሚታወቅበት ስም ነዉ በሚል ተደንግጓል፡፡ ማንኛዉም ነጋዴ የንግድ ስሙን በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ እንዳለበትም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ዓ/ም አንቀጽ 18(1) ተደንግጓል፡፡

የንግድ ስም የመመዝገብ ስልጣንም የንግድ ሚኒስቴር እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ስር ተመልክቷል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለዉ የንግድ ምልክት የሚያገለግለዉ የአንድን ድርጅት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚሰጡት አገልግሎት/ከሚያቀርቡት ዕቃዎች ለመለየት ሲሆን የንግድ ስም ደግሞ አምራቹ ወይም አገልግሎት ሰጪዉ አገልግሎቱን ወይም ዕቃዎቹን ለህበረተሰቡ የሚያቀርብበት ስም መሆኑን እንዲሁም ነጋዴው በንግድ ቦታዉ የንግድ ስሙን በሚታይ ቦታ መለጠፍ በህግ ግዴታ የተጣለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከሳሽ በማስረጃነት ያቀረበዉ የንግድ ምልክት በምዝገባ ቁጥር LTM/3042/2009 E.C በኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት የተመዘገበ መሆኑን፤ ከሳሽም ከ22/9/2015 ዓ/ም አስከ 30/5/2023 እ.ኤ.አ ድረስ ለንግድ ምልክቱ ጥበቃ የተሰጠዉ መሆኑን የንግድ ምልከቱም ለንብረት አቻ ግምት ስራዎች ምድብ 36 የተመዘገበ መሆኑን የቀረበዉ የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት ያስረዳል፡፡ ይህም የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት በአዋጅ ቁጥር አንቀጽ 501/98 አንቀጽ 15 መሰረት የተሰጠ መሆኑን እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረበዉ የንግድ ምልክት ባለቤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የንግድ ምልክቱ የተመዘገበለት ሰዉ የንግድ ምልክቱን ከተመዘገበበት ዕቃ ወይም አገልግሎት  ጋር አያይዞ የመጠቀም ወይም ሌላ ሰዉ እንዲጠቀምበት የመፍቀድ መብት የሚኖረዉ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(1) ስር ተመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ምልከት ባለቤት የሆነ ሰዉ ሌሎች ሰዎች የንግድ ምልክቱን ወይም ህዝብን ሊያሳስት የሚችል ማናቸዉንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበባቸዉ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ወይም ህዝብን ሊያሳስት በሚችል አኳን ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ እንዳይጠቀሙ፤ የንግድ ምልክቱን ወይንም የንግድ ምልክቱን የሚመስል መለያ ያለበቂ ምክንያቶች ጥቅሙን በሚጎዳ አኳኋን እንዳይጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለማገድ የሚችል ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 26(2)(ሀ)(ለ)(ሐ) የሚደነግግ ሲሆን አንድ አይነት መለያ ለአንድ አይነት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ሲውል የመሳከር ሁኔታ እንዳለ ግምት መውስድ የሚቻል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 26(3) ስር ተመልክቷል፡፡

ከሳሽ በማስረጃነት ላቀረቡት የንግድ ምልክት ከላይ የተጠቀሱት የብቸኝነት መብት (exclusive right) ያላቸዉ መሆኑን መረዳት የሚቻል ሲሆን ከሳሽ የሚከራከሩት ተከሳሽ የንግድ ምልክቴን በንግድ ስምነት እየተጠቀሙ ነዉ እንዲሁም አሳሳች የሆነ የንግድ ምልክት እየተጠቀሙ በከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥሰት እየፈጸሙ ይገኛሉ በማለት ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሽ የሚጠቀሙት የንግድ ምልክት አማካይ (average) የሆነ ተጠቃሚን ብንወስድ ተከሳሽ የሚጠቀምበት የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ሲነጻጸር በይዘትም፤ በቅርጽም እንዲሁም በአቀማመጡ ተመሳሳይ ነዉ ሊባል አይችልም እንዲሁም ተጠቃሚዉን ሊያሳስት የሚችል የንግድ ምልክት ነዉ ሊባል አይችልም፤ ከሳሽ ተከሳሽ በማስረጃነት ካቀረበዉ ውጭ ሌላ ከከሳሽ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ የንግድ ምልክት የሚጠቀም ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክትም ሆነ ስም በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26(3) መሰረት ሊወሰድ የሚችለዉንም ግምት ሊያስወስድ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሽ አሳሳች የንግድ ምልክት ተጠቅሟል የሚለዉ ክርክር የከሳሽ የንግድ ምልክት እና የተከሳሽ የንግድ ምልክትን በማነጻጸር ከታየ መሳከርን ይፈጥራል ሊባል የሚችል ካለመሆኑም በላይ ከሳሽ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት ለንብረት አቻ ግምት ስራዎች ሲሆን የንግድ ምልክቱንም በብቸኝነት መጠቅም የሚችሉት ከዚሁ የንግድ ምልክቱን ካስመዘገቡበት አገልግሎት አንጻር እንጂ የከሳሽ ማህበር መመስረቻ ጽሁፍ ላይ ለተመለከቱት አላማዎች በሙሉ አይደለም፤ ተከሳሽ የሚሰራዉ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎት ሲሆን ተከሳሽ የከሳሽን የንግድ ምልክት ከዚህ አገልግሎት ጋር አልተጠቀሙም እንጂ ተጠቅሟል ቢባል እንኳን ከሳሽ ለዚህ አይነት አግልግሎት የንግድ ምልክቱን ባላስመዘገቡበት ሁኔታ ይህን መሰል ተግባር ሊከለከሉ የሚችሉበት የህግ አግባብ የለም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ በንግድ ምልክታቸዉ ላይ የሚጠቀሙት ስም እንደራስ የንብረት አስተዳደር አገልግሎት የሚል ሲሆን ለዚህም ተከሳሽ በቀን 25/12/2008 ዓ/ም የንግድ ስያሜዉን ያስመዘገቡ መሆኑን የቀረበዉ የንግድ ስም የምስክር ወረቀት ያስረዳል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም መካከል ግጭት የለም እንጂ አለ እንኳን ቢባል ህጋችን የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም ግጭት በተፈጠረ ጊዜ እንዴት እንደሚፈታ ያስቀመጠዉ የህግ ማዕቀፍ ባይኖርም ተከሳሽ ይህን የንግድ ስም ያስመዘገቡት በቀን 25/12/2008 ዓ/ም መሆኑ ሲታይ በሌላ በኩል ከሳሽ የንግድ ምልክቱን ያስመዘገቡት እና የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸዉ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ/ም ከመሆኑ አንጻር በአዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 17(1) የንግድ ስም በመዝገብ መግባት የንግድ ስሙን ለመጠቀም መብት የሚሰጥ ተቀዳሚ ማስረጃ ስለመሆኑ የሚያመለክት በመሆኑ እንዲሁም ተከሳሽ የንግድ ስማቸዉን በሚታይ ቦታ መለጠፍ ግዴታ ያለባቸዉ ከመሆኑ አንጻር ተከሳሽ እንድራስ የንብረት አስተዳደር አገልግሎት የሚለዉን ቃል የሚጠቀሙት ከቅን ልቦና  ውጪ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ እንዲሁም ከሳሽ ተከሳሽ የንግድ ስማቸዉን የተጠቀመ ስለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጃ የለም ናሽናል አሴት ማኔጅመንት በሚለዉ ቃል ላይም የብቸኝነት መብት የላቸዉም፡፡ እንደራስ የሚለዉን ቃል ላይም የብቸኝነት መብት ያላቸዉ ንግድ ምልክቱን ካስመዘገቡበት የንብረት አቻ ግምት ስራዎች ጋር በተያያዘ  ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር  ሌሎች ሰዎች እንደራስ የሚለዉን ቃል ከንብረት አቻ ግምት ስራዎች ውጭ ላሉ አገልግሎቶች እንዳይጠቀሙ የመከልከል እና የማስከልከል በህግ ጥበቃ የተሰጣቸዉ መብት የለም፡፡

ከሳሽ አጥብቀዉ የሚከራከሩት የንግድ ምልክቱ ሲመዘገብ ተከሳሽ ተቃውሞ አቅርቦ ወድቅ ተደርጎበታል፡፡ በመሆኑም በንግድ ምልክቱ መጠቀሙ የብቸኝነት መብቴን የሚጥስ ስለሆነ አግባብነት የለዉም በማለት ነዉ፡፡ እዚህ ጋር መታየት ያለበት ነጥብ ተከሳሽ ከሳሽ የንግድ ምልክቱ እንዲመዘገብላቸዉ ለአእምሮዊ ንብረት ባመለከቱ ጊዜ የንግድ ምልክቱ እንዳይመዘገብ ተቃውሞ አቅርበዉ የነበረ ቢሆንም ያቀረቡትን መቃወሚያ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት በጽ/ቤት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ ማለት ከሳሽ የንግድ ስሙን መጠቅም አይችልም ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የንግድ ስሙን የመዘገበዉ በአዋጅ ስልጣን ያለዉ አካል የንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ እና የንግድ ምልክቱ ስለተመዘገበ የንግድ ስሙ ላይ የበላይነት (priority clause) ሊኖረዉ እንደሚችል የሚያስቀምጥ የህግ ማዕቀፍ የሌለ በመሆኑ ነዉ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያዊ አእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት በአዋጅ በተሰጣቸዉ ስልጣን መሰረት ላከናወኑት ተግባር አንዱ በሌላኛዉ ላይ የበላይ የሚሆንበትም አግባብ የለም፡፡

ከሳሽ ያቀረባቸዉ ማስረጃዎች ማለትም የአገልግሎት ክፍያ የተከፈለባቸዉ ደረሰኞች፤ የከሳሽ ማህበር መመሰረቻ ጽሁፍ፤መተዳደሪያ ደንብ፤ ከሳሽ አግልግሎታቸዉን በጋዜጣ ያስተዋዋቀባቸዉ ጋዜጦች፤ ለማስተዋቂያ ስራ የተደረገ ስምምነት፤ ተከሳሽ የከሳሽ የንግድ ምልክት እንዳይመዘገብ ያቀረቡትን አቤቱታ፤ ከሳሽ ግብር የከፈሉ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎች የቀረቡ ቢሆንም እነዚህ ማስረጃዎች የከሳሽ የንግድ ምልክት መብት ላይ ጥስት የተፈጸመ መሆኑን አያስረዱም ለተያዘዉ ጉዳይም አስረጂነት የላቸዉም፡፡ 

ሲጠቃለልም ከሳሽ ተከሳሽ የንግድ ስሙን የተጠቀመ ስለመሆኑ በማስረጃ ያላረጋገጠ በመሆኑ፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ከከሳሽ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይነት የሌለዉ በመሆኑ፤ ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት አማካይ የሆነ ተጠቃሚን ሊያሳስት የሚችል ባለመሆኑ፤ ከሳሽ እና ተከሳሽ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ተከሳሽ የሚጠቀመዉ የንግድ ምልክት ህብረተሰቡን የማያሳክር በመሆኑ፤ ከሳሽ የንግድ ምልክታቸዉን ያስመዘገቡት ለንብረት ግምት አቻ ስራዎች ስለሆነ በንግድ ምልክቱ ላይ ያላቸዉም የብቸኝነት መብት ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በመሆኑ፤ ከሳሽ እንዳራስ የሚለዉን ቃል በብቸነት ሊጠቀሙ የሚችሉት የንግድ ምልክቱን ካሰመዘገቡበት የንብረት ግምት አቻ ስራዎች ጋር በተያያዘ ብቻ በመሆኑ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች እንደራስ የሚለዉን ቃል ለሌሎች አገልግሎቶች መጠቀም እንዳይችሉ ለመከልከል የሚያስችል መብት በህግ ስላልተጠበቀላቸዉ ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ስምም ሆነ የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት አልፈጸምም በማለት ፍርድ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

2ኛ እና 3ኛዉን ነጥቦችን በተመለከተ ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ስም እና የንግድ ምልክት ላይ ጥሰት ያልፈጸሙ መሆኑ ስለተረጋገጠ መመርመር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡

ዉሳኔ

 • ተከሳሽ በከሳሽ የንግድ ምልክት እና የንግድ ስም ላይ ጥሰት አልፈጸመም ተብሏል፡፡
 • ተከሳሽ በከሳሽ ላይ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅርብ መብቱ ተጠብቋል፡፡

ትዕዛዝ

              ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡

              መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት

 

 

የኮ/መ/ቁ 171480

የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- አቶ አብዲሳ በየነ ያደታ

ተከሳሾች፡- 1ኛ) ዶ/ር አበበ ደምስስ

          2ኛ) ፍቅር ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ የካቲት 16 ቀን  2010 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም 2ኛ ተከሳሽ ማህበር በአራት አባላት በብር ሶስት ሚሊዮን ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን ከሳሽ በማህበሩ ዉስጥ ብዛታቸዉ 1,000 የሆኑ እያንዳንዳቸዉ የብር 1,000 ዋጋ ያላቸዉ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸዉ መሆኑን ከሳሽ ወደ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሲቀላቀሉ የነበራቸዉን የመድኃኒት አቅራቢ ደንበኞቻቸዉን ወደ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር በማዛወር ማህበሩ ስራ እንዲጀምር ያደረጉ መሆኑን የማህበሩም ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነዉ በቃለ ጉባኤ ተሾመዉ ማህበሩን ዉጤታማ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆኑን ይሁን እንጂ 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ስራ አስኪያጅነታቸዉ ሃላፊነታቸዉን በንግድ ህጉ፤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መወጣት ሲጠበቅባቸዉ እነዚህን ወደ ጎን በማደረግ ከሂሳብ አሰራር ዉጭ የማህበሩን ገንዘብ ገቢ እና ወጪ የሚያደርጉ መሆኑን፤ ያለ ከሳሽ እውቅና ገንዘብ ከግለሰብ ተብድሪያለሁ በሚል ማህበሩን ባለዕዳ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆኑን፤ የማህበሩ ግማሽ ካፒታል በሚሆን በብር 1.5 ሚሊዮን የቅንጦት መኪና ገዝተዉ የሚጠቀሙ መሆኑን፤ ይህ 1ኛ ተከሳሽ የቅንጦት መኪና የገዙበት መኪና ኤልሲ(LC) ለመክፈት በባንክ ተቀምጦ የነበረ ገንዘብ መሆኑን፤ ይህም ገንዘብ ወጪ በመደረጉ ኤልሲ(LC) ሳይከፈት ቀርቶ ከውጭ መግባት የነበረባቸዉ መድኃኒቶች ሳይገቡ የቀሩ መሆኑን በዚህም ምክንያት ከማህበሩ ዋና መድሃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የነበረዉ የስራ ግኑንነት የተቋረጠ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በተጨማሪ ፋክት፤ ጽጌረዳ ክሊኒክ እና ጽጌረዳ ዳይሊሲስ ሴንተር የተባሉትን ተቋማት በዋና ስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑን በዚህም ምክንያት የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሰራተኞችን በአግባቡ የማይቆጣጠሩ መሆኑን፤ ለማህበሩ ስራም በቂ ትኩረት የማይሰጡ መሆኑን፤ አፋጣኝ ስራዎችም በሚኖሩ ጊዜ የማይገኙ መሆኑን፤ በሰነዶች ላይ የማይፈርሙ መሆኑን፤ በመጋዘን ዉስጥ የሚገኙትን መድሃኒቶች በመሸጥ ለግል ጥቅማቸዉ ያዋሉ መሆኑን፤ በማህበሩ ስምም ሌሎች ስራዎችንም የሚሰሩ መሆኑን፤ የሂሳብ ሪፖርት እንዲሰጡ ሲጠየቁ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸዉን፤ ማህበሩ ትርፍ ያተረፈ ቢሆንም ትርፍ የሌለ በማስመሰል ትርፍ እንዳይከፋፍል የሚያደርጉ መሆኑን፤ ስብሰባ ጠርተዉ የማያውቁ መሆኑን፤ ከሳሽን ያለበቂ ምክንያት ከስራ አሰናብተዉ በማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገኙ የከለከሉ መሆኑን  ገልጸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነታቸዉ ተሽረዉ ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ እንዲሾም እንዲወሰንላቸዉ፤ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ በሂሳብ አጣሪ ተጣርቶ ትርፍ በድርሻቸዉ ልክ እንዲከፈላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ፤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች ኮፒ እንዲሰጣቸዉ እንዲወሰንላቸዉ፤ የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆናቸዉ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ ገብተዉ ስራዎችን እንዲሰሩ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልናል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡ የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ለተከሳሾች ደርሶ ተከሳሾች በሰጡት መልስ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ያመጣቸዉ የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች የሌሉ መሆኑን፤ ከማህበሩ ጋር ይሰሩ የነበሩትንም መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከሳሽ ከማህበሩ በዲሲፕሊን ከተባረረ በኃላ ከማህበሩ ጋር እንዳይሰሩ በማድረግ ኪሳራ ያደረሱ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን የሚመሩት በንግድ ህጉ፤ በማህበሩ መመስረቻ እና በመተዳደሪያ ደንብ መሰረት መሆኑን ከሳሽ ባቀረቡት ክስ ላይ የተገለጹትን ህገ ወጥ ተግባራት ፈጽሟል ተብለዉ በወንጀል ያልተቀጡ መሆኑን ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጭም የተበደሩት ገንዘብ የሌለ መሆኑን፤ አለ አግባብ ወጪ ያደረጉትም ገንዘብ የሌለ መሆኑን፤ የቅንጦት መኪና ያልገዙ መሆኑን፤ የማህበሩን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ያልፈጸሙ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ከአንድ በላይ ማህበር መምራታቸዉ ብቃታቸዉን ከሚያሳይ በቀር ህግ ወጥ ተግባር አለመሆኑን፤ ከአንድ በላይ ማህበር መምራት እንዲችሉ በህግ የተፈቀደ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ የከሳሽን ድርሻ ለመስጠት የገቡት ግዴታ የሌለ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ መጋዘን ዉስጥ የሚገኙ መድኃኒቶችን የሸጡ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን፤ ከሳሽ የማህበሩ አባል ባልሆኑበት ሁኔታ ትርፍ ክፍፍል እና ስብሰባ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረብ የማይችሉ መሆኑን፤ ከሳሽ የማህበሩ ደንበኞች ከማህበሩ እንዲወጡ ያደረጉ መሆኑን፤ ከሳሽ በማህበሩ፤ በሰራተኛዉ እና በስራ አመራር መካከል የኢንዱስትሪ ሰላም እንዳይኖር ያደረጉ መሆኑን፤ የአለቃ ትዕዛዝ የማይቀበሉ መሆኑን፤ በስራ ገበታ ላይም የማይገኙ መሆኑን፤ በስራ አጋጣሚ በእጃቸዉ የገባዉን ቼክ በመጠቀም የ1ኛ ተከሳሽን ስም እና ዝና ያጎደፉ መሆኑን ገልጸዉ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ተከሳሾች ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡ የሰዉ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡

የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ቀጥሎ የተመለከተዉን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡

1ኛ) 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ተሽረዉ በምትካቸዉ ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ ሊሾም ይገባል ወይስ አይገባም?

2ኛ) የ2ኛ ተከሳሽ ማህበሩ ሂሳብ በሂሳብ አጣሪ ተጣርቶ ከሳሽ በድርሻቸዉ ትርፍ ሊከፈላቸዉ ይገባል ወይስ አይገባም?

3ኛ) ከሳሽ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዘገቢያ ሰነዶች ኮፒ ሊሰጣቸዉ ይገባል ወይስ አይገባም?

4ኛ) ከሳሽ በማህበሩ ቅጥር ግቢ ዉስጥ እንዳይገኙ እና ስራ እንዳይሰሩ የተጣለባቸዉ ክልከላ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም?

የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች ከሳሽ የማህበሩ አባል አይደለም በመሆኑም የማህበሩ ስራ አስኪያጅ እንዲሻር ሊጠይቅ አይገባም በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡ ከሳሽ የማህበሩ አባል ናቸዉ ወይስ አይደሉም የሚለዉን ነጥብ በተመለከተ ይህ ፍርድ ቤት ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ከሳሽ አባል መሆናቸዉን በማረጋገጥ ብይን ሰጥቷል ይህ ብይን በይግባኝ አልተሻረም አልተለወጠም፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የማህበሩ አባላት ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ/ም በተያዘ እና በፌዴራል የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በተመዘገበ ቃለ ጉባኤ የማህበሩ አባል እና ስራ አስኪያጅ የሆኑት 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ዉስጥ ከነበራቸዉ 1,500 አክሲዮኖች 500 አክሲዮኖችን፤ ወ/ሮ ክብነሽ ስብስቤ ከነበራቸዉ 750 አክሲዮኖች ዉስጥ 250 አክሲዮችን እንዲሁም ህጻን ዳንኤል አበበ ከነበራቸዉ 750 አክሲዮን ዉስጥ 250ዉን በድምሩ 1,000 አክሲዮኖች በሽያጭ ለከሳሽ የተላለፈ መሆኑን የቀረበዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ ይህ ቃለ ጉባኤ ስለመሻሩ በተከሳሾች በኩል የቀረበ ማስረጃ የለም፡፡ ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዉስጥ በባላ አክሲዮንነት በማህበሩ አክሲዮን መዝገባ ላይ እስከ ተመተዘገቡ ድረስ እንደ ማንኛዉም የማህበሩ አባል ለዉሳኔ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ድምጽ የመስጠት፤ ስራ አስኪያጅ ጥፋት ከፈጸመ ስራ አስኪያጅ እንዲሻር፤ የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራ እና የማህበሩን ሰነዶች ለመመልከት ለመጠየቅ መብት አላዉ፡፡ (የንግድ ህጉ 522፤ 527(5)፤ 533፤ 534፤ 537 ይመለከታቸዋል)፡፡

ተከሳሾች አጥብቀዉ የሚከራከሩት ከሳሽ ከማህበሩ ጋር በገባዉ ግዴታ መሰረት ሶስት የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ከማህበሩ ጋር ቋሚ ውል እንዲዋዋሉ አላደረገም፡፡ በብድር ዉሉ መሰረትም ክፍያዉን አልከፈለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከሳሽ ስራ አስኪያጅ ይነሳልኝ የሚል ዳኝነት ሊጠይቅ አይችልም በማለት ነዉ፡፡ በርግጥ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር እና ከሳሽ በቀን 1/11/2008 ዓ/ም ባደረጉት የብድር ውል ስምምነት ማህበሩ ለከሳሽ ብር አንድ ሚሊዮን ያበደረ መሆኑን አከፋፈሉን በተመለከተ ደግሞ ከሳሽ ከማህበሩ ጋር ጃኖ፤ ፋርኮ እንዲሁም ሌላ አንድ የመድሃኒት አምራች ድርጆቶች ጋር ስምምነት እንዲፈጽም ካደረገ ከሳሽ በብድር ከወሰደዉ ብር አንድ ሚሊዮን ላይ ብር 500,000 እንደከፈለ የሚቆጠር መሆኑን ቀሪዉ 500,000 ደግሞ የሚከፈለዉ ከሳሽ ከተከሳሽ ማህበር በድርሻዉ ከሚያገኘዉ ትርፍ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ከሳሽ ጃኖ፤ፋርኮ እንዲሁም ኤሮፒያን ኤጅብሺያን ከሚባሉ መድሃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር 2ኛ ተከሳሽ ውል እንዲፈጽም ያደጉ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በተከሳሾች በኩል የቀረቡትም ምስክሮች ማህበሩ ጃኖ እና ፋርኮ ከሚባሉ የመድሃኒት አቅራቢዎች መድሃኒት ለሁለት ዙር በውክልና ያስመጣ መሆኑን መስክረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፋርኮ ፋርማሲውቲካልስ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን 2ኛ የሀገር ዉስጥ አከፋፋይ ያደረገ መሆኑን ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በቁጥር ኢቲኤች/ፒኤችአር/001/2016 በቀን 3/13/2008ዓ/ም፤ የጃኖ ፋርማሲዉቲካልስ ኃ/የተ/የግል/ማህበር በቀን 8/2/2009 ዓ/ም ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በጻፈዉ ድብዳቤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን 1ኛ ወኪል ያደረገ መሆኑን የገለጸበትን፤ ለዚህ ለተደረገዉ የአከፋፋይ ውክልና ውልም 50 የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የተከፈለ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎች ከሳሽ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ የኤሮፒያን እና ግብጻያዉን መድሃኒት አምራች እና አከፋፋይ 2ኛ ተከሳሽ ማኅበርን በኢትዮጵያ ዉስጥ 2ኛ ወኪል አከፋፋይ ያደረጋቸዉ መሆኑን ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በቀን 6/1/2009 ዓ/ም በጻፈዉ ደብዳቤ የገለጸበትን እንዲሁም ለወኪል ስምምነት ክፍያም ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና አንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን 50 የአሜሪካን ዶላር የከፈለ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎች ከሳሽ አቅርቧል፡፡

ተከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ቢያንስ ከ5-10 አመት ከማህበሩ ጋር በቋሚነት እንዲሰሩ ውል ማዋዋል ነበረበት በሚል ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ባደረጉት የብድር ውል ላይ ከሳሽ የገባዉ ግዴታ ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጋር ተገቢዉን ስምምነት እንዲያደረጉ ማድረግ የሚል ሲሆን ተገቢዉ ስምምነት የሚለዉ ቃል ግልጽ አይደለም ይህ ከሆነ ደግሞ ውሉ ትርጉም የሚያስፈልገዉ ሲሆን ውሉ ሊተረጎም የሚገባዉ በፍ/ሕ/ቁ 1731 እና 1732 በተደነገገዉ መስረት የግራ ቀኙን መተማመንና ቅን ልቦና፤ ፍትሕን እንዲሁም ልማዳዊ አሰራርን  መሰረት በማድረግ ነዉ፡፡

ከዚህ አንጻር የተያዘዉ ጉዳይ ሲታይ ከሳሽ ግዴታ የገባዉ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን ውጭ ከሚገኙ የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር ተገቢዉን ውል እንዲዋዋል ማድረግ ሲሆን ተገቢው ውል/ስምምነት ደግሞ መድኃኒት አምራቾቹ የሚያቀርቡትን መድሃኒተች/ምርቶች በውክልና ማከፋፈል እንዲችል የሚያደርግ ውል እንዲፈጸም ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም ይገባዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ከላይ የተጠቀሱትን የመድሃኒት አምራቾችን ምርት በውክልና እንደዲያከፋፍል ውክልና ተሰጥቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች የሚያመርቱትን መድኃኒት ለማከፋፈል ውክልና የተሰጣቸዉ ከሆነ ደግሞ በዘርፉ በተለመደዉ አሰራር መሰረት ከሳሽ ተገቢዉ የውል ስምምነት እንዲፈጸም ያደረጉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ተከሳሾች ይህን ውክልና አናውቀዉም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ተከሳሽ እራሱ ያቀረባቸዉ ምስክሮች በሀገር ዉስጥ መድሃኒት ለማከፋፈል ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ የሚያስፈልግ መሆኑን እንዲሁም የውጭ መድሃኒት ሀገር ዉስጥ ማከፋፈል የሚቻለዉ አከፋፋዩ ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒትና የጤና አንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ ሲያገኝ መሆኑን እንዲሁም ማህበሩ ከጃኖ እና ከፋርኮ የመጡ ምርቶችን ሲያከፋፍል የነበረ መሆኑ መስክረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ ከሳሽ በገባዉ ግዴታ መሰረት ግዴታዉን የተወጣ መሆኑን ነዉ፡፡ በሌላ በኩል የተከሳሾች ምስክሮች በሰጡት ምስክርነት ከሳሽ ከላይ ከተጠቀሱት የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር ከ5-10 ሊቆይ የሚችል ስምምነት እንዲደርግ ማድረግ ነበረበት በማለት የምስክርነት ቃል ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዉሉ ላይ ከሳሽ ከ5-10 አመት ድርስ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ውል እንዲገቡ ለማድረግ ግዴታ አልገባም፡፡ የተደረገዉ ውልም ይህን አያመለክትም የተከሳሾች ምስክሮችም ከ5-10 አመት ድርስ ሊያዋውል ይገባል በማለት የሰጡት ምስክርነት የግል አስታያየታቸዉ መሆኑን ከመግለጻቸዉም በላይ በዚህ አይነት ስራ ላይ የቆዩ ባለመሆናቸዉ እና በዘርፉም እውቅት የሌላቸዉ ከመሆኑ እንጻር እንዲሁም በማህበሩ ዉስጥ የመድሃኒት ኢምፖርት ላይ በብቸኝነት ሲሰራ የነበረዉ ከሳሽ መሆኑ በተከሳሾች ምስክሮችም የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ማህበሩም ከሳሽ በአባልነት ከመቀላቀሉ በፊት መድሃኒት አስመጥቶ የማያውቅ መሆኑ ሲታይ ከ5-10 አመት ድረስ ማዋዋል ነበረበት በማለት የሰጡት የምስክርነት ቃል እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ከሳሽ ከ5-10 ዓመት የሚቆይ ቋሚ ውል ማዋዋል ነበረበት በማለት ያቀረቡት ክርክር በተደረገዉ ውል ላይ ያልተገለጸ እና ከሳሽም እንዲያውቀዉ ያልተደረገ ስለሆነ በፍ/ሕ/ቁ 1780(2) መሰረት ከ5-10 አመት ድረስ የሚቆይ ውል ከላይ የተጠቀሱት መድኃኒት አምራቾች ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር እንዲፈጸሙ ለማድረግ ግዴታ ገብቷል ሊባሉ አይችሉም ይህን እንዲፈጽሙም ሊገደዱ አይችልም፡፡

ከሳሽ በበድር ዉሉ መስረት የገባዉ ግዴታ ቀሪዉን ብር 500,000 የሚከፈለዉ ከትርፍ ክፍፍል ላይ ተቀናሽ እየተደረገ መሆኑን ውሉ ስለሚገልጽ እና የግራ ቀኙ ምስክሮችም እስካሁን ድረስ ማህበሩ የትርፍ ክፍፍል አድርጎ የማያውቅ መሆኑን ስለመሰከሩ ከሳሽ ቀሪዉን 500,000 ከትርፍ የመክፍል ግዴታዉን አልተወጣም ሊባል አይችልም፡፡

1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነዉ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 8 መሰረት የተሾሙ መሆኑን በማስረጃነት የቀረበዉ የመመስረቻ ጽሁፍ ያስረዳል፡፡ በመመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ስራ አስኪያጅ ከስራ አስኪያጅት ስልጣኑ ሊሻር የሚችለዉ በንግድ ህጉ 527(1) እና 536(2) መሰረት ከማህበሩ ባለአክሲዮኖች መካከል በሶስት አራተኛ ድምጽ ባላቸዉ ባለአክሲዮኖች ሲደገፍ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌም ተፈጻሚነት ያለዉ የማህበሩን ስራ አስኪያጅ በጠቅላላ ጉባኤ ለመሻር በቀረበ ጊዜ ሲሆን በሌላ በኩል እንድ ስራ አስኪያጅ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ቢሆንም ስራ አስኪያጁ ከስልጣኑ እንዲነሳ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥፋቶች እስካሉ የማህበሩ አባላት ስራ አስኪያጁ በፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲሻር መጠየቅ እንደሚቻሉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም ከሳሽ የማህበሩ አባል መሆናቸዉ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ሶስት የመድሃኒት አምራች ድርጅቶችን ያዋዋሉ በመሆኑ በዚህ ረግድ ያለባቸዉን ግዴታ የተወጡ በመሆኑ፤ ከትርፍ የሚከፈለዉን እዳቸዉ እንዲከፈል ያልተደረገዉ ትርፍ ለአባላት ባለመከፋፈሉ መሆኑ ስለተረጋገጠ እንዲሁም ከሳሽ የማህበሩ አባል እንደመሆናቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ጥፋት የፈጸሙ እንደሆነ ከስራ አስኪያጅነት ስልጣናቸዉ እንዲነሱ ዳኝነት ለመጠየቅ የንግድ ህጉ የሚፈቅድ በመሆኑ ተከሳሾች ከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንዲነሳ ሊጠይቁ አይገባም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡

ፍርድ ቤቱም 1ኛ ተከሳሽ ከስራ አስኪያጅነት ሊያሽራቸዉ የሚችል ጥፋት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም የሚለዉን ነጥብ ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ተፈጽሟል ከተባሉት ተግባራት አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡     

የአንድ ማህበር ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተሾመ ሰዉ ህግን፤ የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ እንዲሁም መተዳደሪያ ድንብ መሰረት አድርጎ ሊሰራ አንደሚገባ ግልጽ ነዉ፡፡

ከዚህ አንጻር 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በተጨማሪ ሌሎች ሶሰት ድርጅቶችን ማለትም ጽጌረዳ ዲያሊሲስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ ጽጌራዳ ቁጥር 1 ክሊንክን እንዲሁም ፋክት የጤና መገልገያዎች ማምረቻ እንዱስትሪን በስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑን እራሳቸዉ በሰጡት ምስክርነት ከማረጋገጣቸዉም በላይ በሌሎች ምስክሮች የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ፡፡ 

በአዋጅ ቁጥር 980/2010 አንቀጽ 41 መሰረት ማንኛዉም ሰዉ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በአንድ ጊዜ በስራ አስኪያጅነት ሊመራ እንደማይችል ተመልክቷል፡፡

ህግ አውጪዉ ይህን ደንጋጌ ሲደነግግ ሊያሳከዉ ያሰበዉ ዓላም ያለ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መንፈስም መረዳት የሚቻለዉ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበር በስራ አስኪያጅነት የሚመራ ሰዉ ለየ ማህበራቱ በቂ ጊዜ ላይሰጥ እንደሚችል፤ የማህበሩን እንቅስቃሴ በተገቢዉ መጠን ክትትል ሊያደርግ የማይችል መሆኑን እንዲሁም ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት እንዳይከሰቱ በማሰብ ጭምር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ ህግን በጣሰ መልኩ ከአንድ በላይ የሆኑ የንግድ ማህበራትን እየመሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ማህበሩን በሚፈለገዉ መጠን ክትትል እያደረጉ እና አስፈላገዉን ጊዜ እየሰጡ እያስተዳደሩት ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩ የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያከናውን ለማስቻል በባዶ ወረቅት ላይ እየፈረሙ በስራ ቦታ ላይ የማይገኙ መሆኑ መረጋገጡ ሲታይ ለማህበሩ በቂ ጊዜ ሰጥተዉ ማህበሩን እየመሩ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል የ1ኛ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 525(1) መሰረት ከአንድ በላይ የሆኑ ድርጅቶችን በስራ አስኪያጅነት ለመምራት ይችላሉ በማለት ክርክር ያቀረቡ ቢሆንም ይህ ድንጋጌ አንድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንድ ወይም ከአንድ በላይ ስራ አስኪያጆች ሊኖሩት እንደሚችል የሚያመለክት ድንጋጌ እንጂ አንድ ስራ አስኪያጅ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በስራ አስኪያጅነት መምራት የሚችል ስለመሆኑ የሚደንግግ ድንጋጌ አይደለም፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ በዚህ ረግድ ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡

ሌላዉ 1ኛ ተከሳሽ በ1.4 ሚሊዮን ብር ለእርሳቸዉ መጓጓዣ የገዙ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን አንድ ስራ አስኪያጅ እያንዳንዱ የሚፈጽዉ ተግባር የማህበሩን አላማ በሚያሳካ መልኩ ሊፈጽመዉ እንደሚገባ ከንግድ ህጉ እና ከማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ ለመመልከት ይቻላል፡፡ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ካፒታል ሶስት ሚሊዮን በሆነበት ሁኔታ፤ ይህ መኪና የተገዛበት ገንዘብ ለኤሊሲ (LC) ፕሮሰስ ተቀምጦ የነበረ መሆኑ እንዲሁም ማህበሩ ዕቃ የሚያመላልሰዉ በኪራይ በተገኘ በሌሎች ሰዎች ተሽከርካሪ በሆነበት ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ ተሽከርካሪዉን የገዙት የማህበሩን አላማ ለማሳካት ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ይልቁንም ማህበሩ ከወጭ መድሃኒት እያስመጣ የሚሸጥ እንደመሆኑ የኤሊሲ ፕሮሰሱ እንዲቋረጥ መደረጉ በማህበሩም ሆነ በማህበሩ አባላት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነዉ፡፡ መኪናዉ የተመዘገበዉ በማህበሩ ስም ቢሆንም 1ኛ ተከሳሽ መኪናዉን የገዙት ለማህበሩ ጥቅም ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ግዥዉም የማህበሩን አቅም ያላገነዘበ ነዉ፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ መኪናዉን ለግል ጥቅማቸዉ ነዉ የገዙት ከሚባል በቀር ለማህበሩ ጥቅም ነዉ የገዙት ሊባል አይችልም፡፡

ከሳሽ የማህበሩ ሂሳብ በተደጋጋሚ እንዲሰጠዉ ጠይቆ በ1ኛ ተከሳሽ የተከለከለ መሆኑን የቀረቡት የከሳሽ ምስክሮች አስረድተዋል፡፡ ይህም ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 የተጠበቀለትን መብት የሚጥስ ተግባር ነዉ፡፡ 1ኛ ተከሳሽም የማህበሩን ሂሳብ የሚያሳይ ሪፖርት ለከሳሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህን አለማድረጉም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በህግ፤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፉ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተጣለባቸዉን ሃላፊነት ያልተወጡ መሆኑን ነዉ፡፡

ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ስብሰባ አይጠራም፤ ስብሰባ እንዲጠራልኝም ስጠይቅ ስብሰባ እንዲደረግ አያደርግም የሚል ክርክር ያቀረበ ሲሆን በንግድ ህጉ 532 የማህበሩ አባላት ቁጥር ከ20 በላይ ከሆነ በመተዳደሪያ ደንቡ በተገለጸዉ ቀን ስብሰባ/ጉባኤ ሊደረግ እንደሚገባ የተመለከተ ሲሆን ሌሎች ጉባኤዎችን/ስብሰባዎቸን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በሌለበት የማህበሩ ተቆጣጣሪዎች ወይም በማህበሩ ዉስጥ ከግማሽ በላይ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸዉ የማህበሩ አባላት ሊጠሩ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዉስጥ ከግማሽ በላይ ድርሻ የሌላቸዉ በመሆኑ ስብሰባ እንዲጠራ ሊያድርጉ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ በ2ኛ ተከሳሽ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 6.1 መሰረት የማህበሩ የሂሳብ አመት ከተዘጋ ከአራት ወር ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ የማህበሩ የሂሳብ አመት ደግሞ ከሐምሌ 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ እንደሆነ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10 ተገልጻል፡፡ ይህ ጉባኤ እንዲደረግ ጥሪ የማድረግ ግዴታ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ነዉ፡፡ 1ኛ ተካሳሽ ስብሰባ የማይጠሩ መሆኑን በከሳሽ ምስክሮች የተረጋገጠ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች 1ኛ ተከሳሽ ስብሰባ ሲጠሩ የነበራ እና ጉባኤዉም ሲካሄድ የነበረ መሆኑን በሚገልጽ መልኩ ምስክርነታቸዉን ሰጥተዉ በከሳሽ ምስክሮች የተሰጠዉን የምስክርነት ቃል አላስተባበሉም፡፡

ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ  2ኛ ተከሳሽ ማህበር ትርፍ እያስመዘገበ ባለበት ሁኔታ በአባላት መካከል ትርፉ እንዳይከፋፈል አድርጓል በማለት ክርክር ያቀረቡ ሲሆን በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 7 መሰረት ዓመታዊ ትርፍ በአባላቱ መካከል የሚከፋፈል መሆኑ የተመለከተ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩ ትርፍ ያገኘ መሆኑን ሳይክዱ ትርፍ ያልተከፈፈለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከሳሽም ሆኑ የተከሳሾች ምስክሮች ማህበሩ ያስመዘገበዉ ትርፍ በአባላት መካከል ያልተከፋፈለ መሆኑን መስክረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ወኪል እንደመሆናቸዉ መጠን በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሃላፊነታቸዉን ያልተወጡ መሆኑን ነዉ፡፡

ሲጠቃለልም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን የምመራዉ በህግ፤ በመመስረቻ ጽሁፍ እንዲሁም በመተዳዳሪያ ደንቡ መሰረት ነዉ በማለት ክርክር ያቅርቡ እንጂ ማህበሩን በህግ፤ በመተዳደሪያ ደንቡ እና በመመስረቻ ጽሁፉ መሰረት የማይመሩ መሆኑን ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑ በመረጋገጡ፤ 1.4 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መኪና መግዛታቸዉ የማህበሩን አላማ ለማሳካት ሊባል የማይችል በመሆኑ፤ ከሳሽ የሂሳብ ሪፖርት እንዲሰጠዉ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸዉ በመረጋገጡ፤ ማሕበሩ ትርፍ ያስመዘገበ ቢሆንም አመታዊ ትርፍ በማህበሩ አባላት መካከል እንዲከፈፈል ያላደረጉ መሆኑ በመረጋገጡ እንዲሁም የማህበሩ አባላት ዓመታዊ ጉባኤ/ስብሰባ  እንዲደረግ የማያደርጉ መሆኑ በመረጋገጡ፤ እነዚህም ድርጊቶች በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) መሰረት ስራ አስኪያጁን ለመሻር የሚያበቁ በቂ ምክንያቶች በመሆናቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ሊሻሩ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡

2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች የማህበሩ ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ አጣሪ/ባለሙያ ተጣርቶ የሚያውቅ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ከሳሽም የማህበሩ ባለድርሻ እንደመሆኑ መጠን የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራ የመጠየቅ በህግ የተሰጠዉ መብት አለዉ፡፡ በመሆኑም የ2ኛ ተከሳሽ ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ ሊጣራ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡ ከሳሽ የጠየቁትን የትርፍ ክፍፍል የማህበሩ ሂሳብ ተጣርቶ ከቀረበ በኃላ የሚወሰን ነዉ፡፡

3ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 መሰረት የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች የማግኘት መብት አለዉ፤ ተከሳሾች እነዚህን ሰነዶች ለከሳሽ የሰጡ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ስለሆነም ተከሳሾች የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዘገቢያ ሰነዶች ኮፒ ለከሳሽ ሊሰጡ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡

4ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ እንደሆኑ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም የተያዘዉ እና በሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ምዝገባ ጽ/ቤት የተመዘገበዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ ይህ ቃለ ጉባኤ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረዉን የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ የሚያሻሽል እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩትን የማህበሩን ምክትል ስራ አስኪያጅ ሽሮ በከሳሽ የሚተካ ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም በማህበሩ አባላት የተያዘዉ ቃል ጉባኤ የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አካል ተድርጎ የሚቆጠር ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽን ከማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅነት መሻር የመተዳደሪያ ደንቡን እንደማሻሻል የሚቆጠር በመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 536(2) መሰረት ከማህበሩ አባላት በሶስት አራተኛ ድምጽ ሊደገፍ ይገባል፡፡ በሌላ አነጋገር 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽን ከምክትል ስራ አስኪያጅነት ስልጣናቸዉ የማሰናበት ህጋዊ ስልጣን የላቸዉም፡፡ በመሆኑም ከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆናቸዉ፤ ተከሳሾች በማስረጃት ያቀረቡት የፍርድ ቤት ዉሳኔዎችም ከሳሽ ከቴክኒካል ማናጀርነታቸዉ የተሰናበቱ መሆኑን እንጂ ከምክትል ስራ አስኪያጅነታቸዉ የተሰናበቱ መሆኑን የማያሳይ በመሆኑ እንዲሁም ከሳሽ የማህበሩ አባል በመሆናቸዉ የማህበሩን እንቅስቀሳሴ የመከታተል ህጋዊ መብት ስላላቸዉ ተከሳሾች ከሳሽ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገባ እና በምክትል ስራ አስኪያጅነት የስራ ድርሻዉ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርጉትን ክልከላ ሊያቆሙ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡

በመጨረሻም ተከሳሾች የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፤ መተዳደሪያ ደንብ፤ ግራ ቀኙ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 199809 በሚያደርጉት ክርክር የቀረበዉ ክስ እና መልስ፤ ግራ ቀኙ አድርጓል የተባለዉን የብድር ውል፤ የማህበሩን የሂሳብ አያያዝ እና የኦዲት ሪፖርት፤ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 173410 የቀረበዉ የወንጅል ክስ መዝገብ  እንዲሁም ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የተሰናበተዉ የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽሞ መሆኑን ያስረዳልናል በማለት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 መሰረት እንዲቀርቡላቸዉ የጠየቁ ሲሆን የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ በከሳሽ በኩል የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች እነዚህ በከሳሽ በኩል የቀረቡት የማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ትክክለኛ ቅጂ አይደሉም በማለት ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እነዚህ ሰነዶች በድጋሚ እንዲቀርቡ የሚታዘዝበት የህግ አግባብ ካለመኖሩም በላይ ሰነዶቹ በማህበሩ የሚገኙ ከመሆኑ አንጻር በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለማስቀርብ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145(2) እና 145(3) ስር የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ በነዚህም ምክንያቶች ፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች ሳያስቅርብ ቀርቷል፡፡ እንዲሁም ግራ ቀኙ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 199809 በሚደርጉት ክርክር የቀረበዉ ክስ እና መልስ እንዲሁም ግራ ቀኙ አድርጓል የተባለዉን የብድር ውል ተከሳሾች ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝላቸዉ ጠይቀዉ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ የተደረገ በመሆኑ በድጋሚ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 እንዲቀርቡ የሚታዘዝበት አግባብ ስለሌለ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች በዚህ ረግድ ያቀረቡትን ጥያቄ አልተቀበለዉም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾች በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 173410 የቀረበዉ የወንጅል ክስ መዝገብ እንዲሁም ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የተሰናበተዉ የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽሞ መሆኑን ያስረዳልናል በማለት ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 መሰረት እንዲቀርብላቸዉ የጠየቁትን ማስረጃዎች ለተያዘዉ ጉዳይ ትክክልኛ ፍርድ ለመስጠት የማይረዱ ለአስረጂነትም ተገቢነት የሌላቸዉ ማስረጃዎች በመሆናቸዉ የተከሳሾች ጥያቄ ተገቢነት የሌለዉ ሆኖ ስለተገኘ ፍርድ ቤቱ ሳያስቀርባቸዉ ቀርቷል፡፡

ዉሳኔ

 1. 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ከዛሬ ጀምሮ ተሽሯል፡፡
 2. የምድቡ ሬጅስተራር ጽ/ቤት የማህበሩ አባላት ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ እንዲመርጡ የማህበሩን ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ ባለሙያ ይመድብ፡፡
 3. የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ አጣሪ እንዲጣራ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም የምድቡ ሬጅስተራር ገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ እንዲመድብ ታዟል፡፡
 4. ተከሳሾች የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች ኮፒ ለከሳሽ ይሰጡ፡፡
 5. ተከሳሾች ከሳሽ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገባ እና በምክትል ስራ አስኪያጅነት የስራ ድርሻዉ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርጉትን ክልከላ ሊያቆሙ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
 6. ከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅርብ መብቱ ተጠብቋል፡፡

ትዕዛዝ

               - ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡

               - መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት

 

                                                                

 

 

Page 4 of 5