Font size: +
13 minutes reading time (2521 words)

ቅጥ አልባ ቅጣቶች በኢትዮጵያ ሕጎች    

ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ወንጀል የዚች ዓለም እውነት ነው፡፡ ቃኤል አቤል መግደሉ ከተሰማበት ይህን ጽሑፍ እርሶ እያነበቡ እስካሉት ቅፅበት ድረስ ወንጀል በሰው ልጆች ላይ በሰው ልጅ በራሱ ይፈፀማል፡፡ ይህ ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር መሳ የሆነ ታሪክ ያለው ወንጀል ወደፊትም ማቆሚያ የሚኖረው አይመስልም፡፡ የሰው ልጅ ማድረግ የቻለው  ወንጀል የሚቀንስበትን አማራጭ መዘየድ እንጂ ወንጀል አልባ ዓለም መፍጠር አይደለም፡፡ ምናልባትም ወንጀል የመቀነስ ሙከራውም ተሳክቶ እንደሆነ እንጃ፡፡

ወጣም ወረደ ሁሉም ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰቡ ታሪካዊና ማህበራዊ ዳራ ራሱን ከወንጀል ለመከላከል በዋናነት የዘየደው መላ ቅጣት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም የወንጀል ቅጣት በኢትዮጵያ ሕግ ያለውን መልክ በመጠኑ ከጠቅላላ የቅጣት መርሆች አኳያ በመቃኘት በአሁኑ ሰዓት እርስ በእርሳቸው ተናባቢነት የሌላቸው በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ ቅጣት የያዙ፣ ለቀላል ወንጀል ከባድ ቅጣት ለከባድ ወንጀል ቀላል ቅጣት የደነገጉ  በግብታዊነት እዚህም እዚያም ቅጣትን እንደ ተራ የመንገድ ጨቃ እያነሱ የሚለጥፉ ሕጎች ከወንጀል ጠቅላላ ዓላማና ግብ አኳያ በአጭሩ መፈተሸ ነው፡፡

የወንጀል ሕግ ዓላማ

የወንጀል ሕግ ዓላማ ማህበረሰቡን ከሚደርስበት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ አካላዊና ሞራላዊ ጥቃት መታደግ ሲሆን ይህንም የሚያድገው አስቀድሞ ወንጀል የሆኑ እና ያልሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በተለይም ወንጀል የተባሉትን ጉዳዮች መፈፀም የሚያስከትለውን ቅጣት በመደንገግ ለጠቅላላው ማህበረሰብ እንዲህ ካደረክ እንዲህ ትሆናለህ የሚል ተገቢውን ማስታወስ በማድረግ በማስጠንቀቅ  ይህን ማስጠንቀቂያ አልፎ ወንጀል የሚፈፅምን ሰው በሌሎች ሕጎችና  የወንጀል ችሎት አመራሮች መሠረት እንዲቀጣም በማድረግ ነው፡፡

የቅጣት ዓላማ

ቅጣት ወንጀል በማህበረሰቡ ላይ የፈፀመውን ወንጀለኛ መበቀያ (Retribution) ነው ከሚሉት ጀምሮ የለም አንድ ሰው ወዶ ወንጀል አይሰራም ወንጀል እንደማንኛውም በሽታ ህመም ነው ስለዚህ የቅጣት ዓላማ በወንጀል የታመመ ወንጀለኛን አክሞ አድኖ ጤነኛ አምራች ዜጋ አድርኖ ወደ ማህበረሰቡ መመለስ ነው እስከሚሉት ድረስ የቅጣት ዓላማ በርካታ ዘውጎች አሉት፡፡

1. ቅጣት እንደ በቀል ማስፈጸሚያ (retribution)

የዚህ የቅጣት ዓላማ አራማጆች ወንጀለኛው ማህበረሰቡ ተው አታድር ያለውን ነገር ተላልፎ በማህበረሰቡ ጤና፣ ሞራል፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ፋይዳ ላይ ጥቃት ስለፈጸመ ለዚህ ተገቢ ያልሆነ ድርጊቱ የጁን ማግኘት አለበት የሚል መነሻ ያላቸው ሲሆን መሠረቱም የሀሙራቢ አይን ያጠፋ አይኑ ይጥፋ መርሆ ነው፡፡ ይህም ለፈፀመው ወንጀል ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ እንደመስጠት ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ወነጀለኛው በማህበረሰቡ ላይ ለፈፀመው ወነጀል በበቀል ስሜት እኛን ያደረገንን እሱም ይቅመሰው በሚል ፈፀመ የተባለውን ወነጀል ይመጥናል ያሉትን ቅጣት መጣል ሲሆን የሰረቀን እጁን  ያመነዘረን ብልቱን መቁረጥ የገደለን መግደል የሚል ምርህን አጥብቆ የሚከተል ነው፡፡ የዚህ ቅጣት ግብ ተቃዋሚዎች ቅጣት እንደዚህ ከሆነ ለሁሉም ወንጀሎች ተመሳሳይ አቻ ቅጣት ልናገኝላቸው አንችልም ለምሳሌ በሀገር ክደት የተወነጀለ ወነጀለኛ አቻ ቅጣት ምንድነው ሲሉ ይጠይቃሉ እንዲሁም እንዲህ  አይነቱ አካሄድ ዓለምን የአይነ ስውራንና የቆራጣዎች ያደርጋታል የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡ በዚህ በአሁኑ ዘመን በአንድ አንድ ሀገሮች ካልሆነ በስተቀር ይህ አይነቱ አስተሳሰብ እንምብዛም አይገኝም፡፡

2. ቅጣን እንደ ወንጀል መከላከያ (deterrence)

በሌላ በኩል ደግሞ የቅጣት ግብ ወደፊት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል እንጂ ወንጀለኛውን መበቀል ሊሆን አይገባውም የፈሰሰ ውሃ ስለማይታፈስ ወንጀለኛው ላደረገው ነገር የምንቀጣው  ላደረገው ነገር እንደ ቅጣት ሳይሆን ወደፊት ቅጣት ፈርቶ ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈፅሙ ለመከላከል ነው የሚሉ ወገኖች ያሉ ሲሆን እንደውም በአንድ ጉዳይ አንድ የአሜሪካ ዳኛ አንድ በግ የሰረቀን ወንጀለኛ ከቀጡ በኋላ አሁን አንተን የቀጣንህ በግ ስለሰረክ አይደለም ይልቁንስ በድጋሜ በግ እንዳይሰረቅ ነው በመሆኑም ራስህን ሌላው ከአንተ አይቶ በሀገሩ ላይ ወንጀል በድጋሚ እንዳይፈፅም እንደተሾመ ወታደር ልትቆጥር ትችላለህ ብለውት ነበር፡፡ በአጭሩ የዳኛው ንግግር መልዕክት የቅጣት ግብ መጨረሻ ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ነው የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወንጀለኛው ወንጀል እንዲፈፅም ያነሳሳው ምክንያት ከቅጣት ፍርሃቱ ሊበልት  ስለሚችል እንዲሁም ሰዎች ወንጀል በሚፈፅሙበት ቅፅበት ቅጣት ትዝ ስለማይላቸው ቅጣት ሁል ጊዜ ይህን ግቡን ላይመታ ይችላል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ይዚህ ግብ ተቃዋሚዎች  በአነድ ወቅት በጥንታዊቷ ታይበር ከተማ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ወነጀለኞች በህዝብ ፊት በአደባባይ የስቅላት ቅጣት በሚፈፀምባቸው ጊዜ ቅጣቱ ሲፈፀም ለመመልከት በተሰበሰበው ህዝብ መሀላ አየተሽሎከለኩ ከህዝቡ ኪስ ገንዝብ ይስርቁ የነበሩ ሌቦች የተያዙነበትን የታሪክ አጋጣሚ በማውሳት ይህን የቅጣት ግብ አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡ በተጨማሪም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ወንጀል የወንጀለኞችን ደጋጋሚነት በማውሳት ቅጣት የማስተማር ግቡን እንዳልተወጣ ያሳያል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

3. ቅጣት እንደ ወንጀለኛውን ማግለያና መለያ (Incapacitation)

በዚህኛው ግብ ደግሞ ቅጣት ወንጀለኛውን ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለዘላለሙ (በሞት ቅጣት) ወንጀል ከሚፈፀምበት ማህበረሰብ በማግለል ወይም በመለየት በማህበረሰቡ ላይ ድጋሜ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ይቻላል የሚሉ ወገኖች ያሉ ሲሆን ወንጀለኛው እስር ቤት በሚሆንበት ጊዜ ማህበረሰቡ ከወንጀል ይገላግላል እንደ ሞት ያሉ ቅጣቶች በሚጣልባቸው ወንጀሎች ደግሞ ወንጀለኛው በድጋሜ ወንጀል የመፈፀም እድል ስለሌለው ማህበረሰቡ ከወንጀለኛው ድጋሚ ጥፋት መታደግ ይቻላል የሚል ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ቅጣት ሁሉ በዚህ የቅጣት ግብ ላይም ትችቶች ያሉ ሲሆን ከሞት ቅጣት ውጭ ባሉ ቅጣቶች ላይ ወንጀለኛው እስር ቤትም ሆኖ  እንደ ስርቆት ፣ ግብረሰዶም፤ግድያና የአካል ጉዳትን የመሳሰሉ ወንጀሎችን መፈፀሙ አይቀርም ወይም ከእስር ሲፈታ ጠብቆ መልሶ ወንጀል ሊሰራ ይችላል እንደውም በእስር ቤት ቆይታው ወንጀል ተምሮ እንዴት በተቃጀና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈፅመው እንዴት የመያዝ እንድሉን እንደሚቀንስ ተምሮ ሊወጣ ስለሚችል ይህ የቅጣ ግብ ብዙ ርቀት አያስጉዝም  እንዲሁም የቅጣቱ ግብ እስረኛውን በማህበረሰቡ ላይ ይበልጥ በቀለኛ ስለሚያደርገው በወንጀል ተግባሩ የመግፋት ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡

4.ቅጣት ወንጀለኛውን እንደ ማረሚያ (Rehabilitation)

የዚህ ቅጣት ግብ መሠረት አጥፊውን ከመረዳት የሚጀምር ሲሆን ወንጀለኛው ወንጀል ውስጥ የገባው ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ወንጀል እንዲፈፅም ገፍተውት ስለሆነ እነዚህ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች በማከም ወንጀለኛውን ከድጋሜ ጥፋት ማረም ይቻላል የሚል ነው፡፡ ወንጀለኛች ተወልደውም ይሁን ተሰርተው (criminal are born not made, criminal are made not born) ወንጀለኛ እንዲሆኑ ያደረገ ሳይኮሎጂካል፣ ባዮሎጂካል፤ ኢኮኖሚካል ወይም አካባቢያዊ አሊያም ማህበራዊ ምክንያት ስለሚኖር ወንጀለኛው ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሳውን ምክንያት በመመርመር ምክንያቱ አክሞ በማዳን ወንጀለኛውን ጤነኛ አምራች ወንጀልን የሚጠየፍ ለማህበረሰቡ ርህራሄ የሚያሳይ አድርጎ መመለስ ስለሚቻል የቅጣት ግብ ይህ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ያለው ነው፡፡

 

5.ቅጣትን እንደ ባለ ብዙ ግብ

የቅጣት ግብ ከፍ ሲል የተገለፁት ዓይነት ሆኖ  ቅጣትን በአንድ ግብ ብቻ ስቅዞ ከመያዝ ለግቦች ቅድሚያ በመስጠት እንደ የወንጀሉ ዓይነት እንደ ወንጀለኛው እየታየ ግቦችን አፈራርቀን መጠቀም እንችላለን የሚል ክርክር ያለ ሲሆን በአሁን ሰዓት በአብዛኛው ቅጣት ግቡ ይህ ነው የሚል አንድ ምክንያት ከመስጠት ይልቅ ሁሉንም ግቦች በቅጣት አይነቶች እንደ ሁኔታው መጠቀም ይመከራል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም በመግቢያውም ሆነ በመውስጡ በቀረፃቸው የቅጣት አይነቶች የቅጣት ግብ አንድ ሳይሆን ብዙ ሆኖ ነገር ግን በዋናነት የቅጣት ግብ አጥፊውን ማረም ነው የሚል መነሻ ያለው ሲሆን እንደሁኔታው ከብቀላ ውጭ ያለውን የወንጀል ቅጣት ግብ እንደየሁኔታው ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡

              በትክክል ካላደረከው ሽህ ግዜ ስታደርገው ትኖራለህ

ወንጀል የዚች ዓለም እውነት ሲሆን ይህ ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነት በመጠን በአፈፃፀም ቴክኒክ እየረቀቀ እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ ሌላ የማንክደው እውነት ነው፡፡የሰው ልጅ ከጥንት እስከ አሁን ወንጀለኛ ያላቸውን በአሰቃቂ የስቅላት ሞት በዘግናኝ እስር ቤት አያያዝ፣ በከባድ ግርፊያና ማሰቃያ መንገዶች እስከ ሰብአዊ እስር ሲቀጣ ቢኖርም ንፁሀኖቹ የናዝሬቱ እየሱስ አቴናውያኑን ሶቅራጠስን እና ጋሊሊዮን እስከመግደል የደረሰ እውነት ወንጀለኛው ወንጀለኛ ስለመሆኑ ወንጀሉ ራሱ ወንጀል ስለመሆኑ በርግጠኝነት አረጋግጠኛ ሆኖ ካለማወቅ ድንቁርናው ጀምሮ ወንጀል እንዴት እንደሚቀንስ ብሎም እንደሚጠፋ ትክክለኛው መንገድ ቸግሮት ለዘመናት ኖሯል፡፡

ከቀጣን አይቀር ቅጣት በትክክል ወንጀለኛውን በትክክል በለየ ወንጀል በድጋሜ እንዳይፈፅም የሚያደርግ ሌላውን ማህበረሰብ ከዚህ የቅጣት አፈፃፀም ተምሮ ወንጀል ከመፈፀም የሚቆጠብ  ወንጀለኛው በማህበረሰቡ ላይ በድጋሜ በበቀል ስሜት ሳይሆን በፀፀትና በይቅርታ ስሜት ወደ ማህበረሰቡ የሚመልስ ቅጣት እና የቅጣት አፈፃፀም ማቀድ ተገቢ ነው፡፡  ዙሮዙሮ ቅጥት ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በሚሰበስብ ገንዘብ የሚፈፀም እንደመሆኑ ወጭ ቆጣቢ በተለይም የወንጀለኛውን ማህበራዊ ተቋማት በትንሹም በትልቁም የማያፈርስ ሊሆን ይገባዋል ይህን ሁኔታ የአሜሪካን የፍትህ አታሸ የነበሩት ዋረን በገን በአንድ ወቅት ወንጀለኛን ከቀጣነው በኋላ ምንም ሳንለውጠው ወደ ማህበረሰቡ መመለስ ማለት አንድን ውጊያ አሸንፈን ነገር ግን አጠቀላይ ጦርነቱን መሸነፍ ነው በማለት ሁኔታን  በሚገባ ገልፀውት ነበር፡፡

ቅጣት ሲፈፀም የተቀጭውን አስተሳሰብ የለወጠ ሌሎችን የሚስተማር ወንጀለኛው ለራሱም ሆን ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚጣዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ስራዎች እየሰራ እንዲቆይ የሚያደርግ የተቀጨውም ሆነ የተቀጭው ቤተሰብ ህይወት በሙሉ የማያፈርስ ማህበራዊ ኪሳራን(social cost) የሚቀንስ ሆኖ ቢፈፀም እጅግ ጥሩ ነው፡፡ 

ወንጀለኛውን ስናስረው ወንጀለኛው ለማሰር የምግብና የመኖሪያ ቤት ወጭ እንዲሁም አስተዳራዊ ወጭ አለብን ይህ ገንዘብ ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በቀጥታ የተሰበሰበ ነው በአንድ መፀሀፍ ላይ ያገኘሁት መረጃ አሜሪካ ለጠቅላ የፍትህ ዘርፍ ከምትመድበው በጀት 1/3ኛ የሚሆነውን በጀት የምትበጅተው ለእስረኛ አስተዳደር ነው፡፡

እስረኛውን ስናስር ማህበራዊ ኪሳራዎች አሉት እስረኛ ከቀደሞ ስራው ማህበራዊ ግንኙነቱ ይነጠላል ምናልባት እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች በአብዛኛው የእስረኛው ጥገኛ የሆኑ ቤተሰቦች ስለሚኖሩ በወንጀለኛው መታሰር ሳቢያ ቤተሰብ ይበተናል በተበተነው ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ልጆች በሚደርስባቸው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ምክንያት አዲስ ወንጀለኛ ሆነው ብቅ የማለት እድላቸው ሰፊ ነው በመሆኑም አንድ ወንጀል ፈፀመ ያልነውን ወንጀለኛ ለመቅጣት ተጨማሪ ወንጀሎች ልንጋብዝ እንችላለን፡፡ ወንጀለኛውን ስናስረው ባስተሳሰብ ላይ ካልሰራን አንድ ወንጀለኛ ስንለው እርግጠኛ ወንጀለኛ መሆኑን ሳናረጋግጥ ከቀጣነው ሁለት ወንጀለኛም ሆኖ ስንቀጣው የወንጀል አስከፊነት ተረድቶ ተለውጦ ማህበረሰቡን ይቅርታ በሚያስጠይቅ ደረጃ ካልቀጣነው አንዲሁ አጉረን መልቅቀ ከሆነ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ጥላቻ ለተጨማሪ ወንጀል የሚገፋው ከመሆኑ በተጨማሪ በድጋሚ እሱን ተቀብሎ የመቀለብ ግዴታ ውስጥ ነው ይመከተን ያወጣነውን ወጭ በብላሽ የሚያሰቀር  የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ባጭሩ ቅጣትን በትክክል ካልፈጸምነው በራሳችን ላይ በርካታ ችግሮች እንጋብዛለን እንደ ማለት ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የተሻለው የቅጣት አፈፃፀም ምንድነው እንዴት ይፈፀማል የሚለው ዝርዝር አይደለም በዚህ ጉዳይ ላይ ጸሐፊው በሌላ ጊዜ በድጋሚ የሚመለስበት ሆኖ አሁን ከፍ ሲል በተቀመጠው መንደርደሪያ ሀሳብ መነሻነት በአሁኑ ሰዓት ቅጣት የሚደነግጉ ከወንጀል ሕጉ ውጭ ያሉ አዋጆችን በአጭሩ መመልከት ነው፡፡

ከባድ ቅጣትን አማራጭ ያደረጉ አዋጆች

ውድ አንባቢዎቼ ይህን የጽሑፉን ክፍል ስታነቡ ዶ/ር ሙሉጌታ መንግሥት ወንጀልና ኢኮኖሚክስ በሚል ርዕስ በዚሁ ድረገጽ የፃፈውን ጽሑፍ ብትመለከቱ ሀሳቡን በተሸለ ጥለቀት ለመረዳት ስልሚያግዝ ይህኑ እንድታደርጉ እመክራለሁ፡፡

ከፍ ሲል እንደተብራራው በየወንጀሎቹ ሥር ከፍ ያለ ቅጣት ስለተቆለለ ብቻ ወንጀልን መከላከል አይቻልም ይልቁንስ የተጠና ከወንጀሎቹ ባህሪና ዓይነት አኳያ ወንጀሎቹን የሚመጥን ቅጣት መደንገግ ተገቢ ነው፡፡ ቅጣት የሚቆልሉ ሕጎች በየጊዜው ከመፈብረክ ይልቅ የወንጀለኛው በትክክል ለይቶ የማወቅ አውቆም ተይዞ ቅጣቱን የሚፈጽምበትን የመያዝ ምጣኔ ማሳደግ ተይዞም ከወንጀሉ ተምሮ አምራች ዜጋ በሚሆንበት መንገድ ቅጣቱን እንዲፈፅም የቅጣ አፈፃፀሙ መምራት እንጂ  ረዥም አመታትን እንዲሁ በስር ቤት እያጎሩ ማስወጣት በመንግስትና በህዝብ ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ ከፍተኛ ነው፡፡

ለዚህ አባባሌ ዋቢ የሚሆኑኝ አዋጆች በመጥቀስ እንደሚከተለው ካነሳሁት ሀሳብ ጋር በመተዛመደ መልኩ ለማሣየት እሞክራለሁ፡፡ በወንጀል ሕጉ ቅጣት እንደየወንጀሉ ዓይነትና አፈፃፀም እንደፈፃሚው ማንነት እየታየ ዳኛው ጉዳዩን  አይቶ ነገሮች መርምሮ ተገቢውን ቅጣት መወሰን እንዲቻለው ለወንጀሎች የሚቀመጠው ቅጣት ከትንሽ እስከ ትልቅ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ አዋጆች ግን የዳኝነትን ፍቅድ ስልጣን በሚጋፋ ሁኔታ ለዛውም በወንጀል ሕጉ ከባድ ተብሎ ከተደነገጉት ወነጀሎች ላነሱ የወንጀል አይነቶች በአመዛዛኝ ሰው አእምሮ ልኬትም ከባድ ለማይባሉ ወንጀሎች ከፍተኛ ቅጣት ለዚያውም የቅጣት መነሻቸው 2 አመት ፣ 5 አመት፤ 7አመት ፤10 አመት በላይ የሆኑ ጣሪያቸው እስከ 25 አመት እና 15 አመት የሚደርሱ ትናንሽ ወንጀሎችን መደንገግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 መሠረት በመንግስትና በህዝብ ላይ የተፈፀመ ከባድ አታላይነት የሚያስቀጣው ከ1-10 ዓመት ሲሆን በንብረት ግዠ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75 መሠረት ደግሞ ተራና ትንሽ የሚባል ከመንግስት ንብረት ግዢ ጋር የተያያዘ የማጭበርበር ተግባር ውስጥ የተገኘ (መቶ ብር በሚሆን ግዥም ቢሆን) የሚቀጣው ከ10-15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ነው በዚህ ሁለት በወንጀል ሕጉ ደግሞ አታላይነት እንደነገሩ ከባድነት ከ5 ዓመት በማይበልጥ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን በጣም ከባድ ነው ከተባለ ከ1-15 አመት በሚደርስ እስር ያስቀጣል፡፡ በመሆኑም በሙስና ወንጀሎች እና በወንጀል ሕጉ መሠረት በሚሊዮን የሚቆጠር ሀበት የመዘበረ ወንጀለኛ ምናልባትም ከ10 አመት የማይበልጥ ቅጣት በማይቀጣበት ሁኔታ ከመንግስ ግዥ ጋር በተያያዘ መቶ ብር ያጭበረበረ ተራ ወንጀለኛ ግን ከ10 ዓመት በላይ ይቀጣል፡፡ ምክንያቱም ሕጉ የመነሻ ቅጣቱ ከ10-15 ዓመት በማለት በግብታዊነት ደንግጎ ስለሚገኝ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ሲወጣ ይህ ቅጣት የተቀመጠው ከሌሎች ወንጀሎች አኳያ ከባድነቱ ተመዝኖ በተለይም በሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ የተቀመጡ ሕጎች ተፈትሾ እንዳልሆነ የቅጣት አቀራረጹን በማየት መረዳት የሚቻል ሲሆን ይህ ሕግ የወጣው የመንግስት ግዥ እና አስተዳደር አዋጅን ማለቴ ነው የወጣው በ2001 ዓ.ም እንደመሆኑ በ1997 አመተምህረት በወጣው የወንጀል ሕግና በ2007 በወጣው የሙስና ወነጀሎች አዋጆች መከከል  መናበብ እንደሌለ ይልቁን ሁሉም በየፊናቸው የመሠላቸው ቅጣት እንደደነገጉ የሚያሳይ ነው፡፡

ቅጣት በግብታዊነት ለዛውም ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ምናልባትም ከግድያ(ተራ ግደያ የሚያስቀጣው 5 አመት እስከ 25 አመት መሆኑን ልብ ይሏል) ምናልባት  ከሀገር ክደት(የሚያስቀጣው ከ15አመት በማይበልጥ እስራት መሆኑን ልብ ይሏል አንቀፅ 249/1) ወንጀሎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ወይም መካከለኛ የሚባሉ ወንጀሎች ከ10 ዓመት ጀምሮ የቅጣት ጣሪያ እስከሆነው የ25 አመት ፅኑ እስራት(በነገራችን ላይ አንድ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሰው አሞክሮ የሚሰከለከል ድርጊት ካልፈፀመ በስተቀር ከፍተኛው ቅጣቱ ከ25 አመት በታች ነው ) ድረስ ደንግገው መገኘታቸው ሕጎች በተቀናጀ በታወቀ እና መአከላዊ በሆነ መንገድ ለሕግ አውጭው እንደማይቀርቡ ይልቁን በስራዬ ላይ ችግር አለ የሚለው ሴክተር መ/ቤት ሁሉ የራሱን ሕግ እያንጠለጠለ ወደ ፓርላማ እንደሚሮጥ የሚያሳዩ ናቸው ለዚህ አባባሌ በቂ አስረጂ እንዲሆነኝ ይህ ሁኔታ የሚታይባቸውን ጥቂት ሕጎች መጥቀስ እጅግ ተገቢ ነው፡፡

1. ከመንግስት ግዢ ጋር በተያያዘ ማናቸውም ገንዘብ (100 ብርም ቢሆን) ለመቀበል ቃል የተገባለት ሰው ገንዘቡን ባይቀበልም ከ10-20 ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣል የንብረት አስተዳደር አዋጅ 649/2001፡፡

2. ከመንግስት ግዥ ጋር በተያያዙ ማንኛውም ግዥ ከ100 እስከ ሚሊዮን ብር ሌላ ሰው እንዲያጭበረብር ለማድረግ ሕግ የጣሰ ከ10-15 ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ አዋጅ ቁጥር 649/2001

3. በሀሰተኛ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰነድ የተጠቀመ ሰነዱን የተተቀመው በተራ ጉዳይም ሆነ ለከባድ የማታለል ጉዳይ ከ5-10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ የወሳኝ ኩነት አዋጅ ቁጥር 760/2004፡፡ ነገር ግን በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 379 መሠረት መንግስታዊ ሰነዶች መሰራት ከወሳኝ ኩነት የበለጠ ሀገራዊ ፋይዳና ጥቅም ያላቸውን ሰነዶች ሳይቀር የሰራ ሰው የሚቀጣው ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ሲሆን የፅኑ እስራት መነሻው 1 ዓመት በመሆኑ 15 አመት ደግሞ ጠሪያው እንጂ የሚቀጣው ባለመሆኑ  ይህ ሰው 1 አመት ሁለት አመት እንደነገሩ ሁኔታ ይቀጣል ባለው በወሳኝ ኩነት አዋጅ ግን ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ዓላማ ብቻ እድሜውን ከ15አመት ወደ 20 ዓመት አድርጎ ሀሰተኛ የልደት ሰርተፍኬት አስርቶ ቢጠቀም  ወንጀለኛው በትንሹ 5 ዓመት ይቀጣል ማለት ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የመንግስት ሰነድ ለከባድ ዓላማ ሲል ካጭበረበረ ወንጀለኛ የበለጠና የከበደ ቅጣት እንደሚጠብቀው ያሳያል ማለት ነው፡፡ እንደውም የወንጀል ሕጉ በአንቀፅ 385/2 ላይ ሀሰተኛ የልደት ሰርተፍኬት መጠቀም የሚያስቀጣው ከሶስት ወር በማንስ ቀላል እስራት ነው በብሎ መደንጉ በህጎቹ መካከል መናበብ የሌለ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

4.     የከተማን ቦታ 1 ካሬ ሜትርም ቢሆን ከህጋዊ ይዞታ ጋር አጥሮ መያዝ ከ7-15 ዓመት በሚደረስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል ከከተማቦታ ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ መረጃ የሰጠ ሰው ደግሞ ከ5-12 ዓመት የሚቀጣ ሲሆን በሀሰት የከተማ ቦታን የፈቀደ ደግሞ ከ7-15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡

እነዚህ አዋጆች ጸሐፊው ለጽሑፉ ቶሎ ለንባብ መድረስ በጊዜው በእጁ ያገኛቸው አዋጆች እንጀ በስራ አጋጣሚው የተመለከታቸው በርካታ አዋጆች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው በብዛት መነሻ ቅጣትን ከፍ አድርገው ያስቀመጡ የቅጣት ጣሪያዎችን ለመደንገግ የማያመነቱ በትንሽ እና በትልቁ ወንጀል መካከል ልዩነት ያላስቀመጡ ከሌሎች አዋጆች እና ከወንጀል ሕጉ ጋር መናበብ የሌላቸው ሆነው አግኝቷቸዋል፡፡

በተለይም በሁሉም አዳዲስ  አዋጆች ላይ በሚባል መልኩ አንድ እጅግ የተለመደ አባባል ያለ ሲሆን ይሄውም ‹‹የዚህን አዋጅ በማንኛው መልኩ የጣሰ ›› በሚል አነጋገር ስር ከ 5-10 ዓመት ይቀጣል ተብሎ ይደነግጋል ለምሳሌ በንግድ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 686 አንቀፅ 1 ነጋዴ የቅር…

የዚህ ጽሑፍ ድምዳሜ አንዳንድ ወንጀሎች ተራ ናቸው በቀላሉ መታለፍ አለባቸው የሚል አይደለም ይሁን እንጂ አዋጆቹ የሚደነግጉት ቅጣት መሠረት ግልፅነት የጎደለው ግብታዊነት የሚታይበት ከሌሎች ሕጎች ጋር ያልተገናዘበ ዳኞች እንደ ወንጀሉ አፈፃፀምና ወንጀለኛው ባህሪ አኳያ ፍቅድ ስልጣናቸው ተጠቅመው ተገቢው ቅጣት እንዳይጥሉ አስቀድሞ መነሻ የቅጣት ጣሪያን ከፍ አድርጎ በማስቀመጥ የዳኞችን ነፃነት የገደበ የቅጣት ዓላማ ግቡን እንዳይመታ እንቅፋት የመሆን እድል አለው፡፡ ከሌሎች የወንጀል ሕጉና ሌሎች ቅጣት የሚደነግጉ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ለሚባል ወንጀል ከፍተኛ ቅጣት ከፍተኛ ለሚባል ወንጀል ዝቅተኛ ቅጣት እንዲጣል በር የከፈቱ ናቸው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ  ትንሽ ወንጀል የፈፀመው አነስተኛ ወንጀል ሲጣልበት ከባድ ወንጀል የፈፀመው ትንሽን ቅጣት ሲጣለበት ወንጀለኛ ሂሳብ መሰራት ወስጥ ይገባሉ ከታሰርኩ አይቀር ከባድ ወንጀል ሰርቼ ልታሰር በሚል ሃሳብ ውስጥ ለሌላ ላልፈለጉት ወንጀል መገፋፋት ያመጣል፡፡

ፅኑ እስራት እንደ ፅኑ ህመም

ሌላው አዋጆቹ በአብዛኛው የዕስራት ቅጣትቶች  ሲጥሉ  የጽኑ እስራት እስራት የሚመርጡ ሲሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ  108 ላይ የፅኑ እስራት ቅጣት የሚጣለው ከባድ ወንጀል ባደረጉ በተለይም ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆኑት ወንጀለኞች ላይ ብቻ እንደሆነ እነዚህ ሰዎችም የሚታሰሩት ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ የፅኑ እስራት ፍርደኞች እስር ቤት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አዋጆቻችን አካሄድ ትንሹም ትልቁንም ወንጀል በፅኑ እስራት ያስቀጣል የምንል ከሆነ ሁሉም ወንጀለኛ አደገኛ ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ሲሆን የፅኑ እሰራት እስረኛ በአንድ ዓይነት ቦታ አንድ ላይ እንዲታሰሩ ሕጉ የሚያዝ እንደመሆኑ 100 ብር ያጭበረበረውም ነፍስ የገደለውም በአንድ እስር ቤት እንዲታሰሩ መፍቀድ ስለሚያስከትል ትንሹ ወንጀለኛ ከትልቁ ወንጀል የወንጀል ቴክኒክ ተምሮ  ይበልጥ አደገኛ ሆኖ ወደ ማህበረሰቡ እንዲመለስ መፍቀድ ሌላ ወንጀል እንዲፈፅምብን እድል መስጠት በመሆኑ ቅጣት በተጠና ከሌሎች የቅጣት አዋጆች ጋር በተናበበ መልኩ ሊወጣ ስለሚገባው ሕግ አውጭው ይህን ጉዳይ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ በፅሁፉ መግቢያ የሚጣለው ቅጣት ለሚፈፀምበት መንገድ፤ የምንቀጣው ሰው እውነተኛ ወነጀለኛ መሆኑን በተቻለ መጠን ማረጋገጥ፤የወንጀለኞችን የመያዝ እድል መጨመር በሚል ለጸገለፁት ጉዳዮች ትኩረት ከመስጠት ጋር በሚገባ ሊኬድበት የሚገባ አንግብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

መደምደሚያ

ቅጣትን እንደ መንገድ ጭቃ እየተነሳ የሚለጠፍ ተራ ነገር ባለመሆኑ የቅጣት ዓላማ ማህበረሰቡን ከወንጀል መጠበቅ እስከሆነ ድረስ በተበተነ መልኩ በየሴክተር መ/ቤቱ ሕግ እየረቀቀ ወደ ፓርላማ የሚሄድበት ስርዓት አብቅቶ በተማከለ መልኩ የሕግ መወጣት መነሻ ከግለሰብም ይሁን ከድርጅት ከየትም ቦታ ይሁን የሕጎችን ተናባቢነት እና ተገቢነት በመመዘን አንድ ተቋም ውስጥ በሚገባ ተብላልተው ለፓርላማ መቅረብ ይገባዋል እንጂ ከየአቅጣጫው ወደ ፓርላማ የሚላኩ የሕግ ረቂቆች ውጤት የማይገባቡ እርስ በርስ የሚቀረኑ አዋጆችን መፈብረክ ነው፡፡ እስከዛሬ በተበታተነ መልኩ የወጡ አዋጆችም ቢሆኑ በድጋሜ ተከልሰው እርስ በርስ የሚናበቡበት እና ይሚጣጣሙበት ስርአት በመጀት አለበት፡፡ ቅጣት እንዲሁ ከመቆለል ይልቅ በተደራጀ መልኩ ለየትኛው ወንጀልና ወንጀለኛ ምን ዓይነት ቅጣት ምን ዓይነት ግብ በሚል መነሻ ተገቢው ቅጣት ለተገቢው ወንጀለኛ ሊሰጥ ይገባዋል ከዚህም ይበልጥ ቅጣት ከመቆለል ይልቅ የወንጀለኛ የመያዝ ምጣኔ ላይ ብኋላ ቅጣታቸው ፈፅመው ሲወጡም አምራች ለማህበረሰቡ ሀዘኔታ የሚሰማቸው አድርጎ ማውጣት ላይ ልናተኩር ይገባል፡፡

{advpoll id='7' view_result='0' width='0' position='center'}

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The Application of other public international laws...
መጥላት ላለብን የጥላቻ ንግግር የተጨማሪ ሕግ አስፈላጊነት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 10 November 2024