በሽብር ወንጀል ተከሰው በክርክር ሒደት ላይ ከሚገኙት ጦማሪያን መካከል አንዱ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋቤላ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ በመባል በአራት ወራት እስራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ አቤል ዋቤላ በተከሰሰበት ወንጀል ክርክር ሂደት መልካም ጸባይ እንዳሳየ በመግለጽ የአራት ወራት እስራቱን በሁለት ዓመታት ገድቦለታል፡፡
ጦማሪ አቤል ይህ ውሳኔ የተወሰነበት ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አዲስ ሲዲ ባቀረበበት ወቅት የቀረበው ሲዲ “የሚመለከተው ሶሊያና ሽመልስን ብቻ ነው? ወይስ እኛንም ያካትታል?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ እንዳይናገር ሲከለክለው በመናገሩና ፍርድ ቤቱን ‹‹ራሳችሁ ሥነ ሥርዓት›› በማለት ኃይለ ቃል ተናግሯል በሚል ነው፡፡