የንግድ ባንክ ስድስት ሠራተኞች በከባድ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

EthiopianReporter Jul 07 2014

ሁሉም የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ናቸው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ስድስት ሠራተኞች በሐሰተኛ መታወቂያ አካውንት በመክፈት፣ ከአንድ ግለሰብ ሒሳብ ላይ በድምሩ ከ482,000 ብር በላይ ወስደዋል በሚል ተጠርጥረው በከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ተከሰሱ፡፡

የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ አቶ ኃይለ ሚካኤል ኃይሉ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን፣ አቶ  ሱሌማን ሳኒ የውስጥ ተቆጣጣሪ፣ አቶ ተመስገን ለሚ የቅርንጫፉ ባልደረባ፣ አቶ ግርማ ወርቄ የገንዘብ ቤት ዋና ኃላፊ፣ አቶ በላይ ታዬ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም አቶ ሞላ አምሳሉ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሥውር በሆነ የጥቅም ግንኙነት ተመሳጥረው የማይገባ ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘትና ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ ከአንድ ግለሰብ ሒሳብ ላይ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

አቶ ኃይለ ሚካኤል የተባሉት ተጠርጣሪ ራሳቸው ብቻ የሚያውቁት፣ በባንኩ መመርያና ግዴታ መሠረት ሌላ ሰው ሊያውቀው የማይገባውን ወደ የኮምፒዩተር መግቢያ ፈቃድ በመጠቀም፣ አቶ ገመቹ አዳም ከተባሉ ግለሰብ ሒሳብ ላይ በተደጋጋሚ በሐሰተኛ መታወቂያ በተከፈተው አካውንት ውስጥ በድምሩ 482,495.45 ገቢ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ሰኔ 30  ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ እንዲነበብላቸው ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

Read 32864 times